የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 14—2 ዜና መዋዕል
ጸሐፊው:- ዕዝራ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም (?)
ተጽፎ ያለቀው:- 460 ከክ.ል.በፊት ገደማ
የሚሸፍነው ጊዜ:- 1037-537 ከክ.ል.በፊት
አንደኛና ሁለተኛ ዜና መዋዕል መጀመሪያ ላይ አንድ መጽሐፍ ስለነበሩ በዘመኑ የነበረውን ታሪክ፣ የመጽሐፉን ጸሐፊ፣ የተጻፈበትን ጊዜ፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑንና ትክክለኛነቱን በሚመለከት ለአንደኛ ዜና መዋዕል የቀረቡት ማስረጃዎች ለሁለቱም መጻሕፍት ይሠራሉ። በቀረቡት ማስረጃዎች መሠረት ዕዝራ ሁለተኛ ዜና መዋዕልን ጽፎ ያጠናቀቀው በ460 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ሲሆን ቦታው ደግሞ በኢየሩሳሌም እንደሆነ ይገመታል። ዕዝራ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸው የነበሩትን ታሪካዊ እሴቶች ጠብቆ የማቆየት ዓላማ ነበረው። ዕዝራ ከመንፈስ ቅዱስ ካገኘው እርዳታ በተጨማሪ ታሪክ ጸሐፊ እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማግኘት የነበረው አጋጣሚና ነጥቦቹን የማውጣት ችሎታው ትክክለኛና ጊዜ የማይሽረው ዘገባ እንዲያሰፍር አስችሎታል። ታሪካዊ ክስተቶች አድርጎ የተመለከታቸውን ነገሮች ለወደፊቱ ጊዜ ተጠብቀው እንዲቆዩ አድርጓል። ቀደም ባሉት መቶ ዘመናት የተጻፉትን ሁሉንም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ማሰባሰቡ አስፈላጊ በመሆኑ ዕዝራ ያከናወነው ሥራ በጣም ወቅታዊ ነበር።
2 በዕዝራ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ዕዝራ በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፈው የታሪክ ዘገባ በእጅጉ ተጠቅመዋል። ዘገባው ለእነርሱ መመሪያ ለመስጠትና እንዲጸኑ ለማበረታታት የተጻፈ ነበር። አይሁዳውያኑ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሰጧቸው መጽናናት ተስፋ ማግኘት ይችሉ ነበር። እስራኤላውያን የዜና መዋዕልን መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሆነ አድርገው የተቀበሉት ከመሆኑም በላይ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ተገንዝበዋል። በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉ ሌሎች መጻሕፍትና ዕዝራ ከጠቀሳቸው በርካታ ታሪኮች ጋር በማመሳከር የመጽሐፉን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይችሉ ነበር። በመንፈስ አነሳሽነት ያልተጻፉትን ሌሎች የታሪክ መዛግብት ለማቆየት ጥረት አላደረጉም። ይሁን እንጂ የዜና መዋዕል መጽሐፍ እንዳለ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርገዋል። የሰብዓ ሊቃናት (ሰፕቱጀንት) ተርጓሚዎችም የዜና መዋዕል መጽሐፍ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል እንዲሆን አድርገዋል።
3 ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የጻፉት ሰዎች 2 ዜና መዋዕል ትክክለኛና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ተቀብለዋል። ኢየሱስ፣ ኢየሩሳሌም የይሖዋን ነቢያትና አገልጋዮች የምትገድልና የምትወግር ከተማ እንደሆነች በመናገር ሲያወግዛት በ2 ዜና መዋዕል 24:21 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመሳሰሉ ክስተቶችን በአእምሮው ይዞ እንደነበር አያጠራጥርም። (ማቴ. 23:35፤ 5:12፤ 2 ዜና 36:16) ያዕቆብ አብርሃምን “የእግዚአብሔር ወዳጅ” ብሎ ሲጠራው፣ ዕዝራ በ2 ዜና መዋዕል 20:7 ላይ የተጠቀመበትን መግለጫ መጠቀሙ ሊሆን ይችላል። (ያዕ. 2:23) መጽሐፉ ያላንዳች መዛነፍ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችንም ይዟል።—2 ዜና 20:17, 24፤ 21:14-19፤ 34:23-28፤ 36:17-20
