ለክርስቲያኖች ተስፋ መልሕቅ፣ ፍቅር ደግሞ የሚገፋፋ ኃይል ሊሆንላቸው ይገባል
“እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።”—1 ቆሮንቶስ 13:13
1. ጳውሎስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል?
ሐዋርያው ጳውሎስ እምነታችን እንደ መርከብ የመሰበር አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል አስጠንቅቋል። “እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፣ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፣ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፣ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና” በማለት ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩት የባሕር ላይ መጓጓዣዎች ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ። ጥንካሬያቸው የተመካው በተሠሩበት እንጨት ጥራትና በአሠራራቸው ላይ ነበር።
2. የእምነታችን መርከብ በጥሩ ሁኔታ መገንባት ያለበት ለምንድን ነው? ይህስ ምን ይጠይቅብናል?
2 በመርከብ ሊመሰል የሚችለው እምነታችን ተነዋዋጭ በሆነው የሰው ዘር ባሕር ላይ መንሳፈፉን መቀጠል አለበት። (ኢሳይያስ 57:20፤ ራእይ 17:15) ስለዚህ በደንብ መገንባት አለበት፤ ይህ ደግሞ በእኛ ላይ የተመካ ነው። በተለይ የአይሁዳውያኑና የሮማውያኑ ዓለም “ባሕር” ለቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች አስቸጋሪ እየሆነ በመጣባቸው ጊዜያት ይሁዳ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር:- “ወዳጆች ሆይ፣ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ [“እምነታችሁ፣” NW] ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” (ይሁዳ 20, 21) ይሁዳ የተናገረው ‘ለቅዱሳን ስለ ተሰጠ እምነት’ መጋደልን በተመለከተ ስለነበረ ‘የተቀደሰ እምነት’ የሚለው መግለጫ የመዳንን ምሥራች ጨምሮ ጠቅላላውን የክርስትና ትምህርት ዘርፍ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። (ይሁዳ 3) የዚህ እምነት መሠረቱ ክርስቶስ ነው። እውነተኛውን የክርስትና እምነት አጥብቀን ለመያዝ ከፈለግን ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል።
“በኑፋቄ ፍርሃት” ስም የሚደርስብንን የተቃውሞ ማዕበል መቋቋም
3. አንዳንዶች ‘በኑፋቄ ፍርሃት’ ስም ምን አድርገዋል?
3 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአናሳ የሃይማኖት ቡድኖች አማካኝነት አሰቃቂ በሆነ መንገድ በጅምላ የገዛ ሕይወትን የማጥፋት፣ የነፍስ ግድያና የሽብር ድርጊቶች ተፈጽመዋል። ቅን አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ግለሰቦች ንጹሐን ሰዎችን፣ በተለይም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ አደገኛ ኑፋቄዎች ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ከዚህ ሁሉ አሰቃቂ ወንጀል በስተጀርባ ያለው ‘የዚህ የነገሮች ሥርዓት አምላክ’ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዶች የኑፋቄ ፍርሃት ብለው የሚጠሩት ነገር እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው እሱ ራሱ ሲሆን የይሖዋን ሕዝቦች ለማጥቃትም መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 12:12) አንዳንዶች ይህን የኑፋቄ ፍራቻ በሥራችን ላይ ተቃውሞ ለማስነሳት ተጠቅመውበታል። አንዳንድ አገሮች ሰዎችን ከ“አደገኛ ኑፋቄዎች” ለመከላከል የሚል ዘመቻ ቢያካሂዱም የይሖዋ ምሥክሮችንም አደገኛ ኑፋቄ ብለው በመፈረጅ በተዘዋዋሪ መንገድ ወንጅለውናል። ይህ ጉዳይ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ከቤት ወደ ቤት መስበክን አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችም ጥናታቸውን እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል። ይህ ደግሞ በአንዳንድ ወንድሞቻችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
4. ተቃውሞ ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባው ለምንድን ነው?
