ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ
“ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:21
1, 2. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናዊው ኑሮ የሚበጅ መጽሐፍ መሆኑን የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ መሆኑን ለማስረዳት የትኞቹን ሦስት ማስረጃዎች መጥቀስ እንችላለን?
መጽሐፍ ቅዱስ በ21ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ላሉት ሰዎች የሚሆን መጽሐፍ ነውን? አንዳንዶች አይደለም ብለው ያስባሉ። ዶክተር ኤላይ ኤስ ቼሰን መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ጊዜ ያለፈበት ነው ብለው እንደሚያስቡ ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በአንድ ዘመናዊ የኬሚስትሪ መማሪያ ክፍል በ1924 የተጻፈ የኬሚስትሪ መማሪያ መጽሐፍ መጠቀም አለብን ብሎ ሊሟገት የሚደፍር ሰው ሊኖር አይችልም። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ስለ ኬሚስትሪ የተገኘው እውቀት የትየለሌ ነው።” እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ላየው ሰው ይህ የመከራከሪያ ሐሳብ ትክክል ይመስል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ወዲህ የሰው ልጅ ስለ ሳይንስ፣ ስለ አእምሮ ጤና እንዲሁም ስለ ሰው ልጅ ባሕርይ ብዙ እውቀት እንዳካበተ አይካድም። በመሆኑም አንዳንዶች ‘እንዲህ ያለ ጥንታዊ መጽሐፍ እንዴት ከሳይንሳዊ ግድፈቶች የጠራ ሊሆን ይችላል?’ ‘እንዴትስ ለዘመናዊው ኑሮ የሚጠቅም ምክር ሊኖረው ይችላል?’ ብለው ይጠይቃሉ።
2 መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ መልሱን ይሰጠናል። በ2 ጴጥሮስ 1:21 ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትን በሚመለከት “በእግዚአብሔር ተልከው . . . በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” የሚል እናነባለን። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ መሆኑን ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ሌሎች ሰዎችን ማሳመን የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያረጋግጡ ሦስት ማስረጃዎችን እንመርመር:- (1) ሳይንሳዊ ትክክለኛነት የተንጸባረቀበት፣ (2) ለዘመናዊው ኑሮ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጊዜ የማይሽራቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ያሉት እንዲሁም (3) ፍጻሜያቸውን አግኝተው በታሪክ ሐቅነት የተረጋገጡ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው።
ከሳይንስ ጋር የሚስማማ መጽሐፍ
3. መጽሐፍ ቅዱስን ሳይንሳዊ ግኝቶች ይሽሩት ይሆን የሚል ስጋት የማይፈጠረው ለምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ የእውነት መጽሐፍ ነው፤ ይህ እውነት ደግሞ ጊዜ ሊሽረው የሚችል አይደለም። (ዮሐንስ 17:17) መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ግኝቶች ውድቅ ያደርጉታል ተብሎ የሚፈራለት መጽሐፍ አይደለም። ከሳይንስ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በሚጠቅስበት ጊዜ ጥንት “ሳይንሳዊ” ተደርገው ከሚታሰቡት ከተራ ተረትነት የማያልፉ ንድፈ ሐሳቦች የጠራ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው አንዳንድ መግለጫዎች ትክክለኛነታቸው በሳይንስ የተረጋገጡ ብቻ ሳይሆኑ በዘመኑ ተቀባይነት የነበራቸውን አስተሳሰቦች በቀጥታ የሚቃረኑ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስና በሕክምና ሳይንስ መካከል ያለውን ስምምነት ተመልከት።
4, 5. (ሀ) የጥንቶቹ ሐኪሞች ስለ በሽታዎች ያልተገነዘቡት ነገር ምን ነበር? (ለ) ሙሴ ከግብጻውያን ሐኪሞች የሕክምና ዘዴዎች ጋር በሚገባ ይተዋወቅ እንደነበር ምንም የማያጠራጥረው ለምንድን ነው?
