ሌሎች በጎችና አዲሱ ቃል ኪዳን
“መጻተኞች፣ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፣ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ።” —ኢሳይያስ 56:6, 7
1. (ሀ) በዮሐንስ ራእይ መሠረት የይሖዋን የጥፋት ፍርድ የሚያስፈጽሙት ነፋሳት ተይዘው እያለ ምን ነገር ተከናውኗል? (ለ) ዮሐንስ የተመለከተው የትኛውን አስገራሚ የሆነ ብዙ ሕዝብ ነው?
ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ አራተኛ ራእይ ውስጥ ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት በሙሉ ታትመው እስኪያበቁ ድረስ የይሖዋን ፍርድ የሚያስፈጽሙት አውዳሚ ነፋሳት እንደተያዙ ተመልክቷል። ዋነኛው የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት የሚባረኩት የመጀመሪያዎቹ ወገኖች እነዚህ ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ዘፍጥረት 22:18፤ ራእይ 7:1-4) በዚሁ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ የሚከተለውን ሁኔታ ተመልክቷል:- “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ . . . በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” (ራእይ 7:9, 10) እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ማዳን የበጉ ነው’ ማለታቸው እነርሱም ጭምር በአብርሃም ዘር አማካኝነት እንደሚባረኩ ያሳያል።
2. እጅግ ብዙ ሰዎች ብቅ ያሉት መቼ ነው? እንዴትስ ታወቁ?
2 እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን መሆናቸው የታወቀው በ1935 ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከአምስት ሚልዮን በላይ ሆኗል። ታላቁን መከራ በሕይወት እንዲያልፉ ምልክት የተደረገላቸው በመሆናቸው ኢየሱስ “በጎችን” “ከፍየሎች” በሚለይበት ጊዜ ለዘላለም ሕይወት ይለያሉ። በእጅግ ብዙ ሰዎች ውስጥ የታቀፉት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ስለ በጎች በረት በሰጠው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት “ሌሎች በጎች” ናቸው። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—ማቴዎስ 25:31-46፤ ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 21:3, 4
3. በአዲሱ ቃል ኪዳን ረገድ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ሌሎች በጎች የሚለያዩት እንዴት ነው?
3 መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ በአብርሃም ቃል ኪዳን አማካኝነት የሚመጡትን በረከቶች የሚያገኙት በአዲሱ ቃል ኪዳን በኩል ነው። የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋዮች እንደመሆናቸው መጠን ‘ይገባናል የማንለው ፍቅራዊ ደግነቱ’ ተጠቃሚዎች ከመሆናቸውም ሌላ ‘ከክርስቶስ ሕግ በታች’ ናቸው። (ሮሜ 6:15፤ 1 ቆሮንቶስ 9:21) በመሆኑም በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን የሚካፈሉት የአምላክ እስራኤል 144,000 አባላት ብቻ መሆናቸው የተገባ ነው፤ ኢየሱስም ቢሆን የመንግሥት ቃል ኪዳን ያደረገው ከእነርሱ ጋር ብቻ ነው። (ሉቃስ 22:19, 20, 29) የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች አይደሉም። ይሁን እንጂ ከአምላክ እስራኤል ጋር ይተባበራሉ፣ ‘በምድራቸውም’ አብረዋቸው ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 66:8 NW) ስለዚህ እነርሱም ቢሆኑ ይገባናል የማንለው የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ሌላ ከክርስቶስ ሕግ በታች ናቸው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል። የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ባይሆኑም የቃል ኪዳኑ ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
“መጻተኞች” እና ‘የአምላክ እስራኤል’
4, 5. (ሀ) በኢሳይያስ ገለጻ መሠረት ይሖዋን የሚያገለግለው ቡድን የትኛው ነው? (ለ) ኢሳይያስ 56:6, 7 በእጅግ ብዙ ሰዎች ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
