የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 10/1 ገጽ 8-13
  • በቤተሰባችሁ ውስጥ አምላክን ታስቀድማላችሁን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቤተሰባችሁ ውስጥ አምላክን ታስቀድማላችሁን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የቤተሰብ ተቃውሞ የሚያመጣው ወጥመድ
  • ተፈታታኙን ሁኔታ መጋፈጥ
  • ሊገኝ የሚችለው ታላቅ ወሮታ
  • ከኢየሱስ መማር
  • ባሎችና ሚስቶች ክርስቶስን ምሰሉት!
  • የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ባሎች—የራስነት ሥልጣንን በመጠቀም ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 10/1 ገጽ 8-13

በቤተሰባችሁ ውስጥ አምላክን ታስቀድማላችሁን?

“አንተም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] አምላክህን በፍጹም ልብህ . . . ውደድ።”—ማርቆስ 12:29, 30 የ1980 ትርጉም

1. ይሖዋን መውደዳችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

አንድ ጸሐፊ “ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ የራሱን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ በዘዳግም 6:4, 5 ላይ ካለው የአምላክ ቃል በመጥቀስ ጥያቄውን መለሰለት። የሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፦ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] አምላካችን አንድ አምላክ ነው፤ አንተም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም አሳብህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ’ የሚል ነው።”—ማርቆስ 12:28–30 የ19 80 ትርጉም

2. (ሀ) ኢየሱስ ምን ተቃውሞ አጋጥሞታል? (ለ) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋን ማስደሰትን አስቸጋሪ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?

2 ኢየሱስ የመጀመሪያው ትእዛዝ በማለት የጠራውን ማለትም ከሁሉ የሚበልጠውን ትእዛዝ መታዘዝ ዘወትር ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር እንድናደርግ ይጠይቅብናል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ በሌላ ወቅት ደግሞ የቅርብ ዘመዶቹ ድርጊቱን ቢቃወሙም እንኳ ኢየሱስ ይህን አድርጓል። (ማቴዎስ 16:21–23፤ ማርቆስ 3:21፤ ዮሐንስ 8:29) አንተስ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? የቤተሰብ አባሎችህ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳታጠና እና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት እንድታቋርጥ ፈለጉ እንበል። እሱን የሚያስደስተውን ነገር በማድረግ አምላክን ታስቀድማለህን? የቤተሰብ አባሎችህ እሱን ለማገልገል የምታደርጋቸውን ጥረቶች በሚቃወሙበት ወቅትም እንኳ አምላክን ታስቀድማለህን?

የቤተሰብ ተቃውሞ የሚያመጣው ወጥመድ

3. (ሀ) የኢየሱስ ትምህርቶች በቤተሰብ ላይ ምን ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ? (ለ) የቤተሰብ አባሎች ከሁሉ የበለጠ የሚወዱት ማንን እንደሆነ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ የእሱን ትምህርቶች የተቀበለ ሰውን ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሲቃወሙ ሊመጣ የሚችለውን ችግር አቅልሎ አልተመለከተም። ኢየሱስ “ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” ብሏል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ቢኖርም “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” በማለት ማን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳይቷል። (ማቴዎስ 10:34–37) ‘የአምላክ ትክክለኛ ነጸብራቅ’ የሆነውን የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች በመከተል ይሖዋ አምላክን እናስቀድማለን።—ዕብራውያን 1:3፤ ዮሐንስ 14:9

4. (ሀ) ኢየሱስ የእሱ ተከታይ መሆን ምንን እንደሚጨምር ተናግሯል? (ለ) ክርስቲያኖች የቤተሰብ አባሎቻቸውን የሚጠሉት በምን መንገድ ነው?

