ጥናት 40
ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍ
አንድ ክርስቲያን የተሳሳተ መረጃ ሊያስተላልፍ የሚችለው እንዴት ነው? ትክክል መሆን አለመሆኑን ሳያረጋግጥ ከሌሎች በስሚ ስሚ የደረሰውን መረጃ አስተላልፎ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ያነበበውን ነገር በተሳሳተ መንገድ በመረዳቱ ምክንያት ጉዳዩን አጋንኖ አቅርቦት ሊሆን ይችላል። አድማጮቻችን ጥቃቅን ስለሆኑት ነገሮች ሳይቀር ትክክለኛ መረጃ ለማስተላለፍ እንደምንጥር ካስተዋሉ ዋናውን የመልእክታችንን ነጥብ እውነተኝነት ማመን አይከብዳቸውም።
በአገልግሎት። አንዳንዶች ብዙም እውቀት እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው አገልግሎት ለመጀመር ይፈራሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ስለ እውነት ባገኙት መሠረታዊ እውቀት ብቻ እንኳ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ለዚህ ወሳኝ የሆነው ነገር አስቀድሞ መዘጋጀት ነው።
ወደ አገልግሎት ከመሄድህ በፊት ከሰዎች ጋር ልትወያይበት ያሰብከውን ርዕሰ ጉዳይ በደንብ ልትረዳው ይገባል። የምታነጋግራቸው ሰዎች ሊያነሱ የሚችሏቸውን ጥያቄዎች አስብ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አጥጋቢ መልስ አዘጋጅ። እንዲህ ካደረግህ ሳትረበሽ ትክክለኛ መልስ መስጠት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠና ከሆነስ? አስቀድመህ ትምህርቱን በደንብ ከልስ። ለጥያቄዎቹ መልሶች ድጋፍ የሚሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ሳይቀር ልትረዳ ይገባል።
አገልግሎት ላይ የምታነጋግረው ሰው ወይም የሥራ ባልደረባህ ያልተዘጋጀህበትን አንድ ጥያቄ ቢያነሳብህስ? መልሱን በትክክል የማታውቀው ከሆነ በግምት አትመልስ። “የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል።” (ምሳሌ 15:28) ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ ወይም “መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት” ከሚለው ቡክሌት ለመልስህ የሚረዳ ጠቃሚ ሐሳብ ልታገኝ ትችላለህ። እነዚህን ጽሑፎች ካልያዝክ መልሱን ሌላ ጊዜ እንደምትነግረው ልትገልጽለት ትችላለህ። ሰውዬው ጥያቄውን ያነሳው በቅን ልቦና ከሆነ ትክክለኛውን መልስ ይዘህለት እስክትሄድ መጠበቅ አይከብደውም። እንዲያውም ባሳየኸው ትሕትና ደስ ሊለው ይችላል።
ልምድ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር አብሮ ማገልገል የአምላክን ቃል በትክክል የመጠቀም ችሎታህን እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። የትኞቹን ጥቅሶች እንደሚጠቅሱና እንዴት እንደሚያብራሯቸው ልብ ብለህ ተከታተል። የሚሰጡህን ማንኛውንም አስተያየት ወይም ምክር በትሕትና ተቀበል። ቀናተኛ ደቀ መዝሙር የነበረው አጵሎስ ከሌሎች ያገኘው እርዳታ ጠቅሞታል። ሉቃስ ስለ አጵሎስ ሲናገር “አዋቂ፣” “በመጻሕፍት እውቀት የበረታ፣” ‘በመንፈስ የሚቃጠል’ እና ‘ስለ ኢየሱስ በትክክል የሚናገርና የሚያስተምር’ ሰው እንደነበር ገልጿል። ይሁንና አጵሎስ ያልተረዳቸው አንዳንድ ነገሮች ነበሩ። ጵርስቅላና አቂላ ይህንን ባስተዋሉ ጊዜ “ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።”—ሥራ 18:24-28
‘በታመነው ቃል መጽናት።’ ጉባኤው “የእውነት ዓምድና መሠረት” በመሆኑ በስብሰባዎች ላይ ክፍል በምናቀርብበት ጊዜ ላገኘነው መብት አክብሮት ሊኖረን ይገባል። (1 ጢሞ. 3:15) እውነትን ማስተማር እንድንችል በንግግራችን የምንጠቀምባቸውን ጥቅሶች ትክክለኛ መንፈስ መረዳታችን በጣም አስፈላጊ ነው። በዙሪያቸው ያለውን ሐሳብና የተጻፉበትን ዓላማ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል።
ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ የተሳሳተ መረጃ ካስተላለፍህ አድማጮችህም ያንኑ ሊያስተጋቡ ይችላሉ። እርግጥ ‘ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን።’ (ያዕ. 3:2) ሆኖም ትክክለኛ መረጃ ለማስተላለፍ የሚረዳህን ልማድ ማዳበርህ አስፈላጊ ነው። ዛሬ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል የሚያቀርቡ ብዙ ወንድሞች ውሎ አድሮ ሽማግሌ ሆነው መሾማቸው አይቀርም። እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት ከተጣለባቸው ወንዶች “ብዙ” ይጠበቃል። (ሉቃስ 12:48) አንድ ሽማግሌ ሳያመዛዝን የተሳሳተ ምክር ቢሰጥና የጉባኤው አባላት ከባድ ችግር ቢገጥማቸው አምላክ በዚህ ሽማግሌ ያዝናል። (ማቴ. 12:36, 37) ስለዚህ አንድ ሽማግሌ ‘በማስተማር ጥበብ ረገድ በታመነው ቃል የሚጸና መሆን ይኖርበታል።’—ቲቶ 1:9
