“እናንት ሕዝቦች፣ያህን አወድሱ!”
“እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን።”—መዝሙር 150:6
1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር? (ለ) ሐዋርያት በቅድሚያ ምን ማስጠንቀቂያዎች ሰጥተው ነበር? (ሐ) ክህደት የተስፋፋው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በክርስቲያናዊ ጉባኤዎች አደራጅቷል። እነዚህ ጉባኤዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን በመንፈሳዊ ሊበለጽጉ ችለዋል። ምንም እንኳ የከረረ ሃይማኖታዊ ተቃውሞ የነበረ ቢሆንም “ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተሰብኳል። (ቆላስይስ 1:23) ይሁን እንጂ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ሰይጣን በተንኮል ክህደት እንዲስፋፋ አደረገ።
2 ሐዋርያት ስለዚህ ክህደት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች እንደሚከተለው እንዳለ እናነባለን፦ “በገዛ ደሙ [“በገዛ ልጁ ደም፣” አዓት] የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።” (ሥራ 20:28-30፤ በተጨማሪም 2 ጴጥሮስ 2:1-3 እና 1 ዮሐንስ 2:18, 19ን ተመልከት።) በዚህ ምክንያት በአራተኛው መቶ ዘመን የክህደት ክርስትና ከሮማ አጼያዊ መንግሥት ጋር ኅብረትና አንድነት ፈጠረ። ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ ከሮማ ሊቀ ጳጳስ ጋር የቅርብ ትስስር የነበረው ቅዱሱ የሮማ አጼያዊ መንግሥት ሰፊ በሆነ የሰው ልጅ ክፍል ላይ መግዛት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የፕሮቴስታንት የተሐድሶ እንቅስቃሴ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግፈኛ ግዛት ላይ ዓመፀ። ቢሆንም እውነተኛውን ክርስትና ማቋቋም አልሆነለትም።
3. (ሀ) የምሥራቹ ለፍጥረት ሁሉ የተሰበከው መቼና እንዴት ነበር? (ለ) በ1914 እውን የሆኑት የትኞቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋዎች ናቸው?
3 ይሁን እንጂ 19ኛው መቶ ዘመን ሊያልቅ በተቃረበበት ጊዜ ቅን የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን ‘ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት በሙሉ የምሥራቹን ተስፋ’ በትጋት ማዳረስና መስበክ ጀምሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶችን በማጥናት ባገኙት እውቀት ከ30 ዓመት በፊት ጀምረው 1914 ‘የተወሰነው የአሕዛብ ዘመን’ ወይም በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ የጀመረው የ2,520 ዓመታት ማለትም ‘ሰባቱ ዘመናት’ የሚያልቁበት ዓመት እንደሚሆን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። (ሉቃስ 21:24፤ ዳንኤል 4:16) ልክ እንደተጠበቀውም 1914 አዲስ የሰው ልጅ ታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት ሆነ። በሰማይም ታሪካዊ ክንውኖች ተፈጽመዋል። የዘላለሙ ንጉሥ ክፋትን በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋትና ገነትን ለመመለስ የሚያስችለውን ዝግጅት ለማድረግ ሲል ተባባሪ ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማያዊ ዙፋን ላይ ያስቀመጠው በዚህ ጊዜ ነበር።—መዝሙር 2:6, 8, 9፤ 110:1, 2, 5
መሲሐዊውን ንጉሥ ተመልከቱ!
4. ኢየሱስ ሚካኤል ከተባለው ስሙ ጋር የሚስማማ ተግባር የፈጸመው እንዴት ነው?
4 ይህ መሲሐዊ ንጉሥ በ1914 እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሚካኤል ተብሎ ተጠርቷል። ትርጓሜውም “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ሲሆን የይሖዋን ልዕልና ለማረጋገጥ ቆርጦ የተነሣ መሆኑን የሚያመለክት ስም ነው። በራእይ 12:7–12 ላይ እንደተመዘገበው ሐዋርያው ዮሐንስ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፣ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” በእርግጥም እጅግ ታላቅ የሆነ ውድቀት ሆነ!
