“ያላያችሁትም እንኳ ቢሆን ትወዱታላችሁ”
“ያላያችሁትም እንኳ ቢሆን ትወዱታላችሁ፤ ያላያችሁት ቢሆንም በእርሱ አምናችሁ . . . ደስ ይላችኋል።”— 1 ጴጥሮስ 1:8 የ1980 ትርጉም
1. በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ኢየሱስን አይቶ የሚያውቅ ሰው ባይኖርም እንኳ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሰዎች ለእሱ ያላቸውን አምልኮታዊ ፍቅር ለማሳየት የሚጥሩት እንዴት ነው?
በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን አይቶ የሚያውቅ ሰው በምድር ላይ የለም። ሆኖም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስን እንደሚወዱት ይናገራሉ። በየዓመቱ ጥር 9 ቀን ፊሊፒንስ ውስጥ በማኒላ ከተማ ሰው የሚያክልና መስቀል የተሸከመ አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐውልት በጎዳናዎች ላይ እየተጎተተ ያልፋል፤ ይህ በአገሪቱ ውስጥ ብዙ ተከታዮች ያሉት ሃይማኖት የሚያካሂደው እጅግ ታላቅና አስደናቂ የሆነ ሥርዓተ አምልኮ እንደሆነ ይነገርለታል። በደስታ ስሜት የሰከረው ሕዝብ እርስ በርሱ ይጋፋል፣ ይገፈታተራል፤ እንዲያውም አንዱ በአንዱ ላይ እየወጣ እንደምንም ብሎ ምስሉን ለመንካት ይሞክራል። ብዙዎቹ በዚህ ወቅት የሚገኙበት ዋናው ምክንያት ይህ ፈንጠዝያ ያለበት ሥነ ሥርዓት ስለሚስባቸው ነው። ሆኖም አንዳንዶቹ በዚህ ሥርዓት ላይ የሚገኙት ለኢየሱስ ባላቸው ልባዊ ፍቅር የተነሣ እንደሆነ አያጠራጥርም። ይህን ስሜታቸውን ለመግለጽ የክርስቶስን ምስል የያዘ መስቀል ያደርጉ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የጣዖት አምልኮ እውነተኛ አምልኮ ተደርጎ ሊታይ ይችላልን?
2, 3. (ሀ) ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል እርሱን ያዩትና የተናገረውን የሰሙት እነማን ናቸው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስን አይተውት ባያውቁም እንኳ የወደዱትና በእሱ ያመኑት ሌሎች ሰዎች እነማን ነበሩ?
2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮማ ግዛቶች በነበሩት በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ በፍርጊያና በገሊላ ይኖሩ የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን በዓይናቸው አይተውታል፤ ሲናገርም ሰምተውታል። ስለ አምላክ መንግሥት በጣም አስደሳች የሆኑ እውነቶችን ሲናገር ሰምተዋል። የፈጸማቸውን ተአምራት በዓይናቸው አይተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እርሱ “ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ በእርግጠኝነት አምነው በመቀበል ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ሆነዋል። (ማቴዎስ 16:16) ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈላቸው ሰዎች ከእነዚህ መካከል አልነበሩም።
3 ጴጥሮስ የጻፈላቸው ሰዎች ይኖሩ የነበረው ጳንጦስ፣ ገላትያ፣ ቀጰዶቅያ፣ እስያና ቢታንያ በሚባሉት የሮማ ግዛቶች ውስጥ ነበር፤ ሁሉም በአሁኑ ጊዜ ቱርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ናቸው። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጻፈላቸው:- “ያላያችሁትም እንኳ ቢሆን ትወዱታላችሁ፤ ያላያችሁት ቢሆንም በእርሱ አምናችሁ በቃላት ሊገለጥ በማይቻልና በከበረ ደስታ ደስ ይላችኋል።” (1 ጴጥሮስ 1:1, 8 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውደድና በእርሱ ለማመን የሚያበቃ እውቀት ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው?
4, 5. ኢየሱስን አይተውት የማያውቁት ሰዎች እንዲወዱትና እንዲያምኑበት ያደረጋቸውን እውቀት ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው?
