የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረርን ማንኛውንም የተሳሳተ ሐሳብ አፍርሱ!
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019 | ሰኔ
    • “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ”

      7. ውስጣዊ ማንነታችንን መቀየር የምንችለው እንዴት ነው?

      7 ዝንባሌያችንን ወይም ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ የሚቻል ነገር ነው? የአምላክ ቃል ይህን ማድረግ እንደሚቻል ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ፤ እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌ. 4:23, 24) ስለዚህ ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ እንችላለን፤ ይህን ማድረግ ቀላል ነው ማለት ግን አይደለም። መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠርና መጥፎ ነገር ከመፈጸም መቆጠብ ብቻውን በቂ አይደለም። ‘አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል’ መለወጥ ያስፈልገናል። ይህም ምኞታችንን፣ ዝንባሌያችንንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋንን ስሜት መቀየርን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው።

      8-9. የአንድ ወንድም ተሞክሮ ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      8 እስቲ የአንድ ወንድምን ምሳሌ እንመልከት፤ ይህ ወንድም ቀደም ሲል ጠበኛ ነበር። ከመጠን በላይ የመጠጣትና የመደባደብ ልማድ ነበረው፤ ይህን ልማዱን ካስተካከለ በኋላ ተጠመቀ፤ ይህም በሚኖርበት ትንሽ ማኅበረሰብ ውስጥ ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል። ሆኖም ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ አንድ ምሽት ላይ ያልጠበቀው ፈተና ገጠመው። አንድ የሰከረ ሰው፣ ወደዚህ ወንድም ቤት መጣና ለጠብ መጋበዝ ጀመረ። መጀመሪያ ላይ ወንድማችን ስሜቱን መቆጣጠር ችሎ ነበር። ሰውየው የይሖዋን ስም መስደብ ሲጀምር ግን በቅርቡ የተጠመቀው ይህ ወንድም ቁጣውን መቆጣጠር አልቻለም። ከቤቱ ወጥቶ ሰውየውን ደበደበው። የዚህ ወንድም ችግር ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ የጠበኝነት ዝንባሌውን ለጊዜው ለመቆጣጠር ቢያስችለውም አእምሮውን የሚያሠራው ኃይል ገና አልተለወጠም ነበር። በሌላ አባባል ውስጣዊ ማንነቱ አልተቀየረም ነበር።

      9 ሆኖም ይህ ወንድም ተስፋ አልቆረጠም። (ምሳሌ 24:16) ሽማግሌዎች በሚሰጡት እርዳታ እየታገዘ ጥሩ እድገት ማድረጉን ቀጠለ። ውሎ አድሮም የጉባኤ ሽማግሌ መሆን ቻለ። አንድ ምሽት ላይ፣ ከዓመታት በፊት የገጠመው ዓይነት ፈተና አጋጠመው። የስብሰባ አዳራሹ ደጅ ላይ አንድ ሰካራም ከጉባኤ ሽማግሌዎች አንዱን ለመማታት ሲጋበዝ አገኘው። ታዲያ ወንድማችን ምን አደረገ? ሰክሮ የሚንገዳገደውን ሰው በትሕትናና በሰከነ መንፈስ በማነጋገር ሁኔታው እንዲረጋጋ ካደረገ በኋላ ወደ ቤቱ ሸኘው። ወንድማችን እንዲህ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? አእምሮውን የሚያሠራውን ኃይል መለወጥ መቻሉ ነው። ውስጣዊ ማንነቱ ተለውጦ ሰላማዊና ትሑት ሰው መሆን ችሏል፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ውዳሴ አምጥቷል!

      10. ውስጣዊ ማንነታችንን ለመለወጥ ምን ያስፈልጋል?

      10 እንደዚህ ያሉ ለውጦች የሚመጡት በአንድ ጀምበር ወይም ያለምንም ጥረት አይደለም። ለዓመታት “ልባዊ ጥረት” ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። (2 ጴጥ. 1:5) በእውነት ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ መቆየታችን ብቻውን ለውጥ ለማድረግ አያስችለንም። ውስጣዊ ማንነታችንን ለመቀየር የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ያለ ለውጥ ለማድረግ የሚረዱን መሠረታዊ ነገሮች አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመርምር።

      አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል መለወጥ የምንችለው እንዴት ነው?