4 ኢየሱስ በሌላ ወቅት የእሱ ተከታይ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ሲያብራራ “ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 14:26) ኢየሱስ ሰዎች ጠላቶቻቸውን እንኳ እንዲወዱ ስላዘዘ ተከታዩቹ የራሳቸውን ቤተሰብ አባሎች ቃል በቃል መጥላት አለባቸው ማለቱ እንዳልነበር ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 5:44) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ይህን ሲናገር ተከታዮቹ ቤተሰቦቻቸውን ከአምላክ ያነሰ መውደድ አለባቸው ማለቱ ነበር። (ከማቴዎስ 6:24 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ማብራሪያ ጋር በመስማማት ያዕቆብ ልያን እንደ ‘ጠላት’ እና ራሔልን እንደ ወደዳት ይናገራል፤ ይህም ያዕቆብ እህቷን ራሔልን የሚወዳትን ያህል ልያን አይወዳትም ነበር ማለት ነው። (ዘፍጥረት 29:30–32) ኢየሱስ ‘ነፍሳችንን’ ወይም ሕይወታችንን እንኳ መጥላት ወይም ከይሖዋ ያነሰ መውደድ እንዳለብን ተናግሯል!

5. ሰይጣን የቤተሰብን ዝግጅት መሠሪ በሆነ መንገድ የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ፈጣሪና ሕይወት ሰጪ እንደ መሆኑ መጠን አገልጋዮቹ በሙሉ የተሟላ አምልኮታዊ ፍቅር ሊያሳዩት ይገባል። (ራእይ 4:11) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “በእግዚአብሔር አብ ፊት በጉልበቴ ተንበርክኬ የምጸልየው በዚህ ምክንያት ነው። በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ እውነተኛ ስሙን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው።” (ኤፌሶን 3:14, 15 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ የቤተሰብ ዝግጅትን የመሠረተው የቤተሰብ አባሎች እርስ በርሳቸው ‘የተፈጥሮ ፍቅር’ ማሳየት በሚችሉበት አስደናቂ በሆነ መንገድ ነው። (1 ነገሥት 3:25, 26፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7) ይሁን እንጂ የሚወዱትን ሰው ማስደሰትን የሚጨምረውን ይህን ተፈጥሮአዊ የቤተሰብ ፍቅር ሰይጣን ዲያብሎስ መሠሪ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። የቤተሰብ ተቃውሞ እየጨመረ እንዲሄድ ስለሚያደርግ ብዙዎች በዚህ ሁኔታ ሥር ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የጸና አቋም መያዝ ፈታኝ ይሆንባቸዋል።—ራእይ 12:9, 12

ተፈታታኙን ሁኔታ መጋፈጥ

6, 7. (ሀ) የቤተሰብ አባሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትንና የክርስቲያናዊ ቅርርብን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) የቤተሰብ አባሎቻችንን በእርግጥ እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

6 አምላክን ወይም አንድን የቤተሰብህን አባል ከማስደሰት መካከል አንዱን እንድትመርጥ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በቤተሰብ ውስጥ ጠብ እንዲፈጠር የሚያደርግ ከሆነ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና እና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሥራ ላይ እንድናውል አይጠብቅብንም በማለት ትቃወማለህን? ሆኖም እስቲ ጉዳዩን አስብበት። ለተቃውሞው ተሸንፈህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ወይም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘትህን ብታቋርጥ የምትወዳቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት የሕይወትና የሞት ጉዳይ መሆኑን እንዴት ሊረዱ ይችላሉ?—ዮሐንስ 17:3፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6–8

7 ሁኔታውን በዚህ መልኩ በምሳሌ ማስረዳት እንችል ይሆናል፦ ምናልባት አንድ የቤተሰብ አባል የአልኮል ሱስ ክፉኛ ተጠናውቶታል። የመጠጥ ችግሩን በቸልታ ማለፍ ወይም እንዲጠጣ መፍቀድ በእርግጥ ይጠቅመዋልን? ችግሩን አሜን ብሎ በመቀበል ሰላም እንዳይደፈርስ መጣርና ችግሩን ለማቃለል የሚረዳ ምንም ነገር ከማድረግ መቆጠብ ይሻላልን? አይሻልም፤ ቁጣውን ወይም ማስፈራሪያውን መቻል ቢያስፈልግም እንኳ የመጠጥ ችግሩን እንዲያሸንፍ መርዳት የተሻለ እንደሚሆን ሳትስማማ አትቀርም። (ምሳሌ 29:25) በተመሳሳይም የቤተሰብ አባሎችህን በእርግጥም የምትወዳቸው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትህን እንድታቆም ለሚያደርጉት ጥረት አትሸነፍም። (ሥራ 5:29) የክርስቶስ ትምህርቶች ሕይወታችንን የሚመለከቱ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ልትረዳቸው የምትችለው ጽኑ አቋም በመያዝ ብቻ ነው።

