ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡ እጅግ ብዙ ሰዎች
“በመቅደሱ ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡለታል።”—ራእይ 7:15 አዓት
1. በ1935 በመንፈሳዊ ማስተዋል ረገድ ምን አዲስ ምዕራፍ ላይ ተደረሰ?
ግንቦት 31, 1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ የይሖዋ ምሥክሮች ባዘጋጁት የወረዳ ስብሰባ ላይ የተገኙ ተሰብሳቢዎች በደስታ ተፍለቅልቀው ነበር። በዚያ ስብሰባ በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹት እጅግ ብዙ ሰዎች ማንነት ከተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር በሚስማማ መንገድና በወቅቱ እየተከሰቱ ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር በሚጣጣም መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ተብራርቶ ነበር።
2. ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ብዙ ሰዎች አምላክ ለሰማያዊ ሕይወት እንዳልጠራቸው ተገንዝበው እንደነበረ ያመለከተው ምንድን ነው?
2 ይህ ከመሆኑ ከስድስት ሳምንታት በፊት በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በተከናወነው የጌታ ራት በዓል ላይ ከተገኙት ሰዎች መካከል 10,681 የሚሆኑት (ከ6 ሰዎች 1ዱ ማለት ይቻላል) ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን አልተካፈሉም፤ ከእነዚህም መካከል 3,688ቱ የአምላክን መንግሥት ለማወጅ በትጋት ይሠሩ ነበር። ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ከመካፈል የታቀቡት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኙት ትምህርት መሠረት አምላክ ለሰማያዊ ሕይወት እንዳልጠራቸው፣ ከዚህ ይልቅ በሌላ መንገድ ከይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅቶች መጠቀም እንደሚችሉ ስለተገነዘቡ ነው። ስለዚህ በዚያ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተናጋሪው “በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላችሁ ሁሉ፣ እስቲ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ” ብሎ ሲናገር ምን ሆነ? በሺህዎች የሚቆጠሩ ብድግ አሉ፤ አድማጮቹም ረዘም ላለ ጊዜ በማጨብጨብ በጋለ የደስታ ስሜት ድጋፋቸውን ገለጹላቸው።
3. እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ተለይተው መታወቃቸው ለመስክ አገልግሎት ትኩስ ጉልበት የሰጠው ለምንድን ነው? ምሥክሮቹ ስለዚህ ጉዳይ የተሰማቸው እንዴት ነበር?
3 በዚያ ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ያገኙት ትምህርት ለአገልግሎታቸው ትኩስ ጉልበት ሰጣቸው። አሮጌው ሥርዓት ከማብቃቱ በፊት በአሁኑ ጊዜ በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ ሳይሆኑ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ገነት በምትሆን ምድር ላይ የሚኖረውን ዘላለማዊ ሕይወት በመጠባበቅ ይሖዋ ለሕይወት መዳን ባዘጋጀው ዝግጅት መታቀፍ የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሚከፈትላቸው ተገነዘቡ። ለእውነት አፍቃሪዎች በዚያ ቦታ የቀረበው መልእክት ምንኛ ልብን በደስታ የሚያስፈነድቅ ነበር! የይሖዋ ምሥክሮች አስደሳች የሆነ ገና ብዙ ሥራ እንዳለ ተገንዝበው ነበር። ከጊዜ በኋላ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ቡዝ ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ “ያ ትልቅ ስብሰባ በጣም እንድንደሰት አድርጎን ነበር” በማለት ያስታውሳል።
4. (ሀ) ከ1935 ጀምሮ የእጅግ ብዙ ሰዎች መሰባሰብ እስከ ምን ደረጃ ድረስ ቀጥሏል? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች ሕያው እምነት እንዳላቸው እያሳዩ ያሉት በምን መንገድ ነው?