4 አንዳንዶቹ ሐዋርያው ጴጥሮስ በ33 እዘአ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ተገኝተው ለነበሩት ብዙ ሰዎች በመሰከረበት ጊዜ በኢየሩሳሌም እንደነበሩ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ከበዓሉ በኋላ ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ከሐዋርያት ተጨማሪ ትምህርት ለማግኘት በኢየሩሳሌም ቆይተዋል። (ሥራ 2:9, 41, 42፤ ከ1 ጴጥሮስ 1:1 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ባደረጋቸው ሚስዮናዊ ጉዞዎች ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ በስሙ የተጻፈውን የመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ደብዳቤ በላከበት አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች መካከልም በቅንዓት አገልግሏል።— ሥራ 18:23፤ 19:10፤ ገላትያ 1:1, 2
5 ኢየሱስን ፈጽሞ አይተውት የማያውቁት እነዚህ ሰዎች ይህን ያህል በኢየሱስ የተማረኩት ለምን ነበር? በዘመናችን በምድር ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጣም ሊወዱት የቻሉት ለምንድን ነው?
የሰሟቸው ነገሮች
6. (ሀ) ጴጥሮስ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ስለ ኢየሱስ ሲመሰክር ብትሰማ ኖሮ ምን ትምህርት ልታገኝ ትችል ነበር? (ለ) ጴጥሮስ የሰጠው ምስክርነት በቦታው ተገኝተው የነበሩትን 3,000 የሚያክሉ ሰዎች የነካው እንዴት ነው?
6 ጴጥሮስ በ33 እዘአ በተከበረው በዓል ላይ ተሰብስበው ለነበሩት ብዙ ሰዎች ንግግር በሰጠበት ጊዜ በኢየሩሳሌም ብትኖር ኖሮ ስለ ኢየሱስ ምን ትማር ነበር? ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ያላንዳች ጥርጥር በአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያሳዩ ነበሩ። ኢየሱስ ኃጢአተኛ ሰዎች ቢገድሉትም እንኳ በመቃብር ውስጥ እንዳልሆነና ከሞት እንደተነሣ ከዚያም ከፍ ከፍ ተደርጎ በሰማይ በአምላክ ቀኝ እንደተቀመጠ ትማር ነበር። ኢየሱስ በእርግጥም ክርስቶስ ማለትም ነቢያት አስቀድመው የጻፉለት መሲሕ እንደሆነ ትማር ነበር። የኢየሱስ ተከታዮች አምላክ በልጁ በኩል እያከናወናቸው ስላሉት አስደናቂ ሥራዎች ከብዙ ብሔራት ለመጡት ሰዎች ወዲያውኑ መመስከር እንዲችሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መንፈስ ቅዱስ እንደፈሰሰባቸው ትገነዘብ ነበር። በዚያ ወቅት የጴጥሮስን ንግግር የሰሙ ብዙ ሰዎች ልባቸው በጥልቅ ተነክቶ ነበር፤ 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችም ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ሆነው ተጠምቀዋል። (ሥራ 2:14-42) አንተ በዚያ ቦታ ብትኖር ኖሮ እንዲህ ዓይነት ቆራጥ እርምጃ ትወስድ ነበርን?
7. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በአንጾኪያ ሲሰብክ በቦታው ብትኖር ኖሮ ምን ልትማር ትችል ነበር? (ለ) በሥፍራው ከነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ አማኞች የሆኑትና የምሥራቹን ለሌሎች ማካፈል የጀመሩት ለምንድን ነው?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ የሮማ ግዛት በነበረችው በገላትያ ውስጥ በምትገኘው በአንጾኪያ ሲያስተምር በቦታው ከተገኙት ሰዎች አንዱ ብትሆን ኖሮ ስለ ኢየሱስ ሌላ ምን ነገር ትማር ነበር? ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ገዥዎች የተፈረደበት የሞት ፍርድ አስቀድሞ በነቢያት ተተንብዮ እንደነበረ ጳውሎስ ሲገልጽ ትሰማ ነበር። በተጨማሪም የዓይን ምሥክሮችን በማስረጃነት በመጥቀስ ኢየሱስ ከሞት የተነሣ መሆኑን ሲገልጽ ትሰማ ነበር። ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት የአምላክ ልጅ መሆኑን እንዳረጋገጠ በመግለጽ ጳውሎስ የሰጠውን ማብራሪያ ስትሰማ በእርግጥም ትደነቅ ነበር። በተጨማሪም በኢየሱስ ላይ በማመን የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ እንደሚችል ስትማር ልብህ በአመስጋኝነት ስሜት አይሞላም ነበርን? (ሥራ 13:16-41, 46, 47፤ ሮሜ 1:4) በአንጾኪያ የነበሩት አንዳንድ ሰዎች የሰሙት ነገር የያዘውን ትልቅ ትርጉም በመገንዘብ ምንም እንኳ የወሰዱት እርምጃ ከባድ ስደት ሊያስከትልባቸው ቢችልም የምሥራቹን ለሌሎች በትጋት በማካፈል ደቀ መዛሙርት ሆኑ።— ሥራ 13:42, 43, 48-52፤ 14:1-7, 21-23
8. ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ የጻፈው ደብዳቤ ሲደርሳቸው አንተ በስብሰባው ላይ ተገኝተህ ቢሆን ኖሮ ምን ትምህርት ልታገኝ ትችል ነበር?
8 ጳውሎስ የሮማ ግዛት በነበረችው በእስያ በምትገኘው የኤፌሶን ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ደብዳቤ በደረሳቸው ጊዜ ከኤፌሶን ክርስቲያን ጉባኤ ጋር ትሰበሰብ የነበረ ቢሆን ኖሮስ? ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስላለው ሚና ምን ልትማር ትችል ነበር? ጳውሎስ በዚያ ደብዳቤ ላይ በሰማይና በምድር ያሉት ነገሮች በሙሉ በክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር እንደሚታረቁ፣ አምላክ በክርስቶስ በኩል ያዘጋጀው ስጦታ ለሁሉም ብሔራት ሕዝቦች እንደተዘረጋ፣ በኃጢአታቸው ምክንያት በአምላክ ፊት ሙታን የነበሩ ግለሰቦች በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ሕያው እንዲሆኑ መደረጉንና በዚህ ዝግጅት አማካኝነትም ሰዎች እንደገና የአምላክ ውድ ልጆች መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ እንደተከፈተ ገልጿል።— ኤፌሶን 1:1, 5-10፤ 2:4, 5, 11-13
9. (ሀ) ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ የያዘውን መሠረታዊ ትርጉም አንተ በግልህ መረዳት አለመረዳትህን ማወቅ እንድትችል ሊረዳህ የሚችለው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ የጠቀሳቸው በሮማ ግዛቶች ውስጥ የነበሩ ወንድሞች ስለ ኢየሱስ የተማሩት ነገር የነካቸው እንዴት ነው?
