-
የይሖዋ ቀን ምን ይገልጣል?መጠበቂያ ግንብ—2010 | ሐምሌ 15
-
-
2 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ በቅጽበት ያልፋሉ፤ ሰማያትና ምድር የተሠሩባቸው ንጥረ ነገሮችም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።” (2 ጴጥ. 3:10) እዚህ ላይ “ሰማያት” እና “ምድር” የተባሉት ምንድን ናቸው? የሚቀልጡት “ንጥረ ነገሮች” ምንድን ናቸው? ጴጥሮስ “ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን በቅርቡ ለሚመጣው አስፈሪ ክስተት ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይረዳናል።
የሚያልፉት ሰማያትና ምድር
3. በ2 ጴጥሮስ 3:10 ላይ የተጠቀሱት “ሰማያት” ምንድን ናቸው? የሚያልፉትስ እንዴት ነው?
3 “ሰማያት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት በአብዛኛው የሚያመለክተው ከተገዥዎቻቸው በላይ ከፍ ብለው ያሉትን ገዥዎች ነው። (ኢሳ. 14:13, 14፤ ራእይ 21:1, 2) ‘የሚያልፉት ሰማያት’ ፈሪሃ አምላክ በሌለው ኅብረተሰብ ላይ የሚገዙትን ሰብዓዊ መንግሥታት የሚወክሉ ናቸው። እነዚህ ሰማያት “በነጎድጓድ ድምፅ” ወይም በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት “በታላቅ ድምፅ” የሚያልፉ መሆናቸው ጥፋታቸው ቅጽበታዊ እንደሚሆን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
4. “ምድር” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ምንድን ነው? የሚጠፋውስ እንዴት ነው?
4 “ምድር” የሚለው ቃል ከአምላክ የራቀውን የሰው ዘር ዓለም ይወክላል። በኖኅ ዘመን እንዲህ ያለ ዓለም ነበረ፤ ይህ ዓለም አምላክ ስለፈረደበት በውኃ ጠፍቷል። “በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።” (2 ጴጥ. 3:7) የጥፋት ውኃው ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች በሙሉ ጠራርጎ ያስወገዳቸው በአንድ ጊዜ ሲሆን ወደፊት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት የሚመጣው ጥፋት ግን የሚከሰተው ደረጃ በደረጃ ይሆናል። (ራእይ 7:14) በመጀመሪያ አምላክ፣ በዚህ ዓለም የፖለቲካ ገዥዎች በመጠቀም ‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ያጠፋታል፤ ለዚህች ሃይማኖታዊ ጋለሞታ ያለውን ጥላቻ በዚህ መንገድ ያሳያል። (ራእይ 17:5, 16፤ 18:8) ቀጥሎም በአርማጌዶን ጦርነት ይሖዋ ራሱ የተቀረውን የሰይጣን ዓለም ጠራርጎ ሲያጠፋው ታላቁ መከራ ይደመደማል።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:19-21
‘ንጥረ ነገሮቹ ይቀልጣሉ’
5. “ንጥረ ነገሮች” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ምን ያመለክታል?
5 “ይቀልጣሉ” የተባሉት “ንጥረ ነገሮች” ምንድን ናቸው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ንጥረ ነገሮች” የሚለውን ሐረግ “መነሻ የሆኑ ነገሮች” ወይም “መሠረታዊ ነገሮች” በማለት ይፈታዋል። ይህ ሐረግ “የንግግር ንጥረ ነገር የሆኑትን ፊደላትን” ለማመልከት እንደተሠራበት መዝገበ ቃላቱ ይናገራል። በመሆኑም ጴጥሮስ የጠቀሳቸው “ንጥረ ነገሮች” ይህ ዓለም አምላካዊ ያልሆነ ባሕርይ፣ ዝንባሌ፣ አካሄድና ግብ እንዲኖረው ያደረጉትን መሠረታዊ ነገሮች ያመለክታሉ። እነዚህ “ንጥረ ነገሮች” “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ” ያለውን “የዓለምን መንፈስ” ይጨምራሉ። (1 ቆሮ. 2:12፤ ኤፌሶን 2:1-3ን አንብብ።) ይህ መንፈስ ወይም ‘አየር’ የሰይጣንን ዓለም ሞልቶታል። ይህ መንፈስ፣ ሰዎች ትዕቢተኛና ዓመፀኛ የሆነውን “የአየሩ ሥልጣን ገዥ” ይኸውም የሰይጣንን አመለካከት በሚያንጸባርቅ መንገድ እንዲያስቡ፣ እቅድ እንዲያወጡ፣ እንዲናገሩና እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።
6. የዓለም መንፈስ የሚገለጸው በምን መንገድ ነው?
