-
ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችመጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
-
-
ምዕራፍ 9
ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች
የሰው ልጆች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በእርግጠኛነት መተንበይ አይችሉም። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ ያደረጓቸው ጥረቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሽፈዋል። በመሆኑም ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ትኩረታችንን እንደሚስበው የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ነው።
1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን መዝግቦ መገኘቱ ምን ያረጋግጣል?
ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ሳይቀር በትክክል ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸው ተቺዎች ትንቢቶቹ የተጻፉት ከተፈጸሙ በኋላ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ ይህ አባባል ከእውነት የራቀ ነው። አምላክ ሁሉን ማድረግ የሚችል ስለሆነ ትንቢት ለመናገር ምንም አያዳግተውም። (ኢሳይያስ 41:21-26፤ 42:8, 9፤ 46:8-10) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንደ ተጻፉ የሚያረጋግጥ እንጂ ከተፈጸሙ በኋላ የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ቀጥሎ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አንዳንድ አስገራሚ ትንቢቶችን እንመለከታለን። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ እንጂ የሰው ቃል እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆነናል።
በባቢሎን በግዞት መቀመጥ
2, 3. ንጉሥ ሕዝቅያስ በቤቱና በግዛቱ ያለውን ንብረት ሁሉ ከባቢሎን ለመጡት መልእክቶች እንዲያሳይ ያደረገው ነገር ምን ነበር?
2 ሕዝቅያስ 30 ለሚያክሉ ዓመታት በኢየሩሳሌም ላይ ነግሦአል። በ740 ከዘአበ በሰሜን በኩል የምታጎራብተው እስራኤል በአሦራውያን እጅ ስትጠፋ ተመልክቷል። በ732 ከዘአበ አሦራውያን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ከሽፎ ወራሪው ሠራዊት ከፍተኛ ውድቀት በደረሰበት ጊዜም የአምላክን የማዳን ኃይል አይቷል።—ኢሳይያስ 37:33-38
3 ከዚያም ከባቢሎን ንጉሥ ከመሮዳክ ባልዳን የተላኩ መልእክተኞች ወደ ሕዝቅያስ መጡ። እንዲሁ ከላይ ሲታይ መልእክተኞቹ የመጡት ሕዝቅያስ ከገጠመው ከባድ ሕመም በማገገሙ እንኳን ደስ ያለህ ለማለት ይመስሉ ነበር። ይሁንና መሮዳክ ባልዳን የዓለም ኃያል የሆነችውን አሦርን ለመውጋት ሕዝቅያስ አጋር ይሆነኛል ብሎ ሳያስብ አልቀረም። ሕዝቅያስ እንዲህ ዓይነቱን አሳብ ለማጥፋት ከመሞከር ይልቅ ጭራሽ ባቢሎናውያኑ ጎብኚዎች በቤቱና በግዛቱ ያለውን ነገር ሁሉ እንዲያዩ አደረገ። ምናልባት እርሱም አሦራውያን ድንገት ተመልሰው ቢመጡ የሚረዳኝ ያስፈልጋል ብሎ አስቦ ይሆናል።—ኢሳይያስ 39:1, 2
4. ኢሳይያስ ትንቢት የተናገረው ሕዝቅያስ የፈጸመው ስህተት የሚያስከትለውን የትኛውን አሳዛኝ ውጤት አስመልክቶ ነበር?
4 ሕዝቅያስ ያደረገው ነገር ጥበብ የጎደለው መሆኑን በወቅቱ የነበረው ታዋቂ ነቢይ ኢሳይያስ አስተውሎ ነበር። ሕዝቅያስ አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት የሚችለው ከባቢሎን ሳይሆን ከይሖዋ እንደሆነ ኢሳይያስ ያውቅ ስለነበር ሀብቱን ለባቢሎናውያን ማሳየቱ አሳዛኝ ውጤት እንደሚያስከትልበት ነግሮታል። ኢሳይያስም “እነሆ፣ በቤትህ ያለው ነገር ሁሉ፣ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል” አለው። ይሖዋም “ምንም አይቀርም” ሲል ተናገረ።—ኢሳይያስ 39:5, 6
5, 6. (ሀ) ኤርምያስ የኢሳይያስን ትንቢት የሚያረጋግጥ ምን ነገር ተናግሯል? (ለ) የኢሳይያስና የኤርምያስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?
5 በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ሆኖ ታይቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ ሁኔታው ተለወጠ። ባቢሎን አሦርን በመተካት የዓለም ኃያል መንግሥት ስትሆን ይሁዳ ደግሞ ሃይማኖታዊ ሁኔታዋ በጣም ስላዘቀጠ አምላክ በረከቱን ከእርሷ ወስዶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኤርምያስ የሚባል ሌላ ነቢይ በመንፈስ ተነሳስቶ ኢሳይያስ የተናገረውን ማስጠንቀቂያ ደግሞ ተናገረ። ኤርምያስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች . . . [ባቢሎናውያንን] አመጣባቸዋለሁ፤ . . . ይችም ምድር ሁሉ ባድማና መደነቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።”—ኤርምያስ 25:9, 11
6 ኤርምያስ ይህንን ትንቢት ከተናገረ ከአራት ዓመት በኋላ ባቢሎናውያን ይሁዳን የግዛታቸው ክፍል አድርገው ጠቀለሏት። ከዚያ ሦስት ዓመት ቆይቶ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ የተወሰነ ሀብትና ጥቂት ምርኮኞችን ወደ ባቢሎን ወሰዱ። ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሁዳ በማመፅዋ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በድጋሚ ተወረረች። በዚህ ጊዜ ከተማዋም ሆነች ቤተ መቅደሷ በሙሉ ወደሙ። ኢሳይያስና ኤርምያስ አስቀድመው እንደተናገሩት ሀብቷም ሆነ አይሁዳውያኑ ራሳቸው ርቃ ወደምትገኘው ወደ ባቢሎን ተወሰዱ።—2 ዜና መዋዕል 36:6, 7, 12, 13, 17-21
7. ኢሳይያስና ኤርምያስ ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ የተናገሯቸውን ትንቢቶች ፍጻሜ በሚመለከት አርኪኦሎጂ ምን ማረጋገጫ ይሰጣል?
7 ዚ አርኪኦሎጂካል ኢንሳይክለፒዲያ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው አስፈሪ የነበረው የባቢሎናውያን ጥቃት ሲያበቃ “ከተማዋ [ኢየሩሳሌም] እንዳልነበረች ሆና ወድማለች።”1 አርኪኦሎጂስቱ ደብልዩ ኤፍ ኦልብራይት እንዲህ ብለዋል:- “በይሁዳ አካባቢ የተደረጉት ቁፋሮዎችና የምድር ገጽ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት የይሁዳ ከተሞች ከለዳውያን ባደረጓቸው ሁለት ወረራዎች ሙሉ በሙሉ መውደም ብቻ ሳይሆን ለብዙ ትውልድ ባድማ ሆነው ቀርተዋል። እንዲያውም ባብዛኛው ከዚያ በኋላ ጭራሽ ሰው አልኖረባቸውም።”2 በመሆኑም አርኪኦሎጂ የዚህን ትንቢት አስገራሚ ፍጻሜ ያረጋግጣል።
የጢሮስ ዕጣ
8, 9. ሕዝቅኤል በጢሮስ ላይ ምን ትንቢት ተናግሯል?
8 በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ትንቢቶችን የመዘገበው ሌላው ጸሐፊ ደግሞ ሕዝቅኤል ነው። ከሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አንስቶ እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን ድረስ ማለትም ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታትና አይሁዳውያን በባቢሎን በምርኮ በነበሩባቸው የመጀመሪያ አሥርተ ዓመታት ወቅት ትንቢት ይናገር ነበር። በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ተቺዎችም እንኳ ሳይቀሩ መጽሐፉ በዚያ ዘመን አካባቢ እንደተጻፈ ይስማማሉ።
9 ሕዝቅኤል የእስራኤል ሰሜናዊ አጎራባች የነበረችውን የጢሮስን ጥፋት በሚመለከት አንድ አስገራሚ ትንቢት መዝግቧል። በመጀመሪያ የአምላክ ሕዝቦች ወዳጅ የነበረችው ጢሮስ በኋላ ተገልብጣ ጠላት ሆናባቸው ነበር። (1 ነገሥት 5:1-9፤ መዝሙር 83:2-8) እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ጢሮስ ሆይ፣ እነሆ፣ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ ሕዝብን አወጣብሻለሁ። የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፣ የተራቆተ ድንጋይም አደርጋታለሁ። . . . ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ።”—ሕዝቅኤል 26:3, 4, 12
10-12. የሕዝቅኤል ትንቢት በመጨረሻ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው? እንዴትስ?
10 ይህ በእርግጥ ተፈጽሟልን? ሕዝቅኤል ይህን ትንቢት ከተናገረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ጢሮስን ተቆጣጠረ። (ሕዝቅኤል 29:17, 18) ይሁንና ጢሮስን የተቆጣጠረው በቀላሉ አልነበረም። የጢሮስ ከተማ ገሚሱ ክፍል (አሮጌው ጢሮስ እየተባለ የሚጠራው) የተቆረቆረው በዋናው የብስ ላይ ቢሆንም ገሚሱ ክፍል የሚገኘው ከውኃው ዳርቻ 800 ሜትር ርቆ በሚገኝ ደሴት ላይ ነበር። ናቡከደነፆር ሙሉ በሙሉ ከተማዋን በቁጥጥሩ ሥር ከማድረጉ በፊት ደሴቲቱን ለ13 ዓመታት ከብቦ ቆይቷል።
11 ይሁንና የሕዝቅኤል ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን ያገኘው በ332 ከዘአበ ነበር። በዚህ ወቅት የመቄዶንያው ባለ ድል ታላቁ እስክንድር እስያን በመውረር ላይ ነበር። ጢሮስ ደሴት ላይ በመሆኗ እጁዋን ሳትሰጥ ቀርታ ነበር። ታላቁ እስክንድር የኋላ ኋላ አደገኛ ጠላት ሆና ልትነሣበት የምትችለውን ጢሮስን ትቶ መሄድ አልፈለገም። በሌላ በኩል ደግሞ ናቡከደነፆር እንዳደረገው ጢሮስን ከብቦ ብዙ ዓመታት ማጥፋትም አልፈለገም።
12 ታዲያ ይህን ወታደራዊ ችግር የሚፈታው እንዴት ይሆን? ወታደሮቹ ተሸጋግረው በደሴቲቱ ከተማ ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዲችሉ ደሴቲቱን ከዋናው የብስ የሚያገናኝ መሻገሪያ ደለደለ። ሆኖም ይህን መሻገሪያ ለመደልደል በምን እንደተጠቀመ ልብ በል። ዚ ኢንሳይክለፒዲያ አሜሪካና “በ332 በዋናው የብስ ላይ ያለችውን ከተማ ካጠፋ በኋላ ፍርስራሿን ባሕር ውስጥ በመደልደል ደሴቲቱን ከዋናው የብስ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ የየብስ መሻገሪያ ሠራ” ሲል ዘግቧል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር ከሆነ ከበባ በኋላ የደሴቲቱ ከተማ ተደመሰሰች። ከዚህም በላይ የሕዝቅኤል ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን አግኝቷል። የጥንቷ ጢሮስ ‘ድንጋይዋ፣ እንጨትዋና መሬቷ’ ሳይቀር ‘በባሕር ውስጥ ወድቀዋል።’
13. አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ተጓዥ የጥንቷ ጢሮስ የነበረችበትን ቦታ የገለጸው እንዴት አድርጎ ነው?
