የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ገጽ 66-ገጽ 70
  • እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ተማር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ተማር
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጠያቂውን አመለካከት ተረዳ
  • ጠያቂው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት
  • “ሁልጊዜ በደግነት ይሁን”
  • የግል ውሳኔዎችና ለሕሊና የተተዉ ጉዳዮች
  • በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መልስ መስጠት
  • መልሶችህን ማሻሻል
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ጥሩ መልስ መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ (2016)
  • መልስ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
  • በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ ተበረታቱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ገጽ 66-ገጽ 70

እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ተማር

አንዳንድ ጥያቄዎች ጫፉ ብቻ ከውኃ በላይ ብቅ ብሎ እንደሚታይ የበረዶ ግግር ናቸው። ግዙፍ የሆነው የበረዶው አካል የሚገኘው ከውኃ በታች ነው። በተመሳሳይም በግልጽ ከቀረበው ጥያቄ ይልቅ ክብደት የሚሰጠው ጥያቄው እንዲነሣ ምክንያት የሆነው ነገር ነው።

እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ የምታውቅ ከሆነ ጠያቂው መልሱን ለማግኘት ቢጓጓ እንኳ ጉዳዩን እስከ ምን ድረስ እንደምታብራራለትና ከምን አቅጣጫ እንደምታስረዳው ማስተዋል አይቸግርህም። (ዮሐ. 16:​12) አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው የማይመለከተውን ወይም ምንም የማይጠቅመውን መረጃ ሊጠይቅ እንደሚችል ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ካደረገው ውይይት መረዳት እንችላለን።​—⁠ሥራ 1:​6, 7

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በደግነት ይሁን’ በማለት ይመክረናል። (ቆላ. 4:​6) በመሆኑም መልስ ከመስጠታችን በፊት ምን እንደምንናገር ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምንናገር ጭምር ማሰብ ይኖርብናል።

የጠያቂውን አመለካከት ተረዳ

ሰዱቃውያን ብዙ ባሎች አግብታ የነበረች ሴት በትንሣኤ ጊዜ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖራት በመጠየቅ ኢየሱስን ለማጥመድ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ ግን ሰዎቹ በትንሣኤ እንደማያምኑ ያውቅ ነበር። በመሆኑም የሰጣቸው መልስ ያተኮረው ጥያቄውን እንዲያነሱ ምክንያት በሆናቸው የተሳሳተ አመለካከት ላይ ነበር። በጥበብ በማስረዳትና አንድ የሚያውቁትን ታሪክ ከቅዱስ ጽሑፉ በመጥቀስ ጨርሶ ባልጠበቁት መንገድ መልስ ሰጥቷቸዋል። አምላክ ሙታንን እንደሚያስነሳ የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ አቅርቧል። ተቃዋሚዎቹ በመልሱ እጅግ ስለተገረሙ ከዚያ ወዲያ አንዳች ነገር ሊጠይቁት አልደፈሩም።​—⁠ሉቃስ 20:​27-40

አንተም እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ለማወቅ በቅድሚያ የጠያቂዎችህን አመለካከትና ማወቅ የፈለጉት ምን እንደሆነ ማስተዋል ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል አብሮህ የሚማር ወይም አብሮህ የሚሠራ አንድ ሰው የገናን በዓል የማታከብረው ለምን እንደሆነ ይጠይቅህ ይሆናል። ጥያቄውን ያነሳው ለምንድን ነው? በእርግጥ የማታከብርበትን ምክንያት ማወቅ ፈልጎ ነው? ወይስ መዝናናትና መደሰት ይፈቀድልህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማጣራት? ማወቅ የፈለገው ነገር ምን እንደሆነ ለመረዳት፣ ጥያቄውን ያነሳበትን ምክንያት መጠየቅ ሊያስፈልግህ ይችላል። ከዚያም የምትሰጠው መልስ ከጥያቄው ምክንያት ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል። እግረ መንገድህንም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ መከተላችን በዓሉ ከሚያስከትለው ጭንቀትና ብስጭት እፎይታ እንድናገኝ እንደረዳን ልትገልጽለት ትችላለህ።

