የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 5/15 ገጽ 24-27
  • መንፈሳዊ እድገት ልታደርግ ትችላለህ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መንፈሳዊ እድገት ልታደርግ ትችላለህ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ አገልጋዮቹን ያበረታል
  • ‘አሮጌውን ሰው ገፋችሁ ጣሉት’
  • በውስጣችን እንዳለ “እሳት”
  • በብረት የተሳሉ ያህል
  • መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚያነሳሳ ጥሩ ምክንያት
  • የይሖዋን ምድራዊ ድርጅት ታደንቃለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ወጣቶች—ከተጠመቃችሁ በኋላ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 5/15 ገጽ 24-27

መንፈሳዊ እድገት ልታደርግ ትችላለህ

የአንድን ነገር ዋጋማነት መገንዘብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ አልማዞችን መጥቀስ ይቻላል። የተጠረገ አልማዝ በጣም የሚያንጸባርቅ ቢሆንም እንኳ ያልተጠረገ አልማዝ የሚሰጠው ነጸብራቅ ደብዛዛ ነው። ሆኖም ያልተጠረገውም አልማዝ ቢሆን ውብ ፈርጥ ሊወጣው እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም።

ክርስቲያኖች ካልተጠረገ አልማዝ ጋር የሚመሰሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ከፍጽምና ብዙ የራ​ቅን ብንሆንም በይሖዋ ዘንድ የላቀ ግምት የሚሰጠው የተሰወረ ውድ ነገር አለን። ልክ እንደ አልማዝ ሁላችንም የራሳችን የሆነ ልዩ ባሕርይ አለን። እንዲሁም እያንዳንዳችን ልባዊ ፍላጎት ካለን መንፈሳዊ እድገት ልናደርግ እንችላለን። ያሉን ባሕርያት ተጠርገው ይበልጥ በማብራት ለይሖዋ ክብር ሊያመጡ ይችላሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​31

አንድ አልማዝ ከተቆረጠና ከተጠረገ በኋላ የአቀማመጡ ሁኔታና የተቀመጠበት ቦታ ይበልጥ እንዲያብረቀርቅ ያደርገዋል። በተመሳሳይም እኛ “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” ከለበስን ይሖዋ በተለያየ መልክ ወይም የሥራ ምድብ ሊጠቀምብን ይችላል።​—⁠ኤፌሶን 4:​20-24

አልማዝ ብዙውን ጊዜ እንደ እንቁ እንደሚያብረቀርቅ ሁሉ እንዲህ ያለው መንፈሳዊ እድገትም እንዲሁ በተፈጥሮ የሚገኝ ነገር አይደለም። አብረውን የቆዩ አንዳንድ ድክመቶችን ልናስወግድና ኃላፊነትን ስለመቀበል ያለንን አመለካከት ልናስተካክል ወይም ምንም መንፈሳዊ እድገት የማናደርግ እንዳንሆን ትግል ልናደርግ ይገባል። ይሖዋ አምላክ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ሊሰጠን ስለሚችል ፍላጎቱ ካለን እድገት ልናደርግ እንችላለን።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7 NW፤ ፊልጵስዩስ 4:​13

ይሖዋ አገልጋዮቹን ያበረታል

አብዛኛውን ጊዜ ካልተጠረገ አልማዝ የተወሰነ ክፍል አንድ ጊዜ ከተቆረጠ ምንም ማድረግ ስለማይቻል አንድ ሰው አልማዝ የሚቆርጠው በችሎታው ሙሉ በሙሉ ተማምኖ መሆን ይኖርበታል፤ ይህ ደግሞ ትክክለኛ እውቀት ይጠይቃል። ተፈላጊውን ቅርጽ ለማግኘት ሲባል ከፍተኛ ዋጋ ያለው፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ 50 በመቶ የሚሆነው የድንጋዩ ክፍል ይቆረጣል። እኛም የግል ባሕርያችንን ቅርጽ ለማስያዝና በመንፈሳዊ ለማደግ ከትክክለኛ እውቀት የሚመነጭ የመተማመን ስሜት ያስፈልገናል። በተለይ ደግሞ ይሖዋ ኃይል እንደሚሰጥን ሙሉ በሙሉ መተማመን ይኖርብናል።

