በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ክርስቲያናዊ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት
“እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል።”—3 ዮሐንስ 8
1. ፈጣሪ በጣም አስፈላጊ የሆኑ እንዴት ያሉ ስጦታዎችን ለሰው ልጆች ሰጥቷል?
“ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና . . . ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል።” (መክብብ 8:15) የጥንቱ ዕብራዊ ሰብሳቢ በእነዚህ ቃላት ይሖዋ አምላክ ሰብዓዊ ፍጥረቶቹ እንዲደሰቱ መፈለግ ብቻ ሳይሆን እንዲደሰቱ የሚያደርጓቸውን ነገሮች እንደሰጠ ጭምር ገልጾልናል። ራስን የማስደሰት ፍላጎት በሰው ልጆች ታሪክ ዘመን በሙሉ በየትም ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ባሕርይ ሆኖ የቆየ ይመስላል።
2. (ሀ) የሰው ልጅ ይሖዋ ያቀደለትን ዓላማ አለ አግባብ የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ለ) ውጤቱስ ምን ሆነ?
2 ዛሬ የምንኖረው ሰዎች ተድላና ፈንጠዝያ አሳዳጅ በሆኑበት ተድላ አምላኪ በሆነ ኅበረተሰብ ውስጥ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተነበየው “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላ የሚወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) እርግጥ እንዲህ ያለው ባሕርይ ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ በጣም የራቀ ነው። ተድላ ማሳደድ በራሱ አንድ ግብ ሲሆን ወይም ራስን ማስደሰት ብቸኛ ዓላማ ሲሆን እውነተኛ እርካታ ይጠፋና ‘ሁሉ ነገር ከንቱ ነፋስንም እንደመከተል ይሆናል።’ (መክብብ 1:14፤ 2:11) በዚህ ምክንያት ዓለም ብቸኛና ብስጩ በሆኑ ሰዎች የተሞላች ሆናለች። ይህ ደግሞ ለብዙዎቹ ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት ሆኗል። (ምሳሌ 18:1) ሰዎች አንዳቸው ሌላውን የሚጠራጠሩ ይሆኑና በዘር፣ በነገድ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ይከፋፈላሉ።
3. እውነተኛ ደስታና እርካታ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
3 ሰዎች እንደ ይሖዋ ቢሆኑና ሌሎችን በደግነት፣ በልግስና፣ በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ቢይዙ ሁኔታው ምንኛ የተለየ ይሆን ነበር! ይሖዋ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው የየራሳችንን ፍላጎት ለማርካት ከመጣጣር እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል። የእውነተኛ ደስታ ቁልፉ የሚከተለው ነው። “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው።” (ሥራ 20:35) እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት ከፈለግን እንቅፋት የሚሆኑብንን ከፋፋይ ድንበሮች ማሸነፍ ይኖርብናል። አብረውን ይሖዋን ለሚያገለግሉ ሰዎች እጃችንን መዘርጋት አለብን። “እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል” የሚለውን ምክር መከተል አለብን። (3 ዮሐንስ 8) ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን ለሚገባቸው ሰዎች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት በሁለት በኩል ጥቅም ያስገኛል። ሰጪውንም ተቀባዩንም ይጠቅማል። ታዲያ ‘በእንግድነት ልንቀበላቸው’ ከሚገቡ ሰዎች መካከል እነማን ይገኛሉ?
“ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም . . . መጠየቅ”
4. በይሖዋ ሕዝቦች መካከል እንኳ ሳይቀር በቤተሰብ ግንኙነት ረገድ ምን ለውጥ ይታያል?
