ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል
“ልጆችህም በማእድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ለምለም ቅርንጫፎች ይሆናሉ።” —መዝሙር 128:3 የ1980 ትርጉም
1. ተክሎችንና ልጆችን ማሳደግ እንዴት ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል?
የልጆች እድገት በብዙ መንገዶች ከአትክልት እድገት ጋር ይመሳሰላል። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ የአንድን ሰው ሚስት “እንደ ፍሬያማ የወይን ተክል” ልጆቹን ደግሞ ‘በማዕዱ ዙሪያ እንዳሉ ለምለም የወይራ ቅርንጫፎች’ አድርጎ መናገሩ አያስደንቅም። (መዝሙር 128:3) አንድ ገበሬ በተለይ የአየሩ ጠባይና የአፈሩ ሁኔታ ጥሩ ካልሆነ ቡቃያውን ተንከባክቦ ለፍሬ ማብቃት አስቸጋሪ እንደሚሆን ይነግራችኋል። በተመሳሳይም በእነዚህ አስጨናቂ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ ልጆችን የተስተካከሉና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አድርጎ ማሳደግ በጣም አስቸጋሪ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
2. ጥሩ ምርት ለማግኘት ብዙውን ጊዜ የሚያስፈልገው ምንድን ነው?
2 አንድ ገበሬ ጥሩ ምርት እንዲያገኝ ከተፈለገ ቡቃያው ለም አፈር፣ የፀሐይ ብርሃንና ውኃ ያስፈልገዋል። ከመኮትኮትና ከማረም በተጨማሪ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች መርጨትና ሌሎች እንክብካቤዎች ማድረግ አለበት። አዝመራው እስኪታጨድ ድረስ በየጊዜው አስቸጋሪ ነገሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። እህሉ በመጨረሻ መጥፎ ቢሆን እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል! ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ጥሩ እህል ቢያጭድ ግን ገበሬው እንዴት ይረካ ይሆን!—ኢሳይያስ 60:20–22፤ 61:3
3. በተፈላጊነት ረገድ ከልጆችና ከአትክልቶች ማንኛቸው ይበልጣሉ? ልጆችስ ምን ዓይነት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል?
3 የተሳካና ፍሬያማ የሆነ ሰብአዊ ሕይወት ማሳለፍ ከአንድ ገበሬ ምርት ይበልጥ ውድ ነገር መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው አንድን ልጅ በጥሩ ሁኔታ ኮትኩቶ ማሳደግ የተትረፈረፈ እህል ለማምረት ከሚያስፈልገው የበለጠ ጊዜና ድካም የሚጠይቅ መሆኑ ምንም አያስገርምም። (ዘዳግም 11:18–21) በሕይወት ማሳ ላይ የተተከለ ልጅ ፍቅርን እንደ ውኃ ካጠጣነውና እንደ ምግብ ከመገብነው እንዲሁም ጤናማ ገደቦችን ካበጀንለት ምግባረ ብልሹ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ በመንፈሳዊ ሊያድግና ሊያብብ ይችላል። ሕፃኑ ከተንገላታና ከተጨቆነ ግን ውስጥ ውስጡን በመንፈሳዊ ሊጠወልግና ሊሞትም ይችላል። (ቆላስይስ 3:21ን ከኤርምያስ 2:21ና ከ12:2 ጋር አወዳድር።) በእርግጥም ልጆች ሁሉ ልዩ ትኩረት ሊደረግላቸው ያስፈልጋል!
ከሕፃንነት አንስቶ በየቀኑ ትኩረት መስጠት
4. ልጆች “ከሕፃንነታቸው” ጀምረው ምን ዓይነት ትኩረት ያስፈልጋቸዋል?
4 ወላጆች አዲስ ለተወለደ ልጃቸው የማያቋርጥ ክትትል ሊያደርጉለት ይገባል። ይሁን እንጂ ሕፃኑ በየቀኑ ሊደረግለት የሚያስፈልገው አካላዊ ክትትል ብቻ ነውን? ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ አገልጋይ ለነበረው ለጢሞቴዎስ “ከሕፃንነትህም ጀምረህ . . . መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል” ብሎ ጽፎለት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ስለዚህ ወላጆቹ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ለጢሞቴዎስ በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድም ክትትል ያደርጉለት ነበር። ሕፃን የሚባለው ከስንት ዓመቱ ጀምሮ ነው?