4 ይሁን እንጂ የሚደርስብን ተቃውሞ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። ይልቁንም የያዝነው እውነተኛውን ክርስትና ስለመሆኑ ያለንን እምነት ሊያጠነክርልን ይገባል። (ማቴዎስ 5:11, 12) የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ሕዝብን የሚያነሣሡ ኑፋቄ ተብለው ተከስሰው የነበረ ሲሆን በየስፍራውም ሁሉ ሰዎች ‘ይቃወሟቸው’ ነበር። (ሥራ 24:5፤ 28:22) ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት አጋሮቹን እንደሚከተለው ብሎ በመጻፍ አጽናንቷቸዋል:- “ወዳጆች ሆይ፣ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፣ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።” (1 ጴጥሮስ 4:12, 13) በተመሳሳይም አንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል አባል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት። ትዕግሥትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።” (ያዕቆብ 1:2-4) ኃይለኛ ነፋሳት የአንድን መርከብ ጥንካሬ እንደሚፈትኑ ሁሉ የተቃውሞ ማዕበሎችም በእምነት መርከባችን ላይ ያለውን ማንኛውም ዓይነት ድክመት ያሳያሉ።
መከራ ጽናትን ያፈራል
5. እምነታችን በመከራ ወቅት ጽኑ እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
5 ክርስቲያኖች ስለ ጽናታቸውና ስለ እምነታቸው ጥንካሬ እርግጠኛ መሆን የሚችሉት የመከራ ማዕበሎችን ተቋቁመው ካሳለፉ ብቻ ነው። ማዕበል በበዛባቸው ባሕሮች ላይ ጽናታችን ‘ሥራውን ሊፈጽም’ የሚችለው ጠንካራ እምነትን ጨምሮ ‘ምንም የሚጐድለን ሳይኖር በማንኛውም መስክ ፍጹማንና ምሉዓን ከሆንን’ ብቻ ነው። ጳውሎስ “በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት” ሲል ጽፏል።—2 ቆሮንቶስ 6:4
6. ‘በመከራ ላይ ብንሆንም መደሰት’ ያለብን ለምንድን ነው? ይህስ ተስፋችንን የሚያጠነክረው እንዴት ነው?
6 አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥሙን ኃይለኛ የመከራ ነፋሳት የእምነት መርከባችን ጠንካራና ጽኑ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚያስችሉን አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ጳውሎስ በሮም ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፣ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፣ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።” (ሮሜ 5:3-5) በመከራ ወቅት መጽናት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝልናል። ይህ ደግሞ በተራው ተስፋችንን ያጠነክርልናል።
የአንዳንዶች የእምነት መርከብ የሚሰበርበት ምክንያት
7. (ሀ) የጳውሎስ ቃላት እንደሚያሳዩት አንዳንዶች የእምነት መርከባቸው የተሰበረባቸው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ከእውነት የራቁት እንዴት ነው?
7 ጳውሎስ ስለ ‘መርከብ መሰበር’ ሲያስጠነቅቅ ጥሩ ሕሊናቸውን “ጥለው” እምነታቸውን ያጡ አንዳንድ ሰዎችን በአእምሮው ይዞ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) ከእነዚህም መካከል ከእውነት አፈንግጠው በመውጣትና ተሳዳቢ በመሆን ወደ ክህደት የገቡት ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ይገኙበት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:20 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:17, 18) በዛሬው ጊዜ ከእውነት አፈንግጠው የሚወጡ ከሃዲዎች ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ በቃላት በመምታት በመንፈሳዊ ይመግባቸው የነበረውን እጅ መልሰው ነክሰዋል። አንዳንዶች “ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል” ከማለት ያልተለየ ነገር በማድረግ ‘ክፉውን ባሪያ’ መስለዋል። (ማቴዎስ 24:44-49፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:14, 15) የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ቅርብ መሆኑን በመካድ የይሖዋ ሕዝቦች የጥድፊያ ስሜታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግ ላይ ያለውን በመንፈሳዊ ንቁ የሆነውን የባሪያ ክፍል ይነቅፋሉ። (ኢሳይያስ 1:3) እንዲህ ያሉት ከሃዲዎች ‘የአንዳንዶችን እምነት በመገልበጥ’ ለመንፈሳዊ ውድቀት እንዲዳረጉ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:18
8. አንዳንዶች የእምነታቸውን መርከብ እንዲሰብሩ ወይም እንዲሸነቁሩ ምክንያት የሆናቸው ምንድን ነው?