4 በዛሬው ጊዜ ዘላቂነት ያለውና ደስታ የሰፈነበት ትዳር ማግኘት በጣም አዳጋች እየሆነ መጥቷል። በዓለም ዙሪያ የፍቺ መብዛትና ከጋብቻ ውጭ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እየበዛ መሄዱ ቀድሞ ይታወቅ የነበረው ዓይነት የቤተሰብ ሕይወት እየተለወጠ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ምክንያት በቅርብ ዓመታት ከፈረሱ ቤተሰቦች የመጡ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። የተፋቱ ወይም ከትዳር ጓደኞቻቸው የተለያዩ ወይም አንድ ወላጅ ብቻ በሚያስተዳድረው ቤት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ እንደተነበየው እርሱ ያስተማረው እውነት ለብዙ ቤተሰቦች መከፋፈል ምክንያት ሆኗል።—ማቴዎስ 10:34-37፤ ሉቃስ 12:51-53
5. ኢየሱስ በእምነት ለተከፋፈሉ ቤተሰቦች ማጽናኛ የሚሆን ምን ነገር ተናግሯል?
5 አዳዲስ ሰዎች ለእውነት የጸና አቋም ሲይዙ ልባችን በደስታ ይሞላል። በሚከተለው የኢየሱስ አጽናኝ ተስፋም እናጽናናቸዋለን፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”—ማርቆስ 10:29, 30
6. በመካከላችን ላሉ “ወላጅ የሌላቸው ልጆችና መበለቶች” ‘ወንድሞችና እህቶች፣ እናቶችና ልጆች’ ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?
6 ይሁን እንጂ እነዚህ ‘ወንድሞችና እህቶች፣ እናቶችና ልጆች’ እነማን ናቸው? አንድ ሰው ከመቶ የሚበልጡ ራሳቸውን ወንድሞችና እህቶች ብለው የሚጠሩ ሰዎች በመንግሥት አዳራሽ ተሰብስበው ስለተመለከተ ብቻ እነዚህ ሰዎች ወንድሞቹና እህቶቹ፣ እናቶቹና ልጆቹ እንደሆኑ ሊሰማው አይችልም። ይህን ነጥብ ልብ በል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ አምልኮታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን “ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፣ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነታችንን መጠበቅ” እንደሚያስፈልገን አሳስቦናል። (ያዕቆብ 1:27) የዓለም ዝንባሌ ተጋብቶብን በሀብታችን ወይም በኑሮ ደረጃችን በመኩራት ለእነዚህ ‘ወላጅ የሌላቸውና መበለቶች የሆኑ’ ሰዎች የርህራሄ በራችንን መዝጋት የለብንም ማለት ነው። በራሳችን ተነሳስተን ወዳጅነታችንንና እንግዳ ተቀባይነታችንን ልናሳያቸው ይገባል።
7. (ሀ) “ወላጆች ለሌላቸው ልጆችና ለመበለቶች” የእንግድነት አቀባበል የምናደርግበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያናዊ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት ረገድ እነማንም ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ?
7 ‘ወላጆች ለሌላቸውና ለመበለቶች’ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ሁልጊዜ ቁሳዊ እርዳታ መስጠትን የሚጠይቅ ላይሆን ይችላል። በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ወይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በኢኮኖሚ የተራቆቱ ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የቤተሰብነት መንፈስ ማሳየት፣ የተለያየ ዕድሜ ካላቸው ሰዎች ጋር መወዳጀትና መንፈሳዊ ነገሮችን አብሮ መካፈል ለእነዚህ ሰዎች በጣም ውድ የሆነ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ‘ወላጆች የሌላቸውና መበለቶችም’ ትልቅ ዋጋ ያለው የሚያሳዩት የፍቅርና የአንድነት መንፈስ እንጂ ለመስተንግዶ የሚቀርበው ዝግጅት አለመሆኑን ተገንዝበው ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውን በእንግድነት ቢቀበሉ ምንኛ መልካም ይሆናል!—ከ1 ነገሥት 17:8-16 ጋር አወዳድር።
በመካከላችን የሌላ አገር ሰዎች ይኖራሉን?
8. በብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ምን ዓይነት ለውጥ ይታያል?