8. ኢየሱስ በታማኝነት የአምላክን ፈቃድ በማድረጉ የተጠቀምነው እንዴት ነው?

8 አንዳንድ ጊዜ አምላክን ማስቀደም በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሰይጣን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለኢየሱስ ጭምር አስቸጋሪ እንዲሆንበት እንዳደረገ አስታውስ። ሆኖም ኢየሱስ ፈጽሞ አልተሸነፈም፤ ሌላው ቀርቶ ለእኛ ሲል በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከ መሠቃየት ድረስ ጸንቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አዳኛችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ሞተልን’ ይላል። (ቲቶ 3:6፤ 1 ተሰሎንቄ 5:10) ኢየሱስ ለተቃውሞ ባለመሸነፉ አመስጋኝ አይደለንምን? በአቋሙ ጸንቶ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞቱ ምክንያት በፈሰሰው ደሙ በማመን ጽድቅ በሚኖርባት ሰላማዊ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ከፊታችን ተዘርግቶልናል።—ዮሐንስ 3:16, 36፤ ራእይ 21:3, 4

ሊገኝ የሚችለው ታላቅ ወሮታ

9. (ሀ) ክርስቲያኖች ሌሎች እንዲድኑ በመርዳት ረገድ ድርሻ ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የጢሞቴዎስ ቤተሰብ ሁኔታ ምን ነበር?

9 በጣም የምትወዳቸውን ዘመዶችህን ጨምሮ ሌሎችን የማዳን አጋጣሚ እንዳለህ ተገንዝበሃልን? ሐዋርያው ጳውሎስ “በእነዚህም [በተማርክበት ነገር] ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” በማለት ጢሞቴዎስን አጥብቆ መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አባቱ አማኝ ያልሆነ ግሪካዊ ስለ ነበር ጢሞቴዎስ የኖረው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። (ሥራ 16:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14) የጢሞቴዎስ አባት ወደ ክርስትና እምነት ስለመለወጡ የምናውቀው ነገር ባይኖርም በባለቤቱ በኤውንቄና በጢሞቴዎስ የታማኝነት ጠባይ አማካኝነት መለወጥ የሚችልበት ሰፊ አጋጣሚ ተከፍቶለት ነበር።

10. ክርስቲያኖች ለማያምኑ የትዳር ጓደኞቻቸው ምን ሊያደርጉላቸው ይችላሉ?

10 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አጥብቀው የሚይዙ ባሎችና ሚስቶች ክርስቲያን ያልሆኑ የትዳር ጓደኞቻቸው አማኞች እንዲሆኑ በመርዳት ለእነዚህ የትዳር ጓደኞቻቸው መዳን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ቅዱሳን ጽሑፎች ይገልጻሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት፤ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፣ አትተወው። አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ፣ አንተ ሰው፣ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?” (1 ቆሮንቶስ 7:12, 13, 16) ሐዋርያው ጴጥሮስ ሚስቶች ባሎቻቸውን እንዴት ሊያድኑ እንደሚችሉ አጥብቆ ሲመክራቸው “ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው” ብሏል።—1 ጴጥሮስ 3:1

11, 12. (ሀ) በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ምን ወሮታ ተከፍሏቸዋል? ይህን ወሮታ ለማግኘት ምን አድርገዋል? (ለ) በታማኝነት በመጽናቱ ምክንያት ወሮታ የተከፈለውን የአንድ ቤተሰብ አባል ተሞክሮ ተናገር።

