ምዕራፍ 5
መንጋውን በእረኝነት የሚጠብቁ የበላይ ተመልካቾች
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት “ጥሩ እረኛ” መሆኑን በተግባር አሳይቷል። (ዮሐ. 10:11) በአንድ ወቅት፣ ከእሱ ለመማር በመጓጓት ይከተለው የነበረውን ብዙ ሕዝብ ሲመለከት “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ኢየሱስ ያሳየውን ፍቅራዊ አሳቢነት አስተውለው ነበር። ኢየሱስ በጎቹ እስኪበታተኑና መንፈሳዊ ጠኔ እስኪይዛቸው ድረስ መንጋውን ችላ ብለው ከነበሩት ሐሰተኛ የእስራኤል እረኞች ፈጽሞ የተለየ ነው! (ሕዝ. 34:7, 8) ኢየሱስ በማስተማርም ሆነ ለበጎቹ ካለው አሳቢነት የተነሳ ሕይወቱን ጭምር በመስጠት የተወውን ግሩም አርዓያ ሐዋርያቱ መመልከታቸው እነሱም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ‘የነፍሳቸው እረኛና ጠባቂ’ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ሊመልሷቸው የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል።—1 ጴጥ. 2:25
2 በአንድ ወቅት ኢየሱስ ጴጥሮስን ሲያነጋግረው፣ በጎቹን መመገቡና በእረኝነት መጠበቁ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አበክሮ ገልጾለታል። (ዮሐ. 21:15-17) ጴጥሮስ በኢየሱስ አነጋገር ልቡ ተነክቶ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፤ ከዓመታት በኋላም በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾችን እንዲህ ሲል አጥብቆ መክሯቸዋል፦ “የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ጠብቁ፤ ሥራችሁን በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ተወጡ፤ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት፣ የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።” (1 ጴጥ. 5:1-3) ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉትን የበላይ ተመልካቾችም ይመለከታል። ሽማግሌዎች የኢየሱስን አርዓያ የሚከተሉ ከመሆኑም ሌላ ለመንጋው ምሳሌ በመሆን በፈቃደኝነትና በቅንዓት ግንባር ቀደም ሆነው ይሖዋን ያገለግላሉ።—ዕብ. 13:7
ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሆነው ይሖዋን በፈቃደኝነትና በቅንዓት በማገልገል ለመንጋው ምሳሌ ይሆናሉ፤ እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ
3 በጉባኤ ውስጥ በመንፈስ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች በመኖራቸው አመስጋኝ ልንሆን ይገባል። ከሚያደርጉልን እንክብካቤ ብዙ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የበላይ ተመልካቾች በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ ሁሉንም ለማበረታታት ጥረት ያደርጋሉ። በየሳምንቱ ሁላችንም መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝባቸውን የጉባኤ ስብሰባዎች በትጋት ይመራሉ። (ሮም 12:8) ሽማግሌዎች፣ መንጋው ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ አካላት (ለምሳሌ ከክፉ ሰዎች) ጥበቃ እንድናገኝ የሚያደርጉት ጥረት መንፈሳዊ ደህንነታችን ለአደጋ እንዳይጋለጥ ያስችላል። (ኢሳ. 32:2፤ ቲቶ 1:9-11) በመስክ አገልግሎት ግንባር ቀደም ሆነው ሲሳተፉ ማየታችን ምሥራቹን ሳንሰብክ አንድም ወር እንዳያልፈን ያበረታታናል። (ዕብ. 13:15-17) ይሖዋ ‘ስጦታ በሆኑት በእነዚህ ሰዎች’ አማካኝነት ጉባኤውን ለማነጽ የሚያስፈልገውን ነገር አቅርቧል።—ኤፌ. 4:8, 11, 12
የበላይ ተመልካቾች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶች
4 ጉባኤው ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኝ፣ የበላይ ተመልካች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚሾሙ ወንዶች በአምላክ ቃል ውስጥ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርባቸዋል። በመንፈስ ቅዱስ ተሹመዋል ሊባል የሚችለው ብቃቱን ካሟሉ ብቻ ነው። (ሥራ 20:28) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ያለባቸው ኃላፊነት ከባድ ስለሆነ ከእነሱ የሚፈለጉት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርቶች በጣም ከፍ ያሉ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ መሥፈርቶች በጣም ከፍ ያሉ ናቸው ሲባል ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ያላቸውና የእሱ መሣሪያ ሆነው ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ክርስቲያን ወንዶች ሊያሟሏቸው አይችሉም ማለት አይደለም። የበላይ ተመልካቾች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግባራዊ ማድረጋቸው ለሁሉም በግልጽ መታየት ይኖርበታል።
የበላይ ተመልካች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚሾሙ ወንዶች በአምላክ ቃል ውስጥ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርባቸዋል፤ ይህም ጉባኤው ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኝ ያስችላል
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤውና ለቲቶ በላከው ደብዳቤ ላይ የበላይ ተመልካቾች የሚጠበቁባቸውን መሠረታዊ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ዘርዝሯል። አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:1-7 እንዲህ ይላል፦ “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል። ስለዚህ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ በልማዶቹ ልከኛ የሆነ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ የማስተማር ብቃት ያለው፣ የማይሰክር፣ ኃይለኛ ያልሆነ፣ ይልቁንም ምክንያታዊ የሆነ፣ የማይጣላ፣ ገንዘብ ወዳድ ያልሆነ፣ ታዛዥና ቁም ነገረኛ የሆኑ ልጆች ያሉትና የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባዋል፤ (ደግሞስ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?) በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ እንዳይፈረድበት አዲስ ክርስቲያን አይሁን። ከዚህም በተጨማሪ እንዳይነቀፍና በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በመልካም የተመሠከረለት ሊሆን ይገባል።”
