የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bsi08-2 ገጽ 19-20
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 60—1 ጴጥሮስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 60—1 ጴጥሮስ
  • “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 17
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 17
bsi08-2 ገጽ 19-20

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 60​—⁠1 ጴጥሮስ

ጸሐፊው:- ጴጥሮስ

የተጻፈበት ቦታ:- ባቢሎን

ተጽፎ ያለቀው:- ከ62 እስከ 64 ከክ.ል.በኋላ ገደማ

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የአምላክን በጎነት በሰፊው በማወጃቸው የመንግሥቱ ሥራ እያደገና በመላዋ የሮማ ግዛት እየተስፋፋ ሄደ። ይሁን እንጂ ይህንን ቀናተኛ የክርስቲያኖች ቡድን በተመለከተ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች ነበሩ። በመጀመሪያ ደረጃ ሃይማኖታቸው የመነጨው ከኢየሩሳሌም ማለትም ከአይሁዶች ዘንድ በመሆኑ አንዳንድ ሰዎች ፖለቲከኛ ከሆኑት አክራሪ አይሁዳውያን ጋር አንድ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። የሮማውያን ቀንበር ያስመረራቸው እነዚህ አይሁዳውን አክራሪዎች አካባቢውን ለሚያስተዳድሩት ገዢዎች የጎን ውጋት ሆነውባቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፣ ክርስቲያኖች ለንጉሠ ነገሥቱ መሥዋዕት ለማቅረብ ወይም በዘመኑ በነበሩት አረማዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ለመካፈል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ከሌሎች የተለዩ ነበሩ። በመሆኑም የተቃውሞ ቃላት ይሰነዘርባቸውና በእምነታቸው ምክንያት የተለያየ ፈተና ይደርስባቸው ነበር። ጴጥሮስ እነዚህ ክርስቲያኖች ጸንተው እንዲቆሙ ለማበረታታትና በዘመኑ ቄሣር በነበረው በኔሮ ግዛት እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ ለመምከር ሲል የመጀመሪያ መልእክቱን ጽፏል። ይህ መልእክት በተገቢው ጊዜ የተጻፈና በጥንቃቄ የታሰበበት መሆኑ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ያሳያል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ታላቅ የስደት ማዕበል ስለተነሳ መልእክቱ በእርግጥም እጅግ ወቅታዊ ነበር።

2 በመልእክቱ መክፈቻ ላይ ያለው ሐሳብ ጸሐፊው ጴጥሮስ መሆኑን ያረጋግጣል። ከዚህም በላይ ኢራንየስ፣ የእስክንድርያው ክሌመንት፣ ኦሪጀንና ተርቱሊያን ከዚህ ደብዳቤ ሲጠቅሱ ጸሐፊው ጴጥሮስ መሆኑን ጠቁመዋል።a የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት፣ እንደ ሌሎቹ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ መልእክቶች ሁሉ ትክክለኛነቱ በሚገባ የተረጋገጠ ነው። ዩሲቢየስ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ሽማግሌዎች ደብዳቤውን በነፃነት ይጠቀሙበት እንደነበርና በዚያ ዘመን (ከ260 እስከ 342 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) ስለ መጽሐፉ ትክክለኛነት አንዳችም ጥርጣሬ እንዳልነበር ይነግረናል። በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖሩ የነበሩት ኢግናቲየስ፣ ሄርማስና በርናባስም ከመልእክቱ ጠቅሰው ጽፈዋል።b አንደኛ ጴጥሮስ፣ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ሲሆን በትንሿ እስያ አገሮች ማለትም ‘በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ’ ለነበሩት በመጻተኝነት ለሚኖሩ አይሁዳውያንና አይሁዳዊ ላልሆኑ ክርስቲያኖች ትልቅ መልእክት ያዘለ ደብዳቤ ነበር።—1 ጴጥ. 1:1

3 ደብዳቤው የተጻፈው መቼ ነው? ከመልእክቱ መንፈስ መረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያኖች ከአረማውያን ወይም ክርስትናን ካልተቀበሉት አይሁዳውያን መከራ እየደረሰባቸው ነበር። ይሁንና በ64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተነሳው የኔሮ የስደት ዘመቻ ገና አልጀመረም ነበር። ጴጥሮስ ደብዳቤውን የጻፈው ይህ ስደት ከመነሳቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ምናልባትም ከ62 እስከ 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ እንደሆነ ከሁኔታው በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። በወቅቱ ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር መሆኑ ይህንን ሐቅ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት (ከ59 እስከ 61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) ማርቆስ አብሮት የነበረ ሲሆን ወደ ትንሿ እስያ ለመሄድም በዝግጅት ላይ ነበር። ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በታሠረበት ወቅት ደግሞ (በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) ማርቆስ ወደ ጳውሎስ ተመልሶ ሊሄድ እየተሰናዳ ነበር። (1 ጴጥ. 5:13፤ ቆላ. 4:10፤ 2 ጢሞ. 4:11) በዚህ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር ለመገናኘት ወደ ባቢሎን የመሄድ አጋጣሚ ነበረው።

