የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ባቢሎን ስትጠፋ የሚኖረው ልቅሶና ደስታ
    ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
    • በጣም አስደንጋጭ የሆነ የደም ወንጀል

      14. ብርቱው መልአክ የይሖዋ ፍርድ ከባድ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ ምን ብሎአል? ኢየሱስም በምድር ሳለ ምን ተመሳሳይ ነገር ተናግሮ ነበር?

      14 ብርቱው መልአክ መልእክቱን ሲያጠቃልል ይሖዋ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲህ ያለ የጭካኔ ፍርድ የፈረደበትን ምክንያት ይነግረናል:- “በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።” (ራእይ 18:24) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ‘ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በምድር ላይ ለፈሰሰው ደም ሁሉ’ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ተናግሮ ነበር። በዚህም ምክንያት ያ ጠማማ ትውልድ በ70 እዘአ ጠፋ። (ማቴዎስ 23:35-38) ዛሬ ደግሞ ሌላ የሃይማኖታዊያን ትውልድ የአምላክን አገልጋዮች በማሳደዱ ምክንያት የደም ዕዳ ተከምሮበታል።

      15. በናዚ ጀርመን የነበረችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሁለት መንገዶች የደም ወንጀለኛ የሆነችው እንዴት ነው?

      15 ጉንተር ሌዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የናዚዋ ጀርመን በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ሚያዝያ 13 ቀን [1933] በባቫሪያ በታገዱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ይህን የተከለከለ ሃይማኖት የሚከተል ማንኛውንም ሰው እንድትጠቁም የትምህርትና የሃይማኖት ሚኒስቴር የሰጣትን የሥራ ድርሻ እንኳን ተቀብላ ነበር።” ስለዚህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በመታጎራቸው በኃላፊነት ትጠየቃለች። እጆችዋም በተገደሉት በመቶ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደም ተጨማልቀዋል። እንደ ቪልኸልም ኩሴሮቭ የመሰሉት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አለምንም ፍርሐት በጥይት ተደብድበው ለመሞት ፈቃደኞች እንደሆኑ በታየ ጊዜ ሂትለር በሕሊና ምክንያት አንዋጋም የሚሉ ሁሉ በጥይት ተረሽነው መገደል የለባቸውም ብሎ ወሰነ። በዚህም ምክንያት ይበልጥ አሰቃቂ የሆነ አገዳደል ተመረጠና የቪልኸልም ወንድም የነበረው ቮልፍጋንግ በ20 ዓመት ዕድሜው ጊሎቲን በተባለው ስለት አንገቱ ተቆርጦ ሞተ። በዚህ ጊዜ ሁሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወጣት ጀርመናውያን ካቶሊኮች ከአባት አገራቸው ሠራዊት ጋር ተሰልፈው እንዲሞቱ ታበረታታ ነበር። የቤተ ክርስቲያን የደም አፍሳሽነት ወንጀል በግልጽ ሊታይ የሚችል ነው።

      16, 17. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን ለየትኛው የደም ወንጀል መጠየቅ ይኖርባታል? ናዚዎች ለፈጸሙት የአይሁዳውያን እልቂት ቫቲካን በወንጀለኛነት መጠየቅ የሚኖርባት ለምንድን ነው? (ለ) በዘመናችን በተደረጉት በመቶ የሚቆጠሩ ጦርነቶች ለሞቱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት በኃላፊነት ከምትጠየቅባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?

      16 ይሁን እንጂ “በምድር ለታረዱ ሁሉ ደም” በወንጀለኛነት የምትጠየቀው ታላቂቱ ባቢሎን እንደሆነች ትንቢቱ ይናገራል። የዘመናችንም ታሪክ ይህን ያረጋግጣል። ለምሳሌ ያህል ሂትለርን በጀርመን አገር ሥልጣን ላይ እንዲወጣ ያስቻለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ደባ ነው። በዚህም ምክንያት ቫቲካን በናዚዎች የእልቂት ዘመቻ ለተገደሉት ስድስት ሚልዮን አይሁዶች ሕይወት ተጠያቂ ነች። ከዚህም በላይ በዚህ ዘመን ከመቶ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በመቶ በሚቆጠሩ ጦርነቶች ተገድለዋል። በዚህስ ረገድ የሐሰት ሃይማኖት ተጠያቂ ትሆናለችን? አዎ፣ በሁለት መንገዶች ተጠያቂ ነች።

      17 አንደኛው መንገድ ብዙዎቹ ጦርነቶች የተደረጉት በሃይማኖታዊ ልዩነቶች ምክንያት መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል ከ1946-48 በሕንድ አገር በሂንዱዎችና በእስላሞች መካከል ተደርጎ የነበረው ግጭት መነሻ ምክንያቱ ሃይማኖት ነበር። በዚህም ግጭት ምክንያት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶአል። በ1980ዎቹ ዓመታት በኢራቅና በኢራን መካከል የተደረገው ጦርነት ምክንያቱ ሃይማኖታዊ ልዩነት ነበር። በዚህም ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሰሜን አየርላንድ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል የሚካሄደው አምባጓሮ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች መሞት ምክንያት ሆኖአል። የርዕሰ አንቀጽ ጸሐፊ የሆኑት ሲ ኤል ሱልዝበርገር በ1976 ስለዚህ ጉዳይ ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከሚደረጉት ጦርነቶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑ በጣም የሚያሳዝን ሐቅ ነው።” እርግጥ ነው ጦርነትና ግጭት የተበጠበጠ ታሪክ ባላት ታላቂቱ ባቢሎን በኖረችበት ዘመን ሁሉ የነበረ ነው።

      18. የዓለም ሃይማኖቶች የደም ወንጀለኞች የሚሆኑበት ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው?