8 የምንኖረው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ፍልሰት ባለበት ዘመን ነው። ወርልድ ፕሬስ ሪቪው እንዳለው “በመላው ዓለም 100 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ዜጎች ባልሆኑባቸው አገሮች የሚኖሩ ሲሆን 23 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ በገዛ አገራቸው ከቀድሞ መኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።” በዚህ ምክንያት በብዙ አካባቢዎች በተለይም በሰፋፊ ከተሞች በአንድ ወቅት አንድ ዓይነት ዘር ወይም ብሔር ያላቸው ሰዎች ብቻ ይገኙባቸው የነበሩ የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ሰዎች የሚገኙባቸው ሆነዋል። ምናልባት አንተ የምትገኝበት ጉባኤ እንዲህ ያለ ይሆን ይሆናል። ይሁን እንጂ ዓለም “መጻተኛ” ወይም “የውጭ አገር ሰዎች” ብሎ የሚጠራቸውን በቋንቋቸው፣ በባህላቸውና በአኗኗር ልማዳቸው ከእኛ ሊለዩ የሚችሉ እነዚህን ሰዎች እንዴት መመልከት ይገባናል?
9. ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለሚመጡ “መጻተኞች” እና “የውጭ አገር ሰዎች” ባለን አመለካከት ረገድ ምን ዓይነት ከባድ እንቅፋት ሊያጋጥመን ይችላል?
9 በቀላል አነጋገር እንግዳ ሰዎችን የመጥላት ዝንባሌ አድሮብን ከእንግዳ ወይም አረመኔ ናቸው ከሚባሉ አገሮች ከመጡ ከእነዚህ ሰዎች የበለጠ እውነትን የማወቅ መብት እንዳለን እንዲሰማን ወይም እነዚህ አዲስ መጪዎች በመንግሥት አዳራሹ ወይም በሌሎች ንብረቶች የመጠቀም መብታችንን እንደተጋፉ አድርገን እንድንመለከት መፍቀድ የለብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የመሰለ አመለካከት ለነበራቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ማንም ሰው ደህንነት ሊያገኝ የቻለው ይገባናል በማንለው የአምላክ ቸርነት እንጂ እንዲያው ስለሚገባው አለመሆኑን ማሳሰብ አስፈልጎ ነበር። (ሮሜ 3:9-12, 23, 24) በአሁኑ ጊዜ ይገባናል የማንለው የአምላክ ቸርነት በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ተነፍጎአቸው ለነበሩ በርካታ ሰዎች በመዳረስ ላይ በመሆኑ ደስ ልንሰኝ ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ታዲያ ለእነርሱ ልባዊ የሆነ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
10. በመካከላችን ላሉ “የውጭ አገር ሰዎች” እንግዳ የመቀበል መንፈስ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
10 “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር ልንከተል እንችላለን። (ሮሜ 15:7) ከሌላ አገር የመጡ ወይም ለየት ያለ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ችግር እንደሚያጋጥማቸው በመገንዘብ አቅምና ችሎታ ሲኖረን አሳቢነትና ደግነት ልናሳያቸው ይገባል። ከእኛ ጋር እንዲቀላቀሉ ልናደርግና “እንደ አገር ልጅ” ልንይዛቸው፣ ‘እንደ ራሳችን ልንወዳቸው’ ይገባል። (ዘሌዋውያን 19:34) ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ቢሆንም “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” የሚለውን ምክር ካስታወስን ሊሳካልን ይችላል።—ሮሜ 12:2
ከቅዱሳን ጋር መካፈል
11, 12. (ሀ) በጥንት እስራኤላውያን ዘመን (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለአንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት ልዩ ዝግጅት ተደርጎ ነበር?