13 አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ተጓዥ በእርሱ ዘመን ከጢሮስ ከተማ የተረፈው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ሰሎሞንና የእስራኤል ነቢያት ከሚያውቋት ከጥንቷ ጢሮስ የተረፈ ነገር ቢኖር በተራራው ጥግ ያለው ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራው መቃብርና የመሠረት ድንጋይ ብቻ ነው። . . . ታላቁ እስክንድር የደሴቷን ከተማ በከበበ ጊዜ በደሴቲቱና በዋናው የብስ መካከል ያለውን ውኃ በመደልደል የባሕር ሰርጥ ያደረጋት ደሴት እንኳ ከመስቀል ጦርነቶች በፊት ስላለው ዘመን የሚዘክር ምንም ቅሪት አይገኝባትም። በአንጻራዊ ሁኔታ ስትታይ አዲስ የሆነችው የዛሬዋ ከተማ የምትገኘው በአንድ ወቅት ደሴት በነበረው ሰሜናዊ ክፍል ላይ ሲሆን የቀረው ግን ምን እንደነበረበት እንኳ መለየት በሚያስቸግር ፍርስራሽ የተሞላ ነው።”3
የባቢሎን ተራ
14, 15. ኢሳይያስና ኤርምያስ ባቢሎንን በሚመለከት ምን ትንቢት መዝግበዋል?
14 አይሁዳውያን በባቢሎን አገዛዝ ሥር እንደሚወድቁ የተናገረው ነቢዩ ኢሳይያስ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሌላ አስገራሚ ነገር ተንብዮ ነበር። ይህም ባቢሎን ሙሉ በሙሉ እንደምትደመሰስ የሚገልጽ ነበር። ግልጽ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ተንብዮአል። “እነሆ፣ . . . ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሣለሁ። እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደነበረው፣ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች። ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፣ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም።”—ኢሳይያስ 13:17-20
15 ነቢዩ ኤርምያስም እንዲሁ ባቢሎን እንደምትወድቅ ተንብዮአል። ይህ ከብዙ ዓመታት በኋላ ፍጻሜውን የሚያገኝ ትንቢት ነበር። የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ዝርዝር ጉዳይም ጨምሮ ተናግሯል:- “ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ። . . . የባቢሎን ኃያላት መዋጋትን ትተዋል በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኃይላቸውም ጠፍቷል [“ደርቋል፣” NW]።”—ኤርምያስ 50:38፤ 51:30
16. ባቢሎን ድል የተደረገችው መቼ ነበር? በማንስ?
16 በ539 ከዘአበ ብርቱው የፋርስ ገዥ ቂሮስ በሜዶናውያን ጦር እየታገዘ በከተማይቱ ላይ በዘመተ ጊዜ የባቢሎን የዓለም ኃያልነት አከተመ። ይሁን እንጂ ቂሮስ የገጠመው ነገር ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ባቢሎን በጣም ግዙፍ በሆነ ቅጥር ተከብባለች፤ የምትደፈር አትመስልም። ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝም የሚያልፈው በከተማዋ መሀል በመሆኑ ለከተማዋ መከላከያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ነበረው።
17, 18. (ሀ) ‘የባቢሎን ውኃዎች ደርቀዋል’ ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ‘የባቢሎን ኃያላን መዋጋት የተዉት’ እንዴት ነው?
17 ቂሮስ ይህን ሁኔታ እንዴት እንደተወጣው ሲገልጽ ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ እንዲህ ብሏል:- “የተወሰኑ ወታደሮችን ውኃው ወደ ከተማ በሚገባበት ቦታ ላይ፣ ሌሎቹን ደግሞ ውኃው ከከተማዋ በሚወጣበት ቦታ ካቆመ በኋላ ውኃው ጎድሎ ለመሻገር አመቺ ሲሆን ወዲያው ወንዙን አቋርጠው ወደ ከተማይቱ እንዲዘልቁ ትእዛዝ ሰጠ። . . . የኤፍራጥስንም ወንዝ በቦይ አድርጎ ረግረግ ወደነበረው ጎድጓዳ ስፍራ [በቀድሞው የባቢሎን ገዥ ወደ ተቆፈረ ሰው ሠራሽ ሐይቅ] እንዲፈስ አደረገው። ወንዙ በጣም ስለጎደለ በዚያ መሻገር ቀላል ሊሆን ችሏል። በዚህ ጊዜ ለዚሁ ዓላማ ሲባል በባቢሎን ወንዝ አጠገብ የቀሩት የፋርስ ወታደሮች ውኃው ቀንሶ እስከ ጭን በሚደርሰው ወንዝ አቋርጠው ወደ ከተማይቱ ዘለቁ።”4
18 ኤርምያስና ኢሳይያስ እንዳስጠነቀቁት ከተማይቱ በዚህ መንገድ ወደቀች። ነገር ግን ይህ ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን እንዳገኘ ልብ በል። ቃል በቃል ‘ድርቅ በውኆችዋ ላይ ሆኗል፤ እነርሱም ደርቀዋል።’ ቂሮስ ወደ ከተማዋ እንዲዘልቅ ያስቻለው የኤፍራጥስ ወንዝ መጉደል ነው። ኤርምያስ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀው ‘የባቢሎን ኃያላን መዋጋት ትተው ነበርን?’ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ግሪካውያኑ ታሪክ ጸሐፊዎች ሄሮዶተስና ዜኖፎን እንደመዘገቡት የፋርስ ሰዎች ወረራውን ባካሄዱ ጊዜ ባቢሎናውያኑ ድል ያለ ድግስ ደግሰው በመደሰት ላይ ነበሩ።5 የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተቀረጸውና የናቦኒደስ ዜና ታሪክ በመባል የሚታወቀው ኦፊሴላዊው ዘገባ እንደሚገልጸው የቂሮስ ወታደሮች ወደ ባቢሎን የገቡት “ያለ ጦርነት” ነው። ይህ ሲባል ያን ያህል ከባድ ውጊያ ሳይደረግ ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው።6 ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የባቢሎን ኃያላን ከተማቸውን ለመጠበቅ ብዙም ያደረጉት ነገር አልነበረም።
19. ባቢሎን ‘ዳግመኛ የሚቀመጥባት አይገኝም’ የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷልን? አብራራ።
19 ባቢሎንን “ዳግመኛ የሚቀመጥባት አይገኝም” የሚለውን ትንቢት በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ትንቢት ከ539 ከዘአበ በኋላ ወዲያውኑ ፍጻሜውን አላገኘም። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ምንም ዝንፍ ሳይል ተፈጽሟል። ባቢሎን ከወደቀችበት ጊዜ አንስቶ በ478 ከዘአበ በአሕሻዊሮስ እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ የበርካታ ዓመፆች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች። በአራተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ታላቁ እስክንድር መልሶ ሊገነባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም ሥራው እምብዛም ሳይገፋ እርሱ ሞተ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ከተማዋ እያሽቆለቆለች ሄደች። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ሳይቀር በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ዛሬ ከጥንቷ ባቢሎን የቀረ ነገር ቢኖር በኢራቅ የሚገኘው የፍርስራሽ ክምር ብቻ ነው። ፍርስራሿ በከፊል ቢጠገን እንኳ የጎብኚዎች መስዕብ ትሆን እንደሆነ እንጂ ሞቅ ደመቅ ያለች ከተማ አትሆንም። ባድማ የሆነው አካባቢዋ በእርሷ ላይ የተነገረው ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጣል።
የዓለም ኃይሎች መፈራረቅ
20, 21. ዳንኤል የዓለም ኃያላንን መፈራረቅ በተመለከተ ምን ትንቢታዊ ራእይ ተመልክቷል? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
20 አይሁዳውያን በባቢሎን በምርኮ በነበሩበት በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዳንኤል የሚባል ሌላ ነቢይ በመንፈስ ተነሳስቶ ወደፊት የዓለም ሁኔታ ምን መልክ እንደሚኖረው የሚጠቁሙ አስገራሚ ራእይዎችን መዝግቧል። ዳንኤል ከእነዚህ ራእይዎች በአንዱ ውስጥ አንዳቸው ሌላውን እያስለቀቁ ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ስላሉ ምሳሌያዊ እንስሳት ገልጿል። አንድ መልአክ እንደገለጸው እነዚህ እንስሳት ከዚያ ጊዜ አንስቶ የሚፈራረቁትን የዓለም ኃይሎች የሚያመለክቱ ናቸው። ስለ መጨረሻዎቹ ሁለት እንስሳት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሱ፣ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፣ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።”—ዳንኤል 8:20-22
21 ይህ ትንቢታዊ መግለጫ በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። የባቢሎናውያን አገዛዝ በሜዶ ፋርስ ሲገለበጥ ከ200 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሜዶ ፋርስ የዓለም ኃይል ሆኖ ብቅ ላለው ለግሪክ ቦታውን ለቅቋል። የግሪክ መንግሥት የሚመራው ‘በታላቁ ቀንድ’ ማለትም በታላቁ እስክንድር ነበር። ይሁን እንጂ እርሱ ከሞተ በኋላ ጄኔራሎች ለሥልጣን መሻኮት ጀመሩ። በመጨረሻም ሰፊ የነበረው ግዛቱ በአራት ትናንሽ ግዛቶች ማለትም ‘በአራት መንግሥታት’ ተከፋፈለ።
22. ከዓለም ኃያላን መፈራረቅ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ተጨማሪ የዓለም ኃይል ትንቢት ተነግሯል?
22 በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይም ገና ከረጅም ጊዜ በኋላ ፍጻሜውን ማግኘት የነበረበት ተመሳሳይ ትንቢት ተገልጿል። የባቢሎናውያን የዓለም ኃይል በአንበሳ፣ የፋርስ በድብ እንዲሁም የግሪክ ጀርባዋ ላይ አራት ክንፎች ባሏት ባለ አራት ራስ ነብር ተመስለዋል። ከዚያም ዳንኤል ‘የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች አሥር ቀንዶችም የነበሩዋት’ አውሬ ተመለከተ። (ዳንኤል 7:2-7) አራተኛዋ አውሬ ጥላ የሆነችለት ኃያል የነበረው የሮም አገዛዝ ብቅ ማለት የጀመረው ዳንኤል ትንቢቱን ከጻፈ ሦስት መቶ ዘመናት ገደማ ቆይቶ ነው።
23. በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጸችው አራተኛዋ አውሬ ‘ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የተለየች’ የሆነችው በምን መንገድ ነው?
