-
እጅግ ብዙ ሰዎችራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
ምዕራፍ 20
እጅግ ብዙ ሰዎች
1. ዮሐንስ የ144,000ዎቹን መታተም ከገለጸ በኋላ የትኛውን ሌላ ቡድን ተመለከተ?
ዮሐንስ ስለ 144,000ዎቹ መታተም ከገለጸ በኋላ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት በጣም አስደናቂ ራእዮች አንዱ የሆነውን ራእይ ያቀርብልናል። ይህንን አስደናቂ ትዕይንት በሚተርክልን ጊዜ ልቡ በደስታ ሳይፈነድቅ አልቀረም። “ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ።” (ራእይ 7:9) አዎ፣ የአራቱ ነፋሳት መገታት ከ144,000ዎቹ የመንፈሳዊ እስራኤል አባሎች ለተለዩ የሰዎች ክፍል መዳንን አስገኝቶአል። ባለ ብዙ ቋንቋ የሆነ ዓለም አቀፍ የብዙ ሰዎች ጭፍራ ከጥፋት እንዲድን አስችሎአል።a—ራእይ 7:1
2. ዓለማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ስለ እጅግ ብዙ ሰዎች እንዴት በማለት ገልጸዋል? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ቢሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት እነዚህን ሰዎች እንዴት ይመለከቱአቸው ነበር?
2 ዓለማውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ክርስትና የተመለሱ ሥጋዊ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው ወይም ወደ ሰማይ የሚሄዱ ክርስቲያን ሰማዕታት ናቸው ብለዋል። ቀደም ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንኳን እነዚህ ሰዎች ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ሰማያዊ ክፍሎች ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። ይህም እምነታቸው በ1886 በታተመው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት፣ መለኮታዊው የዘመናት እቅድ በተባለው መጽሐፍ አንደኛ ጥራዝ ላይ ተገልጾአል:- “የዙፋንና መለኮታዊ ባሕርይ የመልበስ ሽልማት ባያገኙም ከመለኮታዊው ባሕርይ ያነሰ መንፈሳዊ ልጅነት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ቢሆኑም በዓለም መንፈስ ስለሚሸነፉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ አልቻሉም።” በ1930 እንኳን ብርሃን በተባለው መጽሐፍ ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ተገልጾ ነበር:- “የዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች የጌታ ቀናተኛ ምሥክሮች እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥሪ መቀበል ተስኖአቸዋል።” የእውነት እውቀት ቢኖራቸውም ይህን እውነት ለመስበክ ምንም ጥረት ያላደረጉና ራሳቸውን ያጸደቁ ሰዎች ክፍል እንደሆኑ ተገልጾ ነበር። ከክርስቶስ ጋር አብሮ የመንገሥ መብት የማይሰጣቸው ባለ ሁለተኛ ደረጃ ማዕረግ ሆነው ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱ ይታመን ነበር።
3. (ሀ) በኋላ በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት ላሳዩ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የነበራቸው ሰዎች ምን ተስፋ ተገልጾላቸው ነበር? (ለ) በ1923 ወጥቶ የነበረው መጠበቂያ ግንብ የኢየሱስን የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ምን በማለት አብራርቶ ነበር?
3 ይሁን እንጂ በኋለኞቹ ጊዜያት በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት ያሳዩ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ተባባሪ የሆኑ ሰዎች ብቅ ብለዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ የመሄድ ምኞት የላቸውም። ተስፋቸው የይሖዋ ሕዝቦች ከ1918 እስከ 1922 በተከታታይ ያሰሙ ከነበረው የሕዝብ ንግግር ርዕስ ጋር የተስማማ ነበር። በመጀመሪያ ላይ የዚህ ንግግር ርዕስ “የዓለም መጨረሻ ሆኖአል፣ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል ነበር።b ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የጥቅምት 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ስለ ኢየሱስ የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ትርጉም ሲያብራራ (ማቴዎስ 25:31-46) እንዲህ ብሎአል:- “በጎቹ በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሳይሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት በአእምሮአቸው የሚቀበሉትን እንዲሁም በኢየሱስ ግዛት ሥር የሚገኘውን ጥሩ ኑሮ የሚናፍቁትንና ተስፋ የሚያደርጉትን ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ያመለክታሉ።”
4. ስለ ምድራዊው ክፍል የተገኘው ዕውቀት በ1931 በይበልጥ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው? በ1932 እና በ1934ትስ?