11 የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ዘመዶቻቸውን ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ለበርካታ ወራት እንዲያውም ዓመታት ሲቃወሙ የነበሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በቅርብ ዓመታት እነሱ ራሳቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ይህ በአቋማቸው ለጸኑት ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ታላቅ ወሮታ ነው! በተጨማሪም በአንድ ወቅት ተቃዋሚዎች ለነበሩት እንዴት ያለ በረከት ነው! አንድ የ74 ዓመት ዕድሜ ያለው ክርስቲያን ሽማግሌ “ባለቤቴና ልጆቼ እቃወማቸው በነበርኩባቸው ዓመታት በእውነት ጸንተው በመቀጠላቸው ዘወትር አመሰግናቸዋለሁ” በማለት በአድናቆት ተናግሯል። ሌላው ቀርቶ ሚስቱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልትነግረው ስትፈልግ እንኳ ሦስት ዓመት ሙሉ አጥብቆ ይቃወማት እንደ ነበር ገልጿል። “ይሁን እንጂ ይበልጥ ተቀባይ ልሆን የምችልበትን ወቅት ትመርጥና እግሮቼን እያሻሸች መመሥከር ትጀምራለች። በተቃውሞዬ ባለመሸነፏ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ!” ብሏል።

12 ቤተሰቡን ይቃወም የነበረ ሌላ ባል እንዲህ በማለት ጽፏል፦ ‘ባለቤቴ እውነትን ካወቀች በኋላ እዝትባትና ዘወትር እንጣላ ስለነበር ዋና ጠላቷ ሆኜ ነበር፤ ሁልጊዜ ጠብ እፈጥር ነበር ለማለት ፈልጌ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ከንቱ ነበር፤ ባለቤቴ በፍጹም መጽሐፍ ቅዱስን አልተወችም። በዚህ መንገድ እውነትን እንዲሁም ባለቤቴንና ልጄን ክፉኛ ስቃወም አሥራ ሁለት ዓመታት አለፉ። ሁኔታው ሥጋ የለበሰ ዲያብሎስ የሆንኩባቸው ያህል ነበር።’ ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው ምን ዓይነት ጠባይ እንደነበረው መገንዘብ ጀመረ። ‘ምንኛ ጨካኝ እንደ ነበርኩ ተረዳሁ። በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቼ የተጠመቅሁ ክርስቲያን ሆኛለሁ’ ሲል ገልጿል። ባለቤቱ ያገኘችውን ታላቅ ወሮታ እስቲ አስበው፦ እሱ ለ12 ዓመታት ያደረሰባትን ተቃውሞ ችላ በታማኝነት በመጽናቷ ‘ባሏን እንዲድን’ ረዳችው!

ከኢየሱስ መማር

13. (ሀ) ባሎችና ሚስቶች ከክርስቶስ አካሄድ መማር ያለባቸው ዋነኛ ትምህርት ምንድን ነው? (ለ) የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስቸገራቸው ሰዎች ኢየሱስ ካሳየው ምሳሌ ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ባሎችና ሚስቶች ከኢየሱስ አካሄድ ሊማሩት የሚገባቸው ዋነኛ ትምህርት ለአምላክ መታዘዝ ነው። ኢየሱስ “እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁ። የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም” ብሏል። (ዮሐንስ 5:30፤ 8:29) ኢየሱስ በአንድ ወቅት የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሚጠይቅ አንድ ለየት ያለ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ሁኔታውን ከባድ ሆኖ ቢያገኘውም እንኳ ታዛዥ ሆኖ ነበር። “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” በማለት ጸልዮአል። ይሁን እንጂ ወዲያውኑ “ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” በማለት በጸሎቱ ላይ አከለ። (ሉቃስ 22:42) አምላክ ፈቃዱን እንዲለውጥ ኢየሱስ አልጠየቀም፤ አምላክ ለእሱ ያለው ፈቃድ ምንም ይሁን ምን ራሱን በማስገዛት አምላክን በእርግጥ እንደሚወደው አሳይቷል። (1 ዮሐንስ 5:3) ኢየሱስ እንዳደረገው ዘወትር ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ መስጠት በነጠላነት ሕይወት ብቻ ሳይሆን በትዳርና በቤተሰብ ኑሮም ጭምር ስኬታማ ለመሆን በጣም ጠቃሚ ነው። እስቲ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ተመልከት።

14. አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያድርባቸዋል?