6 ጳውሎስ ለቲቶ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “አንተን በቀርጤስ የተውኩህ ያልተስተካከሉትን ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው፤ ይኸውም ከክስ ነፃ የሆነ፣ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም በስድነት ወይም በዓመፀኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ካለ እንድትሾም ነው። ምክንያቱም የበላይ ተመልካች በአምላክ የተሾመ መጋቢ እንደመሆኑ መጠን ከክስ ነፃ መሆን አለበት፤ በራሱ ሐሳብ የሚመራ፣ ግልፍተኛ፣ ሰካራም፣ ኃይለኛና አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚስገበገብ ሊሆን አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ጻድቅ፣ ታማኝ፣ ራሱን የሚገዛ፣ እንዲሁም ትክክለኛ በሆነው ትምህርት ማበረታታትም ሆነ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትን መውቀስ ይችል ዘንድ የማስተማር ጥበቡን ሲጠቀም የታመነውን ቃል በጥብቅ የሚከተል ሊሆን ይገባል።”—ቲቶ 1:5-9
7 ከበላይ ተመልካቾች የሚጠበቁት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች መጀመሪያ ላይ በጣም ከባድ ቢመስሉም ክርስቲያን ወንዶች የበላይ ተመልካች ለመሆን ከመጣጣር መሸሽ አይኖርባቸውም። ከበላይ ተመልካቾች የሚጠበቁትን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ሲያንጸባርቁ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች የእነሱን ምሳሌ ለመከተል ይነሳሳሉ። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ‘ስጦታ ሆነው የተሰጡት’ ለምን እንደሆነ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ያደረገው ቅዱሳንን እንዲያስተካክሉ፣ ሌሎችን እንዲያገለግሉና የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ ነው፤ ይህም ሁላችንም በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆን ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ ነው።”—ኤፌ. 4:8, 12, 13
8 የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙ ወንዶች፣ ገና ልጆች ወይም አዲስ ክርስቲያኖች መሆን የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ በክርስቲያናዊ አኗኗር ተሞክሮ ያካበቱ፣ ሰፊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላቸው፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት የሚረዱ እንዲሁም ለጉባኤው ልባዊ ፍቅር ያላቸው ግለሰቦች ናቸው። መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን በድፍረት ከመናገርና ከማረም ወደኋላ አይሉም፤ ይህም ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች መንጋውን መጠቀሚያ እንዳያደርጉት ለመከላከል ያስችላል። (ኢሳ. 32:2) የበላይ ተመልካቾቹ በመንፈሳዊ የጎለመሱና ለአምላክ መንጋ ከልብ የሚያስቡ ሰዎች መሆናቸውን በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ ይቀበላሉ።
9 የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙ ወንዶች ሕይወታቸውን በጥበብ እንደሚመሩ መታየት አለበት። አንድ የበላይ ተመልካች ያገባ ከሆነ ትዳርን በተመለከተ የወጣውን ክርስቲያናዊ መሥፈርት በጥብቅ ይከተላል፤ ይህም ማለት የአንዲት ሚስት ባል ሊሆን ይገባል እንዲሁም የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር ይኖርበታል። የበላይ ተመልካቹ ታዛዥና ቁም ነገረኛ የሆኑ እንዲሁም በስድነት ወይም በዓመፀኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ካሉት በጉባኤው ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች የቤተሰብ ሕይወትንና ክርስቲያናዊ አኗኗርን በተመለከተ ምክርና ማበረታቻ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ሆነው ወደ እሱ ሊመጡ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ አንድ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ እና ከክስ ነፃ እንዲሁም በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ ጭምር በመልካም የተመሠከረለት መሆን አለበት። የጉባኤውን ስም የሚያጎድፍ ተገቢ ያልሆነ ምግባር ፈጽሟል የሚል መሠረት ያለው ክስ የሚሰነዘርበት ሊሆን አይገባም። ከባድ ስህተት በመፈጸሙ በቅርቡ ተግሣጽ የተሰጠው መሆን የለበትም። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች አስፋፊዎች የእሱን መልካም አርዓያ ለመኮረጅ ሊነሳሱ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚችል ሊተማመኑበት ይገባል።—1 ቆሮ. 11:1፤ 16:15, 16
10 እንዲህ ያሉት ብቃት ያላቸው ወንዶች፣ “ጥበበኛና አስተዋይ የሆኑ እንዲሁም ተሞክሮ ያካበቱ” ተብለው ከተገለጹት የእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር የሚመሳሰል ሚና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሊጫወቱ ይችላሉ። (ዘዳ. 1:13) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከኃጢአት ነፃ አይደሉም፤ ያም ሆኖ አምላክ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ሕይወት በመምራት በጉባኤውም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅንና አምላክን የሚፈሩ ሰዎች መሆናቸውን አስመሥክረዋል። ነቀፋ የሌለባቸው መሆናቸው በጉባኤው ፊት በነፃነት እንዲናገሩ ያስችላቸዋል።—ሮም 3:23
11 የበላይ ተመልካች ሆነው ለመሾም የሚበቁ ወንዶች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነትም ሆነ በልማዳቸው ልከኛ ናቸው። ጽንፈኞች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በአኗኗራቸው ሚዛናዊና ራሳቸውን የሚገዙ ናቸው። በመብል፣ በመጠጥ፣ በመዝናኛ፣ በትርፍ ጊዜ በሚሠሩ ነገሮችና እነዚህን በመሳሰሉ ሁኔታዎች ልከኛ መሆናቸውን ያሳያሉ። ሰካራም ተብለው እንዳይከሰሱ በአልኮል መጠጥ ረገድ ልከኛ ይሆናሉ። የሚያሰክር መጠጥ ወስዶ ስሜቱ የደነዘዘበት ሰው ራሱን መግዛት ያቅተዋል፤ ስለዚህ ለጉባኤው መንፈሳዊ ጉዳዮች ተገቢውን ትኩረት መስጠት አይችልም።
12 አንድ ሰው የጉባኤውን ጉዳዮች ለመምራት በቅድሚያ ሥርዓታማ መሆኑ መታየት ይኖርበታል። ውጪያዊ ቁመናው፣ ቤቱን የሚይዝበት መንገድና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ጥሩ ልማድ እንዳለው የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል። እንደዚህ ያለው ሰው ዛሬ ነገ እያለ ሥራ አያጓትትም፤ ምን እንደሚያስፈልግ በማስተዋል አስፈላጊውን ዕቅድ ያወጣል። ደግሞም አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ይከተላል።