5, 6. (ሀ) ከ1914 በኋላ በሰማይ የታወጀው አስደሳች መልእክት ምንድን ነው? (ለ) ማቴዎስ 24:3-13 ከዚህ ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው?
5 ከዚያም በሰማይ አንድ ኃይለኛ የሆነ ድምፅ እንደሚከተለው ሲል አወጀ። “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል፣ መንግሥትም፣ የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ። ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንደሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። እነርሱም [ታማኝ ክርስቲያኖች] ከበጉ [ከኢየሱስ ክርስቶስ] ደም የተነሣ ከምሥክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፣ ነፍሳቸውንም እስከሞት ድረስ አልወደዱም።” ንጹሕ አቋማቸውን ለጠበቁና ውድ በሆነው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላመኑ ሁሉ መዳን ይሆንላቸዋል ማለት ነው።—ምሳሌ 10:2፤ 2 ጴጥሮስ 2:9
6 ከዚህ በመቀጠል ይህ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ እንዲህ ሲል ተሰማ፦ “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” ለምድር የተተነበየላት ‘ወዮታ’ በዚህ መቶ ዘመን ምድርን ቀስፎ በያዛት የዓለም ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ የምድር መናወጥና ወንጀል ታይቷል። ማቴዎስ 24:3–13 እንደሚተርከው ኢየሱስ እነዚህ ‘የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ምልክት’ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል እንደሆኑ ተንብዮአል። የሰው ልጅ በትንቢቱ መሠረት ከ1914 ጀምሮ በማንኛውም የሰብዓዊ ታሪክ ዘመን አቻ ያልተገኘለት ወዮታ ደርሶበታል።
7. የይሖዋ ምሥክሮች በጥድፊያ ስሜት የሚሰብኩት ለምንድን ነው?
7 ሰይጣናዊ ወዮታ በነገሠበት በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ስለ ወደፊት ሕይወቱ ተስፋ ሊኖረው ይችላልን? አዎን፣ ይችላል! ማቴዎስ 12:21 ኢየሱስን አስመልክቶ “አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። በምድር ብሔራት ላይ የደረሰው የስሜት ቁስል ‘የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ’ የቀረበ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ‘ኢየሱስ’ የመሲሐዊው መንግሥት ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ‘መገኘቱን የሚያረጋግጥ ምልክት’ ጭምር ነው። ኢየሱስ ስለዚህ መንግሥት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የአምላክን መንግሥት የመግዛት ተስፋ የሚሰብክ ብቸኛ ሕዝብ የትኛው ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው! የአምላክ የጽድቅና የሰላም መንግሥት የምድርን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት በጥድፊያ ስሜት ይሰብካሉ። እናንተስ በዚህ ሥራ እየተካፈላችሁ ነው? ከዚህ የበለጠ መብት ልታገኙ አትችሉም!—2 ጢሞቴዎስ 4:2, 5
“መጨረሻው” የሚመጣው እንዴት ነው?
8, 9. (ሀ) ፍርድ “ከእግዚአብሔር ቤት” የጀመረው እንዴት ነው? (ለ) ሕዝበ ክርስትና የአምላክን ቃል ሳታከብር የቀረችው እንዴት ነው?
