የጋብቻ መሐላችሁን አክብሩ!
የሠርግ ቀን አስደሳች ቀን ነው። በተጨማሪም አንድ ትልቅ ቁም ነገር የሚከናወንበት ወቅት ነው። ሙሽራውና ሙሽሪት ቀሪ ሕይወታቸውን የሚለውጥ አንድ ከባድ ቃል ኪዳን ይገባሉ። በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በእንግድነት የተገኙ ሰዎች ለዚህ ከባድ ቃል ኪዳን ምሥክሮች ቢሆኑም ዋንኛው ምሥክር ይሖዋ አምላክ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰኑ ደንቦችን እንድንከተል ወይም አንድ ልዩ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት እንድንፈጽም አያዝም። ሆኖም ጋብቻን ያቋቋመው አምላክ እንደሆነ በመገንዘብ በአንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የጋብቻ መሐላዎችን በመፈጸም መጋባት የተለመደ ነገር ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በርከት ላሉ ዓመታት የሚከተለውን የጋብቻ መሐላ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፦ “እኔ —— ሁለታችንም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚች ምድር ላይ በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለክርስቲያን (ባሎች/ሚስቶች) በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ መሠረት አንቺን (አንተን) ——ን ለማፍቀርና ለመንከባከብ (ሙሽራዋ፦ እንዲሁም በጥልቅ ለማክበር) (ሚስቴ/ባሌ) አድርጌ (ወስጄሻለሁ/ወስጄሃለሁ።)”a
አንድ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር
ለማግባት እያሰብክ ከሆነ ከጋብቻው ቀን በፊት የዚህን መሐላ ጥልቀትና ትርጉም ማሰብህ እጅግ ጠቃሚ ነው። ሰሎሞን “በአፍህ አትፍጠን፣ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል” ብሏል። (መክብብ 5:2) ቀደም ሲል አግብተህ ከሆነስ? እንዲህ ከሆነ በይሖዋ ፊት የገባኸው ከባድ ቃል ኪዳን ምን ያህል ከፍ ተደርጎ እንደሚታይ ብታሰላስል ልትጠቀም ትችላለህ። መሐላውን እያከበርክ ነውን? ክርስቲያኖች የሚገቧቸውን ቃል ኪዳኖች በቁም ነገር ይመለከቷቸዋል። ሰሎሞን በመቀጠል እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል። ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፣ በመልአክም ፊት፦ ስሕተት ነበረ አትበል።”—መክብብ 5:4-6
ይህን የጋብቻ መሐላ አንድ በአንድ መመልከትህ የገባኸውን ከባድ ቃል ኪዳን በይበልጥ እንድታስተውል እንደሚረዳህ አያጠራጥርም።
“ወስጄሻለሁ/ወስጄሃለሁ”፦ በመሐላው ውስጥ እነዚህ ቃላት ይገኛሉ። እነዚህ ቃላት ለማግባት ላደረግኸው ውሳኔ ኃላፊነቱን በግልህ የምትወስድ መሆኑን ያጎላሉ።
በክርስቲያናዊ ዝግጅት ውስጥ አግባ የሚል ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ የለም። ኢየሱስ ራሱ ያላገባ ከመሆኑም በተጨማሪ “ሊቀበለው የሚችል” ካለ በነጠላነት እንዲኖር ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 19:10-12) በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ የኢየሱስ ሐዋርያት ትዳር ነበራቸው። (ሉቃስ 4:38፤ 1 ቆሮንቶስ 9:5) አንድ ሰው ለማግባት የሚወስነው በግሉ እንደሆነ ግልጽ ነው። ማንኛውም ሰው ቢሆን ሌላ ሰው እንዲያገባ የማስገደድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥልጣን የለውም።
ስለዚህ ለማግባት ስትወስን ኃላፊነቱን የምትወስደው ራስህ ነህ። የምታገባውን ሰው የመረጥከው አንተ ራስህ እንደምትሆን የታወቀ ነው። ‘——ን ወስጃለሁ’ በማለት የጋብቻ መሐላ ስትፈጽም ግለሰቧን ከጥሩ ጎኖቿ ወይም ግለሰቡን ከጥሩ ጎኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመጥፎ ጎኖቹ ወይም ከመጥፎ ጎኖቿ ጋር መውሰድህ ወይም መቀበልህ ነው።
