እምነትና ጥበብ ለምን እንደሚያስፈልገን
በያዕቆብ መልእክት ላይ ጎልተው የሚታዩ ነጥቦች
የይሖዋ አገልጋዮች መከራ ሲደርስባቸው መጽናት ያስፈልጋቸዋል። መለኮታዊ ድጋፍ የሚያሳጣ ጠባይም (አኗኗርም) ማስወገድ አለባቸው። እንደነዚህ ያሉ ነጥቦች በያዕቆብ መልእክት ጎላ ተደርገው ተገልጸዋል። ለደብዳቤው ምክሮች የእሺታ ምላሽ መስጠትም በሥራ የሚገለጽ እምነትንና ሰማያዊ ጥበብን ይጠይቃል።
የዚህ መልእክት ጸሐፊ ራሱን የሚያስተዋውቀው ያዕቆብ ተብለው ከተጠሩት ሁለት የኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ ነኝ ብሎ ሳይሆን “የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ” በማለት ነው። በተመሳሳይም የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ይሁዳ “የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም” መሆኑን ይናገራል። (ያዕቆብ 1:1፤ ይሁዳ 1፤ ማቴዎስ 10:2, 3) ስለዚህ በስሙ የተጠራውን የያዕቆብ መልእክት የጻፈው የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ያዕቆብ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።—ማርቆስ 6:3
ይህ መልእክት በ70 እዘአ የደረሰውን የኢየሩሳሌምን መጥፋት አይጠቅስም። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስም የሮማው አቃቤ ሕግ ፊስተስ በ62 እዘአ አካባቢ ከሞተ በኋላ ጥቂት ቆይቶ ያዕቆብ ሰማዕታዊ ሞት እንደ ሞተ አመልክቷል። እንግዲያውስ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው መልእክቱ የተጻፈው ከ62 እዘአ ቀደም ብሎ ሳይሆን አይቀርም። የተጻፈውም “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት” ለጸኑት ስለሆነ ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን “አስራ ሁለት ነገዶች” ታስቦ ነው።—ያዕቆብ 1:1፤ 2:1፤ ገላትያ 6:16
ያዕቆብ ምክሩን ለማስታወስ በሚረዱን ምሳሌዎች ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል “የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላል” በማለት አምላክን የሚለምን ሰው መጠራጠር እንደሌለበት ያሳያል። (1:5-8) አንደበታችን መገራት አለበት ምክንያቱም ልክ መቅዘፊያ መርከብን እንደሚመራ አንደበታችንም የሕይወት መንገዳችንን (ሩጫችንን) ይመራል። (3:1, 4) እንዲሁም ገበሬ ምርቱን በትዕግሥት መጠባበቅ እንዳለበት ሁሉ እኛም በትዕግሥት መጽናት አለብን ብሏል።—5:7, 8
እምነት፣ ፈተናና ሥራ
በመጀመሪያው ላይ ያዕቆብ ፈተና ቢኖርብንም ክርስቲያኖች በመሆናችን ደስተኞች ልንሆን እንደምንችል ይገልጽልናል። (1:1-18) ከነዚህ ፈተናዎች አንዳንዶቹ ለምሳሌ እንደ ሕመም የመሳሰሉት በሰዎች ሁሉ ላይ የሚደርሱ ናቸው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የአምላክና የክርስቶስ ባሪያዎች በመሆናቸው ተጨማሪ ሥቃይ ይደርስባቸዋል። ጥበብ እንዲሰጠን በእምነት መጠየቃችንን ካላቆምን ይሖዋ ለመጽናት የሚያስፈልገንን ጥበብ ይሰጠናል። እሱ ፈጽሞ በክፉ አይፈትነንም፤ መልካም የሆነውን እንደሚሰጠንም በእሱ ልንተማመን እንችላለን።
