-
የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉመጠበቂያ ግንብ—2002 | መስከረም 15
-
-
‘ከተረት’ ራቁ
8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን እምነታችንን ለማጥፋት የሚጥረው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4 ላይ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
8 ሰይጣን በተማርናቸው ትምህርቶች ላይ ጥርጣሬ በመዝራት ጽኑ አቋማችንን ለማበላሸት ይጥራል። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ከሐዲዎችና ሌሎች የቅን ክርስቲያኖችን እምነት ለማጥፋት ይጥራሉ። (ገላትያ 2:4፤ 5:7, 8) አንዳንድ ጊዜ በመገናኛ ብዙሐን አማካኝነት ስለ ይሖዋ ሕዝቦች እንቅስቃሴና ዓላማ የተዛባ አልፎ ተርፎም የሐሰት ወሬ ያሰራጫሉ። ጳውሎስ እንዳስጠነቀቀው አንዳንዶች እውነትን ይተዋሉ። “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፣ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ” በማለት ጽፏል።—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4
9. ጳውሎስ ‘ተረት’ ብሎ ሲናገር በአእምሮው የያዘው ምን ሊሆን ይችላል?
9 አንዳንዶች የጤናማውን ቃል ምሳሌ ከመያዝ ይልቅ ‘በተረት’ ተስበው ነበር። እነዚህ ተረቶች ምንድን ናቸው? ምናልባት ጳውሎስ በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ጦቢት ያሉ ምናባዊ አፈ ታሪኮችን አስመልክቶ መናገሩ ሊሆን ይችላል።a እነዚህ ተረቶች ስሜት የሚመስጡና ግምታዊ ሐሳቦችን የሚያካትቱ ሊሆኑ ይችላል። ከዚህም በላይ አንዳንዶች አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች አቅልሎ የማየት አመለካከትን በሚያራምዱ ወይም በጉባኤ ውስጥ ግምባር ቀደም ሆነው በሚያገለግሉ ወንዶች ላይ ነቀፋ በሚሰነዝሩ ሰዎች ተታልለው “እንደ ገዛ ምኞታቸው” መመላለስ ጀምረው ይሆናል። (3 ዮሐንስ 9, 10፤ ይሁዳ 4) ሰበብ የሆናቸው ነገር ምንም ይሁን ምን አንዳንዶች ከአምላክ ቃል እውነት ይልቅ ውሸትን እንደመረጡ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ብዙም ሳይቆይ የተማሯቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ማዋል ያቆሙ ሲሆን ይህም በመንፈሳዊነታቸው ላይ ውድቀት አስከትሎባቸዋል።—2 ጴጥሮስ 3:15, 16
10. በጊዜያችን የሚነገሩ አንዳንድ ተረቶች የትኞቹ ናቸው? ሐዋርያው ዮሐንስ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
10 እኛም የምናዳምጠውንና የምናነበውን ነገር በጥንቃቄ የምንመርጥ ከሆነ ተማርከን ተረት አናዳምጥም። ለምሳሌ ያህል አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙሐን የሥነ ምግባር ብልግና ይቀርባል። ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ወይም ከነጭራሹ አምላክ የሚባል የለም የሚል ትምህርት ያስፋፋሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ በሚናገረው ሐሳብ ላይ ይሳለቃሉ። እንዲሁም በዘመናችን ያሉ ከሃዲዎች የክርስቲያኖችን እምነት ለማዳከም የጥርጣሬ ዘር ለመዝራት ጥረት ያደርጋሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሐሰተኛ ነቢያት የፈጠሩትን ተመሳሳይ አደጋ በተመለከተ ሲያስጠነቅቅ “ወዳጆች ሆይ፣ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” ብሏል። (1 ዮሐንስ 4:1) ስለዚህ ጠንቃቃ መሆን ይገባናል።
11. በሃይማኖት እንደምንኖር ራሳችንን መፈተንና መመርመር የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