8 በሰው ልጆች ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ዘመን ደርሷል። በ1 ጴጥሮስ 4:17 ላይ “ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት” እንደሚጀምር ተገልጾልናል። ይህም ፍርድ ከ1914-18 ከተካሄደው የመጀመሪያ ዓለም ጦርነት ጀምሮ ባለው በዚህ “የመጨረሻ ቀን” ክርስቲያን ነን በሚሉ ድርጅቶች ላይ ሲፈጸም ቆይቷል። ሕዝበ ክርስትና ምን ፍርድ ተቀብላ ይሆን? አብያተ ክርስቲያናት ከ1914 ጀምሮ በተደረጉ ጦርነቶች የወሰዱትን አቋም መመልከት ብቻ ይበቃል። ቀሳውስት ወደ ጦር ሜዳ እንዲሄዱ በሰበኩላቸው ‘የንጹሐን ድሆች ነፍሳት ደም’ የተጨማለቁ አይደሉምን?—ኤርምያስ 2:34
9 ኢየሱስ በማቴዎስ 26:52 ላይ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሏል። ይህ ቃል በዚህ መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች ምንኛ እውነት ሆኖ ተገኝቷል! ቀሳውስት ከፍተኛ እልቂት ወዳለበት የጦር ሜዳ እንዲዘምቱ ወጣቶችን አበረታተዋል። እነዚህ ወጣቶች የራሳቸው ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ሌሎች ወጣቶችን ማለትም ካቶሊኮች ካቶሊኮችን፣ ፕሮቴስታንቶች ፕሮቴስታንቶችን ገድለዋል። ብሔራዊ ስሜት ከአምላክም ሆነ ከክርስቶስ የበለጠ ክብር ተሰጥቶታል። በቅርቡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የጎሣ ትስስር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የበለጠ ከበሬታ ተሰጥቶታል። አብዛኛው ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆነበት በሩዋንዳ ውስጥ ግማሽ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በጎሣ ብጥብጥ ምክንያት ተገድለዋል። ሊቀ ጳጳሱ ሎሰርቫቶሬ ሮማኖ በተባለው የቫቲካን ጋዜጣ ላይ “ይህ ካቶሊኮች እንኳን በኃላፊነት የሚጠየቁበት የለየለት ዘር የማጥፋት ወንጀል ነው” በማለት አምነዋል።—ከኢሳይያስ 59:2, 3 እና ከሚክያስ 4:3, 5 ጋር አወዳድር።
10. ይሖዋ በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚያስፈጽመው ፍርድ ምንድን ነው?
10 ታዲያ የዘላለሙ ንጉሥ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲጨፋጨፉ ስለሚያበረታታ ወይም አንደኛው የመንጋ ክፍል ሌላውን ክፍል ሲገድል ዝም ብሎ ስለሚመለከት ሃይማኖት እንዴት ይሰማዋል? ራእይ 18:21, 24 የሐሰት ሃይማኖት ዓለም አቀፍ ሥርዓት ስለሆነችው ስለ ታላቂቱ ባቢሎን እንዲህ ይላል፦ “አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል፦ ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።”
11. በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በመፈጸም ላይ ያሉት አጸያፊ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
11 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በጣም አስጸያፊ የሆኑ ነገሮች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። (ከኤርምያስ 5:30, 31፤ 23:14 ጋር አወዳድር።) ቀሳውስት በአብዛኛው በሥነ ምግባር ረገድ ልል በመሆናቸው ምክንያት መንጎቻቸው ከሥነ ምግባር ውጭ በሆኑ ድርጊቶች ተውጠዋል። የክርስቲያን አገር ነው በሚባለው በዩናይትድ ስቴትስ ከጠቅላላ ጋብቻዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት በፍቺ ይፈርሳሉ። በቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል የወጣቶች እርግዝናና ግብረ ሰዶም ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል። ቀሳውስት ትናንሽ ልጆችን በጾታ ያስነወሩባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። በዚህ ምክንያት በፍርድ ቤቶች የሚወሰነው የገንዘብ ካሣ የዩናይትድ ስቴትስን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር ሳያስወጣት እንደማይቀር ይታመናል። ሕዝበ ክርስትና በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ የሚገኘውን የሐዋርያው ጳውሎስ ማስጠንቀቂያ አቃላለች። “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”
12. (ሀ) የዘላለሙ ንጉሥ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እርምጃ የሚወስደው እንዴት ነው? (ለ) ከሕዝበ ክርስትና በተቃራኒ የአምላክ ሕዝቦች “የሃሌ ሉያ” ዝማሬዎችን የሚዘምሩት ለምንድን ነው?
