-
የኢየሱስን ስም አጥብቆ መያዝራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
‘የተሰወረ መና እና ነጭ ድንጋይ’
17. ድል የሚነሱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ሽልማት ይጠብቃቸዋል? የጴርጋሞን ክርስቲያኖች ምን ነገር ማሸነፍ ያስፈልጋቸዋል?
17 በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አመራር የሚሰጠውን የኢየሱስ ምክር የሚከተሉ ሁሉ ታላቅ ሽልማት ይጠብቃቸዋል። እስቲ አድምጥ:- “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፣ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፣ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።” (ራእይ 2:17) ስለዚህ በጴርጋሞን የነበሩት ክርስቲያኖችም በሰምርኔስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች ‘ድል እንዲነሱ’ ማበረታቻ ተሰጥቶአቸዋል። የሰይጣን ዙፋን በነበረበት በጴርጋሞን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ድል ለመንሳት ከፈለጉ ከጣዖት አምልኮ መራቅ ነበረባቸው። ከባላቅ፣ ከበለዓምና ከኒቆላውያን ትምህርት ጋር ግንኙነት የነበረውን የሴሰኝነት፣ የመናፍቅነትና የክህደት መንፈስ ማሸነፍ ነበረባቸው። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ካደረጉ ‘ከተሰወረው መና’ እንዲበሉ ይጋበዛሉ። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?
18, 19. (ሀ) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ይሰጣቸው የነበረው መና ምን ነበር? (ለ) የተሰወረውስ መና ምን ነበር? (ሐ) የተሰወረውን መና መብላት የምን ምሳሌ ነው?
18 ይሖዋ በሙሴ ዘመን እሥራኤላውያንን በምድረ በዳ ጉዞአቸው በሕይወት ለማቆየት መና መግቦአቸው ነበር። በሰንበት ቀን ካልሆነ በስተቀር በየጠዋቱ ሁልጊዜ ደቃቅ ውርጭ የሚመስል ቅርፊት ይታይ ስለነበር ይህ መና የተሰወረ አልነበረም። የእስራኤላውያንን ሕይወት ለመጠበቅ የተደረገ መለኮታዊ ዝግጅት ነበር። ይሖዋም ‘በእሥራኤል ትውልድ ሁሉ’ ለመታሰቢያ እንዲሆን ከዚህ መና ወስዶ በወርቅ ማሰሮ ውስጥ እንዲጨምርና በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ እንዲያስቀምጥ ሙሴን አዝዞት ነበር።—ዘጸአት 16:14, 15, 23, 26, 33፤ ዕብራውያን 9:3, 4
19 ይህ በጣም ተስማሚ የሆነ ምሳሌ ነበር። ይህ መና ለይሖዋ መገኘት ምሳሌ የሆነው ተአምራዊ ብርሃን ከታቦቱ በላይ ሆኖ ይበራ በነበረበት ቅድስተ ቅዱሳን በተባለው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ውስጥ ተደብቆ ነበር። (ዘጸአት 26:34) ማንም ሰው ወደዚህ ቅዱስ ሥፍራ እንዲገባና ከተሰወረው መና እንዲበላ አይፈቀድለትም ነበር። ኢየሱስ ግን ድል ያደረጉ ቅቡዓን ተከታዮቹ ከተሰወረው መና እንደሚበሉ ተናግሮአል። ክርስቶስ ከእነርሱ በፊት እንዳደረገው “በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት” ሳይሆን ወደ ሰማይ ይገባሉ። (ዕብራውያን 9:12, 24) ከሙታን በሚነሱበት ጊዜ ያለመበስበስንና ያለመሞትን ባሕርይ ይወርሳሉ። ይህም አስደናቂ የሆነ የይሖዋ ዝግጅት የማይበላሸውን “የተሰወረ መና” በመቀበላቸው ተመስሎአል። እነዚህ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት ድል ነሺዎች በጣም ታላቅ የሆነ መብት ያገኛሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:53-57
20, 21. (ሀ) ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ነጭ ጠጠር መስጠት የምን ምሳሌ ነው? (ለ) የነጮቹ ጠጠሮች ብዛት 144, 000 ብቻ ስለሆነ እጅግ ብዙ ሰዎች ያላቸው ተስፋ ምንድን ነው?
