የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w00 2/15 ገጽ 4-7
  • ከአደጋ ቀጣናው ራቁ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከአደጋ ቀጣናው ራቁ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አስፈሪው የይሖዋ ቀን
  • አሁኑኑ ተሸሸግ
  • አንዴ ሸሽተህ ከወጣህ አትመለስ
  • ማስጠንቀቂያውን ልብ በሉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • “ከጭንቀት ቀን” ማን ያመልጥ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅታችኋል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • የይሖዋን ቀን በሐሳብህ ቅርብ አድርገህ ተመልከተው
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
w00 2/15 ገጽ 4-7

ከአደጋ ቀጣናው ራቁ!

እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ማጤንና ማስጠንቀቂያ መስጠት የእሳተ ገሞራ አጥኚዎች ተግባር ነው። (የፉገን ተራራ አንዴ ከፈነዳ በኋላ ፖሊስ ሰዎች ወደ አደጋ ቀጣናው እንዳይቀርቡ መከላከል ነበረበት።) በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ምልክት የሆኑትን ነገሮች በማስተዋል ሰዎችን ከፊታቸው ስለተደቀነባቸው አደጋ ያስጠነቅቃሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​3

ስለመጪው ዓለም አቀፍ ጥፋት በሚናገረው በዚያው የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ላይ ጥፋቱ ከመምጣቱ በፊት ስለሚከናወኑ ሁኔታዎች የሚከተለውን ማንበብ እንችላለን:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ . . . ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። . . . ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”​—⁠ማቴዎስ 24:​7-14

በአሁኑ ወቅት ያለውን የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ለማስተዋል የዜና ተንታኞች መሆን አያስፈልገንም። በተለይ ከ1914 ወዲህ በገሃድ እያየነው ነው። ይህ መቶ ዘመን ሁለት ዓለም አቀፍ ጦርነቶችን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የእርስ በርስ ጦርነቶችን፣ አካባቢያዊ ግጭቶችን እንዲሁም የዘርና የሃይማኖት ግጭቶችን አስተናግዷል። የተፈጥሮ አደጋዎች ከሚያስከትሉት ዕጦት በተጨማሪ በእነዚህ ጦርነቶች ጦስ የሰው ዘር በምግብ እጥረት ክፉኛ ተሠቃይቷል። የመሬት መንቀጥቀጥ ባስከተለው አደጋ ሳቢያ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። አጠያያቂ ድርጊት የሚፈጽሙና አክራሪ የሆኑ መሪዎች ያሏቸው ኑፋቄዎች ተነስተዋል። ‘የዓመፃ መብዛት’ ሰዎች ፍቅር እንዲያጡ ከማድረጉም በላይ መልካም ጉርብትና ጨርሶ እየጠፋ መጥቷል።

የምልክቱ ሌላ ገጽታ የሆነው ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። እስቲ የዚህን መጽሔት ሽፋን መለስ በልና ተመልከተው። “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉት ቃላት የመጽሔቱ ርዕስ ክፍል መሆናቸውን ታስተውላለህ። በ132 ቋንቋዎች የሚታተመውና ከ22 ሚልዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች የሚሠራጨው መጠበቂያ ግንብ ‘ይህን የመንግሥት ወንጌል’ በምድር ዙሪያ የሚያውጁ ሰዎች የሚጠቀሙበት ዋነኛ መሣሪያ ነው። ይህ ምሥራች የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት አጥፍቶ ምድርን ገነት የሚያደርግ ሰማያዊ መንግሥት ስለማቋቋሙ የሚገልጸውን መልእክት የሚጨምር ነው። አምላክ በቅርቡ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የሚያሳየው ምልክት በገሃድ እየታየ ነው፤ ይህ ደግሞ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን የሚጠቁም ነው።​—⁠ከ⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:​3, 4፤ ራእይ 6:​1-8 ጋር አወዳድር።

አስፈሪው የይሖዋ ቀን

ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ ሲደርስ ምን ነገር ይከሰታል? በዚያን ጊዜ ምን እንደሚከሰት ራሱ የሰጠውን ሕያው መግለጫ አዳምጥ። “በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፣ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።”​—⁠ኢዩኤል 2:​30, 31

