ምዕራፍ 12
የአምላክ አዲስ ቃል ኪዳን ዓላማውን የሚያከናውንበት ጊዜ ቀርቧል
1. (ሀ) አምላክ ቀንን በሚመለከትና ሌሊትን በሚመለከት ቃል ኪዳኑን ባይጠብቅ ኖሮ ምድራችን ምን ትሆን ነበር? (ለ) አምላክ ከቃል ኪዳኖቹ ጋር በታማኝነት የተጣበቀ በመሆኑ ስለምን ነገር እርግጠኛ ለመሆን እንችላለን?
አምላክ ቀንን በሚመለከትና ሌሊትን በሚመለከት ቃል ኪዳኑን ባይጠብቅ ኖሮ ምን እናደርግ ነበር? ምድራችን ቀንና ሌሊት የሚፈራረቍባት መሆኗ ቀርቶ የማያቋርጥ ብርሃን የሚበራባት ወይም በማያቋርጥ ጨለማ የተሸፈነች ትሆን ነበር። (ዘፍጥረት 1:1, 2, 14–19) ነገር ግን አምላክ በታማኝነት በቃል ኪዳኖቹ ይጸናል። ስለዚህ ጨረቃ፣ ፀሐይና በሰማይ ያሉት የከዋክብት ረጨቶች ፕላኔቷ ምድራችንም ብትሆን ፈጽሞ እንደማይጠፉ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን።
2. ይሖዋ የቀኑንና የሌሊቱን ቃልኪዳኑን በሚመለከት ለአይሁዳውያን ምን ነግሯቸው ነበር?
2 አምላክ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኑን በሚመለከት በዳዊት ቤት ስርወ መንግሥት ሥር ይገዙ ለነበሩት አይሁዳውያን ሲናገር እንዲህ አለ:- “ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪያዬ ከዳዊት ጋር ከአገልጋዮቹም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳን ደግሞ ይፈርሳል።”— ኤርምያስ 33:20, 21
3. እነዚህስ ቃላት ስለ ዘላለማዊ መንግሥት ከዳዊት ጋር ስለ ገባው ቃል ኪዳኑ ምን ነገር ያመለክታሉ?
3 በእነዚህ ቃላት ውስጥ መሬታችን ከፀሐይና ከጨረቃ ጋር ለዘላለም እንደምትኖር በተዘዋዋሪ መንገድ ማስረጃ ተሰጥቷል። (መክብብ 1:4) ምድራችን ሰብዓዊ ነዋሪዎች ለሁልጊዜ ይቀመጡባታል። እነርሱም ቃል ኪዳን ጠባቂ በሆነው አምላክ ማለትም በሰው ፈጣሪ መሪነት የቀኑንና የሌሊቱን ግርማ እያዩ በደስታ ይኖራሉ። ይሖዋ የቀን ቃል ኪዳኑንም ሆነ የሌሊት ቃል ኪዳኑን ሳያዛባ አጥብቆ እንደሚይዘው ሁሉ ከጥንቱ ንጉሥ ዳዊት ጋር በዳዊት የቤተሰብ መስመር አማካኝነት የገባውን የዘላለማዊ መንግሥት ቃል ኪዳኑንም በታማኝነት ጠብቋል። የመንግሥቱ መቀመጫ ከመሬት ወደማይታየው ሰማይ የሚዘዋወር ቢሆንም እንኳ ይህ ነገር እውነት ነው።— መዝሙር 110:1–3
4. (ሀ) አምላክ ስለ ዘላለማዊ መንግሥት ከዳዊት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ከየትኛው ሌላ ቃል ኪዳን ጋር ዝምድና አለው? (ለ) ይህንንስ በሚመለከት ኢየሱስ ምን አለ? በምንስ ሁኔታዎች ስር?
4 በዳዊት የትውልድ መሥመር ውስጥ ለዘላለማዊ መንግሥት የተደረገው የአምላክ ቃል ኪዳን ከሌላ ቃል ኪዳን ጋር ይኸውም ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር የተያያዘ ነው። ይህ አሮጌውን ቃል ኪዳን የሚተካ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ተጠቅሶ ነበር። ይህም የሆነው በኒሣን 14, 33 እዘአ ምሽት ላይ የአይሁዶችን የማለፍ በዓል ከታማኝ ደቀመዛሙርቱ ጋር ካከበረ በኋላ ነበር። በዚያን ጊዜ “የጌታ እራት” ተብሎ የተጠራውን አቋቋመ። በዚያኑ የማለፍ በዓል ዕለት ደሙን መስዋዕት አድርጎ ማፍሰስ እንዳለበት ያውቅ ነበር። በዚህም ምክንያት አንድ ጽዋ ወይን ወሰደ፣ እርሱንም ለታማኝ ሐዋርያቱ ከማሳለፉ በፊት “ይህ ጽዋ ማለት በደሜ የሚሆን አዲስ ቃል ኪዳን ነው” አለ።— ሉቃስ 22:20 አዓት፤ 1 ቆሮንቶስ 11:20, 23–26
5. አምላክ አዲስ ቃል ኪዳን ለማድረግ ቃል የገባው ለማን ነበር? የእስራኤል ሪፖብሊክ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ገብቻለሁ ትላለችን?