ለምሳሌ ያህል በተማሪዎች ፊት ቆመህ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንድትናገር ተጋብዘሃል እንበል። ተናግረህ ከጨረስህ በኋላ ጥያቄዎች ሊያነሡ ይችላሉ። ጥያቄዎቹ በቅንነት የቀረቡ ከሆኑና ከበስተጀርባ ሌላ መልእክት ከሌላቸው ቀላልና ቀጥተኛ መልስ መስጠቱ ከሁሉ የተሻለ ይሆናል። ጥያቄዎቹ የአካባቢው ሰዎች ያላቸውን መሠረተ ቢስ ጥላቻ የሚያንጸባርቁ ከሆነ መልሱን ከመመለስህ በፊት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ብዙኃኑ ያለውን አመለካከት ለማስተካከል የሚረዳ አጠር ያለ ሐሳብ መናገር እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያቸው እንዲሆን የመረጡበትን ምክንያት ማስረዳት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሰዎቹ ጥያቄውን ያነሱት አንተን ለመፈተን ብለው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ጥያቄዎቹን ያነሱት ጉዳዩ ስላሳሰባቸው እንደሆነ አድርጎ ማሰቡ የተሻለ ነው። እንደዚያ ከሆነ የምትሰጠው ምላሽ የአድማጮችህን የአመለካከት አድማስ ለማስፋት የሚረዳ፣ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችልና እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚያስገነዝብ ይሆናል።

በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እረፍት ስትጠይቅ እረፍት ለመስጠት ፈቃደኛ ላልሆነ አሠሪህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? በመጀመሪያ ጉዳዩን በእርሱ ቦታ ሆነህ ለመመልከት ሞክር። ምናልባት በሌላ ጊዜ ትርፍ ሰዓት ሠርተህ እንደምታካክስ መግለጽህ ይበጅ ይሆን? በአውራጃ ስብሰባው ላይ የሚሰጠው ትምህርት ሐቀኛና እምነት የሚጣልብን ሠራተኞች ሆነን እንድንገኝ የሚረዳ እንደሆነ ብትገልጽለት ለውጥ ያመጣ ይሆን? ራስህን በእርሱ ቦታ አስቀምጠህ እንደምታስብ ከተገነዘበ እርሱም በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሰጠኸው ለዚህ ጉዳይ አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንድትፈጽም ቢጠይቅህስ? ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሐሳብ ጠቅሰህ ጥያቄውን እንደማትቀበል በማያሻማ መንገድ መግለጽህ አቋምህን ለማስረዳት በቂ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከዚያ በፊት ዛሬ ለእርሱ ሲል የዋሸና የሰረቀ ሰው ሌላ ጊዜ እርሱንም ሊዋሸውና ከእርሱም ሊሰርቅ እንደሚችል ብታስረዳው የተሻለ ውጤት ታገኝ ይሆን?

በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪ ከሆንክ በትምህርት ቤት በሚደረጉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መካፈል አትፈልግ ይሆናል። አስተማሪው የአንተን አመለካከት የማይደግፍ ሊሆን ቢችልም በክፍል ውስጥ ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነት እንደተጣለበት መዘንጋት የለብህም። ታዲያ ከዚህ አንጻር የሚገጥሙህ ፈታኝ ሁኔታዎች (1) እርሱን የሚያሳስበውን ጉዳይ ግምት ውስጥ ማስገባት (2) አቋምህን በአክብሮት ማስረዳት እንዲሁም (3) ይሖዋን ለማስደሰት ቆራጥ መሆን ናቸው። ውጤቱ ያማረ እንዲሆን ቀላልና ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት በተጨማሪ ሌላም ነገር ያስፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 15:​28) ልጅ ከሆንክ አባትህ ወይም እናትህ ምን ብለህ እንደምትናገር እንደሚያሰለጥኑህ የታወቀ ነው።