14 ከዚህ በፊት እንደተገለጸው አማኞች አምላክን ሲያስቀድሙ ከማያምኑ የትዳር ጓደኞቻቸው ጋር ለመቆየትና ብዙውን ጊዜ ደግሞ እነሱ ለመዳን እንዲበቁ ለመርዳት ይችላሉ። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች አማኞች ቢሆኑም እንኳ ትዳራቸው ምንም እንከን የሌለው ላይሆን ይችላል። ከኃጢአተኝነት ዝንባሌ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ የትዳር ጓደኛሞች አንዱ ለሌላው ፍቅራዊ አሳቢነት ሳያሳዩ ይቀራሉ። (ሮሜ 7:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 7:28) እንዲያውም አንዳንዶች ለፍቺ የሚያበቁ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ባይኖሯቸውም እንኳ ሌላ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እስከ መፈለግ ደርሰዋል። (ማቴዎስ 19:9፤ ዕብራውያን 13:4) አምላክ ባልና ሚስቶች እንዳይለያዩ ያለው ፈቃድ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አድርገው በመመልከት ቢለያዩ እንደሚሻላቸው ያስባሉ። (ሚልክያስ 2:16፤ ማቴዎስ 19:5, 6) ይህ አንድ ሰው የአምላክን ሳይሆን የሰውን ሐሳብ የሚያሳይበት ሌላው ሁኔታ ለመሆኑ አያጠራጥርም።

15. አምላክን ማስቀደም ጥበቃ የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 አምላክን ማስቀደም ተወዳዳሪ የሌለው ጥበቃ ያስገኛል። እንዲህ የሚያደርጉ ባልና ሚስቶች አንድ ላይ ሆነው የአምላክ ቃል በሚሰጠው ምክር መሠረት ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይጥራሉ። በዚህ መንገድ የአምላክን ፈቃድ ቸል ማለት ከሚያስከትላቸው ከማናቸውም ዓይነት አሳዛኝ ነገሮች ይድናሉ። (መዝሙር 19:7–11) ይህ ሁኔታ ለመፋታት በቋፍ ላይ ከደረሱ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ለመከተል በወሰኑ አንድ ወጣት ባልና ሚስት ላይ ታይቷል። ሚስትየው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ያገኘችውን ደስታ መለስ ብላ ስታስብ የሚሰማትን ስሜት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “ከባለቤቴ ጋር ተለያይቼ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ሁሉ ዓመታት እንዴት እገፋቸው እንደ ነበር ሳስብ ቁጭ እልና ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። ከዚያም ወደ ይሖዋ አምላክ እጸልይና እንዲህ ያለ አስደሳች ቅርርብ የፈጠረልንን ምክርና መመሪያ ስለ ሰጠን አመሰግነዋለሁ።”

ባሎችና ሚስቶች ክርስቶስን ምሰሉት!

16. ኢየሱስ ለባሎችና ለሚስቶች ምን ምሳሌ ትቷል?

16 ዘወትር አምላክን የሚያስቀድመው ኢየሱስ ለባሎችም ሆነ ለሚስቶች የሚሆን አስደናቂ ምሳሌ ትቶላቸዋል፤ እነሱም የእሱን ምሳሌ በጥንቃቄ ቢከተሉ ጥሩ ነው። ባሎች ኢየሱስ ለክርስቲያን ጉባኤ አባሎች የሚያሳየውን በርኅራኄ ላይ የመሠረተ ራስነት እንዲኮርጁ በጥብቅ ተመክረዋል። (ኤፌሶን 5:23) በተጨማሪም ክርስቲያን ሚስቶች ኢየሱስ እንከን በሌለው መንገድ ለአምላክ በመገዛት ካሳየው ምሳሌ ሊማሩ ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 11:3