በአንድ አካባቢ ከሚደርስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ወይም የመሬት መንቀጥቀጥ ይበልጥ እጅግ አስፈሪ የሆነው ይህ ቀን የሚመጣበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። ነቢዩ ሶፎንያስ እንደሚከተለው ብሏል:- “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ . . . እጅግም ፈጥኖአል፤ . . . እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።” ምንም እንኳ ‘በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው ባይችልም’ ከዚህ አስፈሪ ቀን መዳን የሚቻልበት መንገድ ግን አለ።​—⁠ሶፎንያስ 1:​14-18

ሶፎንያስ መዳን የሚቻልበትን መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔርም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፣ ተከማቹም። እናንተ . . . የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” (ሶፎንያስ 2:​2, 3) ‘ይሖዋን በመፈለግ፣ ጽድቅን በመፈለግና ትሕትናን በመፈለግ’ ከጥፋቱ ልንሰወር እንችላለን። በዛሬው ጊዜ ይሖዋን እየፈለጉ ያሉት እነማን ናቸው?

ከስብከት ሥራቸው የተነሳ “ይሖዋ” የሚለውን ቃል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደምታያይዘው የታወቀ ነው። ምናልባትም ይህን መጽሔት ያገኘኸው ከእነርሱ ሊሆን ይችላል። በንጹሕ አኗኗራቸው የሚታወቁ ጥሩ ዜጎች ናቸው። ትሕትናን የሚጨምረውን “አዲሱን ሰው” ለመልበስ በመጣር ላይ ናቸው። (ቆላስይስ 3:​8-10) ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው በምድር ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በሚወከለው በሚታየው የይሖዋ ድርጅት አማካኝነት ባገኙት ትምህርት መሆኑን ያምናሉ። አዎን፣ ‘ከዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ጋር በመተባበር’ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ከጥፋት ልትሸሸግ ትችላለህ።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​9

አሁኑኑ ተሸሸግ

ይሖዋን በመፈለግ ከሚመጣው ጥፋት ለመሸሸግ የእሱ ወዳጆች መሆን አለብን። ይህ ምንን ይጨምራል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ያዕቆብ 4:​4) የአምላክ ወዳጅ ለመሆን ከፈለግን በአምላክ ላይ የማመፅን ዝንባሌ ከሚያራምደው ክፉ ዓለም ጋር ያለንን ማንኛውንም ወዳጅነት ማቋረጥ አለብን።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት አጥብቆ ይመክረናል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:​15-17) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች መረን የለቀቀ የፆታ ፍላጎትን፣ ለገንዘብ መስገብገብንና በሥልጣን አለአግባብ መጠቀምን በመሳሰሉ ሥጋዊ ፍላጎቶች የተጠመዱ ናቸው። ሆኖም ከይሖዋ ጎን ለመሰለፍ አንድ ሰው እንደዚህ የመሰሉ ፍላጎቶችን ማሸነፍ አለበት።​—⁠ቆላስይስ 3:​5-8

አልፎ አልፎ ይህን መጽሔት የምታነብና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚሰጠውን ማብራሪያ የምትቀበል ልትሆን ትችላለህ። ይሁንና ተጨማሪ እርምጃ ወስደህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመተባበር ታመነታ ይሆናል። ሆኖም አደጋ በሚያስከትል ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ ማስጠንቀቂያውን መስማቱ ብቻ በቂ ነውን? በፉገን ተራራ ላይ ከደረሰው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ለመመልከት እንደምንችለው የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተን እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል። ቢያንስ 15 የሚሆኑ የዜና ዘጋቢዎችና ፎቶግራፍ አንሺዎች በቅርብ ሁኔታውን ለመከታተል ሲሉ ሕይወታቸውን እንዳጡ እናስታውሳለን። እንዲያውም አንደኛው ፎቶግራፍ አንሺ የሞተው ልክ ጣቱ በካሜራው ማንሻ ላይ እንዳረፈ ነው። አንደኛው የእሳተ ገሞራ አጥኚ ከዚያ ቀደም “ሞቴን እሳተ ገሞራ ዳር ያድርገው” ብሎ ይናገር የነበረ ሲሆን ልክ እንደተመኘውም በእሳተ ገሞራ ሕይወቱ አልፏል። ሁሉም ለሥራቸውና ለሞያቸው ያደሩ ነበሩ። ሆኖም የተነገራቸውን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለታቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ዛሬ ብዙዎች አምላክ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት ስለመወሰኑ የሚገልጸውን መልእክት ይሰማሉ። በተወሰነ ደረጃ ማስጠንቀቂያው እውነትነት እንዳለው ይገነዘባሉ። ‘አንድ ቀን መምጣቱ አይቀርም፤ ዛሬ ግን አይመጣም’ ብለው ያስቡ ይሆናል። በእነሱ አመለካከት አሁን በጣም አስፈላጊ ነው ብለው ከሚያስቡት ነገር ትኩረታቸው እንዳይሰረቅ ሲሉ የይሖዋን ቀን ለእነሱ በሚስማማ መንገድ አርቀው ይመለከቱታል።