4 ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1931 የወጣው መቀደስ አንደኛ መጽሐፍ የተባለው መጽሐፍ ስለ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 9 ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ የዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ ከጥፋት እንዲተርፉ በግምባራቸው ላይ ምልክት የሚደረግባቸው ሰዎች ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ ውስጥ የተገለጹት በጎች እንደሆኑ ገልጾአል። በ1932 የወጣው መቀደስ ሶስተኛ መጽሐፍ ደግሞ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ኢዩ የሐሰት ሃይማኖትን ሲያጠፋ የሚኖረውን ቅንዓት ለማየት ተከትሎት ስለሄደው ስለ ኢዮናዳብ ገልጾ ነበር። ኢዮናዳብ እስራኤላዊ ያልነበረና ቅን ልብ የነበረው ሰው ነበር። (2 ነገሥት 10:15-17) መጽሐፉ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር:- “ኢዮናዳብ የኢዩ ሥራ [የይሖዋን ፍርድ የማወጅ ሥራ] በሚከናወንበት በዚህ ዘመን በምድር ላይ የሚኖሩትን በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች፣ ከሰይጣን ድርጅት ፈጽሞ የተለዩትን ሰዎች፣ በጽድቅ ጎን የተሰለፉትን ሰዎች ያመለክታል ወይም ይወክላል። ጌታ በአርማጌዶን ጊዜ ከጥፋቱና ከመከራው ጠብቆ በማውጣት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ለእነዚህ ሰዎች ነው። ‘የበጎቹ’ ክፍል የሚሆኑት እነዚህ ሰዎች ናቸው።” በ1934 መጠበቂያ ግንብ እነዚህ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው መጠመቅ እንደሚኖርባቸው ገለጸ። ይህን ምድራዊ ክፍል በሚመለከት የፈነጠቀው ብርሃን ይበልጥ እየበራ ሄደ።—ምሳሌ 4:18
5. (ሀ) በ1935 እጅግ ብዙ ሰዎች ምን እንደሆኑ ታወቀ? (ለ) በ1935 ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ተሰብሳቢዎች ሁሉ ብድግ እንዲሉ በጠየቀ ጊዜ ምን ሆነ?
5 በራእይ 7:9-17 ላይ የተገኘው ዕውቀት በሙሉ ድምቀቱና ውበቱ ግልጽ ሆኖ የሚታይበት ጊዜ ደረሰ። (መዝሙር 97:11) የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 3, 1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ ዩ ኤስ ኤ ሊደረግ የታቀደው ስብሰባ በኢዮናዳብ ክፍል ለተመሰሉት ሁሉ ከፍተኛ ጥቅምና ማጽናኛ እንደሚያስገኝ በተደጋጋሚ ገልጾ ነበር። በእርግጥም ከፍተኛ ጥቅምና ማጽናኛ አስገኝቶአል። በዚያን ጊዜ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ 20,000 ለሚያክሉ ተሰብሳቢዎች “ታላቁ ሕዝብ” በሚል ርዕስ ባደረገው ቀስቃሽ ንግግር የዘመናችን ሌሎች በጎች በራእይ 7:9 ላይ ከተጠቀሱት እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር አንድ እንደሆኑ የሚገልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አቅርቦአል። ተናጋሪው በንግግሩ መጨረሻ ላይ “በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ” አለ። ከአድማጮቹ መካከል በጣም ብዙ የሆኑት ብድግ ባሉ ጊዜ ፕሬዚደንቱ “እነሆ፣ ታላቁ ሕዝብ” አለ። ለጥቂት ጊዜ ፍጹም ጸጥታ ከሆነ በኋላ እንደ ነጎድጓድ የሚያስተጋባ የደስታ ጭብጨባ ተሰማ። የዮሐንስ ክፍል የሆኑትም ሆነ የኢዮናዳብ ቡድን ምንኛ ተደስተው ነበር! በሚቀጥለው ቀን 840 የሚያክሉ አዳዲስ ምሥክሮች ተጠመቁ። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል እንደሆኑ የሚናገሩ ነበሩ።
የእጅግ ብዙ ሰዎችን ማንነት ማረጋገጥ
6. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ራሳቸውን የወሰኑ ዘመናዊ የክርስቲያኖች ቡድን ናቸው ብለን ለማመን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የእጅግ ብዙ ሰዎች ነጭ ልብስ ምን ያመለክታል?