ይሁን እንጂ ብቃቱ እንደሌለን ወይም የበለጠ መሥራት እንደማንችል ሆኖ ይሰማን ይሆናል። ባለፉት ዘመናት ይኖሩ የነበሩ የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ዓይነት ስሜት የተሰማቸው ጊዜ ነበር። (ዘጸአት 3:​11, 12፤ 1 ነገሥት 19:​1-4) ኤርምያስ ‘ለአሕዛብ ነቢይ’ እንዲሆን በአምላክ በተመረጠ ጊዜ እኔ ‘ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም’ ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 1:​5, 6) ምንም እንኳ ኤርምያስ ለመናገር አቅማምቶ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን በጥላቻ ለተሞሉ ሕዝቦች እንዲያደርስ የተሰጠውን ቀጥተኛ መልእክት በድፍረት የሚናገር ነቢይ ሆኗል። እንዲህ ለማድረግ የቻለው እንዴት ነው? በይሖዋ መታመንን ተምሮ ነበር። ኤርምያስ በኋላ ላይ “በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው” ሲል ጽፏል።​—⁠ኤርምያስ 17:​7፤ 20:​11

ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ብርታትን ይሰጣል። የአራት ልጆች አባት የሆነውና መንፈሳዊ እድገቱ አዝጋሚ የነበረው ኤድዋርድa ይህን እውነት ሆኖ አግኝቶታል። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ለዘጠኝ ዓመታት ያህል የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ብኖርም በመንፈሳዊ ግን ምንም እድገት አላደረግሁም። ችግሩ የሚገፋፋኝ ነገር አለመኖሩና ትምክህት ማጣት ነበር። ወደ ስፔይን ስዛወር ግን የምሰበሰብበት ጉባኤ አንድ ሽማግሌና አንድ የጉባኤ አገልጋይ ብቻ ነበሩት። የአገልጋዮች እጥረት በመኖሩ ሽማግሌው ብዙ ሥራዎችን እንድሠራ ጠየቀኝ። የመጀመሪያዎቹን ንግግሮቼንና የስብሰባ ክፍሎቼን ሳቀርብ እንቀጠቀጥ ነበር። ሆኖም በይሖዋ ላይ መደገፍን ተማርኩ። ሽማግሌው ሁልጊዜ ያመሰግነኝ ነበር፤ እንዲሁም የማሻሽላቸውን ነገሮች በዘዴ ይነግረኝ ነበር።

“በመስክ አገልግሎት ላይ ያለኝን እንቅስቃሴም ከፍ አደረግሁ፤ እንዲሁም በመንፈሳዊነት ረገድ ለቤተሰቤ ጥሩ ምሳሌ ሆንኩ። በውጤቱም እውነት ለመላው ቤተሰቤ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኗል። እኔም ከምንጊዜውም የበለጠ እርካታ ማግኘት ችያለሁ። አሁን የጉባኤ አገልጋይ ስሆን ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስችሉኝን ባሕርያት ለማዳበር ጠንክሬ በመሥራት ላይ እገኛለሁ።”

‘አሮጌውን ሰው ገፋችሁ ጣሉት’

ኤድዋርድ እንደተገነዘበው መንፈሳዊ እድገት ማድረግ በይሖዋ መታመንን ይጠይቃል። የክርስቶስን ዓይነት ‘አዲስ ስብዕና’ ማዳበርም አስፈላጊ ነው። ይህን እንዴት ማድረግ ይቻላል? ተቀዳሚው እርምጃ የአሮጌው ሰው ክፍል የሆኑ ባሕርያትን ‘ገፍፎ መጣል’ ነው። (ቆላስይስ 3:​9, 10) አንድን ያልተወለወለ አልማዝ የሚያብረቀርቅ ፈርጥ ለማድረግ ባዕድ ንጥረ ነገሮችን ከላዩ ላይ ፍቆ ማንሣት እንደሚያስፈልግ ሁሉ አዲሱ ስብዕናችን ቦግ ብሎ እንዲያበራ ‘የዓለም የሆኑ’ አመለካከቶችን ማስወገድ ይገባናል።​—⁠ገላትያ 4:​3