8 ራሳቸውን የወሰኑ ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ሕሊናቸውን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግና መረን በለቀቀው በዚህ ዓለም ተድላ ወዳድነትና የጾታ ብልግና ውስጥ በመዘፈቅ የእምነታቸውን መርከብ ሰብረዋል። (2 ጴጥሮስ 2:20-22) ሌሎች ደግሞ በእነርሱ አመለካከት አዲስ የነገሮች ሥርዓት የመምጣቱ ጉዳይ ከአድማስ ባሻገር እንኳ የማይታይ በመሆኑ የእምነት መርከባቸው እንዲሰጥም አድርገዋል። አንዳንድ ትንቢቶች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ለማስላት ስላልቻሉ እንዲሁም ‘የይሖዋ ቀን’ ይዘገያል ብለው ስላሰቡ እውነተኛውን አምልኮ ጥለው ወጥተዋል። (2 ጴጥሮስ 3:10-13፤ 1 ጴጥሮስ 1:9) ብዙም ሳይቆዩ ወደዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት የጨቀየ ውኃ ይመለሳሉ። (ኢሳይያስ 17:12, 13፤ 57:20) ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መተባበር ያቆሙ አንዳንድ ሰዎች አሁንም ቢሆን እውነተኛ ሃይማኖት መሆኑን ያምናሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ቃል የገባውን አዲስ ሥርዓት ለመጠባበቅ የሚያስፈልገውን ትእግሥትና ጽናት እንዳጡ የተረጋገጠ ነው። ገነት እነሱ እንዳሰቡት በቶሎ አልመጣም።
9. ራሳቸውን የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን በማድረግ ላይ ናቸው? እነዚህ እውነታዎች ምንን እንድንመረምር ሊያደርጉን ይገባል?
9 በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ራሳቸውን የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች የእምነት መርከባቸውን ሸራዎች የጠቀለሉ ይመስላል። መርከቡ በመንሳፈፍ ላይ ነው፤ ሆኖም በሙሉ እምነት ወደ ፊት ከመግፋት ይልቅ በተዝናና ሁኔታ እያዘገሙ መጓዝን መርጠዋል። አንዳንዶች “ገነት በቅርቡ ይመጣል” በሚለው ተስፋ ተገፋፍተው በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይም አዘውትረው በመገኘት ተስፋውን ለመጨበጥ ይጋደሉ ነበር። አሁን ግን ተስፋ ያደረጓቸው ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜ ከጠበቁት በላይ የሚዘገይ ስለመሰላቸው ተጋድሏቸውን ቀንሰዋል። ይህንንም ሁኔታ የስብከት እንቅስቃሴያቸው ከመቀነሱ፣ በስብሰባዎች ላይ አዘውታሪዎች ካለመሆናቸውና አንዳንድ የትላልቅ ወይም የአውራጃ ስብሰባ ክፍሎች እንዲያመልጧቸው ከመፍቀዳቸው ለመመልከት ይቻላል። ሌሎች ደግሞ መዝናኛንና ቁሳዊ ምቾቶችን በማሳደድ ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ። እነዚህ እውነታዎች ለይሖዋ ከገባነው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ በሕይወታችን ውስጥ የሚገፋፋን ኃይል ምን መሆን እንዳለበት እንድንመረምር ያነሳሱናል። ለእሱ የምናቀርብለት አገልግሎት “ገነት በቅርቡ ይመጣል” በሚለው ተስፋ ላይ የተመካ መሆን አለበትን?