አንዳንድ ጊዜ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ሰው የሚሰነዝርብህን ውንጀላ ማስተባበል ይጠበቅብህ ይሆናል። አንድ የፖሊስ መኮንን፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ወይም ዳኛ አንድን የተወሰነ ሕግ ማክበርን ወይም ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን በተመለከተ ስላለህ አቋም አለዚያም ከብሔራዊ ስሜት ጋር በተያያዙ በዓላት ስለመሳተፍ ያለህን አመለካከት እንድትገልጽ ሊጠይቁህ ይችላሉ። ታዲያ መልስ መስጠት የሚኖርብህ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በትሕትናና በአክብሮት” እንድንመልስ ይመክረናል። (1 ጴጥ. 3:​15 አ.መ.ት ) ከዚህም በተጨማሪ ጉዳዩ ይህን ያህል አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው? ብለህ ራስህን ከጠየቅህ በኋላ ሁኔታው የሚያሳስባቸው ለምን እንደሆነ እንደምትረዳ በአክብሮት ግለጽ። ከዚያስ? ጳውሎስ መብቱን ለማስጠበቅ የሮማውያንን ሕግ እንደጠቀሰ ሁሉ አንተም መብትህን የሚያስጠብቅልህን ሕግ ልትጠቅስ ትችላለህ። (ሥራ 22:​25-29) ምናልባትም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጉዳይ በተመለከተ የወሰዱትን አቋም መግለጽ የባለ ሥልጣኑን አመለካከት ሊያሰፋለት ይችል ይሆናል። ወይም ደግሞ አንድ ሰው አምላክን የሚታዘዝ ከሆነ ሰዎች ያወጧቸውንም ተገቢ ሕግጋት ያለማንም ጉትጎታ ዘወትር እንደሚታዘዝ መግለጽ ትችላለህ። (ሮሜ 13:​1-14) ከዚህ በኋላ ለምን ይህን ዓይነት አቋም እንደያዝክ ለማስረዳት የምታቀርበው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ተቀባይነት ያገኝ ይሆናል።

ጠያቂው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት

ለቀረበልህ ጥያቄ እንዴት መልስ እንደምትሰጥ በምታስብበት ጊዜ ጠያቂህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን አመለካከትም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልግህ ይሆናል። ኢየሱስ ሰዱቃውያን ስለ ትንሣኤ ያነሡትን ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ አድርጓል። ሰዱቃውያኑ የሚቀበሉት የሙሴን መጻሕፍት ብቻ እንደነበር ስላወቀ በኦሪት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ አስረድቷቸዋል። በዚህ ጊዜ ሐሳቡን ከመናገሩ በፊት ‘ስለ ሙታን ትንሣኤ ግን ሙሴ ገልጦታል’ የሚል የመንደርደሪያ ሐሳብ ተጠቅሟል። (ሉቃስ 20:​37 የ1980 ትርጉም ) አንተም በተመሳሳይ አድማጭህ ከሚቀበለውና ከሚያውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መጥቀሱን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል።

አድማጭህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሁሉ መቀበል እንዳለበት የማያምን ሰው ቢሆንስ? ሐዋርያው ጳውሎስ በ⁠ሥራ 17:​22-31 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ንግግር በአርዮስፋጎስ ባቀረበበት ጊዜ ምን እንዳደረገ ልብ በል። ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ መጥቀስ ሳያስፈልገው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን አስተምሯቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አንተም እንደዚያው ማድረግ ትችላለህ። በአንዳንድ አካባቢዎች በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰህ መነጋገር የምትችለው ከሰዎቹ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ ተገናኝተህ ከተወያየህ በኋላ ብቻ ሊሆን ይችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስትጠቅስ የአምላክ ቃል እንደሆነ አስረግጠህ ከመናገር ይልቅ ልንመረምረው የሚገባው ለምን እንደሆነ የሚጠቁሙ ቀለል ያሉ ምክንያቶችን ማቅረብህ ጥበብ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ዋናው ግብህ ስለ አምላክ ዓላማ ግልጽ የሆነ ምሥክርነት መስጠትና አድማጭህ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዲያስተውል መርዳት መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ልናፈልቀው ከምንችለው ከየትኛውም ሐሳብ ይበልጥ የማሳመን ኃይል አለው።​—⁠ዕብ. 4:​12

“ሁልጊዜ በደግነት ይሁን”