4 ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉትንም መጻተኞች፣ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፣ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፣ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ . . . የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ።” (ኢሳይያስ 56:6, 7) ይህ፣ በእስራኤል ዘመን “መጻተኞች” ማለትም እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች ይሖዋን ያመልኩት ይኸውም ስሙን ይወዱ፣ የሕጉን ቃል ኪዳን ስምምነት ይታዘዙ፣ ሰንበትን ይጠብቁና በቤተ መቅደሱ ማለትም በአምላክ “የጸሎት ቤት” መሥዋዕት ያቀርቡ እንደነበር ያሳያል።—ማቴዎስ 21:13
5 በዘመናችን ‘ወደ ይሖዋ የተጠጉት መጻተኞች’ እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከአምላክ እስራኤል ጋር በመተባበር ይሖዋን ያገለግላሉ። (ዘካርያስ 8:23) እነርሱም ልክ እንደ አምላክ እስራኤል ተመሳሳይ የሆነ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ያቀርባሉ። (ዕብራውያን 13:15, 16) አምልኳቸውንም በአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማለትም በእርሱ “የጸሎት ቤት” ውስጥ ያከናውናሉ። (ከራእይ 7:15 ጋር አወዳድር።) ሳምንታዊውን ሰንበትስ ይጠብቃሉ? ቅቡዓኖቹም ሆኑ ሌሎች በጎች እንዲህ እንዲያደርጉ አልታዘዙም። (ቆላስይስ 2:16, 17) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ቅቡዓን ለነበሩት የዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏል:- “እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።” (ዕብራውያን 4:9, 10) እነዚያ ዕብራውያን ራሳቸውን “ለእግዚአብሔር ጽድቅ” ባስገዙና በሕግ ሥራ ራሳቸውን ለማጽደቅ ከመሞከር ባረፉ ጊዜ ወደ አምላክ “የሰንበት ዕረፍት” ገብተዋል። (ሮሜ 10:3, 4) ከአሕዛብ የመጡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለይሖዋ ጽድቅ በማስገዛት ተመሳሳይ እረፍት ያገኛሉ። እጅግ ብዙ ሰዎችም የዚህ እረፍት ተካፋይ ናቸው።
6. በአሁኑ ጊዜ ሌሎች በጎች ከአዲሱ ኪዳን በታች የሆኑት እንዴት ነው?
6 ከዚህም በላይ የጥንቶቹ መጻተኞች ከሕጉ ቃል ኪዳን በታች እንደነበሩ ሁሉ ሌሎች በጎችም ከአዲሱ ቃል ኪዳን በታች ናቸው። በምን መንገድ? የቃል ኪዳኑ ተካፋዮች በመሆን ሳይሆን ከዚያ ጋር ለተያያዙት ሕጎች በመገዛትና ከዝግጅቱ ተጠቃሚዎች በመሆን ነው። (ከኤርምያስ 31:33, 34 ጋር አወዳድር።) እንደ ቅቡዓን ጓደኞቻቸው ሁሉ ሌሎች በጎችም የይሖዋ ሕግ ‘በልባቸው’ ተጽፎላቸዋል። ለይሖዋ ትእዛዛትና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ልባዊ ፍቅር ያላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ሕጎቹን ይታዘዛሉ። (መዝሙር 37:31፤ 119:97) እንደ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እነርሱም ይሖዋን ያውቁታል። (ዮሐንስ 17:3) ስለ ግርዘትስ ምን ማለት ይቻላል? አዲሱ ቃል ኪዳን ከመቋቋሙ 1,500 ዓመታት በፊት ሙሴ እስራኤላውያንን “የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸው ነበር። (ዘዳግም 10:16፤ ኤርምያስ 4:4) ግዴታ የነበረው ሥጋዊ ግርዘት ከሕጉ ጋር ቢያልፍም ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች ልባቸውን ‘መግረዝ’ ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 2:11) በመጨረሻም ይሖዋ በፈሰሰው የኢየሱስ ‘የቃል ኪዳን ደም’ አማካኝነት የሌሎች በጎችን በደል ይቅር ይልላቸዋል። (ማቴዎስ 26:28፤ 1 ዮሐንስ 1:9፤ 2:2) ይሖዋ እንደ 144,000ዎቹ እነርሱን መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ አይቀበላቸውም። ይሁን እንጂ ልክ አብርሃም ጻድቅ ሆኖ የተቆጠረ የአምላክ ወዳጅ ሊሆን እንደቻለ ሁሉ፣ ሌሎች በጎችንም እንደ ጻድቅ አድርጎ ይቆጥራቸዋል።—ማቴዎስ 25:46፤ ሮሜ 4:2, 3፤ ያዕቆብ 2:23
7. እንደ አብርሃም ጻድቃን ሆነው ለተቆጠሩት ሌሎች በጎች ዛሬ ምን ተስፋዎች ተከፍቶላቸዋል?