      አንዲት እህት በመጸለይ፣ ራሷን በመስተዋት እያየች በማሰላሰልና ከጥሩ ጓደኞች ጋር አብራ ጊዜ በማሳለፍ አስተሳሰቧን ለማስተካከል ስትጥር

      11. ጸሎት አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል ለመለወጥ የሚረዳን እንዴት ነው?

      11 ጸሎት የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው። እኛም እንደ መዝሙራዊው “አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” ብለን መጸለይ ያስፈልገናል። (መዝ. 51:10) አእምሯችንን የሚያሠራው ኃይል መለወጥ እንዳለበት አምነን መቀበልና ይሖዋ በዚህ ረገድ እንዲረዳን መለመን ይኖርብናል። ይሖዋ ለውጥ ለማድረግ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው? ይሖዋ በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩትን ልበ ደንዳና እስራኤላውያን በተመለከተ የገባው ቃል፣ እኛንም እንደሚረዳን ለመተማመን ያስችለናል፤ ይሖዋ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ያልተከፋፈለ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ አኖራለሁ፤ . . . የሥጋ ልብ [ለአምላክ አመራር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥን ልብ ያመለክታል] እሰጣቸዋለሁ።” (ሕዝ. 11:19 ግርጌ) ይሖዋ እነዚያን እስራኤላውያን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር፤ እኛንም ሊረዳን ፈቃደኛ ነው።

      12-13. (ሀ) መዝሙር 119:59 እንደሚጠቁመው በምን ላይ ማሰላሰል አለብን? (ለ) ራስህን ምን እያልክ መጠየቅ ይኖርብሃል?

      12 ማሰላሰል ሁለተኛው አስፈላጊ እርምጃ ነው። በየቀኑ የአምላክን ቃል ስናነብ፣ ለውጥ ልናደርግባቸው የሚገቡ አስተሳሰቦችና ስሜቶች የትኞቹ እንደሆኑ ጊዜ ወስደን ማሰላሰል ወይም በጥሞና ማሰብ አለብን። (መዝሙር 119:59⁠ን አንብብ፤ ዕብ. 4:12፤ ያዕ. 1:25) ዓለማዊ ፍልስፍናዎች በአስተሳሰባችንና በስሜታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድረው እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ያሉብንን ድክመቶች በሐቀኝነት አምነን መቀበልና ማስተካከያ ለማድረግ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል።

      13 እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በትንሹም ቢሆን በሌሎች የመቅናት ወይም የምቀኝነት ዝንባሌ አለኝ?’ (1 ጴጥ. 2:1) ‘በአስተዳደጌ፣ በትምህርት ደረጃዬ ወይም በሀብቴ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እኩራራለሁ?’ (ምሳሌ 16:5) ‘እኔ ያሉኝ ነገሮች የሌሏቸውን ወይም ከእኔ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጌ እመለከታለሁ?’ (ያዕ. 2:2-4) ‘የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸው ነገሮች ይማርኩኛል?’ (1 ዮሐ. 2:15-17) ‘የሥነ ምግባር ብልግና እና ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች ያስደስቱኛል?’ (መዝ. 97:10፤ 101:3፤ አሞጽ 5:15) ራስህን ለመመርመር ለሚያስችሉት ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ፣ ለውጥ ማድረግ ያለብህ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ይጠቁምሃል። እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑና ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ከልባችን ስናስወግድ በሰማይ ያለውን አባታችንን እናስደስታለን።—መዝ. 19:14

      14. ጥሩ ጓደኞች መምረጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      14 ጥሩ ጓደኞች መምረጥ ሦስተኛው አስፈላጊ እርምጃ ነው። ለእኛ ባይታወቀንም እንኳ ጓደኞቻችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። (ምሳሌ 13:20) በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን የሚረዱን አይደሉም። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ግን ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞች እናገኛለን። “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” የምንነቃቃው ወይም የምንነሳሳው በስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ነው።—ዕብ. 10:24, 25 ግርጌ

  • ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረርን ማንኛውንም የተሳሳተ ሐሳብ አፍርሱ!
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019 | ሰኔ
አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