5, 6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በእናቱ ማሕፀን ውስጥ ስላለ ሕፃን ምን ይላል? (ለ) ወላጆች ላልተወለደ ሕፃን ደህንነት አሳቢ መሆን እንዳለባቸው የሚያመለክተው ምንድን ነው?
5 ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት (ብሬፎስ የተባለው) የግሪክኛ ቃል ያልተወለደ ሕፃንንም ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል። የአጥማቂው ዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ ለዘመዷ ለማርያም “የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ [ብሬፎስ] በማኅፀኔ በደስታ” ዘለለ ብላት ነበር። (ሉቃስ 1:44) ስለዚህ ያልተወለደ ልጅም ሕፃን ተብሎ ሊጠራ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ፅንስ ከማኅፀን ውጭ የሚደረጉ ነገሮች እንደሚነኩት ያሳያል። በዛሬው ጊዜ በእርግዝና ወራት በእናቱ ማሕፀን ውስጥ ላለው ሕፃን እንክብካቤ ማድረጉ ጥሩ ነው ይባላል። ታዲያ ይህ እንክብካቤ ለፅንሱ መንፈሳዊ ደኅንነት ትኩረት መስጠትንም ሊጨምር ይገባልን?
6 ይህ ሊታሰብበት የሚገባው ነው፤ ምክንያቱም ፅንሱ ከውጭ በሚሰማው ነገር ሊጠቀም አለዚያም ሊጎዳ እንደሚችል ማስረጃዎች ያሳያሉ። አንድ የሙዚቃ ዲሬክተር እየተለማመደው ያለው የሙዚቃ ቅንብር በተለይም ሴሎ የሚባለው የሙዚቃ መሣሪያ ከዚህ በፊት የሚያውቀው መሰለው። ከዚያም ሴሎ በሚባለው የሙዚቃ መሣሪያ የታወቀች ተጫዋች ለሆነችው እናቱ የሚለማመዳቸውን የሙዚቃ ዓይነቶች ሲነግራት እሱን እርጉዝ ሆና ይህንኑ ሙዚቃ ትጫወት እንደነበረ ነገረችው። በተመሳሳይም እናቶቻቸው መጥፎ መልእክት የሚያስተላልፉ የቴሌቪዥን ቲያትሮችን አዘውትረው የሚሰሙ ከሆነ ባልተወለዱት ሕፃናት ላይ ጉዳት ሊያስከትልባቸው ይችላል። ስለሆነም ነው አንድ የሕክምና መጽሔት ስለ “አደገኛ የቴሌቪዥን ቲያትር ሱሰኝነት” የተናገረው።
7. (ሀ) ብዙ ወላጆች ላልተወለደው ሕፃን ደህንነት ትኩረት የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሕፃን ምን ችሎታዎች አሉት?
7 ብዙ ወላጆች አዎንታዊ ግፊት ያለው ማነቃቂያ ለሕፃናት የሚሰጠውን ጥቅም በመገንዘብ ለልጃቸው ማንበብ፣ መናገርና መዝፈን የሚጀምሩት ገና ከመወለዱ በፊት ነው። እናንተም እንዲሁ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ሕፃኑ የምትናገሯቸውን ቃላት ባይረዳቸውም መንፈስን የሚያረጋጋ ድምጻችሁንና ፍቅራዊ ቃናውን መስማቱ ይጠቅመዋል። ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ የምትናገራቸውን ቃላት ምናልባት እናንተ ከጠበቃችሁት በላይ ፈጥኖ መረዳት ሊጀምር ይችላል። አንድ ሕፃን በመስማት ብቻ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት ውስጥ አንድን በጣም ከባድ የሆነ ቋንቋ ሊያውቅ ይችላል። አንድ ሕፃን የመጽሐፍ ቅዱስን ‘ንጹህ ቋንቋ’ ጭምር ማወቅ ሊጀምር ይችላል።—ሶፎንያስ 3:9
8. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ‘ከሕፃንነቱ’ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ ነበር ሲል ምን ማለቱ ነው? (ለ) ጢሞቴዎስን በተመለከተ ምን ነገር እውነት ሆኖ ተገኝቷል?