ከመልሕቅ ጋር የተመሳሰለው ተስፋ
10, 11. ጳውሎስ ተስፋችንን ከምን ነገር ጋር አመሳስሎታል? ይህስ ንጽጽር ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?
10 ይሖዋ በአብርሃም በኩል ሰዎችን ለመባረክ ቃል መግባቱን ጳውሎስ አመልክቷል። ከዚያም ሐዋርያው እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር [በቃሉና በመሐላው]፣ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፣ በመሐላ በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ . . . ነው።” (ዕብራውያን 6:17-19፤ ዘፍጥረት 22:16-18) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ገነት በሆነች ምድር ላይ የመኖር አስደናቂ ተስፋ አላቸው። (ሉቃስ 23:43) እንዲህ የመሰለው ተስፋ ባይኖር ኖሮ እምነት ያለው ሰው ባልተገኘ ነበር።
11 መልሕቅ መርከቡ በአንድ ቦታ ረግቶ እንዲቆይ ወይም እንዳይዋልል ለመከላከል የሚያገለግል በጣም አስፈላጊ የሆነ ጠንካራ የአደጋ መከላከያ ነው። ማንኛውም መርከበኛ መልሕቅ ሳይዝ ከወደብ አይንቀሳቀስም። ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጊዜያት የመርከብ መሰበር አጋጥሞት ስለነበር የመርከበኞች ሕይወት በአብዛኛው የተመካው በመርከባቸው መልሕቅ ላይ መሆኑን ከተሞክሮ ያውቅ ነበር። (ሥራ 27:29, 39, 40፤ 2 ቆሮንቶስ 11:25) በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንድ የመርከብ ካፕቴን መርከቡን እንደ ልቡ እንዲያሽከረክር የሚያስችለው ሞተር አልነበረውም። በመቅዘፊያ ይጠቀሙ ከነበሩ የጦር መርከቦች በስተቀር ሌሎች መርከቦች የሚንቀሳቀሱት በነፋስ ኃይል ነበር። አንድ መርከብ ከዓለት ጋር የመላተም አደጋ የሚያሰጋው ከሆነ የመርከቡ ካፕቴን ያለው ብቸኛ አማራጭ መልሕቁ ከባህሩ በታች ባለው መሬት ላይ ተቸክሎ እንደሚቆይ በመተማመን መልሕቁን ጥሎ ማዕበሉን ማሳለፍ ነው። ስለዚህ ጳውሎስ የአንድን ክርስቲያን ተስፋ ‘ከተረጋገጠና ጽኑ ከሆነ የነፍስ መልሕቅ’ ጋር አመሳስሎታል። (ዕብራውያን 6:19) የተቃውሞ ማዕበል ሲያናውጠን ወይም ሌሎች ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የእምነት መርከባችን አደገኛ በሆኑት የጥርጣሬ ደለሎች ወይም አስከፊ መዘዝ ባላቸው የክህደት ዓለቶች እንዳይመታ በመከላከል ሕያው ነፍሳት ሆነን እንድንጸና የሚረዳን እንደ መልሕቅ የሆነው ነገር አስደናቂው ተስፋችን ነው።—ዕብራውያን 2:1፤ ይሁዳ 8-13
12. ይሖዋን ከመካድ ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን “ወንድሞች ሆይ፣ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ” ብሏቸዋል። (ዕብራውያን 3:12) በግሪክኛው ጥቅስ ላይ ‘መክዳት’ የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “መራቅ” ማለትም ከሃዲ መሆን ማለት ነው። ሆኖም እንዲህ ካለው የመርከብ መሠበር አደጋ ልንጠበቅ እንችላለን። እምነትና ተስፋ ሌላው ቀርቶ እጅግ አስከፊ የሆኑ የፈተና ማዕበሎች በሚያጋጥሙን ወቅት እንኳ ይሖዋን ሙጥኝ እንድንል ያስችሉናል። (ዘዳግም 4:4፤ 30:19, 20) እምነታችን በከሃዲዎች ትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንደሚገፋ መርከብ አይሆንም። (ኤፌሶን 4:13, 14) ተስፋችንን መልሕቅ በማድረግ ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን የሚያጋጥሙንን የሕይወት ማዕበሎች ለመቋቋም እንችላለን።
በፍቅርና በመንፈስ ቅዱስ መገፋፋት
13, 14. (ሀ) የተስፋችን መልሕቅ ብቻውን በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብ የሚገፋፋን ኃይል ምን መሆን አለበት? ለምንስ?