4 በተከታዮቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ ጨመረ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙውን ጊዜ ጭካኔ የተሞላበት ከባድ ስደት ይደርስባቸው የነበረ ቢሆንም በአሥር ዓመት ውስጥ ቁጥራቸው ሦስት እጥፍ ገደማ አድጎ ነበር። እንዲሁም በ1935 በሕዝብ ፊት ምሥክርነት ይሰጡ የነበሩት 56,153 አስፋፊዎች በ1994 ቁጥራቸው አድጎ ከ230 በሚልቁ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከ4,900,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ይሖዋ በደግነቱ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል ለመደመር በከፍተኛ ጉጉት የሚጠባበቁ ናቸው። ከታናሹ መንጋ ጋር ሲነጻጸሩ በእርግጥም እጅግ ብዙ ሰዎች ሆነዋል። እምነት አለን የሚሉ ነገር ግን እምነታቸውን በተግባር የማያሳዩ ሰዎች አይደሉም። (ያዕቆብ 1:22፤ 2:14–17) ሁሉም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ያሰማሉ። ከእነዚህ ደስተኛ ሕዝብ መካከል ነህን? ትጉህ ምሥክር መሆን አንዱ ዐቢይ መለያ ምልክት ነው፤ ይሁን እንጂ ሌላ ነገርም ያስፈልጋል።
‘በዙፋኑ ፊት ቆሙ’
5. እጅግ ብዙ ሰዎች ‘በዙፋኑ ፊት የቆሙ’ መሆናቸው ምን ያመለክታል?
5 ሐዋርያው ዮሐንስ በተሰጠው ራእይ ላይ እነዚህ ሰዎች ‘በዙፋኑና በበጉ ፊት’ ቆመው አይቷቸዋል። (ራእይ 7:9) በጥቅሱ ዙሪያ ባለው ሐሳብ ላይ እንደተገለጸው በአምላክ ዙፋን ፊት መቆማቸው ለይሖዋ ሉዓላዊነት ሙሉ ዕውቅና እንደሰጡ ያመለክታል። ይህ ብዙ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው። ለምሳሌ፦ (1) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ጥሩ ምን እንደሆነ መጥፎ ደግሞ ምን እንደሆነ የመወሰን መብት እንዳለው ይቀበላሉ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ ኢሳይያስ 5:20, 21) (2) ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ሲናገራቸው ያዳምጣሉ። (ዘዳግም 6:1–3፤ 2 ጴጥሮስ 1:19–21) (3) ይሖዋ በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ለሰጣቸው ሰዎች የመገዛትን አስፈላጊነት ይቀበላሉ። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:22, 23፤ 6:1–3፤ ዕብራውያን 13:17) (4) ምንም እንኳ ፍጹም ባይሆኑም እያጉረመረሙ ሳይሆን ከልባቸው በፈቃደኝነት ቲኦክራሲያዊ መመሪያን ለመከተል ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። (ምሳሌ 3:1፤ ያዕቆብ 3:17, 18) ታላቅ አክብሮትና የጠለቀ ፍቅር ለሚያሳዩት ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ በዙፋኑ ፊት ቆመዋል። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች በዙፋኑ ፊት ‘መቆማቸው’ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው እንደተቀበላቸው የሚያመለክት ነው። (ከራእይ 6:16, 17 ጋር አወዳድር።) የተቀበላቸው በምን መሠረት ነው?
‘ነጭ ልብስ ለብሰው’
6. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች “ነጭ ልብስ” መልበሳቸው ምን ያመለክታል? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም ያገኙት እንዴት ነው? (ሐ) እጅግ ብዙ ሰዎች በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ ያላቸው እምነት በሕይወታቸው ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
6 ሐዋርያው ዮሐንስ ስላየው ነገር የሰጠው መግለጫ እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ነጭ ልብስ እንደ ለበሱ’ ያመለክታል። እነዚህ ነጭ ልብሶች በይሖዋ ፊት ያላቸውን ንጹሕ የጽድቅ አቋም የሚወክሉ ናቸው። ይህን የመሰለ አቋም ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው? ዮሐንስ ባየው ራእይ ላይ “በበጉ ፊት” እንደቆሙ ቀደም ሲል ተመልክተናል። ኢየሱስ ክርስቶስን “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” አድርገው ይመለከቱታል። (ዮሐንስ 1:29) በራእዩ ላይ በአምላክ ዙፋን ፊት ካሉት ሽማግሌዎች አንዱ “ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ” በማለት ሲገልጽ ዮሐንስ ሰምቷል። (ራእይ 7:14, 15) ከኃጢአት በሚቤዠው የክርስቶስ ደም ላይ እምነት በማሳየት ልብሶቻቸውን በምሳሌያዊ ሁኔታ አጥበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤዛው የሚሰጠው ትምህርት ትክክል ነው ብለው ማሰባቸው ብቻ አይበቃም። ለቤዛው ያላቸው አድናቆት ውስጣዊ ማንነታቸውን ይነካል፤ በመሆኑም እምነታቸውን የሚያሳዩት ‘በልባቸው’ ነው። (ሮሜ 10:9, 10) ይህም በሕይወታቸው በሚያከናውኑት ነገር ላይ ትልቅ ለውጥ ያስከትላል። በእምነት በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ራሳቸውን ለይሖዋ ይወስናሉ፤ ይህን ውሳኔያቸውን በውኃ ጥምቀት ያሳያሉ፤ ከወሰኑት ውሳኔ ጋር በሚስማማ መንገድ ይመላለሳሉ፤ በዚህም መንገድ ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና ያገኛሉ። በጥንቃቄ ሊጠበቅ የሚገባው እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው!—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15
7, 8. እጅግ ብዙ ሰዎች ልብሳቸው ሳያድፍ እንዲቀጥል የይሖዋ ድርጅት እገዛ የሚያደርግላቸው እንዴት ነው?