13 አንድ የበላይ ተመልካች ምክንያታዊ መሆን ይኖርበታል። በጉባኤው ውስጥ ካሉ ሌሎች ሽማግሌዎች ጋር ያለውን አንድነት መጠበቅና ተባብሮ መሥራት መቻል አለበት። ስለ ራሱ የተጋነነ አመለካከት ሊኖረው አይገባም፤ እንዲሁም ከሌሎች ብዙ መጠበቅ የለበትም። ምክንያታዊ ሰው መሆኑ ሁልጊዜ የእሱ አመለካከት ከሌሎች ሽማግሌዎች የተሻለ እንደሆነ በማሰብ ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ እንዳይል ይረዳዋል። በአንዳንድ ባሕርያት ወይም ችሎታዎች ረገድ ሌሎች ከእሱ ሊበልጡ ይችላሉ። አንድ ሽማግሌ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳየው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ አቋም በመያዝና የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት በማድረግ ነው። (ፊልጵ. 2:2-8) አንድ ሽማግሌ ኃይለኛ መሆን ወይም መጣላት አይኖርበትም፤ ከዚህ ይልቅ ሌሎች ከእሱ እንደሚልቁ አድርጎ በማሰብ ተገቢ አክብሮት ያሳያል። በራሱ ሐሳብ አይመራም፤ በሌላ አባባል ሌሎች ሁልጊዜ የእሱን መንገድ ወይም አመለካከት እንዲቀበሉ ጫና አያሳድርም። ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ሰላማዊ እንጂ ግልፍተኛ አይደለም።
14 ከዚህም ሌላ በጉባኤው ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ለማገልገል የሚሾም ሰው ጤናማ አስተሳሰብ ያለው መሆን ይኖርበታል። ይህም ማለት ለመፍረድ የማይቸኩል አስተዋይ ሰው ይሆናል ማለት ነው። ይሖዋ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን እንደሆኑና እንዴት በሥራ ላይ እንደሚውሉ ጥሩ ግንዛቤ አለው። ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው ምክርና መመሪያ ሲሰጠው በትሕትና ይቀበላል። እንዲሁም ግብዝ አይደለም።
15 ጳውሎስ አንድ የበላይ ተመልካች ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ መሆን እንዳለበት ቲቶን አሳስቦታል። ጻድቅ እና ታማኝ መሆን አለበት። ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት እንዲሁም ትክክልና ጥሩ ለሆነው ነገር በሚወስደው ጽኑ አቋም እነዚህን ባሕርያት ያንጸባርቃል። ምንጊዜም ለይሖዋ ያደረ ከመሆኑም ሌላ ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጎን በታማኝነት ይቆማል። ሚስጥር ጠባቂም ነው። በተጨማሪም ራሱንም ሆነ ንብረቱን በፈቃደኝነት ለሌሎች ጥቅም በመስጠት ከልቡ እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ያሳያል።—ሥራ 20:33-35
16 አንድ የበላይ ተመልካች ኃላፊነቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያከናውን ከተፈለገ የማስተማር ብቃት ያለው መሆን ይኖርበታል። ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው አንድ የበላይ ተመልካች “ትክክለኛ በሆነው ትምህርት ማበረታታትም ሆነ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትን መውቀስ ይችል ዘንድ የማስተማር ጥበቡን ሲጠቀም የታመነውን ቃል በጥብቅ የሚከተል ሊሆን ይገባል።” (ቲቶ 1:9) የበላይ ተመልካቹ ማብራሪያ መስጠት፣ ማስረጃ ማቅረብ፣ ተቃውሞ ሲሰነዘር አጥጋቢ መልስ መስጠት እንዲሁም ሌሎችን በሚያሳምንና እምነታቸውን በሚያጠነክር መንገድ ጥቅሶችን መጠቀም መቻል አለበት። አመቺ በሆነ ጊዜም ይሁን በአስቸጋሪ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን የማስተማር ችሎታ መጠቀም ይኖርበታል። (2 ጢሞ. 4:2) የተሳሳቱ ሰዎችን በገርነት ለመውቀስ ወይም ተጠራጣሪ የሆኑትን ለማሳመንና በእምነት ላይ የተመሠረቱ ጠቃሚ ሥራዎች እንዲያከናውኑ ለማነሳሳት የሚያስችል ትዕግሥት አለው። አንድ የበላይ ተመልካች በስብሰባዎች ላይ ወይም በግለሰብ ደረጃ ሰዎችን ጥሩ አድርጎ የማስተማር ችሎታ ካለው ወሳኝ የሆነውን የማስተማር ብቃት አሟልቷል ሊባል ይችላል።
17 ሽማግሌዎች በአገልግሎት ቀናተኛ መሆናቸው አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የኢየሱስን አርዓያ ለመከተል ጥረት እንደሚያደርጉ በግልጽ መታየት ይኖርበታል፤ ኢየሱስ ምሥራቹን ለመስበኩ ሥራ ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። እንዲያውም ደቀ መዛሙርቱ ውጤታማ ወንጌላውያን እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ረድቷቸዋል። (ማር. 1:38፤ ሉቃስ 8:1) ሽማግሌዎች ሥራ የሚበዛባቸው ቢሆንም ሳያሰልሱ በአገልግሎት መካፈላቸው መላው ጉባኤ ተመሳሳይ ቅንዓት እንዲያሳይ ያነሳሳል። እንዲሁም ሽማግሌዎች ከቤተሰባቸው እንዲሁም ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር አብረው መስበካቸው ‘እርስ በርስ መበረታታት’ የሚችሉበት አጋጣሚ ይከፍታል።—ሮም 1:11, 12
18 ይህን ሁሉ ስንመለከት ከአንድ የበላይ ተመልካች በጣም ብዙ እንደሚጠበቅ ሊሰማን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ላቅ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ አንድም የበላይ ተመልካች ሊኖር አይችልም፤ ሆኖም በጉባኤው ውስጥ ያለ ማንኛውም የተሾመ ሽማግሌ ሌሎች ትልቅ ድክመት እንዳለበት ሆኖ እስኪሰማቸው ድረስ ከእነዚህ መመዘኛዎች በአንዱም እንኳ የጎላ ችግር ሊታይበት አይገባም። አንዳንድ ሽማግሌዎች በተወሰኑ ባሕርያት ልቀው ሲገኙ የተቀሩት ደግሞ በሌሎች መስኮች የተሻሉ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። በውጤቱም መላው የሽማግሌዎች አካል የአምላክን ጉባኤ በሚገባ ለማስተዳደር የሚያስፈልጉት መልካም ባሕርያት በሙሉ ይኖሩታል።