4 አርኪኦሎጂም የሁለተኛ ዜና መዋዕልን መጽሐፍ ትክክለኛነት ያረጋግጣል። የጥንቷ ባቢሎን በነበረችበት አካባቢ በተደረገው ቁፋሮ ናቡከደነፆር ይገዛበት ስለነበረው ዘመን የሚገልጹ የሸክላ ጽላቶች ተገኝተዋል፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ “ያውኪን የያሁድ ምድር ንጉሥ” የሚል ስም የሚጠቅስ ሲሆን ትርጉሙም “የይሁዳ ምድር ንጉሥ የሆነው ዮአኪን” ማለት ነው።a ይህ ደግሞ ናቡከደነፆር በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ዮአኪን ወደ ባቢሎን በምርኮ ተወስዶ እንደነበር ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር ይስማማል።
5 በሁለተኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ውስጥ ያለው ዘገባ፣ በ1037 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከጀመረው የሰሎሞን የግዛት ዘመን አንስቶ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቂሮስ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የይሖዋ ቤት እንዲገነባ ትእዛዝ እስካወጣበት ጊዜ ድረስ በይሁዳ የተከናወኑትን ነገሮች ይዘረዝራል። በዚህ የ500 ዓመት ታሪክ ውስጥ የአሥሩ ነገድ መንግሥት የተጠቀሰው ከይሁዳ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲኖር ብቻ ከመሆኑም ሌላ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት በዚህ ሰሜናዊ መንግሥት ላይ የደረሰው ጥፋት እንኳ አልተገለጸም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ካህኑን ዕዝራን ያሳሰበው ዋነኛ ጉዳይ የይሖዋ አምልኮ በትክክለኛው ቦታ ማለትም በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤቱ መከናወን መቀጠሉና ይሖዋ ለዳዊት በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በዚያ መስመር የሚመጣው መንግሥት ስለነበረ ነው። በመሆኑም ዕዝራ እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍና ይሖዋ የሚያስነሳውን ገዥ በመጠባበቅ በደቡባዊው መንግሥት ላይ ትኩረት አድርጓል።—ዘፍ. 49:10
6 ዕዝራ ገንቢ የሆኑ ጉዳዮችን ለማውሳት ጥረት አድርጓል። ከሁለተኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ 36 ምዕራፎች መካከል የመጀመሪያዎቹ 9 ምዕራፎች ስለ ሰሎሞን ግዛት የሚዘግቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 6ቱ ሙሉ በሙሉ የሚገልጹት ስለ ይሖዋ ቤት ግንባታና ለአምላክ አገልግሎት ስለመወሰኑ ነው። ዘገባው ሰሎሞን ከእውነተኛው አምልኮ መራቁን አይጠቅስም። ከቀሩት 27 ምዕራፎች ውስጥ 14ቱ የሚያተኩሩት ዳዊት ያሳየውን ለይሖዋ አምልኮ በሙሉ ልብ የማደር ዝንባሌ በተከተሉት አምስት ነገሥታት ላይ ሲሆን እነዚህም ንጉሥ አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮአታም፣ ሕዝቅያስ እና ኢዮስያስ ናቸው። በቀሩት 13 ምዕራፎች ውስጥም ቢሆን ዕዝራ ክፉ የነበሩትን ነገሥታት መልካም ጎኖች ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ጥረት አድርጓል። አጽንዖት የሰጣቸው ክንውኖች ከእውነተኛው አምልኮ እንደገና መቋቋምና መቀጠል ጋር የተያያዙ ናቸው። እንዴት ያለ መንፈስ የሚያነቃቃ ዘገባ ነው!
