የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 51—ቈላስይስ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሮም
ተጽፎ ያለቀው:- ከ60–61 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ሁለት ሰዎች ከኤፌሶን ተነስተው በትንሿ እስያ በኩል አድርገው በሚያንደር (ሜንደረስ) ወንዝ አኳያ ወደ ምሥራቅ ተጓዙ። በፍርግያ በሚገኝ ሊከስ እየተባለ የሚጠራ ገባር ወንዝ ጋ ሲደርሱ በተራራ በተከበበው ሸለቆ ውስጥ አድርገው ወንዙን ተከትለው ሽቅብ ወደ ደቡብ ምሥራቅ አቀኑ። ከፊት ለፊታቸው ማራኪ የሆነ በጣም ብዙ የበግ መንጋ የተሰማራበት አረንጓዴ የግጦሽ መስክ ይታያል። (የሱፍ ምርት ለአካባቢው ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነበር።a) እነዚህ መንገደኞች በሸለቆው ውስጥ ሲጓዙ የበለጸገችውንና ለአውራጃው የሮማውያን የአስተዳደር ማዕከል የሆነችውን የሎዶቅያን ከተማ በስተቀኛቸው አልፈው ሄዱ። በስተግራቸው ደግሞ ከወንዙ ባሻገር በቤተ መቅደሶቿና በፍል ውኃዎቿ የታወቀችውን የኢያራ ከተማን መመልከት ይችሉ ነበር። በእነዚህ ሁለት ከተሞችና በሸለቆው የላይኛው ክፍል 16 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በትንሿ የቈላስይስ መንደር የክርስቲያን ጉባኤዎች ነበሩ።
2 እነዚህ ሰዎች የሚጓዙት ወደ ቈላስይስ ነበር። ሁለቱም ክርስቲያኖች ናቸው። ቢያንስ ከሁለቱ አንዱ የቈላስይስ ተወላጅ በመሆኑ አካባቢውን በደንብ ያውቀዋል። ይህ ሰው አናሲሞስ ሲሆን በዚያ የሚገኘው ጉባኤ አባል ወደ ሆነው ጌታው በመመለስ ላይ ነበር። የአናሲሞስ ጓደኛ ነፃ ሰው የነበረው ቲኪቆስ ሲሆን ሁለቱም ሐዋርያው ጳውሎስ “በቈላስይስ ለሚኖሩ፣ በክርስቶስ ለሆኑ . . . ታማኝ ወንድሞች” የላከውን ደብዳቤ የሚያደርሱ መልእክተኞች ነበሩ። እስከምናውቀው ድረስ ጳውሎስ ቈላስይስን ጎብኝቶ አያውቅም። በአብዛኛው አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች የሚገኙበትን የቈላስይስን ጉባኤ የመሠረተው ኤጳፍራ ሳይሆን አይቀርም። ኤጳፍራ በመካከላቸው ያገለገለ ሲሆን አሁን ደግሞ ከጳውሎስ ጋር በሮም ይገኛል።—ቈላ. 1:2, 7፤ 4:12
3 ሐዋርያው ጳውሎስ በመግቢያውና በመደምደሚያው ላይ እንደገለጸው የደብዳቤው ጸሐፊ እሱ ራሱ ነው። (1:1፤ 4:18) በተጨማሪም በመደምደሚያው ላይ ካሰፈረው ሐሳብ ለመረዳት እንደሚቻለው ደብዳቤውን የጻፈው በእስር ቤት ሆኖ ነው። ይህም ከ59-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበትና በርካታ የማበረታቻ ደብዳቤዎችን በጻፈበት ወቅት መሆን አለበት። ለቈላስይስ ሰዎችና ለፊልሞና የተጻፉት ደብዳቤዎች የተላኩት አንድ ላይ ነው። (ቈላ. 4:7-9፤ ፊልሞና 10, 23) ለቈላስይስ ሰዎች በተጻፈው ደብዳቤ ላይ የሰፈሩት ሐሳቦችና ሐረጎች ለኤፌሶን ሰዎች ከተላከው ደብዳቤ ጋር ተመሳሳይነት ስላላቸው ሁለቱም የተጻፉት በአንድ ወቅት ሳይሆን አይቀርም።