19 የሽማግሌዎች አካል፣ የበላይ ተመልካች ለመሆን ይበቃሉ ብሎ የሚያምንባቸውን ወንዶች ለሹመት ሲያቀርብ ጳውሎስ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፦ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው . . . እመክራለሁ።” (ሮም 12:3) እያንዳንዱ ሽማግሌ ራሱን ከሌሎች እንደሚያንስ አድርጎ መመልከት ይኖርበታል። ማንኛውም ሽማግሌ የሌላውን ብቃት በሚመረምርበት ጊዜ “ከልክ በላይ ጻድቅ” መሆን አይኖርበትም። (መክ. 7:16) የሽማግሌዎች አካል ለበላይ ተመልካቾች የወጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች በአእምሯቸው በመያዝ፣ ለሹመት ያጩት ወንድም መሥፈርቶቹን ምክንያታዊ በሆነ መጠን ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ ይወስናሉ። ሽማግሌዎች፣ ለሹመት የታጩትን ወንድሞች ሰብዓዊ አለፍጽምና ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ከአድልዎና ከግብዝነት በመራቅ ለይሖዋ የጽድቅ ሥርዓቶች ተገቢ አክብሮት እንዳላቸውና ለጉባኤው ጥቅም እንደሚያስቡ በሚያሳይ መንገድ የድጋፍ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ። አንድ ወንድም እንዲሾም የድጋፍ ሐሳብ ሲያቀርቡ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ እንዲመራቸው በጸሎት ይጠይቃሉ፤ እንዲሁም ግለሰቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን የሚያሟላ መሆኑን በጥንቃቄ ይመረምራሉ። ይህ ከተጣሉባቸው ከባድ ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ስለሆነ ጳውሎስ “በማንም ሰው ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኩል” ሲል የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርባቸዋል።—1 ጢሞ. 5:21, 22
የመንፈስ ፍሬ
20 መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች በመንፈስ ቅዱስ እንደሚመሩ በተግባር የሚያሳዩ ከመሆኑም ባሻገር የመንፈሱን ፍሬ በሕይወታቸው ያንጸባርቃሉ። ጳውሎስ ዘጠኙ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” እንደሆኑ ገልጿል። (ገላ. 5:22, 23) እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ የበላይ ተመልካቾች ለወንድሞች የእረፍት ምንጭ ናቸው፤ ጉባኤው አንድ ሆኖ ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርብም ይረዳሉ። አኗኗራቸውና የሥራቸው ውጤት እነዚህ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እንደተሾሙ ያረጋግጣል።—ሥራ 20:28
አንድነት ለማስፈን የሚጥሩ ወንዶች
21 ሽማግሌዎች ጉባኤው አንድነት እንዲኖረው ለማድረግ ተባብረው መሥራታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በመካከላቸው የባሕርይ ልዩነት ሊኖር ቢችልም አንድነታቸውን ይጠብቃሉ፤ በሚወያዩበት ጉዳይ ሁሉ ላይ አንድ ዓይነት አቋም ባይኖራቸውም አንዳቸው የሌላውን ሐሳብ በአክብሮት ያዳምጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ እያንዳንዳቸው የሽማግሌዎች አካል ከደረሰበት የመጨረሻ ውሳኔ ጋር ለመስማማትና ውሳኔውን ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። አንድ ሽማግሌ እሺ ባይ መሆኑ ‘ከሰማይ በሆነው ጥበብ’ እንደሚመራ የሚያሳይ ሲሆን ይህ ጥበብ ደግሞ “ሰላማዊ” እና “ምክንያታዊ” ነው። (ያዕ. 3:17, 18) ማንኛውም ሽማግሌ ራሱን ከሌሎቹ ከፍ አድርጎ መመልከት አይኖርበትም፤ ሌሎቹን ለመጫንም አይሞክርም። ሽማግሌዎች ለጉባኤው ጥቅም ሲሉ እንደ አንድ አካል ሆነው ሲያገለግሉ በእርግጥም ከይሖዋ ጋር ተባብረዋል ሊባል ይችላል።—1 ቆሮ. ምዕ. 12፤ ቆላ. 2:19
ብቃቱን ለማሟላት መጣጣር
22 የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶች የበላይ ተመልካች የመሆን ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። (1 ጢሞ. 3:1) ይሁን እንጂ የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል ብዙ ሥራ ማከናወንንና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። አንድ ሽማግሌ የወንድሞችን መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት እነሱን ለማገልገል ራሱን ያቀርባል ማለት ነው። የበላይ ተመልካች ለመሆን መጣጣር ሲባል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ለማሟላት ጥረት ማድረግ ማለት ነው።
አንድ ሰው ያለበት ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል
23 ረዘም ላለ ጊዜ በታማኝነት ያገለገለ አንድ ወንድም ጤንነቱ ሊቃወስ ወይም አቅም ሊያጣ ይችላል። ምናልባት በዕድሜ መግፋት የተነሳ የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነቱን መወጣት ይከብደው ይሆናል። ያም ቢሆን የተሾመ ወንድም እስከሆነ ድረስ እንደ ሽማግሌ ሊታይና ሊከበር ይገባዋል። አቅሙ ውስን ስለሆነ ብቻ ኃላፊነቱን መተው አያስፈልገውም። መንጋውን ለመጠበቅ በትጋት እየሠሩ ላሉ ሽማግሌዎች ሁሉ የሚሰጠው እጥፍ ክብር ለእሱም ሊሰጠው ይገባል።
24 ይሁንና አንድ ወንድም ለማገልገል ያለው አቅም እንዲቀንስ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትና በዚህ የተነሳ ኃላፊነቱን መተዉ የተሻለ እንደሆነ ቢሰማው ሽምግልናውን ሊያቆም ይችላል። (1 ጴጥ. 5:2) ከዚያ በኋላም ቢሆን ሊከበር ይገባዋል። እንደቀድሞው ለሽማግሌዎች የሚመደቡ ሥራዎችና ኃላፊነቶች ባይሰጡትም ለጉባኤው ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል።
በጉባኤ ውስጥ ያሉ የኃላፊነት ቦታዎች
25 ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ይወጣሉ። የበላይ ተመልካቾች የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ፣ ጸሐፊ፣ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች፣ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪና የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች ሆነው ያገለግላሉ። በተጨማሪም በርካታ ሽማግሌዎች የቡድን የበላይ ተመልካቾች ሆነው ያገለግላሉ። ሽማግሌዎቹ በእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ላልተወሰነ ጊዜ ይሠራሉ። እርግጥ ነው፣ ከእነዚህ ሥራዎች አንዱን የያዘ ወንድም ወደ ሌላ ስፍራ ተዛውሮ ቢሄድ ወይም በጤንነቱ ምክንያት ይህንን ኃላፊነት መወጣት ባይችል አሊያም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶቹን ሳያሟላ ቀርቶ ከኃላፊነቱ ቢወርድ ሥራውን የሚረከብ ሌላ ሽማግሌ ይመረጣል። የበላይ ተመልካቾች ቁጥር አነስተኛ በሆነባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ብቃቱን አሟልተው ሽማግሌ ሆነው የሚሾሙ ወንድሞች እስኪገኙ ድረስ አንድ ሽማግሌ ከአንድ በላይ ኃላፊነት ደርቦ ሊይዝ ይችላል።
26 የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው የሽማግሌዎች አካል በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለግላል። ያም ቢሆን የአምላክን መንጋ በመንከባከብ ረገድ ከሌሎቹ ሽማግሌዎች ጋር በትሕትና ይሠራል። (ሮም 12:10፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) ጥሩ የማደራጀት ችሎታ ሊኖረው የሚገባ ከመሆኑም በላይ በትጋት ማስተዳደር መቻል ይኖርበታል።—ሮም 12:8