8 ጳውሎስ ‘ጢሞቴዎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቋል’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጢሞቴዎስ ትንሽ ካደገ በኋላ ሳይሆን ከጨቅላነቱ ጀምሮ መንፈሳዊ ሥልጠና ያገኝ ነበር ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም አባባል በአጠቃላይ አዲስ የተወለደን ሕፃን ለማመልከት ከሚያገለግለው ብሬፎስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉም ጋር የሚስማማ ነው። (ሉቃስ 2:12, 16፤ ሥራ 7:19) ጢሞቴዎስ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማስታወስ ከሚችልበት የሕፃንነቱ ጊዜ ጀምሮ እናቱ ኤውንቄና ሴት አያቱ ሎይድ መንፈሳዊ ትምህርት ሰጥተውታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5) ‘አዲስ ተክል የሰጠኸውን ቅርጽ ተከትሎ ያድጋል’ የሚለው አባባል በጢሞቴዎስ ላይ በትክክል ሠርቷል። ጢሞቴዎስ ‘ሊሄድበት በሚገባው መንገድ’ ስለ ሠለጠነ በመጨረሻው ጥሩ የአምላክ አገልጋይ ለመሆን በቅቷል።—ምሳሌ 22:6፤ ፊልጵስዩስ 2:19–22
ልዩ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል
9. (ሀ) ወላጆች ምን ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው? ለምንስ? (ለ) ሕፃኑ እያደገ ሲሄድ ወላጆች ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል? ምን ምሳሌስ መከተል ይኖርባቸዋል?
9 ልጆችና ተክሎች የሚመሳሰሉባቸው ሁኔታዎች አሉ። እንደ ተክሎች ሁሉ ልጆችም እርስ በርሳቸው በጠባይ ይለያያሉ። አስተዋይ የሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው መካከል ያለውን የባሕርይ ልዩነት ይገነዘባሉ፤ እንዲሁም አንዱን ልጅ ከሌላው ጋር ከማወዳደር ይቆጠባሉ። (ገላትያ 6:4) ልጆቻችሁ ወደ ጥሩ ጉልምስና እንዲደርሱ ከተፈለገ የግል ባሕርያቶቻቸውን ለይታችሁ ማወቅና ጥሩ የሆኑትን መኮትኮት መጥፎ የሆኑትን ደግሞ እንደ አረም እየነቀላችሁ ማረም ያስፈልጋችኋል። አንድ ዓይነት ድክመት ወይም ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ እንዳላቸው ብትገነዘቡ ለምሳሌ የመዋሸት፣ የፍቅረ ንዋይ ወይም የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ብታዩባቸው ምን ታደርጋላችሁ? ኢየሱስ የሐዋርያቱን ድክመት በደግነት እንዳስተካከለ ሁሉ እናንተም ጉድለታችውን በደግነት አስተካክሉት። (ማርቆስ 9:33–37) በተለይ እያንዳንዱ ልጅ ላለው ጠንካራ ጎንና ለሚያሳየው ጥሩ ጠባይ ዘወትር አመስግኑት።
10. ልጆች በተለይ የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው? ይህስ እንዴት ሊሰጣቸው ይችላል?
10 በተለይ ልጆች የሚያስፈልጋቸው ነገር ፍቅራዊ የሆነ የግል ትኩረት መስጠት ነው። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ልዩ ትኩረት ለልጆች ለመስጠት ጊዜ ይወስድ ነበር። በአገልግሎቱ በጣም ሥራ ይበዛበት በነበረባቸው የመጨረሻዎቹ ቀናት እንኳን ጊዜ ወስዶ ልጆችን ያነጋግር ነበር። (ማርቆስ 10:13–16, 32) ወላጆች፣ ይህን ምሳሌ ተከተሉ! ራስ ወዳድ ባለመሆን ከልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፉትን ጊዜ አመቻቹ። ለልጆቻችሁ እውነተኛ ፍቅር ማሳየቱ ሊያሳፍራችሁ አይገባም። ኢየሱስ እንዳደረገው እጃችሁን ትከሻቸው ላይ አሳርፋችሁ አጫውቷቸው፣ ሞቅ ባለ የፍቅር ስሜት እቀፏቸው፤ ሳሟቸው። ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ያሳደጉ ወላጆች ለሌሎች ወላጆች ምን ምክር ትሰጣላችሁ ተብለው ሲጠየቁ ‘በጣም ውደዷቸው፣’ ‘አብራችኋቸው ጊዜ አሳልፉ፣’ ‘እርስ በርስ መከባበርን አዳብሩ፣’ ‘በጥሞና አዳምጧቸው፣’ ‘ከመናገር ይልቅ ጥሩውን አቅጣጫ አሳዩአቸው’ እና ‘የማይቻለውን ነገር አትጠብቁ’ የሚሉት አብዛኞቹ ወላጆች ከሰጧቸው መልሶች መካከል ናቸው።
11. (ሀ) ወላጆች ለልጆቻቸው ልዩ ትኩረት መስጠትን እንዴት ሊመለከቱት ይገባል? (ለ) ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጠቃሚ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ ሊያደርጉ የሚችሉት መቼ ነው?