7 የይሖዋ ድርጅት ለዘላቂ ደህንነታቸው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በማሰብ አንድ ሰው እምነቱን በቃላት ቢገልጽም እንኳ በራእይ 7:9, 10 ላይ ያሉትን ትንቢታዊ መግለጫዎች እንዳያሟላ የሚያደርጉትን መለያ ልብሱን ሊያጎድፉ ወይም ሊያቆሽሹ የሚችሉትን አመለካከቶችና ጠባዮች በተደጋጋሚ አመልክቷል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) መጠበቂያ ግንብ በ1941 እና ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ቀደም ሲል ወጥቶ የነበረውን ሐሳብ በማጠናከር ለሌሎች ሰዎች ሲሰብኩ ከቆዩ በኋላ ከዚያ ውጭ ባሉት ሰዓታት ዝሙትንና ምንዝርን የመሰሉ ድርጊቶች መፈጸም ከባድ ስህተት እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። (1 ተሰሎንቄ 4:3፤ ዕብራውያን 13:4) በ1947 ይሖዋ ለክርስቲያኖች ያወጣው የጋብቻ ሥርዓት በሁሉም አገሮች እንደሚሠራ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። የአካባቢው ወግና ልማድ የሚቀበለው የጋብቻ ሥርዓት ምንም ይሁን ምን ከአንድ ሚስት በላይ አግብተው መኖርን የሚቀጥሉ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሊሆኑ አይችሉም።—ማቴዎስ 19:4–6፤ ቲቶ 1:5, 6
8 በ1973 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የትም ሆኑ የት፣ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በመስክ አገልግሎት ላይ እያሉ ብቻ ሳይሆን በዓለማዊ ሥራ ላይ እያሉም ሆነ ሰው በማያየው ገለል ያለ ሥፍራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ትምባሆ ማጨስን ከመሳሰሉ ያላንዳች ጥርጥር ሰውነትን ከሚያረክሱ ልማዶች መቆጠብ እንዳለባቸው ተገለጸላቸው። (2 ቆሮንቶስ 7:1) በ1987 በተካሄዱ የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባዎች ላይ ክርስቲያን ወጣቶች በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ጠብቀው መመላለስ እንዲችሉ ሁለት ዓይነት ኑሮ ከመኖር መጠበቅ እንዳለባቸው ጠንከር ያለ ምክር ተሰጣቸው። (መዝሙር 26:1, 4) በአምላካችንና በአባታችን ዘንድ “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ” ራስን ‘በዓለም ከሚገኝ እድፍ መጠበቅን’ ስለሚጨምር መጠበቂያ ግንብ ከተለያዩ ዓይነት የዓለም መንፈስ ገጽታዎች እንድንጠበቅ በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል።—ያዕቆብ 1:27
9. ከታላቁ መከራ በኋላ ተቀባይነት ያገኙ ሆነው በአምላክ ዙፋን ፊት የሚቆሙት እነማን ናቸው?
9 ከመጪው ታላቅ መከራ በኋላ ተቀባይነት ያገኙ የአምላክ አገልጋዮች ሆነው ‘በዙፋኑ ፊት እንደቆሙ’ የሚቀጥሉት እምነታቸው ዘወትር በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው እንዲኖሩ የሚገፋፋቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ክርስቲያናዊ አኗኗርን መጀመር ብቻ ሳይሆን በታማኝነት በመጽናት ይህን አኗኗር የሙጥኝ ብለው የሚገፉበት ናቸው።—ኤፌሶን 4:24
“የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው”
10. ዮሐንስ እጅግ ብዙ ሰዎች ይዘውት ያየው የዘንባባ ዝንጣፊ ምን ትርጉም አለው?