4 በጥንት ጊዜ የነበሩ ሐኪሞች በሽታ እንዴት እንደሚተላለፍም ሆነ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ንጽሕና በጣም አስፈላጊ የሆነ ቦታ እንዳለው ሙሉ በሙሉ አልተገነዘቡም ነበር። ብዙዎቹ የሕክምና ዘዴዎቻቸው በዘመናዊ ሰዎች ዘንድ በጣም ኋላ ቀር ሆነው ይታያሉ። እጅግ ጥንታዊ ናቸው ከሚባሉት የሕክምና ጽሑፎች አንዱ በ1550 ከዘአበ ጀምሮ ያለው የግብጻውያን እውቀት የተጠናቀረበት ኤበርስ ፓፒረስ የተባለው ጽሑፍ ነው። በዚህ የመጽሐፍ ጥቅልል ውስጥ “ከአዞ ንክሻ እስከ ጥፍር በሽታ” ለሚደርሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች የሚታዘዙ 700 የሚያክሉ መድኃኒቶች ተዘርዝረዋል። አብዛኞቹ መድኃኒቶች ፈዋሽነት የሌላቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ በጣም አደገኛ ናቸው። ቁስል ለማከም ይታዘዙ ከነበሩት መድኃኒቶች አንዱ ቁስሉ ላይ የሚቀባ የሰውን ዐይነ ምድር ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር በመቀላቀል የሚሠራ ነበር።
5 ይህ የግብጻውያን የመድኃኒት መጽሐፍ የተጻፈው የሙሴ ሕግ የተመዘገበባቸው የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በተጻፉበት ጊዜ ገደማ ነው። በ1593 ከዘአበ የተወለደው ሙሴ ያደገው በግብጽ አገር ነበር። (ዘጸአት 2:1-10) ሙሴ ያደገው በፈርዖን ቤተሰብ ስለነበር ‘የግብጻውያንን ጥበብ በሙሉ ተምሯል።’ (ሥራ 7:22) የግብጻውያንን “ሐኪሞች” በሚገባ ያውቃቸው ነበር። (ዘፍጥረት 50:1-3) ታዲያ የእነዚህ ሐኪሞች ምንም ዓይነት ፈዋሽነት የሌለው ወይም አደገኛ የሆነ ሕክምና በጻፋቸው ጽሑፎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯልን?
6. በዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በሙሴ ሕግ ውስጥ የተጠቀሰው የትኛው የንጽሕና ሕግ ነው?
6 እንዲያውም በተቃራኒው የሙሴ ሕግ በዘመናዊው ሳይንስ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን የንጽሕና ሕጎች ያካተተ ነበር። ለምሳሌ ያህል ስለ ጦር ሠፈር የተሰጠ አንድ ሕግ ዐይነ ምድር ከሠፈሩ ውጭ እንዲቀበር ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 23:13) ይህ በጣም ዘመናዊ የሆነ መሠረታዊ የበሽታ መከላከያ ዘዴ ነው። የውኃ ምንጮች ከብክለት ነጻ እንዲሆኑ ከመርዳቱም በላይ በዛሬውም ጊዜ ሳይቀር በአብዛኛው በታዳጊ አገሮች ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጩትን እንደ ሺጌሎሲስ ያሉትንና ሌሎችን በዝንብ አስተላላፊነት የሚዛመቱ የተቅማጥ በሽታዎች ለማስወገድ ያስችላል።
7. የተላላፊ በሽታዎችን መዛመት ለመግታት የረዳው በሙሴ ሕግ ውስጥ ተጠቅሶ የነበረው የትኛው የንጽሕና መመሪያ ነው?