የአምላክን እርዳታ ለመቀበል እንድንችል እምነታችንን በሚገልጽ ሥራ አማካኝነት አምልኮታችንን ልናቀርብለት ያስፈልገናል። (1:19 እስከ 2:26) ይህም ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን “የቃሉ አድራጊዎች” እንድንሆን ይጠይቅብናል። አንደበታችንን መቆጣጠር፣ ወላጆች የሞቱባቸውን ልጆችና መበለቶችን በመከራቸው መጠየቅና ከዓለም ዕድፍ ራሳችንን ሁልጊዜ መጠበቅ አለብን። ለሀብታሞች የምናደላ ድሆችን የምንንቅ ከሆንን ንጉሣዊውን የፍቅርን ሕግ እንጥሳለን። በተጨማሪም የአብርሃምና የረአብ ምሳሌነት እንደሚያሳየው እምነት በሥራ እንደሚገለጽ ማስታወስ ይኖርብናል። በእርግጥም “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።”
ሰማያዊ ጥበብና ጸሎት
አስተማሪ የሆኑ ክርስቲያኖች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እምነትና ጥበብ ያስፈልጋቸዋል። (3:1-18) በአስተማሪነታቸው ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። እንደነሱ እኛም አንደበታችንን መቆጣጠር አለብን። ይህንኑም እንድናደርግ ሰማያዊ ጥበብ ይረዳናል።
ከዚህም በላይ ጥበብ ለዓለማዊ ፍላጎቶች መሸነፍ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና እንደሚያበላሽብን እንድንገነዘብ ይረዳናል። (4:1 እስከ 5:12) የስስት ዓላማዎችን ለማከናወን ተዋግተን ወይም ወንድሞቻችንን ኮንነን ከሆነ ንስሐ መግባት ያስፈልገናል። ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን መንፈሳዊ ምንዝርና በመሆኑ የዓለም ወዳጅነትን ማስወገድ እንዴት አስፈላጊ ነው! ሥጋዊ ዕቅዶችን በማውጣት የአምላክን ፈቃድ ፈጽሞ መዘንጋት አይገባንም። ከትዕግሥት ማጣትና አንዱ በሌላው ላይ ከማጉረምረም እንጠበቅ።
በመንፈሳዊ የታመመ ማንኛውም ሰው የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ አለበት። (5:13-20) ኃጢአት ተፈጽሞ ከሆነም የሽማግሌዎቹ ጸሎትና ጥበብ ያለበት ምክር ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ መንፈሳዊ ጤንነት ለመመለስ ይረዳል። እንዲያውም “ኃጢአተኛውን ከተሳሳተ መንገዱ የሚመልስ የኃጢአተኛውን ነፍስ [ከመንፈሳዊና ከዘላለማዊ] ሞት ያድነዋል።”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቃሉ አድራጊዎች፦ ‘የቃሉ አድራጊዎች እንጂ ሰሚዎች ብቻ መሆን የለብንም።’ (ያዕቆብ 1:22-25) ሰሚ ብቻ የሆነው ሰው “የተፈጥሮ ፊቱን በመስታወት የሚያይን ሰው ይመስላል።” ላንዳፍታ ፊቱን አየት አድርጎ ወዲያው ይሄዳል “እንደምን (ምን ዓይነት ሰው) እንደሆነ ይረሳል።” የቃሉ አድራጊ ግን ክርስቲያኖች የሚፈለግባቸውን ግዴታ ሁሉ ያቀፈውን የአምላክን ፍጹም ወይም የተሟላ ሕግ በጥንቃቄ ይመለከታል። ከሕጉ ጋር በይበልጥ ተስማምቶ ለመኖር ሲል መስተካከሎችን ለማድረግ ሕጉን ዘወትር በጥንቃቄ እየመረመረ “ይጸናበታል።” (መዝሙር 119:16) “ሥራን የሚሠራው” ሰው መልኩን በመስታወት አይቶ ምን እንዳየ ወዲያው ከሚረሳው ሰው የሚለየው እንዴት ነው? አድራጊው የይሖዋን ሕግ በሥራ ስለሚያውለው የሱን ሞገስ ያገኛል!—መዝሙር 19:7-11