23 መልአኩ ሮምን በሚመለከት ትንቢት ተናግሯል:- “አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፣ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፣ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።” (ዳንኤል 7:23) ኤች ጂ ዌልስ ኤ ፖኬት ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “በሁለተኛውና በአንደኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በምዕራቡ ዓለም የበላይነትን ተቀዳጅቶ ብቅ ያለው ይህ አዲሱ የሮም ኃይል እስካሁን ድረስ በሰለጠነው ዓለም ከታዩት ከየትኞቹም ታላላቅ ግዛቶች ሁሉ በበርካታ መንገዶች የተለየ ነው።”7 አጀማመሩ እንደ ሪፐብሊካዊ አገዛዝ ቢሆንም በመጨረሻው ንጉሣዊ አገዛዝ ሆኗል። እንደ ሌሎቹ ግዛቶች በአንድ ድል አድራጊ የተፈጠረ ሳይሆን ለብዙ መቶ ዘመናት የማያቋርጥ እድገት ሲያደርግ የኖረ መንግሥት ነው። ከዚያ ቀደም ከነበሩት መንግሥታት የግዛት ዘመን ሁሉ ለሚበልጥ ጊዜ የዘለቀና ግዛቱም ከየትኛውም መንግሥት የበለጠ ስፋት የሚያካልል ነበር።
24, 25. (ሀ) የአውሬው አሥር ቀንዶች ብቅ ያሉት እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል በአውሬው ቀንዶች መካከል ስለሚደረገው ስለየትኛው ትግል አስቀድሞ ተመልክቷል?
24 ይሁን እንጂ ስለዚህ ግዙፍ የሆነ አውሬ አሥር ቀንዶችስ ምን ማለት ይቻላል? መልአኩ እንዲህ ብሏል:- “አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፣ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፣ ሦስቱን ነገሥታት ያዋርዳል።” (ዳንኤል 7:24) ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
25 በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የሮማ ግዛት እየተዳከመ መሄድ ሲጀምር ወዲያውኑ በሌላ የዓለም ኃይል አልተተካም። ከዚህ ይልቅ ወደተለያዩ “አሥር መንግሥት” ተከፋፈለ። በመጨረሻም የብሪታንያ ግዛት ተቀናቃኝ የነበሩትን ሦስቱን የስፔይን፣ የፈረንሳይና የኔዘርላንድስን መንግሥታት ድል በማድረግ ዋና የዓለም ኃይል ሆነ። በዚህ መንገድ አዲስ የመጣው ‘ቀንድ’ ሌሎቹን “ሦስቱን ነገሥታት” አዋርዷቸዋል።
የዳንኤል ትንቢቶች—ከክንውኑ በኋላ የተጻፉ ናቸውን?
26. ተቺዎች ዳንኤል መጽሐፉን ጽፏል የሚሉት በየትኛው ጊዜ ነው? ለምንስ?
26 መጽሐፍ ቅዱስ የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደሆነ ይጠቁመናል። ይሁን እንጂ ትንቢቶቹ ፍጹም ትክክለኛ የሆነ ፍጻሜያቸውን ከማግኘታቸው የተነሣ ተቺዎች ትንቢቱ የተጻፈው በትንቢቱ ውስጥ ያሉት በርካታዎቹ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ በ165 ከዘአበ ገደማ መሆን አለበት ብለዋል።8 እንዲህ ለማለት ያበቃቸው ብቸኛውና እውነተኛው ምክንያት የዳንኤል ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ቢሆንም የዳንኤል ትንቢት ተጻፈ የሚባልበት ይህ ዘመን እንደ ትክክለኛ ወቅት እንደሆነ ተቆጥሮ በብዙ የማመሳከሪያ ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል።
27, 28. የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በ165 ከዘአበ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡት አንዳንድ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
27 ይሁንና ይህን አባባል የሚቃረኑትን የሚከተሉትን እውነታዎች ማጤን ይኖርብናል። በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፉ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በተዘጋጁ እንደ መቃባውያን የመጀመሪያ መጽሐፍ ባሉት የአይሁዳውያን የጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ተካትቷል። የዚህ ትርጉም ሥራ የተጀመረው በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነው።9 በሦስተኛ ደረጃ የዳንኤል መጽሐፍ ቅጂ ቁርጥራጮች በሙት ባሕር ከተገኙት ጥቅልሎች መካከል በተደጋጋሚ የሚታይ ሲሆን እነዚህ ቁርጥራጮች ደግሞ በ100 ከዘአበ የተዘጋጁ እንደሆኑ ይታመናል።10 የዳንኤል መጽሐፍ ተጻፈ በሚባልበት ዘመን በሰፊው የሚታወቅና ከፍተኛ አክብሮት ያተረፈ ሆኖ ነበር። ይህም ተቺዎቹ ከሚሉት ዘመን ከረጅም ጊዜ በፊት እንደተጻፈ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
28 ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል በሁለተኛው መቶ ዘመን የሚኖር ጸሐፊ ሊያውቃቸው የማይችላቸውን ታሪካዊ ሁኔታዎች ይዞ እናገኘዋለን። ከነዚህ መካከል ሊጠቀስ የሚገባው ባቢሎን በ539 ከዘአበ በወደቀች ጊዜ የተገደለው የባቢሎን ገዥ የብልጣሶር ጉዳይ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ስለ ባቢሎን መውደቅ መረጃ የምናገኝባቸው ጉልህ ምንጮች ሄሮዶተስ (አምስተኛው መቶ ዘመን)፣ ዜኖፎን (አምስተኛውና አራተኛው መቶ ዘመን) እንዲሁም ቤሮሰስ (ሦስተኛው መቶ ዘመን) ናቸው። ከእነርሱ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ስለ ብልጣሶር የሚያውቁት ነገር የለም።11 ከእርሱ በፊት የነበሩት እነዚህ ጸሐፊዎች ሊያውቁ ያልቻሉትን ነገር በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረ ጸሐፊ እንዴት ሊያውቅ ይችላል! በዳንኤል ምዕራፍ 5 ላይ ብልጣሶርን በሚመለከት የሰፈረው ታሪክ ዳንኤል መጽሐፉን የጻፈው እነዚህ ጸሐፊዎች የጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ከማዘጋጀታቸው አስቀድሞ እንደሆነ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።a
29. የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በውስጡ የያዛቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ካገኙ በኋላ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
29 በመጨረሻም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ከ165 ከዘአበ ብዙ ቆይተው ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል የሮማን መንግሥት በሚመለከት የተነገረውና ቀደም ሲል የጠቀስነው ትንቢት ይገኝበታል። ሌላው በጣም አስደናቂ ትንቢት ደግሞ ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚናገረው ትንቢት ነው።
የመሲሑ መምጣት
30, 31. (ሀ) መሲሑ ስለሚገለጥበት ጊዜ የሚናገረው የትኛው የዳንኤል ትንቢት ነው? (ለ) በዳንኤል ትንቢት መሠረት መሲሑ የሚገለጥበትን ዓመት ማስላት የምንችለው እንዴት ነው?
30 ይህ ትንቢት ተመዝግቦ የሚገኘው በዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ ሲሆን እንዲህ ይነበባል:- “በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ [የዓመታት ሳምንታት ወይም 490 ዓመታት] ተቀጥሮአል።”b (ዳንኤል 9:24 ዚ አምፕሊፋይድ ባይብል) በእነዚህ 490 ዓመታት ውስጥ የሚከናወነው ነገር ምንድን ነው? እንዲህ እናነባለን:- “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ ቅቡዕ [መምጣት] ድረስ ሰባት ሱባዔና [የዓመታት ሳምንታት] ስድሳ ሁለት ሱባዔ [የዓመታት ሳምንታት] ይሆናል።” (ዳንኤል 9:25 ኤቢ) በመሆኑም ይህ ‘የተቀባው’ መሲሕ የሚመጣበትን ጊዜ የሚጠቁም ትንቢት ነው። ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
31 ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ‘ትእዛዝ የወጣው’ የፋርስ ንጉሥ በነበረው “በንጉሥ አርጤክስስ በሃያኛው ዓመት” ሲሆን ይህም በ455 ከዘአበ ነው። (ነህምያ 2:1-9) 49ኛው ዓመት (7 የዓመታት ሳምንታት) ሲያበቃ ኢየሩሳሌም አብዛኛውን ክብሯን መልሳ አግኝታለች። ከ455 ከዘአበ ተነስተን ሙሉውን 483 ዓመታት (7 እና 62 የዓመታት ሳምንታት) ስንቆጥር ወደ 29 እዘአ እንደርሳለን። ይህ ደግሞ ‘ጢባሪዮስ ቄሣር የነገሠበት አሥራ አምስተኛ ዓመት’ ሲሆን ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀው በዚሁ ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 3:1) በዚህ ወቅት ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑ በይፋ ታውቆ ለአይሁድ ብሔር ምሥራቹን በመስበክ አገልግሎቱን ጀምሯል። (ማቴዎስ 3:13-17፤ 4:23) ‘ቅቡዕ’ ወይም መሲሕ የሆነው በዚህ ጊዜ ነበር።
32. በዳንኤል ትንቢት መሠረት የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ለምን ያህል ጊዜ የሚዘልቅ ነው? ይህ ጊዜ ሲፈጸምስ ምን ነገር ይከናወናል?
32 ትንቢቱ በመጨመር እንዲህ ይላል:- “ከስድሳ ሁለት [የዓመታት] ሳምንትም በኋላ የተቀባው ይገደላል።” አክሎም “እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሳምንት [ሰባት ዓመታት] ያደርጋል፤ በሳምንቱም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቁርባኑን ያስቀራል።” (ዳንኤል 9:26, 27, ኤቢ) ከዚህ ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ኢየሱስ የሄደው ወደ ‘ብዙዎች’ ማለትም ወደ ሥጋዊ አይሁዳውያን ብቻ ነበር። በተወሰነው የቅዱስ ጽሑፉ ክፍል ያምኑ ለነበሩት ነገር ግን ከዋናው የአይሁድ እምነት ተገንጥለው የራሳቸውን ወገን ለመሠረቱት ሳምራውያንም የሰበከባቸው ወቅቶች ነበሩ። ከዚያም ‘በሳምንቱ እኩሌታ’ ማለትም ለሦስት ዓመት ተኩል ከሰበከ በኋላ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ፣ በሌላ አባባል ‘ተቆረጠ።’ ይህም የሙሴ ሕግ ከነመሥዋዕቱና ቁርባኑ ወደ ፍጻሜው እንደመጣ የሚያሳይ ነበር። (ገላትያ 3:13, 24, 25) በመሆኑም ኢየሱስ በሞቱ ‘መሥዋዕቱና ቁርባኑ’ እንዲቀር አድርጓል።
33. ይሖዋ ትኩረቱን በአይሁዳውያን ላይ ብቻ አድርጎ የሚቆየው እስከ መቼ ነበር? ይህ ጊዜ እንዳበቃ ያሳየውስ ምንድን ነበር?
