የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”
    መጠበቂያ ግንብ—2002 | ታኅሣሥ 15
    • “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”

      “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።”​—⁠ያዕቆብ 4:8

      1, 2. (ሀ) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ምን ብለው ይናገራሉ? (ለ) ያዕቆብ ምን ምክር ሰጥቷል? ምክሩስ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

      “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚሉት ቃላት በብሔራዊ ባንዲራዎች ላይ አልፎ ተርፎም በወታደሮች የደንብ ልብስ ላይ ተጽፈው ይታያሉ። “በአምላክ እንታመናለን” የሚሉት ቃላት በዚህ ዘመን በሚሠራባቸው ቁጥር ስፍር በሌላቸው ሳንቲሞችና የብር ኖቶች ላይ ታትመዋል። ብዙ ሰዎች ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ስላሉ ወይም ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉትን ጥቅሶች በየቦታው ስለ ለጠፉ ብቻ ከአምላክ ጋር ዝምድና ሊኖራቸው የሚችል ይመስልሃል?

      2 መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት እንደሚቻል ይገልጻል። ይሁንና ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንኳ ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረቱትን ዝምድና ማጠናከር አስፈልጓቸው ነበር። ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የነበረው ያዕቆብ አንዳንዶች ሥጋዊ አስተሳሰብ የነበራቸው በመሆኑና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ሳይጠብቁ በመቅረታቸው ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈልጎታል። በሰጣቸው ምክር ውስጥ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚል ብርቱ ማሳሰቢያ ይገኝበታል። (ያዕቆብ 4:​1-12) ያዕቆብ “ቅረቡ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

      3, 4. (ሀ) “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ” የሚለው የያዕቆብ ማሳሰቢያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ አንባቢዎችን ምን አስታውሷቸው ሊሆን ይችላል? (ለ) ወደ አምላክ መቅረብ እንደሚቻል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      3 ያዕቆብ እዚህ ላይ የተጠቀመበት አገላለጽ ለአብዛኛው አንባቢ እንግዳ አልነበረም። የሙሴ ሕግ ካህናቱ ሕዝቡን ወክለው ወደ ይሖዋ ‘በሚቀርቡበት ጊዜ’ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ ይዟል። (ዘጸአት 19:​22) በመሆኑም የያዕቆብን መልእክት የሚያነብቡ ሰዎች ወደ ይሖዋ የመቅረብን ጉዳይ አቅልለው እንዳይመለከቱት ሳያስታውሳቸው አልቀረም። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻውን ከፍተኛ ሥልጣን የያዘ አካል ነው።

      4 በሌላ በኩል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “[በያዕቆብ 4:​8] ላይ የሚገኘው ጥብቅ ምክር በከፍተኛ ደረጃ አዎንታዊ አመለካከት ይንጸባረቅበታል” ብለዋል። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ በፍቅር ተነሳስቶ ጥሪ ያቀርብላቸው እንደነበር ያዕቆብ ያውቃል። (2 ዜና መዋዕል 15:​2) የኢየሱስ መሥዋዕት ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል። (ኤፌሶን 3:​11, 12) በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻልበት መንገድ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ክፍት ነው! ይሁንና በዚህ ግሩም አጋጣሚ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ አምላክ መቅረብ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች በአጭሩ እንመረምራለን።

      ስለ አምላክ ‘እውቀት መቅሰማችሁን’ ቀጥሉ

      5, 6. የወጣቱ ሳሙኤል ምሳሌ ስለ አምላክ ‘እውቀት መቅሰምን’ በተመለከተ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

      5 ኢየሱስ በዮሐንስ 17:​3 ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ የተረጎሙበት መንገድ ከአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በመጠኑ የተለየ ነው። ስለ አምላክ “እውቀት መቅሰም [NW ]” ከማለት ይልቅ አምላክን “ማወቅ” የሚለውን ግስ ተጠቅመዋል። ይሁን እንጂ በርካታ ምሁራን መጀመሪያ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል ከዚያ የበለጠ ስፋት ያለው ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። ይህም ከሌላው ወገን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ወደመመሥረት ሊያደርስ የሚችል ቀጣይነት ያለውን ሂደት የሚያመለክት ነው።

      6 አምላክን በቅርብ ማወቅ ኢየሱስ ያመጣው አዲስ ሐሳብ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሳሙኤል ልጅ እያለ “እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። (1 ሳሙኤል 3:​7) እንዲህ ሲባል ታዲያ ሳሙኤል ስለ አምላኩ የነበረው እውቀት በጣም ውስን ነበር ማለት ነው? አይደለም። ወላጆቹና ካህናቱ ስለ አምላክ ብዙ ነገር አስተምረውት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም አንድ ምሁር እንደተናገሩት በዚህ ጥቅስ ላይ የገባውን የዕብራይስጥ ቃል “በጣም የቀረበ ትውውቅ ላላቸው ወዳጆችም መጠቀም” ይቻላል። ሳሙኤል የይሖዋ ቃል አቀባይ ሆኖ ባገለገለበት ወቅት ይሖዋን ከበፊቱ በበለጠ በቅርብ ሊያውቀው ችሏል። ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ ይሖዋን ይበልጥ በማወቁ ከእሱ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና መመሥረት ችሏል።​—⁠1 ሳሙኤል 3:​19, 20

      7, 8. (ሀ) ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ከማጥናት ወደኋላ ማለት የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ቃል የያዛቸው ልናጠናቸው የሚገቡ አንዳንድ ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