ውሎ አድሮ በትዳር ጓደኛህ ላይ ቀደም ሲል ግልጽ ያልነበሩልህን ባሕርያት ልታገኝ ትችላለህ። አልፎ አልፎ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት ይናገራል። (ሮሜ 3:23) ስለዚህ ከትዳር ጓደኛህ ባሕርይ ጋር ለመስማማት አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ይህ ከባድ ሊሆንና አንዳንድ ጊዜም ተስፋ እንድትቆርጥ ሊያደርግህ ይችላል። ሆኖም የጋብቻ መሐላ ያደረግኸው በይሖዋ ፊት እንደሆነ አስታውስ። እርሱ ጋብቻህ እንዲሳካልህ ሊረዳህ ይችላል።
“(ሚስቴ/ባሌ) አድርጌ”፦ አዳምና ሔዋን በተጋቡበት በመጀመሪያው ሠርግ ላይ ይሖዋ አምላክ “አንድ ሥጋ ይሆናሉ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24፤ ማቴዎስ 19:4-6) ስለዚህ የጋብቻ ጥምረት በሁለት ሰዎች መካከል ሊኖሩ ከሚችሉት ዝምድናዎች በሙሉ በይበልጥ የሚያቀራርብ ነው። ጋብቻ አዲስ ዝምድና እንድትፈጥሩ ያደርጋችኋል። አንድን ግለሰብ እንደ “ባልሽ” አድርገሽ ትቀበያለሽ ወይም አንዲትን ግለሰብ እንደ “ሚስትህ” አድርገህ ትቀበላለህ። ይህ ሁኔታ ከማንኛውም ዝምድና የተለየ ነው። በሌሎች ዝምድናዎች ውስጥ እምብዛም የማይጎዱ ነገሮች በጋብቻ ውስጥ ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ለምሳሌ ያህል በኤፌሶን 4:26 ላይ የሚገኘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንውሰድ። እዚህ ጥቅስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” ይላል። ምናልባት ከዘመዶችህ ወይም ከወዳጆችህ ጋር የሚፈጠሩ ችግሮችን ቶሎ መፍታት ሲኖርብህ ብዙውን ጊዜ ሳታስወግዳቸው ቀርተህ ይሆናል። ሆኖም የትዳር ጓደኛህ ከማንኛውም ዘመድ ወይም ወዳጅ ይበልጥ ትቀርብሃለች። ከትዳር ጓደኛህ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ቶሎ ሳትፈታ መቅረትህ በመካከላችሁ ያለውን ልዩ ዝምድና አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።
በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንዲያድግና ለረጅም ጊዜ ቆይቶ የሐዘንና የብስጭት መንስኤ እንዲሆን ትፈቅዳለህን? አለመግባባቶችና የሚያበሳጩ ሁኔታዎች ለብዙ ቀናት ይቆያሉን? መሐላህን ለማክበር እንድትችል ችግሮች ሲከሰቱ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ሰላም ሳትፈጥር አንዲት ቀን እንድታልፍ አትፍቀድ። ይህም ይቅርታ ማድረግንና የተበደሉትን በደል መርሳት አልፎ ተርፎም የራስን ድክመቶችና ስሕተቶች ማመን ማለት ነው።—መዝሙር 51:5፤ ሉቃስ 17:3, 4
“ለማፍቀር”፦ ባል ሙሽራይቱን “ለማፍቀርና ለመንከባከብ” ቃል ይገባል። ይህ ፍቅር እርስ በርስ ያስተሳሰራቸውን በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚኖረውን ፍቅር ይጨምራል። ይሁን እንጂ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚኖረውን ፍቅር ማሳየት ብቻ አይበቃም። አንድ ክርስቲያን ለትዳር ጓደኛዋ ወይም ለትዳር ጓደኛው የሚምለው ሞቅ ያለና የተሟላ ፍቅር ለማሳየት ነው።
ኤፌሶን 5:25 “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ይላል። ኢየሱስ ለጉባኤው ያለው ፍቅር በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚፈጠረው ፍቅር ዓይነት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራባቸው “ውደዱ” እና “ወደዳት” የሚሉት ቃላት በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራውን ፍቅር ከሚያመለክተው አጋፔ ከሚለው ቃል የመጡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ ባሎች ለሚስቶቻቸው የማያቋርጥ፣ የማያወላውልና ጽኑ ፍቅር እንዲያሳዩ ያዛል።
ይህ “ስለምትወጂኝ እወድሻለሁ” በሚል ዓይነት ስሜት የተፈጠረ ፍቅር አይደለም። ባል ለሚስቱ ደኅንነት ከራሱ አስበልጦ የሚያስብ ከመሆኑም በተጨማሪ ሚስቱም እንደዚሁ ታደርጋለች። (ፊልጵስዩስ 2:4) ለትዳር ጓደኛህ ያለህን ፍቅር ማጎልበትህ የጋብቻ መሐላህን እንድታከብር ይረዳሃል።