33 የሆነ ሆኖ አዲሱ የክርስቲያን ጉባኤ ለተጨማሪ ሦስት ዓመት ተኩል ለአይሁዳውያን ብቻና ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ለሚዛመዱት ሳምራውያን ሰብኳል። ይሁን እንጂ ሰባው የዓመታት ሳምንታት በ36 እዘአ ሲያበቁ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ለነበረው ለቆርኔሌዎስ እንዲሰብክ መመሪያ ተሰጥቶታል። (ሥራ 10:1-48) ከዚህ በኋላ ‘ከብዙዎች ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን’ ለአይሁዳውያን ብቻ የተወሰነ መሆኑ ቀረ። ላልተገረዙትም አሕዛብ ጭምር መዳን ተሰበከላቸው።
34. ከዳንኤል ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ሥጋዊ እስራኤላውያን መሲሑን ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው ምን ደሶባቸዋል?
34 የአይሁድ ብሔር ኢየሱስን አልቀበልም በማለቱና እንዲገደል በማሴሩ ሮማውያን መጥተው በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምን ሲያጠፉ ይሖዋ ሳያስጥላቸው ቀርቷል። በዚህ መንገድ የሚከተሉት የዳንኤል ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል:- “የሚመጣውም ሌላው አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጎርፍ ይሆናል፣ እስከ መጨረሻም ድረስ በጦርነት ይሆናል።” (ዳንኤል 9:26 ኤቢ) ይህ ሁለተኛው “አለቃ” ኢየሩሳሌምን በ70 እዘአ ያጠፋው ሮማዊው ጄኔራል ቲቶ ነው።
በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረ ትንቢት
35. ስለ ኢየሱስ የተነገሩት የትኞቹ ተጨማሪ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል?
35 በዚህ መንገድ ዳንኤል ስለ ሰባው ሳምንታት የተናገረው ትንቢት በአስገራሚ ሁኔታ በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። እርግጥ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነው። ከእነዚህ መካከል በርከት ያሉትም ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ትንቢቶች ናቸው። ኢየሱስ የሚወለድበት ቦታ፣ ለአምላክ ቤት የሚኖረው ቅንዓት፣ የስብከት እንቅስቃሴው፣ በ30 ብር አልፎ እንደሚሰጥ፣ አሟሟቱ፣ በልብሱ ላይ ዕጣ መጣጣላቸውና የመሳሰሉት ዝርዝር ሁኔታዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በትንቢት ተነግረዋል። እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ያለ ምንም ጥርጥር ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን ትንቢቶቹም በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነበር።—ሚክያስ 5:2፤ ሉቃስ 2:1-7፤ ዘካርያስ 11:12፤ 12:10፤ ማቴዎስ 26:15፤ 27:35፤ መዝሙር 22:18፤ 34:20፤ ዮሐንስ 19:33-37
36, 37. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ምን ነገር ያስተምረናል? ይህንንስ ማወቃችን ምን ትምክህት እንድናሳድር ያደርገናል?
36 መፈጸም የነበረባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሁሉም ነገሮች ልክ መጽሐፍ ቅዱስ በተናገረላቸው መሠረት ተፈጽመዋል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ይህን ያህል ትክክል ሊሆኑ የቻሉት ከበስተጀርባ ያለው ኃይል ከሰብዓዊ ጥበብ እጅግ የላቀ ነገር በመሆኑ ነው።
37 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚያ ዘመን ፍጻሜያቸውን ያላገኙ ሌሎች ትንቢቶችም ይገኛሉ። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ትንቢቶች የሚፈጸሙት በዚህ በእኛ ዘመንና ገና ወደፊት በመሆኑ ነው። የጥንቶቹ ትንቢቶች አስተማማኝ ሆነው መገኘት እነዚህ ሌሎች ትንቢቶችም ያለምንም ጥርጥር እንደሚፈጸሙ ማረጋገጫ ይሆነናል። ደግሞም ይህ አባባል እውነት እንደሆነ በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ብሉይ ኪዳን ምን ያህል ተዓማኒነት አለው?” የሚለውን ምዕራፍ 4 አንቀጽ 16ና 17 ተመልከት።
b በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ በቅንፍ የተቀመጡት ሐሳቦች ተርጓሚው ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ የጨመራቸው ናቸው።
[በገጽ 133 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መፈጸም የነበረባቸው ትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሁሉም ነገሮች ልክ መጽሐፍ ቅዱስ በተናገረላቸው መሠረት ተፈጽመዋል
[በገጽ 118 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ጨርሶ እንዳጠፋት አርኪኦሎጂስቶች ደርሰውበታል
[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዘመናችን ያለችው ጢሮስ ፎቶግራፍ። የእስራኤል ነቢያት ከሚያውቋት ጢሮስ አንዳች የቀረ ነገር የለም
[በገጽ 123 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንቷ ባቢሎን የነበረችበትን ቦታ የሚጎበኙ ሰዎች በከተማዋ ላይ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ስለማግኘቱ ምሥክሮች ናቸው
[በገጽ 126 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳንኤል የዓለም ኃያላንን መፈራረቅ በተመለከተ የተናገረው ትንቢት በትክክል ፍጻሜውን ከማግኘቱ የተነሣ የዘመናችን ተቺዎች ትንቢቱ የተጻፈው ነገሮቹ ከተፈጸሙ በኋላ ነው ብለው አስበዋል
ባቢሎን
ፋርስ
ግሪክ
ሮም
ብሪታንያ
[በገጽ 130 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳንኤል መሲሑ በእስራኤል የሚገለጥበትን ትክክለኛ ጊዜ በትንቢት ተናግሯል
-
-
አንተ ራስህ ሲፈጸም ያየኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትመጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
-
-
ምዕራፍ 10
አንተ ራስህ ሲፈጸም ያየኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት
ዛሬ ያሉት ሁኔታዎች ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት ከነበሩት በጣም የተለዩ የሆኑት ለምን ይሆን ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አንዳንድ ነገሮች ተሻሽለዋል። ያኔ ሰው ይጨርሱ የነበሩት በሽታዎች ዛሬ በብዙ አገሮች ውስጥ በቀላሉ ይፈወሳሉ። በዛሬው ጊዜ ያለው የኑሮ ደረጃ አያት ቅድመ አያቶቻችን ፈጽሞ አልመውትም ሆነ አስበውት የማያውቁት ነው ለማለት ይቻላል። በአንጻሩ ደግሞ በዚህ በእኛ ዘመን እጅግ አስከፊ ጦርነቶችና በሰው ዘር ታሪክ ከደረሱት አሰቃቂ እልቂቶች ሁሉ የከፉ ድርጊቶች ታይተዋል። ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት፣ የአካባቢ መበከልና በዓለም ዙሪያ በብዛት ተከማችተው የሚገኙት የኑክሊየር፣ ባዮሎጂያዊና ኬሚካላዊ ጦር መሣሪያዎች የሰውን ልጅ ብልጽግና አልፎ ተርፎም ሕልውናውን ሥጋት ላይ ጥለውታል። ይህ ሃያኛው መቶ ዘመን ከቀደሙት መቶ ዘመናት ሁሉ ይህን ያህል የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?
1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ሃያኛው መቶ ዘመን ከዚያ ቀደም ከነበሩት መቶ ዘመናት የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) ጊዜያችን ልዩ የሆነበትን ምክንያት እንድንገነዘብ የሚረዳን ምንድን ነው?
የዚህ ጥያቄ መልስ አንተ ራስህ ሲፈጸም ካየኸው አንድ አስገራሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር የተዛመደ ነው። ይህ ኢየሱስ ራሱ የተናገረው ትንቢት መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በዓለም ላይ እጅግ አስገራሚ ለውጥ ሊካሄድ በተቃረበበት ዘመን ላይ እንደምንኖር የሚጠቁም ነው። ይህ ትንቢት ምንድን ነው? ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለስ እንዴት እናውቃለን?
ታላቁ የኢየሱስ ትንቢት
2, 3. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን የጠየቁት ጥያቄ ምን ነበር? የሰጠውን መልስስ የት ላይ እናገኘዋለን?
2 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም ስለ ነበረው ድንቅ የቤተ መቅደስ ሕንጻ ይወያያሉ። በቤተ መቅደሱ ግዝፈትና ጥንካሬ ተደንቀው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፣ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።”—ማቴዎስ 24:1, 2
3 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዚህ አባባሉ ተገርመው መሆን አለበት። ደቀ መዛሙርቱ ትንሽ ቆየት ብለው መጡና ተጨማሪ ጥያቄ አቀረቡለት:- “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምንድን ነው?” (ማቴዎስ 24:3 NW) ኢየሱስ የሰጠው መልስ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ውስጥ ይገኛል። እነዚሁ ነገሮች በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና ሉቃስ ምዕራፍ 21 ውስጥም ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከተናገራቸው ትንቢቶች ሁሉ ይበልጥ በጣም አስፈላጊ ትንቢት ነው።
4. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያቀረቡት ጥያቄ የትኞቹን የተለያዩ ነገሮች የሚመለከት ነው?
4 እርግጥ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የጠየቁት ስለ አንድ ነገር ብቻ አልነበረም። በመጀመሪያ ያነሱት ጥያቄ “እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ?” የሚል ነው። በሌላ አባባል ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ የሚጠፉት መቼ ነው? ማለታቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በሥልጣኑ መገኘቱንና የዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ መቅረቡን የሚያሳዩትን ምልክቶች ለማወቅ ፈልገው ነበር።
5. (ሀ) የኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር? ይሁን እንጂ የተናገራቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼ ነው? (ለ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ላነሱት ጥያቄ የሰጠውን መልስ የጀመረው እንዴት ነው?
5 የኢየሱስ መልስ እነዚህን ሁለት ነጥቦች ያካተተ ነበር። ኢየሱስ የተናገራቸው ብዙዎቹ ነገሮች በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው አሰቃቂ ጥፋት በፊት በነበሩት ዓመታት ውስጥ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (ማቴዎስ 24:4-22) ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት በተለይ ለእኛ ዘመን ከዚያ የበለጠ ትርጉም ያዘለ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ምን አለ? መልሱን የጀመረው በቁጥር 7 እና 8 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት ቃላት ነበር:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።”
6. በማቴዎስ 24:7, 8 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት የትኛውን ተመሳሳይ ትንቢት ያስታውሱናል?
6 ኢየሱስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ ታላቅ ሁከት እንደሚሆን ግልጽ ነው። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ስለ አራቱ ፈረሰኞች የሚናገረው ከዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆነው ትንቢት ይህ ሁኔታ እንደሚኖር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። (ራእይ 6:1-8) ከእነዚህ ፈረሰኞች የመጀመሪያው የሚያመለክተው ድል አድራጊ ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስን ነው። ሌሎቹ ጋላቢዎችና ፈረሶቻቸው ኢየሱስ መግዛት ሲጀምር በምድር ላይ የሚከሰቱትን እንደ ጦርነት፣ ረሃብና በተለያዩ ምክንያቶች በሞት መቀጨት የመሳሰሉትን ሁኔታዎች የሚያመለክቱ ናቸው። ዛሬ እነዚህ ሁለት ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነውን?
