የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አፍቃሪ ለሆኑት እረኞች በትሕትና ተገዙ
    መጠበቂያ ግንብ—2007 | ሚያዝያ 1
    • 7. ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ምን ምክር ሰጥቷል?

      7 በሰማይ ያሉት እረኞቻችን ማለትም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ላስቀመጧቸው የበታች እረኞች እንድንታዘዝና እንድንገዛ ይጠብቁብናል። (1 ጴጥሮስ 5:5) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው። ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጒዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።”—ዕብራውያን 13:7, 17

      8. ጳውሎስ ስለምን ነገር ‘እንድንመለከት’ አበረታቶናል? ‘ታዛዥ’ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

      8 ጳውሎስ፣ ሽማግሌዎች በአኗኗራቸው ታማኝ መሆናቸው ያስገኘላቸውን ውጤት ‘እንድንመለከት’ ወይም በጥንቃቄ እንድንመረምር እንዲሁም በእምነታቸው እንድንመስላቸው አበረታቶናል። ከዚህም በላይ፣ ለእነዚህ የተሾሙ ወንዶች እንድንታዘዝና ለሚሰጡን መመሪያ እንድንገዛ መክሮናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ሪቻርድ ፍራንስ እንደገለጹት በዚህ ጥቅስ ላይ “ታዘዙ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መታዘዝን ለማመልከት የሚሠራበት የተለመደው ቃል” አይደለም። “ከዚህ ይልቅ ይህ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‘አምናችሁ ተቀበሉ’ ማለት ሲሆን ይህም የሽማግሌዎችን የመሪነት ቦታ በፈቃደኝነት መቀበልን ያመለክታል።” ሽማግሌዎችን የምንታዘዘው የአምላክ ቃል እንዲህ እንድናደርግ ስለሚያሳስበን ብቻ ሳይሆን ስለመንግሥቱ ፍላጎትና ስለደህንነታችን ከልብ የሚጨነቁ መሆናቸውን ስለምንገነዘብም ጭምር ነው። የሽማግሌዎችን የመሪነት ቦታ በፈቃደኝነት አምነን መቀበላችን ደስታ እንደሚያመጣልን ጥርጥር የለውም።

      9. ታዛዥ ከመሆን በተጨማሪ ‘መገዛት’ ያለብን ለምንድን ነው?

      9 ይሁንና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሽማግሌዎች ከሚሰጡት መመሪያ የተሻለ አማራጭ እንዳለ ሆኖ ቢሰማንስ? መገዛት የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚገጥሙን ጊዜ ነው። ግልጽ ለሆኑልንና ለምንስማማባቸው መመሪያዎች ወይም ውሳኔዎች መታዘዝ ቀላል ነው፤ ይሁንና መመሪያው ግልጽ በማይሆንልን ጊዜም እንኳ ለመገዛት ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያ የሆነው ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነት የተገዥነት ባሕርይ አሳይቷል።—ሉቃስ 5:4, 5

  • አፍቃሪ ለሆኑት እረኞች በትሕትና ተገዙ
    መጠበቂያ ግንብ—2007 | ሚያዝያ 1
    • 12. የበላይ ተመልካቾች ‘ስለ ነፍሳችን የሚተጉት’ እንዴት ነው?

      12 ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጋር እንድንተባበር የሚያነሳሳን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ‘ስለ ነፍሳችን የሚተጉ’ መሆናቸው ነው። እነዚህ የበላይ ተመልካቾች መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል አንድ ዓይነት ዝንባሌ ወይም ባሕርይ ማሳየት እንደጀመርን ከተገነዘቡ ወዲያውኑ አስፈላጊውን ምክር ይሰጡናል። ይህን የሚያደርጉትም እኛን ለማስተካከል በማሰብ ነው። (ገላትያ 6:1) “ይተጋሉ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ” የሚል ፍቺ አለው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዳሉት ይህ ቃል “እረኛው ሁልጊዜ ንቁ መሆኑን ያመለክታል።” ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው ከመኖር ባሻገር ስለ እኛ መንፈሳዊ ደህንነት በማሰብ እንቅልፍ አጥተው ሊያድሩ ይችላሉ። ታዲያ፣ ‘ታላቅ እረኛ’ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ጥልቅ አሳቢነት ለመኮረጅ ከልብ ከሚጥሩት ከእነዚህ አፍቃሪ እረኞች ጋር በፈቃደኝነት መተባበር አይገባንም?—ዕብራውያን 13:20

      13. የበላይ ተመልካቾችም ሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች በማን ዘንድ ተጠያቂዎች ናቸው? የሚያስጠይቃቸውስ ምንድን ነው?

      13 ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጋር እንድንተባበር የሚያነሳሳን ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ “በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለ” ነው። የበላይ ተመልካቾች በሰማይ ባሉት እረኞች ማለትም በይሖዋና በኢየሱስ ሥር ሆነው የሚያገለግሉ የበታች እረኞች መሆናቸውን አይዘነጉም። (ሕዝቅኤል 34:22-24) የበጎቹ ባለቤት ይሖዋ ሲሆን እርሱም ‘በገዛ ልጁ ደም ዋጅቷቸዋል፤’ በመሆኑም የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች በጎቹን ይሖዋ በሚይዝበት መንገድ ማለትም ‘በርኅራሄ’ ስለመያዛቸው ይጠየቁበታል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28, 29 የታረመው የ1980 ትርጉም) ይህም በመሆኑ ሁላችንም ብንሆን ከይሖዋ ለምናገኘው መመሪያ የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ በእርሱ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን። (ሮሜ 14:10-12) ከዚህም በተጨማሪ፣ ለተሾሙ ሽማግሌዎች መታዘዛችን የጉባኤው ራስ ለሆነው ለክርስቶስ እንደምንገዛ ያሳያል።—ቈላስይስ 2:19

      14. ክርስቲያን ሽማግሌዎች “በሐዘን” እንዲያገለግሉ ምክንያት የሚሆነው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ይህስ ምን ውጤት ይኖረዋል?

      14 ጳውሎስ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በትሕትና መገዛት አስፈላጊ የሆነበትን አራተኛ ምክንያት ሲገልጽ “ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:17) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ማስተማርን፣ እረኝነትን፣ በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆንን፣ ልጆቻቸውን ማሳደግን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች እልባት መስጠትን የመሳሰሉ ከባድ ኃላፊነቶች አሉባቸው። (2 ቆሮንቶስ 11:28, 29) ከሽማግሌዎች ጋር የማንተባበር ከሆነ ተጨማሪ ሸክም እንሆንባቸዋለን። ይህም ‘እንዲያዝኑ’ ምክንያት ይሆናል። የትብብር መንፈስ የማናሳይ ከሆነ ይሖዋን የምናሳዝን ከመሆኑም ባሻገር ለእኛም አይበጀንም። ከዚህ ይልቅ ተገቢ የሆነ አክብሮትና የትብብር መንፈስ ማሳየታችን ሽማግሌዎች ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ያደርጋል፤ እንዲሁም በመካከላችን አንድነት እንዲኖርና በመንግሥቱ ስብከት ሥራ በደስታ እንድንካፈል ይረዳናል።—ሮሜ 15:5, 6

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