11 እንዲህ ያለ ልዩ ትኩረት መስጠት አስደሳች ሊሆን ይችላል። በተሳካ ሁኔታ ልጆቹን ያሳደገ አንድ ወላጅ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁለቱ ልጆቻችን ገና ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ እነሱን ለመኝታ ማዘጋጀቱ፣ ለእነሱ ጽሑፍ ማንበቡ፣ አለባብሶ ማስተኛቱና አብሯቸው መጸለዩ በጣም የሚያስደስት ነበር።” ከልጃችሁ ጋር አብራችሁ የምታሳልፉት ይህ ዓይነቱ ጊዜ ወላጅንም ሆነ ልጅን ሊያበረታታ የሚችል የሐሳብ መለዋወጥ ለማድረግ ያስችላችኋል። (ከሮሜ 1:11, 12 ጋር አወዳድር) አንድ ባልና ሚስት የሦስት ዓመት ልጃቸው አምላክ “ዋሊን” እንዲባርክ ሲጠይቅ ሰሙ። በተከታታይ ምሽቶች ስለ “ዋሊ” ጸለየ። በዚያን ወቅት በማላዊ ከባድ ስደት ስለነበረ ወላጆቹ በማላዊ ለሚገኙት ወንድሞች እየጸለየ እንዳለ ሲያውቁ በጣም ተበረታቱ። አንዲት ባለትዳር ሴት ‘ገና የአራት ዓመት ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እናቴ ሳህኖቹን የምታጥብበት ገንዳ ላይ ለመድረስ ወንበር ላይ ቆሜ ያጠበቻቸውን ሳህኖች በመወልወል ስረዳት እናቴ ጥቅሶችንና የመንግሥቱን መዝሙሮች በቃል እንድይዝ ትረዳኝ ነበር’ ብላለች። ከልጆቻችሁ ጋር ጠቃሚ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ልትደሰቱ የምትችሉበትን ጊዜ ማሰብ ትችላላችሁን?
12. ክርስቲያን ወላጆች አስተዋይ በመሆን ለልጆቻቸው ምን ያደርጋሉ? ምን ዘዴዎችንስ ሊጠቀሙ ይችላሉ?
12 አዋቂ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች ቋሚ የጥናት ፕሮግራም ያወጣሉ። ምንም እንኳን መደበኛ በሆነ የጥያቄና መልስ አጠናን ዘዴ መጠቀም ብትችሉም ለሁላችሁም፣ በተለይም ለወጣት ልጆች ደስ በሚል መንገድ የሐሳብ ልውውጥ እንዲካሄድ የአጠናኑን ዘዴ እንደ ሁኔታው ልትለዋውጡ ትችላላችሁን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ታሪካዊ ቦታዎችን መሳልን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን መናገርን ወይም አንድ ልጅ አስቀድሞ ስለ አንድ ርዕስ አስቀድሞ እንዲዘጋጅ በማድረግ ያዘጋጀውን ማዳመጥን ተጨማሪ ዘዴ ልታደርጉት ትችላላችሁ። ልጆቹ ለአምላክ ቃል ጉጉት እንዲያድርባቸው በተቻላችሁ መጠን ቃሉ እንዲጣፍጣቸው አድርጉ። (1 ጴጥሮስ 2:2, 3) አንድ አባት ‘ልጆቻችን ገና ትንንሾች በነበሩበት ጊዜ ወለሉ ላይ እየዳኽን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን የታወቁ ባለ ታሪኮች ጨምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ሁኔታዎችን አብረናቸው እንሠራ ነበር። ይህን ልጆቹ በጣም ይወዱት ነበር’ ብሏል።
13. የልምምድ ፕሮግራም ማውጣት ምን ጥቅም ያስገኛል? በዚህ ፕሮግራም ወቅትስ ምን ነገሮችን ልትለማመዱ ትችላላችሁ?