11 ልናስብላቸውና መስተንግዶ ልናደርግላቸው ከሚገቡ ሰዎች መካከል ለመንፈሳዊ ደህንነታችን የሚደክሙ የጎለመሱ ክርስቲያኖች አሉ። ይሖዋ በጥንት እስራኤላውያን መካከል ለነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ልዩ ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ዘኁልቅ 18:25-29) በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ክርስቲያኖች በልዩ የሥራ ምድብ ለሚያገለግሏቸው ክርስቲያኖች ልዩ አሳቢነት እንዲያሳዩ ተመክረዋል። በ3 ዮሐንስ 5-8 ላይ ያለው ዘገባ በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መካከል ስለነበረው ፍቅርና መተሳሰር ፍንጭ ይሰጠናል።
12 ጋይዮስ ጉባኤውን እንዲጎበኙ ለተላኩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ያሳየውን ደግነትና እንግዳ ተቀባይነት አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ በጣም አመስግኖ ጽፏል። እነዚህ ወንድሞች፣ ደብዳቤውን እንዲያዳርስ የተሰጠው ድሜጥሮስ ጭምር ለአካባቢው እንግዶችና ከዚያ በፊት ከጋይዮስ ጋር የማይተዋወቁ ነበሩ። ይሁን እንጂ [በአምላክ] ስም የተላኩ በመሆናቸው’ ጥሩ መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል። ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል።”—3 ዮሐንስ 1, 7, 8
13. ዛሬም የእንግድነት አቀባበል ሊደረግላቸው የሚገቡ በመካከላችን ያሉ እነማን ናቸው?
13 ዛሬም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ለመላው የወንድሞች ማኅበር ተግተው የሚሠሩና የሚደክሙ ወንድሞች አሉ። ከእነዚህ መካከል ከሳምንት ሳምንት ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ጉባኤዎችን ለማነጽ ተግባር የሚያውሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ በባዕድ አገሮች ለመስበክ ሲሉ ቤተሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ትተው የወጡ ሚስዮናውያን፣ ምድር አቀፉን የስብከት ሥራ የሚደግፍ ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሰጡ በቤቴል ቤቶች ወይም በቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚያገለግሉ፣ እንዲሁም አብዛኛውን ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፉ አቅኚዎች ይገኛሉ። በመሠረቱ እነዚህ በሙሉ የሚደክሙት የግል ክብር ወይም ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ለክርስቲያን ወንድሞቻቸውና ለይሖዋ ፍቅር ስላላቸው ነው። በሙሉ ነፍሳቸው የሚያገለግሉ በመሆናቸው ልንመስላቸው የሚገባ ከመሆኑም በላይ ጥሩ መስተንግዶ ሊደረግላቸው የሚገቡ ናቸው።
14. (ሀ) ለታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት የተሻልን ክርስቲያኖች የምንሆነው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች” ያለው ለምን ነበር?
14 ሐዋርያው ዮሐንስ እንደገለጸው “እንዲህ ያሉትን በእንግድነት” ስንቀበል ‘ከእውነት ጋር አብረን ሠራተኞች እንሆናለን።’ በሌላ አባባል ይህን በማድረጋችን የተሻልን ክርስቲያኖች እንሆናለን። ምክንያቱም ክርስቲያናዊ ሥራዎች ለእምነት ባልደረቦች መልካም ማድረግን ይጨምራሉ። (ምሳሌ 3:27, 28፤ 1 ዮሐንስ 3:18) ሌላ ዓይነት ጥቅምም ማግኘት ይቻላል። ማርያምና ማርታ ኢየሱስን በቤታቸው በተቀበሉ ጊዜ ማርታ “ብዙ ነገር” ለኢየሱስ በማዘጋጀት ጥሩ አስተናጋጅ ለመሆን ፈልጋ ነበር። ማርያም ያደረገችለት የእንግድነት አቀባበል ግን ከዚህ የተለየ ነበር። “እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች።” ኢየሱስም “መልካም ዕድልን መርጣለች” ሲል አመስግኗታል። (ሉቃስ 10:38-42) የረዥም ዓመታት ተሞክሮ ካላቸው ጋር መነጋገርና መወያየት ከእነርሱ ጋር ሆነን ከምናሳልፋቸው ምሽቶች ከምናገኛቸው ጥቅሞች ዋነኛው ነው።—ሮሜ 1:11, 12
ልዩ በሆኑ አጋጣሚዎች
15. የይሖዋ ሕዝቦች እንዴት ባሉ ልዩ አጋጣሚዎች ሊደሰቱ ይችላሉ?