11 ጳውሎስ ይህን በማስመልከት “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) ሐዋርያው ከአጠቃላዩ የክርስትና እምነት ጋር ተስማምተን የምንኖር መሆናችንን ለማወቅ አለማቋረጥ ራሳችንን እንድንመረምር አሳስቦናል። ባላቸው የማይረኩ ሰዎች የሚናገሩትን የማዳመጥ ዝንባሌ ካለን ራሳችንን በጸሎት መመርመር ይገባናል። (መዝሙር 139:23, 24) በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ስህተት የመለቃቀም ዝንባሌ አለን? ከሆነ፣ ለምን? አንድ ወንድም በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ተጎድተናል? እንደዚያ ከሆነ፣ ለሁኔታው ተገቢ አመለካከት መያዝ እንችላለን? በዚህ ሥርዓት የሚደርስብን ማንኛውም ዓይነት መከራ ጊዜያዊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:17) በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን እንኳ አምላክን ማገልገል የምናቆምበት ምን ምክንያት አለ? የተጎዳንበት ነገር ካለ ችግሩን ለመፍታት የቻልነውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ መተዉ የተሻለ አይሆንም?—መዝሙር 4:4፤ ምሳሌ 3:5, 6፤ ኤፌሶን 4:26
12. የቤሪያ ሰዎች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑን እንዴት ነው?
12 የተቺነት ዝንባሌ ከመያዝ ይልቅ በግል ጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት ለምናገኛቸው ትምህርቶች በመንፈሳዊ ጤናማ የሆነ አመለካከት እንያዝ። (1 ቆሮንቶስ 2:14, 15) ደግሞም የአምላክን ቃል ከመጠራጠር ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቅ ይመረምሩ የነበሩትን የቤሪያ ሰዎች ዝንባሌ መያዙ ምንኛ የተሻለ ነው! (ሥራ 17:10, 11) እንዲሁም ከተረት ርቀን እውነትን አጥብቀን በመያዝ የተማርነውን በሥራ ላይ እናውል።
13. እንደ ተረት ያለ መሠረተ ቢስ ወሬ ሳናስበው ልናሰራጭ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ልናስወግደው የሚገባ ሌላም የተረት ዓይነት አለ። አብዛኛውን ጊዜ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰራጩ እጅግ በርካታ ቀልብ የሚስቡ ዘገባዎች አሉ። በተለይ አንድ መረጃ ከማን እንደተላከ የማናውቅ ከሆነ ጥንቃቄ ማድረጋችን ጥበብ ነው። አንድ ተሞክሮ ወይም ታሪክ የደረሰን ከአንድ ከምናምነው ክርስቲያን ቢሆንም እንኳ ግለሰቡ እውነታዎቹን በተመለከተ በቀጥታ የሚያውቀው ነገር ላይኖር ይችላል። ያልተረጋገጡ ዘገባዎችን ለሌሎች ማውራትን ወይም መላክን በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ‘እግዚአብሔርን የማያስከብር ርባና ቢስ አፈ ታሪክ’ [አ.መ.ት ] ወይም ‘ለዚህ ዓለም የሚመች ተረት’ ለሌሎች ማውራት እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:7) በተጨማሪም እርስ በርሳችን እውነትን የመነጋገር ግዴታ ስላለብን ሳናስበው ውሸት እንድንናገር የሚያደርገንን ማንኛውንም ነገር ማስወገዳችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ኤፌሶን 4:25
-
-
የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉመጠበቂያ ግንብ—2002 | መስከረም 15
-
-
a መጽሐፈ ጦቢት በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደተጻፈ የሚገመት ሲሆን ጦቢያስ ስለተባለ አንድ አይሁዳዊ ሰው የሚናገር በአጉል እምነት የተሞላ ታሪክ ነው። ይህ ሰው የአንድ አስፈሪ አሣ ልብ፣ የሐሞት ከረጢትና ጉበት በመጠቀም በሽታ የመፈወስና አጋንንት የማውጣት ኃይል እንዳለው ይነገርለት ነበር።
-