የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋ
    ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
    • የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይን ጠጅ

      13. (ሀ) ኃያሉ መልአክ የታላቂቱ ባቢሎን ግልሙትና በጣም የተስፋፋ መሆኑን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው የትኛው በጥንትዋ ባቢሎን ውስጥ የነበረ የፆታ ብልግና ነው?

      13 ኃያሉ መልአክ ከዚህ ቀጥሎ የታላቂቱ ባቢሎን ግልሙትና በጣም የተስፋፋ ስለመሆኑ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋaቁጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋልና፣ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም [“ተጓዥ፣” NW] ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሣ ባለጠጋዎች ሆኑ” (ራእይ 18:3) እርኩስ በሆነው ሃይማኖታዊ አካሄድዋ የምድርን አሕዛብ በሙሉ በክላለች። በጥንትዋ ባቢሎን ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ እንደጻፈው እያንዳንዷ ልጃገረድ በቤተ መቅደሱ ይፈጸም በነበረው የአምልኮ ሥርዓት ድንግልናዋን እንድትሰጥ ይፈለግባት ነበር። በጦርነት በፈራረሰችው በካምፑቺያ አገር በአንጎር ዋት ለማየት የሚያስነውሩ የፆታ ግንኙነቶችን የሚያሳዩ ምስሎች እስከ ዛሬ ድረስ ይታያሉ። በሕንድ አገር በካጁራሆ በሚገኙ ቤተ መቅደሶች ደግሞ ቪሽኑ የተባለው የሂንዱዎች አምላክ አስጸያፊ በሆኑ የፆታ ግንኙነት ስሜት ቀስቃሽ ትርዒቶች ተከቦ የሚያሳዩ ምስሎች አሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በ1987 እና በ1988 የቴሌቪዥን ወንጌላውያንን ዓለምን ያናጋው የፆታ ብልግና መጋለጡና የሃይማኖት መሪዎች በግብረ ሰዶም ልማድ የተበከሉ መሆናቸው መታወቁ ሕዝበ ክርስትናም በጣም አስነዋሪ የሆኑ የዝሙት ድርጊቶችን የምትፈቅድ መሆኑን አረጋግጦአል። ይሁን እንጂ ብሔራት በሙሉ ከዚህ ይበልጥ ከባድ የሆነ የዝሙት ድርጊት የፈጸሙበት መንገድ አለ።

      14-16. (ሀ) በፋሽስት ኢጣልያ ውስጥ ምን ዓይነት ሕገወጥ የሃይማኖትና የፖለቲካ ዝምድና ተመስርቶ ነበር? (ለ) ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ምን መግለጫ አውጥተው ነበር?

      14 ሂትለርን በናዚ ጀርመን የሥልጣን እርካብ ላይ ስላቆናጠጠው ሕገወጥ የሆነ የሃይማኖትና የፖለቲካ ጥምረት ቀደም ስንል ተመልክተናል። ሌሎች ብሔራትም ቢሆኑ ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች በመዘባረቅዋ ምክንያት ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የካቲት 11 ቀን 1929 የቫቲካንን ከተማ ሉዓላዊ መንግሥት ያደረገው የላተራን ውል የተባለው ስምምነት በሙሶሎኒና በካርዲናል ጋስፓሪ ተፈረመ። በዚህ ጊዜ ፓፓ ፓየስ 11ኛ “ኢጣልያን ለአምላክ መልሼ አስረክቤአለሁ፣ አምላክም ወደ ኢጣልያ ተመልሶአል” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነበርን? ከስድስት ዓመት በኋላ የሆነውን ነገር እንመልከት። ጥቅምት 3 ቀን 1935 ኢጣልያ “አሁንም የባሪያ ንግድ የሚፈጸምባት የአረመኔዎች አገር ነች” የሚል ሰበብ በማቅረብ ኢትዮጵያን ወረረች። ይሁን እንጂ የአረመኔ ድርጊት የፈጸመው ማን ነበር? የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሙሶሎኒን አረመኔያዊ ድርጊት አውግዛ ነበርን? ፓፓው ግልጽ አቋም ያልያዘ መግለጫ ቢሰጡም ጳጳሶቻቸው “የአባት አገራቸውን” የኢጣልያን ጦር ኃይል በይፋ ባርከዋል። አንቶኒ ሮድስ ዘ ቫቲካን ኢን ዘ ኤጅ ኦፍ ዘ ዲክታተርስ (ቫቲካን በአምባገነኖች ዘመን) በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለው ነበር:-