12 በቅርቡ የዘላለሙ ንጉሥ ይሖዋ በሰማይ ዋና የጦር አዛዥ አድርጎ በሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ታላቁን መከራ ይለቃል። በመጀመሪያ ሕዝበ ክርስትናና ከዚያም ሌሎቹ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች በሙሉ የይሖዋን ፍርድ ይቀበላሉ። (ራእይ 17:16, 17) ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ያዘጋጀውን ማዳን ሊያገኙ የማይበቁ መሆናቸውን አሳይተዋል። የአምላክን ቅዱስ ስም አዋርደዋል። (ከሕዝቅኤል 39:7 ጋር አወዳድር።) በተንቆጠቆጡ ግዙፍ ሃይማኖታዊ ሕንፃዎቻቸው “ሃሌ ሉያ” የሚል ዝማሬ ማሰማታቸው እንዴት ያለ ቀልድ ነው! ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውድ የሆነውን የይሖዋ ስም ቢያስወግዱም “ሃሌ ሉያ” ማለት “ያህን አወድሱ” ማለት እንደሆነና “ያህ” “ይሖዋ” የሚለው ስም አሕጽሮተ ቃል እንደሆነ ያስተዋሉ አይመስልም። በራእይ 19:1-6 ላይ አምላክ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸመውን ፍርድ ለማወደስ በቅርቡ የሚዘመሩትን የ“ሃሌ ሉያ” ዝማሬዎች መመዝገቡ ተገቢ ነው።
13, 14.(ሀ)ቀጥሎ የተፈጸሙት ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ምን አስደሳች በረከቶች ያገኛሉ?
13 ከዚህ ቀጥሎ የሚፈጸመው ኢየሱስ በብሔራትና በሕዝቦች ላይ ፍርድ ለመስጠት ‘የሚመጣበት’ ጊዜ ነው። እርሱ ራሱ እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “የሰው ልጅ [ክርስቶስ ኢየሱስ] በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ [በፍርድ] ዙፋን ይቀመጣል [በምድር ላይ ያሉ] አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” (ማቴዎስ 25:31-34) ቀጥሎ ቁጥር 46 ሲናገር የፍየሎቹ ቡድን “ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” ይላል።
14 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” የሆነው ሰማያዊ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአርማጌዶን ጦርነት የሰይጣንን የፖለቲካና የንግድ ዓለም እንዴት ፈጽሞ እንደሚደመስስ ይገልጻል። በዚህ መንገድ ክርስቶስ በመላው የሰይጣን ምድራዊ ግዛት ላይ “ሁሉን የሚችለውን አምላክ ቁጣ” ያፈስሳል። እነዚህ ‘የቀድሞው ሥርዓት’ ክፍሎች ሲጠፉ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች አምላክ ‘እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ወደሚያብስበት’ ዕፁብ ድንቅ አዲስ ዓለም ይገባሉ።—ራእይ 19:11-16፤ 21:3-5
ያህ የሚወደስበት ጊዜ
15, 16. (ሀ) የይሖዋን ትንቢታዊ ቃል መታዘዛችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ነቢያትና ሐዋርያት ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብን ጠቁመዋል? በዛሬው ጊዜ ይህ ለብዙዎች ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል?
15 ይህ የፍርድ ቀን በጣም ቀርቧል! ስለዚህ የዘላለሙን ንጉሥ የትንቢት ቃል ብንሰማ እንጠቀማለን። አንድ ሰማያዊ ድምፅ እስከ አሁን ድረስ በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች ተተብትበው ለተያዙ ሁሉ “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” የሚል ጥሪ ያቀርባል። ይሁን እንጂ ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥተው የሚሸሹት ወዴት ነው? ከአንድ የበለጠ እውነት ሊኖር ስለማይችል እውነተኛው ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው። (ራእይ 18:4፤ ዮሐንስ 8:31, 32፤ 14:6፤ 17:3) የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ይህን ሃይማኖት በማግኘትና የዚህንም ሃይማኖት አምላክ በመታዘዝ ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 83:18 ላይ “አንተ ብቻ ስምህ ይሖዋ የሆንከው በመላዋ ምድር የመጨረሻው የበላይ መሆንህን ሰዎች ይወቁ” በማለት ወደዚህ አምላክ ይመራናል።—ኪንግ ጄምስ ቨርሽን
16 ይሁን እንጂ የዘላለሙን አምላክ ስም ማወቅ ብቻውን በቂ አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ስለ ዋና ዋና ባሕርያቱና ዓላማዎቹ ማወቅ ያስፈልገናል። በተጨማሪም በሮሜ 10:9-13 ላይ እንደተገለጸው በዚህ በዘመናችን እንዲፈጸም የሚፈልገውን ፈቃዱን ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ ትንቢቶችን ጠቅሶ “የጌታን [“የይሖዋን፣” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚል መደምደሚያ ሰጥቷል። (ኢዩኤል 2:32፤ ሶፎንያስ 3:9) ይድናል? አዎን፣ ብዙዎች ይድናሉ። ምግባረ ብልሹ በሆነው የሰይጣን ዓለም ላይ በሚፈርድበት ጊዜ በዛሬው ዘመን የሚኖሩ ይሖዋ በክርስቶስ በኩል ባዘጋጀው ቤዛዊ ዝግጅት እጅግ ብዙ ሰዎች ከሚመጣው ታላቅ መከራ ይድናሉ።—ራእይ 7:9, 10, 14
17. አሁን የሙሴንና የበጉን ቅኔ እንድንዘምር የሚያነሣሣን የትኛው ታላቅ ተስፋ ነው?