4 የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት የተጻፈው የት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ስለ መጽሐፉ ትክክለኛነት፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ስለመሆኑ፣ ስለ ጸሐፊው ማንነትና ግምታዊ ቢሆንም እንኳ ስለተጻፈበት ጊዜ ያላቸው አመለካከት ተመሳሳይ ቢሆንም የተጻፈበትን ቦታ አስመልክተው የሚሰጡት ሐሳብ ግን የተለያየ ነው። ጴጥሮስ እንደተናገረው ከሆነ መልእክቱን የጻፈው በባቢሎን ሆኖ ነው። (1 ጴጥ. 5:13) ይሁን እንጂ አንዳንዶች፣ “ባቢሎን” የሮም ምሥጢራዊ ስም ስለነበር መልእክቱን የጻፈው ሮም ሆኖ ነው በማለት ይናገራሉ። ማስረጃው ግን ይህንን አባባል አይደግፍም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ባቢሎን የሚለው መጠሪያ ሮምን ያመለክት እንደነበር የሚጠቁም ነገር የለም። ጴጥሮስ መልእክቱን የላከው ቃል በቃል በጳንጦስና በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንደነበር ሁሉ ባቢሎንንም ሲጠቅስ ቃል በቃል አገሩን ለማመልከት ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። (1:1) ጴጥሮስ በወቅቱ በባቢሎን የሚሆንበት በቂ ምክንያት ነበረው። ‘ለተገረዙት ምሥራቹን እንዲሰብክ’ አደራ ተጥሎበት የነበረ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን ደግሞ በባቢሎን ይኖሩ ነበር። (ገላ. 2:7-9) ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ስለ ባቢሎናውያን ታልሙድ አዘገጃጀት ሲናገር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ “ባቢሎን ውስጥ” ይገኙ ስለነበሩት የአይሁዳውያን “ታላላቅ የትምህርት ተቋማት” ጠቅሷል።c

5 ጴጥሮስ የጻፋቸውን ሁለት መልእክቶች ጨምሮ ቅዱሳን መጻሕፍት ጴጥሮስ ወደ ሮም ስለ መሄዱ የሚናገሩት ነገር የለም። ጳውሎስ በሮም እንደነበር የገለጸ ቢሆንም ጴጥሮስ በዚያ ስለመኖሩ ምንም ያለው ነገር የለም። ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ 35 ስሞችን ሲዘረዝርና 26 የሚሆኑ ሰዎችን በስም ጠቅሶ ሰላምታ ሲልክ ጴጥሮስን ሳይጠቅስ የቀረው ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ጴጥሮስ በወቅቱ በዚያ ስላልነበረ ነው! (ሮሜ 16:3-15) ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልእክቱን የጻፈባት “ባቢሎን” በመስጴጦምያ ባለው በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ትገኝ የነበረችው ባቢሎን እንደነበረች ግልጽ ነው።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

11 የመጀመሪያው የጴጥሮስ መልእክት ለበላይ ተመልካቾች ጠቃሚ ምክር ይዟል። ኢየሱስ በዮሐንስ 21:15-17 ላይ እንዲሁም ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ 20:25-35 ላይ የሰጡትን ምክር በመከተል፣ ጴጥሮስ የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነት የእረኝነት ሥራ መሆኑንና ሥራው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት፣ በፈቃደኝነት መንፈስና በሙሉ ፍላጎት ሊሠራ እንደሚገባ በድጋሚ ገልጿል። አንድ የበላይ ተመልካች፣ “የእረኞች አለቃ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ሆኖ የሚያገለግል የበታች እረኛ ሲሆን የአምላክን መንጋ በሚመለከት በኢየሱስ ፊት ተጠያቂ ነው። እረኛው ለመንጋው ምሳሌ መሆንና የመንጋውን ፍላጎት በትሕትና ማሟላት ይኖርበታል።—5:2-4