      7 አንተስ ይሖዋን በቅርብ ለማወቅ የሚያስችልህን እውቀት እየቀሰምክ ነው? እንዲህ ለማድረግ አምላክ ለሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ‘ምኞት’ ማሳደር ይኖርብሃል። (1 ጴጥሮስ 2:​2) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶች ማወቅህ ብቻውን በቂ አይደለም። ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ለማወቅ ጥረት አድርግ። (ዕብራውያን 5:​12-14) እንደዚህ ዓይነት ትምህርቶች ለመረዳት ይከብዳሉ በማለት ፈርተህ ትተዋቸዋለህ? ከሆነ ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ መሆኑን አትዘንጋ። (ኢሳይያስ 30:​20) ፍጽምና ለሚጎድላቸው ሰዎች ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶችን እንዴት ማስተማር እንዳለበት ያውቃል። እንዲሁም የሚሰጥህን ትምህርት ለመረዳት ከልብ የምታደርገውን ጥረት ሊባርክልህ ይችላል።​—⁠መዝሙር 25:​4

      8 “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳለህ ለማወቅ ለምን ራስህን አትመረምርም? (1 ቆሮንቶስ 2:​10) እነዚህ ጉዳዮች የሃይማኖት ምሁራንና ቀሳውስት ዘወትር እያነሱ የሚነጋገሩባቸው ዓይነት አሰልቺ ርዕሶች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ስለ አፍቃሪው አባታችን በጣም ማራኪ እውቀት የምንቀስምባቸው ጠቃሚ መሠረተ ትምህርቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል ቤዛው፣ ይሖዋ የገለጠው ቅዱስ “ምሥጢር” እና ይሖዋ ሕዝቡን ለመባረክና ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ ከሰዎች ጋር የገባቸው የተለያዩ ቃል ኪዳኖች እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ርዕሶች በግል ምርምርና ጥናት ማድረግ የምንችልባቸው አስደሳችና የሚክሱ ርዕሶች ናቸው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​7 አ.መ.ት 

      9, 10. (ሀ) ኩራት መጥፎ ባሕርይ ነው የሚባለው ለምንድን ነው? ኩራትን እንድናስወግድስ ምን ይረዳናል? (ለ) ይሖዋ ማለቂያ የሌለው እውቀት እንዳለው ማወቃችን ትሑት እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

      9 ጥልቀት ስላላቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች ያለህ እውቀት እያደገ በሄደ መጠን ብዙ አውቃለሁ በሚል ኩራት እንዳያድርብህ ተጠንቀቅ። (1 ቆሮንቶስ 8:​1) ኩራት ሰዎችን ከአምላክ የሚያርቅ መጥፎ ባሕርይ ነው። (ምሳሌ 16:​5፤ ያዕቆብ 4:​6) ማንኛውም ሰው ቢሆን በእውቀቱ የሚኩራራበት ምክንያት እንደሌለ አስታውስ። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የሰው ልጅ በቅርቡ ስላገኘው ሳይንሳዊ እድገት የሚያትት አንድ መጽሐፍ በመግቢያው ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ ተመልከት:- “ብዙ ባወቅን መጠን እውቀታችን ምን ያህል ቁንጽል እንደሆነ እንገነዘባለን። . . . እስካሁን ያካበትነውን እውቀት ወደፊት ከምንማረው ጋር ስናስተያየው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።” እንዲህ ዓይነቱ የትሕትና ባሕርይ ያስደስታል። እኛ ያለንን ኢምንት የሆነ እውቀት ይሖዋ አምላክ ካለው ማለቂያ የሌለው እውቀት ጋር ስናነጻጽር ደግሞ የበለጠ ትሑት መሆን እንዳለብን እንዲሰማን ያደርጋል። ለምን?

      10 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ የሚናገራቸውን አንዳንድ ሐሳቦች ተመልከት። ‘አሳብህ እጅግ ጥልቅ ነው።’ (መዝሙር 92:​5) ይሖዋ ‘ለጥበቡ ቁጥር የለውም።’ (መዝሙር 147:​5) የይሖዋ ‘ማስተዋል አይመረመርም።’ (ኢሳይያስ 40:​28) “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው።” (ሮሜ 11:​33) ስለ ይሖዋ ማወቅ የሚቻለውን ሁሉ አውቀን መጨረስ እንደማንችል ግልጽ ነው። (መክብብ 3:​11) አስደናቂ የሆኑ ብዙ ነገሮችን አስተምሮናል። ሆኖም መቼም ቢሆን እውቀት የምንቀስምበት ማለቂያ የሌለው የእውቀት ክምችት አለ። ይህን ማወቃችን አስደሳችና ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ የሚያስገድድ ሐቅ አይደለም? በመሆኑም በእውቀት እያደግን በሄድን መጠን እውቀታችንን ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት ልንጠቀምበት ይገባናል።​—⁠ማቴዎስ 23:​12፤ ሉቃስ 9:​48

      ለይሖዋ ያለህን ፍቅር በተግባር አሳይ

      11, 12. (ሀ) ስለ ይሖዋ የምንቀስመው እውቀት በእኛ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይገባል? (ለ) አንድ ሰው ለአምላክ ያለው ፍቅር እውነተኛ መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው በምንድን ነው?

      11 ሐዋርያው ጳውሎስ በእውቀትና በፍቅር መካከል ዝምድና መኖሩን መግለጹ ትክክል ነው። “ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 1:​9) ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የምንማረው ውድ እውነት በትዕቢት እንድንነፋ ከማድረግ ይልቅ ለሰማያዊ አባታችን ያለንን ፍቅር ሊያሳድግልን ይገባል።

      12 ብዙ ሰዎች ለአምላክ ፍቅር እንዳላቸው ቢናገሩም ለእሱ እውነተኛ ፍቅር እንደሌላቸው የታወቀ ነው። አምላክን ከልብ እንደሚወድዱት በቅንነት ይናገሩ ይሆናል። አምላክን መውደድ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ጥሩ ባሕርይ ከመሆኑም በላይ የሚያስመሰግንም ነው። ይህ ማለት ግን ለአምላክ እውነተኛ ፍቅር አላቸው ማለት አይደለም። ለምን? የአምላክ ቃል እውነተኛ ፍቅርን በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል:- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:3) በመሆኑም አንድ ሰው ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር አለኝ ማለት የሚችለው ታዛዥነቱን በተግባር በመግለጽ ብቻ ነው።

      13. አምላካዊ ፍርሃት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በተግባር እንድንገልጽ የሚረዳን እንዴት ነው?

