-
‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
-
-
ሄኖክ ‘ስለ እነዚህ ሰዎች ተንብዮአል’
ሄኖክ እምነት በሌለው ዓለም ውስጥ የእምነት ሰው ሆኖ ሲኖር ብቸኝነት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። አምላኩ ይሖዋስ ሄኖክን ተመልክቶት ይሆን? አዎ። አንድ ቀን ይሖዋ ይህን ታማኝ አገልጋዩን አነጋገረው። ሄኖክ በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች አንድ መልእክት እንዲያስተላልፍ አምላክ ተልእኮ ሰጠው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ሄኖክን ነቢይ አድርጎ ላከው፤ በመሆኑም መልእክታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ከሚገኙ ነቢያት መካከል ሄኖክ የመጀመሪያው ነው። ይህን ማወቅ የቻልነው የኢየሱስ ወንድም የሆነው ይሁዳ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ፣ ሄኖክ ስለተናገረው ትንቢት በመንፈስ መሪነት በመጻፉ ነው።a
ሄኖክ የተናገረው ትንቢት ምን ነበር? ትንቢቱ እንዲህ የሚል ነበር፦ “እነሆ! ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።” (ይሁዳ 14, 15) እዚህ ላይ ሄኖክ ትንቢቱን የተናገረው ልክ እንደተፈጸመ ማለትም አምላክ በትንቢቱ ላይ የተገለጸውን ነገር እንደፈጸመ አድርጎ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። ሌሎች በርካታ ትንቢቶችም የተጻፉት በዚህ መንገድ ነው። ነቢዩ፣ ገና ያልተፈጸመን ነገር እንደተፈጸመ አድርጎ የተናገረው ትንቢቱ መፈጸሙ እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ስለሆነ ነው።—ኢሳይያስ 46:10
ሄኖክ በጥላቻ ይመለከተው ለነበረው ማኅበረሰብ የአምላክን የፍርድ መልእክት በድፍረት አውጇል
ሄኖክ ይህን የፍርድ መልእክት ሲያውጅ ወይም እያዳመጡት ላሉ ሰዎች ሲሰብክ ምን ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው ይመስልሃል? የማስጠንቀቂያ መልእክቱ በጣም ኃይለኛ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው” እንደሆኑ የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ ድርጊታቸው ‘ለአምላክ አክብሮት የሌለው’ እና ‘ክፉ’ እንደሆነ ይናገራል። ትንቢቱ የሰው ልጆች ከኤደን ከተባረሩ በኋላ የገነቡት ዓለም ሙሉ በሙሉ ብልሹ መሆኑን የሚገልጽ ነው። በወቅቱ የነበረው ዓለም፣ ይሖዋ ለጦርነት ከተሰለፉትና ኃያላን ከሆኑት “አእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ” ጋር በሚመጣበት ጊዜ ከባድ ጥፋት ይጠብቀው ነበር። ሄኖክ ይህን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በድፍረት አውጇል፤ ያውም ብቻውን! በወቅቱ ወጣት የነበረው ላሜህ አያቱ ያሳየውን ድፍረት በመገረም ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ሄኖክ ያሳየው ድፍረት የሚያስገርም ነበር።
ሄኖክ ስላሳየው እምነት መመርመራችን እኛም ለምንኖርበት ዓለም ያለን አመለካከት አምላክ ካለው አመለካከት ጋር ተመሳሳይ መሆን አለመሆኑን ቆም ብለን እንድናስብ ያነሳሳን ይሆናል። ሄኖክ በድፍረት ያወጀው የፍርድ መልእክት በዚያ ዘመን ለነበረው ዓለም ያስፈልግ እንደነበረ ሁሉ አሁን ላለንበት ዓለምም አስፈላጊ ነው። ሄኖክ በተናገረው ማስጠንቀቂያ መሠረት ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበረውን ፈሪሃ አምላክ የሌለው ዓለም በውኃ አጥፍቶታል። በዚያን ወቅት የተከሰተው ጥፋት ወደፊት ለሚመጣው ይበልጥ ታላቅ የሆነ ጥፋት ምሳሌ ሆኗል። (ማቴዎስ 24:38, 39፤ 2 ጴጥሮስ 2:4-6) አምላክ በዚያ ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ፈሪሃ አምላክ በሌለው በዚህ ዓለም ላይ የጽድቅ ፍርዱን ለማስፈጸም ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ነው። እያንዳንዳችን ሄኖክ ያወጀውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት እንዲሁም ይህን ማስጠንቀቂያ ለሌሎች መናገር ያስፈልገናል። እርግጥ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ከእኛ የተለየ አቋም ይይዙ ይሆናል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ሄኖክን እንዳልተወው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም!
-
-
‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
-
-
a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን፣ ይሁዳ ይህን ሐሳብ የወሰደው መጽሐፈ ሄኖክ ከሚባል አንድ የአዋልድ መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይህ የአዋልድ መጽሐፍ ምንጩ ያልታወቀና እውነት የማይመስሉ ታሪኮችን የያዘ ከመሆኑም ሌላ ሄኖክ እንደጻፈው ተደርጎ መነገሩ ሐሰት ነው። መጽሐፉ የሄኖክን ትንቢት በትክክል የሚጠቅስ ቢሆንም ይህ ሐሳብ የተወሰደው አሁን ከጠፋ ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ ወይም በቃል ሲተላለፍ ከቆየ ታሪክ ሊሆን ይችላል። ይሁዳም ይህን ትንቢት ያገኘው ከተመሳሳይ ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ የሄኖክን ሕይወት ከሰማይ ሆኖ የተመለከተው ኢየሱስ ነግሮት ሊሆን ይችላል።
-