ይሖዋ ደግ አምላክ ነው። የእርሱ አገልጋዮች ንግግራቸው “በጨው እንደተቀመመ ሁልጊዜ በደግነት” እንዲሆን ምክር መሰጠቱ ምንኛ ተገቢ ነው! (ቆላ. 4:​6 NW፤ ዘጸ. 34:​6 NW ) ይህም ደግነት ማሳየት እንደሌለብን በሚሰማን ጊዜ እንኳ ሳይቀር ንግግራችን ደግነት የተንጸባረቀበት ሊሆን ይገባል ማለት ነው። ንግግራችን ለዛ ያለው እንጂ ሸካራ ወይም ዘዴኛነት የጎደለው መሆን የለበትም።

ብዙ ሰዎች ውጥረት ስለሚበዛባቸውና በየዕለቱም መጥፎና ሸካራ አነጋገር ስለሚሰሙ ስናነጋግራቸው በኃይለ ቃል ይመልሱልን ይሆናል። ታዲያ የእኛ ምላሽ ምን መሆን ይኖርበታል? መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች” ይላል። እንዲህ ያለው መልስ፣ የመቃወም ዝንባሌ ያለውን ሰው አመለካከት እንኳ ሳይቀር ሊያለዝብ ይችላል። (ምሳሌ 15:​1፤ 25:​15) በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ሸካራ አነጋገር መስማት የለመዱ ሰዎች ደግነት የተንጸባረቀበት አነጋገርና የድምፅ ቃና ሊማርካቸው ስለሚችል የምንናገረውን ምሥራች ደስ ብሏቸው ሊያዳምጡ ይችላሉ።

ለእውነት ምንም ዓይነት አክብሮት ከሌላቸው ሰዎች ጋር የመከራከር ፍላጎት የለንም። ከዚህ ይልቅ ምኞታችን ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሰን ማስረዳት ነው። የሚገጥመን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን መልሳችን ደግነት የተሞላ እንዲሁም ውድ በሆነው የአምላክ ተስፋ ላይ የጸና እምነት እንዳለን የሚያሳይ መሆን እንዳለበት አንዘነጋም።​—⁠1 ተሰ. 1:​5

የግል ውሳኔዎችና ለሕሊና የተተዉ ጉዳዮች

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ወይም የእምነት ባልንጀራህ አንድን ጉዳይ በሚመለከት ምን ማድረግ እንዳለበት ቢጠይቅህ መልስህ ምን ሊሆን ይገባል? የአንተ ውሳኔ ምን እንደሆነ ታውቅ ይሆናል። ይሁንና እያንዳንዱ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የራሱን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። (ገላ. 6:​5) ሐዋርያው ጳውሎስ ቃሉን የሰበከላቸው ሰዎች ‘በእምነት እንዲታዘዙ’ አበረታትቷል። (ሮሜ 16:​26) ይህ እኛም ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው። አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪውን ወይም ሌላውን ግለሰብ ለማስደሰት ብሎ ውሳኔ የሚያደርግ ከሆነ በእምነት እየኖረ ሳይሆን ሰዎችን እያገለገለ ነው ሊባል ይችላል። (ገላ. 1:​10) በመሆኑም ጥያቄውን ያቀረበው ሰው ቀላልና ቀጥተኛ መልስ ብትሰጠው አይደሰት ይሆናል።

ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ መልስ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው? ከጉዳዩ ጋር የሚስማሙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ልትጠቅስለት ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜም ራሱ ምርምር አድርጎ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምሳሌዎች እንዴት ማግኘት እንደሚችል ልታሳየው ትችል ይሆናል። መሠረታዊ ሥርዓቶቹና ምሳሌዎቹ ያዘሉትን ትርጉም በተመለከተ ልታወያየው ትችላለህ። ይሁንና ከተነሳው ጉዳይ ጋር በቀጥታ ማያያዝ የለብህም። ከመሠረታዊ ሥርዓቶቹና ከምሳሌዎቹ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ ምን ነገር እንዳገኘ ጠይቀው። በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምሳሌዎች ላይ ተመሥርቶ ምን ዓይነት ውሳኔ ቢያደርግ ይሖዋ ሊደሰት እንደሚችል እንዲያገናዝብ አበረታታው። እንዲህ ካደረግህ ‘መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በመለየት ረገድ የማስተዋል ችሎታውን እንዲያሰለጥን’ እየረዳኸው ነው ማለት ነው።​—⁠ዕብ. 5:​14