ከእነዚህ አመለካከቶች አንዱ ኃላፊነት ከተቀበልኩ ብዙ ይጠበቅብኛል ብሎ በመፍራት ከኃላፊነት መሸሽ ነው። እርግጥ ነው፣ ኃላፊነት ሥራ ያስከትላል። ይሁን እንጂ ሥራው የሚያረካ ነው። (ከሥራ 20:​35 ጋር አወዳድር።) ጳውሎስ ለአምላክ ያደሩ መሆን ‘ድካምና ጥረት’ እንደሚጠይቅ ተናግሯል። ለመሰል ክርስቲያኖችና ለሌሎች የሠራነውን መልካም ሥራ በማይረሳው “በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ” ይህን በደስታ እንደምናደርገው ተናግሯል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​9, 10፤ ዕብራውያን 6:​10

አንዳንድ አልማዞች በሚሠሩበት ጊዜ “እክል” ስለሚኖራቸው በጥንቃቄ መያዝ አለባቸው። ሆኖም ፖላሪስኮፕ በተባለ መሣሪያ አጋዥነት አልማዙን የሚጠርገው ሰው እክል ያለበትን ቦታ ለይቶ ሊያውቅና በተሳካ ሁኔታ ሊሠራ ይችላል። ምናልባት እኛም ባሳለፍነው ሕይወት ወይም አንድ ገጠመኝ ባስከተለብን የስሜት ጉዳት ምክንያት ውስጣዊ እክል ወይም የባሕርይ ችግር ይኖርብን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን? በቅድሚያ ችግሩ እንዳለብን አምነን መቀበል እንዲሁም ችግሩን ለማስወገድ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠን መነሣት ያስፈልገናል። ወደ ይሖዋ መጸለይና ሸክማችንን በእሱ ላይ መጣል ይኖርብናል። በተጨማሪም አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን።​—⁠መዝሙር 55:​22፤ ያዕቆብ 5:​14, 15

እንዲህ ያለው ውስጣዊ እክል በኒኮላስ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ነበር። “አባቴ የአልኮል ሱሰኛ ነበር፤ ይህም እኔንና እህቴን ለብዙ ስቃይ ዳርጎናል” ሲል ተናግሯል። “ትምህርቴን ስጨርስ ወደ ውትድርናው ዓለም ገባሁ። ይሁን እንጂ ዓመፀኛው ባሕርዬ ብዙም ሳልቆይ ችግር ውስጥ ከተተኝ። አደንዛዥ ዕፅ ሳዘዋውር በመያዜ በሠራዊቱ ባለ ሥልጣናት ታሰርኩ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ከሠራዊቱ ኮብልዬ ነበር። በመጨረሻ ሠራዊቱን ትቼ ብወጣም ከችግር አልተላቀቅሁም ነበር። አደንዛዥ ዕፅ እወስድና ከልክ በላይ እጠጣ ስለነበር ሕይወቴ የተመሰቃቀለ ነበር። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎት ነበረኝ፤ እንዲሁም ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት እመኝ ነበር። ውሎ አድሮ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁና የአኗኗር ዘይቤዬን ለውጬ እውነትን ያዝኩ።

“ይሁን እንጂ በባሕሪዬ ላይ ችግር እንዳለብኝ አምኜ ለመቀበል ዓመታት ፈጀብኝ። ለሥልጣን ከፍተኛ ጥላቻ የነበረኝ ከመሆኑም በላይ ማንኛውም ዓይነት ምክር ሲሰጠኝ በቁጣ እገነፍል ነበር። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀምብኝ ብፈልግም ይህ ድክመቴ እንቅፋት ሆነብኝ። በመጨረሻ አስተዋይ በሆኑ ሁለት ሽማግሌዎች እርዳታ አማካኝነት ችግሬን አምኜ በመቀበል በፍቅር የለገሱኝን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በተግባር ላይ ማዋል ጀመርኩ። አልፎ አልፎ ቅሬታ የሚሰማኝ ቢሆንም የዓመፀኝነት ባሕርዬን ልቆጣጠር ችያለሁ። ይሖዋ ላሳየኝ ትዕግሥትና ሽማግሌዎቹ ለለገሱኝ ፍቅራዊ እርዳታ እጅግ አመስጋኝ ነኝ። መንፈሳዊ እድገት በማድረጌ በቅርቡ የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ እንዳገለግል ተመድቤያለሁ።”

