ለአልኮል መጠጦች ያለህ አመለካከት አምላካዊ ነውን?
ከሀያ ዓመት በፊት አካባቢ በኢራን አገር ዩርሚ ተብላ በምትታወቀው ከተማ አቅራቢያ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች አንድ ጥንታዊ የሆነ ከጡብ የተሠራ ቤት በቁፋሮ አገኙ። በቤቱ ውስጥም በሳይንቲስቶቹ አባባል የሰው ልጅ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሄዶ መስፈር ወደጀመረበት ጊዜ የሚደርስ ብዙ ሺህ ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ ከሸክላ የተሠራ ማሠሮ አገኙ። የማሰሮውን ምንነት ለማወቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በፈጠረው ዘዴ ከፍተኛ ምርምር ተደርጓል። ሳይንቲስቶቹ በጥንት ጊዜ የወይን ጠጅ ለማዘጋጀት የሚያገለግል የኬሚካል ቅመም በማሰሮው ውስጥ በማግኘታቸው በጣም ተገረሙ።
መጽሐፍ ቅዱስም ከጥንት ጊዜያት ጀምሮ ሰዎች የወይን ጠጅ፣ ቢራና ሌሎች የአልኮል መጠጦችን ይጠጡ እንደነበር በማያሻማ መንገድ ያሳያል። (ዘፍጥረት 27:25፤ መክብብ 9:7፤ ናሆም 1:10) እንደ ሌሎች ምግቦች ሁሉ ይሖዋ የአልኮል መጠጦችን የመጠጣትም ሆነ ያለመጠጣትን ምርጫ ለእኛ ትቶልናል። ኢየሱስ ከምግብ ጋር የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ ደግሞ ከአልኮል ተቆጥቦ ነበር።—ማቴዎስ 11:18, 19
መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ መጠጣትን ይከለክላል። ስካር በአምላክ ላይ ኃጢአት የመፈጸም ተግባር ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ከእነዚህ ጋር በመስማማት የይሖዋ ምሥክሮች ንስሐ የማይገባ ማንኛውም ሰካራም ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንዲኖር አይፈቅዱም። በጉባኤ ውስጥ የሚኖሩ የአልኮል መጠጦችን ለመጠጣት የመረጡ ግለሰቦች መጠጥ በሚጠጡበት ጊዜ ልከኛ መሆን ይገባቸዋል።—ቲቶ 2:2, 3
አምላካዊ ያልሆነ አመለካከት
በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ለአልኮል መጠጦች አምላካዊ አመለካከት የላቸውም። ሰይጣን ጥንታዊ ዕድሜ ያለውን ይህን ምርት አለአግባብ የመጠቀምን መንፈስ እያስፋፋ እንዳለ ለማስተዋል አያስቸግርም። ለምሳሌ በደቡባዊ ፓስፊክ ደሴቶች በሚኖሩ ወንዶች ዘንድ በቤት ውስጥ የተዘጋጀ ብዙ የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት መሰባሰብ የተለመደ ነገር ነው። እነዚህ የጨዋታ ጊዜያት ረዥም ሰዓታት የሚቆዩና በተደጋጋሚ የሚደረጉ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ወንዶች በየቀኑ በመጠጣት ይህን ልማድ ይከተላሉ። አንዳንዶች ይህን ልማድ እንደ ተራ ባሕል አድርገው ይመለከቱታል። አንዳንድ ጊዜ እቤት በሚዘጋጁ መጠጦች ምትክ ወይም በተጨማሪ ቢራና ሌሎች የአልኮል መጠጦችን ይጠጣሉ። በውጤቱም ብዙውን ጊዜ ስካር ይከተላል።
በሌላ የፓስፊክ ውቅያኖስ የሚኖሩ ወንዶች የአልኮል መጠጥ በልክ መጠጣታቸው ፈጽሞ የማይታወቅ ነገር ነው። ለመጠጣት ከተቀመጡ እስኪሰክሩ ድረስ ይጠጣሉ። በተለይ በደሞዝ ቀን ብዙ ወንዶች በቡድን ሆነው ይሰባሰቡና 24 ጠርሙሶች የሚይዙ ብዙ የቢራ ሣጥኖች ይገዛሉ። መጠጣት የሚያቆሙት ቢራው ሲያልቅ ብቻ ነው። በዚህም የተነሳ በየመንገዱ የሰከረ ሰው መመልከት የተለመደ ነገር ነው።
