“መጽናት ያስፈልጋችኋል”
‘የተሰጠንን የተስፋ ቃል’ ለማግኘት ‘መጽናት ያስፈልገናል።’ (ዕብራውያን 10:36) ሐዋርያው ጳውሎስ “መጽናት” ብሎ ሲጽፍ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል አንዳንድ ጊዜ “አንድ ተክል አስቸጋሪና በመጥፎ ሁኔታዎች ሥር ለመኖር ያለውን ችሎታ” እንደሚያመለክት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ተናግረዋል።
በአውሮፓ ተራሮች ውስጥ እንዲህ ያለ ተክል ይበቅላል። ይህ ተክል ዘላለም መኖር ተብሎ መጠራቱ ያስደንቃል። በእርግጥ አልፓይን ተብሎ የሚጠራው ይህ ተክል ለዘላለም ባይኖርም ለብዙ ዓመታት ከመጽናቱም በላይ በጋ በመጣ ቁጥር ያብባል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ዘላለም መኖር የተባለው ስም ለዚህ ተክል የተሰጠው “ባለው ችግር የመቋቋም ችሎታና ጽናት” እንደሆነ ይናገራል። (በተጨማሪም ከሴምፐርቪቨም ጂነስ የሚመደበው የዚህ ተክል ሳይንሳዊ ስም “ዘላለም መኖር” የሚል ትርጉም አለው።)
ይህን ጽኑ ተክል አስደናቂ ያደረገው በጣም ጠፍ በሆኑ ቦታዎች መብቀሉ ነው። የሙቀቱ መጠን በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ ከ35 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ በሆነ መጠን ሊቀንስ በሚችልበት በነፋሻማ ተራራ ላይ ሊበቅል ይችላል። አነስተኛ አፈር ባለበት የዓለት ስንጥቅ ውስጥ ሥር ሊሰድ ይችላል። በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለመጽናት ያስቻለው ምሥጢሩ ምንድን ነው?
ዘላለም መኖር የተባለው ተክል በቅጠሎቹ ውስጥ ብዙ ውኃ ያጠራቅማል። ይህም ከዝናብ ወይም ከቀለጠ በረዶ በሚገኘው እርጥበት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ያስችለዋል። በተጨማሪም አንድ ላይ ሆነው በብዛት በማደግ የበቀሉበትን ድንጋይ ቆንጥጠው ለመቆም እንዲያስችላቸው ኃይላቸውን ያስተባብራሉ። ምንም እንኳ ዓለቱ ትንሽ አፈር ቢኖረውም በስንጥቅ ዓለት ውስጥ ሥራቸውን መስደዳቸው በተወሰነ መጠን ከመጥፎ የአየር ሁኔታ ይከላከልላቸዋል። በሌላ አነጋገር ይህ ተክል የሚያጋጥሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየተጠቀመባቸው ያድጋል።
በመንፈሳዊ ሁኔታም ጽናታችንን በሚፈትኑ ሁኔታዎች ውስጥ እየኖርን ይሆናል። ፈተና ሲደርስብን ለመጽናት የሚረዳን ምንድን ነው? ዘላለም መኖር እንደተባለው ተክል ሕይወት ሰጪ ውኃ የሆነውን የአምላክ ቃል ማከማቸት እንዲሁም ድጋፍና ጥበቃ ለማግኘት ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብ እንችላለን። ከሁሉ በላይ እንደ አልፓይንስ አበባ ‘ዓለታችን’ ከሆነው ከይሖዋ፣ ከቃሉና ከድርጅቱ ጋር እንደ ሙጫ መጣበቅ አለብን።—2 ሳሙኤል 22:2
በእርግጥም ያሉትን ዝግጅቶች ከተጠቀምንባቸው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ መጽናት እንደምንችል ዘላለም መኖር ከተባለው ተክል በጣም ጥሩ የሆነ ትምህርት እናገኛለን። መጽናታችን ‘የተሰጠንን ተስፋ ለመውረስ’ እንደሚያስችለን ማለትም ቃል በቃል የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝልን ይሖዋ ቃል ገብቶልናል።—ዕብራውያን 6:12፤ ማቴዎስ 25:46