6 እጅግ ብዙ ሰዎች በአምላክ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ናቸው ብለን በእርግጠኝነት ለመናገር የምንችለው ለምንድን ነው? ቀደም ሲል ዮሐንስ ‘ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ’ ሁሉ ለአምላክ የተዋጁትን የሰማይ ክፍል አባሎች በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 5:9, 10) እጅግ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ አመጣጥ ቢኖራቸውም የመጨረሻ ዕጣቸው የተለየ ነው። ቁጥራቸውም ቢሆን እንደ አምላክ እስራኤል አባሎች አስቀድሞ የተወሰነ አይደለም። ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚሆን በቅድሚያ ሊያውቅ የሚችል ሰው የለም። ልብሳቸው በበጉ ደም ታጥቦ ነጭ ሆኖአል። ይህም በኢየሱስ መስዋዕት በማመናቸው ምክንያት በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም ማግኘታቸውን ያመለክታል። (ራእይ 7:14) በተጨማሪም የዘንባባ ዝንጣፊ እያወዛወዙ መሲሑ ንጉሣቸው መሆኑን በይፋ በማወጅ ላይ ናቸው።
7, 8. (ሀ) የዘንባባ ዝንጣፊ ማወዛወዙ ዮሐንስን የትኛውን ጊዜ አስታውሶት ሊሆን ይችላል? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ማወዛወዛቸው ምን ትርጉም አለው?
7 ዮሐንስ ይህን ራእይ በተመለከተበት ጊዜ ሐሳቡ ከ60 ዓመታት በፊት ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት የመጨረሻ ሳምንት ወደ ሆነው ነገር ሳይወስደው አልቀረም። ኒሳን 9 ቀን 33 እዘአ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ሊቀበሉት በተሰበሰቡ ጊዜ “የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና ሆሣዕና በጌታ [“በይሖዋ፣” NW] ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ ይጮሁ ነበር። (ዮሐንስ 12:12, 13) እጅግ ብዙ ሰዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የዘንባባ ዝንጣፊ እያወዛወዙ መጮሃቸው ይሖዋ የሾመውን የኢየሱስን ንግሥና ሲቀበሉ የተሰማቸውን ገደብ የለሽ ደስታ ያመለክታል።
8 የዘንባባው ዝንጣፊና የእልልታው ጩኸት ዮሐንስን የጥንቶቹ እስራኤሎች ያከብሩት የነበረውን የዳስ በዓል አስታውሶት እንደነበረ አያጠራጥርም። ይሖዋ ስለዚህ በዓል የሚከተለውን ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። “በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የሰሌን ቅርንጫፍ፣ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፣ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ።” የዘንባባ ወይም የሰሌን ዝንጣፊ የደስታ ምልክት ሆኖ ያገለግል ነበር። ጊዜያዊ የነበሩት ዳሶች ደግሞ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ አውጥቶ በምድረ በዳ በድንኳን ውስጥ እንዳኖራቸው የሚያሳስቡ ናቸው። በዚህ በዓል “መጻተኛ፣ ድሃ አደግና መበለትም” መካፈል ነበረባቸው። መላው እስራኤል ደስተኛ መሆን ነበረበት።—ዘሌዋውያን 23:40፤ ዘዳግም 16:13-15
9. እጅግ ብዙ ሰዎች በየትኛው የእልልታ ጩኸት ይተባበራሉ?
9 ስለዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች የመንፈሳዊ እስራኤል ክፍል ባይሆኑም እንኳን ድል አድራጊነትና ማዳን የአምላክና የበጉ እንደሆነ በደስታና በአመስጋኝነት ስለሚናገሩ የዘንባባ ዝንጣፊ ማወዛወዛቸው ተገቢ ነው። ይህንንም ዮሐንስ በራእይ ተመልክቶአል:- “በታላቅ ድምፅ እየጮሁ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” (ራእይ 7:10) እጅግ ብዙ ሰዎች ከተለያዩ ነገዶችና ጎሣዎች የተውጣጡ ቢሆኑም የሚጮሁት በአንድ “ታላቅ ድምፅ” ብቻ ነው። የተለያየ ቋንቋና ብሔር እያላቸው በአንድ ድምፅ ለመጮህ የቻሉት እንዴት ነው?