      15 “የኡዲን [ኢጣልያ] ጳጳስ ጥቅምት 19 ቀን [1935] በጻፉት የጵጵስና መልእክታቸው ‘እርምጃው ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎ መናገር ለእኛ ተገቢም ወቅታዊም አይደለም። የኢጣልያዊነትም ሆነ የክርስቲያንነት ግዴታችን ለጦር ኃይላችን ድል ማግኘት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው’ ሲሉ ጽፈዋል። የፓዱዋ ጳጳስ ደግሞ ጥቅምት 21 ቀን ‘በዚህ በተደቀነብን አስቸጋሪ ጊዜ በመሪዎቻችንና በጦር ኃይላችን ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራችሁ እንጠይቃለን’ ሲሉ ጽፈዋል። ጥቅምት 24 ቀን የክሬሞና ጳጳስ የበርካታ ክፍለ ጦሮችን የዘመቻ አርማ ከባረኩ በኋላ ‘በአፍሪካ ምድር ለኢጣልያውያን ሊቅ ሕዝቦች ለም መሬት በሚያስገኙትና ለአፍሪካውያኑም የሮማንና የክርስትናን ወግና ባሕል በሚያደርሱት በእነዚህ ወታደሮች ላይ የእግዚአብሔር በረከት ይኑር። ኢጣልያ ለመላው ዓለም የክርስትና ጠባቂና ሞግዚት ሆና እንደገና ትቁም’ ብለዋል።”

      16 ኢትዮጵያ በሮማ ካቶሊክ ቀሳውስት ቡራኬ ተወረረች። ከእነዚህ ቀሳውስት መካከል አንዳቸው እንኳን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹህ ነኝ” ሊሉ ይችላሉን?—ሥራ 20:26

      17. ስፓኝ ቀሳውስትዋ “ሰይፋቸውን ማረሻ” አድርገው ባለመቀጥቀጣቸው ምክንያት ምን ዓይነት ችግር ደርሶባታል?

      17 ከጀርመን፣ ከኢጣልያና ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የታላቂቱ ባቢሎን ምንዝር ሰለባ የሆነች አንዲት ሌላ አገር እንጨምር። እርስዋም ስፓኝ ናት። በዚያች አገር ከ1936 እስከ 1939 ለተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በአብዛኛው ምክንያት የሆነው ዲሞክራሲያዊው መንግሥት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ሥልጣንና ኃይል ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ነበር። ጦርነቱ በተፋፋመበት ጊዜ የአብዮታዊው ሠራዊት ፋሽስታዊ መሪ የነበሩት ካቶሊኩ ፍራንኮ ራሳቸውን “የቅዱስ መስቀል ሠራዊት ክርስቲያን ጄኔራል” ብለው ይጠሩ ነበር። በኋላ ግን ይህን የማዕረግ ስማቸውን ትተውታል። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስፓኞች በጦርነቱ ሞቱ። በጦርነቱ ከሞቱት ከእነዚህ ሰዎች ሌላ የፍራንኮ ብሔረተኞች በአነስተኛ ግምት 40, 000 የሚያክሉ የሕዝባዊ ግንባር አባሎችን ሲገድሉ ሕዝባዊው ግንባር ደግሞ 8, 000 መነኮሳትን፣ ቀሳውስትንና ደናግሎችን ገድለዋል። ማንኛውም የእርስበርስ ጦርነት ይህን የመሰለ አሳዛኝ ሁኔታና መከራ ያስከትላል። ይህም ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሥፍራው መልስ” ሲል የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። (ማቴዎስ 26:52) ሕዝበ ክርስትና እንዲህ ባለው ደም መፋሰስ መካፈልዋ በጣም የሚዘገንን ነገር ነው። ቀሳውስትዋ “ሠይፋቸውን ማረሻ” ለማድረግ እንዳልቻሉ ግልጽ ነው።—ኢሳይያስ 2:4

  • ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋ
    ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
    • [በገጽ 236 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      “ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ”