4 ለቈላስይስ ሰዎች የተላከውን ደብዳቤ ትክክለኛነት ለመጠራጠር የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለም። በ200 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በተጻፈው በቼስተር ቢቲ ፓፒረስ ቁ. 2 (P46) ከሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች ጋር አንድ ላይ መገኘቱ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ከጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ያምኑ እንደነበር ያሳያል። የሌሎቹን የጳውሎስ ደብዳቤዎች ትክክለኛነት ያረጋገጡት እነዚያው ቀደምት ማስረጃዎች ስለዚህ ደብዳቤ ትክክለኛነትም መሥክረዋል።
5 ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች ደብዳቤ እንዲጽፍ የገፋፋው ምን ነበር? አንደኛ ነገር፣ አናሲሞስ ወደ ቈላስይስ ተመልሶ ሊሄድ ነበር። ከጳውሎስ ጋር በቅርቡ የተገናኘው ኤጳፍራ በቈላስይስ ስላለው ሁኔታ የሰጠው አንዳንድ መረጃ ደብዳቤውን ለመጻፍ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነው አያጠራጥርም። (ቈላ. 1:7, 8፤ 4:12) በዚያ የሚገኘውን የክርስቲያን ጉባኤ ስጋት ላይ የጣለ አንድ አደገኛ ሁኔታ ነበር። በጊዜው የነበሩት ሃይማኖቶች በመፈራረስ ላይ የነበሩ ሲሆን ከአሮጌዎቹ ሃይማኖቶች አንዳንድ ሐሳቦችን ወስዶ በማቀላቀል አዳዲስ ሃይማኖቶች ይፈለሰፉ ነበር። መናፍስታዊ ድርጊቶችንና ከጣዖት አምልኮ ጋር የተያያዙ አጉል እምነቶችን ያቀፈው አረማዊ ፍልስፍና ከምግብ መታቀብንና አንዳንድ ቀናትን ማክበርን ከሚያዘው የአይሁዳውያን ትምህርት ጋር ተዳምሮ በአንዳንድ የጉባኤ አባላት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር አልቀረም። ችግሩ ምንም ይሁን ምን ኤጳፍራ ከጳውሎስ ጋር ለመገናኘት ያንን የሚያህል ረዥም መንገድ የተጓዘው በቂ ምክንያት ኖሮት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ኤጳፍራ ስለ ፍቅራቸውና ስለ ጽኑ አቋማቸው ያቀረበው የሚያበረታታ ሪፖርት፣ ጉባኤው በአጠቃላይ ሲታይ ጊዜ በማይሰጥ ችግር ላይ እንዳልነበረ ያሳያል። ጳውሎስ ሪፖርቱን ካዳመጠ በኋላ ይህን ደብዳቤ ለቈላስይስ ሰዎች በመጻፍ ለትክክለኛው እውቀትና ለንጹሕ አምልኮ ጠንካራ የሆነ የመከላከያ ሐሳብ አቅርቧል። ከአረማዊ ፍልስፍና፣ ከመላእክት አምልኮና ከአይሁድ ባሕል ጋር ሲወዳደር አምላክ ለክርስቶስ የሰጠው ቦታ ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
12 እነዚህ ሁለት ወንድሞች ከሮም የመምጣታቸው ዜና በቈላስይስ ወንድሞች ዘንድ እንዴት በአንዴ ሊዳረስ እንደሚችል መገመት እንችላለን። ዜናውን የሰሙት ክርስቲያኖች የጳውሎስ ደብዳቤ ምን እንደሚል ለመስማት በከፍተኛ ጉጉት (በፊልሞና ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም) አንድ ላይ ይሰባሰባሉ። (ፊልሞና 2) ክርስቶስ ስላለው ትክክለኛ ቦታና ስለ ትክክለኛ እውቀት አስፈላጊነት በደብዳቤው ውስጥ የሰፈሩት እውነቶች ምንኛ ማራኪ ናቸው! ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችና የአይሁዳውያን ልማዶች ሊኖራቸው የሚገባው ቦታ በግልጽ የተቀመጠ ከመሆኑም ሌላ ለሰላምና ለክርስቶስ ቃል ጉልህ ስፍራ ተሰጥቷቸዋል። በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ማለትም ለበላይ ተመልካቾች፣ ለባሎች፣ ለሚስቶች፣ ለአባቶች፣ ለልጆች፣ ለጌቶችና ለባሮች አእምሮንና ልብን የሚያድስ መንፈሳዊ ምግብ ቀርቦላቸዋል። ደብዳቤው፣ በድጋሚ ጌታና ባሪያ ሆነው ለሚኖሩት ለፊልሞናና ለአናሲሞስ የሚሆን ጠቃሚ ምክር እንደያዘ ምንም ጥርጥር የለውም። ለበላይ ተመልካቾች መንጋውን ወደ ትክክለኛው መሠረተ ትምህርት መመለስን በተመለከተ እጅግ ግሩም መመሪያ ተሰጥቷል። የጳውሎስ ቃላት የቈላስይስ ሰዎች ለይሖዋ ሲሉ በሙሉ ነፍስ የመሥራትን መብት እንዲያደንቁ ጥሩ ማበረታቻ ሰጥተዋቸዋል። እንዲሁም ለባርነት ከሚዳርጉ አስተሳሰቦችና ከዓለማዊ ልማዶች ነፃ ስለመውጣት ለቈላስይስ ሰዎች የተሰጠው ገንቢ ምክር በጊዜያችን ላሉ ጉባኤዎችም ሕያው መልእክት ይዟል።—ቈላ. 1:9-11, 17, 18፤ 2:8፤ 3:15, 16, 18-25፤ 4:1
13 ለክርስቲያን አገልጋዮች የሚሆን ግሩም ምክር በቈላስይስ 4:6 ላይ ተዘግቦ ይገኛል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን።” በጸጋ የተሞሉ የእውነት ቃላት ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች የሚማርኩ ሲሆኑ ዘላቂ ጥቅምም ያስገኙላቸዋል። በተጨማሪም የአንድ ክርስቲያን ትጋት የተሞላበትና ከአድናቆት የመነጨ ጸሎት የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። “ከማመስገን ጋር ነቅታችሁ በትጋት ጸልዩ።” እንዲሁም በክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረት መሃል መገኘት ምንኛ የሚያስደስትና መንፈስን የሚያረካ ነው! ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ . . . በልባችሁ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] ዘምሩ” ብሏል። (4:2፤ 3:16) የቈላስይስን መልእክት ስትመረምር እንደ ዕንቁ የሆኑ አስተማማኝና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎችን ልታገኝ ትችላለህ።
14 ደብዳቤው የሙሴን ሕግ መጠበቅን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።” (2:17) ይህ እውነታ ለቈላስይስ ሰዎች በተላከው ደብዳቤ ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ደብዳቤው ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው ሰዎች ስለተዘጋጀላቸው ክብራማ ሰማያዊ ተስፋ ደጋግሞ ይገልጻል። (1:5, 27፤ 3:4) እነዚህ ሰዎች አብ ከጨለማው ባለ ሥልጣን ነፃ አውጥቶ “ወደሚወደው ልጁ መንግሥት” ስላስገባቸው እጅግ አመስጋኞች ናቸው። በዚህ መንገድ ‘ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ለሆነውና ለማይታየው አምላክ አምሳል’ ተገዥዎች ሆነዋል። ምክንያቱም ‘ሁሉ ነገር በእሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእሱና ለእሱ ተፈጥሯል።’ ይህ ልጅ በአምላክ መንግሥት ላይ በጽድቅ የመግዛት ብቃት አለው። በመሆኑም ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል።—1:12-16፤ 3:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘ ኒው ዌስትሚንስትር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል፣ 1970 ገጽ 181