የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018 | ጥር
    • 2. ከአምላክ የራቁ ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅር ምን ዓይነት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

      2 በሌላ በኩል ግን ከላይ ከተጠቀሰው በጣም የተለየ ዓይነት ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎችም በዚህ ዘመን እንደሚኖሩ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ተናግረዋል፤ ከአምላክ የራቁት እነዚህ ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅር ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞ. 3:1-4) እነዚህ ሰዎች የሚያሳዩት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር ጋር ይቃረናል። ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸው ግቦችን የሚያሳድዱ ሰዎች የሚፈልጉትን ደስታ አያገኙም። እንዲያውም እንዲህ ያለው ፍቅር፣ ዓለማችን ራስ ወዳድ በሆኑ ግለሰቦች የተሞላና “ለመቋቋም የሚያስቸግር” እንዲሆን አድርጓል።

  • እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018 | ጥር
    • አምላክን መውደድ ወይስ ራስን መውደድ?

      4. ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ራስን መውደድ ስህተት እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

      4 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። ታዲያ ራስን መውደድ ስህተት ነው ማለት ነው? አይደለም፤ እንዲያውም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ራስን መውደድ፣ ተገቢ ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ነው። ይሖዋ የፈጠረን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን አድርጎ ነው። ኢየሱስም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማር. 12:31) ራሳችንን የማንወድ ከሆነ ባልንጀራችንን መውደድ አንችልም። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቱን የሚወድ ሰው ራሱን ይወዳል፤ የገዛ አካሉን የሚጠላ ማንም ሰው የለምና፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል።” (ኤፌ. 5:28, 29) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በተገቢው መጠን ራሳችንን ልንወድ ይገባል።

      ራሷን ከሚገባው በላይ የምትወድ ሴት

      5. ራሳቸውን ከመጠን በላይ ስለሚወዱ ሰዎች ምን ማለት ይቻላል?

      5 በ2 ጢሞቴዎስ 3:2 ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ፍቅር ተገቢ ከሆነው ፍቅር የተለየ ነው። ጳውሎስ የተናገረው ራሳቸውን ከመጠን በላይ ስለሚወዱ ሰዎች ነው። እንዲህ ያሉት ራስ ወዳድ ሰዎች ከሚገባው በላይ ስለ ራሳቸው ያስባሉ። (ሮም 12:3⁠ን አንብብ።) በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚሰጡት ለራሳቸው ስለሆነ ለሌሎች ያን ያህል ግድ የላቸውም። የሆነ ስህተት ሲፈጠር ጥፋታቸውን ከማመን ይልቅ በሌሎች ላይ ማሳበብ ይቀናቸዋል። ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እውነተኛ ደስታ የላቸውም።

      6. አምላክን የሚወዱ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

      6 ጳውሎስ በመጨረሻዎቹ ቀናት በስፋት እንደሚታዩ ከጠቀሳቸው መጥፎ ባሕርያት መካከል መጀመሪያ ላይ ያስቀመጠው ራስን መውደድን ነው፤ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚናገሩት ጳውሎስ እንዲህ ያደረገው አንድ ሰው፣ ሌሎቹን መጥፎ ባሕርያት እንዲያንጸባርቅ የሚያነሳሳው ራስ ወዳድነት ስለሆነ ነው። ከዚህ በተቃራኒ አምላክን የሚወዱ ሰዎች መልካም ባሕርያትን ያንጸባርቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንድናዳብር የሚፈልገውን ዓይነት ፍቅር ከደስታ፣ ከሰላም፣ ከትዕግሥት፣ ከደግነት፣ ከጥሩነት፣ ከእምነት፣ ከገርነትና ራስን ከመግዛት ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ገላ. 5:22, 23) መዝሙራዊው “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” በማለት ጽፏል። (መዝ. 144:15) ይሖዋ ደስተኛ አምላክ ነው፤ ሕዝቡም ቢሆን ደስተኛ ነው። ከዚህም ሌላ ራሳቸውን ከሚወዱና ከሌሎች ስለሚያገኙት ነገር ብቻ ከሚያስቡ ሰዎች በተለየ የይሖዋ አገልጋዮች ለሌሎች በመስጠት ደስታ ያገኛሉ።—ሥራ 20:35

      አገልግሎት ላይ ያለች እህት

      ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

      7. አምላክን ከራሳችን አስበልጠን እንደምንወደው ለማወቅ የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል?

      7 አምላክን ከራሳችን አስበልጠን እንደምንወደው ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በፊልጵስዩስ 2:3, 4 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ልብ እንበል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።” ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህን ምክር በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ? የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ከልቤ እጥራለሁ? በጉባኤ ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ላይ ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እፈልጋለሁ?’ እርግጥ ነው፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሌሎችን ለመርዳት ማዋል ሁልጊዜ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። የራሳችንን ጥቅም መሠዋት ብሎም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊኖርብን ይችላል። ይሁንና የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢ ሞገስ እንዳገኘን ከማወቅ በላይ ምን ሊያስደስተን ይችላል?

      8. አንዳንዶች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?

