የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 9/15 ገጽ 16-20
  • ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላካዊ ባሕርያት የግድ አስፈላጊ ናቸው
  • “ከእኔ ጋር ማን ነው?”
  • ለእውነተኛው አምልኮ የተሰጠ ልባዊ ድጋፍ
  • አስደናቂ የሆነ ክንውን ከፊታችን ይጠብቀናል!
  • የኤልሳዕ ዓይነት ቅንዓት በመያዝ ማገልገል
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ኤልሳዕ የእሳት ሠረገሎችን አይቷል አንተስ ይታዩሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • የራስን ጥቅም የመሰዋትና በታማኝነት የመጣበቅ ምሳሌ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • የይሖዋ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 9/15 ገጽ 16-20

‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?

“የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?”​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​11, 12

1. በኤልያስ መንፈስና ኃይል የሚሠሩት እነማን ናቸው?

ይሖዋ አምላክ ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ተባባሪ ገዥ የሚሆኑትን ሰዎች ከሰው ዘር መካከል መርጧል። (ሮሜ 8:​16, 17) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና በምድር እያሉም በኤልያስ መንፈስና ኃይል ይሠራሉ። (ሉቃስ 1:​17) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሚያከናውኗቸው ተግባራትና ነቢዩ ኤልያስ ባከናወናቸው ነገሮች መካከል ያሉትን አንዳንድ ተመሳሳይ ነገሮች በመጀመሪያው የጥናት ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ ኤልያስን የተካው ነቢዩ ኤልሳዕ ስላከናወናቸው ሥራዎችስ ምን ለማለት ይቻላል?​—⁠1 ነገሥት 19:​15, 16

2. (ሀ) ኤልያስ የፈጸመው የመጨረሻ ተአምር ምን ነበር? ኤልሳዕ የፈጸመው የመጀመሪያ ተአምርስ? (ለ) ኤልያስ ወደ ሰማይ እንዳልሄደ ምን የሚያረጋግጥ ነገር አለ?

2 ኤልያስ በመጎናጸፊያው የዮርዳኖስን ወንዝ መትቶ ለሁለት በመክፈል የመጨረሻውን ተአምር ፈጽሟል። ይህም ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ መሬት እንዲሻገሩ አስችሏቸዋል። በወንዙ ምሥራቃዊ ዳርቻ እየተጓዙ ሳለ ኃይለኛ ነፋስ ኤልያስን ወደ ሌላ የምድር ክፍል ወሰደው። (“ኤልያስ የተነጠቀው ወደየትኛው ሰማይ ነው?” በሚል ርዕስ ገጽ 15 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ኤልያስ መጎናጸፊያውን ትቶ ሄዶ ነበር። ኤልሳዕ በዚህ መጎናጸፊያ ዮርዳኖስን ወንዝ በመታ ጊዜ ውኃው እንደገና ለሁለት ተከፈለና በደረቅ መሬት ተመልሶ ለመሻገር ቻለ። ኤልሳዕ በእስራኤል እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት በኤልያስ እግር የተተካ መሆኑን ይህ ተአምር ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነበር።​—⁠2 ነገሥት 2:​6-15

አምላካዊ ባሕርያት የግድ አስፈላጊ ናቸው

3. ጳውሎስና ጴጥሮስ የኢየሱስን መገኘትና ‘የይሖዋን ቀን’ በማስመልከት ምን ብለዋል?

3 ኤልያስና ኤልሳዕ ከኖሩበት ዘመን ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ መጪውን ‘የይሖዋ ቀን’ ከክርስቶስ መገኘትና ከዚያም ቀጥሎ ከሚመጣው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ጋር አያይዘው ጠቅሰዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:​1, 2፤ 2 ጴጥሮስ 3:​10-13) አምላክ ጠላቶቹን በሚያጠፋበትና ሕዝቦቹን በሚያድንበት ጊዜ ከታላቁ የይሖዋ ቀን በሕይወት ለመትረፍ ይሖዋን መፈለግ እንዲሁም ገርነትንና ጽድቅን ማንጸባረቅ ይገባናል። (ሶፎንያስ 2:​1-3) ይሁን እንጂ ከነቢዩ ኤልሳዕ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች በምንመረምርበት ጊዜ አንዳንድ ተጨማሪ ባሕርያትን እናገኛለን።

4. ቅንዓት በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ምን ሚና ይጫወታል?