እቤት የሚጠመቁ መጠጦች ለምሳሌ ከዘንባባ ግንድ ወለላ የሚሠራ የወይን ጠጅና ሌሎች በአካባቢው የሚዘጋጁ መጠጦች በአፍሪካ አገሮች እንደ ባህል መጠጦች ሆነው ይዘጋጃሉ። እንግዶች ሲመጡ የአልኮል መጠጦች እንዲቀርቡ በአንዳንድ መንደሮች ያለው ባሕል ያዛል። ጥሩ እንግዳ ተቀባይ የሆነ ቤተሰብ ሊጠይቅ ለመጣው ሰው መጠጣት ከሚችለው በላይ በዘልማድ መጠጥ ያቀርባል። በአንድ አካባቢ ያለው ልማድ በእያንዳንዱ እንግዳ ፊት 12 ጠርሙስ ቢራ መደርደር ነው።
በጃፓን የሚገኙ ብዙ ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው የአውቶቡስ ጉዞ ያዘጋጃሉ። ብዛት ያለው የአልኮል መጠጥ መኪናው ውስጥ አብሯቸው ይጫናል። ስካር ይፈቀዳል። እነዚህ ለሽርሽር የወጡት ሠራተኞች ሁለት ወይም ሦስት ቀናት እዚያው ይቆያሉ። ኤዢያዊክ የተሰኘው መጽሔት በጃፓን “በባሕሉ መሠረት ሩዝ አምራች ከሆነው ገበሬ አንስቶ እስከ ባለ ጠጋ የፖለቲካ ሰው ድረስ የአንድ ሰው ወንድነት የሚለካው በሚወስደው የአልኮል መጠን ነው” በማለት ዘግቧል። በሌሎች የእስያ አገሮችም ተመሳሳይ ዝንባሌ ይታያል። ኤዢያዊክ “ደቡብ ኮርያውያን በነፍስ ወከፍ የሚጠጡት የአልኮል መጠጥ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከሚጠጡት የበለጠ እንደሆነ” አትቷል።
ከመጠን በላይ መጠጣት ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ኮሌጆች ውስጥ በሰፊው የተዛመተ ልማድ ሆኗል። ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን በሰጠው ዘገባ መሠረት “ከመጠን በላይ የሚጠጡ ሰዎች የመጠጥ ችግር እንዳለባቸው አይታወቃቸውም።”a በብዙ አገሮች ያሉ የዜና ማሰራጫዎች ጠጪነትን እንደ ጀብዱ፣ እንደ ፋሽንና የአዋቂነት መግለጫ አድርገው ስለሚያቀርቡት ይህ ሁኔታ ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ ብዙውን ጊዜ የሚያነጣጥረው በወጣቶች ላይ ነው።
በብሪታንያ የቢራ ጠጪዎች ቁጥር በ20 ዓመት ውስጥ በእጥፍ አድጓል። ኃይለኛ መጠጥ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ድግሞ በሦስት እጥፍ ከፍ ብሏል። መጠጥ የሚጀመርበት ጊዜ ዝቅ እያለ የመጣ ሲሆን የሴት ጠጪዎች ቁጥርም ከበፊቱ የበለጠ ከፍ ብሏል። ተመሳሳይ የሆነ አዝማሚያ በምሥራቅ አውሮፓና በላቲን አሜሪካ አገሮች እየታየ ነው። ይህም እያሻቀበ በሚሄደው የአልኮል ሱሰኝነትና ከአልኮል ጋር በተያያዘ መንገድ የሚደርሰው የሰውን ሕይወት የሚያጠፉ የትራፊክ አደጋ ጉልህ ማስረጃ ነው። አልኮልን ያለአግባብ መጠቀም በዓለም ዙሪያ እያደገ እንዳለ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
ከመጠን ያለፈ የሚባለው ምን ያህሉ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለአልኮል መጠጦች ያለው አመለካከት ሚዛኑን የጠበቀ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች የወይን ጠጅ “የሰውን ልብ ደስ” የሚያሰኝ የይሖዋ አምላክ ስጦታ እንደሆነ ይናገራሉ። (መዝሙር 104:1, 15) በሌላ በኩልም መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ መጠጣትን ለማውገዝ “የመጠጥ ብዛት፣” ‘በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም መጠጣት፣’ ‘ለብዙ ወይን ጠጅ የሚጎመጅ’ እና “ለብዙ ወይን ጠጅ የሚገዙ” የሚሉትን አነጋገሮች ይጠቀማል። (ሉቃስ 21:34፤ 1 ጴጥሮስ 4:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:8፤ ቲቶ 2:3) ይሁን እንጂ “ብዙ ወይን ጠጅ” የሚባለው ምን ያህል ነው? አምላክ ለአልኮል መጠጦች ያለው አመለካከት ምን ነገሮች እንደሚያካትት አንድ ክርስቲያን ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?