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
34 ሁለተኛ ዜና መዋዕል አስደሳች ነገሮች ስለተከናወኑበት ከ1037-537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ስላለው ጊዜ ሌሎች ምሥክሮች በሚሰጡት መግለጫ ላይ ተጨማሪ ጠንካራ ማስረጃ ያቀርባል። ከዚህም በላይ የቅዱስ ጽሑፉ ክፍል በሆኑት በሌሎች ታሪኮች ውስጥ የማይገኙ ጠቃሚ መረጃዎችን ይዟል። ሁለተኛ ዜና መዋዕል ምዕራፍ 19፣ 20 እና ከ29 እስከ 31 ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው። ዕዝራ በብሔሩ ታሪክ ውስጥ መሠረታዊና ቋሚ የሆኑትን ነገሮች ማለትም እንደ ክህነት ሥርዓቱና አገልግሎቱ፣ ቤተ መቅደሱ እንዲሁም የመንግሥቱን ቃል ኪዳን የመሳሰሉትን ርዕሰ ጉዳዮች በመምረጥ ጎላ ብለው እንዲታዩ አድርጓል። ይህም ብሔሩ መሲሑንና በእርሱ የሚመራውን መንግሥት ተስፋ በማድረግ አንድ ሆኖ እንዲቆይ ለማጠናከር አስፈላጊ ነበር።
35 የሁለተኛ ዜና መዋዕል የመደምደሚያ ቁጥሮች (36:17-23) በኤርምያስ 25:12 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን ስለማግኘቱ አጥጋቢ ማረጋገጫ ከመስጠታቸውም በላይ ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ከጠፋችበት ጊዜ አንስቶ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት የይሖዋ አምልኮ በኢየሩሳሌም እንደገና እስከተቋቋመበት ጊዜ ድረስ ድፍን 70 ዓመት መቆጠር እንዳለበት ይጠቁማሉ። ከዚህ በመነሳት ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት መሆኑን ማወቅ ይቻላል።b—ኤር. 29:10፤ 2 ነገ. 25:1-26፤ ዕዝራ 3:1-6
36 ሁለተኛ ዜና መዋዕል በክርስትና እምነት ለሚመላለሱ ሰዎች ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ይዟል። ብዙዎቹ የይሁዳ ነገሥታት አጀማመራቸው ጥሩ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ወደ ክፋት ጎዳና ዘወር ብለዋል። ይህ የታሪክ ዘገባ ስኬታማ መሆናችን የተመካው ለአምላክ ታማኝ ሆነን በመገኘታችን ላይ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል! እንግዲያው “አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት” እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል። (ዕብ. 10:39) ታማኙ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንኳ ሳይቀር ከሕመሙ ካገገመ በኋላ ታብዮ የነበረ ሲሆን ከይሖዋ ቁጣ ሊድን የቻለው ወዲያውኑ ራሱን በማዋረዱ ነው። ሁለተኛ ዜና መዋዕል የይሖዋን ድንቅ ባሕርያት ጎላ አድርጎ ይገልጻል፤ እንዲሁም ስሙንና ሉዓላዊነቱን ከፍ ከፍ ያደርጋል። የታሪኩ አጠቃላይ አቀራረብ ለይሖዋ ብቻ የተለየ አምልኮ በመስጠት አስፈላጊነት ላይ የሚያጠነጥን ነው። ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በይሁዳ ንጉሣዊ መስመር ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ መጠን “የዳዊት ልጅ” በሆነው በታማኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት አማካኝነት ንጹሕ አምልኮ ክብር ተጎናጽፎ የማየት ተስፋችንን ያጠናክርልናል።—ማቴ. 1:1፤ ሥራ 15:16, 17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 147
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 463፤ ጥራዝ 2 ገጽ 326