4 ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ለመትረፍ ለአምላክ አገልግሎት ቅንዓት ማሳየት እጅግ አስፈላጊ ነው። ኤልያስና ኤልሳዕ ለይሖዋ አገልግሎት ቀናተኞች ነበሩ። ቀሪዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ቅንዓት በማሳየት፣ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብና ምሥራቹን በግንባር ቀደምትነት በመስበክ ላይ ይገኛሉ።a ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉና በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው እንዲጠመቁ ሲያበረታቱ ቆይተዋል። (ማርቆስ 8:​34፤ 1 ጴጥሮስ 3:​21) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚህ ማበረታቻ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ በኃጢአት ሞተው ነበሩ። አሁን ግን የአምላክን እውነት ተምረዋል፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አግኝተዋል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ቀናተኞች ናቸው። (መዝሙር 37:​29፤ ራእይ 21:​3-5) በሚያሳዩት ቅንዓት፣ ትብብር፣ እንግዳ ተቀባይነትና በሌሎች ጥሩ ሥራዎች ምድር ለቀሩት ለክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች ትልቅ የማበረታቻ ምንጭ ሆነውላቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 25:​31-46

5. ለኢየሱስ “ወንድሞች” መልካም ነገሮችን ማድረግ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በኤልሳዕ ዘመን የተፈጸመ የትኛው ምሳሌ አለን?

5 እነዚህ ቅቡዓን የኢየሱስ ተከታዮች መሆናቸውን በማወቅ ለኢየሱስ “ወንድሞች” መልካም የሚያደርጉ ሁሉ ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት የመትረፍ ተስፋ አላቸው። በሱነም ይኖሩ የነበሩ አንድ ባልና ሚስት ለኤልሳዕና ለአገልጋዩ የደግነትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየታቸው በእጅጉ ተባርከዋል። እነዚህ ባልና ሚስት ልጅ አልነበራቸውም፤ ባልየውም በዕድሜ ገፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ ኤልሳዕ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ለሱናማዊቷ ሴት ቃል ገባላት። ልክ እንዳለውም ተፈጸመ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይህ ልጅ በሞተ ጊዜም ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሄዶ ከሞት አስነሳው። (2 ነገሥት 4:​8-17, 32-37) ለኤልሳዕ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየታቸው ምንኛ ተባርከዋል!

6, 7. ንዕማን ምን ምሳሌ ትቷል? ይህስ ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ከመትረፍ ጋር ምን ዝምድና አለው?

6 ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት የመትረፍ ተስፋ በመያዝ ከክርስቶስ “ወንድሞች” መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ለመቀበል ትሕትና አስፈላጊ ነው። የሶርያውያን የጦር አዛዥ የነበረው ለምፃሙ ንዕማን በምርኮ ተወስዳ የነበረችው አንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ያቀረበችውን ሐሳብ ለመቀበልና ኤልሳዕ እንዲፈውሰው ወደ እስራኤል ለመሄድ ትሕትና ማሳየት ነበረበት። ኤልሳዕ ከቤቱ ወጥቶ ንዕማንን ከመቀበል ይልቅ “በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፣ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ” የሚል መልእክት ላከበት። (2 ነገሥት 5:​10) ንዕማን ክብሩ ስለ ተነካ በጣም ተቆጣ። ሆኖም ትሕትና በማሳየት ዮርዳኖስ ውስጥ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ካለ በኋላ “ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፣ ንጹሕም ሆነ።” (2 ነገሥት 5:​14) ንዕማን ወደ ቤቱ ከመመለሱ በፊት የይሖዋን ነቢይ ለማመስገን ረዥም መንገድ ተጉዞ ወደ ሰማርያ ሄደ። ኤልሳዕ አምላክ በሰጠው ኃይል ቁሳዊ ኃብት ላለማትረፍ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ንዕማንን ሊቀበለው ከቤቱ ወጣ፤ ሆኖም ምንም ዓይነት ስጦታ አልተቀበለም። ንዕማን በትሕትና “እኔ ባሪያህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብም” በማለት ለኤልሳዕ ነገረው።​—⁠2 ነገሥት 5:​17