ጦርነት!
7. በራእይ ውስጥ በተገለጸው ሁለተኛ ፈረሰኛ በትንቢታዊ ሁኔታ የተመሰለው ነገር ምንድን ነው?
7 እስቲ እነዚህን ትንቢቶች በጥልቀት እንመርምር። በመጀመሪያ ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” ብሏል። ይህ ስለ ጦርነት የተነገረ ትንቢት ነው። ከአራቱ የራእይ ፈረሰኞች መካከል ሁለተኛውም እንዲሁ ጦርነትን የሚያመለክት ነው። እንዲህ እናነባለን:- “ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” (ራእይ 6:4) የሰው ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲዋጋ ኖሯል። ታዲያ እነዚህ ቃላት ለእኛ ዘመን ልዩ ትርጉም እንዲኖራቸው የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
8. ጦርነት የምልክቱ ጉልህ ገጽታ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?
8 ጦርነት ብቻውን ለኢየሱስ መገኘት ምልክት እንደማይሆን አስታውስ። ምልክቱ በጥቅሉ ሲታይ በተመሳሳይ ወቅት የሚፈጸሙትን በኢየሱስ ትንቢት ውስጥ የተዘረዘሩትን ክንውኖች ሁሉ ያቀፈ ነው። ይሁን እንጂ ከምልክቱ ገጽታዎች መካከል መጀመሪያ የተጠቀሰው ጦርነት በመሆኑ ትኩረታችንን በሚስብ አስገራሚ መንገድ ፍጻሜውን ያገኛል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ጥንት የተደረጉት ጦርነቶች በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከተደረጉት ጦርነቶች ጋር ፈጽሞ እንደማይተካከሉ የሚክድ ሰው አይኖርም።
9, 10. ጦርነትን በሚመለከት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት የጀመሩት እንዴት ነው?
9 ለምሳሌ ያህል ጥንት የተደረጉት ብዙዎቹ ጦርነቶች የቱንም ያህል ጭካኔ የሞላባቸውና ብዙ ውድመት ያስከተሉ ቢሆኑም እንኳ ያደረሱት ጥፋት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከታዩት ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ጋር መተካከል ቀርቶ ጨርሶ አይቀርቡም። እንዲያውም አንደኛው የዓለም ጦርነት ከብዙዎቹ አገሮች ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ የሰው ሕይወት ማለትም የ14 ሚልዮን ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። እውነትም “ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን” ተሰጥቶታል ማለት እንችላለን።
10 እንደ ትንቢቱ አገላለጽ ከሆነ በጦርነት ለተመሰለው ለሁለተኛው የራእይ ፈረሰኛ ‘ትልቅ ሰይፍ ተሰጥቶታል።’ ይህ ምን ማለት ነው? የጦር መሣሪያዎች ከበፊቱ እጅግ የከፋ እልቂት የሚያስከትሉ ይሆናሉ። በታንክ፣ በአውሮፕላን፣ ገዳይ በሆኑ መርዘኛ ጋዞች፣ በሰርጓጅ መርከቦች እንዲሁም ብዙ ኪሎ ሜትሮች በሚወነጨፉ ሚሳይሎች የታጠቀው የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መሰሉን በቀላሉ ለመግደል የሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ደግሞ የራዲዮ መገናኛዎች፣ ራዳሮች፣ የተራቀቁ ጠብመንጃዎች፣ ባክቴሪያዊና ኬሚካላዊ የጦር መሣሪያዎች፣ እሳት የሚተፉ መሣሪያዎች፣ የናፓልም ጋዞች፣ አዳዲስ የቦምብ ዓይነቶች፣ አሕጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች፣ ኑክሊየር ተሸካሚ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች፣ የተራቀቁ አውሮፕላኖች እንዲሁም ግዙፍ የጦር መርከቦች በመሠራታቸው ‘ታላቁ ሰይፍ’ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አውዳሚ ሆኗል።
“የምጥ ጣር መጀመሪያ”
11, 12. አንደኛው የዓለም ጦርነት “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ብቻ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
11 የኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያዎቹ ቁጥሮች የሚደመደሙት “እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው” በሚሉት ቃላት ነው። ይህ በተለይ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እውነት ሆኖ ታይቷል። የአንደኛው ዓለም ጦርነት በ1918 ማብቃቱ ያስገኘው ሰላም ላፍታም አልቆየም። ወዲያው በኢትዮጵያ፣ በሊቢያ፣ በስፔይን፣ በሩስያ፣ በሕንድና በሌሎችም አገሮች ላይ መለስተኛ መጠን የነበራቸው ነገር ግን አስከፊ ውጤት ያስከተሉ ወታደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ወታደሮችንና ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውና እጅግ አስፈሪ የነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቷል።
12 ከዚህም በላይ ጊዜያዊ የሰላም ስምምነቶች ቢደረጉና ጦርነቶች አንዳንዴ ጋብ ቢሉም ዛሬም የሰው ልጅ ከጦርነት አላረፈም። በ1987 ሪፖርት እንደተደረገው ከ1960 ወዲህ የተደረጉት 81 ትላልቅ ጦርነቶች የ12,555,000 ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነዋል። በ1987 የተካሄዱት ጦርነቶች መጠን ከዚያ ቀደም በነበረ በየትኛውም ዓመት ከተደረጉት ጦርነቶች ቁጥር እጅግ የሚበልጥ ነበር።1 ከዚህም በላይ ለጦር ዝግጅቶችና ወታደራዊ ወጪዎች በየዓመቱ የሚወጣው ጠቅላላ ገንዘብ ወደ 1,000,000,000,000 የአሜሪካ ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም የዓለምን ኤኮኖሚ የሚያዛባ ነው።2 ኢየሱስ ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል’ ሲል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ዳማው የጦርነት ፈረስ በምድር ላይ አስፈሪ ግልቢያውን ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ስለ ምልክቱ ሁለተኛ ዘርፍ ምን ማለት ይቻላል?
የምግብ እጥረት!
13. ኢየሱስ ስለ የትኛው አሳዛኝ ሁኔታ አስቀድሞ ተናግሯል? ስለ ሦስተኛው የራእይ ፈረሰኛ የተሰጠው መግለጫስ የእርሱን ትንቢት የሚደግፈው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ “ራብም [“የምግብ እጥረትም።” NW] . . . በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” ሲል ተንብዮአል። ይህ ሁኔታ በራእይ ላይ ከተገለጸው ሦስተኛ ፈረሰኛ ግልቢያ ጋር እንዴት እንደሚስማማ ልብ በል። ይህን ፈረሰኛ በሚመለከት እንዲህ የሚል ሐሳብ ተጠቅሶልናል:- “አየሁም፣ እነሆም፣ ጒራቻ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ:- አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፣ ዘይትንና ወይንንም አትጒዳ ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:5, 6) አዎን፣ ከባድ የምግብ እጥረት እንደሚኖር የሚያሳይ ነው!
14. የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረጉት ከ1914 ወዲህ የተከሰቱት የትኞቹ ታላላቅ ረሃቦች ናቸው?
14 አንዳንድ አገሮች ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በደረሱበት በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነው ለማለት ይቻላልን? የመላውን ዓለም ሁኔታ መለስ ብሎ መቃኘት ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ ይሰጠናል። ከታሪክ መረዳት እንደምንችለው የረሃብ መንስኤዎች ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው። እንግዲያው ከአቅሙ በላይ የተፈጥሮ አደጋዎችንና ጦርነቶችን እያስተናገደ ያለው ይህ የእኛ መቶ ዘመን በተደጋጋሚ በረሃብ አለንጋ መገረፉ ምንም አያስገርምም። ከ1914 ወዲህ ብዙዎቹ የዓለም ክፍሎች በእነዚህ አደጋዎች ተጠቅተዋል። አንድ ሪፖርት እንደዘገበው ከ1914 ወዲህ ተራርቀው በሚገኙ በግሪክ፣ በኔዘርላንድስ፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት፣ በናይጄርያ፣ በቻድ፣ በቺሊ፣ በፔሩ፣ በባንግላዴሽ፣ በቤንጋል፣ በካምፖዲያ፣ በኢትዮጵያና በጃፓን 60 ከባድ ረሃቦች እንደደረሱ ተመዝግቧል።3 ከእነዚህ ረሃቦች መካከል አንዳንዶቹ በርከት ላሉ ዓመታት የዘለቁ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወትም ቀጥፈዋል።
15, 16. ዛሬ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ላይ ያለው ሌላው የምግብ እጥረት የትኛው ነው?
15 አስከፊ የረሃብ አደጋዎች ሲከሰቱ ጉዳዩ ሰፊ መወያያ ይሆንና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ችግሩ ሲያልፍ ከረሃቡ የተረፉት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ወደ ቀድሞው ኑሯቸው ይመለሳሉ። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን ሌላ ዓይነት አስጊ የምግብ እጥረት ብቅ ብሏል። ይህ የዚያን ያክል የከፋ ባለመሆኑ ብዙውን ጊዜ በቸልታ ይታለፋል። ነገር ግን ችግሩ ከዓመት ዓመት ይቀጥላል። ይህ ከፕላኔታችን ነዋሪዎች መካከል አንድ አምስተኛውን የሚያጠቃ የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር ሲሆን በየዓመቱ ከ13 እስከ 18 ሚልዮን ለሚያክሉ ሰዎች ሞት ምክንያት ይሆናል።4
16 በሌላ አባባል ከእንዲህ ዓይነቱ የምግብ እጥረት የተነሣ በሂሮሽማ በአቶም ቦምብ የሞቱትን ሰዎች የሚያክል ብዛት ያላቸው ሰዎች በየሁለቱ ቀን ይሞታሉ። እንዲያውም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከረሃብ የተነሣ የሚሞቱት ሰዎች ብዛት በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሞቱት ወታደሮች ጠቅላላ ቁጥር ይበልጣል። ከ1914 ወዲህ ‘በልዩ ልዩ ቦታ የምግብ እጥረት’ ነበረን? አዎን፣ ነበር!
የመሬት መንቀጥቀጦች
17. ከ1914 በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተከሰተው ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ የመሬት መንቀጥቀጥ የትኛው ነው?
