የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • ምዕራፍ 41. እጅ ለእጅ የተያያዙ አንድ ወንድና አንዲት ሴት

      ምዕራፍ 41

      መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?

      ብዙ ሰዎች ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ይከብዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ሆኖም ጨዋነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይናገራል። የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ እኛን የሚጠቅም መረጃ ይዟል። ይህ መሆኑ አያስገርምም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ይሖዋ ያጻፈው መጽሐፍ ነው። ይሖዋ ደግሞ ለእኛ የተሻለውን ነገር ያውቃል። እሱን ለማስደሰትና ለዘላለም በደስታ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል።

      1. ይሖዋ ለፆታ ግንኙነት ምን አመለካከት አለው?

      የፆታ ግንኙነት ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው። ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ደስታ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ይህ ስጦታ ባለትዳሮች ልጆች እንዲወልዱ ብቻ ሳይሆን አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ተፈጥሯዊ በሆነና እርካታ በሚያስገኝ መንገድ እንዲገልጹ ያስችላቸዋል። የአምላክ ቃል “ከወጣትነት ሚስትህ . . . ጋር ደስ ይበልህ” የሚለው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 5:18, 19) ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑ ይፈልጋል፤ በመሆኑም ባለትዳሮች ምንዝር ከመፈጸም ሊርቁ ይገባል።—ዕብራውያን 13:4⁠ን አንብብ።

      2. የፆታ ብልግና ምንድን ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሴሰኞች [የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች] የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የፆታ ብልግናን ለመግለጽ ፖርኒያ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅመዋል። ይህ ቃል (1) ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነትa (2) ግብረ ሰዶምን እና (3) ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት ያካትታል። ‘ከፆታ ብልግና መራቃችን’ ይሖዋን የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ እኛንም ይጠቅመናል።—1 ተሰሎንቄ 4:3

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      ከፆታ ብልግና መራቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነና የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ እንመለከታለን።

      ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት ሲሸሽ። የጶጢፋር ሚስት የዮሴፍን ልብስ በእጇ ይዛለች

      3. ከፆታ ብልግና ሽሽ

      ዮሴፍ የተባለ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን ለመጠበቅ ብዙ ትግል አድርጓል። ዘፍጥረት 39:1-12⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ዮሴፍ የሸሸው ለምንድን ነው?—ቁጥር 9⁠ን ተመልከት።

      • ዮሴፍ ያደረገው ነገር ትክክል ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል ከፆታ ብልግና መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ ከሥነ ምግባር ብልግና ሽሹ (5:06)

      ይሖዋ ሁላችንም ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ይፈልጋል። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:18⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • የፆታ ብልግና ወደመፈጸም ሊመሩ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

      • ከፆታ ብልግና መሸሽ የምትችለው እንዴት ነው?

      4. ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችላለህ

      የፆታ ብልግና እንድንፈጽም የሚደረግብንን ጫና መቋቋም ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ፈተናን ለመቋቋም ይረዳል (3:02)

      • በቪዲዮው ላይ የታየው ወንድም፣ የሚያስባቸውና የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች ለባለቤቱ ያለውን ታማኝነት እንዲያጓድል ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሲገነዘብ ምን አደረገ?

      ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ አስተሳሰባቸው ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ለማድረግ መታገል ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የብልግና ሐሳቦችን እንዳታውጠነጥን ምን ይረዳሃል? ፊልጵስዩስ 4:8⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ስለ ምን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል?

      • መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላችን ኃጢአት ለመፈጸም ስንፈተን የሚረዳን እንዴት ነው?

      5. ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተላችን ይጠቅመናል

      ይሖዋ ለእኛ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነና እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ገልጾልናል። ምሳሌ 7:7-27⁠ን አንብቡ ወይም ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ በማስተዋል ተመላለሱ (9:31)

      • እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ወጣት ራሱን ፈተና ውስጥ ያስገባው እንዴት ነው?—ምሳሌ 7:8, 9⁠ን ተመልከት።

      • ምሳሌ 7:23, 26 ላይ እንደተገለጸው የፆታ ብልግና መፈጸም አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ከየትኞቹ ችግሮች ያድነናል?

      • የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ለዘላለም በደስታ ለመኖር የሚያስችለን እንዴት ነው?

      አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ የሚናገረው ሐሳብ ፍቅር የጎደለው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ሁሉም ሰው ለዘላለም በደስታ እንዲኖር ይፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • በዚህ ጥቅስ መሠረት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ግብረ ሰዶም ብቻ ነው?

      አምላክን ለማስደሰት ሁላችንም የተለያዩ ለውጦች ማድረግ ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ ነው? መዝሙር 19:8, 11⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ ያወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምክንያታዊ ወይም ተገቢ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      1. በሐዘን የተዋጠች አንዲት ወጣት ከወንድ ጓደኛዋ አጠገብ ተቀምጣ። ከጓደኞቿ ጋር የምሽት ክበብ ውስጥ ሆና እየጠጣችና እያጨሰች ነው 2. ያቺው ሴት በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከእህቶች ጋር በደስታ ስታወራ

      ይሖዋ ብዙዎች እሱ ካወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር እንዲችሉ ረድቷል። አንተንም ሊረዳህ ይችላል

      አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ማንም ሰው ከፈለገው ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይችላል። ዋናው ነገር መዋደዳቸው ነው።”

      • አንተ ምን ትላለህ?

      ማጠቃለያ

      የፆታ ግንኙነት ትዳር በመሠረቱ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ሊፈጸም የሚገባ የይሖዋ ስጦታ ነው።

      ክለሳ

      • የፆታ ብልግና ምን ነገሮችን ያካትታል?

      • ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ምን ይረዳናል?

      • ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      አምላክ አብረው መኖር የሚፈልጉ ወንድና ሴት ትዳር እንዲመሠርቱ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

      “መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጋቡ አብሮ መኖርን በተመለከተ ምን ይላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም የሚያስተምረው ትምህርት ጥላቻን የሚያስፋፋ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

      “ግብረ ሰዶም ስህተት ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      አምላክ ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ጋር በተያያዘ ያወጣው ሕግ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

      “በአፍ የሚፈጸም ወሲብ የፆታ ግንኙነት ነው ሊባል ይችላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      “የያዙኝ በአክብሮት ነበር” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ግብረ ሰዶማዊ የነበረ አንድ ሰው አምላክን ለማስደሰት ሲል አኗኗሩን እንዲቀይር ያነሳሳው ምን እንደሆነ ተመልከት።

      “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” (መጠበቂያ ግንብ ሚያዝያ 1, 2011)

      a በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፆታ ግንኙነት በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነትን፣ የሌላን ግለሰብ የፆታ ብልት ማሻሸትንና እንዲህ የመሳሰሉ ሌሎች ድርጊቶችን ያካትታል።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ ስለመኖርና ስለ ትዳር ምን ይላል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • ምዕራፍ 42. አንድ ባልና ሚስት እንዲሁም አንዲት ያላገባች እህት ሻይ ቤት ቁጭ ብለው በደስታ ሲያወሩ

      ምዕራፍ 42

      መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ ስለመኖርና ስለ ትዳር ምን ይላል?

      በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ሰው ካላገባ ደስተኛ ሊሆን እንደማይችል ይታመናል። ሆኖም ትዳር የመሠረቱ ሰዎች በሙሉ ደስተኞች ናቸው ማለት አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትዳር ባይመሠርቱም ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ መኖርም ሆነ ትዳር መመሥረት ስጦታዎች እንደሆኑ ይናገራል።

      1. ሳያገቡ መኖር ምን ጥቅሞች አሉት?

      መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሚያገባ ሁሉ መልካም ያደርጋል፤ ሳያገባ የሚኖር ሁሉ ደግሞ የተሻለ ያደርጋል።” (1 ቆሮንቶስ 7:32, 33, 38⁠ን አንብብ።) ያላገቡ ሰዎች ‘የተሻለ ያደርጋሉ’ የተባለው ከምን አንጻር ነው? ያላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛን ፍላጎት የማሟላት ጉዳይ አያሳስባቸውም። በመሆኑም በጥቅሉ ሲታይ የበለጠ ነፃነት አላቸው። አንዳንዶች ይሖዋን የበለጠ ለማገልገል ሁኔታቸው ይፈቅድላቸዋል፤ ለምሳሌ ወደ ሌላ አገር ሄደው ምሥራቹን መስበክ ችለዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚያስችል ሰፋ ያለ ጊዜ አላቸው።

      2. ሕጋዊ ጋብቻ መመሥረት ምን ጥቅሞች አሉት?