7 አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ ጻድቅ ሆነው መቆጠራቸው በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ እንዲያገኙ በር ከፍቶላቸዋል። (ሮሜ 8:16, 17፤ ገላትያ 2:16) ሌሎች በጎች ደግሞ ጻድቅ እንደሆኑ የአምላክ ወዳጆች ተደርገው መቆጠራቸው አንድም የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል በመሆን ከአርማጌዶን በሕይወት ተርፈው አለዚያም ‘በጻድቃን ትንሣኤ’ አማካኝነት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። (ሥራ 24:15) እንዲህ ዓይነት ተስፋ ማግኘትና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ወዳጅ መሆን እንዲሁም ‘በእርሱ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት መቀመጥ’ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (መዝሙር 15:1, 2) አዎን፣ ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች በጎች የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት አስደናቂ በሆነ መንገድ ተባርከዋል።
ብልጫ ያለው የሥርየት ቀን
8. በሕጉ ሥር ይከናወኑ የነበሩት የስርየት ቀን መሥዋዕቶች ለምን ነገር ጥላ ነበሩ?
8 ጳውሎስ ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ሲናገር አድማጮቹን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ስለነበረው የስርየት ቀን አስታውሷቸዋል። በዚያ ዕለት የተለያዩ መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር፤ ይኸውም አንዱ ለሌዊ የካህናት ነገድ ሲሆን ሌላው ደግሞ የካህናት ነገድ ላልሆኑት ለተቀሩት 12 ነገዶች የሚቀርብ ነበር። ይህ ነገር ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው 144,000ዎቹም ሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ታላቁን የኢየሱስ መሥዋዕት እንደሚያመለክት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲገለጽ ቆይቷል።a ጳውሎስ ይህ ፍጻሜውን እንዴት እንደሚያገኝ ሲገልጽ ሰዎች ከክርስቶስ መሥዋዕት ተጠቃሚ የሚሆኑት በአዲስ ኪዳን ሥር በሚኖረው የሚበልጥ የሥርየት ቀን አማካኝነት እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ በዚህ ታላቅ ቀን ሊቀ ካህን ሆኖ የሚያገለግል እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጅ “የዘላለም መዳን” እንዲያገኝ ሲል ፍጹም የሆነውን ሕይወቱን የስርየት መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል።—ዕብራውያን 9:11-24
9. ዕብራውያን ክርስቲያኖች በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ በመታቀፋቸው ምን ነገር መጨበጥ ችለው ነበር?
9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ ዕብራውያን ክርስቲያኖች “ለ[ሙሴ] ሕግ ይቀኑ” ነበር። (ሥራ 21:20) እንግዲያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ማሳሰቢያ መስጠቱ የተገባ ነበር:- “የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን ዘላለማዊ ርስት እንዲወርሱ፣ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማዕከላዊ ሆኗል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን ከመጀመሪያው ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው።” (ዕብራውያን 9:15 የ1980 ትርጉም) አዲሱ ቃል ኪዳን የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ኃጢአተኛነታቸውን ገሃድ ካወጣው አሮጌ ቃል ኪዳን ነጻ አድርጓቸዋል። ለአዲሱ ቃል ኪዳን ምስጋና ይግባውና “ዘላለማዊ [የሰማይ] ርስት” መውረስ ችለዋል።
10. ቅቡዓንና ሌሎች በጎች አምላክን የሚያመሰግኑበት ምን ምክንያት አላቸው?