9 ለዚህ ሁሉ ነገር ያለህ አድናቆት ለአምላክ ልጅ ያለህን ፍቅር ያጠነክርልህ ነበርን? ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 4 እስከ 6 ላይ በሰጠው ማበረታቻ መሠረት ይህ ፍቅር በዕለታዊ ኑሮህ ላይ ለውጥ ያመጣ ነበርን? እንዲህ ዓይነቱ አድናቆት በኑሮህ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች በጥንቃቄ እንድትመረምር ይገፋፋህ ነበርን? የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር መሆን እንዲችል ለአምላክ ባለህ ፍቅርና ለልጁ ባለህ የአመስጋኝነት ስሜት ተገፋፍተህ አስፈላጊውን ሁሉ ማስተካከያ ታደርግ ነበርን? (ኤፌሶን 5:15-17) ሐዋርያው ጴጥሮስ በእስያ፣ በገላትያና በሌሎች የሮማ ግዛቶች የሚኖሩ ክርስቲያኖች እየተማሩት ባለው ነገር እንዴት እንደተነኩ በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “ኢየሱስ ክርስቶስን ያላያችሁትም እንኳ ቢሆን ትወዱታላችሁ፤ . . . በእርሱ አምናችሁ በቃላት ሊገለጥ በማይቻልና በከበረ ደስታ ደስ ይላችኋል።”— 1 ጴጥሮስ 1:8 የ1980 ትርጉም
10. (ሀ) የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስን እንዲወዱት ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ ምን እንደሆነ አያጠራጥርም? (ለ) እኛም ከዚህ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
10 ጴጥሮስ የጻፈላቸው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለአምላክ ልጅ የነበራቸውን ፍቅር ያጠነከረላቸው ሌላም ነገር እንደነበረ አያጠራጥርም። ይህ ነገር ምንድን ነው? ጴጥሮስ የመጀመሪያውን ደብዳቤ በጻፈበት ጊዜ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ወንጌሎች ማለትም የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌሎች በስፋት እየተሰራጩ ነበር። ኢየሱስን አይተውት የማያውቁት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን የወንጌል ታሪኮች ማንበብ ይችላሉ። እኛም ማንበብ እንችላለን። ወንጌሎቹ በመላ ምት ላይ የተመሠረቱ ታሪኮች አይደሉም፤ አንድ ከፍተኛ እምነት የሚጣልበት ታሪክ የሚያሟላቸውን ባሕርያት በሙሉ ያሟሉ ናቸው። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት በእነዚህ ዘገባዎች ውስጥ ለአምላክ ልጅ ያለንን ፍቅር የሚያጠናክሩ ብዙ ነገሮች እናገኛለን።
ኢየሱስ ያሳየው ባሕርይ
11, 12. ኢየሱስ እንድትወደው የሚያደርግህ ምን ባህርይ ለሌሎች ሰዎች አሳይቷል?
11 ስለ ኢየሱስ ሕይወት በተጻፈው ዘገባ ላይ ኢየሱስ ከሌሎች ሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበረ እንማራለን። ኢየሱስ ከሞተ ከ1,960 ዓመታት በላይ ያለፉ ቢሆንም ያሳየው ባሕርይ በአሁኑ ጊዜ ያሉትንም ሰዎች ልብ እንኳን ሳይቀር ነክቷል። በሕይወት ያለ ሰው ሁሉ ኃጢአት ባስከተለው መዘዝ በመንገላታት ላይ ይገኛል። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የፍትሕ መጓደል ደርሶባቸዋል፣ ከበሽታ ጋር ይታገላሉ፣ አሊያም ደግሞ በሌሎች ምክንያቶች የተነሣ ስሜታቸው ክፉኛ ተጎድቷል። ኢየሱስ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች በሙሉ እንደሚከተለው ብሏል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”— ማቴዎስ 11:28-30
12 ኢየሱስ ለድሆች፣ ለተራቡትና ሐዘን ላይ ለወደቁት ሰዎች የጠለቀ የአሳቢነት ስሜት አሳይቷል። አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ መግቧል። (ሉቃስ 9:12-17) በባርነት ቀንበር ሥር ካስገቧቸው ወጎች ነፃ አውጥቷቸዋል። አምላክ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆናን ለማስወገድ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ ያላቸውንም እምነት አጠንክሮላቸዋል። ኢየሱስ ከፍተኛ ጭቆና የደረሰባቸውን ሰዎች ቅስም አልሰበረም። በአሳቢነትና በፍቅር መንፈስ ቅን ሰዎችን በዘዴ አነቃቅቷል። ታጥፎ እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆና ሊጠፋ እንደተቃረበ የሚጤስ የጥዋፍ ክር ሆነው የነበሩትን ሰዎች መንፈስ አድሷል። እስከ ዛሬ ድረስ ስሙ ፈጽሞ አይተውት በማያውቁት ሰዎች ልብ ውስጥ እንኳ ሳይቀር የተስፋ ስሜት ያሳድራል።— ማቴዎስ 12:15-21፤ 15:3-10
13. ኢየሱስ ለኃጢአተኞች ያሳየው ባሕርይ ሰዎችን የማረከው ለምንድን ነው?
