-
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ደፋር የነበረው ሄኖክመጠበቂያ ግንብ—1997 | ጥር 15
-
-
አምላክ ሄኖክን የወሰደው እንዴት ነው?
ሰይጣን ወይም የእሱ ምድራዊ አገልጋዮች ሄኖክን እንዲገድሉት ይሖዋ አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ታሪክ ‘እግዚአብሔር ወሰደው’ ይላል። (ዘፍጥረት 5:24) ሐዋርያው ጳውሎስ ሁኔታውን በዚህ መንገድ ይገልጸዋል:- “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፣ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና።”— ዕብራውያን 11:5
ሄኖክ ‘ሞትን እንዳያይ የተወሰደው’ እንዴት ነው? ወይም በአር ኤ ክኖክስ የእንግሊዝኛ ትርጉም መሠረት “ሄኖክ ሞትን ሳይቀምስ የተወሰደው” እንዴት ነው? አምላክ ሄኖክን በሕመም ወይም በጠላቶቹ እጅ ወድቆ በመንገላታት የሞትን ጣር ሳይቀምስ በሰላም እንዲሞት አድርጓል። አዎን፣ ይሖዋ የሄኖክን ሕይወት በ365 ዓመት ዕድሜው ማለትም በእሱ ዘመን የነበሩት ሌሎች ሰዎች ከኖሩበት ዕድሜ አንፃር ሲታይ ገና በወጣትነቱ በአጭሩ ቀጭቶታል።
ሄኖክ “እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ የተመሰከረለት” እንዴት ነው? ምን ተጨባጭ ማስረጃ ነበረው? ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን የወደፊት መንፈሳዊ ገነት በራእይ በተመለከተበት ጊዜ ‘እንደ ተነጠቀ’ ወይም በሐሳብ እንደተወሰደ ሁሉ አምላክ ሄኖክም በሐሳብ እንዲወሰድ አድርጎት ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:3, 4) ሄኖክ አምላክን ደስ እንዳሰኘ ለማረጋገጥ የተሰጠው አንዱ ምሥክር ወይም ማስረጃ የአምላክን ሉዓላዊነት የሚደግፉ ሰዎች ሁሉ የሚኖሩባትን ወደፊት የምትመጣውን ምድራዊ ገነት በራእይ ማየቱ ሊሆን ይችላል። አምላክ ምናልባትም ሄኖክ በሐሳብ ተመስጦ ራእይ እየተመለከተ ባለበት ወቅት በትንሣኤ እስከሚነሳበት ቀን ድረስ ያለምንም ጣር በዚያው በሞት እንዲያንቀላፋ አድርጎት ይሆናል። ይሖዋ በሙሴ እንዳደረገው ሁሉ የሄኖክንም አስከሬን ስለሰወረው ይመስላል “አልተገኘም።”— ዕብራውያን 11:5፤ ዘዳግም 34:5, 6፤ ይሁዳ 9
-
-
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ደፋር የነበረው ሄኖክመጠበቂያ ግንብ—1997 | ጥር 15
-
-
ሄኖክ ወደ ሰማይ ተወስዷልን?
“ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ።” አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን የዕብራውያን 11:5 ክፍል ያስቀመጡት ሄኖክ እንዳልሞተ በሚጠቁም መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል በጄምስ ሞፋት የተዘጋጀው አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (A New Translation of the Bible) “ሄኖክ በፍጹም ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሰማይ ተስዷል” በማለት ይገልጻል።
ሆኖም ሄኖክ ከኖረበት ዘመን ከ3,000 ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) የ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ይላል። ኢየሱስ ይህን ሲናገር እሱ ራሱ እንኳ ገና ወደ ሰማይ አልወጣም ነበር።— ከሉቃስ 7:28 ጋር አወዳድር።
ሐዋርያው ጳውሎስ ሄኖክም ሆነ ሌሎቹ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ እንደ ደመና የሆኑ ምሥክሮች ‘ሁሉ አምነው እንደሞቱ’ እና ‘የተሰጠውን የተስፋ ቃል’ እንዳላገኙ ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:13, 39) ለምን? ምክንያቱም ሄኖክን ጨምሮ ሁሉም የሰው ዘሮች ከአዳም ኃጢአትን ወርሰዋል። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) መዳን የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። (ሥራ 4:12፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በሄኖክ ዘመን ደግሞ ይህ ቤዛ ገና አልተከፈለም ነበር። ስለዚህ ሄኖክ ወደ ሰማይ አልሄደም፤ ከዚህ ይልቅ በሞት አንቀላፍቶ በዚሁ በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኝበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ነው።— ዮሐንስ 5:28, 29
-