10 “በልጁ የሚያምን ሁሉ” ከቤዛዊ መሥዋዕቱ ተጠቃሚ ይሆናል። (ዮሐንስ 3:16, 36) ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስ ደግሞ፣ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሠዋ በኋላ፣ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታያቸዋል።” (ዕብራውያን 9:28) ዛሬ ኢየሱስን ከሚጠባበቁት መካከል በሕይወት ያሉት የአምላክ እስራኤል ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል የሆኑት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። እጅግ ብዙ ሰዎችም ቢሆኑ ውርሻቸው ዘላለማዊ ነው። ሁለቱም ወገኖች ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን እንዲሁም የሚበልጠውን የስርየት ቀንና ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ በሰማያዊው ቅድስተ ቅዱሳን የሚያከናውነውን አገልግሎት ጨምሮ ከዚህ ቃል ኪዳን ጋር ተያይዘው ስለሚመጡት ሕይወት ሰጪ በረከቶች አምላክን ያመሰግኑታል።
በቅዱስ አገልግሎት መጠመድ
11. ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ባገኙት ንጹህ ሕሊና በደስታ ምን ያደርጋሉ?
11 ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ በአሮጌው ኪዳን ሥር ለኃጢአት ይቅርታ ይቀርቡ ከነበሩት መሥዋዕቶች ጋር በማወዳደር በአዲሱ ቃል ኪዳን ዝግጅት ውስጥ የቀረበው የኢየሱስ መሥዋዕት እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ዕብራውያን 9:13-15) የተሻለው የኢየሱስ መሥዋዕት ‘ሕያው ለሆነው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ከሞተ ሥራ ሕሊናችንን ሊያነጻልን’ ይችላል። ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እነዚህ ‘የሞቱ ሥራዎቸ’ ‘በመጀመሪያው ኪዳን ሥር ሆነው የፈጸሟቸውን መተላለፎች’ ይጨምራሉ። ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ደግሞ ቀደም ሲል ባሳለፉት ሕይወት የሠሯቸውንና እውነተኛ ንስሐ ገብተው አምላክ ይቅር ያለላቸውን ኃጢአቶች ይጨምራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በንጹሕ ሕሊና ‘ለሕያው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ።’ እጅግ ብዙ ሰዎችም እንዲሁ። “በበጉ ደም” ሕሊናቸውን ስላነጹ በአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ “ቀንና ሌት ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ።”—ራእይ 7:14, 15 NW
12. ‘ስለ እምነታችን ሙሉ ትምክህት’ እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው?
12 ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት [“ስለ እምነታችን ሙሉ ትምክህት ኖሮን፣” NW] በቅን ልብ እንቅረብ።” (ዕብራውያን 10:22) “ስለ እምነታችን ሙሉ ትምክህት” እንዳለን እንዴት ማሳየት እንችላለን? ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧል:- “የ[ሰማያዊ] ተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:23-25) እኛም ብንሆን እምነታችን ሕያው ከሆነ ‘መሰብሰባችንን አንተውም።’ ወንድሞቻችንን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ስናነቃቃቸውና እኛም በእነርሱ ስንነቃቃ እንዲሁም ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ስለ ተስፋችን ለሕዝብ ለማወጁ አንገብጋቢ ሥራ የሚያነቃቃንን ብርታት ስናገኝ ደስ ይለናል።—ዮሐንስ 13:35
‘የዘላለሙ ቃል ኪዳን’
13, 14. አዲሱ ቃል ኪዳን ዘላለማዊ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
13 ከመቶ አርባ አራት ሺህዎቹ መካከል የመጨረሻዎቹ ሰማያዊ ተስፋውን ሲጨብጡ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል? አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን ያቆማልን? በዚያ ጊዜ በምድር ላይ የሚቀር የአምላክ እስራኤል አባል አይኖርም። ሁሉም የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ከኢየሱስ ጋር ‘በአባቱ መንግሥት’ ይገኛሉ። (ማቴዎስ 26:29) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ‘የሰላም አምላክ በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን አወጣው’ ሲል የተናገራቸውን ቃላት እናስታውሳለን። (ዕብራውያን 13:20፤ ኢሳይያስ 55:3) አዲሱ ቃል ኪዳን ዘላለማዊ የሆነው በምን መንገድ ነው?