      በ18 መቶዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ነጋዴዎች መጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኦፒየም ወደ ቻይና በድብቅ ያስገቡ ነበር። ቻይናውያን ባለ ሥልጣኖች በመጋቢት ወር 1839 ላይ 20, 000 ሳጥን ዕጽ ከብሪታንያ ነጋዴዎች በመንጠቅ ይህን ሕገወጥ ንግድ ለማቆም ሞክረው ነበር። በዚህም ምክንያት በቻይናና በብሪታንያ መካከል ግጭት ተፈጠረ። በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት እየተበላሸ በሄደበት ጊዜ የፕሮቴስታንት ሚሲዮኖች እንደሚከተሉት ያሉትን መግለጫዎች በማሰማት ብሪታንያ ውጊያ እንድትጀምር ይቀሰቅሱ ነበር:-

      “የእንግሊዝ መንግሥት ተቆጥቶ የሚነሳና አምላክም በዚህ በመጠቀም የክርስቶስ ወንጌል ወደ ቻይና እንዳይገባ የከለከሉትን እንቅፋቶች የሚያስወግድ ስለሚመስለኝ እነዚህ ችግሮች መቀስቀሳቸው በጣም ያስደስተኛል።”—ሄንሪየታ ሹክ፣ የደቡብ ባፕቲስት ሚሲዮናዊ።

      በመጨረሻም ጦርነቱ ተጀመረ። ይህም ጦርነት በዛሬው ዘመን የኦፒየም ጦርነት ተብሎ የሚጠራው ነው። ሚሲዮናውያን እንደሚከተሉት ያሉትን ቃላት በማሰማት ከብሪታንያ ጎን በሙሉ ልባቸው ተሰልፈው ነበር:-

      “በአሁኑ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ እንደ ኦፒየም ወይም እንደ እንግሊዝ ጉዳይ ሳይሆን አምላክ በሰው ልጅ የክፋት ድርጊት በመጠቀም ቻይና የተገለለችበትን ግድግዳ አፍርሶ ምህረቱን ሊያወርድላት ያሰበውን ዓላማ ለማስፈጸም ያደረገው ጉዳይ እንደሆነ አድርጌ ለመመልከት እገደዳለሁ።”—ፒተር ፓርከር፣ ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ።

      ሌላው ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ ሳሙኤል ደብልዩ ዊልያምስ ደግሞ በመጨመር “በተደረገው ነገር ሁሉ የአምላክ እጅ እንዳለበት ግልጽ ነው። በምድር ላይ ሠይፍ ይዤ መጥቼአለሁ ያለው [ኢየሱስ] ጠላቶቹን በአፋጣኝ እርምጃ ለማጥፋትና የራሱን መንግሥት ለማቋቋም እንደመጣ የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። አምላክ የሰላሙን መስፍን በቦታው እስኪያስቀምጥ ድረስ እየደጋገመ ይገለባብጣቸዋል” ብለዋል።

      ሚሲዮናዊው ጄ ሉዊስ ሹክ በቻይናውያን ብሔረተኞች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንዲህ ያለውን ትዕይንት . . . አምላክ መለኮታዊው እውነት እንዳይስፋፋ እንቅፋት የሆኑትን ጥራጊ ቆሻሻዎች ለማስወገድ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበት እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ።”

      ኤላይጃ ሲ ብሪጅማን የተባሉት ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ ደግሞ እንዲህ በማለት አክለዋል:- “አምላክ ብዙ ጊዜ ጠንካራ ክንድ ያላቸውን የሕዝብ ባለ ሥልጣናት በመጠቀም ለመንግሥቱ ጥርጊያ መንገድ አዘጋጅቶአል። . . . በእነዚህ ታላላቅ ጊዜያት ሁሉ መሣሪያ የሆኑት ሰዎች ሲሆኑ አስፈጻሚው ኃይል ግን መለኮታዊ ነበር። የብሔራት ሁሉ የበላይ ገዥ የሆነው አምላክ እንግሊዝን መሣሪያ በማድረግ ቻይናን ቀጥቶአል፣ አዋርዶአል።” ጥቅሱ የተወሰደው ዘ ሚሽነሪ ኢንተርፕራይዝ ኢን ቻይና ኤንድ አሜሪካ (በጆን ኬ ፌይርባንክ የታተመ የሃርቫርድ ጥናት) በተባለው ጽሑፍ ላይ ከሰፈረው “ኢንድስ ኤንድ ሚንስ” ከተባለው የስትዋርት ክሬይተን ሐተታ ነው።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