የምትሰነዝረው ሐሳብ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኘው እውነት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ሊሆን ይገባል። (2 ጢሞ. 1:13) ይህ ሲባል ግን ስጋት ሊያድርብህ ይገባል ማለት አይደለም። ምናልባት ገና መጽሐፍ ቅዱስን አንብበህ አልጨረስህ ይሆናል። ማንበብህን ቀጥል። ያም ሆኖ ስታስተምር የምትጠቀምባቸውን ነጥቦች ለማጤን የሚረዱህን ቀጥሎ የቀረቡትን አንዳንድ መንገዶች ልብ በል።
በመጀመሪያ ደረጃ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ሐሳብ እስካሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርኩት ነገር ጋር ይጣጣማል? አድማጮቼ በይሖዋ እንዲታመኑ የሚያደርግ ነው? ወይስ የዓለምን ጥበብ በማወደስ ሰዎች በዚያ እንዲመሩ የሚያበረታታ?’ ኢየሱስ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐ. 17:17፤ ዘዳ. 13:1-5፤ 1 ቆሮ. 1:19-21) ከዚያም ታማኝና ልባም ባሪያ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ተጠቅመህ ምርምር አድርግ። ይህም ጥቅሱን በትክክል እንድትረዳው ብቻ ሳይሆን ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ሚዛኑን የጠበቀ ማብራሪያ ለመስጠት ያስችልሃል። ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍ ከፈለግህ ንግግርህ በአምላክ ቃል ውስጥ ካለው እውነት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም ጥቅሶችን የምታብራራበትና ለአድማጮች ያላቸውን ጠቀሜታ የምትገልጽበት መንገድ ታማኝና ልባም ባሪያ ከሚሰጠው ማብራሪያ ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል።
ትክክለኛ መረጃ መሆኑን ማረጋገጥ። አንዳንድ ነጥቦችን በምሳሌ ለማስረዳት ወይም እንዴት በሥራ መተርጎም እንደሚቻል ግልጽ ለማድረግ የዜና ዘገባዎችን፣ ከሌላ ምንጭ የተወሰዱ ሐሳቦችንና ተሞክሮዎችን መጠቀም ጥሩ ሊሆን ይችላል። እነዚህ መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? መረጃዎቹ ከታመኑ ምንጮች የተገኙና ጊዜ ያላለፈባቸው ሊሆኑ ይገባል። አኃዛዊ መረጃዎች በየጊዜው ይለዋወጣሉ፣ ሳይንሳዊ መረጃዎች በአዲስ ይተካሉ፤ እንዲሁም ሰዎች ስለ ታሪክና ስለ ጥንታዊ ቋንቋዎች ያላቸው እውቀት እያደገ ሲሄድ ቀደም ሲል በነበሩት መረጃዎች ላይ የተመሠረተው ግንዛቤ ይለወጣል። ከጋዜጣ፣ ከቴሌቪዥን፣ ከራዲዮ ወይም ከኢንተርኔት ያገኘኻቸውን መረጃዎች መጠቀምን በተመለከተ ጥንቃቄ ልታደርግ ይገባል። ምሳሌ 14:15 “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” በማለት ምክር ይሰጣል። ‘ሐሳቡን ያገኘሁት ትክክለኛ መረጃ በማስተላለፍ ረገድ ጥሩ ስም ካተረፈ ምንጭ ነውን? ትክክለኛነቱን ከሌላ ወገን ማረጋገጥ እችላለሁን?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ትክክለኛነቱን ከተጠራጠርክ አትጠቀምበት።
የመረጃ ምንጮቹን ተዓማኒነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ያገኘኸውን ሐሳብ በንግግርህ እንዴት እንደምትጠቀምበትም በጥሞና ልታስብ ይገባል። ከጽሑፍ ወይም ከሌላ ምንጭ የተወሰዱ ሐሳቦችና አኃዛዊ መረጃዎች ስትጠቀም ከተጠቀሱበት ምንጭ የተለየ ሐሳብ የሚያስተላልፉ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ነጥቡን አጋንነህ ለመግለጽ በምታደርገው ጥረት “አንዳንድ ሰዎች” የሚለው መግለጫ “አብዛኞቹ ሰዎች፣” “ብዙዎቹ ሰዎች” የሚለው ደግሞ “ሁሉም ሰዎች” እንዲሁም “አንዳንድ ጊዜ” የሚለው መግለጫ “ሁልጊዜ” የሚል መልእክት እንዳያስተላልፍብህ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ጉዳዩን ከመጠን በላይ አክብዶ መግለጽ እንዲሁም ከአኃዝ፣ ከአንድ ነገር ስፋት ወይም አሳሳቢነት ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን አጋንኖ ማቅረብ የተናጋሪውን ተዓማኒነት ጥያቄ ላይ ይጥለዋል።
ሁልጊዜ ትክክለኛ ነገር የምትናገር ከሆነ ሌሎች ለእውነት የቆምክ ሰው መሆንህን ያስተውላሉ። ይህ በአጠቃላይ ለይሖዋ ምሥክሮችም መልካም ስም ያተርፋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ያስከብራል።—መዝ. 31:5