      ሳያገቡ መኖር የራሱ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ትዳር መመሥረትም የራሱ ጥቅም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:9) በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በትዳራቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ይህ ጥቅስ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ማየት ይችላሉ። ሕጋዊ ጋብቻ የሚመሠርቱ ባለትዳሮች እርስ በርስ ለመዋደድ፣ ለመከባበርና አንዳቸው ሌላውን ለመንከባከብ ቃል ይገባሉ። እንዲህ ያለ ቃለ መሐላ የገቡ ባለትዳሮች በአብዛኛው ሳይጋቡ ከሚኖሩ ጥንዶች የበለጠ የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል። በተጨማሪም ሕጋዊ ጋብቻ መመሥረት ልጆች ከስጋት ነፃ ሆነው እንዲያድጉ ያስችላል።

      3. ይሖዋ ለትዳር ምን አመለካከት አለው?

      ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋብቻን ዝግጅት ሲያቋቁም እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል።” (ዘፍጥረት 2:24) ይሖዋ ባልና ሚስት በሕይወት እስካሉ ድረስ እርስ በርስ እንዲዋደዱና ሳይለያዩ አብረው እንዲኖሩ ይፈልጋል። አንድ ባልና ሚስት ፍቺ እንዲፈጽሙ የሚፈቅደው አንደኛው ወገን ካመነዘረ ብቻ ነው። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ይሖዋ የተበደለው ወገን ፍቺ ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም መወሰን እንዲችል መብት ሰጥቶታል።a (ማቴዎስ 19:9) ይሖዋ ክርስቲያኖች ከአንድ በላይ እንዲያገቡ አይፈቅድም።—1 ጢሞቴዎስ 3:2

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      ያላገባህም ሆንክ ትዳር የመሠረትክ ደስተኛ መሆንና ይሖዋን ማስደሰት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

      4. ያላገባህ መሆንህ የሚያስገኝልህን ነፃነት በአግባቡ ተጠቀምበት

      ኢየሱስ ሳያገቡ መኖር ስጦታ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:11, 12) ማቴዎስ 4:23⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ኢየሱስ አለማግባቱ ያስገኘለትን ነፃነት አባቱን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት የተጠቀመበት እንዴት ነው?

      ያላገቡ ክርስቲያኖችም የኢየሱስ ዓይነት ሕይወት በመምራት ደስታ ማግኘት ይችላሉ። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ያላገባችሁ ታማኝ አገልጋዮች (3:11)

      • ያላገቡ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን በየትኞቹ አስደሳች መንገዶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ?

      ይህን ታውቅ ነበር?

      መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ትዳር ሊመሠርት የሚገባው ስንት ዓመት ሲሞላው እንደሆነ አይናገርም። ሆኖም ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ካለፈ’ በኋላ ማግባት የተሻለ እንደሆነ ይመክራል፤ ምክንያቱም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የፆታ ስሜት ስለሚያይል ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 7:36

      5. የትዳር ጓደኛህን በጥበብ ምረጥ

      በሕይወትህ ውስጥ ከምታደርጋቸው ከባድ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የትዳር ጓደኛን መምረጥ ነው። ማቴዎስ 19:4-6, 9⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ክርስቲያኖች በችኮላ ትዳር መመሥረት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የትዳር አጋር የሚሆንህን ሰው ለማወቅ ይረዳሃል። ትዳር መመሥረት የሚፈልጉ ሰዎች ከሁሉ በላይ ሊያሳስባቸው የሚገባው ሊያገቡ ያሰቡት ሰው ይሖዋን የሚወድ መሆኑ ነው።b አንደኛ ቆሮንቶስ 7:39⁠ን እና 2 ቆሮንቶስ 6:14⁠ን አንብቡ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ከእኛ ጋር አንድ ዓይነት እምነት ያለውን ሰው ብቻ ማግባት ያለብን ለምንድን ነው?

      • ይሖዋ እሱን የማይወድ ሰው ብናገባ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?