10 ሐዋርያው ዮሐንስ ከተመለከታቸው የእጅግ ብዙ ሰዎች ዋና ዋና ገጽታዎቹ አንዱ ‘የዘንባባ ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው መያዛቸው’ ነው። ይህ ምን ትርጉም አለው? እነዚህ የዘንባባ ዝንጣፊዎች ዮሐንስ በዕብራውያን የቀን መቁጠሪያ ላይ ካሉት በዓላት ሁሉ ይበልጥ አስደሳች የሆነውን ከበጋ መከር በኋላ የሚደረገውን የአይሁዶች የዳስ በዓል እንዳስታወሱት አያጠራጥርም። ሕጉ በሚያዘው መሠረት የሌሎች ዛፎችን ቅርንጫፎች ጨምሮ የዘንባባ ዝንጣፊዎች በበዓሉ ወቅት ሰዎች የሚቀመጡባቸውን ዳሶች ለመሥራት ይውሉ ነበር። (ዘሌዋውያን 23:39–40፤ ነህምያ 8:14–18) በተጨማሪም የዘንባባ ዝንጣፊዎች የሐሌል (መዝሙር 113–118) መዝሙሮች ሲዘመሩ ለአምልኮ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጡ ሰዎች ይውለበለቡ ነበር። እጅግ ብዙ ሰዎች የዘንባባ ዝንጣፊዎችን ማውለብለባቸው ዮሐንስ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ ለአምልኮ መጥተው የነበሩ በጣም ብዙ ሰዎች በደስታ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን እያውለበለቡና “በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ ሲጮኹ የነበረውን ሁኔታ ሳያስታውሰው አልቀረም። (ዮሐንስ 12:12, 13) ስለዚህ የዘንባባ ዝንጣፊዎቹ መውለብለብ እጅግ ብዙ ሰዎች በደስታ የይሖዋን መንግሥትና የተቀባውን ንጉሡን በእልልታ እንደሚቀበሉ ያመለክታል።
11. የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን በማገልገል እውነተኛ ደስታ የሚያገኙት ለምንድን ነው?
11 እጅግ ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም እንኳ ይሖዋን ሲያገለግሉ ይህን የመሰለ የደስታ መንፈስ ያሳያሉ። ይህ ማለት ግን ምንም ዓይነት መከራ አያጋጥማቸውም ወይም ምንም ዓይነት ሐዘን ወይም ሥቃይ አይደርስባቸውም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋን ከማገልገልና ከማስደሰት የሚገኘው እርካታ እነዚህን ነገሮች ለመቻልና ለመርሳት ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ከባሏ ጋር ለ45 ዓመታት በጓቲማላ ያገለገለች አንዲት ሚስዮናዊት ያጋጠሟቸውን ኋላ ቀር ሁኔታዎች፣ ሕንዶች በሚኖሩባቸው መንደሮች የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ያሳለፉትን የሕይወታቸው ክፍል ሆኖ የነበረውን ከባድ ሥራና አደገኛ ጉዞ በማስታወስ ተናግራለች። “በሕይወታችን ውስጥ በጣም ደስተኞች የነበርንባቸው ጊዜያት ነበሩ” በማለት ደምድማለች። ምንም እንኳ የዕድሜ መግፋትና በሽታ የሚያስከትሉት ጣጣ እየደረሰባት የነበረ ቢሆንም የዕለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኟን በዘገበችበት ማስታወሻዋ ላይ ከሰፈሩት የመጨረሻ ነጥቦች ውስጥ “ግሩም ሕይወት ነበር፤ ትልቅ እርካታ ያገኘሁበት ሕይወት” የሚሉት ቃላት ይገኙበታል። በምድር ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አገልግሎታቸው የሚሰማቸው ስሜት ይኸው ነው።
‘ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት’
12. ይሖዋ በቀንም ይሁን በሌሊት በዚህች ምድር ላይ ምን ይመለከታል?
12 እነዚህ ደስተኛ አምላኪዎች ለይሖዋ “በመቅደሱ ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት” ያቀርባሉ። (ራእይ 7:15 አዓት) በምድር ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ቅዱስ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። በአንዳንድ አገሮች ሌሊት ሲሆንና በእነዚህ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ሲተኙ በሌሎቹ አገሮች ፀሐይ ወጥታ የይሖዋ ምሥክሮች በምሥክርነቱ ሥራቸው ይጠመዳሉ። ምድር ያለማቋረጥ ስትዞር እነርሱም ዘወትር ቀንና ሌሊት ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙሮች ይዘምራሉ። (መዝሙር 86:9) ይሁን እንጂ በራእይ 7:15 ላይ የተጠቀሰው ቀንና ሌሊት የሚቀርብ አገልግሎት ይበልጥ የሚያመለክተው በግለሰብ ደረጃ የሚከናወነውን አገልግሎት ነው።
13. “ቀንና ሌሊት” ማገልገል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያመለክቱት እንዴት ነው?