14 በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ሕጉ ቃል ኪዳን በሌላ የሚተካ አይደለም። ሁለተኛ ደግሞ ልክ እንደ ኢየሱስ ንግሥና የሚያስገኘውም ውጤት ዘላቂ ነው። (ሉቃስ 1:33ን ከ1 ቆሮንቶስ 15:27, 28 ጋር አወዳድር።) ሰማያዊው መንግሥት በይሖዋ ዓላማዎች ውስጥ ያለው ቦታ ዘላለማዊ ነው። (ራእይ 22:5) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ሌሎች በጎችም ከአዲሱ ኪዳን ዝግጅት መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅትም የታመኑ ሰዎች እንደዛሬው ‘ለይሖዋ ሌትና ቀን በመቅደሱ ቅዱስ አገልግሎት’ ማቅረባቸውን ይቀጥላሉ። ይሖዋ በኢየሱስ ‘የቃል ኪዳን ደም’ አማካኝነት ይቅር የተባለላቸውን የቀድሞ ኃጢአታቸውን ዳግመኛ አያስብም። የይሖዋ ወዳጆች በመሆን በፊቱ ጻድቅ ሆነው መመላለሳቸውን ይቀጥላሉ፤ ሕጉም በልባቸው ውስጥ እንደተጻፈ ይኖራል።
15. ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከምድራዊ አምላኪዎቹ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ግለጽ።
15 ይሖዋ እነዚህ ሰብዓዊ አገልጋዮቹን በሚመለከት ‘እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፣ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል’ ሊል ይችል ይሆን? አዎን። “ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።” (ራእይ 21:3 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ‘የቅዱሳን ሰፈር’ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ ሙሽራ የሆነችው ‘የተወደደችው ከተማ’ ምድራዊ ወኪሎች ይሆናሉ። (ራእይ 14:1፤ 20:9፤ 21:2) ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው በፈሰሰው የኢየሱስ ‘የቃል ኪዳን ደም’ ላይ ባላቸው እምነትና በምድር ሳሉ የአምላክ እስራኤል ለነበሩት ለሰማያዊዎቹ ነገሥታትና ካህናት ራሳቸውን በማስገዛታቸው ነው።—ራእይ 5:10
16. (ሀ) ምድራዊ ትንሣኤ የሚያገኙትን ሙታን ምን ሁኔታ ይጠብቃቸዋል? (ለ) በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ምን በረከቶች ይመጣሉ?
16 በምድር ላይ ትንሣኤ አግኝተው ስለሚነሡት ሙታንስ ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐንስ 5:28, 29) እነርሱም ጭምር የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት ‘ራሳቸውን እንዲባርኩ’ ግብዣ ይቀርብላቸዋል። (ዘፍጥረት 22:18) እነርሱም ቢሆኑ የይሖዋን ስም መውደድ፣ እርሱን ማገልገል፣ ተቀባይነት ያላቸው መሥዋዕቶች ማቅረብና በጸሎት ቤቱ ቅዱስ አገልግሎት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉ ወደ አምላክ ዕረፍት ይገባሉ። (ኢሳይያስ 56:6, 7) በሺህው ዓመት መጨረሻ ላይ የታመኑ ሆነው የተገኙት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስና በ144,000 ረዳት ካህናቱ አገልግሎት አማካኝነት ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። እንደ አምላክ ወዳጆች ጻድቃን ሆነው ከመቆጠር አልፈው ጻድቃን ይሆናሉ። ከአዳም ከወረሱት ኃጢአትና ሞት ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለሚሆኑ ‘በሕይወት ይኖራሉ።’ (ራእይ 20:5፤ 22:2) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ይሆናል! ዛሬ ካለን ማስተዋል አንጻር የኢየሱስ እና የ144,000ዎቹ የክህነት ሥራ በዚያን ጊዜ የሚጠናቀቅ ይመስላል። ታላቁ የሥርየት ቀን የሚያስገኛቸው በረከቶች ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ‘መንግሥቱን መልሶ ለአምላኩና ለአባቱ ያስረክባል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:24) ለሰው ልጅ የመጨረሻ ፈተና ከቀረበ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:7, 10
17. ከፊታችን ከሚጠብቀን ደስታ አንጻር የእያንዳንዳችን ቁርጥ ውሳኔ ምን መሆን አለበት?