“ልንከባከብ”፦ አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚለው “መንከባከብ” ማለት ‘እንደ ውድ ነገር አድርጎ መያዝ፣ የፍቅር ስሜት ማሳደር ወይም ፍቅር ማሳየት’ ማለት ነው። ፍቅርህን በቃልም ሆነ በተግባር መግለጽ ይኖርብሃል! በተለይ ሚስት ባሏ ለእርሷ ያለውን ፍቅር ሁልጊዜ በተግባር እንዲያሳያት ትፈልጋለች። ባሏ ሥጋዊ ፍላጎቶቿን በተገቢ ሁኔታ ሊያሟላላት ቢችልም ይህን ማድረጉ ብቻ አይበቃም። ምንም እንኳ በቂ ምግብና ምቹ መኖሪያ ቤት ቢኖራቸውም የትዳር ጓደኞቻቸው ችላ ስላሏቸው ወይም ከነጭራሹ ስለተዉአቸው በጣም የሚማረሩ ሚስቶች አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የምትወደድና ተገቢው እንክብካቤ የሚደረግላት ሚስት የምትደሰትበት በቂ ምክንያት አላት። ይህ ሁኔታ በባል አኳያም ይሠራል። ልባዊ የሆኑ የፍቅር መግለጫዎች እውነተኛ ፍቅር እንዲጎለብት ያደርጋሉ። በመኃልየ መኃልይ ውስጥ አፍቃሪው እረኛ እንዲህ በማለት አድናቆቱን ገልጿል፦ “እህቴ ሙሽራ ሆይ፣ ፍቅርሽ እንዴት መልካም ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ እንዴት ይሻላል! የዘይትሽም መዓዛ ከሽቱ ሁሉ!”—መኃልየ መኃልይ 4:10
“እንዲሁም በጥልቅ ለማክበር”፦ ለብዙ መቶ ዘመናት በሴቶች ላይ ግፍ የሚፈጽሙና ሴቶችን የሚያዋርዱ ወንዶች ነበሩ። ወርልድ ሄልዝ የተባለው መጽሔት እንደተናገረው በዛሬው ጊዜም እንኳን “በሁሉም አገሮች ውስጥ፣ በማናቸውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ በሚገኙ ቦታዎች በሴቶች ላይ ዓመፅ ይፈጸምባቸዋል። በአብዛኞቹ ባሕሎች ባል ሚስቱን የመደብደብ መብት እንዳለው ይታመናል።” አብዛኞቹ ወንዶች በእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ተጠያቂ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ብዙ ወንዶች ሴቶችን ለሚመለከቱ ጉዳዮች ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ አይመስልም። በዚህም ምክንያት ብዙ ሴቶች ለወንዶች አሉታዊ አመለካከት አላቸው። አንዳንድ ሚስቶች “ባሌን እወደዋለሁ፤ ሆኖም ላከብረው አልችልም!” ሲሉ ይደመጣሉ።
ሆኖም የምትፈልገውን ነገር ሁሉ አንዳንድ ጊዜ ባያሟላላትም እንኳ ባሏን ለማክበር የምትጥር ሴት በይሖዋ አምላክ ዘንድ ከፍተኛ ግምት ይሰጣታል። ይህች ሴት ባሏ አምላክ የሰጠው ሥራ ወይም ቦታ እንዳለው ትገነዘባለች። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:23) ስለዚህ ለባሏ ያላት ጥልቅ አክብሮት የአምልኮቷና ለይሖዋ የምታሳየው ታዛዥነት ክፍል ነው። አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ሴቶች የሚያሳዩትን ታዛዥነት አምላክ አቅልሎ አይመለከተውም።—ኤፌሶን 5:33፤ 1 ጴጥሮስ 3:1-6፤ ከዕብራውያን 6:10 ጋር አወዳድር።
በጋብቻ ውስጥ እርስ በርስ መከባበር ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም ይህ አክብሮት ስለተፈለገ ወይም አክብሩኝ ተብሎ ሳይሆን በጥረት የሚገኝ መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል አሽሙር ወይም የሚያስከፋ አነጋገር በጋብቻ ውስጥ ቦታ የለውም። ባልሽን ወይም ሚስትህን በተመለከት የሚያዋርዱ አስተያየቶችን መሰንዘር ፍቅርን ወይም አክብሮትን የሚያንጸባርቅ አይደለም። የትዳር ጓደኛህን ጉድለቶች ለሌሎች መንገር ወይም በሰዎች ፊት ስለ ጉድለቶቹ ማውራት አንዳች አይጠቅምም። በዚህ ረገድ ቀልድ እንኳ መናገር አክብሮት ማጣትን ያሳያል። በኤፌሶን 4:29, 32 ላይ የሚገኙት ቃላት በባልና ሚስት ላይ ይሠራሉ። እዚህ ጥቅስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።”
“በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ . . . በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ መሠረት”፦ አምላክ በምርጫችንና በምናደርጋቸው ነገሮች ነፃነት እንዲሰማን ይፈልጋል። እርሱ ትዳርን የሚቆጣጠሩ ከመጠን በላይ የበዙ ሕጎችን በመስጠት ሸክም አልጫነብንም። ሆኖም ለራሳችን ጥቅም ሲል አንዳንድ መመሪያዎችን ሰጥቶናል።