13 የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑት ግለሰቦች ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ። ይህ ማለት የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር እንደ ቅዱስ አገልግሎት ይታያል ማለት ነውን? ምንም ይሁን ምን የሚሠሩትን ነገር ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ ማከናወንን እንደለመዱ የታወቀ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:31፤ ቆላስይስ 3:23) ይሁን እንጂ “ቅዱስ አገልግሎት” ሲባል ከአንድ ሰው የአምልኮ ተግባር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነገር ብቻ ማለት ነው። በአንድ ሥራ “ቀንና ሌሊት” መሳተፍ አዘውታሪነትን ወይም ወለም ዘለም አለማለትን እንዲሁም ኮስተር ብሎ ተግባርን በቁም ነገር መያዝን ያመለክታል።—ከኢያሱ 1:8፤ ከሉቃስ 2:37፤ ከሥራ 20:31ና ከ2 ተሰሎንቄ 3:8 ጋር አወዳድር።
14. በግል የምናከናውነውን የመስክ አገልግሎት “ቀንና ሌሊት” የሚቀርብ አገልግሎት ነው ሊያሰኘው የሚችለው ምንድን ነው?
14 እጅግ ብዙ ሰዎች የተባሉት ይሖዋን በታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባዮች ሲያገለግሉት በመስክ አገልግሎት ወለም ዘለም ሳይሉ ዘወትር ለመሳተፍ ይጥራሉ። ብዙዎች በየሳምንቱ በሚካሄደው የመስክ አገልግሎት የተወሰነ ድርሻ ማበርከቱን ግባቸው አድርገውታል። ሌሎች ደግሞ የዘወትር አቅኚዎች ወይም ረዳት አቅኚዎች ሆነው ለማገልገል ጥረት አድርገዋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ አቅኚዎች ጠዋት ጠዋት በመንገዶችና በሱቆች ሲመሰክሩ ይታያሉ። አንዳንድ ምሥክሮች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የሚመቻቸውን ሰዓት በመምረጥ በጣም ከመሸ በኋላም ሳይቀር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ። ገበያ ሲወጡ፣ ሲጓዙ፣ በምሳ ሰዓትና በስልክ ይመሰክራሉ።
15. ከመስክ አገልግሎት ሌላ በቅዱስ አገልግሎታችን ውስጥ ምን ነገሮች ተካትተዋል?
15 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መካፈልም ከቅዱስ አገልግሎታችን አንዱ ነው፤ ለክርስቲያናዊ ስብሰባ የሚያስፈልጉ ቤቶችን በመሥራትና በመንከባከብ የሚጠፋው ጊዜም እንደዚሁ ነው። ክርስቲያን ወንድሞች በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ሆነው እንዲቀጥሉ በመንፈሳዊና በቁሳዊ ነገሮች ለመርዳትና ለማበረታታት የሚደረጉት ጥረቶችም ከዚሁ ጋር የሚደመሩ ናቸው። ይህም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎቻችንንም ሥራ ያጠቃልላል። ሁሉም ዓይነት የቤቴል አገልግሎት እንዲሁም በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በፈቃደኝነት የሚሠራ ሥራ ሁሉ ቅዱስ አገልግሎት ነው። በእርግጥም ኑሯችን ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ሲያተኩር በቅዱስ አገልግሎት ይሞላል። ጥቅሱ እንደሚለው የይሖዋ ሕዝቦች “ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት” ያቀርባሉ፤ ይህንንም በማድረግ ትልቅ ደስታ ያገኛሉ።—ሥራ 20:35፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11
“ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ”
16. እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ከሕዝብ ሁሉ የተውጣጡ’ መሆናቸው እየተረጋገጠ ያለው እንዴት ነው?
16 እጅግ ብዙ ሰዎች ከሁሉም ሕዝቦች እየመጡ ነው። አምላክ አያዳላም፤ በኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበው የቤዛ ዝግጅትም ለሁሉም የሚበቃ ነው። እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን እንደሆኑ በ1935 በመጀመሪያ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ሲብራራ የይሖዋ ምሥክሮች በ115 አገሮች ውስጥ ይንቀሳቀሱ ነበር። በ1990ዎቹ ዓመታት በግ መሰል ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ከሁለት እጥፍ በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ተስፋፍቷል።—ማርቆስ 13:10
17. ከሁሉም ‘ነገዶች፣ ወገኖችና ቋንቋዎች’ የተውጣጡ ሰዎች ከእጅግ ብዙ ሰዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ለመርዳት ምን እየተደረገ ነው?