27 ጸሐፊው የጉባኤውን መዝገብ ይይዛል፤ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የመረጃ ልውውጦችን ለሽማግሌዎች ያሳውቃል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሌላ ሽማግሌ ወይም ጥሩ ችሎታ ያለው የጉባኤ አገልጋይ እንዲረዳው ሊመደብ ይችላል።
28 ለመስክ አገልግሎት የሚደረጉ ዝግጅቶችና አገልግሎትን የሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች በአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሥር ናቸው። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሁሉንም የመስክ አገልግሎት ቡድኖች በየጊዜው መጎብኘት የሚችልበት ፕሮግራም በማውጣት በየወሩ ቅዳሜና እሁድ አንድ ቡድን ይጎበኛል። ጥቂት የአገልግሎት ቡድኖች ብቻ ባሏቸው አነስተኛ ጉባኤዎች ውስጥ እያንዳንዱን ቡድን በዓመት ሁለት ጊዜ ለመጎብኘት ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። በጉብኝቱ ሳምንት የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ይመራል፣ በቡድኑ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር በመስክ አገልግሎት ይካፈላል እንዲሁም አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቅ በሚያደርጉበትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚመሩበት ጊዜ ይረዳቸዋል።
የቡድን የበላይ ተመልካቾች
29 በጉባኤ ውስጥ ካሉት ትልቅ ኃላፊነቶች አንዱ የቡድን የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል ነው። የቡድን የበላይ ተመልካቹ ካሉት ኃላፊነቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ (1) በመስክ አገልግሎት ቡድኑ ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ አስፋፊ መንፈሳዊነት ትኩረት መስጠት፣ (2) በቡድኑ ውስጥ የታቀፈ እያንዳንዱ አስፋፊ በአገልግሎት አዘውታሪ እንዲሆን ብሎም አገልግሎቱ ትርጉም ያለውና አስደሳች እንዲሆንለት መርዳት እንዲሁም (3) በቡድኑ ውስጥ ያሉ የጉባኤ አገልጋዮች የጉባኤ ኃላፊነቶችን ለመሸከም ብቁ እንዲሆኑ ድጋፍና ሥልጠና መስጠት። ይህ የሥራ ምድብ የሚጠይቃቸውን ኃላፊነቶች በሙሉ ለመወጣት የተሻለ ብቃት ያላቸው እነማን እንደሆኑ የሚወስነው የሽማግሌዎች አካል ነው።
30 ይህ የሥራ ምድብ ከሚያስከትላቸው ኃላፊነቶች አንጻር የሚቻል ከሆነ በቡድን የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግሉት ወንድሞች ሽማግሌዎች ቢሆኑ ይመረጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ኃላፊነት ሊረከብ የሚችል ሽማግሌ እስኪገኝ ድረስ ጥሩ ችሎታ ያለው የጉባኤ አገልጋይ በዚህ ቦታ ላይ ሊመደብ ይችላል። አንድ የጉባኤ አገልጋይ ይህን ኃላፊነት እንዲወጣ ከተመደበ የቡድን አገልጋይ ተብሎ ይጠራል፤ ይህ መጠሪያ የሚሰጠው የበላይ ተመልካች ሆኖ ስላልተሾመ ነው። በመሆኑም የቡድን አገልጋዩ፣ ሽማግሌዎች የሚሰጡትን መመሪያ በመከተል ኃላፊነቱን ይወጣል።
31 የቡድን የበላይ ተመልካቹ ከሚያከናውናቸው አስፈላጊ ሥራዎች መካከል አንዱ በመስክ አገልግሎት ግንባር ቀደም መሆን ነው። አዘውታሪ፣ ቀናተኛና ሞቅ ያለ መንፈስ ያለው መሆኑ በቡድኑ ውስጥ ያሉትን ያበረታታል። አስፋፊዎች አንድ ላይ ሆነው መሥራታቸው እርስ በርስ እንዲበረታቱና እንዲረዳዱ ያስችላቸዋል፤ በመሆኑም ለአብዛኞቹ አስፋፊዎች ተስማሚ የሆነ የመስክ ስምሪት ፕሮግራም ማውጣት ያስፈልጋል። (ሉቃስ 10:1-16) የበላይ ተመልካቹ ቡድኑ የሚሠራበት በቂ የአገልግሎት ክልል ምንጊዜም እንዲኖር ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል። በጥቅሉ ሲታይ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባውን የሚመራው እሱ ነው፤ እንዲሁም አስፋፊዎችን መድቦ ያሰማራል። በስምሪት ስብሰባው ላይ መገኘት ካልቻለ ሌላ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ፣ ካልሆነ ደግሞ ጥሩ ብቃት ያለው አስፋፊ ይህን ኃላፊነት እንዲሸፍን ያደርጋል፤ በዚህ መንገድ አስፋፊዎች አስፈላጊውን መመሪያ ማግኘት ይችላሉ።
32 የቡድን የበላይ ተመልካቹ፣ ለአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት አስቀድሞ ዕቅድ በማውጣት የጉብኝቱን ጊዜ በቡድኑ ውስጥ ላሉት አስፋፊዎች ያሳውቃል፤ እንዲሁም ከጉብኝቱ ጥቅም ለማግኘት በጉጉት እንዲጠባበቁ ያደርጋል። በቡድኑ ውስጥ ያሉት ሁሉ ስለ ዝግጅቱ በሚገባ ከተነገራቸው ዝግጅቱን በቅንዓት ሊደግፉ ይችላሉ።
33 በእያንዳንዱ የአገልግሎት ቡድን ውስጥ የሚካተቱት አስፋፊዎች ቁጥር አነስ እንዲል የሚደረገው በዓላማ ነው። ይህም የቡድን የበላይ ተመልካቹ በቡድኑ ከተመደቡት ከሁሉም አስፋፊዎች ጋር በደንብ እንዲተዋወቅ ያስችለዋል። አፍቃሪ እረኛ እንደመሆኑ መጠን ስለ እያንዳንዳቸው ከልብ ያስባል። ከመስክ አገልግሎትና ከጉባኤ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ በቡድኑ ውስጥ ላሉ ሁሉ በግለሰብ ደረጃ እርዳታና ድጋፍ ለመስጠት ጥረት ያደርጋል። በተጨማሪም እያንዳንዱ አስፋፊ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ አይልም። የታመሙ ወይም ከመንፈስ ጭንቀት ጋር የሚታገሉ ወንድሞች የቡድን የበላይ ተመልካቹ በግለሰብ ደረጃ ከሚያደርግላቸው ጉብኝት ጥቅም ያገኛሉ። አንዳንድ አስፋፊዎች ማበረታቻ ወይም ምክር ቢሰጣቸው በጉባኤው ውስጥ ተጨማሪ መብቶች ለማግኘት ሊጣጣሩ ይችላሉ፤ ይህም ወንድሞቻቸውን በተሻለ ሁኔታ የማገልገል አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። የቡድን የበላይ ተመልካቹ በቡድኑ ውስጥ ያሉትን በመርዳት ላይ ማተኮሩ የሚጠበቅ ነገር ነው። ያም ቢሆን ሽማግሌና እረኛ እንደመሆኑ መጠን በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሁሉ ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ችግር ለገጠመው ለማንኛውም አስፋፊ እርዳታ ከመስጠት ወደኋላ አይልም።—ሥራ 20:17, 28
34 የቡድን የበላይ ተመልካቹ ካሉት ኃላፊነቶች አንዱ በአገልግሎት ቡድኑ ውስጥ የተመደቡትን አስፋፊዎች የመስክ አገልግሎት ሪፖርት መሰብሰብ ነው። ከዚያም ሪፖርቶቹን ለጸሐፊው ይሰጣል። እያንዳንዱ አስፋፊ የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን በወቅቱ በመመለስ ከቡድን የበላይ ተመልካቹ ጋር መተባበር ይችላል። በወሩ መጨረሻ ላይ አስፋፊዎቹ ሪፖርታቸውን በቀጥታ ለቡድን የበላይ ተመልካቹ መስጠት ወይም በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ በሚገኘው የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ለመሰብሰብ በተዘጋጀው ሣጥን ውስጥ መክተት ይችላሉ።
የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ
35 የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ የሚያከናውናቸው አንዳንድ ሥራዎች አሉ፤ ኮሚቴው የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪውን፣ ጸሐፊውንና የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን ያቀፈ ነው። የአገልግሎት ኮሚቴው የስብሰባ አዳራሹን ለጋብቻና ለቀብር ንግግሮች የመፍቀድ እንዲሁም አስፋፊዎችን በመስክ አገልግሎት ቡድኖች የመደልደል ኃላፊነት አለበት። ከዚህም ሌላ ይህ ኮሚቴ ለዘወትርና ለረዳት አቅኚነት አገልግሎት ብሎም ለሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን ያጸድቃል። የአገልግሎት ኮሚቴው ሥራውን የሚያከናውነው በሽማግሌዎች አካል አመራር ሥር ሆኖ ነው።
36 ቅርንጫፍ ቢሮው፣ እነዚህ ወንድሞች በተናጠል የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪውና የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካቹ ብሎም የሌሎቹ የሽማግሌዎች አካል አባላት የሥራ ድርሻዎች ምን እንደሆኑ ያሳውቃል።
37 በእያንዳንዱ ጉባኤ ያለው የሽማግሌዎች አካል ከጉባኤው መንፈሳዊ እድገት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በየተወሰነ ጊዜው ይሰበሰባል። በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወቅት ከሚደረገው የሽማግሌዎች ስብሰባ በተጨማሪ እያንዳንዱ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ካለፈ ከሦስት ወር ገደማ በኋላ የሽማግሌዎች ስብሰባ ይካሄዳል። እርግጥ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ሽማግሌዎቹ በማንኛውም ጊዜ ሊሰበሰቡ ይችላሉ።
ለሽማግሌዎች ተገዙ
38 የበላይ ተመልካቾች ፍጹማን አይደሉም፤ ይሁንና ይህ ዝግጅት የይሖዋ በመሆኑ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ ለእነሱ እንዲገዙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። የበላይ ተመልካቾች፣ ለሚያደርጉት ነገር በእሱ ፊት ተጠያቂ ናቸው። እሱንና ቲኦክራሲያዊ አገዛዙን በመወከል ይሠራሉ። ዕብራውያን 13:17 እንዲህ ይላል፦ “ተግተው ስለሚጠብቋችሁና ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ይህን የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያከናውኑ ነው፤ አለዚያ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሐዘን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።” ይሖዋ አንድን ሰው ለመሾም መንፈስ ቅዱስን እንደሚጠቀም ሁሉ ግለሰቡ በሕይወቱ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማንጸባረቁን ካቆመና በሚመራው የሕይወት ጎዳና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርቶችን ካጓደለ ይሖዋ በዚህ ጊዜም መንፈስ ቅዱስን ተጠቅሞ ከበላይ ተመልካችነቱ ይሽረዋል።
39 የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች የሚያሳዩት ትጋትና መልካም ምሳሌነታቸው የሚደነቅ አይደለም? ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለወንድሞች ይህን ማሳሰቢያ አስፍሯል፦ “ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን።” (1 ተሰ. 5:12, 13) የጉባኤው የበላይ ተመልካቾች በትጋት የሚያከናውኑት አብዛኛው ሥራ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት እንዲቀለንና ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልን ይረዳናል። በተጨማሪም ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለበላይ ተመልካቾች ሊኖራቸው የሚገባውን አመለካከት በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ በተለይ ደግሞ በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።”—1 ጢሞ. 5:17
በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች
40 አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ ሽማግሌዎች የሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች አባላት ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማሉ። ሌሎች ደግሞ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን ወደተለያዩ ሆስፒታሎች በመሄድና ዶክተሮችን በማነጋገር ለይሖዋ ምሥክሮች ያለደም ሕክምና መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታታሉ። የስብሰባ አዳራሾችንና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን በመገንባትና በመጠገን ወይም የክልል ስብሰባ ኮሚቴዎች አባላት ሆነው በማገልገል ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያራምዱ የበላይ ተመልካቾችም አሉ። በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ፣ እነዚህ ወንድሞች በትጋት የሚያከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ራሳቸውን ሳይቆጥቡ በፈቃደኝነት ማቅረባቸውን በእጅጉ ያደንቃሉ። በእርግጥም ‘እንደ እነዚህ ያሉትን ሰዎች በአክብሮት እንይዛቸዋለን።’—ፊልጵ. 2:29
የወረዳ የበላይ ተመልካች
41 የበላይ አካሉ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲሾሙ ዝግጅት ያደርጋል። እነዚህ ወንድሞች በወረዳቸው ውስጥ ያሉትን ጉባኤዎች በዓመት ሁለቴ እንዲጎበኙ ቅርንጫፍ ቢሮው ይመድባቸዋል። በተጨማሪም ራቅ ብለው በሚገኙ ክልሎች የሚያገለግሉ አቅኚዎችን በየተወሰነ ጊዜው ይጎበኛሉ። ጉባኤዎቹን ለመጎብኘት ፕሮግራም ካወጡ በኋላ የሚመጡበትን ጊዜ ለእያንዳንዱ ጉባኤ አስቀድመው ያሳውቃሉ፤ እንዲህ የሚያደርጉት ጉባኤው ከጉብኝቱ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ ነው።
42 ጉብኝቱ ሁሉንም በመንፈሳዊ የሚያነቃቃ እንዲሆን የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ግንባር ቀደም በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል። (ሮም 1:11, 12) የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ስለ ጉብኝቱ እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቱ (ያገባ ከሆነ) ምን እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልጽ መረጃ ከደረሰው በኋላ በተለያዩ ወንድሞች አማካኝነት ማረፊያ ቦታና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዲዘጋጁ ያደርጋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጨምሮ ሁሉም ወንድሞች ስለተደረጉት ዝግጅቶች እንዲያውቁ ያደርጋል።