17 ‘የዘላለሙ ቃል ኪዳን’ በዚያን ጊዜ በሚጀምረው አስደናቂ ዘመን ውስጥ የሚጫወተው ሚና ይኖር ይሆን? ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ይሖዋ ዛሬ የሚያስፈልገንን ያህል አሳውቆናል። ልዩ ትንግርት ነው። ‘የአዲሱ ሰማይና የአዲሱ ምድር’ ክፍል በመሆን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስቡት! (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህንን ተስፋ ለመውረስ ያለንን ምኞት ምንም ነገር እንዲያዳክምብን አንፍቀድ። ጸንቶ መቆም ቀላል ላይሆን ይችላል። ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል” ብሏል። (ዕብራውያን 10:36) ይሁንና ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥመን፣ የቱንም ያህል ተቃውሞ ቢመጣብን ከፊታችን ከሚጠብቀን ደስታ አንጻር ከምንም እንደማይቆጠር አትዘንጉ። (2 ቆሮንቶስ 4:17) እንግዲያውስ ማንኛችንም ብንሆን ‘ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት’ መካከል አንሁን። ይልቁንም “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ” መካከል መሆናችንን አናረጋግጥ። (ዕብራውያን 10:39) ሁላችንም የቃል ኪዳን አምላክ በሆነው በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ይኑረን፤ ይህም ሁላችንም ዘላለማዊ በረከት እንድናገኝ ያስችለናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 13ን ተመልከት።
ነጥቡ ገብቶሃልን?
◻ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች በተጨማሪ በአብርሃም ዘር የሚባረኩት እነማን ናቸው?
◻ በአዲሱ ቃል ኪዳን በመባረክ ረገድ ሌሎች በጎች በአሮጌው ኪዳን ሥር ከነበሩት ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
◻ ሌሎች በጎች በሚበልጠው የስርየት ቀን ዝግጅት አማካኝነት የተባረኩት እንዴት ነው?
◻ ጳውሎስ አዲሱን ቃል ኪዳን ‘የዘላለም ቃል ኪዳን’ ሲል የጠራው ለምንድን ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚቀርበው ቅዱስ አገልግሎት
እጅግ ብዙ ሰዎች ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ሆነው በይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ውስጥ አምልኮአቸውን ያከናውናሉ። (ራእይ 7:14, 15፤ 11:2) እነርሱ የሚገኙት በተለየ የአሕዛብ አደባባይ ውስጥ ነው ብለን የምንደመድምበት ምንም ምክንያት የለም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የአሕዛብ አደባባይ ነበር። ይሁን እንጂ ከመለኮታዊ ምንጭ በተገኘው ንድፍ በተሠራው የሰሎሞን ቤተ መቅደስም ሆነ በሕዝቅኤል ቤተ መቅደስ ውስጥ የአሕዛብ አደባባይ የሚባል ዝግጅት አልነበረም። በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውስጥ እስራኤላውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ወንድ ሴት ሳይል አንድ ላይ አምልኮአቸውን የሚያከናውኑበት ውጨኛ አደባባይ ነበር። ይህ እጅግ ብዙ ሰዎች ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡበት ዮሐንስ የተመለከተውን የመንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ የሚያመለክት ትንቢታዊ ጥላ ነበር።
ይሁን እንጂ ታላቁ መሠዊያ ወደ ሚገኝበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ መግባት የሚችሉት ካህናትና ሌዋውያን ብቻ የነበሩ ሲሆን ወደ ቅድስት የሚገቡት ደግሞ ካህናት ብቻ ነበሩ። እንዲሁም ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የሚችለው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር። ውስጠኛው አደባባይና ቅድስቱ በጥላነት የሚያመለክቱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ሳሉ የሚኖራቸውን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ እንደሆነ ተረድተናል። ቅድስተ ቅዱሳኑ ደግሞ የሚያመለክተው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሰማያዊ ሊቀ ካህናታቸው ጋር የማይሞት ሕይወት የሚያገኙበትን ሰማይን ነው።—ዕብራውያን 10:19, 20
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከፊታችን ከሚጠብቀን ደስታ አንጻር ‘ሕይወታችንን የሚያድን እምነት’ ይኑረን