17 እጅግ ብዙ ሰዎችን ፈልጎ በማግኘት ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ትኩረት የሰጡት ለብሔራት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ብሔራት ውስጥ ለሚገኙ ነገዶችና ወገኖች እንዲሁም ለተለያዩ ቋንቋዎች ጭምር ነው። መልእክቱን ለእነዚህ ሰዎች ለማዳረስ ምሥክሮቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የተዘጋጁ ጽሑፎችን ከ300 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ያትማሉ። ይህ ደግሞ ብቃት ያላቸው የተርጓሚዎች ቡድኖችን ማሰልጠንና ማደራጀትን፣ በእነዚህ ሁሉ ቋንቋዎች መሥራት የሚችሉ የኮምፒዩተር መሣሪያዎች ማቅረብን እንዲሁም የኅትመቱን ሥራ ማከናወንን ይጨምራል። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 98,000,000 የሚጠጉ ሰዎች የሚናገሯቸው 36 ቋንቋዎች ጽሑፎች በሚዘጋጁባቸው ቋንቋዎች ዝርዝር ውስጥ ተጨምረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ምሥክሮቹ እነዚህ ሰዎች የአምላክ ቃል እንዲገባቸው ለመርዳት ሲሉ በግለሰብ ደረጃ ያሉበት ድረስ ሄደው ለማነጋገር ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 28:19, 20
“ከታላቁ መከራ የመጡ”
18. (ሀ) ታላቁ መከራ ሲፈነዳ ከለላ የሚያገኙት እነማን ናቸው? (ለ) በዚያን ጊዜ ምን አስደሳች አዋጆች ይሰማሉ?
18 መላእክቱ በራእይ 7:1 ላይ የተጠቀሱትን የጥፋት ነፋሳት ሲለቁ የይሖዋን ፍቅራዊ ከለላ የሚያገኙት ቅቡዓኑ ‘የአምላካችን ባሮች’ ብቻ ሳይሆኑ በእውነተኛ አምልኮ የተባበሯቸው እጅግ ብዙ ሰዎችም ናቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደተናገረው እጅግ ብዙ ሰዎች ከጥፋቱ በመትረፍ በሕይወት ‘ታላቁን መከራ ያልፋሉ።’ ከዚያ በኋላ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” በማለት የሚያሰሙት የምስጋናና የውዳሴ ጩኸት ምንኛ ታላቅ ይሆናል! በሰማያት ያሉት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በሙሉ “አሜን፣ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን” ብለው በመናገር እነርሱም ድምፃቸውን ያሰማሉ።—ራእይ 7:10–14
19. ከጥፋቱ በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች በየትኛው አስደሳች ሥራ ለመካፈል ይጓጓሉ?
19 ያ ጊዜ እንዴት ያለ የደስታ ጊዜ ይሆናል! በሕይወት የሚኖሩ ሁሉ የብቸኛው እውነተኛ አምላክ አገልጋዮች ይሆናሉ! እነዚህ ሰዎች በሙሉ የሚያገኙት ከሁሉ የላቀ ደስታ ይሖዋን በማገልገል የሚገኘው ደስታ ይሆናል። ብዙ አስደሳች ሥራ ይኖራል! ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። በብዙ ሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን ይነሣሉ፤ ከዚያም የይሖዋን መንገዶች ይማራሉ። በዚህ ሥራ መካፈል እንዴት ያለ አስደሳች መብት ነው!
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ በ1935 የተከሰቱት ሁኔታዎች በይሖዋ ምሥክሮች የመስክ አገልግሎት ላይ ምን ለውጥ አስከትለዋል?
◻ እጅግ ብዙ ሰዎች ‘በዙፋኑ ፊት ቆመው’ መታየታቸው ምን ያመለክታል?
◻ ለበጉ ደም ያለን አድናቆት አኗኗራችንን እንዴት ሊነካው ይገባል?
◻ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን ማውለብለባቸው ምን ያመለክታል?
◻ እጅግ ብዙ ሰዎች ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት እንዴት ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቅዱስ አገልግሎታቸው አዘውታሪነትን፣ ትጋትንና አገልግሎትን በቁም ነገር መያዝን ያንጸባርቃል