-
ጋይዮስ ወንድሞቹን የረዳበት መንገድመጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017 | ግንቦት
-
-
አስቸጋሪውን ሁኔታ እንዲቋቋም የተሰጠ እርዳታ
ዮሐንስ ለጋይዮስ ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሳሳው እሱን ለማመስገን ብቻ አይደለም። ጋይዮስ ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲወጣ ሊረዳው ስለፈለገም ጭምር ነው። ዲዮጥራጢስ የተባለው የጉባኤው አባል ተጓዥ ክርስቲያኖችን በእንግድነት ለመቀበል አልፈለገም ነበር፤ ይህን ያደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም። ዲዮጥራጢስ፣ ሌሎችም እንግዶችን እንዳይቀበሉ ለመከላከል ይሞክር ነበር።—3 ዮሐ. 9, 10
ታማኝ ክርስቲያኖች አጋጣሚው ቢኖራቸውም እንኳ ዲዮጥራጢስ ጋ ማረፍ እንደማይፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ዲዮጥራጢስ በጉባኤው ውስጥ የመሪነት ቦታ ለመያዝ የሚፈልግ ከመሆኑም በላይ ከዮሐንስ የመጣ ማንኛውንም ነገር በአክብሮት አይቀበልም ነበር፤ በተጨማሪም ስለ ሐዋርያውና ስለ ሌሎች ክፉ ቃላት ይለፈልፍ ነበር። ዮሐንስ፣ ዲዮጥራጢስን ሐሰተኛ አስተማሪ ብሎ በቀጥታ ባይጠራውም ዲዮጥራጢስ የሐዋርያውን ሥልጣን እየተቃወመ እንደነበር ግልጽ ነው። ዲዮጥራጢስ፣ ትልቅ ቦታ ለማግኘት የነበረው ፍላጎትና ከክርስቲያኖች የማይጠበቅ አመለካከት መያዙ በታማኝነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር። የዲዮጥራጢስ ሁኔታ፣ ሥልጣን ለማግኘት የሚመኙና ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎች በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ዮሐንስ “መጥፎ የሆነውን ነገር አትከተል” በማለት ለጋይዮስ የሰጠው ምክር ለሁላችንም ይሠራል።—3 ዮሐ. 11
-
-
ጋይዮስ ወንድሞቹን የረዳበት መንገድመጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017 | ግንቦት
-
-
ሁለተኛ፣ በጉባኤ ውስጥ ያለውን ሥልጣን የማይቀበሉ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢነሱ መገረም አይኖርብንም። የሐዋርያው ዮሐንስን ሥልጣን የማያከብሩ ሰዎች ነበሩ፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞታል። (2 ቆሮ. 10:7-12፤ 12:11-13) እኛስ በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶት ነበር፦ “የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቁ የሆነና በደል ሲደርስበት ራሱን የሚገዛ፣ እንዲሁም ቀና አመለካከት የሌላቸውን በገርነት የሚያርም ሊሆን ይገባዋል።” የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥመንም እንኳ የገርነት መንፈስ ማሳየታችንን ከቀጠልን ነቃፊ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ውሎ አድሮ አመለካከታቸውን ሊያስተካክሉ ይችላሉ። ይሖዋም “ትክክለኛ የእውነት እውቀት ያገኙ ዘንድ ለንስሐ ያበቃቸው ይሆናል።”—2 ጢሞ. 2:24, 25
-