13 አንድ ክርስቲያን ይሖዋን ለማገልገል የሚገፋፋው ነገር ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ብቻ ከሆነ ወደ አዲሱ ሥርዓት የሚያደርገውን ጉዞ አይገፋበትም። የተስፋ መልሕቁን ጸንቶ እንዲኖር የሚያስችለው መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም በተስፋውና በእምነቱ ላይ የሚገፋፋ ኃይል የሆነውን ፍቅርን መጨመር አለበት። ጳውሎስ “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” ብሎ በጻፈ ጊዜ የዚህን አስፈላጊነት አስምሮበታል።—1 ቆሮንቶስ 13:13
14 ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚገፋፋን ኃይል ለይሖዋ ያለን ልባዊ ፍቅርና እሱ ላሳየን ወደር የለሽ ፍቅር ምላሽ ለመስጠት መነሳሳታችን መሆን አለበት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።” (1 ዮሐንስ 4:8, 9, 19) ለይሖዋ አመስጋኝነት ካለን በዋነኛነት የሚያሳስበን ጉዳይ የግል መዳናችን ሳይሆን የስሙ መቀደስና የትክክለኛ ሉዓላዊነቱ መረጋገጥ ሊሆን ይገባል።
15. ለይሖዋ ያለን ፍቅር በሉዓላዊነቱ ላይ ከተነሳው ጥያቄ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
15 ይሖዋ፣ ገነት ለመግባት ስንል ብቻ ሳይሆን ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን እንድናገለግለው ይፈልጋል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋልa (እንግሊዝኛ) የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክለፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ሉዓላዊነቱም ሆነ ፍጡራኑ ለሉዓላዊነቱ የሚሰጡት ድጋፍ በዋነኛነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ደስ ይለዋል። እሱ የሚፈልገው ባሉት ጥሩ ባህርያት እንዲሁም ጻድቅ በመሆኑ ምክንያት ከሌላው ነገር አስበልጠው የእሱን ሉዓላዊነት የሚመርጡ ሰዎችን ብቻ ነው። (1 ቆሮ 2:9) ራሳቸውን በራሳቸው ከመምራት ይልቅ በእሱ ሉዓላዊነት ሥር ሆነው ለማገልገል ይመርጣሉ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ስለ ማንነቱ፣ ፍቅሩ፣ ፍትሑና ጥበቡ ባላቸው እውቀትና በእነዚህ ነገሮች ረገድ ከእነሱ እጅግ የላቀ መሆኑን በመገንዘባቸው ነው። (መዝ 84:10, 11)”—ጥራዝ 2 ገጽ 275
16. ለኢየሱስ ያለን ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ የሚገፋፋ ኃይል የሆነው እንዴት ነው?
16 ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን ኢየሱስ ላሳየን ፍቅር ምላሽ እኛም ፍቅራችንን እንገልጽለታለን። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ይህን ስለ ቈረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) መንፈሳዊ ሕይወታችን፣ እምነታችንና ተስፋችን የተገነባበት መሠረት ክርስቶስ ነው። ለክርስቶስ ኢየሱስ ያለን ፍቅር በተለይ በከባድ የፈተና ማዕበሎች ወቅት ተስፋችንን ያጠነክርልናል፤ እምነታችንም ጽኑ እንዲሆን ያደርጋል።—1 ቆሮንቶስ 3:11፤ ቆላስይስ 1:23፤ 2:6, 7
17. ይሖዋ የትኛውን ብርቱ ኃይል ይሰጠናል? የዚህ ኃይል አስፈላጊነትስ በሥራ 1:8ና በኤፌሶን 3:16 ላይ የተገለጸው እንዴት ነው?