7 በሙሴ ሕግ ውስጥ ተዛማች በሽታዎች እንዳይስፋፉ የሚከላከሉ ሌሎች የንጽሕና ሕጎችም ተካትተዋል። ተላላፊ በሽታ የያዘው ወይም እንደያዘው የሚጠረጠር ሰው ለብቻው ተገልሎ እንዲቆይ ይደረግ ነበር። (ዘሌዋውያን 13:1-5) ሞቶ የተገኘ እንስሳን (በበሽታ ምክንያት ሊሆን ይችላል) የነካ ልብስ ወይም ዕቃ ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት መታጠብ አለበለዚያም ፈጽሞ መወገድ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 11:27, 28, 32, 33) ሬሳ የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ እንደሆነ ተቆጥሮ የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጽም ይገደድ ነበር። ይህ ሥርዓት ልብሱን ማጠብና ገላውንም መታጠብን ይጨምር ነበር። ርኩስ ሆኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት ከሌሎች ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አይኖረውም።—ዘኁልቁ 19:1-13
8, 9. በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኘው የንጽሕና መመሪያ ከዘመኑ ጥበብ የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
8 ይህ የንጽሕና ሕግ በዘመኑ ከነበረው ጥበብ ሁሉ የመጠቀ ነበር። ዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ የበሽታዎችን መዛመትና መከላከያ በተመለከተ ብዙ ነገር አውቋል። ለምሳሌ ያህል በ19ኛው መቶ ዘመን በሕክምናው መስክ የተገኘው እመርታ በበሽታዎች መለከፍን ለመቀነስ ንጽሕናን መጠበቅ የሚለውን ሐሳብ (አንቲሴፕሲስ) አስተዋውቋል። በዚህ ምክንያት በተላላፊ በሽታዎች ያለ ዕድሜ መቀጨት በእጅጉ ሊቀንስ ችሏል። በ1900 በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮችና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሰዎች አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን ከ50 ዓመት ያነሠ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ግን በእጅጉ ጨምሮ ተገኝቷል። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው በሽታን በመከላከል ረገድ የተደረገው የሕክምና መሻሻል ብቻ ሳይሆን ጥሩ የንጽሕና ልማድ መዳበርና የሰዎች አኗኗር መሻሻል ነው።
9 ይሁንና የሕክምና ሳይንስ በሽታዎች ስለሚዛመቱባቸው መንገዶች ከማወቁ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊ የሆኑ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎችን አዝዟል። ሙሴ በዘመኑ የነበሩት እስራኤላውያን ዕድሜ በጥቅሉ ሲታይ 70 ወይም 80 እንደሆነ መናገሩ አያስደንቅም። (መዝሙር 90:10) ሙሴ እነዚህን የንጽሕና ሕግጋት ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ‘ሕጉ በመላእክት በኩል እንደተላለፈ’ በመግለጽ መልሱን ይሰጠናል። (ገላትያ 3:19) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ጥበብ የተንጸባረቀበት መጽሐፍ አይደለም። ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ ነው።
ለዘመናዊው ኑሮ የሚሆን ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው መጽሐፍ
10. መጽሐፍ ቅዱስ ከተጠናቀቀ ወደ 2,000 ዓመታት የሚጠጋ ቢሆንም ምክሩን በተመለከተ ምን ነገር እውነት ሆኖ ይገኛል?
10 ምክር የሚሰጡ መጻሕፍት ጊዜ ያለፈባቸው እየሆኑ እንደገና ይሻሻላሉ ወይም በሌላ መጻሕፍት ይተካሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ልዩ መጽሐፍ ነው። መዝሙር 93:5 “ምሥክርህ [“ማሳሰቢያህ፣” NW] እጅግ የታመነ ነው” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ ወደ 2,000 ዓመታት ገደማ ቢሆንም ምክሩ ዛሬም ቢሆን ይሠራል። የትኛውም ዓይነት የቆዳ ቀለም ቢኖረን ወይም ደግሞ በትኛውም አገር የምንኖር ብንሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለሁላችንም እኩል ይሠራል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶቹን ጊዜ የማይሽራቸውንና ‘ፍጹም እምነት የሚጣልባቸውን’ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተመልከት።
11. ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ብዙ ወላጆች ልጆችን መቅጣትን በተመለከተ ምን ብለው እንዲያምኑ ተደርገው ነበር?