      13 አምላካዊ ፍርሃት ካለን ይሖዋን መታዘዝ ቀላል ይሆንልናል። ለይሖዋ ከፍተኛ አድናቆትና ጥልቅ አክብሮት የሚያድርብን ስለ እሱ እውቀት ስንቀስም ነው። ይህም ወደር የለሽ ስለሆነው ቅድስናው፣ ክብሩ፣ ኃይሉ፣ ፍትሑ፣ ጥበቡና ፍቅሩ መማርን ይጨምራል። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ወደ እሱ እንድንቀርብ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው። እንዲያውም መዝሙር 25:​14 “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው [“ወዳጃቸው፣” የ1980 ትርጉም ] ነው” እንደሚል ልብ በል። በመሆኑም ተወዳጅ የሆነውን ሰማያዊ አባታችንን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት የሚሰማን ከሆነ ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። አምላካዊ ፍርሃት “በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን በምሳሌ 3:​6 ላይ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር እንድንከተል ይረዳናል። ይህ ምን ማለት ነው?

      14, 15. (ሀ) በዕለታዊ ሕይወታችን የሚያጋጥሙን አንዳንድ ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) አምላካዊ ፍርሃት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ውሳኔዎችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

      14 ከባድም ይሁን ቀላል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ነገሮች በየቀኑ ያጋጥሙሃል። ለምሳሌ ያህል ከሥራ ባልደረቦችህ፣ በትምህርት ቤት አብረውህ ከሚማሩት ተማሪዎችና ከጎረቤቶችህ ጋር የምትጫወተው ስለምን ጉዳይ ነው? (ሉቃስ 6:​45) የተሰጠህን ሥራ በትጋት ታከናውናለህ ወይስ የግብር ይውጣ ሥራ መሥራት ይቀናሃል? (ቆላስይስ 3:​23) ለይሖዋ ፍቅር ከሌላቸው ሰዎች ጋር የመቀራረብ ፍላጎት አለህ? ወይስ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ዝምድናህን ለማጠናከር የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለህ? (ምሳሌ 13:​20) አነስተኛ በሚመስሉ ጉዳዮችም እንኳ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ጥረት ታደርጋለህ? (ማቴዎስ 6:​33) በየቀኑ ውሳኔ ስታደርግ ከላይ እንደተጠቀሱት ባሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትመራ ከሆነ በእርግጥም “በመንገድህ ሁሉ” ይሖዋን አውቀሃል ማለት ይቻላል።

      15 በሌላ አባባል ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ እያልን ማሰብ ይኖርብናል:- ‘ይሖዋ ምን እንዳደርግ ይፈልግብኛል? ከሁሉ ይበልጥ እሱን የሚያስደስተው እንዴት ያለ ውሳኔ ባደርግ ነው?’ (ምሳሌ 27:​11) በዚህ መንገድ አምላካዊ ፍርሃት ማሳየታችን ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ግሩም መንገድ ነው። በተጨማሪም አምላካዊ ፍርሃት መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አካላዊ ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ ይገፋፋናል። ያዕቆብ ክርስቲያኖች ‘ወደ አምላክ እንዲቀርቡ’ ባሳሰበበት በዚያው ጥቅስ ላይ “እናንተ ኃጢአተኞች፣ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፣ ልባችሁን አጥሩ” የሚል ምክርም እንደሰጠ ልብ በል።​—⁠ያዕቆብ 4:​8

      16. ለይሖዋ በመስጠታችን ምን እንዳደረግንለት ሊሰማን አይገባም? ሆኖም የምናደርገው ነገር የምን መግለጫ ሊሆን ይችላል?

      16 እርግጥ ነው፣ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምንገልጸው ከመጥፎ ነገር በመራቅ ብቻ አይደለም። ፍቅር ጥሩ እንድናደርግም ይገፋፋናል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለሚያሳየን የተትረፈረፈ ልግስና ምን ምላሽ እንሰጣለን? ያዕቆብ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፣ . . . ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:17) ከሃብታችን ውስጥ የተወሰነውን ለይሖዋ ብንሰጥም እንኳ ምንም እንደማንጨምርለት የታወቀ ነው። በዓለም ላይ ያለው ሀብት ሁሉ የእሱ ነው። (መዝሙር 50:​12) እንዲሁም ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ለይሖዋ ስንሰጥ የግድ የእኛ እርዳታ ያስፈልገዋል ማለት አይደለም። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ፈቃደኞች ባንሆን እንኳ ድንጋዮች እንዲናገሩ ማድረግ ይችላል! ታዲያ ጥሪታችንን፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ለይሖዋ የምንሰጠው ለምንድን ነው? እንዲህ በማድረግ በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን እንደምንወደው መግለጽ ስለምንፈልግ ነው።​—⁠ማርቆስ 12:​29, 30

      17. ለይሖዋ በደስታ እንድንሰጥ ሊያነሳሳን የሚችለው ምንድን ነው?