12 በጴጥሮስ መልእክት ውስጥ ክርስቲያናዊ ተገዥነትን የሚመለከቱ ሌሎች ዘርፎች የተገለጹ ከመሆኑም ሌላ በዚህ ዙሪያ ግሩም ምክሮች ሰፍረዋል። በ1 ጴጥሮስ 2:13-17 ላይ እንደ ነገሥታትና ገዥዎች ላሉት ባለ ሥልጣናት ተገዥነት ማሳየት እንደሚገባ ምክር ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ተገዥነት ለጌታ ስንል የምናደርገውና ክርስቲያኖች ባሪያ የሆኑለትን ‘አምላክ በመፍራት’ የሚያሳዩት አንጻራዊ ተገዥነት ነው። የቤት ሠራተኞች ለአሳዳሪዎቻቸው እንዲገዙ እንዲሁም ‘በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖራቸው ሲሉ’ መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ችለው እንዲያልፉ ተመክረዋል። ሚስቶችም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸውም ጭምር ለባሎቻቸው መገዛትን በሚመለከት እጅግ ጠቃሚ ምክር ተሰጥቷቸዋል። ንጹሕና አክብሮት የተሞላበት አኗኗራቸው ‘በአምላክ ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ’ እንደሆነና ባሎቻቸውን ወደ እውነት ሊስባቸው እንደሚችል ጠቁሟቸዋል። ጴጥሮስ ይህን ነጥብ ለማጠናከር ሲል ሣራ በታማኝነት ለባሏ ለአብርሃም ያሳየችውን ተገዥነት እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። (1 ጴጥ. 2:17-20 NW፤ 3:1-6፤ ዘፍ. 18:12) ባሎችም እንዲሁ የራስነት ሥልጣናቸውን እንደ “ተሰባሪ ዕቃ” ለሆኑት ሚስቶቻቸው አሳቢነት በማሳየት በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። ጴጥሮስ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ሳይወጣ “ጐልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ከዚያም፣ በመላው መልእክቱ ውስጥ ጎላ ያለ ስፍራ የተሰጣቸውን ራስን ዝቅ የማድረግንና የትሕትናን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።—1 ጴጥ. 3:7-9 NW፤ 5:5-7፤ 2:21-25

13 ጴጥሮስ አስፈሪ ችግሮችና ስደቶች ብቅ ብቅ ማለት በጀመሩበት ጊዜ ጥንካሬ የሚጨምር ማበረታቻ ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ መልእክቱ ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ፈተና ለሚያጋጥማቸው ሁሉ ይህ ነው የማይባል ጠቃሚ ምክር ይዟል። ጴጥሮስ የይሖዋን ቃል በሚጠቅስበት ጊዜ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዴት እንደተጠቀመባቸው ልብ በል:- “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።” (1 ጴጥ. 1:16፤ ዘሌ. 11:44) ከዚያም፣ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ከሌሎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት በብዛት በጠቀሰበት ምዕራፍ ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ በክርስቶስ መሠረት ላይ በሕያዋን ድንጋዮች የተገነባ መንፈሳዊ ቤት የሆነበትን መንገድ አስረድቷል። ይህን ያደረገበት ዓላማ ምን ነበር? ጴጥሮስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2:4-10፤ ኢሳ. 28:16፤ መዝ. 118:22፤ ኢሳ. 8:14፤ ዘፀ. 19:5, 6፤ ኢሳ. 43:21፤ ሆሴዕ 1:10፤ 2:23) ጴጥሮስ ‘የማይጠፋ፣ የማይበላሽና የማይለወጥ ርስት፣’ ‘የማይጠፋ አክሊል’ እንዲሁም ‘በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የመጠራትን’ የመንግሥቱን ተስፋ እንደሚያገኝ የተናገረለት ‘የንጉሥ ካህናት፣’ የአምላክ ቅዱስ ብሔር የሆነው የካህናት ቡድን ነው። እነሱም ‘ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታቸው ታላቅ እንዲሆን’ መደሰታቸውን እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—1 ጴጥ. 1:4፤ 5:4, 10፤ 4:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የማክሊንቶክ እና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ፣ 1981 በድጋሚ የታተመ፣ ጥራዝ VIII ገጽ 15

b ኒው ባይብል ዲክሽነሪ፣ ሁለተኛ እትም፣ 1986 በጄ. ዲ. ዳግላስ የተዘጋጀ፣ ገጽ 918

c ኢየሩሳሌም፣ 1971፣ ጥራዝ 15፣ ዓምድ 755

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