ቅናትን በተመለከተ ማወቅ ያለብህ ነገር
ቅናት ምንድን ነው? አንድን ግለሰብ እንዲሰጋ፣ እንዲያዝን ወይም እንዲናደድ ሊያደርገው የሚችል ኃይለኛ ስሜት ነው። አንድ ሰው በአንድ ዓይነት ሥራ ከእኛ ይልቅ የተሳካለት ሲመስለን እንቀና ይሆናል። ወይም ደግሞ አንድ ወዳጃችን ከእኛ የበለጠ ሲመሰገን ልንቀና እንችላለን። ይሁን እንጂ ቅናት ሁሉ ስሕተት ነውን?
በቅናት የተሸነፉ ሰዎች ወደፊት ሊቀናቀኗቸው የሚችሉ ሰዎችን ወደ መጠርጠሩ ያዘነብላሉ። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። በመጀመሪያ ጋሻ ጃግሬው የነበረውን ዳዊትን ይወደው ነበር፤ እንዲያውም የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር። (1 ሳሙኤል 16:21፤ 18:5) ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ሴቶች “ሳኦል ሺህ፣ ዳዊትም እልፍ ገደለ” ብለው ዳዊትን ሲያወድሱት ንጉሥ ሳኦል ሰማ። (1 ሳሙኤል 18:7) ሳኦል ይህ ሁኔታ ከዳዊት ጋር የነበረውን ጥሩ ግንኙነት እንዲያበላሽበት መፍቀድ አልነበረበትም። ይሁንና ጉዳዩ በጣም አናደደው። “ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ [“በጥርጣሬ” አዓት] ተመለከተው።”—1 ሳሙኤል 18:9
አንድ ቀናተኛ ሰው ሌላውን ሰው ለመጉዳት አይፈልግ ይሆናል። እሱ ወይም እሷ አንድ ወዳጃቸው ስለተሳካለት ቅር ሊሰኙና ተመሳሳይ ችሎታ እንዲኖራቸው ወይም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸው ይመኙ ይሆናል። በሌላ በኩል ምቀኝነት የቅናት አሉታዊ ገጽታ ነው። የተመቀኘው ግለሰብ ያስቀናው ሰው ጥሩ ነገር እንዳያገኝ ለማድረግ በድብቅ ይጥር ወይም በሰውዬው ላይ መጥፎ ነገር እንዲደርስበት ይመኝ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ምቀኛ ሰው ስሜቱን መደበቅ ያቅተዋል። ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል እንደሞከረ ሁሉ ምቀኛ ሰው ሌላውን ግለሰብ በግልጽ ለመጉዳት ውስጣዊ ግፊት ሊያድርበት ይችላል። ሳኦል ዳዊትን ‘ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ’ ብሎ በማሰብ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጦሩን ወርውሮበታል።—1 ሳሙኤል 18:11፤ 19:10
‘ሆኖም እኔ ቀናተኛ አይደለሁም’ ትል ይሆናል። እርግጥ፣ ቅናት ሕይወትህን ላይቆጣጠረው ይችላል። ይሁንና ሁላችንም ብንሆን በራሳችንም ሆነ በሌሎች ሰዎች የቅናት ስሜት በተወሰነ ደረጃ መነካታችን አይቀርም። የሌሎችን ቅናት ወዲያውኑ ለማየት ብንችልም በራሳችን ውስጥ ያለው ቅናት ቶሎ ላይታወቀን ይችላል።
“የቅናት ዝንባሌ”
የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው የሰው የኃጢአተኝነት ሁኔታ ብዙውን ጊዜ በቅናት ሳቢያ የተፈጸሙ ኃጢአቶችን ያጎላል። የቃየንን እና የአቤልን ታሪክ ታስታውሳለህን? እነዚህ የአዳምና የሔዋን ልጆች ሁለቱም ለአምላክ መሥዋዕት አቅርበው ነበር። አቤል ይህን ያደረገው የእምነት ሰው ስለነበረ ነው። (ዕብራውያን 11:4) አምላክ ምድርን በተመለከተ ያለውን ታላቅ ዓላማ ለመፈጸም ችሎታ እንዳለው ያምን ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 3:15፤ ዕብራውያን 11:1) በተጨማሪም አቤል በመጪዋ ምድራዊት ገነት ውስጥ አምላክ ለታማኝ ሰዎች ሕይወት እንደሚሰጣቸው ያምን ነበር። (ዕብራውያን 11:6) ስለዚህ አምላክ በአቤል መሥዋዕት እንደተደሰተ አሳየ። ቃየን በእውነት ወንድሙን የሚወድ ቢሆን ኖሮ አምላክ አቤልን በመባረኩ ይደሰት ነበር። ከዚህ ይልቅ ቃየን “እጅግ ተናደደ።”—ዘፍጥረት 4:5