      17 ‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ስለሚወድ’ ለይሖዋ ስንሰጥ በደስታ መሆን አለበት። (2 ቆሮንቶስ 9:​7) ዘዳግም 16:​17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው “አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደ ሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት በደስታ እንድንሰጥ ያበረታታናል። ይሖዋ ያሳየንን ልግስና ስናስብ ለእሱ በደስታ የመስጠት ፍላጎት ያድርብናል። አንድ ወላጅ ከሚወድደው ልጁ የተሰጠው ትንሽ ስጦታ እንደሚያስደስተው ሁሉ ይሖዋም በደስታ ስንሰጥ ይደሰታል። በዚህ መንገድ ፍቅራችንን መግለጻችን ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል።

      በጸሎት አማካኝነት የጠበቀ ወዳጅነት ገንቡ

      18. የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻላችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

      18 በግል የምናቀርበው ጸሎት ወደ ሰማያዊ አባታችን ይበልጥ ለመቅረብና የልባችንን አውጥተን እንድንነግረው የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ፊልጵስዩስ 4:​6) ጸሎት ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚያስችለን ወሳኝ መንገድ በመሆኑ የጸሎታችንን ይዘት በተመለከተ ቆም ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው። ጸሎታችን በቃላት አመራረጡና ይዘቱ የላቀ መሆን አለበት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምናቀርበው ጸሎት ከልባችን የመነጨ መሆን አለበት። የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

      19, 20. ከመጸለያችን በፊት ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው? ልናሰላስልባቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

      19 ከመጸለያችን በፊት ማሰላሰል እንችላለን። አስቀድመን ማሰላሰላችን በጸሎታችን ልንጠቅሳቸው የፈለግናቸውን ነገሮች በደፈናው ከመግለጽ ይልቅ ለይተን ለመናገር ያስችለናል። በዚህ መንገድ በጣም የተለመዱና በቀላሉ ወደ አእምሯችን የሚመጡ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ከመደጋገም እንቆጠባለን። (ምሳሌ 15:​28, 29) ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ በጠቀሳቸው አንዳንድ ነጥቦች ላይ ማሰላሰላችንና ከእኛ ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ማሰባችን ሊጠቅመን ይችላል። (ማቴዎስ 6:​9-13) ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ፈቃድ በምድር እንዲሆን እኛ በበኩላችን ምን ድርሻ ማበርከት እንደምንችል ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። አቅማችን የፈቀደውን ያህል እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዳለን ለይሖዋ መግለጽና የሰጠን የአገልግሎት መብት ምንም ይሁን ምን መወጣት እንድንችል እንዲረዳን መጠየቅ እንችል ይሆን? ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን የማሟላቱ ኃላፊነት ጫና ፈጥሮብን ይሆን? ይሖዋ ይቅር እንዲለን የምንፈልገው የትኛውን በደላችንን ነው? በይበልጥ የይቅር ባይነት ባሕርይ ማሳየት የሚኖርብን ለእነማን ነው? ምን ፈተናዎች አጋጥመውናል? በዚህ ረገድ የይሖዋ ጥበቃ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልገን ተገንዝበናልን?

      20 በተጨማሪም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ስለምናውቃቸው ሰዎች ማሰብ እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 1:​11) ምስጋና ማቅረብ እንደሚያስፈልገንም መርሳት አይኖርብንም። ቆም ብለን ካሰብንበት ይሖዋ ላሳየን ከፍተኛ ደግነት በየዕለቱ እሱን የምናመሰግንበትና የምናወድስበት ምክንያት አናጣም። (ዘዳግም 8:​10፤ ሉቃስ 10:​21) እንዲህ ማድረጋችን ተጨማሪ ጥቅም ያስገኝልናል፤ ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ አዎንታዊና አመስጋኝ እንድንሆን ይረዳናል።

      21. ይሖዋን በጸሎት መቅረብን በተመለከተ የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ማጥናታችን ይጠቅመናል?

      21 በተጨማሪም ጥናት የጸሎታችን ይዘት እንዲሻሻል ሊረዳን ይችላል። በአምላክ ቃል ላይ ተመዝግበው የሚገኙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ያቀረቧቸው ግሩም ጸሎቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ከባድ ችግር አጋጥሞን ጭንቀት ካደረብን እንዲሁም ሁኔታው የራሳችንን ወይም የምናፈቅራቸውን ሰዎች ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል ከተሰማን ያዕቆብ ቂመኛ ከሆነው ከወንድሙ ከዔሳው ጋር የሚገናኝበት ጊዜ ሲደርስ ያቀረበውን ጸሎት ማንበብ እንችላለን። (ዘፍጥረት 32:​9-12) ወይም ደግሞ ንጉሥ አሳ አንድ ሚልዮን የሚያህል የኢትዮጵያ ሠራዊት በአምላክ ሕዝብ ላይ ስጋት በፈጠረ ጊዜ ያቀረበውን ጸሎት ማጥናት እንችላለን። (2 ዜና መዋዕል 14:​11, 12) በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ሊያስከትል የሚችል ችግር ካጋጠመን ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ በበኣል አምላኪዎች ፊት ያቀረበውን ጸሎት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ኢየሩሳሌም የነበረችበትን አሳዛኝ ሁኔታ በተመለከተ ነህምያ ያቀረበው ጸሎትም በዚህ ረገድ ይጠቅመናል። (1 ነገሥት 18:​36, 37፤ ነህምያ 1:​4-11) እንዲህ ዓይነቶቹን ጸሎቶች ማንበብና በዚያም ላይ ማሰላሰል እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም በላይ የሚያስጨንቁንን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ለይሖዋ መግለጽ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ፍንጭ ይሰጡናል።

      22. የ2003 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? በዓመቱ ውስጥ በየጊዜው ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

      22 ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ” ሲል የሰጠውን ምክር ከመከተል የበለጠ ክብርም ሆነ የላቀ ግብ ሊኖር አይችልም። (ያዕቆብ 4:​8) ስለ አምላክ ያለንን እውቀት እያሳደግን በመሄድ፣ ለእሱ ያለንን ፍቅር ከበፊቱ በተሻለ መንገድ ለመግለጽ በመጣርና በጸሎታችን ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት በማጠናከር ወደ እሱ እንቅረብ። በ2003 የዓመቱ ጥቅስ የሆነውን ያዕቆብ 4:​8ን በአእምሯችን ይዘን በእርግጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብን ስለመሆናችን ምንጊዜም ራሳችንን እንጠይቅ። “ወደ እናንተም ይቀርባል” ስለሚለው ዓረፍተ ነገርስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ‘ወደ እኛ የሚቀርበው’ እንዴት ነው? ይህስ ምን በረከቶች ያስገኝልናል? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