15 እውነተኛ ክርስቲያኖች የተለመዱ ባሕሎችን የማይከተሉና ዓለማዊ በዓላትን የማያከብሩ ቢሆኑም አንድ ላይ ሆነው የሚደሰቱባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከመገኘቱም በላይ የመጀመሪያውን ተአምር በማድረግ ለተጋባዦቹ ደስታ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። (ዮሐንስ 2:1-11) ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ባሉ ልዩ አጋጣሚዎች በሚዘጋጁ ተገቢ የሆኑ ድግሶች ይደሰታሉ። ይሁን እንጂ ተገቢ የሆኑ ሲባል ምን ማለት ነው?
16. ልዩ በሆኑ አጋጣሚዎች እንኳን ልናሳይ ስለሚገባን ትክክለኛ ጠባይ ምን መመሪያ ተሰጥቷል?
16 ለክርስቲያኖች የሚገባ ጠባይ እንዴት ያለ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ተምረናል። ይህንንም በማናቸውም ጊዜና አጋጣሚ እንከተላለን። (ሮሜ 13:12-14፤ ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 5:3-5) ለሠርግም ሆነ ለማንኛውም ሌላ ምክንያት ማኅበራዊ ስብሰባ ወይም ድግስ በሚዘጋጅበት ጊዜ ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን ለመተላለፍ ወይም በሌላ ጊዜ የማናደርገውን ነገር ለማድረግ ወይም የምንኖርበት አገር ባሕል የሚጠይቀውን በሙሉ ለመፈጸም ነጻነት እንዳገኘን ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ከእነዚህ ባሕላዊ ልማዶች ብዙዎቹ በሐሰት ሃይማኖት ወይም በአጉል እምነቶች ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ የማይችሉ ጠባዮች የሚንጸባረቁባቸው ናቸው።—1 ጴጥሮስ 4:3, 4
17. (ሀ) በቃና የተደረገው የሠርግ ድግስ በሚገባ የተደራጀና ተገቢ ቁጥጥር የተደረገለት መሆኑን የሚያመለክተን ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ለዚህ ድግስ ድጋፍ ሰጥቶ እንደነበረ የሚያመለክተን ምንድን ነው?
17 ዮሐንስ 2:1-11ን ካነበብን ሠርጉ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት እንደሆነና ብዙ እንግዶችም የተጠሩበት እንደሆነ ለመገንዘብ አያስቸግረንም። ይሁን እንጂ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ “ወደ ሠርጉ ታድመው ነበር።” ቢያንስ አንዳንዶቹ ከደጋሹ ጋር የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሊሆኑ ቢችሉም ዝም ብለው ሳይጠሩ አልሄዱም። በተጨማሪም “አገልጋዮች” እና በድግሱ ላይ ስለሚቀርቡትና ስለሚደረጉት ነገሮች አመራር የሚሰጥ “አሳዳሪ” እንደነበሩ እናስተውላለን። ይህ ሁሉ የሚያመለክተን በሚገባ የተደራጀና ተገቢ ቁጥጥር የተደረገበት ድግስ እንደነበረ ነው። ታሪኩ ኢየሱስ ባደረገው ነገር “ክብሩን ገለጠ” በማለት ይደመድማል። ቅጥ የሌለውና መረን የለቀቀው ድግስ ቢሆን ያንን አጋጣሚ ክብሩን ለመግለጥ ይመርጥ ነበርን? በፍጹም አያደርገውም።
18. በማንኛውም ማኅበራዊ ስብሰባ ወቅት በጥሞና ሊታሰብባቸው የሚገቡ ምን ነገሮች አሉ?