17 አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ በጥር 13, 1915 በኢጣሊያ አብሩዚ ከተማ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የ32,610 ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ይህ ከፍተኛ አደጋ በኢየሱስ መገኘት ጊዜ ከሚታዩት ጦርነቶችና ረሃብ በተጨማሪ የሚታየውን ሌላ ክስተት ያስታውሰናል:- “የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል።” እንደ ጦርነቱና ረሃቡ ሁሉ በአብሩዚ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥም ‘የምጥ ጣር መጀመሪያ’ ብቻ ነበር።a
18. ኢየሱስ የመሬት መንቀጥቀጥን በሚመለከት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
18 ሃያኛው መቶ ዘመን የመሬት መንቀጥቀጦች ዘመን ሆኗል። ከፍተኛ እድገት ያደረገው የመገናኛ ብዙሐን ምስጋና ይግባውና የሰው ዘር በሙሉ እነዚህ የመሬት መንቀጥቀጦች ስለሚያደርሱት ጉዳት አሳምሮ ያውቃል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በ1920 ቻይና ውስጥ በመሬት መንቀጥቀጥ 200,000 ሰዎች ሲሞቱ በ1923 በጃፓን 99,300 ሰዎች፣ በ1935 ደግሞ በሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ በዛሬዋ ፓኪስታን 25,000 ሰዎች አልቀዋል። በ1939 በቱርክ 32,700 ሰዎች፣ በ1970 በፔሩ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ 66,800 ሰዎች ሞተዋል። እንዲሁም በ1976 በቻይና ታንግሻን ወደ 240,000 ሰዎች (ወይም እንደ አንዳንዶቹ ምንጮች 800,000) ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በ1988 ደግሞ በአርሜኒያ በተከሰተው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ 25,000 የሚያህሉ ሰዎች ሞተዋል።b በእርግጥም ‘በልዩ ልዩ ስፍራ የመሬት መንቀጥቀጥ’ ተከስቷል!6
‘ቀሳፊ በሽታዎች’
19. ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረለትና አራተኛው የራእይ ፈረሰኛ ጥላ የሆነለት የትኛው የምልክቱ ክፍል ነው?
19 ሌላው በኢየሱስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰው ነገር በሽታ ነው። ወንጌላዊው ሉቃስ በዘገባው ውስጥ ኢየሱስ “በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” ይሆናል ሲል እንደተነበየ መዝግቧል። (ሉቃስ 21:11) ይህም ቢሆን ከራእይ አራት ፈረሰኞች ትንቢታዊ ራእይ ጋር ይስማማል። የአራተኛው ፈረሰኛ ስም ሞት ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተውን ድንገተኛ ሞት የሚያመለክት ሲሆን ‘ቀሳፊ በሆኑ በሽታዎችና በምድር አራዊት’ የሚሞቱትንም ይጨምራል።—ራእይ 6:8 NW
20. ኢየሱስ ስለ ቸነፈር የተናገረው ትንቢት በከፊል ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያስቻለው የትኛው ጎላ ብሎ የሚጠቀስ ወረርሽኝ ነው?
20 በ1918 እና 1919 ቁጥራቸው ከ1,000,000,000 በላይ ሰዎች በኅዳር በሽታ ተይዘው ከ20,000,000 የሚበልጡት ሞተዋል። በሽታው የገደላቸው ሰዎች ቁጥር በታላቁ ጦርነት ከሞቱት ሰዎች በልጦ ተገኝቷል።7 ከዚህም ሌላ ዛሬ የሕክምናው መስክ እጅግ አስገራሚ መሻሻሎችን ያደረገ ቢሆንም ‘ቀሳፊ በሽታዎች’ ወይም ‘ቸነፈሮች’ ይህን ትውልድ ማሰቃየታቸውን አላቆሙም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ድሃ አገሮች ከሳይንሳዊ እድገት ተጠቃሚ የመሆን አጋጣሚያቸው ውስን መሆኑ ነው። ድሃ የሆኑ ሰዎች በቀላሉ ታክመው ሊድኑ ሲችሉ የገንዘብ አቅማቸው ስለማይፈቅድ ብቻ ታመው ይሞታሉ።
21, 22. በሃብታምም ሆነ በድሃ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ‘ቀሳፊ በሆኑ በሽታዎች’ የተጠቁት እንዴት ነው?
21 ከዚህ የተነሣ በምድር ዙሪያ ከ300 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወባ በሽታ ይሰቃያሉ። 200 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ደግሞ በቢልሃርዚያ ተለክፈዋል። 20 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሻጋዝ በሚባለው በሽታ ተለክፈዋል። 126 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሪቨር ብላይንድነስ በሚባል ዓይን በሚያሳውር በሽታ ሊጠቁ በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታዎች በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን እንደ ቅጠል ያረግፋሉ።8 ሳንባ ነቀርሳና ሥጋ ደዌ ዛሬም ቢሆን ከባድ የጤና ችግሮች ናቸው። ‘በልዩ ልዩ ሥፍራ የሚከሰተው ቸነፈር’ ግምባር ቀደም ተጠቂዎች የዓለማችን ድሆች ናቸው።
22 ይሁን እንጂ ሃብታሞች አይነኩም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ኢንፉሌንዛ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉንም ያጠቃል። በ1957 የተከሰተው ኢንፉሌንዛ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ 70,000 ሰዎችን ገድሏል። ጀርመን ውስጥ ከስድስት ሰዎች አንዱ በካንሰር እንደሚሰቃይ ተገምቷል።9 በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሃብታሞችንም ሆነ ድሃዎችን ያጠቃሉ። ጨብጥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚታዩት ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ሲሆን በአፍሪካ አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ እስከ 18.9 በመቶ የሚያክለውን ነዋሪ የሚያሰቃይ በሽታ ነው።10 በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉትና ሰፋ ባለ አካባቢ ተዛምተው ከሚገኙት ‘ወረርሽኝ በሽታዎች’ መካከል ቂጥኝ፣ ክላሚዲያ እንዲሁም በጾታ ብልት አካባቢ የሚወጣው ኸርፕስ የሚባል ቫይረስ ይገኙበታል።
23. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜና አውታሮችን ትኩረት የሳበው ‘ቀሳፊ በሽታ’ የትኛው ነው?
23 ከ1980ዎቹ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ‘ቀሳፊ በሽታ’ የሆነው ኤድስ በዚህ ‘የቸነፈር’ ዝርዝር ላይ ተጨምሯል። ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ኤድስ ምንም መድሃኒት ያልተገኘለት በመሆኑና የሰለባዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ አስፈሪ በሽታ ሆኗል። ዘ ወርልድ አልማናክ ቡክ ኦቭ ፋክትስ 1997 እንደገለጸው “በምድር ዙሪያ 21.8 ሚልዮን ሰዎች በኤድስ በሽታ ተይዘዋል ወይም በኤድስ አማጪው ቫይረስ (በኤች አይ ቪ) ተለክፈዋል። . . . 5.8 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ደግሞ በኤድስ ሞተዋል።”11 በጽሑፍ የሰፈረ አንድ ሌላ ግምታዊ ዘገባ እንደሚጠቁመው በእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ አዲስ ሰው በኤድስ ቫይረስ ይጠቃል። በእርግጥም ‘ቀሳፊ በሽታ’ ነው! ይሁን እንጂ በምድር አራዊት ምክንያት የሚከሰት ሞት እንደሚኖር የሚገልጸውን ትንቢት በሚመለከትስ ምን ማለት ይቻላል?
‘የምድር አራዊት’
24, 25. (ሀ) ነቢዩ ሕዝቅኤል የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ‘አራዊት’ ነው? (ለ) ኢየሱስ እርሱ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ ስለሚኖሩት ‘አራዊት’ ምን ብሏል?
24 ዛሬ በአብዛኛው በጋዜጦች ላይ የምናነበው ከምድር ገጽ እንዳይጠፉ የሚያሰጋቸው ወይም ሊጠፉ የተቃረቡ የአራዊት ዝርያዎች አሉ የሚል ዜና ነው። ዛሬ የሰውን ልጅ የሚያሰጉት “የምድር አራዊት” መሆናቸው ቀርቶ በተቃራኒው የሰው ልጅ የእነርሱን ሕልውና አደጋ ላይ እየጣለ መጥቷል። ያም ሆኖ ግን በሕንድ የሚገኙትን የነብር ዝርያዎች የመሳሰሉ እንስሳት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ሕይወት ያጠፋሉ።
25 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ስጋት የፈጠሩ ሌሎች አራዊት እንዳሉ ይጠቁመናል። ነቢዩ ሕዝቅኤል ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎችን ከአራዊት ጋር በማወዳደር እንደሚከተለው ብሏል:- “በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኩላዎች ናቸው።” (ሕዝቅኤል 22:27) ኢየሱስ ‘የዓመፃ ብዛት’ እንደሚኖር ትንቢት ሲናገር እርሱ በሥልጣኑ በሚገኝበት ወቅት እንደነዚህ ያሉ ‘አራዊት’ በምድር ላይ እንደሚኖሩ መግለጹ ነበር ለማለት ይቻላል። (ማቴዎስ 24:12) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስም “በመጨረሻው ቀን” ሰዎች “ገንዘብን የሚወዱ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች መልካም የሆነውን የማይወዱ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) ከ1914 ወዲህ ይህ ነገር ተከስቷልን?
26-28. እንደ “አራዊት” ያሉ ወንጀለኞች በምድር ላይ እያደቡ መሆናቸውን የሚያሳዩት ከዓለም ዙሪያ የተገኙት ሪፖርቶች የትኞቹ ናቸው?