  • ‘ወደ እናንተ ይቀርባል’
    መጠበቂያ ግንብ—2002 | ታኅሣሥ 15
    • ‘ወደ እናንተ ይቀርባል’

      “[አምላክ] ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።”​—⁠ሥራ 17:​27

      1, 2. (ሀ) በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ስንመለከት ፈጣሪን በተመለከተ ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን? (ለ) ሰዎች በይሖዋ ዓይን ከፍ ተደርገው እንደሚታዩ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

      ጥርት ባለ ምሽት በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ተመልክተህ ተደምመህ ታውቃለህ? ለቁጥር የሚታክተው የከዋክብት ብዛትና ዳርቻ የሌለው የሕዋ ስፋት በአድናቆት እንድንዋጥ ያደርገናል። እጅግ ሰፊ በሆነው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ምድር ኢምንት ሆና ትታያለች። ታዲያ እንዲህ ሲባል ‘በምድር ሁሉ ላይ ልዑል’ የሆነው ፈጣሪ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የሰው ልጆችን ከቁብ አይቆጥርም ወይም ከሰዎች በጣም የራቀና ሊታወቅ የማይችል ነው ማለት ነውን?​—⁠መዝሙር 83:​18

      2 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ እንደማይመለከት ይገልጽልናል። እንዲያውም የአምላክ ቃል “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” በማለት አምላክን እንድንፈልገው ያበረታታናል። (ሥራ 17:​27፤ 1 ዜና መዋዕል 28:​9) በእርግጥም ወደ አምላክ ለመቅረብ አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰድን እርሱም ለጥረታችን ምላሽ ይሰጣል። ምን በማድረግ? የ2003 የዓመት ጥቅሳችን ‘ወደ እናንተ ይቀርባል’ በማለት የሚያስደስት መልስ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 4:​8) ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ከሚያዘንብላቸው አስደናቂ በረከቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።

      የይሖዋ ስጦታ

      3. ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሚሰጣቸው ስጦታ ምንድን ነው?

      3 በመጀመሪያ ደረጃ፣ የይሖዋ አገልጋዮች እሱ ለሕዝቡ ያዘጋጀውን ውድ ስጦታ አግኝተዋል። ይህ ሥርዓት የሚያቀርበው ማንኛውም ሥልጣን፣ ሀብትና እውቀት ይህን ስጦታ ሊያስገኝ አይችልም። ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ብቻ የሚሰጠው ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ ምንድን ነው? የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “ለማስተዋል ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና።” (ምሳሌ 2:3-6) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች “የአምላክን እውቀት” ማግኘት ይችላሉ እንደተባለ ልብ በል! ይህ ስጦታ ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውቀት ‘ከተቀበረ ገንዘብ’ ጋር ተመሳስሏል። ለምን?

      4, 5. ‘የአምላክ እውቀት ከተቀበረ ገንዘብ’ ጋር የተወዳደረው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

      4 አንደኛው ምክንያት የአምላክ እውቀት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ነው። ከሚያስገኛቸው ውድ በረከቶች መካከል አንዱ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ነው። (ዮሐንስ 17:​3) ይሁንና ይህ እውቀት በአሁኑ ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት ያስገኝልናል። ለምሳሌ ይህል የአምላክን ቃል በጥንቃቄ በማጥናታችን እንደሚከተሉት ላሉ አበይት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ችለናል:- የአምላክ ስም ማን ነው? (ዘጸአት 6:​3 የ1879 ትርጉም ) ሙታን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? (መክብብ 9:​5, 10) አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው? (ኢሳይያስ 45:​18) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት መምራት ችለናል። (ኢሳይያስ 30:​20, 21፤ 48:​17, 18) የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም እንዲሁም እውነተኛ ደስታና እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት እንድንመራ የሚረዳንን ትክክለኛ መመሪያ አግኝተናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክን ቃል ማጥናታችን የይሖዋን አስደናቂ ባሕርያት እንድናውቅና ወደ እሱ እንድንቀርብ አስችሎናል። ‘የአምላክን እውቀት’ በመቅሰም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ከመመሥረት የበለጠ ዋጋ ያለው ምን ነገር ሊኖር ይችላል?

      5 የአምላክ እውቀት ‘ከተቀበረ ገንዘብ’ ጋር ሊመሳሰል የቻለበት ሌላም ምክንያት አለ። እንደ አብዛኞቹ የተቀበሩ ሀብቶች ሁሉ ይህም እውቀት በዓለም ላይ እንደ ልብ የሚገኝ አይደለም። ከስድስት ቢልዮን የምድር ነዋሪዎች መካከል ‘የአምላክን እውቀት’ ያገኙት ቁጥራቸው ስድስት ሚልዮን የሚያክለው የይሖዋ አምላኪዎች ብቻ ናቸው። ይህም ከ1, 000 ሰዎች መካከል አንዱ እንደማለት ይሆናል። የአምላክ ቃል የያዘውን እውነት የሚረዱት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ምን ይሆናሉ? የሚለውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ብቻ እንመርምር። ነፍስ ሟች መሆኗንና ሙታን ምንም እንደማያውቁ ከቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ተረድተናል። (ሕዝቅኤል 18:​4) ሆኖም በዓለማችን ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በሰው ውስጥ የምትገኝ ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለች የሚል የሐሰት ትምህርት ያስተምራሉ። ይህ ትምህርት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖቶች መሠረታዊ ትምህርት ነው። የሂንዱ፣ የሲክ፣ የሺንቶ፣ የቡድሃ፣ የታኦ፣ የእስልምና፣ የአይሁድና የጃይኒዝም እምነቶችም ይህን ትምህርት በሰፊው ያስተምራሉ። በዚህ የሐሰት መሠረተ ትምህርት ብቻ እንኳ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተታልለዋል!