      ጠንካራ በሬና ትንሽ አህያ በአንድ ቀንበር ተጠምደው ለማረስ ሲታገሉ

      ሁለት የተለያዩ እንስሳት በአንድ ቀንበር ከተጠመዱ ሁለቱም ይሠቃያሉ። ይሖዋን የማያገለግል ሰው የሚያገቡ ክርስቲያኖችም ብዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል

      6. ለትዳር የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑርህ

      በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ ወንዶች እንደፈለጉ ለመኖር ሲሉ ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር። ሚልክያስ 2:13, 14, 16⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር በሚጋጭ መንገድ የሚፈጸምን ፍቺ የሚጠላው ለምንድን ነው?

      በጣም ያዘነች አንዲት እናት ባለቤቷ ቤት ጥሎ ሲወጣ ስታየው። ልጃቸው በሐዘን ተውጣ እናቷን አቅፋታለች

      ምንዝርና ፍቺ፣ በደል በተፈጸመበት ወገንና በልጆች ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ

      ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ትዳር—ዘላቂ ጥምረት (4:30)

      • ይሖዋን ከማይወድ ሰው ጋር ትዳር የመሠረቱ ሰዎች ትዳራቸው አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

      7. ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መሥፈርት ተከተል

      አንድ ሰው ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መሥፈርት ለመከተል ሲል ብዙ መሥዋዕትነት መክፈል ሊያስፈልገው ይችላል።c ሆኖም ይሖዋ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን ይባርካል። ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መሥፈርት መከተል ትችላለህ (4:14)

      ዕብራውያን 13:4⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣው መሥፈርት ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      ይሖዋ ክርስቲያኖች ጋብቻ ወይም ፍቺ ሲፈጽሙ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያስመዘግቡ ይጠብቅባቸዋል፤ ምክንያቱም የብዙ አገሮች ሕግ እንዲህ እንዲደረግ ያዛል። ቲቶ 3:1⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ትዳር የመሠረትክ ከሆንክ ጋብቻህን ሕጋዊ አድርገሃል?

      አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የግድ መጋባት ያስፈልጋል? እንዲሁ አብሮ መኖር ምን ችግር አለው?”

      • ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      ማጠቃለያ

      ሳያገቡ መኖርም ሆነ ትዳር የይሖዋ ስጦታዎች ናቸው። ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ሰዎች ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እስከኖሩ ድረስ ደስታና እርካታ ማግኘት ይችላሉ።

      ክለሳ

      • ያላገቡ ሰዎች ነፃነታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

      • መጽሐፍ ቅዱስ የእኛ ዓይነት እምነት ያለውን ሰው ብቻ እንድናገባ የሚያዝዘው ለምንድን ነው?

      • በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ፍቺ መፈጸም የሚቻልበት ብቸኛው ምክንያት ምንድን ነው?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      “በጌታ ብቻ” ማግባት ሲባል ምን ማለት ነው?

      “የአንባቢያን ጥያቄዎች” (መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1, 2004)

      ከመጠናናት እና ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱህን ሁለት ቪዲዮዎች ተመልከት።

      ለጋብቻ መዘጋጀት (11:53)

      አንድ ወንድም ይሖዋ የሰጠው ነገር እሱ መሥዋዕት ካደረገው ከየትኛውም ነገር እንደሚበልጥ የሚሰማው ለምንድን ነው?

      እውነትን ትቀበላለች ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር (1:56)

      አንድ ሰው ለመፋታት ወይም ለመለያየት ከመወሰኑ በፊት የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት?

      “አምላክ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ይኑራችሁ” (መጠበቂያ ግንብ ታኅሣሥ 2018)

      a ባለትዳሮች፣ ምንዝር ባይፈጸምም ለመለያየት ሊወስኑ የሚችሉባቸውን ምክንያቶች ለማየት ተጨማሪ ሐሳብ 4⁠ን ተመልከት።

      b በአንዳንድ ባሕሎች ለልጆቻቸው የትዳር አጋር የሚመርጡት ወላጆች ናቸው። እንዲህ ያለ ባሕል ያላቸው አፍቃሪ ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ ሲመርጡ በገንዘብ ወይም በኑሮ ደረጃ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋን የሚወድ ሰው ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።

      c በአሁኑ ወቅት ካላገባሃት ሴት ጋር አብረህ እየኖርክ ከሆነ ለመለየት ወይም ለመጋባት የራስህን ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