በዛሬው ጊዜ ጋብቻን በተመለከተ እጅግ ብዙ የሆኑ ጽሑፎች ይወጣሉ፤ ከዚህም በላይ ብዙ ሰዎች የራሳቸው ፍልስፍና አላቸው። ሆኖም ተጠንቀቁ! ጋብቻን በተመለከተ በመሰራጨት ላይ የሚገኙት አያሌ ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ናቸው።
በተጨማሪም አንድ ባልና ሚስት ያላቸው ሁኔታ ከሌሎቹ ባልና ሚስቶች ሁኔታ ጋር እንደሚለያይ አስተውሉ። በአንዳንድ መንገዶች ሲታይ የተጋቡ ባልና ሚስቶች ከበረዶ ቅንጣቶች ጋር ይመሳሰላሉ፤ እነዚህ የበረዶ ቅንጣቶች ከሩቅ ሲታዩ ተመሳሳይ ሊመስሉ ቢችሉም እያንዳንዳቸው ከሌሎቹ በጣም የተለዩ ናቸው። የአንተና የትዳር ጓደኛህ ባሕርይ ሲቀናጅ በዓለም ውስጥ ከሚገኝ ከማናቸውም ባልና ሚስት ባሕርይ ጋር አይመሳሰልም። ስለዚህ የሌሎችን የግል አስተያየት ለመቀበል አትቸኩል። በሁሉም ጋብቻ ላይ የሚሠራ አንድም ሰው ሠራሽ ደንብ የለም!
ከዚህ በተቃራኒ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ትክክለኛና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ መዝሙር 119:151) መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብክና የሚሰጣቸውን ትምህርቶች በዕለት ተለት ሕይወትህ መመሪያህ አድርገህ ከተጠቀምክባቸው የጋብቻ መሐላህን ልታከብር ትችላለህ።—መዝሙር 119:105
“ሁለታችንም . . . በዚች ምድር ላይ በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ”፦ ይህ መሐላ ለረጅም ጊዜያት አብሮ ስለ መኖር ይገልጻል። አምላክ “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል” ሲል አዟል። (ዘፍጥረት 2:24) ይሖዋ አንድ ላይ እንድትሆኑ ይፈልጋል። አብራችሁ አምላክን አገልግሉ። ቃሉን አብራችሁ አጥኑ። አንድ ላይ ሆናችሁ ለመንሸራሸር፣ ለመቀመጥና ለመመገብ ጊዜ መድቡ። አብራችሁ ተደሰቱ!
አንዳንድ ባልና ሚስት በየቀኑ አንድ ላይ ሆነው ለመነጋገር ብቻ ብለው ጊዜ ይመድባሉ። ለብዙ ዓመታት በትዳር ካሳለፉም በኋላ እንኳ አብረው መሆናቸው ከጋብቻ ለሚያገኙት ደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
“በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር”፦ ትዳር የይሖዋ አምላክ ስጦታ ነው፤ የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው እሱ ነው። (ምሳሌ 19:14) የእርሱን ዝግጅት ሳታከብር መቅረትህ በጋብቻ የምታገኘውን ደስታ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ ጋር ያለህን ዝምድና አደጋ ላይ ይጥለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ባልና ሚስት የፈጣሪን ሥርዓቶች በማክበር ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ካጠነከሩ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ዝምድና ይኖራቸዋል።—ምሳሌ 16:7
ለገባኸው የጋብቻ መሐላ ዋንኛው ምሥክር ይሖዋ መሆኑን በጭራሽ አትርሳ። ይህን ከባድ መሐላ ማክበርህን ቀጥል። እንዲህ ካደረግህ ጋብቻህ ለይሖዋ አምላክ ክብርና ውዳሴ የሚያመጣ ይሆናል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በአንዳንድ አገሮች በአካባቢው ሕጎች የተነሣ በዚህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች የተደረገበትን መሐላ መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል። (ማቴዎስ 22:21) ሆኖም በአብዛኞቹ አገሮች ክርስቲያን የሆኑ ወንድና ሴት በሚጋቡበት ጊዜ ከላይ በሚገኘው መሐላ ይጠቀማሉ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአንዳንድ መንገዶች ባልና ሚስት ከበረዶ ቅንጣቶች ጋር ይመሳሰላሉ። ከሩቅ ሲታዩ ሁሉም ባልና ሚስቶች ተመሳሳይ ሊመስሉ ቢችሉም እያንዳንዳቸው ከሌሎቹ በጣም የተለዩ ናቸው
[ምንጭ]
Snow Crystals/ Dover