      6, 7. (ሀ) ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት የሚችሉት እነማን ብቻ ናቸው? (ለ) ይሖዋ ‘ጥበበኞችና አስተዋዮች’ የሆኑ ብዙ ሰዎች ያላገኙትን ማስተዋል በመስጠት እንደባረከን የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?

      6 ብዙ ሰዎች ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት ያልቻሉት ለምንድን ነው? አንድ ሰው የአምላክ ቃል የያዘውን ትርጉም ያለ እርሱ እርዳታ ሙሉ በሙሉ መረዳት ስለማይችል ነው። ይህ እውቀት ስጦታ መሆኑን አትዘንጋ። ይሖዋ ይህን ስጦታ የሚሰጠው ቃሉን በቅን ልቦና ተነሳስተው በትሕትና ለመመርመር ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች “እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች” ላይሆኑ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 1:​26) እንዲያውም ከመካከላቸው አብዛኞቹ በዓለም መሥፈርት ሲመዘኑ “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” ተደርገው ይታዩ ይሆናል። (ሥራ 4:​13) ሆኖም ዋናው ቁም ነገር ዓለማዊ ትምህርት ማግኘቱ አይደለም። ይሖዋ ‘የአምላክን እውቀት’ የሚሰጠን ልባችን ውስጥ በሚያያቸው ባሕርያት የተነሳ ነው።

      7 አንድ ምሳሌ ተመልከት። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ በርካታ ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፊ ትንታኔ የሚሰጡ በርካታ የጽሑፍ ሥራዎችን አዘጋጅተዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ የማመሳከሪያ ጽሑፎች የአንድን ነገር ታሪካዊ አመጣጥ፣ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላትን ፍቺዎችና ሌሎች ጉዳዮችን ያብራሩ ይሆናል። እነዚህ ምሁራን ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው መሆኑ በእርግጥ ‘የአምላክን እውቀት’ አስገኝቶላቸዋል? የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ መሆኑ በግልጽ ገብቷቸዋል? ይሖዋ አምላክ የሥላሴ ክፍል አለመሆኑን አውቀዋል? እኛ ግን እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት አለን። ለምን? ይሖዋ ‘ጥበበኞችና አስተዋዮች’ የሆኑ ብዙ ሰዎች ሊረዱት ያልቻሉትን መንፈሳዊ እውነት የመረዳት ችሎታ በመስጠት ስለባረከን ነው። (ማቴዎስ 11:​25) ይሖዋ ወደ እሱ የሚቀርቡትን ምንኛ ይባርካቸዋል!

      ‘ይሖዋ የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል’

      8, 9. (ሀ) ዳዊት ወደ ይሖዋ የሚቀርቡ ሰዎች የሚያገኙትን ተጨማሪ በረከት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች መለኮታዊ ጥበቃ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

      8 ወደ ይሖዋ የሚቀርቡ ሰዎች ሌላም በረከት ይኸውም መለኮታዊ ጥበቃ ያገኛሉ። ብዙ መከራና ችግር የተፈራረቀበት መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል።” (መዝሙር 145:18-20) አዎን፣ ይሖዋ ለሚወድዱት ሰዎች ቅርብ በመሆኑ እርዳታ ለማግኘት ለሚያቀርቡት ልመና አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል።

      9 መለኮታዊ ጥበቃ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ መኖር ከሚያስከትልባቸው ጫና በተጨማሪ የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት የሆነው የሰይጣን ዲያብሎስ ልዩ ዒላማ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ይህ መሠሪ ጠላት እኛን ‘ለመዋጥ’ ቆርጦ ተነስቷል። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ሰይጣን ስደትና ፈተና ያደርስብናል። በተጨማሪም የአእምሯችንንና የልባችንን ዝንባሌ ተመልክቶ በዚያ እኛን ለማጥመድ ይጥራል። እምነታችንን የማዳከምና በመንፈሳዊ ሁኔታ እኛን የመዋጥ ዓላማ አለው። (ራእይ 12:​12, 17) ከእንዲህ ዓይነት ኃይለኛ ጠላት ጋር ውጊያ የገጠምን በመሆኑ ‘ይሖዋ የሚወድዱትን ሁሉ እንደሚጠብቅ’ ማወቃችን አያጽናናንም?

      10. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚጠብቀው እንዴት ነው? (ለ) ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ጥበቃ የትኛው ነው? ለምንስ?

      10 ይሁንና ይሖዋ ሕዝቡን የሚጠብቀው እንዴት ነው? ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመጠበቅ ቃል ገብቶልናል ሲባል በዚህ ሥርዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይደርስብን ዋስትና ሰጥቶናል ወይም ለእኛ ሲል ተዓምር የመሥራት ግዴታ ውስጥ ገብቷል ማለት አይደለም። ይሁንና ይሖዋ ለሕዝቦቹ በቡድን ደረጃ አካላዊ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ደግሞም ዲያብሎስ እውነተኛ አምላኪዎችን ከምድር ገጽ ላይ ጠራርጎ እንዲያጠፋቸው አይፈቅድለትም! (2 ጴጥሮስ 2:​9) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል። ፈተናዎችን በጽናት እንድንወጣና ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና እንድንጠብቅ የሚያስችለንን ትጥቅ በመስጠት ያስታጥቀናል። ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ጥበቃ መንፈሳዊ ጥበቃ ነው። ለምን? ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና እስከተጠበቀ ድረስ ሌላው ቀርቶ ሞትም እንኳ ቢሆን ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም።​—⁠ማቴዎስ 10:​28

      11. ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ምን ዝግጅቶች አድርጓል?