ባሮክ የዚህ ዓይነት ችግር ነበረበት። የጥንቱ ነቢይ የኤርምያስ ጸሐፊ እንደመሆኑ መጠን በኢየሩሳሌም ላይ ከተደቀነው ጥፋት እንዲድኑ እስራኤላውያንን በድፍረት ሲያስጠነቅቅ ነበር። ይሁንና በአንድ ወቅት በተሰጠው ተልእኮ ተሰላቸ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ “ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? . . . አትፈልገው” ሲል አመለካከቱን እንዲያስተካክል ምክር ሰጠው። ባሮክ እንደ ሀብት፣ ዝና ወይም ቁሳዊ ንብረት የመሳሰሉትን ‘ታላላቅ ነገሮች መፈለግ’ አልነበረበትም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ ጎን እንዲቆሙ ለመርዳት የአምላክን ፈቃድ በመፈጸሙ ተግባር ላይ ማተኮር ነበረበት። ይህን ካደረገ ‘ነፍሱን እንደ ምርኮ’ ይቀበላል። (ኤርምያስ 45:​1-5) በተመሳሳይ እኛም ‘ለራሳችን ታላላቅ ነገሮችን ከመፈለግ’ ይልቅ ሕይወታችንን ማዳን እንድንችል ይሖዋን መፈለግ ይኖርብናል።

በፉገን ተራራ ከአሥራ ሁለት የሚበልጡ ፖሊሶችና ፈቃደኛ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉ በእሳተ ገሞራው ተቀብረዋል። አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመርዳትና ለመጠበቅ በመጣር ላይ ነበሩ። በቅን ልቦና ተነሳስተው ይህን ዓለም ለማሻሻል ደፋ ቀና ከሚሉ ወንዶችና ሴቶች ጋር ይመሳሰላሉ። ሐሳባቸው መልካም ቢሆንም “ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም።” (መክብብ 1:​15) ይህ ጠማማ የነገሮች ሥርዓት ሊቃና አይችልም። አምላክ ሊያጠፋው የወሰነውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማዳን በመጣር “የዓለም ወዳጅ” መሆን ምክንያታዊ ነውን?

አንዴ ሸሽተህ ከወጣህ አትመለስ

አደጋ ከተደቀነበት ከዚህ ሥርዓት መውጣት አንድ ነገር ሲሆን “በዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር” ውስጥ እንደተሸሸጉ መቀጠል ደግሞ ሌላ ነገር ነው። (1 ጴጥሮስ 2:​17 NW ) ሸሽተው ከወጡ በኋላ በፉገን ተራራ አጠገብ የሚገኘውን እርሻቸውን ለማየት የተመለሱትን ገበሬዎች መርሳት የለብንም። ምናልባትም “ወደተለመደው” ኑሯቸው ለመመለስ ቸኩለው ይሆናል። ወደዚያ ለመመለስ መወሰናቸው ጥበብ እንዳልነበረ ትገነዘባለህ። የአደጋ ቀጣናውን አልፈው ሲሄዱ ያ የመጀመሪያቸው ላይሆን ይችላል። ወደ አደገኛው አካባቢ ለአጭር ጊዜ ደረስ ብለው ምንም ሳይሆኑ ተመልሰው ይሆናል። በሚቀጥለው ጊዜ በዚሁ አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተው አሁንም ምንም ሳይሆኑ ተመልሰው ይሆናል። በዚህ መንገድ ወደ አደጋ ቀጣናው ዘልቆ መግባቱን ልማድ አድርገውት እንዲሁም በዚያ አካባቢ ለመቆየት ድፍረት እያገኙ መጥተው ይሆናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ወቅት ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚከሰት ጠቅሶ ነበር። እንዲህ አለ:- “በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።”​—⁠ማቴዎስ 24:​3, 38, 39

