-
የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር—ታላቁና ክብራማ መደምደሚያው!ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
8. (ሀ) የሰባተኛው መለከት መነፋት በብሔራት ላይ ምን ዓይነት ውጤት አስከትሎአል? (ለ) ብሔራት የተቆጡት በማን ላይ ነው?
8 በሌላ በኩል ደግሞ የሰባተኛው መለከት መነፋት ለአሕዛብ ምንም ዓይነት ደስታ አላመጣላቸውም። የይሖዋን ቁጣ የሚቀምሱበት ጊዜ ደርሶባቸዋል። ዮሐንስ እንደሚገልጸው:- “አሕዛብም ተቆጡ፣ ቁጣህም መጣ፣ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፣ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፣ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።” (ራእይ 11:18) አሕዛብ ከ1914 ጀምሮ እርስ በርሳቸው፣ በአምላክ መንግሥትና በተለይም በይሖዋ ሁለት ምሥክሮች ላይ በአስፈሪ ሁኔታ ሲቆጡ ቆይተዋል።—ራእይ 11:3
9. ብሔራት ምድርን ሲያጠፉ የቆዩት እንዴት ነው? አምላክስ ምን ለማድረግ ወስኖአል?
9 አሕዛብ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለአንድ አፍታ እንኳን ጋብ ባላለው ጦርነታቸውና በመጥፎ አያያዛቸው ምድርን ሲያጠፉ ወይም ሲያበላሹ ቆይተዋል። ከ1914 ወዲህ ግን ይህ ምድርን የማጥፋት ድርጊት በጣም ተባብሶ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሶአል። በስግብግብነትና በምግባረ ብልሹነት ምክንያት በረሐዎች ተስፋፍተዋል፣ ብዙ ለም መሬቶች ጠፍ ሆነዋል። የአሲድ ዝናብና የሬዲዮ ጨረር የሚያዘንቡ ዳመናዎች ሰፊ አካባቢዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ለምግብነት የሚያገለግሉ ዕጽዋትና አዝርዕት ተበክለዋል። የምንተነፍሰው አየርና የምንጠጣው ውኃ ተበክሎአል። ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣው ቆሻሻ በምድርና በባሕር ፍጥረታት ሕይወት ላይ አደገኛ ሁኔታ ደቅኖአል። በአንድ ወቅት ልዕለ ኃያላን መንግሥታት የሰው ልጆችን በሙሉ በኑክሌር መሣሪያ ሙሉ በሙሉ ያጠፋሉ የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ምድርን የሚያጠፉትን ስለሚያጠፋ’ ደስ ሊለን ይገባል። ምድርን እንደዚህ ወዳለው አሳዛኝ ሁኔታ በጣሉአት ትዕቢተኛና አምላክ የለሽ ሰዎች ላይ የቅጣት ፍርዱን ይፈጽማል። (ዘዳግም 32:5, 6፤ መዝሙር 14:1-3) በዚህም ምክንያት ይሖዋ እነዚህን ክፉ አድራጊዎች ወደ ፍርድ ለማቅረብ ሦስተኛው ወዮታ እንዲመጣ አድርጎአል።—ራእይ 11:14
ምድርን ለሚያጠፉ ወዮላቸው!
10. (ሀ) ሦስተኛው ወዮታ ምንድን ነው? (ለ) ሦስተኛው ወዮታ በማሠቃየት ብቻ የማያበቃው በምን መንገድ ነው?
10 ሦስተኛው ወዮታ እነሆ! ፈጥኖ ይመጣል! ይህ ወዮታ ይሖዋ “የእግሩ መረገጫ” የሆነችውን ይህችን ውብ ምድር የሚያረክሱትን ሰዎች የሚያጠፋበት መሣሪያ ነው። (ኢሳይያስ 66:1) ወዮታውን የሚያንቀሳቅሰው የአምላክ ቅዱስ ምስጢር የሆነው የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ነው። የአምላክ ጠላቶች በተለይም የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ከአንበጣው መቅሰፍትና ከፈረሰኞቹ ሠራዊት ከመጡት ሁለት ወዮታዎች ብዙ ሥቃይ ተቀብለዋል። የይሖዋ መንግሥት ራሱ የሚያመጣው ሦስተኛ ወዮታ ግን ሥቃይ በማድረስ ብቻ ተወስኖ አይቀርም። (ራእይ 9:3-19) በአጥፊው የሰው ልጆች ኅብረተሰብና በገዥዎቹ ላይ የሞት ቅጣት በማምጣት ከቦታቸው ያስወግዳቸዋል። ይህም የሚሆነው የይሖዋ ፍርድ የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት በአርማጌዶን ጦርነት ነው። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው ይሆናል። “በእነዚያም ነገሥታት [ምድርን በሚያጠፉት ገዥዎች] ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል። ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል። እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች፣ ታጠፋቸውማለች ለዘላለምም ትቆማለች።” የአምላክ መንግሥት እንደ አንድ ግርማ ያለው ውብ ተራራ በመሆን ክብር በተጎናጸፈች ምድር ላይ ትገዛለች። ይህም የይሖዋን ሉዓላዊነት ከማረጋገጡም በላይ ለሰው ልጆች ሁሉ ዘላለማዊ ደስታ ያመጣል።—ዳንኤል 2:35, 44፤ ኢሳይያስ 11:9፤ 60:13
11. (ሀ) ትንቢቱ የሚገልጸው የትኞቹን ተከታታይ የሆኑ አስደሳች ክንውኖች ነው? (ለ) ለሰው ልጆች የሚዘረጋው የማይገባ ደግነት ምንድን ነው? ይህስ የሚፈጸመው በማንና እንዴት ነው?