7 በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቅቡዓን የሚሰጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በትሕትና በመከተላቸው በብዙ ተባርከዋል። ከዚህም በላይ እነዚህ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳየት በመንፈሳዊ ነጽተዋል። አሁን የይሖዋ አምላክና የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች የመሆን መብት በማግኘት እየተደሰቱ ነው። (መዝሙር 15:​1, 2፤ ሉቃስ 16:​9) እንዲሁም ለአምላክና ለአገልግሎቱ ከፍተኛ ፍቅር ማሳየታቸው ከፊታችን እየገሰገሰ በመምጣት ላይ ያለው ‘የይሖዋ ቀን’ በትዕቢተኞችና ንስሐ በማይገቡ ኃጢአተኞች ላይ ዘላለማዊ ጥፋት በሚያደርስበት ጊዜ በሕይወት እንዲተርፉ ያደርጋቸዋል።​—⁠ሉቃስ 13:​24፤ 1 ዮሐንስ 1:​7

“ከእኔ ጋር ማን ነው?”

8. (ሀ) ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት የሚተርፉ ሁሉ መለኮታዊውን ፈቃድ በማድረግ በኩል እንዴት ያለ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) ኢዩ ምን ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር? (ሐ) በኤልዛቤል ላይ ምን ነገር ሊደርስባት ነው?

8 ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ለመትረፍ ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ መለኮታዊውን ፈቃድ ለማድረግ ቆራጥ መሆን አለባቸው። ኤልያስ ነፍሰ ገዳይና የበኣል አምላኪ የሆነው የአክዓብ ቤተሰብ እንደሚጠፋ በድፍረት ትንቢት ተናግሯል። (1 ነገሥት 21:​17-26) ይህ ፍርድ ከመፈጸሙ በፊት ግን በኤልያስ እግር የተተካው ኤልሳዕ ሊፈጽማቸው የሚገቡ አንዳንድ ያላለቁ ሥራዎች ነበሩ። (1 ነገሥት 19:​15-17) ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኤልሳዕ ኢዩ የተባለውን የጦር አለቃ የእስራኤል አዲስ ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው አንድ ሎሌ ላከ። መልእክተኛው በኢዩ ራስ ላይ ዘይት ካፈሰሰ በኋላ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ። የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፣ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። የአክዓብም ቤት ሁሉ ይጠፋል” አለው። ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል ለውሾት ትጣላለች እንጂ በሥርዓት አትቀበርም።​—⁠2 ነገሥት 9:​1-10

9, 10. ኤልዛቤልን በሚመለከት ኤልያስ የተናገረው ቃል ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

9 ከኢዩ ጋር የነበሩት ሰዎች የሱን መቀባት በመቀበል የእስራኤል አዲስ ንጉሥ መሆኑን አወጁ። ኢዩ የበኣል አምልኮ ከሃዲ በሆኑት ቀንደኛ መሪዎች ላይ የፍርድ እርምጃውን ለመውሰድ ፈጥኖ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። ኢዩ በመጀመሪያ የፍርድ ኢላማውን ማነጣጠር የፈለገው በአክዓብ ልጅ በንጉሥ ኢዮራም ላይ ነበር። ኢዮራምም ኢዩ የመጣው የሰላም መልእክት ይዞ መሆኑን ለመጠየቅ ከከተማ እየጋለበ ወጣ። “የእናትህ የኤልዛቤል ግልሙትናዋና መተትዋ ሲበዛ ምን ሰላም አለ?” በማለት ኢዩ መለሰለት። ይህንንም ብሎ በቀስት ወጋው፤ ቀስቱም የኢዮራምንም ልብ በስቶ ወጣ።​—⁠2 ነገሥት 9:​22-24