13 ኢየሱስ ኃጢአትን አልደገፈም፤ ሆኖም በሕይወታቸው ውስጥ ስሕተት የፈጸሙና በኋላ ግን ንስሐ ገብተው እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ የመጡ ሰዎችን ስሜት ተረድቶላቸዋል። (ሉቃስ 7:36-50) በመንፈሳዊ ለመርዳት የሚያስችል አጋጣሚ የሚከፍትለት ሆኖ ከተሰማው በማኅበረሰቡ ከተናቁ ሰዎች ጋር አብሮ ይመገብ ነበር። (ማቴዎስ 9:9-13) ኢየሱስ ያሳየው ባሕርይ በተመሳሳይ ሁኔታዎች ሥር የሚገኙና ኢየሱስን ፈጽሞ አይተውት የማያውቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እሱን ለማወቅ ጥረት እንዲያደርጉና በእሱ እንዲያምኑ ገፋፍቷቸዋል።
14. ኢየሱስ የታመሙ፣ አካለ ስንኩል የሆኑ ወይም የቅርብ ዘመድ የሞተባቸውን ሰዎች የረዳበትን መንገድ በተመለከተ አንተን የማረከህ ነገር ምንድን ነው?
14 ኢየሱስ ለታመሙ ወይም አካለ ስንኩል ለሆኑ ሰዎች ያደረገው ነገር ወዳጃዊ ስሜት ያለውና ሩኅሩኅ እንዲሁም እፎይታ ሊያመጣላቸው የሚችል መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። በመሆኑም በሥጋ ደዌ ክፉኛ የተጎዳ አንድ በሽተኛ ወደ እሱ ቀርቦ እንዲረዳው ሲለምነው ኢየሱስ ሰውዬውን ማየት ተጸይፎ ወደ ኋላ አላፈገፈገም። በተጨማሪም በጣም እንዳዘነለት ገልጾ በሽታው በጣም ሥር ስለ ሰደደ ምንም ነገር ሊደረግልህ አይችልም አላለውም። ሰውዬው “ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ ያላንዳች ማመንታት የሥጋ ደዌ የያዘውን ሰው ዳሰሰውና “እወዳለሁ፣ ንጻ” አለው። (ማቴዎስ 8:2, 3) በሌላ ወቅት ደግሞ አንዲት ሴት በምሥጢር የልብሱን ጫፍ በመንካት ለመፈወስ ፈልጋ ነበር። ኢየሱስ ያነጋገራት በደግነትና በሚያጽናና ሁኔታ ነበር። (ሉቃስ 8:43-48) በተጨማሪም ወደ ቀብር የሚሄዱ ሰዎች ባጋጠሙት ጊዜ አንድ ልጅዋ ሞቶባት ሐዘን ላይ ለወደቀችው መበለት አዘነላት። ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ኃይል ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለራሱ ምግብ ለማግኘት ሊጠቀምበት ያልፈለገ ቢሆንም የሞተውን ሰው አስነስቶ ለእናቱ ለመስጠት ይህን ኃይል በነፃ ተጠቅሞበታል።— ሉቃስ 4:2-4፤ 7:11-16
15. የኢየሱስን ታሪክ የሚገልጹትን ዘገባዎች ማንበብና በእነርሱ ላይ ማሰላሰል በአንተ ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?
15 እነዚህን ታሪኮች ስናነብና ኢየሱስ ባሳየው ባሕርይ ላይ ስናሰላስል ለዘላለም መኖር እንድንችል ሲል ሰብዓዊ ሕይወቱን ለሠዋው ለዚህ ሰው ያለን ፍቅር ይበልጥ ይጠነክራል። አይተነው ባናውቅም እንኳ ወደ እሱ ለመቅረብ እንገፋፋለን፤ ዱካውንም ለመከተል እንፈልጋለን።— 1 ጴጥሮስ 2:21
በትሕትና አምላክን መመኪያው አድርጓል
16. ኢየሱስ ከሁሉ በፊት ትኩረት ያደረገው በማን ላይ ነው? እኛስ ምን እንድናደርግ አበረታቶናል?
