-
በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግተህና ተማምነህ ኑርወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
-
-
“ፍቅርን ልበሱት”
9. ይሖዋ ፍቅር በማሳየት ረገድ አርዓያ የሆነን እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ “የፍጻሜ ማሠሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት” ሲል ጽፏል። (ቆላስይስ 3:14) ይሖዋ በታላቅ ቸርነቱ ይህን ልብስ አዘጋጅቶልናል። እንዴት? ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳየት የሚችሉት ፍቅር ከይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች አንዱ ስለሆነ ነው። እነዚህን ፍሬዎች የሚሰጠው አምላክ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) ይሖዋ ራሱ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል አንድያ ልጁን በመላክ ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ ታላቅ ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐንስ 3:16) ይህ ታላቅ የሆነ የፍቅር መግለጫ ይህን ባሕርይ እንድናሳይ አብነት ይሆነናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል” ሲል ጽፏል።— 1 ዮሐንስ 4:11
10. ‘ከመላው የወንድማማች ማኅበር’ የምንጠቀመው እንዴት ነው?
10 በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ፍቅር ለማሳየት ግሩም አጋጣሚ ይሰጥሃል። በእነዚህ ስብሰባዎች የተለያዩ ሰዎችን ታገኛለህ። ብዙዎቹን ወዲያው እንደምትወዳቸው አያጠራጥርም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋን በሚያገለግሉ ሰዎች መካከል እንኳን የጠባይ ልዩነት ይኖራል። ከዚህ በፊት በጠባይ ወይም በፍላጎት የማይመስልህን ሰው ስትርቅ ኖረህ ይሆናል። ክርስቲያኖች ግን “መላውን የወንድማማች ማኅበር” መውደድ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት) ስለዚህ በመንግሥት አዳራሹ ከሚሰበሰቡት ሁሉ ጋር፣ ከአንተ ጋር በዕድሜ፣ በባሕርይ፣ በዘር ወይም በትምህርት ደረጃ ከሚለዩት ግለሰቦች ጭምር ለመተዋወቅ ዓላማህ ይሁን። ሁሉም የሚወደዱባቸው የየራሳቸው ጠባይ ያላቸው ሆነው ታገኛቸዋለህ።
11. በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ልዩ ልዩ ባሕርይ ማየትህ ቅር ሊያሰኝህ የማይገባው ለምንድን ነው?
11 በጉባኤው ውስጥ ያሉት ሰዎች በጠባያቸው የተለያዩ መሆናቸው ሊረብሽህ አይገባም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በአንድ አውራ መንገድ ላይ መኪና እየነዳህ ስትሄድ ከአንተ ጋር የሚጓዙ በርካታ ተሽከርካሪዎች አሉ እንበል። ሁሉም ተሽከርካሪዎች በአንድ ዓይነት ፍጥነት አይጓዙም፤ የሁሉም ይዞታ አንድ ዓይነት አይደለም። አንዳንዶቹ መኪኖች ብዙ ኪሎ ሜትር የሄዱ ሲሆን ሌሎቹ ግን አንተ እንደምትነዳው ተሽከርካሪ ብዙ ያልሠሩ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም ይህን የመሰለ ልዩነት ቢኖራቸውም በመንገዱ ላይ ይሽከረከራሉ። የአንድ ጉባኤ አባላት የሆኑ ግለሰቦችም እንዲሁ ናቸው። ሁሉም በአንድ ዓይነት ፍጥነት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አያዳብሩም። ከዚህም በላይ የሁሉም አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሁኔታ አንድ ዓይነት አይደለም። አንዳንዶች ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ሲያመልኩ የቆዩ ሲሆኑ አንዳንዶቹ በቅርቡ የጀመሩ ናቸው። ሆኖም ሁሉም “በአንድ ልብና በአንድ አሳብ” ተባብረው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና በመጓዝ ላይ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ስለዚህ የጉባኤውን አባሎች ደካማ ጎኖች ሳይሆን ጠንካራ ጎናቸውን ተመልከት። እንዲህ ብታደርግ አምላክ በእርግጥ ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር እንደሆነ ስለምትገነዘብ ልብህ በደስታ ይሞላል። አንተም እንደነዚህ ካሉት ሕዝቦች አንዱ ለመሆን እንደምትፈልግ አያጠራጥርም።— 1 ቆሮንቶስ 14:25
12, 13. (ሀ) በጉባኤው ውስጥ ያለ ሰው ቢጎዳህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? (ለ) ቂም አለመያዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 የሰው ልጆች በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸው ስለሆኑ በጉባኤው ውስጥ ያለ ግለሰብ ቅር የሚልህ ነገር ሊናገር ወይም ሊያደርግ ይችላል። (ሮሜ 3:23) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው” በማለት ያለውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። (ያዕቆብ 3:2) አንድ ሰው ቅር ቢያሰኝህ ምን ይሰማሃል? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የሰው አስተዋይነት ቁጣውን ያዘገይለታል፣ በደልንም ማለፍ ውበት ይሆንለታል” ይላል። (ምሳሌ 19:11 አዓት) አስተዋይነት ሲባል ላይ ላዩን ከሚታየው አልፎ ውስጣዊ ሁኔታውን ማየት፣ አንድ ሰው አንድን ነገር ለመናገር ወይም ለማድረግ ምክንያት የሆነውን ነገር መረዳት ማለት ነው። አብዛኞቻችን ራሳችን ለሠራነው ስህተት ማሳበቢያ በማግኘት ረገድ በጣም አስተዋዮች ነን። ታዲያ ይህንኑ አስተዋይነታችንን ለምን የሌሎችን ጉድለት ለመረዳትና ለማለፍ አንጠቀምበትም?— ማቴዎስ 7:1–5፤ ቆላስይስ 3:13
13 ይሖዋ ይቅር እንዲለን ከፈለግን እኛም ሌሎችን ይቅር ማለት እንደሚኖርብን ፈጽሞ መዘንጋት የለብህም። (ማቴዎስ 6:9, 12, 14, 15) በእውነት የምንመላለስ ሰዎች ከሆንን ሌሎች ሰዎችን በፍቅር እንይዛቸዋለን። (1 ዮሐንስ 1:6, 7፤ 3:14–16፤ 4:20, 21) ስለዚህ በጉባኤው ውስጥ ከሚገኝ አንድ ግለሰብ ጋር ብትጋጭ ይህን ግለሰብ እንድትቀየም የሚገፋፋህን ዝንባሌ ታግለህ አሸንፈው። ፍቅርን ከለበስክ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ትጥራለህ። ቅር ያሰኘኸው አንተ ከሆንክም ይቅርታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትልም።— ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15–17
14. ምን ዓይነት ባሕርያት መልበስ ይኖርብናል?
14 መንፈሳዊ ልብሳችን ከፍቅር ጋር የቅርብ ተዛምዶ ያላቸውን ሌሎች ባሕርያት የሚጨምር መሆን አለበት። ጳውሎስ “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” ሲል ጽፏል። እነዚህ በፍቅር ውስጥ የሚካተቱ ባሕርያት አምላካዊ አቋም የሚያንጸባርቀው ‘አዲስ ሰውነት’ ክፍል ናቸው። (ቆላስይስ 3:10, 12) ይህን ልብስ ለመልበስ ጥረት ታደርጋለህን? በተለይ ወንድማዊ ፍቅርን ከለበስክ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መለያ ምልክት የሆነው ባሕርይ ይኖርሃል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።— ዮሐንስ 13:35
-
-
በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግተህና ተማምነህ ኑርወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
-
-
[በገጽ 165 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
-