11 ሦስተኛው ወዮታ በጌታ ቀን በተከታታይ በሚፈጸሙ አስደሳች ክንውኖች የታጀበ ነው። ሙታን የሚፈረዱበትና አምላክ ‘ለባሪያዎቹ ለነቢያትና ስሙን ለሚፈሩ ቅዱሳን ዋጋቸውን የሚሰጥበት’ ጊዜ ነው። የሙታን ትንሣኤ ይሆናል ማለት ነው። ከአሁን በፊት ያንቀላፉ ቅቡዕ የሆኑ ቅዱሳን ከሙታን የተነሱት በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:15-17) ከዚያ በኋላ ደግሞ የቀሩት ቅዱሳን ቅጽበታዊ ትንሣኤ እያገኙ አብረዋቸው ይኖራሉ። የይሖዋን ስም የሚፈሩት ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚያልፉት እጅግ ብዙ ሰዎችም ሆኑ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከሙታን የሚነሱት ‘ታላላቅና ታናናሽ ሙታን’ እንዲሁም በጥንት ዘመን ነቢያት የነበሩ የአምላክ ባሮች ዋጋቸውን ይቀበላሉ። የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት የሞትንና የሲኦልን ቁልፍ ስለያዘ መሲሑ ለዚህ ከፍተኛ ዝግጅት ለሚበቁ ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ሽልማት እንዲዘረጋ መንገዱን ይከፍትለታል። (ራእይ 1:18፤ 7:9, 14፤ 20:12, 13፤ ሮሜ 6:22፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ይህ የሕይወት ስጦታ፣ ሞት የማይደፍረው ሰማያዊ ሕይወትም ሆነ የዘላለም ምድራዊ ሕይወት እያንዳንዱ ተሸላሚ በከፍተኛ አመስጋኝነት ሊቀበለው የሚገባ የይሖዋ የማይገባ ደግነት ነው!—ዕብራውያን 2:9
-
-
የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር—ታላቁና ክብራማ መደምደሚያው!ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
[በገጽ 175 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምድርን ማበላሸት
“በየሦስት ሴኮንድ አንድ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክል ደን ይወድማል። . . . የእነዚህ ደኖች መውደም ደግሞ በሺህ የሚቆጠሩ የእጽዋትና የእንስሳት ዘሮች እንዲጠፉ ምክንያት ሆኖአል።”—ኢሉስትሬትድ አትላስ ኦፍ ዘ ወርልድ (ራንድ ማክናሊ)
“በሁለት መቶ ዘመናት ውስጥ [ታላላቆቹ ሐይቆች] የዓለም ታላላቅ የቆሻሻ ፍሳሽ ማጠራቀሚያዎች ሆነዋል።”—ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል (ካናዳ)
በሚያዝያ ወር 1986 በቸርኖብል ዩ ኤስ ኤስ አር የደረሰው ፍንዳታና ቃጠሎ “ሂሮሽማና ናጋሳኪ ከተደበደቡበት ጊዜ ወዲህ የታየ በጣም ከባድ የኑክሌር ፍንዳታ ነው። በዓለም አየር፣ ውኃና አፈር ላይ እስከ አሁን የፈነዱትን የሙከራ ኑክሌር ቦምቦች ሁሉ የሚያክል ጨረር እንዲሰራጭ አድርጎአል።”—ጃማ፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ
በጃፓን አገር በሚናማታ ከሚገኝ የኬሚካል ፋብሪካ ሜቲልሜርኩሪ የተባለው ቅመም ወጥቶ ወደ ባሕር ውስጥ ፈስሶአል። በዚህ ኬሚካል የተመረዙትን ዓሦች የበሉ ሰዎች ሚናማታ ዲዚዝ (MD) የተባለ በሽታ ይዞአቸዋል። “ይህም በሽታ በጣም ከባድ የሆነ የነርቭ ቀውስ የሚያመጣ ሲሆን እስከ [1985] ድረስ በጃፓን አገር በሙሉ 2, 578 ሰዎች በሚናማታ በሽታ (MD) እንደተለከፉ ተረጋግጦአል።”—ኢንተርናሽናል ጆርናል ኦፍ ኤፒዶሞሎጂ
[በገጽ 176 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በራእይ 11:15-19 ላይ የሚገኙት ከባድ መልእክቶች ለሚቀጥሉት ራእዮች መግቢያ ይሆናሉ። ራእይ ምዕራፍ 12 በራእይ 11:15, 17 ላይ የሚገኘውን ታላቅ ማስታወቂያ የሚያብራራና በዝርዝር የሚገልጽ ራእይ ነው። ምዕራፍ 13 ደግሞ በምድር ላይ ጥፋት ያመጣው የሰይጣን የፖለቲካ ድርጅት ከየት እንደተገኘና እንዴት እንደተስፋፋ ስለሚገልጽ ለ11:18 ማብራሪያ ይሰጣል። ምዕራፍ 14 እና 15 ከሰባተኛው መለከት መነፋትና ከሦስተኛው ወዮታ ጋር የሚዛመዱትን የመንግሥት ፍርዶች በዝርዝር ይገልጻል።
-