10. እጅግ ብዙ ሰዎች በብሔርና በቋንቋ የተለያዩ ቢሆኑም በአንድ ድምፅ ሊጮሁ የቻሉት እንዴት ነው?
10 እጅግ ብዙ ሰዎች በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ሕብረትና አንድነት ያለው ከልዩ ልዩ ብሔራት የተውጣጣ ድርጅት ክፍል ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሚኖሩባቸው አገሮች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓት ይጠብቃሉ እንጂ እንደየአገሩ የሚለያይ የአቋም ደረጃ አያወጡም። በብሔራዊና አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች አይካፈሉም። ‘ሠይፋቸውን ማረሻ አድርገው ቀጥቅጠዋል።’ (ኢሳይያስ 2:4) በተለያዩ ኑፋቄዎችና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የተከፋፈሉ ስላልሆኑ እንደ ሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች እርስበርሱ የሚቃረን ወይም የተምታታ መልእክት አያሰሙም። ደመወዝተኛ ቀሳውስት እነርሱን ወክለው አምላክን እንዲያወድሱላቸው አያደርጉም። ሦስትነት በአንድነት ያለው የሥላሴ አምላክ ባሪያዎች ስላልሆኑ ማዳን የመንፈስ ቅዱስ ነው ብለው አይጮሁም። በምድር ዙሪያ ከ200 በሚበልጡ ጂኦግራፊያዊ ክልሎች በአንዱ የእውነት ንጹሕ ልሳን እየተናገሩ በአንድ ድምፅ የይሖዋን ስም ይጠራሉ። (ሶፎንያስ 3:9) መዳን የሚመጣላቸው የመዳን አምላክ ከሆነው ከይሖዋና የእርሱ የመዳን ዋና ወኪል ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በሕዝብ ፊት ማሳወቃቸው የተገባ ነው።—መዝሙር 3:8፤ ዕብራውያን 2:10
11. ዘመናዊው ቴክኖሎጂ እጅግ ብዙ ሰዎች ድምፃቸውን በጣም ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ የረዳቸው እንዴት ነው?
11 ዘመናዊው ቴክኖሎጂ በአንድነት እጅግ ብዙ ሰዎች የሚያሰሙት ድምፅ ይበልጥ ጎልቶ እንዲሰማ አስችሎአል። ለሰዎች ሁሉ አንድነት ያለው መልእክት ለማዳረስ ፍላጎት ያለው ሌላ የሃይማኖት ድርጅት ስለሌለ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማዘጋጀት ያስፈለገው አንድም ሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት በምድር ላይ የለም። ለዚህም ሥራ አጋዥ እንዲሆን በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር ክፍል ቅቡዓን አባሎች የበላይ ቁጥጥር ሥር (ሜፕስ) የተባለ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ለኅትመት የሚያስፈልጉ ቅጂዎችን የሚያዘጋጅ የኮምፒተር ፕሮግራም ተዘጋጅቶአል። ይህ መጽሐፍ እስከ ታተመበት ጊዜ ድረስ በምድር ዙሪያ በሚገኙ ከ125 በሚበልጡ ቦታዎች የተለያዩ ዓይነት የሜፕስ ፕሮግራሞች በሥራ ላይ ውለዋል። ይህም መጠበቂያ ግንብ የተባለው በየሁለት ሣምንት የሚወጣ መጽሔት በአንድ ጊዜ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታትሞ እንዲወጣ አስችሏል። በተጨማሪም የይሖዋ ሕዝቦች እንደዚህ መጽሐፍ ያሉትን የተለያዩ መጻሕፍት በአንድ ጊዜ በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅተው ያወጣሉ። በዚህ መንገድ በአብዛኛው እጅግ ብዙ ሰዎች የሚገኙበት የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት በየዓመቱ በታወቁት ቋንቋዎች በሙሉ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ጽሑፎችን ለማሰራጨት ችለዋል። ይህም ከነገድና ከቋንቋ የተውጣጡ ተጨማሪ ብዙ ሰዎች የአምላክን ቃል አጥንተው ድምፃቸውን ከእጅግ ብዙ ሰዎች ድምፅ ጋር እንዲያስተባብሩ አስችሎአል።—ኢሳይያስ 42:10, 12
በሰማይ ወይስ በምድር?