ስካርን ለይቶ ማወቅ ይህን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። ስካር የሚያስከትላቸው ውጤቶች ምን እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቁሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? . . . ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን [“እንግዳ ነገሮችን፣” አዓት] ያያሉ፣ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል።”—ምሳሌ 23:29-33
ብዙ አልኮል መጠጣት ብዥታን፣ ቅዠትን፣ ራስን መሳትና ሌሎች አእምሯዊና አካላዊ ሕመምን ሊያስከትል ይችላል። አንድ ሰው በአልኮል ተገፋፍቶ ባሕሪውን መቆጣጠር ተስኖት በራሱና በሌሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ሰካራሞች አሳፋሪ፣ ቀፋፊና ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንደሚፈጽሙ የታወቀ ነው።
እስኪሰክሩ ማለትም ከላይ የተጠቀሱት ውጤቶች እስኪታዩ ድረስ መጠጣት ከልክ ያለፈ ድርጊት ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የሰከረ ሰው የሚያሳያቸው ዓይነት ምልክቶች ሳይታዩበት መጠኑን እንደሳተ ሊያሳይ ይችላል። በዚህም የተነሳ አንድ ሰው ከልክ በላይ ጠጥቷል ወይም አልጠጣም የሚለው ጥያቄ ብዙውን ጊዜ አከራካሪ ጉዳይ ነው። በልከኝነትና ከመጠን በላይ በመጠጣት መካከል ያለው ድንበር የቱ ነው?
የማሰብ ችሎታችሁን ጠብቁ
መጽሐፍ ቅዱስ በደም ውስጥ ያለው የአልኮል መጠን ከዚህ ማለፍ የለበትም በማለት ወይም ሌላ ዓይነት መለኪያ በመጠቀም ገደብ አያበጅም። አልኮል የመቋቋም ችሎታ ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሠሩና አምላክ ለአልኮል መጠጦች ያለውን አመለካከት እኛም እንዲኖረን ሊረዱን ይችላሉ።
ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠውን ትእዛዝ ሲናገር “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:37, 38) አልኮል በአእምሮ ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ከመጠን በላይ መጠጣት ከሁሉም ለሚበልጠው ሕግ ያለህን ታዛዥነት ይነካብሃል። አእምሮ የሚያከናውናቸውን የማመዛዘን፣ ለችግሮች መፍትሄ የማምጣት፣ ራስን የመግዛትና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የአእምሮ ሥራዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያቃውስ ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎችም “መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን [“የማሰብ ችሎታን፣” አዓት] ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፣ ለአንገትህም ሞገስ” በማለት አጥብቀው ይመክሩናል።—ምሳሌ 3:21, 22
ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰውነታችሁን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም በማመዛዘን ችሎታችሁ ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው” በማለት ክርስቲያኖችን ተማጽኗል። (ሮሜ 12:1 አዓት) አንድ ክርስቲያን ‘በማመዛዘን ችሎታው’ መጠቀም እሰኪሳነው ድረስ አልኮል ቢጠጣ “በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት” ይኖረዋልን? ብዙውን ጊዜ ከልክ በላይ መጠጣት የጀመረ ሰው አልኮል በቀላሉ የማይበግረው ይሆናል። ከባድ ጠጪ መሆኑ በቀላሉ የማይሰክር እንደሆነ አድርጎ ሊያስብ ይችላል። ይሁን እንጂ በአልኮል ላይ ተገቢ ያልሆነ ጥገኝነት እያዳበረ ሊሆን ይችላል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ሰውነቱን “ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት” አድርጎ ሊያቀርብ ይችላልን?