17 አምላክ ከጥፋቱ እንተርፋለን ብለው ተስፋ ለሚያደርጉ ሰዎች ያለው ፈቃድ ምንድን ነው? አሁንም እንኳን ቢሆን ወደፊት የሚቀዳጀውን ድል እየጠበቅን የዘላለሙን ንጉሥ በማወደስ የሙሴንና የበጉን መዝሙር እንድንዘምር ፈቃዱ ነው። ይህንንም የምናደርገው ክብራማ ስለሆነ ዓላማው ለሌሎች በመናገር ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባለን ማስተዋል እያደግን ስንሄድ ደግሞ ሕይወታችንን ለዘላለሙ ንጉሥ ለመወሰን እንችላለን። ይህም ኃያሉ ንጉሥ በኢሳይያስ 65:17, 18 ላይ እንደሚከተለው በማለት የሚገልጸው ሁኔታ በሚሰፍንበት ምድር ለዘላለም እንድንኖር ያስችለናል። “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና [የኢየሱስን መሲሐዊ መንግሥት] አዲስ ምድር [ጻድቃንን ያቀፈ አዲስ የሰው ልጆች ኅብረተሰብ] እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።”
18, 19. (ሀ)ዳዊት በመዝሙር 145 ላይ የተናገራቸው ቃላት ምን እንድናደርግ ሊገፋፉን ይገባል? (ለ) ይሖዋ የትኛውን ተስፋ እንደሚፈጽምልን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
18 መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም” በማለት ስለ ዘላለሙ ንጉሥ ይገልጻል። (መዝሙር 145:3) ታላቅነቱ እንደ ሕዋና እንደ ጊዜ ዳርቻ የሌለውና የማይመረመር ነው! (ሮሜ 11:33) ስለ ፈጣሪያችንና እርሱ በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ስላዘጋጀው የቤዛ ዝግጅት ያለንን እውቀት እየጨመርን በሄድን መጠን የዘላለሙን ንጉሣችንን ይበልጥ ለማወደስ እንፈልጋለን። መዝሙር 145:11–13 እንደሚገልጸው ለማድረግ እንፈልጋለን። “የመንግሥትን ክብር ይናገራሉ፣ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፣ ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ። መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፣ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።”
19 አምላካችን “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” የሚለውን ተስፋ እንደሚፈጽምልን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። የዘላለሙ ንጉሥ ከእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በርኅራሄና በፍቅር መርቶ ያወጣናል። ዳዊት “እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፣ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል” በማለት ያረጋግጥልናል።—መዝሙር 145:16, 20
20. በመጨረሻዎቹ የመዝሙር መጽሐፍ አምስት ምዕራፎች ላይ የዘላለሙ ንጉሥ ላቀረበው ግብዣ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
20 የመጨረሻዎቹ የመዝሙር መጽሐፍ አምስት ምዕራፎች የተከፈቱትና የተዘጉት “ሃሌ ሉያ” በሚል ግብዣ ነው። መዝሙር 146ም እንዲህ በማለት ይጋብዘናል። “ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፣ እግዚአብሔርን አመስግኚ። በሕይወቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ።” ለዚህ ጥሪ ምላሽ ትሰጣለህን? ይሖዋን ለማወደስ እንደምትፈልጉ አያጠራጥርም! መዝሙር 148:12, 13 “ጎልማሶችና ቆነጃጅቶች፣ ሽማግሌዎችና ልጆች፣ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፣ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፣ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው” በማለት ከገለጻቸው ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃችሁ። ሁላችንም በሙሉ ልባችን “እናንት ሕዝቦች፣ ያህን አመስግኑ” ለሚለው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እንስጥ። ሁላችንም በአንድ ድምፅ የዘላለሙን ንጉሥ እናወድስ!