26 በትክክል ተከስቷል። በዓለም ዙሪያ ካሉት ትላልቅ ከተሞች በአንዱ የምትኖር ከሆነ ይህ ለአንተ አዲስ አይደለም። ይሁን እንጂ የምትጠራጠር ከሆነ በቅርቡ በጋዜጦች ላይ ከወጡ ዘገባዎች የተወሰዱትን ሐሳቦች ተመልከት። ከኮሎምቢያ:- “ባለፈው ዓመት ፖሊስ . . . 10,000 የሚያክሉ ነፍስ ግድያዎችንና 25,000 የሚያክሉ በመሣሪያ የተፈጸሙ የዝርፊያ ወንጀሎችን መዝግቧል።” ከቪክቶሪያ፣ አውስትራሊያ:- “የከባድ ወንጀሎች መጠን በእጅጉ ጨምሯል።” ከዩናይትድ ስቴትስ:- “በኒው ዮርክ የሚፈጸመው ግድያ እስካሁን ታይቶ ወደማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ነው።” “ባለፈው ዓመት ዴትሮይት በመላው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ካሉት ትላልቅ ከተሞች መካከል ከነዋሪው ቁጥር አንጻር ከፍተኛውን የነፍስ ግድያ ቁጥር በመያዝ የቀዳሚነቱን ስፍራ ከጌሪ ተረክባለች። ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል 58 የሚሆኑት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።”
27 ከዚምባቡዌ:- “የሕፃናትን ሕይወት የማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።” ከብራዚል:- “እዚህ የሚፈጸመው ወንጀልም ሆነ መሣሪያው በገፍ ስለሆነ ዓመፅ እንደተፈጸመ መስማት የሚያስገርም ዜና መሆኑ ቀርቷል።” ከኒው ዚላንድ:- “የፆታ ጥቃቶችና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ፖሊስን በእጅጉ እያሳሰቡ መጥተዋል።” “በኒው ዚላንድ ውስጥ አንዱ በሌላው ላይ የሚፈጽመው የወንጀል ዓይነት እጅግ አረመኔያዊ እየሆነ መጥቷል።” ከስፔይን:- “ስፔይን እየጨመረ ከመጣው ወንጀል ጋር ትንቅንቅ ይዛለች።” ከኢጣሊያ:- “የሲሲሊያ ወንበዴዎች ከገጠማቸው ሽንፈት ዳግም አንሰራርተው የግድያ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።”
28 ይህ መጽሐፍ ከመዘጋጀቱ ትንሽ ቀደም ባሉት ዓመታት በተነበቡ ጋዜጦች ላይ የወጡት እነዚህ ዘገባዎች እንዲሁ ለናሙና ያክል ብቻ የቀረቡ ናቸው። በእርግጥም ‘የምድር አራዊት’ በምድር ላይ እያደቡ በመሆናቸው ለሰዎች ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ፈጥረዋል።
የምሥራቹ ስብከት
29, 30. በኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
29 ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ወቅት በሚኖረው በችግር የታመሰ ጊዜ ውስጥ ሃይማኖትስ ምን ያደርግ ይሆን? በአንድ በኩል ኢየሱስ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንደሚጨምር ትንቢት ተናግሯል:- “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ።” (ማቴዎስ 24:11) በሌላ በኩል ደግሞ በጥቅሉ ሲታይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ሰዎች ለአምላክ እምብዛም ደንታ የሌላቸው እንደሚሆኑ ተናግሯል። “የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።”—ማቴዎስ 24:12
30 ይህ ዛሬ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ነገር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። በአንድ በኩልም ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ እያጡ መጥተዋል። በአንድ ወቅት ጠንካራ የፕሮቴስታንቶች ይዞታ በነበረው በሰሜን አውሮፓና በእንግሊዝ ሃይማኖት የተረሳ ነገር ሆኗል። በተመሳሳይም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እጥረት እንዲሁም የደጋፊዎቿ ቁጥር በመመናመኑ ችግር ላይ ወድቃለች። በሌላ በኩል ደግሞ ትናንሽ ሃይማኖታዊ ወገኖች በፍጥነት እየተበራከቱ ነው። ከምሥራቃውያን ሃይማኖቶች የሚወጡ ኑፋቄዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። ስስታም የቴሌቪዥን ወንጌላውያንም በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ያጋብሳሉ።
31. ኢየሱስ ዛሬ ያለውን እውነተኛ ክርስትና ለይተን ለማወቅ የሚያስችለን ምን ነገር ተንብዮአል?
31 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስላቋቋመውና ሐዋርያቱ ስለሰበኩት ሃይማኖት ማለትም ስለ እውነተኛው ክርስትናስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜም ይኖራል፤ ይሁን እንጂ ተለይቶ የሚታወቀው እንዴት ነው? እውነተኛው ክርስትና ተለይቶ የሚታወቅባቸው ነገሮች በርካታ ሲሆኑ አንደኛው በኢየሱስ ታላቅ ትንቢት ውስጥ ተገልጾ እናገኘዋለን። ይህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የሚጠመዱበት ወቅት ነው። ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:14
32. በማቴዎስ 24:14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ትንቢት የፈጸመው የትኛው ቡድን ብቻ ነው?
32 በአሁኑ ጊዜ ይህ የስብከት ሥራ በከፍተኛ መጠን እየተከናወነ ነው! ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት ሃይማኖታዊ ሰዎች በክርስትና ታሪክ ታይቶ በማያውቅ ከፍተኛ መጠን የስብከቱን ሥራ እያከናወኑ ነው። (ኢሳይያስ 43:10, 12) በ1919 ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መጨረሻው ያላማረውን የቃል ኪዳኑን ማኅበር ሲያሞካሹ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ምድር አቀፍ የስብከት ዘመቻ ለማጧጧፍ ተዘጋጅተው ነበር።
33, 34. የመንግሥቱ ምሥራች በመላዋ ምድር የተሰበከው እስከ ምን ድረስ ነው?
33 በወቅቱ የነበሩት ምሥክሮች 10,000 ብቻ ቢሆኑም ሥራው መሠራት እንዳለበት ተገንዝበው ነበር። በድፍረት የስብከቱን ሥራ ተያያዙት። ቀሳውስትና ምዕመናን ተብሎ መከፋፈል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ጋር ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ከተዉትም ምሳሌ ጋር እንደማይጣጣም ተገንዝበው ነበር። ከዚህ የተነሣ ከላይ እስከ ታች ድረስ ሁሉም ለጎረቤታቸው ስለ አምላክ መንግሥት መናገርን በመማራቸው የሰባኪዎች ድርጅት ሆነዋል።
34 ጊዜው እየገፋ ሲሄድ እነዚህ ሰባኪዎች ከፍተኛ ተቃውሞዎችን መጋፈጥ አስፈልጓቸዋል። አውሮፓ ውስጥ ከነበሩ የተለያዩ አምባገነን መንግሥታት ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ ውስጥ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፤ እንዲሁም የሕዝብ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ አክራሪ ሃይማኖተኞች የሚያንጸባርቁትን መሠረተ ቢስ ጥላቻና ጨካኝ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደሮች ያደረሱባቸውን ምህረት የለሽ ስደት መቋቋም ነበረባቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እየተስፋፋ የመጣውን ጥርጣሬ የሞላበትና ራስህን አስደስት የሚል መንፈስ መጋፈጥ አስፈልጓቸዋል። ይሁን እንጂ በመጽናታቸው ዛሬ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ከአምስት ሚልዮን ተኩል በላይ ሆነዋል። ምሥራቹ የአሁኑን ያህል በስፋት የተሰበከበት ጊዜ አለመኖሩ በዚህ ረገድ የተነገረው ትንቢት አስገራሚ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጣል!
ታዲያ ይህ ሁሉ ምን ያሳያል?
35. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የትንቢቶች ፍጻሜ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ፍጻሜውን ማግኘቱ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው?
35 ኢየሱስ የሰጠው ታላቅ ምልክት ፍጻሜውን ሲያገኝ እንደተመለከትን ምንም አያጠራጥርም። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ይህንን ከሚያህል ረጅም ዘመን በፊት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ምን ነገሮች እንደሚከናወኑ አስቀድሞ ሊናገር የሚችል ሰው አይኖርም። ከዚህም በላይ እነዚህ ምልክቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ኢየሱስ በሥልጣኑ በተገኘበትና የዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ በቀረበበት ዘመን ላይ እንደምንኖር የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 24:3 NW) ይህስ ምን ትርጉም ይኖረዋል? የኢየሱስ መገኘት ምን ነገሮችን ይጨምራል? የሚደመደመው የነገሮች ሥርዓትስ የትኛው ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳየውን ሌላ ጠንካራ ማስረጃ ይኸውም አስገራሚ የሆነውን የመጽሐፉን የእርስ በርስ ስምምነት መመርመር ይኖርብናል። ቀጥለን ይህን ጉዳይ በመመርመር የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ ታላቅ ፍጻሜውን ሊያገኝ የተቃረበው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከ1914 እስከ 1918 ባለው ጊዜ ውስጥ በአብሩዚ ከደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የሚበልጡና በሬክተር መለኪያ 8 ወይም ከዚያ በላይ የደረሱ ቢያንስ አምስት የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ርዕደ መሬቶች የተሰሙት ርቀው በሚገኙ የምድር ክፍሎች በመሆኑ እንደ ኢጣሊያው የመሬት መንቀጥቀጥ እምብዛም ትኩረት አልተሰጣቸውም።5
b በአንዳንዶቹ አደጋዎች ወቅት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በሚመለከት የተለያዩ አኃዞች ሪፖርት ተደርገዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።
-
-
የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ስምምነትመጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
-
-
ምዕራፍ 11
የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ስምምነት
አንድ ሺህ ስድስት መቶ በሚያክሉ ዓመታት ውስጥ 40 የተለያዩ ሰዎች የጻፏቸው 66 መጻሕፍት የሚገኙበት ቤተ መጻሕፍት አለ እንበል። በተለያዩ ቦታዎች የነበሩት እነዚህ ጸሐፊዎች ሦስት ቋንቋዎችን ተጠቅመዋል። ጸሐፊዎቹ የተለያየ ባሕርይ፣ ችሎታና አስተዳደግ የነበራቸው ናቸው። ይሁን እንጂ የጻፏቸው መጻሕፍት ከጊዜ በኋላ አንድ ላይ ሲሰባሰቡ ከዳር እስከ ዳር አንድ ጭብጥ ያለው ታላቅ መጽሐፍ ወጥቷቸዋል። ይህ ይሆናል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። አይደለም? ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ቤተ መጻሕፍት ነው።
1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚመሰክረው በውስጡ የተንጸባረቀው የትኛው አስገራሚ ስምምነት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ሆኖ ሳለ አንድ ወጥ መጽሐፍ ሆኖ መገኘቱ የማያስገርመው ሐቀኛ የሆነ ተማሪ አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የሚያበረታታው የማይለዋወጡ ባሕርያት ላሉት አንድ አምላክ አምልኮ ማቅረብን ነው። ከዚህም በላይ ሁሉም መጻሕፍት ጎላ ብሎ የሚታይ አንድ ጭብጥ የሚያዳብሩ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚንጸባረቀው ይህ አጠቃላይ ስምምነት በእርግጥም መጽሐፉ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።
2, 3. በኤደን የተነገረው ተስፋ ሰጭ ትንቢት የትኛው ነው? ይህ ትንቢት እንዲነገር ያደረጉት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
2 ዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በመጀመሪያው የዘፍጥረት መጽሐፍ መክፈቻ ምዕራፎች ውስጥ ተገልጿል። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ፍጹም ሆነው እንደተፈጠሩና ኤደን በምትባል ገነታዊ የአትክልት ስፍራ እንደተቀመጡ እናነባለን። ይሁን እንጂ አንድ እባብ ወደ ሔዋን ቀረብ አለና የአምላክን ሕግ ትክክለኛነት አጠያያቂ አስመስሎ በማቅረብ መሰሪ በሆነ ውሸት አታልሎ ወደ ኃጢአት መራት። አዳምም የእርሷን ፈለግ በመከተል አምላክን ሳይታዘዝ ቀረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ሁለቱም ሞት ተፈርዶባቸው ከገነት ተባረሩ። እኛ ዛሬ እየተሰቃየን ያለነው ያ የመጀመሪያ ዓመፅ ባስከተለው መዘዝ ነው። ሁላችንም ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል።—ዘፍጥረት 3:1-7, 19, 24፤ ሮሜ 5:12
3 ይሁን እንጂ በዚያ አሳዛኝ ወቅት አምላክ ተስፋ የሚሰጥ አንድ ትንቢት ተናገረ። ትንቢቱ የተነገረው ለእባቡ ቢሆንም አዳምና ሔዋንም ለልጆቻቸው ሊነግሯቸው ይችሉ ዘንድ እነርሱም እየሰሙ ነበር። አምላክ እንደሚከተለው ብሏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።”—ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 8:20, 21
4. ይሖዋ በኤደን በተናገረው ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱት ወገኖች የትኞቹ ናቸው? በዘመናት ሂደት በመካከላቸው የሚኖረው ሁኔታስ ምን ይመስላል?