5 እንደ አሮጌው ቃል ኪዳን ሁሉ አዲሱም ቃል ኪዳን የተደረገው ከአንድ ሕዝብ ጋር ነው፤ ይሁን እንጂ ከየትኞቹም የስመ ክርስትና ብሔራት ጋር አይደለም። የአዲሱ ቃል ኪዳን ተስፋ ከ2, 500 ዓመታት በፊት በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ለእስራኤል ሕዝብ የተገለጸ ቢሆንም እንኳ የዛሬዋ የእስራኤል ሪፖብሊክ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንደገባች አትናገርም። በዚህ ፋንታ የእስራኤል ሪፓብሊክ የተባበሩት መንግሥታት አባል ሆናለች።
6. በኤርምያስ ምዕራፍ 31 መሠረት አምላክ አዲስ ቃል ኪዳን ማድረጉን አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት የሚያስከትል ይሆናል?
6 አምላክ አዲስ ቃል ኪዳን የፈለገው ለምን ነበር? ኤርምያስ 31:31–34 እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “እነሆ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል [ይሖዋ (አዓት)]፤ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱም በኪዳኔ አልጸኑምና፣ እኔም ቸል አልኋቸው፣ ይላል [ይሖዋ (አዓት)]። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል [ይሖዋ (አዓት)]፤ ሕጌን በልቦናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን እያንዳንዱም ወንድሙን:- [ይሖዋን (አዓት)] እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፣ ይላል [ይሖዋ (አዓት)]። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።”
የተሻለ ቃል ኪዳን ከተሻለ መካከለኛ ጋር
7. አዲሱ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን ያፈረሱት ቃል ኪዳን በአዲስ መልክ ተቋቍሞ የቀረበ ነውን? ከሕጉ ቃል ኪዳን የተሻለ የሆነውስ ለምንድን ነው?
7 አዲሱ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን ያፈረሱት የቀድሞው ቃል ኪዳን በአዲስ መልክ ተቋቍሞ የቀረበ ነገር አይደለም። በፍጹም እንደዚህ አይደለም! ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ይገኙ ለነበሩት ክርስቲያኖች “ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና” በማለት ጽፎላቸው ነበር። (ሮሜ 6:14) ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን እንዲገቡ የሚፈቅድላቸውን በሚመለከት ነገሮችን ሊያሻሽላቸው ስለሚችል በእርግጥ ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ነው። አዲሱን ቃል ኪዳን ሲመሠርት አንድን የተሻለ መካከለኛ ወይም አዋዋይ አስነሳ። ይህ መካከለኛ ኃጢአት እንደበከለው ሰው እንደ ሙሴ ፍጽምና የጎደለው አይደለም።
8. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን ከሕጉ ቃል ኪዳን የተሻለ የሚያደረገው ምን ነገር አለው? (ለ) የተሻለው የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ማን ነው? (ሐ) ዕብራውያን 8:6, 13 ስለ አዲሱ ቃል ኪዳንና መካከለኛው ብልጫ ያለው ስለመሆኑ ምን ይናገራል? በቀድሞ ቃል ኪዳንስ ላይ ምን ውጤት የሚያስከትል ይሆናል?
8 በነቢዩ ሙሴ መካከለኝነት የተደረገው የሕግ ቃል ኪዳን በራሱ ጥሩ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ያ ቃል ኪዳን ሰብዓዊ ኃጢአቶችን በፍጹም ሊያጥብ የማይችለውን የእንስሳት መስዋዕታዊ ደም ማቅረብን ይጨምር ነበር። ስለዚህ ይሖዋ አምላክ የተሻለ ቃል ኪዳን እንዲያቋቁም ከተሻለ መስዋዕት ጋር የተሻለ መካከለኛ መገኘት ነበረበት። ይህ በሁሉም በኩል አስፈላጊ የሆነው መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ተገኘ። ይህ መካከለኛ ከነቢዩ ሙሴ ጋር ሲወዳደር ያለውን ከፍተኛ ብልጫ ለይቶ ለማመልከት መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን መግለጫ ይሰጠናል:- “አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል [በሕጋዊ መንገድ] በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን፣ በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል [የሕዝብ] አገልግሎት አግኝቶአል። . . . [‘አዲስ ቃል ኪዳን’] በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቷል።”— ዕብራውያን 8:6, 13
‘ያረጀው’ አሮጌ ቃል ኪዳን በሌላ ተተክቷል
9. (ሀ) አሮጌው ቃል ኪዳን ያበቃው በምን ቀን ላይ ነበር? (ለ) በዚያን ዕለት ጠዋት ምን ነገር ሆነ? ለምንስ ነገር ማረጋገጫ ሆነ?