43 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ጨምሮ የጉባኤ ስብሰባዎችን ፕሮግራም በተመለከተ ከአስተባባሪው ጋር ይነጋገራል። እነዚህ ስብሰባዎች የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚያቀርባቸው ሐሳቦችና ከቅርንጫፍ ቢሮው በሚመጣው መመሪያ መሠረት ይዘጋጃሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከጉባኤው፣ ከአቅኚዎች እንዲሁም ከሽማግሌዎችና ከጉባኤ አገልጋዮች ጋር ስብሰባ የሚያደርግበትን ጊዜና ቦታ እንዲሁም የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚካሄድበትን ጊዜና ቦታ የጉባኤው አስፋፊዎች ሁሉ አስቀድመው እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል።
44 ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የጉባኤ የአስፋፊ መዝገቦችን፣ የተሰብሳቢዎችን ቁጥር የያዘውን መዝገብ እንዲሁም የክልልና የሒሳብ መዝገቦችን ይመረምራል። በዚህ መንገድ ጉባኤው በየትኞቹ አቅጣጫዎች እርዳታ እንደሚያስፈልገውና መዝገቦቹን የሚይዙትን ወንድሞች እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል የተወሰነ ግንዛቤ ያገኛል። የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ፋይሎቹ ለወረዳ የበላይ ተመልካቹ አስቀድመው እንዲደርሱት ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል።
45 በጉብኝቱ ወቅት የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በጉባኤ ስብሰባና በመስክ አገልግሎት ላይ፣ በምግብ ሰዓት ብሎም በሌሎች አጋጣሚዎች በተቻለው መጠን ጊዜ ወስዶ ወንድሞችን በግል ያነጋግራል። በተጨማሪም ከሽማግሌዎችና ከጉባኤ አገልጋዮች ጋር በሚያደርገው ስብሰባ ላይ አስፈላጊ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች፣ ሐሳቦችና ማበረታቻዎች ያካፍላቸዋል፤ ይህም በእነሱ ሥር ያለውን መንጋ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 27:23፤ ሥራ 20:26-32፤ 1 ጢሞ. 4:11-16) በተጨማሪም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ አቅኚዎችን በሥራቸው እንዲገፉ ለማበረታታትና ከአገልግሎታቸው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ካሉ በግል እርዳታ ለመስጠት ከእነሱ ጋር ይሰበሰባል።
46 ትኩረት የሚያሻቸው ሌሎች ጉዳዮች ካሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በጉብኝቱ ሳምንት አቅሙ የሚፈቅድለትን እገዛ ያበረክታል። በጉብኝቱ ሳምንት እነዚህን ጉዳዮች መቋጨት ካልተቻለ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሽማግሌዎች ወይም ግለሰቦች በዚያ ዙሪያ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ለማግኘት ምርምር እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል። ቅርንጫፍ ቢሮው ሊከታተለው የሚገባ ነገር ካለ የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን የሚመለከት ዝርዝር ሪፖርት ለቢሮው ያቀርባሉ።
47 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን በሚጎበኝበት ሳምንት በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል። ከቅርንጫፍ ቢሮው በሚላኩ መመሪያዎች መሠረት አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለውጥ ሊደረግ ይችላል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን ለማበረታታት፣ ለማነቃቃት፣ ለማስተማርና ለማጠናከር የሚረዱ ንግግሮችን ይሰጣል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለይሖዋ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስና ለድርጅቱ ፍቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ ይጥራል።
48 ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ዓላማዎች አንዱ ጉባኤው በመስክ አገልግሎት ቀናተኛ እንዲሆን ማበረታታትና ተግባራዊ የሚሆኑ ሐሳቦችን መጠቆም ነው። በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ብዙ አስፋፊዎች በዚያ ሳምንት በመስክ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ፕሮግራማቸውን ሊያስተካክሉ ምናልባትም እሱ በሚጎበኝበት ወር ረዳት አቅኚ ሊሆኑ ይችላሉ። ከእሱም ሆነ ከባለቤቱ ጋር ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ፕሮግራም ሊያስይዙ ይችላሉ። የጉባኤው አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመሩ ወይም ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ወይም ባለቤቱን መጋበዛቸው ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። በዚህ ረገድ ጉብኝቱን በተሟላ ሁኔታ ለመደገፍ የምታደርጉት ተጨማሪ ጥረት በእጅጉ ይደነቃል።—ምሳሌ 27:17
49 እያንዳንዱ ወረዳ በዓመት ሁለት የወረዳ ስብሰባዎች ያደርጋል። በእነዚህ ጊዜያት ስብሰባው በደንብ ተደራጅቶ እንዲካሄድ የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የስብሰባ የበላይ ተመልካችና ረዳት የስብሰባ የበላይ ተመልካች ይሾማል። እነዚህ ወንድሞች ስብሰባዎቹ በሚገባ የተደራጁ እንዲሆኑ ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጋር በቅርብ ተባብረው ይሠራሉ። ይህም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ትኩረቱን በዋነኝነት በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ያስችለዋል። በተጨማሪም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከስብሰባው ጋር በተያያዙ ሌሎች የሥራ ክፍሎች ላይ እንዲያገለግሉ ብቃት ያላቸው ሌሎች ወንዶችን ይመድባል። እንዲሁም ከእያንዳንዱ የወረዳ ስብሰባ በኋላ የወረዳው ሒሳብ እንዲመረመር ያደርጋል። በዓመቱ ውስጥ በሚኖረው አንደኛው የወረዳ ስብሰባ ላይ ጎብኚ ተናጋሪ ሆኖ የሚላክ የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ ይገኛል። በጉባኤዎቹ መካከል ባለው ርቀት ወይም የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ሰፊ ባለመሆናቸው የተነሳ አንዳንድ ወረዳዎች ተከፋፍለው እንዲሰበሰቡ የሚደረግ ሲሆን እያንዳንዱ ምድብ ራሱን ችሎ የወረዳ ስብሰባ ያደርጋል።