ኢየሱስ ስለ መብላት፣ ስለ መጠጣትና ስለ ማግባት እንደጠቀሰ ልብ በል። በይሖዋ ፊት እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት አይደሉም። ታዲያ ስህተቱ ምን ላይ ነበር? በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ሕይወታቸውን በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረጋቸው ‘አላስተዋሉም።’ በአደጋ ጊዜ ዘና ብሎ “መደበኛ” ኑሮውን የሚመራ ሰው ሊኖር አይችልም። ጥፋት ከሚጠብቀው ከዚህ ዓለም አንዴ ሸሽተህ ከወጣህ ወይም ከተለየህ በኋላ አንዳንድ ነገር ለመለቃቀም ብለህ ተመልሰህ እንድትገባ የሚገፋፋህን ማንኛውንም ተጽዕኖ መዋጋት አለብህ። (1 ቆሮንቶስ 7:​31) ከስጋት ነፃ ከሆነው መንፈሳዊ ቀጣና ወጥተህ ስትባዝን ከቆየህ በኋላ ማንም ልብ ሳይልህና ምንም ጉዳት ሳይደርስብህ ተመልሰህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ የልብ ልብ እንዲሰማህ ሊያደርግና እንደገና ወደ ዓለም ተመልሰህ በዚያ ረዘም ላለ ጊዜ እንድትቆይ ሊያደርግህ ይችላል። ብዙም ሳትቆይ “መጨረሻው ገና ነው” የሚል ዝንባሌ ልታዳብር ትችላለህ።

በተጨማሪም የዜና ዘጋቢዎችንና ፎቶግራፍ አንሺዎችን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ አካባቢውን ባጥለቀለቀው የእሳተ ገሞራ ፍሳሽ ሕይወታቸውን ያጡትን የታክሲ ሹፌሮች አስብ። ዛሬም ወደ ዓለም ለመመለስ የሚዳፈሩ ሰዎችን ተከትለው የሚሄዱ አንዳንድ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ብቻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አደገኛ ተብሎ ወደተከለለ ቀጣና መግባት የሚያስከትለው ኪሳራ የከፋ መሆኑ ግልጽ ነው።

በፉገን ተራራ በደረሰው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሕይወታቸውን ያጡት ሁሉ የተከለለውን የአደጋ ቀጣና አልፈው ወደ ውስጥ ዘልቀው ገብተዋል። ተራራው አንድ ቀን እንደሚፈነዳ ቢጠብቁም የዚያን ዕለት ይሆናል ብሎ ያሰበ ግን አልነበረም። ብዙዎች የዚህን የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቶች በማስተዋል የይሖዋ ቀን ከዕለታት አንድ ቀን እንደሚመጣ ቢጠብቁም በቅርቡ ይሆናል ብለው ግን አያስቡም። እንዲያውም አንዳንዶች ይህ ቀን ፈጽሞ “ዛሬ” ሊሆን አይችልም ብለው ያስባሉ። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በጣም አደገኛ ነው።

ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል’ ሲል አስጠንቅቋል። ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቅንና እያስቸኮልን’ ነቅተን መኖር እንዲሁም ‘ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆነን በሰላም እንድንገኝ’ መትጋት ያስፈልገናል። (2 ጴጥሮስ 3:​10-14) ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከጠፋ በኋላ በአምላክ መንግሥት የሚተዳደር ገነት የሆነ ምድር ይጠብቀናል። የይሖዋ ቀን ወደ ዓለም ተመልሰን በገባንበት ዕለት ሊመጣ ስለሚችል በምንም ዓይነት አደገኛ ወደሆነው ቀጣና ተዳፍረን ለመግባት አንፈተን።

በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ተሸሸግ፤ ከዚያም አትውጣ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ተሸሸግ፤ ከዚያም አትውጣ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Iwasa/Sipa Press

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