11 ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ወላጆች ስለ ልጆች አስተዳደግ በተሰጡት “አዳዲስ ሐሳቦች” በመመራት “ልጆችን መገሰጽ ተገቢ አይደለም” ብለው ያስቡ ነበር። ልጆች በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ ገደብ ማድረግ የልጆችን ስሜት ሊጎዳና ሊያበሳጫቸው ይችላል የሚል ሥጋት ነበራቸው። ስለ ልጆች አስተዳደግ ምክር የሚሰጡ ሊቃውንት፣ ወላጆች ልጆችን በለዘብተኝነት ከማረም የበለጠ ነገር ከማድረግ እንዲታቀቡ ይመክሩ ነበር። አሁን ግን ከእነዚህ ሊቃውንት ብዙዎቹ “ወላጆች ትንሽ ጥብቅ እንዲሆኑና እንደገና መቆጣጠር እንዲጀምሩ እየወተወቱ ነው” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
12. “ዲሲፕሊን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም ትርጉም ምንድን ነው? ልጆችስ እንዲህ ዓይነቱ ዲሲፕሊን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
12 መጽሐፍ ቅዱስ ግን በዚህ ሁሉ ጊዜ በልጆች አስተዳደግ ረገድ ግልጽና ምክንያታዊ የሆነ ምክር ሲሰጥ ቆይቷል። “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና ተግሳጽ [“ዲሲፕሊን፣” NW] አሳድጓቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” በማለት ይመክራል። (ኤፌሶን 6:4) ተግሣጽ ወይም “ዲሲፕሊን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማሳደግ፣ ማሰልጠን፣ መመሪያ መስጠት” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ዓይነቱ ዲሲፕሊን ወይም መመሪያ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 13:24) ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የሚያስችላቸውን ግልጽ የሆነ የሥነ ምግባር መመሪያ ካገኙ በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ። በአግባቡ የተሰጠ ዲሲፕሊን የሚንከባከባቸው ሰው እንዳለ እንዲሰማቸው ከማድረጉም ሌላ ወላጆቻቸው ወደ ፊት ስለሚኖራቸው ስብዕናና ማንነት አጥብቀው እንደሚያስቡ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል።—ከምሳሌ 4:10-13 ጋር አወዳድር።
13. (ሀ) ዲሲፕሊንን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆችን ምን በማለት ያስጠነቅቃል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ዲሲፕሊን እንዲሰጥ ያበረታታል?
13 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ለወላጆች ማስጠንቀቂያም ይሰጣል። የወላጅነት ሥልጣን አላግባብ ሊሠራበት አይገባም። (ምሳሌ 22:15) የትኛውም ልጅ ቢሆን ፈጽሞ ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት ሊሰጠው አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እየተመራ በሚኖር ቤተሰብ ውስጥ ድብደባ ቦታ የለውም። (መዝሙር 11:5) እንደ ሻካራ ቃላት፣ የማያባራ ትችት፣ የቃላት ዱላና የሽሙጥ ንግግር የመሳሰሉት የልጁን ቅስም ሊሰብሩ የሚችሉ በስሜት ላይ የሚፈጸሙ በደሎችም ቦታ የላቸውም። (ከምሳሌ 12:18 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ “ልባቸው እንዳይዝል [ወይም “ልባቸው እንዳይሸፍት፣” ፊሊፕስ ትርጉም] ልጆቻችሁን አታስቆጡአቸው” ሲል በማስጠንቀቅ ለወላጆች ጥበብ የሞላበት ምክር ይሰጣል። (ቆላስይስ 3:21) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የመከላከያ እርምጃዎች መውሰድን ያበረታታል። በዘዳግም 11:19 ላይ ወላጆች ሌሎች ነገሮችን በሚያደርጉባቸው ጊዜያት ሳይቀር በልጆቻቸው ውስጥ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እሴቶችን እንዲቀርጹ ይመክራል። የልጆችን አስተዳደግ በሚመለከት የተሰጠው እንዲህ ዓይነት ግልጽና ምክንያታዊ ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሠራ እንደነበር ሁሉ ለዛሬ ጊዜም ተስማሚ ነው።
14, 15. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ የሞላበት ምክር በመስጠት ብቻ የማይወሰነው በምን መንገድ ነው? (ለ) የተለያየ ዘርና ብሔር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች እርስ በርሳቸው በእኩል ዓይን እንዲተያዩ የሚረዳቸው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ የሞላበት ምክር በመስጠት ብቻ አይወሰንም። መልእክቶቹ ልብ የሚነኩ ናቸው። ዕብራውያን 4:12 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም፣ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ልብን የማነሳሳት ኃይል እንዳለው የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
15 በዛሬው ጊዜ ሰዎች በቀለም፣ በብሔርና በጎሳ ድንበሮች ተከፋፍለዋል። በእነዚህ ሰው ሠራሽ ድንበሮች ምክንያት ንጹሐን ሰዎች በዓለም ዙሪያ በተደረጉ ጦርነቶች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የተለያየ ቀለምና ብሔር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በእኩልነት እንዲተያዩ የሚረዱ ትምህርቶችን አቅፏል። ለምሳሌ ያህል ሥራ 17:26 እግዚአብሔር “የሰውን ወገን ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” ይላል። ይህ ቃል አንድ የሰው ዘር ብቻ እንጂ ብዙ ዘሮች እንደሌሉ ይጠቁማል! ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ 10:34, 35 ላይ ‘ለሰው ፊት አያዳላም፣ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ ነው’ ሲል የገለጸውን አምላክ ‘እንድንመስል’ ያበረታታናል። (ኤፌሶን 5:1፤ ሥራ 10:34, 35) የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ከልባቸው የአኗኗራቸው መመሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ይህ ያገኙት እውቀት በመካከላቸው አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል። ወደ ሰዎች ልብ ጠልቆ በመግባት ሰዎችን የሚከፋፍሉትን ሰው ሠራሽ አጥሮች ያፈርሳል። ታዲያ ይህ ትምህርት በዚህ ዘመን ሊሠራ ይችላልን?
16. የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር እንዳላቸው የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ተናገር።
16 አዎን፣ በእርግጥ ይሠራል! የይሖዋ ምሥክሮች ከአሁን ቀደም በመካከላቸው ሰላም ያልነበራቸውንና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች አንድ ሊያደርግ በቻለው ዓለም አቀፍ ወንድማማችነታቸው የታወቁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በሩዋንዳ በነበረው የጎሳ ግጭት ወቅት በሁለቱም ጎሳዎች ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው በሌላው ጎሳ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን አድነዋል። በአንድ አጋጣሚ የሁቱ ተወላጅ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤቱ ውስጥ በእርሱ ጉባኤ የሚገኝ ስድስት አባላት ያሉት አንድ የቱትሲ ቤተሰብ ደብቆ ነበር። የሚያሳዝነው ይህ የቱትሲ ቤተሰብ ተገኘና ሁሉም ተገደሉ። ሁቱው ወንድምና ቤተሰቡ የገዳዮቹ ቁጣ ስለነደደባቸው አገራቸውን ጥለው ወደ ታንዛንያ ለመሰደድ ተገደዋል። ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ሪፖርት ተደርገዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነት አንድነት ሊኖር የቻለው ልብን የሚያነሳሳው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ልባቸውን በጥልቅ ስለነካው እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ሰዎችን አንድ ሊያደርግ መቻሉ ራሱ ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ ለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ ነው።
የእውነተኛ ትንቢት መጽሐፍ
17. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሰው ፈጠራ ከሆኑ ትንበያዎች የሚለዩት እንዴት ነው?
17 ሁለተኛ ጴጥሮስ 1:20 [NW] “በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያለው ትንቢት ሰዎች ከግል ግንዛቤያቸው ተነስተው ያሰፈሩት ነገር አይደለም” ይላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያሉትን ሁኔታዎች አዝማሚያ ዓይተው ለእነዚህ ሁኔታዎች የራሳቸውን ትርጓሜ በመስጠት የወደፊቱን ሁኔታ ለመገመት የሞከሩ ሰዎች አይደሉም። ከዚህም በተጨማሪ የሚናገሩት ወደፊት ከሚፈጸሙ ሁኔታዎች ጋር በግድ እንዲስማሙ የሚደረጉ የተድበሰበሱ ትንበያዎችን አልነበረም። እስቲ አሁን እጅግ ግልጽ የነበረና በጊዜው የነበሩት ሰዎች ይጠብቁት ከነበረው ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ነገር እንደሚፈጸም የሚገልጽ አንድ ትንቢት እንመልከት።
18. የጥንቷ ባቢሎን ነዋሪዎች ተረጋግተው እንዲኖሩ ያደረጋቸው ነገር ምን ነበር? ይሁንና ኢሳይያስ ባቢሎንን በሚመለከት ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር?