ኒኮላስ እንደተገነዘበው ሥር የሰደዱ ባሕርያትን መለወጥ ቀላል አይደለም። እኛም ተመሳሳይ የሆነ ትግል ሊያጋጥመን ይችላል። ምናልባት ትንሿ ነገር ታስከፋን ይሆናል። በውስጣችን የታመቀ ቅሬታ ወይም ከሚገባው በላይ በራስ ፈቃድ የመመራት ፍላጎት ይኖረን ይሆናል። በመሆኑም ክርስቲያናዊ እድገታችን ውስን ይሆናል። አልማዝን የሚጠርጉ ሰዎች ናአትስ ብለው በሚጠሯቸው ድንጋዮች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ያጋጥማቸዋል። እነዚህ ድንጋዮች ቀልጠው በመዋሃድ አልማዝ ይፈጥራሉ። ናአትስ ሁለት ተቃራኒ የእድገት አቅጣጫ ስላላቸው አልማዙን በተፈለገው መንገድ መቁረጥ ያስቸግራል። ነገሩን ወደ ራሳችን ስናመጣው ቀና የሆነው ዝንባሌያችን ፍጽምና ከጎደለው ሥጋችን ጋር ይዋጋል። (ማቴዎስ 26:​41፤ ገላትያ 5:​17) አንዳንድ ጊዜ በባሕርያችን ላይ የሚታዩት የአለፍጽምና ውጤቶች ያን ያህል ትኩረት የሚያሻቸው አይደሉም ብለን በመደምደም የምናደርገውን ትግል ወደ ማቆሙ እናዘነብል ይሆናል። ‘አሁንም ቢሆን ቤተሰቤና ጓደኞቼ ይወዱኛል’ እንል ይሆናል።

ይሁን እንጂ ወንድሞቻችንን ለማገልገልና ሰማያዊው አባታችንን ይሖዋን ለማስከበር አዲሱን ሰው በመልበስ ‘በአእምሯችን መንፈስ መታደስ’ አለብን። ኒኮላስም ሆነ ሌሎች ብዙዎች እንደሚመሠክሩት ጥረታችን መልሶ የሚክስ ነው። አንድ የአልማዝ ጠራጊ አንድ እንከን የአልማዙን መልክ ሊያጠፋው እንደሚችል ያውቃል። በተመሳሳይም በባሕርያችን ላይ የሚታየውን ጉድለት ችላ ብለን በማለፍ መንፈሳዊ ገጽታችንን ልናበላሽ እንችላለን። ከዚህም የሚከፋው ደግሞ ከባድ የሆነ ድክመት ለመንፈሳዊ ውድቀት ሊዳርገን የሚችል መሆኑ ነው።​—⁠ምሳሌ 8:​33

በውስጣችን እንዳለ “እሳት”

አልማዝን የሚወለውል ሰው በአልማዙ ውስጥ ያለውን እንደ እሳት የሚያበራ ብርሃን ጠብቆ ለማቆየት ይፈልጋል። ይህ የሚሆነው ቀስተ ደመና ለመፍጠር በሚችሉበት መልክ ገጽታዎቹን አስተካክሎ በመሥራት ነው። በአልማዙ ውስጥ ሕብረ ቀለማት ያሉት ብርሃን ወደ ኋላና ወደፊት በመፈንጠቅ አልማዞች ለማብረቅረቅ የሚያስችላቸውን እሳት የመሰለ ነገር ይፈጥራል። በተመሳሳይም የአምላክ መንፈስ በውስጣችን እንዳለ “እሳት” ሊሆንልን ይችላል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​19፤ ሥራ 18:​25፤ ሮሜ 12:​11

ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ማነቃቂያ እንደሚያስፈልገን ከተሰማንስ? ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ‘መንገዳችን ማሰብ’ ያስፈልገናል። (መዝሙር 119:​59, 60) ይህ በመንፈሳዊ አዝጋሚ እንድንሆን ያደረጉንን ነገሮች ለይቶ ማወቅንና ይበልጥ ልንሠራባቸው የሚገቡን ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የትኞቹ መሆናቸውን መወሰንን ይጨምራል። መደበኛ በሆነ የግል ጥናትና ልባዊ ጸሎት አማካኝነት ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለን አድናቆት ጥልቀት እንዲኖረው ማድረግ እንችላለን። (መዝሙር 119:​18, 32፤ 143:​1, 5, 8, 10) ከዚህም በላይ ጠንክረው ከሚሠሩ የእምነት ሰዎች ጋር በመወዳጀት ይሖዋን በቅንዓት ለማገልገል የገባነውን ቃል ይበልጥ እናጠነክራለን።​—⁠ቲቶ 2:​14

ልዊዝ የምትባል አንዲት ክርስቲያን እህት እንዲህ ስትል ሐቁን ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ከመሆኔ በፊት ለሁለት ዓመታት ያህል ስለ ዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ሳስብ ቆይቻለሁ። አቅኚ እንዳልሆን ምንም የሚያግደኝ ነገር አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ያዳበርኩት ልማድ ተስማምቶኝ የነበረ ሲሆን ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ደግሞ ምንም ጥረት አላደረግሁም። ከዚያም በድንገት አባቴ ሞተ። ሕይወት እንደ ተሰባሪ ዕቃ በቀላሉ ሊጠፋ እንደሚችልና ሕይወቴን በተሻለ መንገድ ጥቅም ላይ አለማዋሌን ተገነዘብሁ። ስለዚህ የነበረኝን መንፈሳዊ አመለካከት በመቀየር በአገልግሎት ያለኝን ተሳትፎ ከፍ አደረግሁ፤ የዘወትር አቅኚም ሆንኩ። የመስክ አገልግሎት ዝግጅቶችን ሁልጊዜ የሚደግፉና አዘውትረው ከእኔ ጋር የሚያገለግሉ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ በተለይ በዚህ በኩል ልዩ እርዳታ አበርክተውልኛል። በክፉም ይሁን በደጉ የምንወዳጃቸው ሰዎች ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸውን ነገሮችና ግቦቻቸውን መጋራታችን እንደማይቀር ከዚህ ተምሬያለሁ።”

በብረት የተሳሉ ያህል

አልማዝ በምድር ላይ በተፈጥሮ ከሚገኙ ነገሮች ሁሉ እጅግ ጠንካራ ነው። በመሆኑም አንድን አልማዝ ለመቁረጥ ሌላ አልማዝ ያስፈልጋል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን “ብረት ብረትን ይስለዋል ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” የሚለውን ምሳሌ ያስታውሳቸዋል። (ምሳሌ 27:​17) አንድ ሰው ባልንጀራውን ‘የሚስለው’ እንዴት ነው? አንድ ብረት ተመሳሳይ የሆነውን ሌላውን ብረት ለመሳል ሊያገለግል እንደሚችል ሁሉ አንድም ግለሰብ የሌላውን አእምሯዊና መንፈሳዊ ሁኔታ ሊስል ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ነገር እንደጠበቅነው ሆኖ ባለመገኘቱ ተበሳጭተን የመንፈስ ጭንቀት ቢይዘን የሌላው ሰው ማበረታቻ ሊያነቃቃን ይችላል። አመለካከታችን ብሩህ ሊሆንና እንደገና በቅንዓት መንፈስ ለመሥራት ልንነሳሳ እንችላለን። (ምሳሌ 13:​12) በተለይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻዎችንና ለእድገት የሚረዱ ምክሮችን በመስጠት ሊስሉን ይችላሉ። “ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፣ ጥበብንም ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው፣ እውቀትንም ያበዛል” በማለት ሰሎሞን የተናገረውን መሠረታዊ ሥርዓት ይከተላሉ።​—⁠ምሳሌ 9:​9