      11 ይሖዋ ወደ እሱ የሚቀርቡ ሰዎች መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያገኙበትን በርካታ ዝግጅቶች አድርጓል። በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ማሸነፍ የሚቻልበትን ጥበብ አስፍሮልናል። (ያዕቆብ 1:​2-5) ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሚገኘውን ተግባራዊ ምክር በሥራ ማዋል በራሱ ጥበቃ ያስገኛል። በተጨማሪም ይሖዋ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን’ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:​13) ይህ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል በመሆኑ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ችግር ወይም ፈተና በተሳካ ሁኔታ እንድንወጣ ሊያስታጥቀን ይችላል። ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:​8) እነዚህ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው እርዳታ በሚሰጡበት ጊዜ የይሖዋን የመሰለ ከልብ የመነጨ የርኅራኄ ስሜት ለማንጸባረቅ ይጥራሉ።​—⁠ያዕቆብ 5:​14, 15

      12, 13. (ሀ) ይሖዋ በተገቢው ሰዓት መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብልን በምን አማካኝነት ነው? (ለ) ይሖዋ ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን በማሰብ ስላደረገልን ዝግጅቶች ምን ይሰማሃል?

      12 ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው በማቅረብ እኛን ለመጠበቅ የሚያስችል ሌላም ዝግጅት አድርጓል። (ማቴዎስ 24:​45) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ጨምሮ ታትመው በሚወጡ ጽሑፎች እንዲሁም በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች አማካኝነት ይሖዋ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ ያቀርብልናል። በጉባኤ ወይም በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ልብህን የነካውና ብርታትና ማጽናኛ ያገኘህበትን ትምህርት ያዳመጥክበት ጊዜ ትዝ ይልሃል? ከላይ ከተጠቀሱት መጽሔቶች በአንዱ ላይ የወጣ ርዕስ አንብበህ ለአንተ እንደተጻፈ ሆኖ የተሰማህ ጊዜ አለ?

      13 ሰይጣን በጣም ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው የማጥቂያ ዘዴዎች አንዱ ተስፋ መቁረጥ ሲሆን እኛም የዚህ ጥቃት ዒላማ ከመሆን ነጻ አይደለንም። ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ ከባድ የከንቱነት ስሜት ከተዋጥን ኃይላችን ሊሟጠጥና በቀላሉ ለጥቃት ልንጋለጥ እንደምንችል ያውቃል። (ምሳሌ 24:​10) ሰይጣን የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መሣሪያ አድርጎ ስለሚጠቀም እርዳታ ማግኘት ያስፈልገናል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ተስፋ መቁረጥን ማሸነፍ የሚቻልባቸውን ዘዴዎች የሚያብራሩ ርዕሶችን በተለያየ ጊዜ አውጥተዋል። አንዲት እህት ከእነዚህ ርዕሶች መካከል አንዱን በተመለከተ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ይህን ርዕስ በየቀኑ አንብቤዋለሁ ማለት እችላለሁ፤ ባነበብኩት ቁጥር እንባዬ ይፈስስ ነበር። የተስፋ መቁረጥ ስሜት በተሰማኝ ቁጥር እንዳነብበው ስል መጽሔቱን አልጋዬ አጠገብ አስቀምጨዋለሁ። እንደዚህ ያሉ ርዕሶች ሳነብብ በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንደገባሁ ያህል ሆኖ ይሰማኛል።”a ይሖዋ በወቅቱ ለሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ አመስጋኞች መሆን አይኖርብንም? ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን ሲል ያደረገልን ዝግጅቶች ለእኛ ቅርብ መሆኑንና በእቅፉ ውስጥ እንዳለን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መሆናቸውን አትዘንጋ።

      ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነውን አምላክ ማነጋገር

      14, 15. (ሀ) ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሰጣቸው ግሩም መብት ምንድን ነው? (ለ) በጸሎት ወደ ይሖዋ በነፃነት መቅረብ መቻላችን ግሩም መብት ነው የሚባለው ለምንድን ነው?

      14 ሰዎች ሥልጣናቸው እየጨመረ በሄደ መጠን በሥራቸው ያሉ ሰዎች እነርሱን አግኝተው ማነጋገር እንዲህ ቀላል እንደማይሆንላቸው አስተውለህ ታውቃለህ? ታዲያ ከዚህ አኳያ ሲታይ ስለ ይሖዋ አምላክስ ምን ማለት ይቻላል? ካለው የላቀ ቦታ አንጻር ተራ የሆኑ ሰዎች የሚያሰሙትን ጸሎት ከቁም ነገር ቆጥሮ ይሰማል ብሎ መጠበቅ ይቻላልን? እንዴታ! የጸሎት መብት ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሰጠው ሌላው በረከት ነው። ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ እንደ ልብ መቅረብ መቻል በእርግጥ ግሩም መብት ነው። (መዝሙር 65:​2) ለምን?

      15 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- የአንድ ትልቅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ በርካታ ኃላፊነቶች አሉት እንበል። የትኞቹን ጉዳዮች እሱ ራሱ በቀጥታ እንደሚያከናውናቸውና የትኞቹን ደግሞ ለሌሎች በኃላፊነት እንደሚሰጥ ይወስናል። በተመሳሳይ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የትኞቹን ጉዳዮች እርሱ ራሱ እንደሚያከናውናቸውና የትኞቹን ደግሞ ለሌሎች እንደሚሰጥ የመወሰን መብት አለው። ይሖዋ ለሚወድደው ልጁ ለኢየሱስ የሰጠውን የሥራ ድርሻ ተመልከት። ወልድ “ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን” ተሰጥቶታል። (ዮሐንስ 5:​27) መላእክት ‘ይገዙለታል።’ (1 ጴጥሮስ 3:​22) ኢየሱስ በምድር ላይ ለሚገኙት ደቀ መዛሙርቱ አመራር መስጠት እንዲችል የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ተሰጥቶታል። (ዮሐንስ 15:​26፤ 16:​7) ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ሊል ችሏል። (ማቴዎስ 28:​18) ሆኖም ይሖዋ የምናቀርበውን ጸሎት እሱ ራሱ መስማት ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ስም ለይሖዋ ብቻ ጸሎት ማቅረብ እንዳለብን የሚያዝዘን ለዚህ ነው።​—⁠መዝሙር 69:​13፤ ዮሐንስ 14:​6, 13