የአልኮሉ መጠን የአንድ ክርስቲያን ‘መልካም ጥበብና ጥንቃቄ’ ወይም “ተግባራዊ ጥበብና የማሰብ ችሎታ [አዓት]” የሚያኮላሽ ከሆነ መጠኑ ከልክ ያለፈ ነው።
ለአልኮል መጠጥ ያለህን አመለካከት የሚቀርጸው ምንድን ነው?
አንድ ክርስቲያን ለመጠጥ ያለው አመለካከት ወቅታዊው የሰዎች አዝማሚያ ወይም የአካባቢው ባህል ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደሆነና እንዳልሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል። የአልኮል መጠጦችን በሚመለከት በባሕል ወይም በዜና ማሰራጫ ልፈፋ ላይ የተመሠረተ ምርጫ ማድረግ እንደማትፈልግ የተረጋገጠ ነው። የራስህ ዝንባሌ ምን እንደሆነ ለመወሰን እንድትችል እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ ‘ለመጠጥ ያለኝ አመለካከት በአካባቢው ዘንድ ተቀባይነት ባለው ነገር ተጽዕኖ ደርሶበታልን? ወይስ ለመጠጥ ያለኝ አቋም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመረኮዘ ነው?’
ምንም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ባሕልን የሚጻረሩ ባይሆኑም በአሁኑ ጊዜ በሰፊው ተቀባይነት ያላቸውን ብዙ ልማዶች ይሖዋ እንደሚጸየፍ ያውቃሉ። አንዳንድ አካባቢዎች ጸንስ ማስወረድን፣ ደም በደም ሥር መውሰድን፣ ግብረ ሰዶማዊነትንና ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትን ይፈቅዳሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች አምላክ ለእነዚህ ነገሮች ካለው አመለካከት ጋር የሚስማማ ሥራ እየሠሩ ይኖራሉ። አዎን፣ በአካባቢው ባሕሎች ተቀባይነት ቢኖራቸው ወይም ባይኖራቸው አንድ ክርስቲያን እንደነዚህ የመሰሉትን ልማዶች እንዲጠላ አምላካዊ አመለካከት ያነሳሳዋል።—መዝሙር 97:10
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስካርንና ያለ ልክ መጠጣትን’ በውስጡ አቅፎ ስለያዘው ስለ “አሕዛብ ፈቃድ” ይናገራል። “ያለ ልክ መጠጣት” የሚለው ሐረግ ብዙ አልኮል ለመጠጣት ሲባል ሆን ተብሎ የሚደረገውን ጠጪዎች ወደ አንድ ቦታ ሄደው የሚገናኙበትን ዝግጅት ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ምንም ቢጠጡ ሞቅታ እንኳ የማይሰማቸው መሆናቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ ወይም የላቀ ጠጪ ማን እንደሆነ ለማየት የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች የነበሩ ይመስላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነቱን አኗኗር ንስሐ የገቡ ክርስቲያኖች ፈጽሞ ካስወገዱት “መዳራት” ጋር አያይዞ ጠቅሶታል።—1 ጴጥሮስ 4:3, 4
አንድ ሰው እስካልሰከረ ድረስ የትም ቦታ፣ በየትኛውም ጊዜ ወይም ምንም ያህል ይጠጣ ዋናው ጉዳይ አለመስከሩ ነው የሚለውን አመለካከት አንድ ክርስቲያን ቢቀበል ምክንያታዊ ነውን? እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት አምላክ ያለው አመለካከት ነውን? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል ለመጠጣት ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ቢሰባሰቡ ሁሉም ላይሰክሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ተግባራቸው ይሖዋን ያስከብራልን? “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ይመክራል።—ሮሜ 12:2
ሌሎችን ከማደናቀፍ መቆጠብ