17 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሕይወታችን ውስጥ የሚገፋፋን ዋነኛው ኃይል ለአምላክና ለልጁ ያለን ፍቅር ቢሆንም ይሖዋ ጉልበትና ጥንካሬ በመስጠት በአገልግሎቱ ወደፊት እንድንገፋ የሚያደርግ ተጨማሪ ነገር ይሰጠናል። ይህም አንቀሳቃሽ ኃይሉ ወይም ቅዱስ መንፈሱ ነው። “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በመሠረቱ የሚያመለክቱት እንደ ነፋስ ያለውን ኃይለኛ የአየር እንቅስቃሴ ነው። ጳውሎስ የተጓዘባቸውን የመሳሰሉ መርከቦች ወዳሰቡበት ቦታ መድረሳቸው የተመካው በማይታየው የነፋስ ኃይል ላይ ነበር። በተመሳሳይም የእምነት መርከባችን በይሖዋ አገልግሎት ወደ ፊት ለመግፋት እንዲረዳን ከተፈለገ ፍቅርና የማይታየው የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ያስፈልገናል።—ሥራ 1:8፤ ኤፌሶን 3:16
ወደ መድረሻችን መገስገስ!
18. ወደፊት በእምነታችን ላይ የሚመጡትን ፈተናዎች በጽናት ለማሳለፍ የሚያስችለን ምንድን ነው?
18 ወደ አዲሱ የነገሮች ሥርዓት ከመግባታችን በፊት እምነታችንና ፍቅራችን ከባድ የሆነ ፈተና ሊያጋጥመው ይችላል። ሆኖም ይሖዋ “እርግጥና ጽኑ የሆነ” መልሕቅ ማለትም አስደናቂ ተስፋ ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 6:19፤ ሮሜ 15:4, 13) ተቃውሞ ወይም ሌሎች ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ መልሕቅ የሆነውን ተስፋችን ቆንጥጠን ከያዝን መጽናት እንችላለን። አንደኛው ማዕበል አለፈ ብለን ሳንዘናጋ ተስፋችንን ለመገንባትና እምነታችንን ለማጠናከር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
19. የእምነታችን መርከብ ጉዞውን እንዲቀጥል በማድረግ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመድረስ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ስለ “ነፍስ መልሕቅ” ከመጥቀሱ በፊት እንዲህ ብሎ ነበር:- “በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፣ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ [“እንድትፈጥኑ፣” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] እንመኛለን።” (ዕብራውያን 6:11, 12) ለይሖዋና ለልጁ ባለን ፍቅር ተገፋፍተንና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተን አምላክ ተስፋ ወደሰጠበት አዲስ ዓለም እስክንገባ ድረስ የእምነታችንን መርከብ ጉዞውን እንዲቀጥል ለማድረግ እንጣጣር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
ለክለሳ ያህል
◻ እምነታችንን በተመለከተ ጳውሎስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
◻ አንዳንዶች የእምነት መርከባቸው የተሰበረባቸው እንዴት ነው? ሌሎችስ በማዝገም ላይ ያሉት እንዴት ነው?
◻ በእምነታችን ላይ ልንጨምረው የሚገባን አምላካዊ ባሕርይ የትኛው ነው?
◻ አምላክ ተስፋ ወደሰጠበት አዲስ ዓለም እንድንደርስ ሊረዳን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእምነት መርከባችን የሕይወትን ማዕበሎች ለመቋቋም እንዲችል በደንብ መገንባት አለበት
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእምነት መርከባችን የመሰበር አደጋ ሊገጥመው ይችላል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተስፋ የክርስቲያን ሕይወታችን መልሕቅ ነው