10 አምላካዊ የሆኑ ሴቶች በማንኛውም መልኩ ኤልዛቤልን ከመምሰል ይቆጠባሉ። (ራእይ 2:​18-23) ኢዩ ኢይዝራኤል በደረሰ ጊዜ ኤልዛቤል ማራኪ ሆና ለመታየት ሙከራ አድርጋ ነበር። በመስኮት ቁልቁል እየተመለከተች በምጸት አነጋገር ሰላምታ ሰጠችው። “ከእኔ ጋር ማን ነው?” በማለት ጃንደረቦቿን ጠየቀ። ወዲያውም ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ወደ ታች ተመለከቱ። ከኢዩ ጎን ይቆሙ ይሆን? “ወደታች ወርውሩአት” በማለት ቆጣ ብሎ ተናገረ። ወዲያውም ክፉዋን ኤልዛቤልን በመስኮት በመወርወር ያለምንም ማወላወል እርምጃ ወሰዱ። ፈረሶቹ ኮቴ አጠገብ ሳይሆን አይቀርም ተፈጠፈጠች። አሷን ለመቅበር ሰዎች በመጡ ጊዜ ‘ከጭንቅላቷ፣ ከእግሯና ከመዳፏ በስተቀር ምንም አላገኙም።’ ኤልያስ “የኤልዛቤልን ሥጋ ውሾች ይበላሉ” በማለት ለተናገረው ቃል እንዴት ያለ አስደናቂ ፍጻሜ ነበር!​—⁠2 ነገሥት 9:​30-37

ለእውነተኛው አምልኮ የተሰጠ ልባዊ ድጋፍ

11. ኢዮናዳብ ማን ነበር? ለእውነተኛው አምልኮ የነበረውን ድጋፍ ያሳየው እንዴት ነበር?

11 ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ተርፈው በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ እውነተኛውን አምልኮ በሙሉ ልብ መደገፍ አለባቸው። ኢዮናዳብ ወይም ዮናዳብ የተባለውን እስራኤላዊ ያልሆነ የይሖዋ አምላኪ መምሰል አለባቸው። ኢዩ ተልእኮውን በቅንዓት መፈጸሙን በቀጠለ ጊዜ ኢዮናዳብ ለኢዩ የነበረውን አድናቆትና ድጋፍ ለመግለጽ ፈለገ። የአክዓብን ቤት ርዝራዦች ለመበቀል ወደ ሰማሪያ ይሄድ የነበረውን አዲሱን የእስራኤል ንጉሥ ለመገናኘት ወጣ። ኢዩ ኢዮናዳብን ሲያየው “ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?” በማለት ጠየቀው። የኢዮናዳብ አዎንታዊ ምላሽ ኢዩ እጁን እንዲዘረጋና የጦር ሰረገላው ላይ እንዲወጣ ኢዮናዳብን እንዲጋብዝ ገፋፋው። “ከእኔ ጋር ና፣ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ አለው።” ምንም ሳይዘገይ ለተቀባው የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ድጋፍ ማሳየቱን እንደ መብት አድርጎ ተቀበለ።​—⁠2 ነገሥት 10:​15-17

12. ይሖዋ እርሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

12 ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ የሆነው ይሖዋ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲሰጠው የሚፈልግና የእኛም አምልኮ የሚገባው በመሆኑ ለእውነተኛው አምልኮ ከልብ የመነጨ ድጋፍ መስጠት ተገቢ ነው። እስራኤላውያንን “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም” በማለት አዝዟቸው ነበር። (ዘጸአት 20:​4, 5) ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ለመትረፍ የሚፈልጉ ሁሉ እርሱን ብቻ ማምለክ አለባቸው። ይህንንም “በእውነትና በመንፈስ” ማድረግ አለባቸው። (ዮሐንስ 4:​23, 24) እንደ ኤልያስ፣ እንደ ኤልሳዕና እንደ ኢዮናዳብ ለእውነተኛ አምልኮ የጸና አቋም መያዝ አለባቸው።

13. የኢዮናዳብ ልብ ከኢዩ ጋር እንደነበረ ሁሉ መሲሐዊውን ንጉሥ ከልብ የሚቀበሉት እነማን ናቸው? ይህንንስ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

13 የአክዓብ ቤት ፈጽሞ ከጠፋ በኋላ ንጉሥ ኢዩ የበኣል አምላኪዎችን ማንነት ለይቶ ለማወቅና ይህን የሐሰት አምልኮ ከእስራኤል ጠራርጎ ለማጥፋት ሌሎች ተከታታይ እርምጃዎችን ወሰደ። (2 ነገሥት 10:​18-28) ዛሬ ሰማያዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ ጠላቶች ላይ ፍርድ እንዲያስፈጽምና የይሖዋን ልዕልና እንዲያረጋግጥ ተሹሟል። የኢዮናዳብ ልብ ከኢዩ ጋር እንደነበረ ሁሉ የኢየሱስ ሌሎች በጎች የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስ መሲሐዊ ንጉሥ መሆኑን ከልብ በመቀበል በምድር ላይ ካሉት ከእርሱ መንፈሳዊ ወንድሞች ጋር ይተባበራሉ። (ራእይ 7:​9, 10፤ ዮሐንስ 10:​16) ይህንንም ለማረጋገጥ እውነተኛውን ሃይማኖት በመተግበርና በክርስቲያናዊ አገልግሎት በቅንዓት በመካፈል በፍጥነት እየቀረበ በመምጣት ላይ ያለውን ‘የይሖዋ ቀን’ ለአምላክ ጠላቶች ያስጠነቅቃሉ።​—⁠ማቴዎስ 10:​32, 33፤ ሮሜ 10:​9, 10

