ከሰው ሠራሹ “ሰላምና ደኅንነት” ባሻገር መመልከት
ሰዎች በፍጹም እውነተኛውንና ዘላቂውን ሰላም ሊያመጡ አይችሉም፤ ሐቁ ይህ ነው። ለምን አይችሉም? ምክንያቱም ምንም እንኳ ሰዎች በደም በጨቀየው ታሪካቸው ተካፋይ ቢሆኑም ዋነኞቹ ሰላም አደፍራሾች እነርሱ አይደሉም። ዋነኛው ሰላም አደፍራሽ ከሰው እጅግ በጣም የበለጠ ኃይለኛ ነው። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለምን ሁሉ የሚስተው” ተብሎ ከተገለጸው ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።—ራእይ 12:9
መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው [በሰይጣን] ኃይል ሥር” እንዳለ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) ስለዚህ እውነተኛ ሰላምና ዘላቂ የሆነ ደኅንነት ማግኘቱ ሰይጣንን እርሱ ከገነባውና በግልጽ ከሚቆጣጠረው የዓለም ሥርዓት ጋር ከመድረኩ ማስወገድን መጨመር ይኖርበታል። (ከኢሳይያስ 48:22፤ ሮሜ 16:20 ጋር አወዳድር) ሰዎች ይህንን ለማድረግ አይችሉም።
ታዲያ ሰላምንና ደኅንነትን ለማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? በአምላክ ኃይል ነው፤ እርሱም ከሰይጣን እጅግ በጣም የላቀ ኃይል አለው። ሰይጣን በሰዎች መካከል ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉን የሚችለው አምላክ የጊዜ ገደብ አድርጎለታል። ይህ የጊዜ ገደብ ሲደርስም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ላይ “ድንገተኛ ጥፋት” ይመጣበታል። (1 ተሰሎንቄ 5:3-7) ያለው ማስረጃ በጠቅላላው ይህ በቅርቡ ይፈጸማል ወደሚለው መደምደሚያ ይመራናል።
ሰላምና ደኅንነት አሁን!
ዛሬስ እንዴት ነው? ዛሬም ቢሆን የተወሰነ መጠን ያለው ሰላምና ደኅንነት ማግኘት ይቻላል። እንዴት? ይህ የሚሆነው ብዙ የሃይማኖት መሪዎች እንደሞከሩት በዚህ ዓለም ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ሳይሆን የአምላክን ትዕዛዛትና ምክር በመከተል ነው።
እንደዚህ ያለው አካሄድ በእርግጥ ሰላምን ያመጣልን? አዎን ያመጣል። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምስክሮች ይህንን ፈትነውት በእርግጥ እውነተኛ ሰላምና እንዲሁም መጠነኛ ደኅንነት ለማግኘት የሚቻል ሆኖ አግኝተውታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹትን የአምላክን ትዕዛዛት መከተላቸው ከየትኛውም ዘር፣ ብሔር ወይም ቋንቋ ቢመጡም እውነተኛ ሰላም ባለው አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ በአንድነት እንዲሰበሰቡ አስችሏቸዋል።—መዝሙር 133:1
መለኮታዊውን ሕግ በመታዘዝ በምሳሌያዊ መንገድ ‘ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውን ማጭድ አድርገዋል፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።’ (ኢሳይያስ 2:2-4) በአምላክ ፍቅር ውስጥ የመተማመን ስሜት ይሰማቸዋል፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው እንደሚያስቡላቸው ትምክህት አላቸው። (ሮሜ 8:28, 35-39፤ ፊልጵስዩስ 4:7) ይህ ነገር እውነት መሆኑን የምትጠራጠር ከሆነ ከመንግሥት አዳራሾቻቸው ወደ አንዱ በመሄድ ራስህ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።
በዓለም ዙሪያ የሚሰፍን ሰላምና ደኅንነት
ይሁን እንጂ ሰላምና ደኅንነት እንደሚመጣ ለሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የመጨረሻው ፍጻሜ ይህ አይደለም። ከዚህ በጣም የላቀ ነው! ይህኛው ሁሉም ሰው የአምላክን ሕጎች ቢታዘዝ ኖሮ ዓለም ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይ የተስፋ ብልጭታ ብቻ ነው። በቅርቡ ይህ የተስፋ ብልጭታ እውን ይሆናል።
አምላክን የማያገለግሉ ሰዎች “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ [በራሳቸው መንገድ በመጨረሻው ሰላምንና ደኅንነትን እንዳመጡ ሲመስላቸው] ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል” ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። (1 ተሰሎንቄ 5:3) ሰይጣን የሰውን ልጅ ያሳተበት ጊዜ ያበቃል ብሎ አምላክ የሚወስንበት ጊዜ ይመጣል። ከዚያም በኋላ እርሱ በእርሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ምግባረ ብልሹ የዓለም ሥርዓት የሚወገዱበት ጊዜ ይሆናል። ከዚያም የሚከተለው የዳንኤል ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ ይሆናል፦ “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፣ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44
ይህ በአምላክ በኩል የተወሰደ ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ይሆናልን? በምንም መንገድ አይሆንም። ድንገተኛ ጥፋት የሚመጣው በአምላክ ፍርድ፣ በአምላክ የአቋም ደረጃዎች መሠረት ጥፋት በሚገባቸው ላይ ብቻ ይሆናል። በዚህ ረገድ ፈጣሪ ፍትሐዊ ውሳኔ ያደርጋል ብለህ ትተማመንበታለህን? ጉዳዩን ያለ ምንም ስጋት ለእርሱ ልንተውለት እንችላለን። የፍርዱ ሥራ ውጤትስ ምን ይሆናል? የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኃጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) ክፉዎች በመጥፋታቸው የሚያዝን ይኖራልን?
ሰላም አደፍራሾች ከተወገዱ በኋላ ሰውን ጠቃሚ በሆነው የአምላክ አገዛዝ ሥር እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት በመላው ምድር ላይ የሰው ዘር የሚያገኘው ዕጣ ይሆናል። “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር [ይሖዋን (አዓት)] በማወቅ ትሞላለችና።” (ኢሳይያስ 11:9) ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ታምንበታለህን? እነዚህ ነገሮች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ትምክህት አለህን? ጥርጣሬ ካለብህ ነገሩን በስፋት እንድትመረምረው እናበረታታሃለን። ሰው ሲጠብቀው የኖረውን ትክክለኛ ሰላምና እውነተኛ ደኅንነት ለማግኘት የሚችልበት ብቸኛ መንገድ የአምላክ መንገድ ነው። ሐቁ ይኸው ነው።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ሕዝቦች ዛሬም ቢሆን በተወሰነ መጠን እውነተኛ ሰላምና ጥሩ የሆነ ደኅንነት አግኝተዋል