18 በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ባቢሎን ፈጽሞ ልትደፈር የማትችል የምትመስል የባቢሎን አጼያዊ ግዛት ዋና ከተማ ሆና ነበር። ከተማዋ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የተገነባች ስትሆን ይህ ወንዝ ከተማዋን ከጠላት ወረራ ለመከላከል የሚያገለግል ሰፊና ጥልቅ የሆነ የውኃ ጉድጓድ በከተማዋ ዙሪያ እንዲኖር ከማገልገሉም በላይ በበርካታ ቦዮች ተከፋፍሎ እንዲፈስ ተደርጎ ነበር። በተጨማሪም ከተማዋ በጣም ግዙፍ የሆነ ድርብ የግንብ አጥር ነበራት። የባቢሎን ከተማ ነዋሪዎች ምንም ነገር አይደርስብንም ብለው ተረጋግተው መኖራቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ይሁንና በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የባቢሎን ክብር ታላቅ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው፣ . . . ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች። ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፣ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም፤ ዓረባውያንም ድንኳንን በዚያ አይተክሉም፣ እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም።” (ኢሳይያስ 13:19, 20) ትንቢቱ ባቢሎን እንደምትጠፋ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ሰው የማይኖርባት ምድር እንደምትሆን መናገሩን ልብ በሉ። እንዲህ ያለ ትንቢት ለመናገር ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል! ኢሳይያስ ይህን ትንቢት የጻፈው ባቢሎን ባድማ መሆኗን ከተመለከተ በኋላ ሊሆን ይችላልን? ታሪክ አይደለም የሚል መልስ ይሰጣል!
19. የኢሳይያስ ትንቢት ጥቅምት 5 ቀን 539 ከዘአበ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያላገኘው ለምንድን ነው?
19 ጥቅምት 5 ቀን 539 ከዘአበ ምሽት ላይ ባቢሎን በታላቁ ቂሮስ ይመራ በነበረው በሜዶ ፋርስ ሠራዊት እጅ ወደቀች። የኢሳይያስ ትንቢት ግን ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኘው በዚህ ጊዜ አልነበረም። ባቢሎን በቂሮስ እጅ ከወደቀች በኋላ የቀድሞ ታላቅነቷን ብታጣም ለበርካታ መቶ ዘመናት ሰው የሚኖርባት ከተማ ነበረች። በሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል በተገለበጠበት ጊዜ ማለትም በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ገደማ ፓርታውያን ባቢሎንን በግዛታቸው ሥር አስገቧት። ባቢሎን በዚህ ጊዜ በዙሪያዋ ያሉ መንግሥታት ለየራሳቸው ሊያደርጓት የሚሻሙባት አገር ሆና ነበር። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው” አይሁዳውያን በባቢሎን ይኖሩ እንደነበር ዘግቧል። ዘ ካምብሪጅ ኤንሸንት ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ የፓልሚራ ነጋዴዎች በ24 እዘአ በባቢሎን ውስጥ የደራ የንግድ ቦታ አግኝተው እንደነበረ ዘግቧል። በመሆኑም እስከ አንደኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ ባቢሎን ጨርሳ ባድማ አልሆነችም ነበር፤ ይሁንና የኢሳይያስ መጽሐፍ ተጽፎ የተጠናቀቀው ከዚህ ጊዜ እጅግ ቀደም ብሎ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:13
20. ባቢሎን በመጨረሻው “የድንጋይ ክምር” መሆኗን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
20 ባቢሎን ሰው የማይኖርባት ባድማ ስትሆን ኢሳይያስ በሕይወት አልነበረም። ይሁን እንጂ በትንቢቱ ፍጻሜ መሠረት “የድንጋይ ክምር” ሆናለች። (ኤርምያስ 51:37) የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር በሆነው በጄሮም (በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ የተወለደ ነው) ዘመን ባቢሎን “የተለያዩ” ዓይነት አራዊት የሚፈነጩባት የአደን ምድር ሆና የነበረ ሲሆን እስከ ዛሬም ድረስ ባድማ ሆና ቀርታለች። ባቢሎን ተመልሳ ብትቋቋም ቱሪስቶች የሚጎርፉባት ቦታ ትሆን ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው ‘ዘርና ትውልድ’ ለዘላለም ጠፍቷል።—ኢሳይያስ 14:22
21. የታመኑ ነቢያት የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት ፍጹም ትክከል የሆነ ትንቢት ሊናገሩ የቻሉት እንዴት ነው?
21 ነቢዩ ኢሳይያስ ግምታዊ ሐሳብ አልሰነዘረም። ወይም ደግሞ ትንቢት ለማስመሰል ሲል የተፈጸመ ታሪክ በድጋሚ አልጻፈም። ኢሳይያስም ሆነ ሌሎቹ የታመኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት እውነተኛ ነቢያት ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ማንም ሰው የሌለውን ወደፊት የሚሆነውን ነገር በትክክል የመናገር ችሎታ ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው? መልሱ ግልጽ ነው። ትንቢቶቹ የፈለቁት ‘ከመጀመሪያ መጨረሻውን ከሚናገረው’ እና የትንቢት አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ነበር።—ኢሳይያስ 46:10
22. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ራሳቸው እንዲመረምሩ ለማበረታታት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ለምንድን ነው?