አስደናቂ የሆነ ክንውን ከፊታችን ይጠብቀናል!

14. የሐሰት ሃይማኖት ወደፊት ምን ይጠብቀዋል?

14 ኢዩ በእስራኤል የነበረውን የበኣል አምልኮ ለማጥፋት እርምጃ ወስዷል። በጊዜያችንም በታላቁ ኢዩ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አምላክ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ጥፋት ያመጣል። መልአኩ ለሐዋርያው ዮሐንስ የነገረውን ቃል ፍጻሜ በቅርቡ እናያለን። “ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን [ታላቁቱ ባቢሎንን] ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል። እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና።” (ራእይ 17:​16, 17፤ 18:​2-5) “አሥሩ ቀንዶች” በምድር ላይ የሚገኙትን ወታደራዊ የፖለቲካ ኃይላትን ያመለክታሉ። በአሁኑ ጊዜ ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር መንፈሳዊ ግልሙትና እየፈጸሙ ያሉ ቢሆንም ጊዜዋ ተሟጦ አልቋል። እነዚህ የዓለም የፖለቲካ ኃይላት የሐሰት ሃይማኖትን ይደመስሳሉ፤ “አሥሩ ቀንዶች” እርሷን በሚያጠፉበት ጊዜ “አውሬው” ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትልቁን ሚና ይጫወታል።b ያ ጊዜ ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችል እንዴት ያለ አስደሳች ወቅት ይሆናል!​—⁠ራእይ 19:​1-6

15. የአምላክን ምድራዊ ድርጅት ለማጥፋት ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ ምን ነገር ይከናወናል?

15 ንጉሡ ኢዩ በበኣል አምልኮ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ሥረወ መንግሥቱ ትኩረቱን በእስራኤል ፖለቲካዊ ጠላቶች ላይ አነጣጠረ። ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል። በኣል መሰል የሆነው የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ የፖለቲካ ኃይላት ይቀራሉ። እነዚህ የይሖዋ ልዕልና ጠላቶች በሰይጣን ዲያብሎስ ገፋፊነት የአምላክን ምድራዊ ድርጅት ለመደምሰስ አጠቃላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። (ሕዝቅኤል 38:​14-16) ይሁን እንጂ ይሖዋ በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ‘በታላቁ ሁሉን በሚችለው አምላክ ጦርነት’ ማለትም በአርማጌዶን እንዲደመሰሱ በማድረግ ሉዓላዊነቱን ያረጋግጣል።​—⁠ራእይ 16:​14, 16፤ 19:​11-21፤ ሕዝቅኤል 38:​18-23

የኤልሳዕ ዓይነት ቅንዓት በመያዝ ማገልገል

16, 17. (ሀ) ኤልሳዕ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ቅንዓት እንደነበረው እንዴት እናውቃለን? (ለ) በእውነት ቀስት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ‘የይሖዋ ቀን’ የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እስኪያመጣ ድረስ የአምላክ አገልጋዮች እንደ ኤልሳዕ ደፋሮችና ቀናተኞች ይሆናሉ። ኤልሳዕ የኤልያስ ሎሌ ሆኖ ያገለገለበት ጊዜ ሳይቆጠር የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ብቻውን አገልግሏል! እንዲሁም ኤልሳዕ ረዥሙ የሕይወት ዘመኑ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ጊዜ ቅንዓቱ አልደበዘዘም ነበር። ልክ ሊሞት ሲል የኢዩ የልጅ ልጅ ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ መጥቶ ነበር። በመስኮት በኩል ቀስት እንዲወነጭፍ ኤልሳዕ ነገረው። ቀስቱ ዒላማውን በመምታቱ ኤልሳዕ “የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያውያንን በአፌቅ ትመታለህ” በማለት ተናገረ። በኤልሳዕ አሳሳቢነት ዮአስ መሬቱን በቀስት መታው። ሆኖም ይህን ያደረገው ቅንዓት በጎደለው መንገድ ስለነበር መሬቱን የመታው ሦስት ጊዜ ብቻ ነበር። በዚህም የተነሳ ዮአስ በሶርያ ላይ ድል የሚቀዳጀው ሦስት ጊዜ ብቻ እንደሚሆን ኤልሳዕ ተናገረ። የሆነውም ልክ እንደዚሁ ነበር። (2 ነገሥት 13:​14-19, 25) ንጉሥ ዮአስ “እስኪያጠፋቸው ድረስ” ሶርያውያንን አልመታም።