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ የኢየሱስ ሐዋርያት አስቀድመው ያስጠነቀቁት ምንድን ነው?
◻ ከ1914 ጀምሮ ወሳኝ የሆኑ ምን ድርጊቶች ተፈጽመዋል?
◻ ይሖዋ ወደፊት የሚፈጽማቸው ፍርዶች የትኞቹ ናቸው?
◻ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን የዘላለሙን ንጉሥ ማወደስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከፍተኛ እልቂት የደረሰበት የሁከት ዘመን
የ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ የሁከት ዘመን መባቻ እንደነበረ ብዙዎች አምነዋል። ለምሳሌ ያህል የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዳንኤል ፓትሪክ ሞይንሃን በ1993 ባሳተሙት ፓናዴሞንየም የተባለ መጽሐፍ መቅድም ላይ “በ1914 የደረሰው እልቂት” በሚል ርዕስ በጻፉት ሐተታ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ጦርነት መጣና ዓለም ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። በ1914 የነበሩና እስከ አሁን ድረስ አገዛዛቸው በዓመፅ ሳይገለበጥ የቆዩ መንግሥታት ስምንት ብቻ ናቸው። . . . የቀሩት በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ 170 የሚያክሉ መንግሥታት በጣም በቅርቡ የተቋቋሙ ስለሆኑ ከአሁን በፊት የታዩትን ሁከቶች አልቀመሱም።” በእርግጥም ከ1914 ወዲህ ያለው ዘመን መከራ የተፈራረቀበት ዘመን ነው!
በተጨማሪም በ1993 አውት ኦቭ ኮንትሮል፣ ግሎባል ተርሞይል ኦን ዘ ኢቭ ኦቭ ዘ ትዌንቲ ፈርስት ሴንቸሪ (ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ምድር አቀፍ ሁከት፣ በ21ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ) የተባለ መጽሐፍ ታትሟል። ደራሲው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ኃላፊ የነበሩት ዝብግኒፍ ብርዥንስኪ ሲሆኑ እንዲህ ብለዋል፦ “የሃያኛው መቶ ዘመን መባቻ ብዙ ሰዎች በሰጡት ሐሳብ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚነግሥበት ዘመን ተብሎ ተወድሶ ነበር። . . . ግን እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ሃያኛው መቶ ዘመን ከማንኛውም ዘመን ይበልጥ ደም እንደ ጎርፍ የፈሰሰበት፣ ጥላቻ የነገሠበት፣ ፖለቲካዊ ቅዠትና አሠቃቂ ግድያ የተስፋፋበት ዘመን ሆኗል። የጭካኔ ድርጊት ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን በተደራጀ መልኩ የሚፈጸም ከመሆኑም በላይ የተቀናጀ የጅምላ ጭፍጨፋ ተካሂዷል። የሳይንስ በጎ ውጤት የማስገኘት አቅም ከተፈጸመው ፖለቲካዊ ግፍ ጋር ሲነጻጸር በጣም ያስደነግጣል። የአሁኑን ያህል በመላው ዓለም ግድያ የተስፋፋበት፣ ይህን የሚያክል ሕይወት የተቀጨበት፣ ምክንያታዊ ላልሆኑ ግትር ዓላማዎች ሲባል የሰው ልጅ ሕይወት ሆን ተብሎ የተጨፈጨፈበት ዘመን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ኖሮ አያውቅም።” እውነተኛ አባባል ነው!
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ ሚካኤል ሰይጣንንና ጭፍሮቹን ወደ ምድር ጥሏቸዋል