13 በተጨማሪም ጠቃሚ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችሏችሁን የልምምድ ፕሮግራም አውጡ። ልጆቹ በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው እውነተኛ ሁኔታዎች እንዲዘጋጁ ይረዷቸዋል። በናዚ ስደት ወቅት ለአምላክ የታመኑ ሆነው ከቆሙት ከኩስሮው ቤተሰብ 11 ልጆች መካከል አንዷ ስለ ወላጆቿ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቻችን ምን ማድረግ እንዳለብንና በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ስለ አቋማችን እንዴት መከላከያ ማቅረብ እንደምንችል አሳይተውናል። [1 ጴጥሮስ 3:15] ብዙ ጊዜ ጥያቄ የመጠየቅና መልሶችን የመስጠት የልምምድ ፕሮግራሞችን እናደርግ ነበር።” እናንተስ ለምን ይህን የመሰለ ፕሮግራም አታወጡም? አንድ ወላጅ እንደ ቤቱ ባለቤት ሆኖ በመሥራት ለአገልግሎቱ የሚረዱ ልዩ ልዩ የመልእክት አቀራረብ ልትለማመዱ ትችላላችሁ። ወይም የልምምድ ፕሮግራሙ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 1:10–15) “አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በድራማ መልክ መለማመድ የአንድን ልጅ ችሎታና ድፍረት ይገነባል” ሲሉ አንዲት ግለሰብ ገልጸዋል። “ልምምዱ አንድ ጓደኛው ለልጃችሁ ሲጋራ፣ መጠጥ፣ ዕፅ እንዲወስድ ሲጋብዘው ምን ብሎ መመለስ እንዳለበት የሚጨምር ሊሆን ይችላል።” እነዚህ ፕሮግራሞች ልጆቻችሁ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ለማስተዋል ሊረዷቸው ይችላሉ።
14. ከልጆቻችሁ ጋር የምታደርጉት ፍቅራዊና ርኅራኄ የተሞላበት ውይይት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ከልጃችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ በምታደርጉበት ጊዜ የሚከተሉት ቃላት ጸሐፊ እንዳደረገው በርኅራኄ አነጋገር ለመማረክ ሞክር፦ “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።” (ምሳሌ 3:1, 2) ልጃችሁ ታዛዥ እንዲሆን የምትፈልጉት ሰላምና ረጅም ዕድሜ፣ አልፎ ተርፎም በአምላክ ሰላማዊ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ብላችሁ እንደሆነ ብትነግሩት ይህ የልጃችሁን ልብ አይነካምን? ልጃችሁን ከአምላክ ቃል ምክንያቱን እያሳያችሁ በምታስረዱበት ጊዜ የልጃችሁን ባሕርይ ግምት ውስጥ አስገቡ። ይህንን በጸሎት አድርጉት፤ ይሖዋም ጥረታችሁን ይባርክላችኋል። እንዲህ ዓይነቱ በፍቅርና በርኅራኄ የሚደረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ጥሩ ውጤት እንደሚኖረውና ዘላቂ ጥቅም እንደሚያመጣ የተረጋገጠ ነው።—ምሳሌ 22:6
15. ወላጆች ልጆቻቸው ችግሮችን እንዲፈቱ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ የሐሳብ ልውውጥ የሚደረገው ቀደም ሲል በታቀደው የጥናት ወቅት ባይሆንም ሐሳብህ በሌሎች ጉዳዮች እንዲወሰድ አትፍቀድ። ልጅህ የሚናገረውን ብቻ ሳይሆን ሐሳቡ እንዴት ሆኖ እንደተገለጸ ጭምር በጥሞና አዳምጥ። አንድ ባለሙያ “ልጅህን ተመልከተው ሙሉ ትኩረትህን ስጠው። እንዲያው መስማት ብቻ ሳይሆን የሚናገረውን መረዳት ያስፈልግሃል። እንዲህ ዓይነቱን ተጨማሪ ጥረት የሚያደርጉ ወላጆች በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ” ብለዋል። በዘመናችን ልጆች በትምህርት ቤትም ሆነ በየትኛውም ሥፍራ ብዙ ጊዜ ከባድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ልጁ ሐሳቡን በነፃነት እንዲናገር አድርገውና ጉዳዩን በአምላክ አመለካከት እንዲያየው እርዳው። ችግሩ እንዴት እንደሚፈታ ካላወቅህ በቅዱሳን ጽሑፎችና “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያወጣቸው ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርግ። (ማቴዎስ 24:45) አደራ፣ ልጃችሁ ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ልዩ ትኩረት ስጡት።
አብራችሁ የምታሳልፉትን ጊዜ በሚገባ ተጠቀሙበት
16, 17. (ሀ) ዛሬ በተለይ ወጣቶች ልዩ ትኩረትና ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ልጆች በወላጆቻቸው ተግሳጽ በሚሰጣቸው ጊዜ ምን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል?