18 ታዲያ አንድ ዓይነት ልዩ አጋጣሚ አዘጋጅተን እንግዳ ተቀባዮች በምንሆንበት ጊዜ ምን ማድረግ ይገባናል? ሌሎችን የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት ምክንያት በእውነት ውስጥ አብረን ሠራተኞች ለመሆን እንደሆነ ማስታወስ ይገባናል። ስለዚህ አንድን ግብዣ “የምሥክሮች” ግብዣ ነው የሚል ስያሜ መስጠት ብቻውን በቂ አይሆንም። ለማንነታችንና ለምናምነው ነገር ምሥክር ይሆናልን? የሚል ጥያቄ መጠየቅ ይገባናል። እንደነዚህ ያሉትን አጋጣሚዎች የዓለምን መንገዶች በመኮረጅና ‘በሥጋ ምኞት፣ በዐይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ’ በማለት ረገድ ከዓለም ጋር ምን ያህል ልንወዳደር እንደምንችል የምናሳይበት አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን መመልከት አይገባንም። (1 ዮሐንስ 2:15, 16 አዓት) ከዚህ ይልቅ እነዚህ ወቅቶች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን በጥሩ ሁኔታ የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም የምናደርገው ነገር ሁሉ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ የሚያመጣ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባናል።—ማቴዎስ 5:16፤ 1 ቆሮንቶስ 10:31-33
‘ያለማንጎራጎር እንግዶችን ተቀበሉ’
19. ‘ሳናጉረመርም እርስ በርሳችን እንግድነት ልንቀባበል’ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
19 የዓለም ሁኔታ በጣም እየከፋ በሄደና ሕዝቦችም ይበልጥ እየተከፋፈሉ በሄዱ መጠን በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን የፍቅር መተሳሰር ለማጠንከር የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይገባናል። (ቆላስይስ 3:14) ለዚህም “እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” የሚለውን የጴጥሮስ ምክር ሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። ከዚያም ተግባራዊ ምክር ሲሰጥ “ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 4:7-9) በራሳችን ተነሳስተን ወንድሞቻችንን እንግድነት ለመቀበል፣ ደጎች ለመሆንና ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኞች ነንን? ወይስ እንዲህ እንድናደርግ የሚጠይቅብን ሁኔታ ሲያጋጥመን እናጉረመርማለን? እንዲህ ብናደርግ ልናገኝ የምንችለውን ደስታ እናጣለን። መልካም ከማድረግ የሚገኘውንም አስደሳች ዋጋ ሳናገኝ እንቀራለን።—ምሳሌ 3:27፤ ሥራ 20:35
20. በዚህ እርስ በርሱ በተከፋፈለ ዓለም እንግዳ ተቀባዮች ብንሆን ምን ዓይነት በረከት እናገኛለን?
20 ከክርስቲያን ባልደረቦቻችን ጋር ተቀራርበን መሥራት፣ ደግ መሆንና እርስ በርስ እንግድነት መቀባበል ገደብ የሌለው በረከት ያስገኝልናል። (ማቴዎስ 10:40-42) እንዲህ ለሚያደርጉ ሁሉ ይሖዋ “ድንኳኑን ይዘረጋላቸዋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም።” በይሖዋ ድንኳን ውስጥ መኖር ማለት የይሖዋን ጥበቃና መስተንግዶ ማግኘት ማለት ነው። (ራእይ 7:15, 16 አዓት፤ ኢሳይያስ 25:6) አዎን፣ በይሖዋ መስተንግዶ ለዘላለም የመደሰት ተስፋ በፊታችን ተዘርግቷል።—መዝሙር 27:4፤ 61:3, 4
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት ከፈለግን ምን ነገር ችላ ማለት አይገባንም?
◻ “ወላጅ የሌላቸውና መበለቶች” የተባሉት እነማን ናቸው? እንዴትስ ‘ልንጠይቃቸው’ እንችላለን?
◻ በመካከላችን ያሉትን “መጻተኞች” እና “የውጭ አገር ሰዎች” እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
◻ በዛሬው ጊዜ ልዩ አያያዝ ሊደረግላቸው የሚገቡ እነማን አሉ?
◻ ልዩ የሆኑ አጋጣሚዎች እውነተኛ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው መሆን የሚገባቸው እንዴት ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንዳንድ ልዩ ወቅቶች ለውጭ አገር ሰዎች፣ ወላጅ ለሌላቸው ልጆች፣በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለተሰማሩና ለሌሎች ሰዎች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ልናሳይ እንችላለን