20 በተጨማሪም እነዚህ ድል አድራጊዎች “ነጭ ድንጋይ” ይቀበላሉ። በሮማ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ውሣኔ ሲሰጥ በጠጠር መጠቀም የተለመደ ነበር።b ነጭ ጠጠር ነጻ መሆንን የሚያመለክት ሲሆን ጥቁር ጠጠር ደግሞ ጥፋተኛ ነህ የሚል ፍርድ፣ አብዛኛውን ጊዜ የሞትን ፍርድ ያመለክት ነበር። ኢየሱስ በጴርጋሞን ለነበሩት ክርስቲያኖች “ነጭ ድንጋይ” [ወይም “ጠጠር፣” NW] መስጠቱ ንፁሕ፣ ነቀፋና ነውር የሌለባቸው ናቸው ብሎ እንደፈረደላቸው ያመለክታል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ቃል ሌላም ተጨማሪ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በሮማውያን ዘመን ጠጠር በጣም ታላቅ ወደሆነ ዝግጅት እንደሚያስገባ ቲኬት ሆኖ ያገለግል ነበር። ስለዚህ አንድ ድል አድራጊ ቅቡዕ ክርስቲያን ነጭ ጠጠር መቀበሉ በበጉ ሠርግ ጊዜ በሰማይ ላይ ልዩ የክብር ቦታ እንዲያገኝ የመፈቀዱን በጣም ልዩ የሆነ መብት ሊያመለክት ይችላል። የእነዚህ ጠጠሮች ወይም ድንጋዮች ብዛት 144, 000 ብቻ ነው።—ራእይ 14:1፤ 19:7-9
21 ታዲያ አንተ የቅቡዓኑ ተባባሪ አምላኪዎች የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ከሆንክ ጨርሶ ተጥለሃል ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። ወደ ሰማይ የሚያስገባው ነጭ ድንጋይ ባይሰጥህም ጸንተህ ከቆምክ ከታላቁ መከራ አልፈህ ገነትን በምድር ላይ መልሶ ለመመሥረት በሚደረገው አስደሳች ሥራ ልትካፈል ትችላለህ። በዚህም ሥራ ከሙታን የሚነሱት ከክርስትና በፊት የነበሩ ታማኝ ሰዎችና በቅርብ ጊዜያት የሞቱ የሌሎች በጎች ክፍል አባላት የሆኑ ሰዎች አብረውህ ይካፈላሉ። የክርስቶስ ቤዛ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች በየተራ ከሙታን ተነስተው በመጨረሻ ሁሉም በገነቲቱ ምድር የመኖር ዕድል ያገኛሉ።—መዝሙር 45:16 የ1980 ትርጉም፤ ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9, 14
22, 23. ለቅቡዓን ክርስቲያኖች በሚሰጠው ጠጠር ላይ የተጻፈው ስም ትርጉም ምንድን ነው? ይህስ እንዴት ያለ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል?
22 በድንጋዩ ላይ የተጻፈው አዲስ ስም ምንድን ነው? ስም አንድ ሰው የሚታወቅበትና ከሌሎች የሚለይበት ነገር ነው። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጠጠሩን የሚቀበሉት ምድራዊ ሥራቸውን በድል አድራጊነት ከጨረሱ በኋላ ነው። ስለዚህ በጠጠሩ ላይ ያለው ስም በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የመሆን መብታቸውን የሚያመለክት ነገር መሆን ይኖርበታል። ይህም መብት ሰማያዊውን መንግሥት የሚወርሱት ብቻ የሚያውቁትና የሚቀበሉት በጣም ልዩ የሆነ ቅርርብ ያለበት የቅዱስ አገልግሎት ደረጃ ነው። ስለዚህ ‘ከሚቀበለው በስተቀር ማንም የማያውቀው’ ስም ወይም የማዕረግ ስያሜ ነው።—ከራእይ 3:12 ጋር አወዳድር።
23 ይህም የዮሐንስ ክፍል የሆኑት “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን” እንዲሰሙና በሥራ እንዲያውሉ የሚያነሳሳቸው እንዴት ያለ ጠንካራ ምክንያት ነው! በተጨማሪም ባልንጀሮቻቸው የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ አብረዋቸው እስካሉ ድረስ ከእነርሱ ጋር በመተባበር በታማኝነት እንዲያገለግሉና የይሖዋን መንግሥት በማሳወቁ ሥራ እንዲካፈሉ የሚገፋፋቸው ጠንካራ ምክንያት ነው።
-
-
የኢየሱስን ስም አጥብቆ መያዝራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
[በገጽ 45 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ጥቂት መና ተደብቆ ነበር። ድል ለነሱት ቅቡዓን የተሰወረ መና መሰጠቱ ያለመሞትን ባሕርይ እንደሚወርሱ ያመለክታል
[በገጽ 45 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነጩ ድንጋይ የሚሰጠው ወደ በጉ ሠርግ እንዲገቡ ለተፈቀደላቸው ነው
-