      8 አንዳንዶች ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ሲሉ፣ ዳጎስ ያለ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ሥራቸውን ትተዋል፤ ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን ኤሪካን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኤሪካ ሐኪም ብትሆንም በዚህ ሙያ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከመጣር ይልቅ የዘወትር አቅኚ ሆነች፤ በተጨማሪም ከባለቤቷ ጋር ሆነው ወደተለያዩ አገሮች እየሄዱ አገልግለዋል። እንዲህ ብላለች፦ “የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ ስናገለግል ያገኘናቸው በርካታ ተሞክሮዎች እንዲሁም ያፈራናቸው ወዳጆች ሕይወታችን በጣም አስደሳች እንዲሆን አድርገዋል። አሁንም ቢሆን ሐኪም ሆኜ መሥራቴን አልተውኩም፤ ሆኖም ጊዜዬንና ጉልበቴን በዋነኝነት የማውለው ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳትና በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ለማከናወን መሆኑ ልባዊ ደስታና ጥልቅ እርካታ አስገኝቶልኛል።”

      በሰማይ ያለ ሀብት ወይስ በምድር ያለ ሀብት?

      ቁሳዊ ነገሮችን የሚወድ ሰው

      9. ገንዘብን መውደድ ደስታ የማያስገኘው ለምንድን ነው?

      9 ጳውሎስ፣ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች “ገንዘብ የሚወዱ” እንደሚሆኑ ጽፏል። በአየርላንድ የሚኖር አንድ አቅኚ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከአንድ ሰው ጋር ስለ አምላክ ተወያይቶ ነበር። ሰውየው ከኪስ ቦርሳው ውስጥ ገንዘብ አውጥቶ ለወንድም እያሳየ “የእኔ አምላክ ይሄ ነው!” በማለት በኩራት ተናገረ። ብዙዎች እንደዚህ ሰው አመለካከታቸውን በግልጽ ባይናገሩም ዓለማችን ገንዘብንና ገንዘብ የሚገዛቸውን ነገሮች በሚወዱ ሰዎች የተሞላ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ብርን የሚወድ ብርን አይጠግብም፤ ሀብትንም የሚወድ በሚያገኘው ገቢ አይረካም” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (መክ. 5:10) ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች ምንጊዜም ተጨማሪ ለማግኘት ይጥራሉ እንጂ በቃኝ አይሉም፤ ይህ ደግሞ “ብዙ ሥቃይ” ያስከትልባቸዋል።—1 ጢሞ. 6:9, 10

      10. መጽሐፍ ቅዱስ ሀብትንና ድህነትን በተመለከተ ምን ይላል?

      10 ሁላችንም ገንዘብ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። ገንዘብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጥበቃ ያስገኛል። (መክ. 7:12) ይሁን እንጂ ለመሠረታዊ ፍላጎቶቹ ብቻ የሚበቃ ገንዘብ ያለው ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል? አዎ ይችላል! (መክብብ 5:12⁠ን አንብብ።) የያቄ ልጅ አጉር “ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ። ብቻ የሚያስፈልገኝን ቀለብ አታሳጣኝ” ሲል ጽፏል። አጉር በድህነት መቆራመድ ያልፈለገበትን ምክንያት መረዳት አይከብደንም። ቀጥሎ እንደተናገረው ድህነት ወደ ስርቆት ሊመራው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአምላክን ስም ያሰድባል። አጉር “ባለጸጋ አታድርገኝ” በማለት የጸለየውስ ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “አለዚያ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ከዚያም ‘ይሖዋ ማን ነው?’ እላለሁ።” (ምሳሌ 30:8, 9) አንተም ከአምላክ ይልቅ በሀብታቸው የሚታመኑ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል።

      11. ኢየሱስ ገንዘብን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?

      11 ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች አምላክን ማስደሰት አይችሉም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።” ኢየሱስ ይህን ምክር ከመስጠቱ በፊት እንደሚከተለው በማለት ተናግሮ ነበር፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።”—ማቴ. 6:19, 20, 24

      12. አኗኗርን ቀላል ማድረግ አምላክን ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

      12 ብዙዎች አኗኗራቸውን ቀላል ማድረጋቸው ይበልጥ ደስተኞች ለመሆን ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ለማገልገል ተጨማሪ ጊዜ አስገኝቶላቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ጃክ ከባለቤቱ ጋር በአቅኚነት ለማገልገል ስለፈለገ የነበራቸውን ትልቅ ቤትና ድርጅታቸውን ሸጠ። ጃክ እንዲህ ብሏል፦ “ከከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን የሚያምር ቤታችንንና ንብረታችንን ለመሸጥ መወሰን ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ ለዓመታት፣ በሥራ ቦታ በሚያጋጥሙኝ ችግሮች የተነሳ ወደ ቤት የምመለሰው እየተበሳጨሁ ነበር። የዘወትር አቅኚ የሆነችው ባለቤቴ ግን ምንጊዜም ደስተኛ ናት። ‘የእኔ አለቃ ከማንም የተሻለ ነው!’ ትለኝ ነበር። አሁን እኔም አቅኚ ስለሆንኩ ሁለታችንም የምንሠራው ለአንድ አካል ይኸውም ለይሖዋ ነው።”

      በመዋጮ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ ማስገባት

      ለገንዘብና ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

      13. ለገንዘብ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆኑን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?

      13 ለገንዘብ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆኑን ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠቀም ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመራችን ጠቃሚ ነው፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን በተመለከተ የሚሰጠውን ምክር ከልቤ አምንበታለሁ? አኗኗሬስ ይህን ያሳያል? በሕይወቴ ውስጥ ከምንም በላይ የሚያሳስበኝ ገንዘብ የማግኘት ጉዳይ ነው? ከይሖዋና ከሰዎች ጋር ካለኝ ወዳጅነት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለቁሳዊ ነገሮች ነው? ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንደሚያሟላልኝ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ?’ ይሖዋ እሱን ተስፋ የሚያደርጉትን መቼም ቢሆን እንደማያሳፍራቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴ. 6:33

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