ቃየን እንደ አቤል እንዲባረክ ከፈለገ መልካም እንዲሠራ አምላክ መከረው። ከዚያም አምላክ “መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” በማለት አስጠነቀቀው። (ዘፍጥረት 4:7) ቃየን ቅናት የፈጠረበትን ንዴት መቆጣጠር አለመቻሉ ያሳዝናል። ቅናት ጻድቅ ወንድሙን እንዲገድል ገፋፋው። (1 ዮሐንስ 3:12) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጦርነቶችና ግጭቶች በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። “ከጦርነት መሠረታዊ መንስኤዎች አንዳንዶቹ ተጨማሪ መሬት፣ ሀብትና ሥልጣን መመኘት ወይም ደኅንነትን ለማስከበር መፈልግ ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ይገልጻል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ጦርነቶች አይካፈሉም። (ዮሐንስ 17:16) ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ግለሰብ ክርስቲያኖች በቃላት ግጭቶች ውስጥ መግባታቸው ያሳዝናል። ሌሎች የጉባኤ አባላት በእነዚህ የቃላት ግጭቶች ውስጥ ከገቡ ደግሞ እነዚህ ግጭቶች ወደ ከባድ የቃላት ጦርነቶች ሊለወጡ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ?” በማለት መሰል አማኞችን ጠየቃቸው። (ያዕቆብ 4:1) ለቁሳዊ ነገሮች የነበራቸውን ስግብግብነት በማጋለጥ ለዚህ ጥያቄ መልስ ከሰጠ በኋላ “ትመኛላችሁ” ወይም “ቀናተኛ” ትሆናላችሁ በማለት አከለ። (ያዕቆብ 4:2፣ የአዓት የግርጌ ማስታወሻ።) አዎን፣ ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር እንድንመኝና የተሻሉ ሁኔታዎች ያላቸው በሚመስሉ ሰዎች ላይ እንድንቀና ሊያደርገን ይችላል። በዚህ ምክንያት ያዕቆብ ስለ ሰብዓዊው “የቅናት ዝንባሌ” አስጠንቅቋል።—ያዕቆብ 4:5 አዓት
የቅናትን መንስኤዎች መገንዘብ ምን ጥቅሞችን ያስገኛል? ሐቀኛ እንድንሆንና ከሌሎች ሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል። በተጨማሪም በይበልጥ ሁኔታዎችን የምንረዳ፣ ታጋሾችና ይቅር ባዩች እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለመዳንና ከሰብዓዊ የኃጢአተኝነት ዝንባሌዎች ለመላቀቅ የሚያስችለው የአምላክ ፍቅራዊ ዝግጅት ለሰው ልጆች ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ያጎላል።—ሮሜ 7:24, 25
መጥፎ ቅናት የማይኖርበት ዓለም
ከሰው አንፃር ሲታይ መጥፎ ቅናት የሌለበት ዓለም ሊመጣ የሚችል አይመስልም። ራም ላንዱአ የተባሉ ደራሲ እንዲህ በማለት ይህን ሐቅ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል፦ “ስለ ጉዳዩ የተናገሩት እነዚህ ሁሉ ፈላስፋዎችና . . . የሥነ ልቦና ጠበብት ለአያሌ ትውልዶች ያከማቹት ጥበብ በቅናት ለተጠቃው ሰው የሰጠው መመሪያ የለም። . . . ቀናተኛ ሰውን ያዳነ ሐኪም አለን?”
ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ማንም ሰው አምላካዊ ባልሆነ ቅናት ወይም በምቀኝነት በማይጠቃበት አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት እንደምናገኝ የሚገልጽ ተስፋ ይዞልናል። ከዚህም በተጨማሪ የዚህ አዲስ ዓለም ሰላም እንደዚህ ዓይነቱን መጥፎ ባሕርይ በሚያሳዩ ሰዎች አይበጠበጥም።—ገላትያ 5:19–21፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ሆኖም ሁሉም ዓይነት ቅናት መጥፎ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘ቀናተኛ አምላክ’ እንደሆነ ይናገራል። (ዘጸአት 34:14) ይህ ምን ማለት ነው? በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ ስለ ሆነው ቅናት ምን ይላል? አንድ ግለሰብ ተገቢ ያልሆነ ቅናትን መቆጣጠር የሚችለውስ እንዴት ነው? የሚቀጥሉትን ርዕሶች ተመልከት።