      18 ሁለተኛውስ መንገድ ምንድን ነው? ዓለማዊ ሃይማኖቶች በሙሉ በይሖዋ ዓይን የደም ወንጀለኞች ናቸው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ስለሚፈልገው ብቃት የሚገልጸውን እውነት በሚያሳምን መንገድ ለተከታዮቻቸው አላስተማሩም። የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ኢየሱስ ክርስቶስን መምስል እንደሚኖርባቸውና የማንኛውንም ብሔርና ጎሣ አባላት ማፍቀር እንደሚኖርባቸው በሚያሳምን ሁኔታ አላስተማሩም። (ሚክያስ 4:3, 5፤ ዮሐንስ 13:34, 35፤ ሥራ 10:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12) የታላቂቱ ባቢሎን አባላት የሆኑት ሃይማኖቶች እነዚህን ነገሮች ስለማያስተምሩ ተከታዮቻቸው በዓለም አቀፋዊ ግጭቶችና ጦርነቶች ተላልቀዋል። ለዚህም በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተፈጸሙት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በቂ መረጃ ናቸው። እነዚህ ሁለት ጦርነቶች ተቀስቅሰው ሃይማኖት አለን የሚሉ ሰዎችን እርስበርሳቸው ያጨራረሱት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ታዛዥ ቢሆኑ ኖሮ እነዚህ ጦርነቶች ሊጀመሩ አይችሉም ነበር።

      19. ታላቂቱ ባቢሎን እንዴት ያለ አስደንጋጭ የደም ወንጀል ተሸክማለች?

      19 ይሖዋ ለዚህ ሁሉ ደም መፋሰስ ተወቃሽ የሚያደርገው ታላቂቱ ባቢሎንን ነው። ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ በተለይም የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ለሕዝቦቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ቢያስተምሩ ኖሮ ይህን የሚያክል የደም ጎርፍ አይፈስም ነበር። ስለዚህ ታላቂቱ አመንዝራና ታላቂቱ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት፣ ታላቂቱ ባቢሎን ራስዋ ላሳደደቻቸውና ለገደለቻቸው “ነቢያትና ቅዱሳን ደም” ብቻ ሳይሆን “በምድር ለታረዱ ሁሉ ደም” ጭምር ለይሖዋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልስ መስጠት ይኖርባታል። በእርግጥም ታላቂቱ ባቢሎን በጣም ከባድ የደም ዕዳ በጫንቃዋ ላይ ተሸክማለች። ፍጻሜዋ በሚደርስበት ጊዜ ድምጥማጥዋ መጥፋቱ እንዴት ያለ ጥሩ ነገር ይሆናል!

  • ባቢሎን ስትጠፋ የሚኖረው ልቅሶና ደስታ
    ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
    • [በገጽ 270 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ጽኑ አቋም ይዞ አለመቆም የሚያስከትለው ኪሣራ

      ጉንተር ሌዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የናዚዋ ጀርመን በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “የጀርመን ካቶሊክ ሃይማኖት ከመጀመሪያው አንስቶ የናዚን መንግሥት ቢቃወም ኖሮ የዓለም ታሪክ ከአሁኑ የተለየ አቅጣጫ ይከተል ነበር። የቤተ ክርስቲያን ጥረት ሂትለርን ለማሸነፍና ብዙዎቹ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ለመከልከል ባይችልም እንኳን የቤተ ክርስቲያንን ሞራልና ክብር በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን ከፍ ሊያደርገው ይችል ነበር። እንዲህ ያለ ተቃውሞ ማቅረብ በሰዎች ላይ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መሥዋዕትነት በጣም ከፍተኛ ለሆነ ዓላማ ይውል ነበር። ሂትለር የገዛ አገሩ ሁኔታ እንደማያስተማምን ሲመለከት ሌሎች አገሮችን ለመውረር አይደፍርም ነበር። በዚህም መንገድ በሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት ከሞት ይተርፍ ነበር። . . . በሺህ የሚቆጠሩ ፀረ ናዚ ጀርመኖች በሂትለር ኮንሴንትሬሽን ካምፖች ውስጥ በሥቃይ ሲሞቱ፣ በሺህ የሚቆጠሩ የፖላንድ ምሁራን ሲጨፈጨፉ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሩስያውያን ኡንተርሜንሸን [ከሰው በታች የሆኑ ፍጥረታት] ናቸው ተብለው ሲገደሉ፣ 6, 000, 000 የሚያክሉ ሰዎች በዘራችሁ አርያውያን አይደላችሁም ተብለው ሲታረዱ በጀርመን አገር የነበሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች የመንግሥቱን አቋም እያጠነከሩ ለእነዚህ ወንጀሎች ተባባሪ ሆነው ነበር። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ራስና ከፍተኛ የሥነ ምግባር አስተማሪ የሆኑት የሮማው ፓፓም ይህ ሁሉ ሲፈጸም ጸጥ ብለው ነበር።”—ገጽ 320, 341

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