16 ኢየሱስ ከሁሉም በላይ የእሱም ሆነ የእኛ ትኩረት በሰማያዊ አባቱ በይሖዋ አምላክ ላይ እንዲያርፍ አድርጓል። በሕጉ ውስጥ ከሁሉ የላቀው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲያመለክት እንዲህ ብሏል:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።” (ማቴዎስ 22:36, 37) ደቀ መዛሙርቱን “በእግዚአብሔር እመኑ” ብሎ አጥብቆ መክሯቸዋል። (ማርቆስ 11:22) እምነታቸው ከባድ ፈተና ገጥሞት በነበረ ጊዜ “ትጉና ጸልዩ” በማለት አሳስቧቸዋል።— ማቴዎስ 26:41
17, 18. (ሀ) ኢየሱስ በትህትና በአባቱ ላይ መመካቱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እርሱ ያደረገው ነገር ለእኛ እጅግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
17 በዚህ ረገድ ኢየሱስ ራሱ ምሳሌ ሆኗል። ጸሎት በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። (ማቴዎስ 14:23፤ ሉቃስ 9:28፤ 18:1) ኢየሱስ ሐዋርያቱን የሚመርጥበት ጊዜ ሲደርስ ምንም እንኳ ቀደም ሲል በሰማይ ያሉት መላእክት ሁሉ በእሱ ቁጥጥር ሥር የነበሩ ቢሆንም በራሱ የማመዛዘን ችሎታ አልተመካም። በትሕትና አንድ ሙሉ ሌሊት ወደ አባቱ ጸልዮአል። (ሉቃስ 6:12, 13) ኢየሱስ የሚያዝበትና በአሠቃቂ ሁኔታ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ የአባቱን እርዳታ ለማግኘት አጥብቆ ጸልዮአል። ሰይጣንን በሚገባ ስለማውቀው ይህ ክፉ መንፈስ ምንም ዓይነት ዘዴ ቢጠቀም በቀላሉ ልቋቋመው እችላለሁ ብሎ አላሰበም። ኢየሱስ በፈተናው አለመውደቁ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ተልዕኮውን መወጣት ባይችል ኖሮ በአባቱ ላይ እንዴት ያለ ነቀፋ ያስከትል ነበር! የሰው ዘሮች የሕይወት ተስፋቸው የተመካው ኢየሱስ በሚያቀርበው መሥዋዕት ላይ ስለነበር ይህ ሁኔታ ትልቅ ኪሳራ ያስከትልባቸው ነበር!
18 ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በኢየሩሳሌም በአንድ ደርብ ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ እያለ በተደጋጋሚ ጸልዮአል፤ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ በነበረ ጊዜ ደግሞ ከዚያ ይበልጥ ውስጣዊ ስሜቱ የተንጸባረቀበት ጸሎት አቅርቧል። (ማቴዎስ 26:36-44፤ ዮሐንስ 17:1-26፤ ዕብራውያን 5:7) በመከራው እንጨት ላይ ተሰቅሎ እየተሰቃየ በነበረበት ወቅት ሲያሾፉበት የነበሩትን ሰዎች አልሰደባቸውም። ከዚህ ይልቅ ባለማወቅ መጥፎ ድርጊት እየፈጸሙ ለነበሩት ሰዎች “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል ጸልዮላቸዋል። (ሉቃስ 23:34) “በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ” በመስጠት ሐሳቡ በአባቱ ላይ እንዳተኮረ እንዲቀጥል አድርጓል። በመከራው እንጨት ላይ ሆኖ በመጨረሻ ያሰማው ቃልም ለአባቱ ያቀረበው ጸሎት ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:23፤ ሉቃስ 23:46) ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ በመመካት አባቱ የሰጠውን ሥራ በታማኝነት በመፈጸሙ ምንኛ እናመሰግነዋለን! ኢየሱስ ክርስቶስን አይተነው ባናውቅም እንኳ በፈጸመው ሥራ በጣም እንወደዋለን!
ለእሱ ያለንን ፍቅር መግለጽ
19. ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ስንገልጽ ጨርሶ ልናስወግዳቸው የሚገቡ ተገቢ ያልሆኑ ልማዶች ምንድን ናቸው?