17, 18. ኢየሱስ ለባሎች ጥሩ ምሳሌ የተወው በምን መንገዶች ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ” በማለት ያዛል። (ኤፌሶን 5:25) ኢየሱስ ለጉባኤው አባላት ያለውን ፍቅር ያሳየበት አንዱና ዋነኛ መንገድ ለተከታዮቹ የቅርብ ወዳጅ በመሆን ነው። ኢየሱስ “ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጥሁላችሁ ወዳጆቼ ብያችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 15:15) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በመነጋገር ያሳለፈውን ጊዜ ማለትም ከእነሱ ጋር ያደረጋቸውን ብዙ ውይይቶችና ምን ያህል ይተማመንባቸው እንደነበር አስብ! ይህ ለባሎች ግሩም ምሳሌ አይሆንምን?

18 ኢየሱስ ለምድራዊ ደቀ መዛሙርቱ ከልብ ያስብላቸው ነበር፤ ለእነሱም እውነተኛ ፍቅር ነበረው። (ዮሐንስ 13:1) ትምህርቱ ግልጽ ሳይሆንላቸው ሲቀር ጊዜ መድቦ በትዕግሥት ያብራራላቸው ነበር። (ማቴዎስ 13:36–43) ባሎች ሆይ ለራሳችሁ መንፈሳዊ ደኅንነት የምትሰጡትን ያህል ለሚስቶቻችሁ መንፈሳዊ ደኅንነት ከፍተኛ ቦታ ትሰጣላችሁን? የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በሁለታችሁም አእምሮና ልብ ውስጥ በግልጽ እንዲቀረጹ ለማድረግ ከእሷ ጋር የተወሰነ ጊዜ ታሳልፋላችሁን? ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር ወደ አገልግሎት ይሄድ ነበር፤ ምናልባትም በዚህ መንገድ እያንዳንዳቸውን ሳያሠለጥናቸው አልቀረም። አብረህ ከቤት ወደ ቤት በመሄድና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ከሚስትህ ጋር ታገለግላለህን?

19. ሐዋርያት በተደጋጋሚ ጊዜያት ድክመት ባሳዩበት ወቅት ኢየሱስ የእነሱን ድክመት ለማስተካከል ያደረገው ነገር ለባሎች ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

19 ኢየሱስ በተለይ ሐዋርያቱ የነበራቸውን ድክመቶች እንዲያሻሽሉ በመርዳት ረገድ ለባሎች በጣም ግሩም የሆነ ምሳሌ ትቶላቸዋል። ከሐዋርያት ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ እራት ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት የፉክክር መንፈስ ተመልክቶ ነበር። ይህን ስላደረጉ ኃይለ ቃል በመናገር ነቀፋቸውን? በፍጹም፣ ከዚህ ይልቅ በትሕትና የእያንዳንዳቸውን እግር አጠበ። (ማርቆስ 9:33–37፤ 10:35–45፤ ዮሐንስ 13:2–17) ለሚስትህ እንደዚህ ዓይነት ትዕግሥት ታሳያታለህን? በተደጋጋሚ ጊዜያት በምታየው ድክመት ከመማረር ይልቅ በትዕግሥት እሷን በመርዳትና ምሳሌ በመሆን ልቧን ለመንካት ትሞክራለህን? ሐዋርያት ከጊዜ በኋላ እንዳደረጉት ሁሉ ሚስቶችም ለእንዲህ ዓይነቱ ፍቅራዊ ርኅራኄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው አይቀርም።

20. ክርስቲያን ሚስቶች በጭራሽ መርሳት የሌለባቸው ነገር ምንድን ነው? ለዚህ ምሳሌ የሚሆናቸው ማን ነው?