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መልስ መስጠት

ብዙውን ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እምነታችንን በሰዎች ፊት መግለጽ የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች እናገኛለን። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ጥያቄዎች ሲጠየቁ መልስ መስጠት ነው። መልስ መስጠት ያለብን እንዴት ነው? ዓላማችን ይሖዋን መባረክ ወይም ማወደስ መሆን አለበት። መዝሙራዊው ዳዊትም “በማኅበር” መካከል ይሖዋን አወድሷል። (መዝ. 26:12) በተጨማሪም መልሳችን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳሳሰበው የእምነት ወንድሞቻችንን የሚያበረታታ እንዲሁም ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቃ’ መሆን አለበት። (ዕብ. 10:​23-25) ትምህርቱን አስቀድመን ማጥናታችን ይህንን ለማድረግ ሊረዳን ይችላል።

መልስ የመስጠት አጋጣሚውን ስታገኝ መልስህ ያልተወሳሰበ፣ ግልጽና አጭር ይሁን። አንቀጹን ከላይ እስከ ታች አታዳርስ። ከዚህ ይልቅ በአንድ ነጥብ ላይ ብቻ አተኩር። የተወሰነውን ክፍል ብቻ ከመለስክ ሌሎች ተጨማሪ ሐሳብ ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ይኖራቸዋል። በተለይ ሐሳባቸውን አንቀጹ ውስጥ ያልተጠቀሰውን ጥቅሶች ማጉላት ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ ጊዜ እየተብራራ ካለው ሐሳብ ጋር በሚዛመደው የጥቅሱ ክፍል ላይ ለማተኮር ሞክር። በቀጥታ ከአንቀጹ ከማንበብ ይልቅ በራስህ አባባል መመለስን ተማር። የሰጠኸው መልስ ትክክል ሆኖ ባይገኝ አትረበሽ። መልስ የሚሰጥ ማንኛውም ሰው አልፎ አልፎ ሊሳሳት ይችላል።

እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብን ማወቅ ማለት መልሱን ማወቅ ብቻ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ማስተዋል ይጠይቃል። ይሁንና ከልብ የመነጨና ሌሎችንም የሚያረካ መልስ መስጠት መቻል በጣም ያስደስታል!​—⁠ምሳሌ 15:​23

መልስ ከመስጠትህ በፊት የሚታሰብባቸው ጉዳዮች

  • ጥያቄው የተነሣበት ምክንያት ምንድን ነው?

  • መልሱ በግልጽ የሚጨበጥ እንዲሆን ምን መሠረት መጣል ያስፈልጋል?

  • ሌላኛውን ወገን የሚያሳስበውን ጉዳይ አንተም እንዳሰብክበት በሚያሳይ መንገድ አቋምህን መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው?

  • ሐሳብህን በደግነትና በልበ ሙሉነት መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው?

  • መልስህ ቀጥተኛ መሆን አለበት ወይስ ሌላኛው ሰው ምን ማድረግ እንደሚገባው ራሱ እንዲወስን የሚረዱትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምሳሌዎች የሚጠቁም?

በስብሰባ ላይ ሐሳብ ስትሰጥ

  • ለጥያቄው የመጀመሪያውን መልስ የምትሰጠው አንተ ከሆንህ መልስህ ያልተወሳሰበና ቀጥተኛ ይሁን

  • ተጨማሪ ሐሳብ ለመስጠት (1) ምዕራፍና ቁጥራቸው የተጠቀሱት ጥቅሶች እየተብራራ ካለው ነጥብ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ፣ (2) ጉዳዩ እኛን የሚመለከተን እንዴት እንደሆነ፣ (3) ትምህርቱን እንዴት ልንሠራበት እንደምንችል አስረዳ ወይም (4) ቁልፍ የሆኑትን ነጥቦች የሚያጎላ አጭር ተሞክሮ ተናገር

  • ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት እንድትችል ሌሎች ሐሳብ ሲሰጡ በጥሞና አዳምጥ

  • በራስህ አባባል ለመመለስ ሞክር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