      16. ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      16 ይሖዋ በእርግጥ ጸሎታችንን ይሰማል? ለእኛ የማያስብ ቢሆን ኖሮ ‘በጸሎት እንድንጸና’ ወይም ሸክማችንንና ጭንቀታችንን በእሱ ላይ እንድንጥል አያበረታታንም ነበር። (ሮሜ 12:​12፤ መዝሙር 55:​22፤ 1 ጴጥሮስ 5:​7) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ ታማኝ አገልጋዮች ይሖዋ ጸሎታቸውን እንደሚሰማላቸው ፍጹም ትምክህት ነበራቸው። (1 ዮሐንስ 5:​14) በመሆኑም መዝሙራዊው ዳዊት ‘[ይሖዋ] ቃሌን ይሰማኛል’ ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 55:​17) እኛም ብንሆን ይሖዋ ቅርብ መሆኑንና ሐሳባችንንና ጭንቀታችንን በሙሉ ለመስማት ዝግጁ መሆኑን እንድናምን የሚያስችለን አጥጋቢ ምክንያት አለን።

      ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ ይከፍላል

      17, 18. (ሀ) ይሖዋ ማስተዋል ያላቸው ፍጡራኑ የሚያከናውኑትን የታማኝነት አገልግሎት እንዴት ይመለከተዋል? (ለ) በርኅራኄ ስሜት ተነሳስተን የምናደርገው ነገር ከይሖዋ የተሰወረ አለመሆኑን ምሳሌ 19:​17 የሚያሳየው እንዴት ነው?

      17 ሰዎች የሚፈለግባቸውን ነገር ቢያደርጉም ባያደርጉም በይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ አድናቆቱን መግለጽ የሚወድድ አምላክ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራኑ በታማኝነት የሚያከናውኑትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (መዝሙር 147:​11) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ ይከፍላቸዋል። ወደ ይሖዋ የሚቀርቡ ሰዎች ከሚያገኟቸው በረከቶች መካከል አንደኛው ይህ ነው።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

      18 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያከናውኑትን ሥራ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት በግልጽ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፣ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” የሚል እናነብባለን። (ምሳሌ 19:17) ይሖዋ ለድሆች የሚያሳየው ርኅራኄ በሙሴ ሕግ ላይ ተንጸባርቋል። (ዘሌዋውያን 14:​21፤ 19:​15) ይሖዋ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በመርዳት የእሱን የመሰለ ርኅራኄ ስናንጸባርቅ ምን ይሰማዋል? ውለታ ይመለስልኛል ብለን ሳንጠብቅ ለተቸገረ ሰው የሚያስፈልገውን በምንሰጥበት ጊዜ ይሖዋ ለእሱ እንዳበደርነው አድርጎ ይቆጥረዋል። ይሖዋ ሞገስ በማሳየትና በረከቱን በማዝነብ ብድሩን መልሶ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 10:​22፤ ማቴዎስ 6:​3, 4፤ ሉቃስ 14:​12-14) አዎን፣ ችግር ላይ ለወደቀ የእምነት ባልንጀራችን ርኅራኄ ስናሳይ አድራጎታችን የይሖዋን ልብ ይነካል። በርኅራኄ ስሜት የምናደርገውን ነገር ሰማያዊ አባታችን እንደሚያየው ማወቃችን ምንኛ ያስደስታል!​—⁠ማቴዎስ 5:​7

      19. (ሀ) ይሖዋ በስብከቱና ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ የምናከናውነውን አገልግሎት እንደሚያደንቅ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ መንግሥቱን በመደገፍ ለሚደረግ አገልግሎት ወሮታ የሚከፍለው እንዴት ነው?

      19 ይሖዋ በተለይ ለመንግሥቱ ብለን የምናደርገውን ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ወደ እሱ ስንቀርብ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ሃብታችንን የመንግሥቱን ስብከትና ደቀ መዝሙር የማድረጉን ሥራ በተሟላ መንገድ ለመደገፍ ልናውለው እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 28:​19, 20) አንዳንድ ጊዜ የምናበረክተው ድርሻ በጣም አናሳ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ፍጹም ያልሆነው ልባችን ይሖዋ በምናደርገው ጥረት ይደሰት እንደሆነና እንዳልሆነ ጥርጣሬ ሊገባው ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:​19, 20) ሆኖም ይሖዋ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን እንኳ ከፍቅር የመነጨ ማንኛውንም ስጦታ በአድናቆት ይቀበላል። (ማርቆስ 12:​41-44) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 6:10) በእርግጥም ይሖዋ፣ መጠኑ አነስተኛም ቢሆን መንግሥቱን ለመደገፍ የሚደረገውን አገልግሎት የማይዘነጋ ከመሆኑም በላይ ወሮታ የሚከፍል አምላክ ነው። አሁን ከምናገኘው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት በተጨማሪ በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘውን አስደሳች ሕይወት በጉጉት እንጠባበቃለን። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ሁሉ እጁን ከፍቶ ፍላጎታቸውን ያረካላቸዋል!​—⁠መዝሙር 145:​16፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

      20. በያዝነው ዓመት የትኛውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? ይህስ ምን ያስገኝልናል?

      20 የ2003ን የዓመት ጥቅስ በአእምሯችን በመያዝ ወደ ሰማያዊ አባታችን ለመቅረብ የማያቋርጥ ጥረት እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ምላሽ እንደሚሰጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ደግሞም ይሖዋ ‘አይዋሽም።’ (ቲቶ 1:​2) ወደ ይሖዋ ከቀረብን እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። (ያዕቆብ 4:​8) ይህስ ምን ያስገኝልናል? በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት ወደፊት ደግሞ ለዘላለም ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ የመኖር አጋጣሚ ያስገኝልናል!

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a በግንቦት 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28-31 ላይ ለወጣው “ይሖዋ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” ለሚለው ርዕስ የተላከ የአድናቆት መግለጫ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