17 ቅቡዓን ቀሪዎች እንደ ኤልሳዕ ዓይነት ቅንዓት በመያዝ ከሐሰት አምልኮ ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ ተያይዘውታል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ጓደኞቻቸውም ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ነው። ከዚህም በላይ ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ለመትረፍ ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ኤልሳዕ ምድሩን በቅንዓት ስለመምታት ከተናገራቸው ቃላት ልብ ሊሏቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ሁላችንም የእውነትን የጦር ዕቃ በመያዝ አዎን፣ ይሖዋ እነርሱን በመጠቀም የምንሠራው ሥራ ፍጻሜውን ማግኘቱን እስከሚነግረን ድረስ ደግመን ደጋግመን በቅንዓት ለመምታት እንጠቀምባቸው።

18. ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:​11, 12 ላይ ለሰፈሩት ቃላት የምንሰጠው ምላሽ እንዴት ያለ መሆን ይገባዋል?

18 ‘የይሖዋ ቀን’ ይህን የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ ያስወግደዋል። ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ በተናገራቸው ልብ በሚነኩ ቃላት ንቁዎች እንሁን። “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል።” (2 ጴጥሮስ 3:​11, 12) የዚህ ሥርዓት ክፍል በጠቅላላ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በአምላክ የቁጣ ትኩሳት ሲቀልጥ ትክክለኛ ምግባርና ለአምላክ የማደር መንፈስ እንዳላቸው የተመሰከረላቸው ብቻ ይተርፋሉ። ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና መያዝ የግድ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም በክርስቲያን አገልግሎታችን በኩል በመንፈሳዊ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት ለመሰል የሰው ልጆች ያለንን ፍቅር እናሳይ።

19. ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ለመትረፍ ምን ማድረግ አለብን?

19 በቃልም ሆነ በድርጊት አምላክን በታማኝነትና በቅንዓት እያገለገልክ እንዳለህ እያሳየህ ነውን? ከሆነ ‘የይሖዋን ቀን’ በሕይወት አልፈህ አምላክ ቃል ወደገባው አዲስ ዓለም የመግባት ተስፋ ሊኖርህ ይችላል። አዎን፣ ሱናማዊቷ መበለት ኤልሳዕን በእንግድነት እንደተቀበለችው ሁሉ የእርሱ ተከታዮች በመሆናቸው ምክንያት ለክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች መልካም የምታደርግ ከሆነ አንተም በሕይወት ልትተርፍ ትችላለህ። በሕይወት ለመትረፍ መለኮታዊ መመሪያን በትህትና ተቀብሎ የይሖዋ አምላኪ የሆነውን ንዕማንን መምሰል አለብህ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የምትናፍቅ ከሆነ ኢዮናዳብ እንዳደረገው እውነተኛውን አምልኮ ከልብ የምትደግፍ መሆንህን ማሳየት አለብህ። እንዲህ ካደረግህ “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ከሚያዩት ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መካከል አንዱ ልትሆን ትችላለህ።​—⁠ማቴዎስ 25:​34

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን “ስምህ ይቀደስ” (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 18ንና 19ን ተመልከት።

b በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ—⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 254-6 ተመልከት።

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት ለማለፍ የሚረዱ አንዳንድ ባሕርያት ምንድን ናቸው?

◻ በኤልሳዕ ዘመን በሱነም ይኖሩ የነበሩ ባልና ሚስት ምን ምሳሌ ትተዋል?

◻ ከንዕማን ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

◻ የኢዮናዳብን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

◻ ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:​11, 12 እንዴት ሊነካን ይገባል?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