የሚያስገርመው ግን ብዙውን ጊዜ ከመጠን በላይ መጠጣትን የሚቀበሉ ባሕሎች የአምላክ አገልጋይ ነኝ የሚል አንድ ሰው ከባድ ጠጪ ከሆነ ከልክ በላይ መጠጣቱን ያወግዛሉ። በደቡብ ፓስፊክ ባለ አንድ ትንሽ መንደር የሚኖር አንድ ታዛቢ “እናንተን ሰዎች በጣም አደንቃለሁ። እውነትን ትሰብካላችሁ። ችግሩ ግን የእናንተ ሰዎች ብዙ አልኮል ይጠጣሉ” በማለት ተናግሯል። ዘገባው እንደሚያሳየው ግለሰቦቹ አልሰከሩም፤ ይሁን እንጂ ይህ ሐቅ በመንደሩ ለሚኖሩት ለአብዛኞቹ ሰዎች ግልጽ አይደለም። በቡድን ሆነው ከሚጠጡ ሰዎች ጋር አብረው የሚጠጡ ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ምሥክሮቹም አብረው ቢጠጡ ይሰክራሉ ብለው ተመልካቾች በቀላሉ ሊደመድሙ ይችላሉ። ሰዎች ተሰባስበው በሚጠጡበት ቦታ አብሮ የሚጠጣ አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ጥሩ ስም ሊያተርፍና ሳይሸማቀቅ አገልግሎቱን ሊያከናውን ይችላልን?—ሥራ 28:31
አልፎ አልፎ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የአልኮል መጠጥ ጠጥተው አፋቸው እየሸተተ ወደ መንግሥት አዳራሽ እንደሚመጡ ከአንድ የአውሮፓ አገር የመጣ ዘገባ ይጠቁማል። ይህም የሌሎችን ሕሊና ረብሿል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው” በማለት አጥብቆ ይመክራል። (ሮሜ 14:21) ለአልኮል መጠጥ አምላካዊ አመለካከት ያለው አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በአንዳንድ ወቅቶች አልኮል ፈጽሞ ባለመጠጣት ለሌሎች ሕሊና በጥልቅ እንዲያስብ ይገፋፋል።
ክርስቲያኖች ፍጹም የተለዩ ናቸው
የሚያሳዝነው ይህ ዓለም የአልኮል መጠጦችን ጨምሮ አምላክ ለሰው ዘሮች የሰጣቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች አላግባብ በመጠቀም ይሖዋን የሚያስከፋ ነገር ያደርጋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን በሰፊው ተንሰራፍቶ ከሚገኘው አምላካዊ ካልሆነ አመለካከት ለመራቅ መጣጣር ይኖርበታል። በዚህ መንገድ ሰዎች “በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል” ያለውን ልዩነት ለማየት መቻል ይኖርባቸዋል።—ሚልክያስ 3:18
የአልኮል መጠጦችን በተመለከተ በይሖዋ ምሥክሮችና በዓለም መካከል ያለው ‘ልዩነት’ የማያሻማ መሆን ይኖርበታል። የአልኮል መጠጦችን መጠጣት በእውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የሚይዝ ነገር አይደለም። በአደገኛ ሁኔታ ወደ ስካር በመቃረብ አልኮል የመቋቋም ችሎታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅም አይሞክሩም። እንዲሁም የአልኮል መጠጦች ጉዳት እንዲያደርስባቸው ወይም በማንኛውም መንገድ በሙሉ ነፍሳቸውና በንጹህ አእምሮ ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንዲያስተጓጉልባቸው አይፈቅዱም።
በቡድን ደረጃ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ለአልኮል መጠጦች ያለው ዓይነት አመለካከት አላቸው። ግን አንተስ? “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፣ . . . ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ የምንከተል ከሆነ እያንዳንዳችን የይሖዋን በረከት ልናገኝ እንችላለን።—ቲቶ 2:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “አምስት ወይም ከዚያ የበለጡ መጠጦችን በተከታታይ የሚጠጡ ወንዶችና አራት ወይም ከዚያ የበለጡ መጠጦችን በተከታታይ የሚጠጡ ሴቶች ከባድ ጠጪ ይባላሉ።”—ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የምትወዱት ሰው የሚለውን አዳምጡ
ከመጠን በላይ የሚጠጣ ሰው ይህ ችግር እንዳለበት የሚገነዘበው ብዙውን ጊዜ ከሌሎች በኋላ ነው። ዘመዶች፣ ጓደኞችና ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሚዛኑን መጠበቅ ላቃተው ሰው እርዳታ ከመለገስ ማመንታት አይኖርባቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ የሚወዱህ ሰዎች አልኮል የመጠጣት ልማድህ ቢያሳስባቸው ጥሩ ምክንያት ይኖራቸዋል ብለህ መገመት አለብህ። ስለዚህ የሚናገሩትን በጥሞና አስብበት።—ምሳሌ 19:20፤ 27:6