22 ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሊመረመር የሚገባው መጽሐፍ ነው? አዎን፣ ልንመረምረው የሚገባ መጽሐፍ እንደሆነ አውቀናል! ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለውን አሳማኝ ማስረጃ ሊያገኙ አልቻሉም። መጽሐፍ ቅዱስን ጨርሶ አንብበው የማያውቁ ቢሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የግላቸውን አስተያየት ይሰጣሉ። በመጀመሪያው ርዕስ መግቢያ ላይ ተጠቅሰው የነበሩትን ፕሮፌሰር አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማምተው መጽሐፉን በጥንቃቄ ከመረመሩ በኋላ በእርግጥም የአምላክ ቃል ነው ወደሚል መደምደሚያ ደረሱ። ከጊዜ በኋላ ተጠመቁና የይሖዋ ምሥክር ሆኑ። ዛሬ እኚህ ፕሮፌሰር ሽማግሌ ሆነው ያገለግላሉ! ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩና ከዚያ በኋላ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ እናበረታታ። ሌሎች የሚሉትን ከመስማት አልፈው ራሳቸው ቢመረምሩት ይህ በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ መጽሐፍ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ መሆኑን እንደሚገነዘቡ እርግጠኞች ነን!
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ የሥራ ውጤት እንዳልሆነ ለማሳየት የሙሴን ሕግ በማስረጃነት መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጊዜ የማይሽራቸውና ለዘመናዊው ኑሮ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ምን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይገኛሉ?
◻ በኢሳይያስ 13:19, 20 ላይ የሚገኘው ትንቢት ከታሪኩ ፍጻሜ በኋላ የተጻፈ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
◻ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ልናበረታታቸው ይገባል? ለምንስ?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሳይንስ ሊረጋገጥ የማይችለውስ ሐሳብ?
መጽሐፍ ቅዱስ በተናጠል ሳይንሳዊ ማስረጃ የማይገኝላቸው አንዳንድ ሐሳቦችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚኖሩበት በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ ዓለም ስለመኖሩ የሚናገረው ቃል ሳይንሳዊ ማስረጃ ሊገኝለትም ሆነ እውነት አይደለም የሚል ማስረጃ ሊቀርብበት አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የመሰሉ በተናጠል ተጨባጭ ማስረጃ የማይገኝላቸው ሐሳቦች መቀመጣቸው መጽሐፉ ከሳይንሳዊ ሐቅ የራቀ ነው የሚያሰኝ ነውን?
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመሩ አንድ የፕላኔቶች ከርስ ተመራማሪ ፊት የተጋረጠው ጥያቄ ይህ ነበር። “አንዳንዶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ አባባሎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ ስላልቻልኩ መጀመሪያ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን አምኜ ለመቀበል ተቸግሬ እንደነበር አልክድም” በማለት ያስታውሳሉ። እኚህ ቅን ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን ቀጠሉና ያሉት ማስረጃዎች ራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን በግልጽ እንደሚያሳዩ አምነው ተቀበሉ። እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ይህ ነገር ለእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል በተናጠል ሳይንሳዊ ማስረጃ ሊገኝለት ይገባል የሚለውን ጉጉት ቀንሶልኛል። ሳይንሳዊ ዝንባሌ ያለው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሳዊ ነገሮች ዓይን ለመመርመር ፈቃደኛ መሆን አለበት፤ አለዚያ ግን እውነትን ፈጽሞ ሊቀበል አይችልም። ሳይንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን ሐሳብ በማስረጃ ያረጋግጥልናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ሐሳቦች ተጨባጭ ሳይንሳዊ ማስረጃ ስላልተገኘላቸው ብቻ ስህተት ናቸው ማለት አይደለም። ዋናው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ሊገኝላቸው በሚችልባቸው ሐሳቦቹ ረገድ ሁልጊዜ ትክክለኛ ሆኖ መገኘቱ ነው።”
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ ከዘመኑ ጥበብ እጅግ የመጠቁ የንጽሕና ሕጎችን መዝግቧል