9 ‘ያረጀው’፣ ጊዜ ያለፈበት ቃል ኪዳን የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ከሞት ከተነሳ ከ50 ቀናት በኋላ ተወግዷል። ይህም የሆነው በጴንጠቆስጤ ዕለት ነበር። በዚያኑ ዕለት ጠዋት የአይሁዶች የእህል መክተቻ በዓል ምሳሌ የሆነለት እውነተኛው ነገር መፈጸም ጀምሮ ነበር። እንዴት? 120 የሚያክሉ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ታማኝ ደቀመዛሙርት በኢየሩሳሌም በአንድ ፎቅ ውስጥ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ በኢዩኤል 2:28–32 ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ። ይህም ለሁሉም ተመልካቾች የሚሰማና የሚታይ ማስረጃ በማቅረብ የአዲሱን ቃል ኪዳን መጀመር አረጋገጠ።
10. በጴንጠቆስጤ ዕለት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ መቀባታቸው ግልጽ የሆነው አንዴት ነበር?
10 ኢየሱስ ከተጠመቀበት ውሃ ውስጥ ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ሲፈስስበት መንፈሱ በተዓምር ከራሱ ላይ በሚያንዣብብ ርግብ ተመስሎ ነበር። ይሁን እንጂ በጴንጠቆስጤ ዕለት ዕብራውያን የሆኑት 120 ደቀመዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸው በግልጽ የታወቀው እንዴት ነበር? ከራሳቸው በላይ እንደ እሳት የመሰሉ ልሳኖች በመታየታቸውና የአምላክን ቃል ከዚያ በፊት በፍጹም በማያውቋቸው የሌላ አገር ቋንቋዎች ለማወጅ ችሎታ በማግኘታቸው ነበር።— ማቴዎስ 3:16፤ ሥራ 2:1–36
11. (ሀ) ለአይሁዳውያን ግልጽ መሆን የነበረበት ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) አይሁዶች እርስ በእርሳቸው “ይሖዋን እወቅ!” እንደማይባበሉ እንዴት እናውቃለን? ምንስ ደስታ የላቸውም?
11 ከዚህ በኋላ ለአይሁዶችና ለረቢዎቻቸው የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን እንደማይሠራ ግልጽ መሆን ነበረበት። እነርሱ በ70 እዘአ ኢየሩሳሌም በሮማውያን ሠራዊት ከጠፋችበት ጊዜ ጀምሮ ቤተመቅደስ አልነበራቸውም። በዚያን ጊዜ የትውልድ ሐረግ መዝገቦቻቸው ጠፍተው ወይም ተደምስሰው ነበር። በዚህም ምክንያት ዛሬ ከሌዊ ነገድ የሆነው ማን እንደሆነና ለአይሁድ ሕዝብ ሊቀካህን ሆኖ ለማገልገል ችሎታ ያለው የአሮን ዝርያ ማን መሆኑን አያውቁም። እርስ በእርሳቸውም “ይሖዋን እወቅ!” ከመባባል ይልቅ መለኮታዊውን ስም መጥራቱ ስሙን ማራከስ እንደሆነ ይቆጥሩታል። በዚህም ምክንያት ‘ያረጀው’ አሮጌ ቃል ኪዳን በአዲስ ቃል ኪዳን መተካቱን አውቀው የይሖዋ ምስክሮች ካገኙት ደስታ ተካፋይ አይሆኑም።
“ዘላለማዊ ቃል ኪዳን”
12. (ሀ) የይሖዋ ምስክሮች ከልባቸው በየትኛው ጸሎት ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ? (ለ) ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ከምን ጋር ነበር?