19 ለእሱ ያለን ፍቅር በቃላት ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የሚወደው አባቱ ምስሎችን ሠርቶ ማምለክን የሚከለክል በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ምስል በአንገታችን ማንጠልጠላችን ወይም ምስሉን ተሸክመን በጎዳናዎች ላይ መሄዳችን ለኢየሱስ ክብር እንደማያመጣለት ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘጸአት 20:4, 5፤ ዮሐንስ 4:24) በተቀሩት የሳምንቱ ቀናት ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር ተስማምተን የማንመላለስ ከሆነ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መገኘታችን ለኢየሱስ ምንም ክብር አያመጣለትም፤ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ በሳምንት ውስጥ ብዙ ጊዜ የምንገኝ ቢሆንም እንኳ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ኢየሱስ “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል” ብሏል።— ዮሐንስ 14:21, 23፤ 15:10
20. ኢየሱስን ከልባችን የምንወደው መሆን አለመሆናችንን የሚያሳዩ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
20 ኢየሱስ ምን ትእዛዞችን ሰጥቶናል? ከሁሉም በላይ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ብቻ እንድናመልክ አዞናል። (ማቴዎስ 4:10፤ ዮሐንስ 17:3) በተጨማሪም ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ በሚጫወተው ሚና የተነሳ የአምላክ ልጅ እንደሆነ አድርገን ልናምንበት እንደሚገባና ይህንንም ከክፉ ሥራዎች በመራቅና በብርሃን በመመላለስ ማሳየት እንዳለብን ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16-21) ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን እንድናስቀድም መክሮናል። (ማቴዎስ 6:31-33) እሱ እንደወደደን እኛም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ አዞናል። (ዮሐንስ 13:34፤ 1 ጴጥሮስ 1:22) እሱ ለአምላክ ዓላማ ምሥክር ሆኖ እንዳገለገለ ሁሉ እኛም ለዚህ ዓላማ ምሥክሮች የመሆን ተልዕኮ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ራእይ 3:14) ምንም እንኳ ኢየሱስን አይተውት ባያውቁም በአሁኑ ጊዜ አምስት ሚልዮን የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ለእሱ ያላቸው እውነተኛ ፍቅር እነዚህን ትእዛዛት እንዲጠብቁ ገፋፍቷቸዋል። በግለሰብ ደረጃ ኢየሱስን አይተውት የማያውቁ መሆኑ ታዛዥ ለመሆን ያላቸውን ቁርጥ አቋም በምንም መንገድ አያላላውም። ጌታቸው ሐዋርያው ቶማስን ምን እንዳለው ያስታውሳሉ:- “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው።”— ዮሐንስ 20:29
21. በዚህ ዓመት መጋቢት 23 እሁድ ዕለት በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ በመገኘት ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
21 አምላክ ለሰው ልጆች ያሳየውን ከሁሉ የላቀ የፍቅር መግለጫ ለማስታወስና የታማኝ ልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በዓለም ዙሪያ መጋቢት 23, 1997 እሁድ ዕለት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ከሚሰበሰቡት ሰዎች አንዱ እንደምትሆን ተስፋ እናደርጋለን። በዚያ ወቅት የሚነገረውም ሆነ የሚደረገው ነገር ለይሖዋና ለልጁ ያለህን ፍቅር ሊያጠነክርልህና ወዲያውም የአምላክን ትእዛዛት ለመጠበቅ ያለህን ፍላጎት ሊጨምርልህ ይገባል።— 1 ዮሐንስ 5:3
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የአንደኛ ጴጥሮስ መጽሐፍ የተጻፈላቸው ሰዎች ኢየሱስን ሊያውቁትና ሊወዱት የቻሉት እንዴት ነው?
◻ የጥንት ክርስቲያኖች ከሰሟቸው ነገሮች መካከል ስሜትህን የማረኩት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ ከኢየሱስ ባሕርያት መካከል ለእሱ ያለህን ፍቅር ያጠነከረልህን የትኛውን ባሕርይ ልትጠቅስ ትችላለህ?
◻ ኢየሱስ በትህትና በአምላክ ላይ መመካቱ ለእኛ እጅግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ ያሳየው ባሕርይ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ያደርገናል