50 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን በወሩ መጨረሻ ላይ በቀጥታ ለቅርንጫፍ ቢሮው ይልካል። ከመጓጓዣ፣ ከምግብ፣ ከማረፊያ ቦታና ከሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ መጠነኛ ወጪዎች ቢኖሩትና ያወጣውን ገንዘብ እየጎበኘው ያለው ጉባኤ ካልሸፈነለት ወጪውን ለቅርንጫፍ ቢሮው መላክ ይችላል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የይሖዋን መንግሥት ፍላጎቶች ካስቀደሙ ኢየሱስ በሰጠው ተስፋ መሠረት የሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች እንደሚሟሉላቸው ሙሉ እምነት አላቸው። (ሉቃስ 12:31) ጉባኤዎች ሊያገለግሏቸው ለሚመጡት ለእነዚህ ቀናተኛ ሽማግሌዎች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት የሚችሉበት ይህ መብት እንዳያመልጣቸው ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።—3 ዮሐ. 5-8
የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ
51 በዓለም ዙሪያ ባለው በእያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸውና የጎለመሱ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ወንድሞች የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ሆነው ያገለግላሉ፤ ኮሚቴው በቅርንጫፍ ቢሮው ሥር ባለ አገር ወይም አገሮች ውስጥ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በበላይነት ይመራል። ከኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው አስተባባሪ ሆኖ ያገለግላል።
52 የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ያሉትን ጉባኤዎች የሚመለከቱ ጉዳዮችን ይከታተላሉ። ኮሚቴው ለቅርንጫፍ ቢሮው በተመደበው ክልል ውስጥ የመንግሥቱ ምሥራች እንዲሰበክ የማድረጉን ሥራ በበላይነት ይከታተላል፤ እንዲሁም ለመስኩ የሚያስፈልጉ ነገሮችን እንዲያሟሉ ጉባኤዎችና ወረዳዎች እንዲቋቋሙ ያደርጋል። በተጨማሪም የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው ሚስዮናውያን እንዲሁም ልዩ አቅኚዎች፣ ዘወትር አቅኚዎችና ረዳት አቅኚዎች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትኩረት ይሰጣል። ትላልቅ ስብሰባዎች በሚኖሩበት ጊዜ ኮሚቴው “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት” እንዲካሄድ ተገቢውን ዝግጅት ያደርጋል፤ የተለያዩ ኃላፊነቶችንም ይሰጣል።—1 ቆሮ. 14:40
53 በአንዳንድ አገሮች ውስጥ በሌላ አገር በሚገኝ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አመራር ሥር ሆኖ የሚሠራ የአገር ኮሚቴ ይሾማል። ይህም የአገር ኮሚቴው ባለበት አገር ውስጥ የሚካሄደውን ሥራ በቅርብ ለመከታተል ያስችላል። ይህ ኮሚቴ ከቤቴል ቤትና ቢሮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይከታተላል፣ ደብዳቤ ይጻጻፋል፣ ሪፖርቶችን ይላላካል፣ በተጨማሪም በመስኩ ላይ የሚካሄደውን ሥራ ይከታተላል። የአገር ኮሚቴው ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ ሲል ከቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው ጋር ተባብሮ ይሠራል።
54 የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴና የአገር ኮሚቴ ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች በሙሉ የሚሾሙት በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ነው።
የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካዮች
55 የበላይ አካሉ፣ ብቃት ያላቸው ወንድሞች በየተወሰነ ጊዜ በምድር ዙሪያ ያሉትን ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲጎበኙ ዝግጅት ያደርጋል። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚያገለግል አንድ ወንድም የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ ይባላል። ተቀዳሚ ሥራው የቤቴል ቤተሰብን ማበረታታት እንዲሁም የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው ከስብከቱና ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በተያያዘ ላጋጠሙት ችግሮች መፍትሔ መስጠት ወይም ጥያቄዎቹን መመለስ ነው። በተጨማሪም ይህ ወንድም ከተወሰኑ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር ስብሰባ ያደርጋል፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በመስክ ከሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ጋር ስብሰባ ያደርጋል። በዚህ ወቅት ስለ ችግሮቻቸውና ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ያነጋግራቸዋል፤ በተጨማሪም የላቀ ቦታ ከሚሰጠው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራቸው ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ማበረታቻ ይሰጣቸዋል።
56 የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ የመንግሥቱን ምሥራች ከመስበክና ከሌሎች የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ በመስኩ ላይ ለተከናወኑት ነገሮች ትኩረት ይሰጣል። ጊዜ የሚፈቅድለት ከሆነ የርቀት የትርጉም ቢሮዎችን ይጎበኛል። የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ አንድን ቅርንጫፍ ቢሮ ሲጎበኝ ሁኔታው የፈቀደለትን ያህል የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ይካፈላል።
የመንጋው እረኛ እንዲሆኑ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ለሚሰጡን አመራር መገዛታችንን ከቀጠልን የጉባኤው ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ይኖረናል
ፍቅራዊ አመራር
57 የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶች ከሚያከናውኑት ትጋት የተሞላበት ሥራና ከሚያደርጉልን ፍቅራዊ ጥበቃ ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን። የመንጋው እረኛ እንዲሆኑ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ለሚሰጡን አመራር መገዛታችንን ከቀጠልን የጉባኤው ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ይኖረናል። (1 ቆሮ. 16:15-18፤ ኤፌ. 1:22, 23) በውጤቱም የአምላክ መንፈስ በዓለም ዙሪያ ባሉት ጉባኤዎች ላይ ያለምንም ገደብ ይሠራል፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደምንመራ በግልጽ ይታያል።—መዝ. 119:105