6 የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ያደረገባቸው ሰዎች፣ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ሰይጣን አእምሯቸውንና ልባቸውን እንዲቀርጸው ስለሚፈቅዱ የእሱን አስተሳሰብና አመለካከት ያንጸባርቃሉ። በዚህም የተነሳ የአምላክን ፈቃድ ችላ በማለት የፈለጉትን ያደርጋሉ። ለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጡት ኩራት ወይም ራስ ወዳድነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው፤ እንዲሁም በሥልጣን ላይ የማመፅ ዝንባሌ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ለሥጋ ምኞትና ለዓይን አምሮት’ ያደሩ ናቸው።—1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።a
7. ‘ልባችንን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?
7 እንግዲያው ከጓደኛ ምርጫ፣ ከምናነባቸው ነገሮች፣ ከመዝናኛ እንዲሁም ኢንተርኔት ላይ ከምንመለከታቸው ድረ ገጾች ጋር በተያያዘ ከአምላክ ቃል በተማርነው መሠረት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ በማድረግ ‘ልባችንን መጠበቃችን’ ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ምሳሌ 4:23) ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት ጽፏል። (ቆላ. 2:8) የይሖዋ ቀን እየቀረበ በመሆኑ ይህን መመሪያ መከተላችን ይበልጥ አጣዳፊ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይህ ቀን የሰይጣንን ሥርዓት “ንጥረ ነገሮች” በሙሉ በኃይለኛ ሙቀት በማቅለጥ የአምላክን ቁጣ ትኩሳት መቋቋም የማይችሉ መሆናቸውን ያጋልጣል። ይህም በሚልክያስ 4:1 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ጥቅስ ያስታውሰናል፦ “እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል።”
“ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ”
8. ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮች ‘የሚጋለጡት’ እንዴት ነው?
8 ጴጥሮስ “ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ” በማለት ሲጽፍ ምን ማለቱ ነበር? የሰይጣን ዓለም ይሖዋንና መንግሥቱን ስለሚቃወም ጥፋት የሚገባው መሆኑን አምላክ በታላቁ መከራ ወቅት እንደሚያጋልጥ መግለጹ ነበር። ይህንን ጊዜ በተመለከተ በኢሳይያስ 26:21 ላይ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሯል፦ “በምድር ላይ የሚኖረውን ሕዝብ ስለ ኀጢአቱ ለመቅጣት፣ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያው ወጥቶ ይመጣል፤ ምድር በላይዋ የፈሰሰውን ደም ትገልጣለች፤ የተገደሉትንም ከእንግዲህ አትሸሽግም።”
9. (ሀ) ምን ነገሮችን ማስወገድ ይኖርብናል? ለምንስ? (ለ) የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብናል? ለምንስ?
9 ዓለምና ክፉ የሆነው የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሰዎች በይሖዋ ቀን እርስ በርስ በመገዳደል ጭምር እውነተኛ ማንነታቸውን ይገልጣሉ። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ዓመፅ የሞላባቸው በርካታ መዝናኛዎች የብዙዎችን አእምሮ በመቅረጽ ‘አንዱ ሌላውን ለሚወጋበት’ ለዚያ ቀን እያዘጋጇቸው ያሉ ይመስላል። (ዘካ. 14:13) እንግዲያው አምላክ የሚጠላቸውን እንደ ኩራትና ዓመፅን መውደድ ያሉ ዝንባሌዎች እንድናዳብር ሊያደርጉን የሚችሉ ፊልሞችን፣ መጻሕፍትን፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችንና እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ ማስወገዳችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (2 ሳሙ. 22:28፤ መዝ. 11:5) ከዚህ በተቃራኒ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆኑትን ባሕርያት እናዳብር፤ ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያት በይሖዋ ቀን የሚኖረውን ምሳሌያዊ ትኩሳት መቋቋም ይችላሉ።—ገላ. 5:22, 23
-
-
የይሖዋ ቀን ምን ይገልጣል?መጠበቂያ ግንብ—2010 | ሐምሌ 15
-
-
ለይሖዋ ታላቅ ቀን ተዘጋጁ
12. የይሖዋ ቀን ለዓለም ዱብ እዳ የሚሆንበት ለምንድን ነው?
12 ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ የይሖዋ ቀን የሚመጣው “እንደ ሌባ” ይኸውም ሳይታሰብ በድንገት እንደሆነ አስቀድመው ተናግረዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:1, 2ን አንብብ።) ይህን ቀን ለሚጠብቁ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንኳ ቀኑ ድንገተኛ ይሆናል። (ማቴ. 24:44) ለዚህ ዓለም ግን ቀኑ ድንገተኛ ከመሆን ባለፈ የሚያስከትለው ነገር አለ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ከይሖዋ የራቁ ሰዎች] ‘ሰላምና ደኅንነት ሆነ!’ ሲሉ የምጥ ጣር እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።”—1 ተሰ. 5:3
-