16 ዛሬ ወጣቶች ከምን ጊዜውም የበለጠ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፤ ምክንያቱም የምንኖረው ‘አስጨናቂ’ በሆኑት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ማቴዎስ 24:3–14) ወላጆችም ሆኑ ልጆች ‘የራሱ ያደረጋትን በሕይወት የምትጠብቀው’ ጥበብ ታስፈልጋቸዋለች። (መክብብ 7:12) አምላካዊ ጥበብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተን እውቀት በሥራ ላይ ማዋልን የሚጨምር ስለሆነ ልጆች ዘወትር የአምላክን ቃል መማር ያስፈልጋቸዋል። ስለሆነም ከልጆቻችሁ ጋር ቅዱሳን ጽሑፎችን አጥኑ። ስለ ይሖዋ ንገሯቸው፤ እሱ ምን እንደሚፈልግባቸው በሚገባ አብራሩላቸው፤ እንዲሁም ስለ ታላላቅ ተስፋዎቹ ፍጻሜ ብሩህ የሆነ ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጉ። እቤት በምትቀመጡበት ጊዜ፣ አብራችሁ ስትሄዱ፣ እንዲሁም አመቺ በሚሆንበት በማንኛውም ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ንገሯቸው።—ዘዳግም 6:4–7
17 አንድ ሁኔታ ለሁሉም ዓይነት ተክሎች እድገት ተስማሚ እንደማይሆን ገበሬዎች ያውቃሉ። ተክሎች ልዩ የባለሞያ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። በተመሳሳይም እያንዳንዱ ልጅ ከሌላው የተለየ ነው፤ ስለሆነም ልዩ ትኩረት፣ ሥልጠናና ተግሳጽ ያስፈልገዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ልጅ የሚሠራውን መጥፎ ድርጊት እንዲተው ለማድረግ ወላጅ ፊቱን ኮስተር አድርጎ ቢያየው በቂ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ልጅ ግን ጠንከር ያለ ተግሳጽ ሊፈልግ ይችላል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ የልጆቹ አነጋገር ወይም ድርጊቶች ለምን እንደማትደሰቱ ልጆቻችሁ ሁሉ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። እንዲሁም በተግሳጹ ረገድ ሁለቱም ወላጆች አንድ አቋም በመያዝ እርስ በርሳቸው መተባበር ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) በተለይ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚስማማ ግልጽ መመሪያ መስጠታቸው በጣም አስፈላጊ ነው።
18, 19. ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው? ይህን ኃላፊነት በሚገባ ከተወጡትስ ምን ውጤት ሊገኝ ይችላል?