12, 13. እጅግ ብዙ ሰዎች ‘በዙፋኑና በበጉ ፊት የቆሙት’ በምን መንገድ ነው?
12 እጅግ ብዙ ሰዎች “በአምላክ ዙፋን ፊት” መቆማቸው ወደ ሰማይ መሄዳቸውን የሚያመለክት አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን? ይህን ጉዳይ ግልጽ የሚያደርግልን ብዙ ማስረጃ አለ። ለምሳሌ ያህል እዚህ ላይ “ፊት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ኤኖፕዮን) ቃል በቃል ትርጉሙ “ትይዩ” ማለት ሲሆን በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በይሖዋ “ፊት” ወይም በይሖዋ “ትይዩ” መቆማቸውን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:21፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:14፤ ሮሜ 14:22፤ ገላትያ 1:20) አንድ ጊዜ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ሙሴ ለአሮን “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ፊት ቅረቡ በል” ብሎት ነበር። (ዘጸአት 16:9) በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ በይሖዋ ፊት እንዲቆሙ ወደ ሰማይ መወሰድ አላስፈለጋቸውም። (ከዘሌዋውያን 24:8 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ እዚያው በምድረ በዳ እንዳሉ በይሖዋ ለመታየት ቆሙ። ይሖዋም ትኩረቱን ወደ እነርሱ አዞረ።
13 በተጨማሪም እንዲህ እናነባለን:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ . . . አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ።”c ይህ ትንቢት በሚፈጸምበት ጊዜ መላው የሰው ዘር በሰማይ ይሆናል ማለት አይደለም። “ወደ ዘላለም ቅጣት” የሚሄዱት ሰዎችም ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 25:31-33, 41, 46) ከዚህ ይልቅ መላው የሰው ልጅ በምድር ላይ ሆኖ በኢየሱስ ትይዩ ይቆማል። ኢየሱስም ትኩረቱን ወደ ሰው ልጆች በማዞር ይዳኛቸዋል። እጅግ ብዙ ሰዎችም በተመሳሳይ በይሖዋና በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚታዩበት ቦታ ሆነው ጥሩ ፍርድ ሲፈረድላቸው “በዙፋኑና በበጉ ፊት” ይቆማሉ።
14. (ሀ) ‘በዙፋኑ ዙሪያና’ በሰማያዊቱ ‘የጽዮን ተራራ’ እንዳሉ የተነገረላቸው እነማን ናቸው? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት “በመቅደሱ” መሆኑ እነርሱን የካህናት ክፍል የማያደርጋቸው ለምንድን ነው?
14 24ቱ ሽማግሌዎችና 144,000ዎቹ ቅቡዓን በይሖዋ ዙፋን ዙሪያና በሰማያዊቱ “የጽዮን ተራራ” ላይ እንዳሉ ተገልጾአል። (ራእይ 4:4፤ 14:1) እጅግ ብዙ ሰዎች የክህነት ሹመት ስለሌላቸው ይህን ከፍተኛ ቦታ አያገኙም። እርግጥ ነው በራእይ 7:15 ላይ “በመቅደሱ” እንደሚያገለግሉት ተገልጾአል። ይሁን እንጂ ይህ መቅደስ የውስጠኛውን ቅድስተ ቅዱሳን አያመለክትም። የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ነው። እዚህ ላይ “መቅደስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ናኦስ ሲሆን ለይሖዋ አምልኮ የቆመውን ሕንጻና ቅጥር በሙሉ ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜ ይህ መቅደስ ሰማይንና ምድርን የሚያጠቃልል መንፈሳዊ ሕንጻ ነው።—ከማቴዎስ 26:61፤ ከማቴዎስ 27:5, 39, 40፤ ከማርቆስ 15:29, 30ና ከዮሐንስ 2:19-21 ባለማጣቀሻው አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ጋር አወዳድር።
-
-
እጅግ ብዙ ሰዎችራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
-