-
የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?መጠበቂያ ግንብ—2014 | መስከረም 1
-
-
የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?
“ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—ንጉሥ ሰሎሞን፣ 11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.a
በጥንት ዘመን የኖረው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ፣ ጠዋት ታይቶ ቀን ላይ እንደሚጠፋ ጤዛ የሆነው የሰው ልጅ ዕድሜ ከምድር ዘላለማዊነት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። በእርግጥም ላለፉት ሺህ ዓመታት ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ ቆይቷል፤ ፕላኔቷ ምድራችን ግን እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ አደገኛ ሁኔታዎችን ተቋቁማ በውስጧ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ማኖር ችላለች።
አንዳንዶች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባሉት ዓመታት ዓለማችን በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠች እንደሆነ ይናገራሉ። የአንድ ሰው የሕይወት ዘመን በሚያክል ጊዜ ብቻ እንኳ በትራንስፖርት፣ በመገናኛ አውታሮችና በሌሎች የቴክኖሎጂ መስኮች ታላቅ እመርታ የታየ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አስከትሏል። ብዙዎች በአንድ ወቅት ፈጽሞ የማይታሰብ የነበረ የቅንጦት ሕይወት እየመሩ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ የዓለም የሕዝብ ብዛት በሦስት እጥፍ ያህል አድጓል።
ይህ ሁሉ ለውጥ ግን ያስከተለው ጉዳት አለ። የሰው ልጆች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሕይወት አስፈላጊ በሆኑ የምድር ተፈጥሯዊ ዑደቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይነገራል። እንዲያውም አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ የሰው ልጆች ባለፉት ጥቂት መቶ ዓመታት ያደረጉት እንቅስቃሴ በምድር ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያስከተለ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጆች ‘ምድርን የሚያጠፉበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ራእይ 11:18) አንዳንዶች፣ የምንኖረው እንዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ያስባሉ። ወደፊት በምድር ላይ ምን ያህል ጉዳት ይደርስ ይሆን? ደግሞስ ጉዳቱ፣ ሊቀለበስ የማይችል ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል? በእርግጥ የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?
ሊቀለበስ የማይችል ደረጃ ላይ ይደርሳል?
ምድር ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ሊቀለበስ የማይችል ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው? አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ በምድር ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የሚያስከትለውን ውጤት አስቀድሞ መተንበይ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ድንገተኛና ያልተጠበቁ የአየር ንብረት ለውጦች አውዳሚ የሆነ ውጤት የሚያስከትሉበት ጊዜ ቀርቧል የሚል ስጋት አላቸው።
ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አንታርክቲካ የሚገኘውን የበረዶ ንጣፍ እንመልከት። የምድር ሙቀት መጨመር በዚሁ ከቀጠለ የበረዶው ንጣፍ ሊቀለበስ በማይችል ሁኔታ መቅለጥ እንደሚጀምር አንዳንዶች ያምናሉ። ምክንያቱም በረዶ በተፈጥሮው የፀሐይን ጨረሮች አንጥሮ የመመለስ ችሎታ አለው። ይሁን እንጂ የበረዶ ንጣፉ እየሳሳና መጠኑ እየቀነሰ ሲሄድ ከሥር ያለው የውቅያኖሱ ክፍል ውሎ አድሮ ለፀሐይ ጨረር ይጋለጣል፤ የውቅያኖስ ውኃ ደግሞ የፀሐይ ጨረሮችን አንጥሮ የመመለስ ችሎታው አነስተኛ ነው። ጠቆር ያለው ላይኛው የውቅያኖስ ክፍል ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት ይዞ ስለሚያስቀር በረዶው ይበልጥ እንዲቀልጥ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ማቆሚያ የሌለው አውዳሚ ዑደት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። የበረዶው መቅለጥ የባሕር ውኃ ከፍታ እንዲጨምር ያደርጋል፤ በዚህም የተነሳ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
-