12 ዛሬ ካሉት አይሁዶች ሁኔታ ጋር በጕልህ በሚለይ መንገድ የይሖዋ ምስክሮች በሰማያት በአምላክ ቀኝ የተቀመጠ፣ ሕያው የሆነና በሥራ ላይ ያለ ሊቀካህን አላቸው። እርሱም የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ነው፣ ከሙሴም እጅግ በጣም የሚበልጥ መካከለኛ ነው። እነዚህ የይሖዋ ምስክሮች የዕብራውያን 13:20, 21 ጸሐፊ ባቀረበው ጸሎት ከልባቸው ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ:- “በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ . . . ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን (የታጠቃችሁ) ያድርጋችሁ።” ይህ “ትልቅ እረኛ” “ለበጎቹ” ሲል ሰብዓዊ ሕይወቱን የሰጠ በመሆኑ የማይሞትና ደም አልባ የሆነ መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት ሊነሳ ችሏል፣ ይህም የሆነው በታማኝነት በተጠበቀውና በሚያስከትላቸው መልካም ውጤቶች ዘላለማዊ በሆነው የአዲስ ኪዳን ደሙ ዋጋ ነው።
13. (ሀ) የይሖዋ ምስክሮች በየዓመቱ የአዲሱን ቃል ኪዳን መካከለኛ ሞት የሚያስታውሱት እንዴት ነው? (ለ) ምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ ምን ያመለክታሉ?
13 የይሖዋ ምስክሮች በየዓመቱ በሚያከብሩት “በጌታ ራት” መታሰቢያ በዓል ላይ የአዲሱን ቃል ኪዳን መካከለኛ የኢየሱስ ክርስቶስን መስዋዕታዊ ሞት ያስታውሱታል። በዚያም ‘የእራት’ በዓል ላይ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡት የሚካፈሉት ያልቦካ ቂጣ የመካከለኛውን ፍጹም ሥጋ ያመለክታል፤ ወይኑም በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት የመካከለኛውን የሕይወት ዋጋ የያዘውን ንጹህና ያልተበከለ ደም ያመለክታል።— 1 ቆሮንቶስ 11:20–26፤ ዘሌዋውያን 17:11
14. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡት ሁሉ በመታሰቢያው ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና ወይን ጠጅ ሲካፈሉ በምሳሌያዊ አባባል ምን ማድረጋቸው ነው?
14 በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡት ‘በጌታ ራት’ በዓል ላይ ከመታሰቢያው የወይን ጽዋ በሚካፈሉበት ጊዜ የአዲሱን ቃል ኪዳን መካከለኛ ደም የሚጠጡት በምሳሌያዊ መንገድ ብቻ ነው። እንዲሁም ከመታሰቢያው ያልቦካ ቂጣ ሲካፈሉ ሥጋውን የሚበሉት በምሳሌያዊ መንገድ ነው። ይህንን በማድረጋቸውም ሁሉንም የሰው ዘር በሚዋጀው በአምላክ ልጅ ቤዛዊ መስዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት በምሳሌያዊ መንገድ ያሳያሉ።
15. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን እስካሁን ድረስ ለምን ያህል ጊዜ ቆይቷል? በእርግጥም የተሻለ ቃል ኪዳን መሆኑ የተረጋገጠውስ እንዴት ነው? (ለ) አዲሱ ቃል ኪዳን “ዘላለማዊ ቃል ኪዳን” ተብሎ ሊጠቀስ የሚቻለው ለምንድን ነው?
15 አሁን 1950 ዓመታት የሆነው አዲሱ ቃል ኪዳን ዓላማውን ወደ መፈጸሙ ተቃርቧል። እስካሁን ድረስ የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ከቆየባቸው ለሚበልጡ ምዕተ ዓመታት ቆይቷል። በተሻሉ ተስፋዎችና ከተሻለ መካከለኛ ጋር በተሻለ መስዋዕት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በእርግጥም የተሻለ ቃል ኪዳን መሆኑ ተረጋግጧል። በሌላ በአዲስ ቃል ኪዳን መተካት ወይም መቀየር ስለማያስፈልገውም ይህ የተሟላ አዲስ ቃል ኪዳን “ዘላለማዊ ቃል ኪዳን” ተብሎ ተጠቅሷል።— ዕብራውያን 13:20
16. ይሖዋ አምላክን ስለምን ነገር ማመስገን ይገባናል?
16 የሙሴን የሕግ ቃል ኪዳን ሕጋዊ በሆነ መንገድ በመከራ እንጨት ላይ በመጠረቅና የዘላለማዊ የአዲስ ኪዳን ደም በማቅረብ ከመንገድ ለማስወገድ የሚችልበትን ከሙሴ የተሻለ መካከለኛ በማስነሣቱ ሁሉን ለሚችለው አምላክ ለይሖዋ ምስጋና ይድረሰው።
[በገጽ 105 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ መካከለኛነት የተደረገው አዲሱ ቃል ኪዳን በሙሴ መካከለኛነት ከተደረገው ከቀድሞው ቃል ኪዳን እጅጉን የበለጠ ነው