እርግጥ ነው መንፈሳዊ ሥልጠና ጊዜ ይወስዳል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት ተሞክሮውንና የማስተማር ዘዴውን ለጢሞቴዎስ አካፍሎታል። (1 ቆሮንቶስ 4:​17፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​6, 16) ሙሴ ለኢያሱ የሰጠው ከ40 ዓመታት በላይ የፈጀ ሥልጠና የእስራኤልን ብሔር ለረጅም ጊዜ ጠቅሟል። (ኢያሱ 1:​1, 2፤ 24:​29, 31) ኤልሳዕ ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ለ6 ዓመታት ያህል ሳያገለግል አይቀርም፤ በእነዚህ ጊዜያት ያገኘው ሥልጠና ለ60 ዓመታት ያህል ላከናወነው አገልግሎት ጠቅሞታል። (1 ነገሥት 19:​21፤ 2 ነገሥት 3:​11) ሽማግሌዎች በትዕግሥት ቀጣይ የሆነ ሥልጠና በመስጠት የጳውሎስን፣ የሙሴንና የኤልያስን ምሳሌ ይከተላሉ።

ምሥጋና ማቅረብ የማሠልጠኛ ዋነኛ ክፍል ነው። በጥሩ ሁኔታ ለተከናወኑ ወይም ለሚያስመሰግኑ ተግባራት ልባዊ አድናቆትን መግለጽ ሌሎች አምላክን በተሟላ መንገድ እንዲያገለግሉ ሊገፋፋቸው ይችላል። ምሥጋና በራስ የመተማመን መንፈስን ይገነባል። ይህ ደግሞ በተራው አንድ ሰው ድክመቶቹን ለማስወገድ ጥረት እንዲያደርግ ያነሣሣዋል። (ከ1 ቆሮንቶስ 11:​2 ጋር አወዳድር።) በመንግሥቱ ስብከት ሥራና በሌሎች የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግም በእውነት ውስጥ ለማደግ የሚያስችል ማበረታቻ ያስገኛል። (ሥራ 18:​5) ሽማግሌዎች ወንድሞችን ከመንፈሳዊ የእድገት ደረጃቸው ጋር የሚሄድ ኃላፊነት ሲሰጧቸው የላቀ ጠቀሜታ ያለው ተሞክሮ ያካብታሉ፤ በመንፈሳዊ የማደግ ፍላጎታቸውንም ያጎለብትላቸዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​8, 9

መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚያነሳሳ ጥሩ ምክንያት

አልማዞች የከበሩ ነገሮች ተደርገው ይታያሉ። ከዓለም አቀፉ የይሖዋ አምላኪዎች ማኅበር ጋር አሁን በመተባበር ላይ ያሉትም እንዲሁ ናቸው። እንዲያውም አምላክ ከአሕዛብ ሁሉ የመጡ ‘የተመረጡ’ ወይም ‘የከበሩ’ እቃዎች ሲል ይጠራቸዋል። (ሐጌ 2:​7፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ባለፈው ዓመት 375,923 የሚያክሉ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ይህን ጭማሪ ለማስተናገድ ‘የድንኳኑን ሥፍራ ማስፋት’ ያስፈልጋል። በመንፈሳዊ በማደግና ክርስቲያናዊ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ በመጣጣር በመስፋፋት ላይ ባለው በዚህ ሥራ የድርሻችንን ልናበረክት እንችላለን።​—⁠ኢሳይያስ 54:​2፤ 60:​22

በባንክ ካዝናዎች ውስጥ ከሚቀመጡትና አልፎ አልፎ ከሚታዩት ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ብዙ አልማዞች ይልቅ ውድ የሆኑት ክርስቲያናዊ ባሕሪዎቻችን ይበልጥ ሊያበሩ ይችላሉ። ክርስቲያናዊ ባሕሪዎቻችንን ዘወትር የምንጠርግና በግልጽ የምናሳይ ከሆነ ይሖዋ አምላክን እናስከብራለን። ኢየሱስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ሲል ተከታዮቹን አጥብቆ አሳስቧል። (ማቴዎስ 5:​16) በእርግጥም ይህ መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ጠንካራ ምክንያት ይሆነናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህ ርዕስ ሥር ምትክ ስሞችን ተጠቅመናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