20 ሚስቶችም የኢየሱስን ምሳሌ ማስታወስ አለባቸው፤ እሱ ‘የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር’ እንደሆነ በጭራሽ ረስቶ አያውቅም። ለሰማያዊ አባቱ ዘወትር ይገዛ ነበር። በተመሳሳይም ሚስቶች ‘የሴት ራስ ወንድ’ እንደሆነ አዎን፣ ባላቸው የእነሱ ራስ መሆኑን መርሳት የለባቸውም። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:23) ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ሚስቶች ‘ቅዱሳን ሴቶች’ ያሳዩትን ምሳሌ በተለይም ደግሞ አብርሃምን ‘ጌታ ብላ እየጠራችው የታዘዘችለት’ ሣራ ያሳየችውን ምሳሌ እንዲያስታውሱ አጥብቆ መክሯቸዋል።—1 ጴጥሮስ 3:5, 6

21. የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ ሲሳካ የሎጥና የሚስቱ ጋብቻ ያልተሳካው ለምንድን ነው?

21 ሣራ በማታውቀው አገር በድንኳን ውስጥ ለመኖር በአንድ የበለጸገ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ምቹ የሆነ መኖሪያ ቤቷን ትታ እንደ ወጣች ገልጽ ነው። ለምን? ይህን አኗኗር ስለ መረጠች ነበርን? በፍጹም ሊሆን አይችልም። ባሏ ከተማውን ለቀው እንዲሄዱ ጥያቄ ስላቀረበላት ነውን? ሣራ በአምላካዊ ባሕሪዎቹ ምክንያት አብርሃምን ታፈቅረውና ታከብረው ስለ ነበር ይህ አንዱ ምክንያት እንደሚሆን አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 18:12) ይሁን እንጂ ከባሏ ጋር እንድትሄድ የገፋፋት ዋናው ምክንያት ለይሖዋ ያላት ፍቅርና የአምላክን መመሪያዎች ለመከተል የነበራት ልባዊ ፍላጎት ነበር። (ዘፍጥረት 12:1) አምላክን መታዘዝ ያስደስታት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የሎጥ ሚስት የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ስላንገራገረች በትውልድ ከተማዋ በሰዶም ውስጥ ጥላቸው የወጣቻቸውን ነገሮች በመመኘት ወደ ኋላዋ ተመለከተች። (ዘፍጥረት 19:15, 25, 26፤ ሉቃስ 17:32) ለአምላክ ባለመታዘዟ ምክንያት ብቻ የዚያ ትዳር ፍጻሜ መሆኑ እንዴት ያሳዝናል!

22. (ሀ) የቤተሰብ አባሎች ራሳቸውን ምን ብለው ቢመረምሩ ጥበብ ይሆንላቸዋል? (ለ) በሚቀጥለው ጥናት ላይ የምንመለከተው ምንድን ነው?

22 ስለዚህ ባሎችም ሆናችሁ ሚስቶች ራሳችሁን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቃችሁ እጅግ ጠቃሚ ነው፦ ‘በቤተሰባችን ውስጥ አምላክ የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛልን? አምላክ በቤተሰቤ ውስጥ የሰጠኝን የሥራ ድርሻ ለመወጣት በእርግጥ እጥራለሁን? የትዳር ጓደኛዬን ለማፍቀርና ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንድትመሠርት (እንዲመሠርት) ወይም ከይሖዋ ጋር ያላትን (ያለውን) ጥሩ ግንኙነት እንድትንከባከብ (እንዲንከባከብ) ልባዊ ጥረት አደርጋለሁን?’ በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ውስጥ ልጆችም አሉ። ከዚህ ቀጥሎ ወላጆች የሚጫወቱትን ሚና እና እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው አምላክን ማስቀደማቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንመለከታለን።

ታስታውሳለህን?

◻ የኢየሱስ ትምህርቶች በብዙ ቤተሰቦች ላይ የሚያስከትሉት ውጤት ምን ሊሆን ይችላል?

◻ በሺህ የሚቆጠሩ በአቋማቸው የጸኑ ክርስቲያኖች ምን ወሮታ አግኝተዋል?

◻ የትዳር ጓደኛሞች ከመጥፎ ሥነ ምግባርና ከፍቺ እንዲጠበቁ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

◻ ባሎች ከኢየሱስ ምሳሌ ሊማሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ ሚስቶች ትዳርን አስደሳች ለማድረግ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሣራ ለጋብቻዋ ስምረት አስተዋጽኦ ያደረገችው እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