18 አንድ ገበሬ በተገቢው ጊዜ መዝራትና መኮትኮት አለበት። ቢዘገይ ወይም ዘርቶ ሰብሉን ቸል ብሎ ቢተወው የሚያገኘው አዝመራ በጣም ጥቂት ይሆናል ወይም ምንም አያገኝም። እንግዲህ ልጆቻችሁም በሚቀጥለው ወር ወይም በሚቀጥለው ዓመት ሳይሆን አሁኑኑ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው በማደግ ላይ ያሉ “ተክሎች” ናቸው። ከአምላክ ቃል ጋር ተስማሚ የሆነ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የምታደርጉባቸውና በመንፈሳዊ እንዲጠወልጉና እንዲሞቱ ሊያደርጓቸው የሚችሉትን ዓለማዊ አስተሳሰቦች እንደ አረም ነቅላችሁ መጣል የምትችሉባቸው ውድ የሆኑ አጋጣሚዎች ሳትጠቀሙባቸው አይለፏችሁ። ይህ ጊዜ ፈጥኖ ስለሚያልፍ ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ ጊዜ ለማሳለፍ የታደላችሁባቸውን ሰዓታትና ቀናት በጥሩ ሁኔታ ተጠቀሙባቸው። የታመኑ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በመሆን ለሚገኘው አስደሳች ሕይወት የሚያስፈልጉትን አምላካዊ ባሕርያት በልጆቻችሁ ውስጥ ለመኮትኮት ከፍተኛ ጥረት አድርጉ። (ገላትያ 5:22, 23፤ ቆላስይስ 3:12–14) ይህ የሌላ ሰው ሥራ አይደለም፤ የእናንተው ሥራ ነው። አምላክም ተግባራችሁን እንድትፈጽሙ ሊረዳችሁ ይችላል።
19 ለልጆቻችሁ ትልቅ መንፈሳዊ ሀብት አውርሷቸው። የአምላክን ቃል አብራችኋቸው አጥኑ፤ እንዲሁም ጤናማ በሆነ መዝናኛ አብራችኋቸው ተደሰቱ። ልጆቻችሁን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛችኋቸው ሂዱ። እንዲሁም በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ስትሠማሩ ከጎናችሁ አድርጓቸው። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኘውን ባሕርይ በተወደዱት ልጆቻችሁ ውስጥ ገንቡ። የኋላ ኋላ ታላቅ ደስታ እንደሚያመጡላችሁ የተረጋገጠ ነው። በእርግጥም “የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፣ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል። አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።”—ምሳሌ 23:24, 25
አስደናቂ የድካም ውጤት
20. በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆችን በተሳካ መንገድ ለማሳደግ ቁልፉ ምንድን ነው?
20 ልጆችን ማሳደግ በጣም ውስብስብ የሆነ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ የወላጆች ሥራ ነው። እነዚህን ‘በማዕድህ ዙሪያ ያሉ የወይራ ቡቃያዎች’ የመንግሥቱን ፍሬ የሚያፈሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አድርጎ ማሳደግ የ20 ዓመት ፕሮጀክት ተብሎ ተጠርቷል። (መዝሙር 128:3፤ ዮሐንስ 15:8) ብዙውን ጊዜ ልጆች ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲደርሱ ይህ ፕሮጀክት እየከበደ ይመጣል። በዚህ እድሜ ላይ ያለባቸው ግፊት ያይላል፤ ስለሆነም ወላጆች ጥረታቸውን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ ያገኙታል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የተሳካ ውጤት ለማግኘት ቁልፉ ለልጆቹ ትኩረት መስጠት፣ ፍቅራዊ ስሜት ማሳየትና ሁኔታቸውን መረዳት ነው። ልጆቻችሁ በግል ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚያስፈልግ አስታውሱ። ለደህንነታቸው እውነተኛ ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየት እንዲህ ዓይነቱን ትኩረት ልትሰጧቸው ትችላላችሁ። እነሱን ለመርዳት ከተፈለገ ጊዜ፣ ፍቅርና አሳቢነት በመስጠት ስለ እነርሱ መድከም አለባችሁ።
21. ለልጆች ልዩ ትኩረት መስጠት ምን ዋጋ ሊያስገኝ ይችላል?
21 ይሖዋ በአደራ የሰጣችሁን ውድ ፍሬ ተንከባክቦ ለማሳደግ የምታደርጉት ጥረት የሚከፍላችሁ ዋጋ ማንኛውም ገበሬ ከሚያገኘው የተትረፈረፈ ምርት ይበልጥ የሚያረካ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 127:3–5) ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻችሁ ልዩ ትኩረት መስጠታችሁን ቀጥሉ። ለልጆቻችሁ ጥቅምና ለሰማያዊ አባታችን ለይሖዋ ክብር ስትሉ ይህን አድርጉት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አትክልቶችንና ልጆችን ማሳደግ እንዴት ሊመሳሰል ይችላል?
◻ አንድ ልጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በየቀኑ ምን ዓይነት ትኩረት ማግኘት ያስፈልገዋል?
◻ ልጆች ምን ልዩ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል? ይህስ እንዴት ሊሰጣቸው ይችላል?
◻ ለልጆቻችሁ ልዩ ትኩረት መስጠት ያለባችሁ ለምንድን ነው?