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በተመሠረተበት በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተገለጹትን አራት ወገኖች ልብ በል። እነርሱም እባቡና ዘሩ እንዲሁም ሴቲቱና የእርሷ ዘር ናቸው። በቀጣዮቹ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በሚከናወኑት ነገሮች ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት እነዚህ ወገኖች ነበሩ። በአንድ ወገን ሴቲቱና ዘርዋ በሌላው ወገን ደግሞ እባቡና ዘሩ ሆነው በመካከላቸው ቋሚ የሆነ ጠላትነት ሊኖር ነው። ይህ ጠላትነት በእውነተኛው አምልኮና በሐሰተኛ አምልኮ እንዲሁም በትክክለኛ ምግባርና በክፋት መካከል ያለውን ዘላቂ የሆነ ጠላትነትም የሚጨምር ነው። አንድ ወቅት ላይ እባቡ የሴቲቱን ዘር ተረከዝ ሲቀጠቅጥ የቀናው መስሎ ይታያል። ይሁንና የሴቲቱ ዘር የኋላ ኋላ የእባቡን ራስ ሲቀጠቅጠውና የመጀመሪያው ዓመፀኛ ርዝራዦች በሙሉ ሲጠፉ የአምላክ ሉዓላዊነት ይረጋገጣል።
5. በትንቢቱ ውስጥ የተገለጸችው ሴት ሔዋን እንዳልሆነች እንዴት እናውቃለን?
5 ሴቲቱ ማን ነች? እባቡስ ማን ነው? እንዲሁም ዘሮቻቸው እነማን ናቸው? ሔዋን የመጀመሪያ ልጅዋን ቃየንን በወለደች ጊዜ “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” ብላ ነበር። (ዘፍጥረት 4:1) ምናልባትም በትንቢቱ ላይ የተገለጸችው ሴት እርሷ እንደሆነችና ዘሩም ልጅዋ እንደሆነ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ቃየን ራሱ እንደ እባቡ መጥፎ ልብ የነበረው ሰው ነው። የገዛ ታናሽ ወንድሙን የአቤልን ሕይወት በማጥፋት ነፍሰ ገዳይ መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 4:8) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ትንቢቱ አምላክ ብቻ ሊያብራራው የሚችለውን ጥልቅ ምሳሌያዊ ትርጉም ያዘለ ነበር። ደግሞም አምላክ በየጊዜው ደረጃ በደረጃ አብራርቶታል። በዚህም ሆነ በዚያ 66ቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የመጀመሪያው ትንቢት ያዘለው ትርጉም ግልጽ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል።
እባቡ ማን ነው?
6-8. ከእባቡ በስተጀርባ የነበረውን ኃይል ማንነት እንድናስተውል የሚረዱን የትኞቹ የኢየሱስ ቃላት ናቸው? አብራራ።
6 በመጀመሪያ ደረጃ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰው እባብ ማን ነው? ዘገባው በኤደን ውስጥ አንድ እባብ ሔዋንን ቀርቦ እንዳነጋገራት ይገልጻል፤ ሆኖም እባቦች መናገር አይችሉም። ስለዚህ ከበስተጀርባ ሆኖ እባቡ እንዲናገር ያደረገ ሌላ ኃይል መኖር አለበት። ይህ ኃይል ምንድን ነበር? ኢየሱስ በዚህች ምድር ላይ አገልግሎቱን እስካከናወነበት እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ የዚህ ኃይል ማንነት ግልጽ አልነበረም።
7 በአንድ ወቅት ኢየሱስ የአብርሃም ልጆች ነን በማለት ይኩራሩ ከነበሩ ተመጻዳቂ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ሲነጋገር ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ይሰብከው የነበረውን እውነት ለመቀበል በግትርነት አሻፈረን ብለው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”—ዮሐንስ 8:44
8 እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ኃይለኛና ቀጥተኛ ነበሩ። ዲያብሎስን “ነፍሰ ገዳይ” እና ‘የሐሰት አባት’ ሲል ጠርቶታል። በጽሑፍ ሰፍሮ የምናገኘው የመጀመሪያው ውሸት እባቡ በኤደን የተናገረው ውሸት ነው። ይህንን ውሸት የተናገረው ማንም ይሁን ማን በእውነትም “የሐሰት አባት” መባሉ ተገቢ ነው። ከዚህም ሌላ ይህ ውሸት አዳምና ሔዋን እንዲሞቱ ምክንያት ስለሆነ ይህ የመጀመሪያው ሐሰተኛ ነፍሰ ገዳይም ሆኗል። ከዚህ በግልጽ እንደምንረዳው በኤደን ገነት ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ይሖዋም ያንን ጥንታዊ ትንቢት የተናገረው ለሰይጣን ነበር።
9. ሰይጣን ከየት መጣ?
9 አንዳንድ ሰዎች አምላክ ክፋት የሌለበት ከሆነ እንደ ዲያብሎስ ያለ ፍጡር ለምን ፈጠረ? ብለው ይጠይቃሉ። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ለዚህ ጥያቄም የሚሆን መልስ ይዘዋል። ኢየሱስ ስለ ሰይጣን ሲገልጽ “እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር” ብሏል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በመሆኑም ሰይጣን መሆን የጀመረው በኤደን ለሔዋን ውሸት በነገራት ጊዜ ነበር። ሰይጣን የሚለው ቃል “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ቀደም ሲል የታመነ የነበረ አንድ መልአክ በልቡ የተሳሳተ ምኞት እንዲያድግ በመፍቀዱ ምክንያት ሰይጣን ሆነ እንጂ አምላክ ሰይጣን አድርጎ አልፈጠረውም።—ዘዳግም 32:4፤ ከኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-10፤ ያዕቆብ 1:13-15 ጋር አወዳድር።
የእባቡ ዘር
10, 11. ኢየሱስና ሐዋርያው ዮሐንስ የእባቡን ዘር ማንነት እንድናውቅ የሚረዱን እንዴት ነው?
10 ይሁንና ስለ እባቡ ዘርስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ይህንን የእንቆቅልሹን ክፍልም ለመፍታት ይረዱናል። እነዚያን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች “እናንተ ከአባታችሁ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ” ብሏቸዋል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህ አይሁዳውያን በእርግጥም እንዳሉት የአብርሃም ዘር ነበሩ። ይሁን እንጂ የክፋት አድራጎታቸው የኃጢአት ምንጭ የሆነው የሰይጣን መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
11 ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲጽፍ የእባቡ ማለትም የሰይጣን ዘር የሚሆኑት እነማን እንደሆኑ በግልጽ አስረድቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፣ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። . . . የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” (1 ዮሐንስ 3:8, 10) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የእባቡ ዘር በሰው ልጅ ታሪክ ሁሉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ኖሯል!
የሴቲቱ ዘር ማን ነው?
12, 13. (ሀ) ይሖዋ የሴቲቱ ዘር ከልጆቹ መካከል እንደሚገኝ ለአብርሃም የገለጸለት እንዴት ነው? (ለ) ዘሩን በተመለከተ የተሰጠውን የተስፋ ቃል የወረሰው ማን ነው?
12 ታዲያ ‘የሴቲቱ ዘር’ ማን ነው? የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጥ የመጀመሪያው ዓመፅ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ የሚያስወግደው የሴቲቱ ዘር በመሆኑ ይህ ጥያቄ እስከ ዛሬ ድረስ ከተነሡት ጥያቄዎች ሁሉ ይበልጥ አንገብጋቢ ነው። በ20ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አምላክ ታማኝ ሰው ለነበረው ለአብርሃም ስለዚህ ዘር ማንነት ጎላ ያለ ፍንጭ ሰጥቶታል። አብርሃም ትልቅ እምነት ስለነበረው ለእርሱ የሚወለድለትን ልጅ በተመለከተ አምላክ በተከታታይ ቃል ገብቶለታል። ከተገባለት ቃል መካከል አንዱ ‘የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው’ ‘የሴቲቱ ዘር’ ከአብርሃም ልጆች መካከል እንደሚወጣ የሚገልጽ ነበር። አምላክ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ዘርህም የጠላቶችህን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና።”—ዘፍጥረት 22:17, 18
13 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ ለአብርሃም የገባውን ቃል ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅ ከዚያም ለልጅ ልጁ ለያዕቆብ በድጋሚ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 26:3-5፤ 28:10-15) በኋላም የያዕቆብ ልጆች አሥራ ሁለት ነገድ በሆኑ ጊዜ ይሁዳ አንድ ልዩ የተስፋ ቃል ተሰጠው። “በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፣ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፣ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።” (ዘፍጥረት 49:10) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ዘሩ የሚመጣው በይሁዳ ነገድ በኩል ነበር።
14. ለዘሩ መምጣት ዝግጅት ለማድረግ የተደራጀው ብሔር የትኛው ነው?
14 በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ላይ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች የአምላክ ልዩ ሕዝብ በመሆን በብሔር ደረጃ ተዋቀሩ። አምላክም ይህን ለማድረግ ሲል ከእነርሱ ጋር በቃል ኪዳን ተሳሰረ፤ ሕግም ሰጣቸው። ይህንን ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት ለዘሩ መምጫ የሚሆን ሕዝብ ለማዘጋጀት ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6፤ ገላትያ 3:24) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሰይጣን ለሴቲቱ ዘር ያለው ጥላቻ አሕዛብ ለተመረጡት የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩት ጥላቻ ይንጸባረቅ ጀመር።
15. ከአብርሃም ዝርያዎች መካከል ዘሩ የሚገኝበትን ቤተሰብ በሚመለከት ምን የመጨረሻ ፍንጭ ተሰጥቷል?
15 ዘሩ ከየትኛው ቤተሰብ እንደሚገኝ የሚጠቁመው የመጨረሻው ፍንጭ የተገኘው በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። በዚያ ወቅት አምላክ የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት ዘሩ በእርሱ መስመር እንደሚመጣና ዙፋኑም ‘ለዘላለም እንደሚጸና’ ገለጸለት። (2 ሳሙኤል 7:11-16) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ይህ ዘር የዳዊት ልጅ ተብሎ ሊጠራ ችሏል።—ማቴዎስ 22:42-45
16, 17. ኢሳይያስ ዘሩ የሚያስገኛቸውን በረከቶች የገለጸው እንዴት ነው?
16 ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታትም አምላክ በመንፈስ ተነሳስተው ስለ መጪው ዘር ተጨማሪ መረጃዎችን የሚሰጡ ነቢያትን አስነሥቷል። ለምሳሌ ያህል በስምንተኛው መቶ ዘመን ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። . . . በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7
17 ኢሳይያስ ይህንኑ ዘር በሚመለከት ተጨማሪ ትንቢት ተናግሯል:- “ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ . . . ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ . . . በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:4-9) እንዴት ያሉ የተትረፈረፉ በረከቶችን የሚያስገኝ ዘር ነው!
18. ዳንኤል ዘሩን በሚመለከት ምን ተጨማሪ መረጃ ዘግቧል?
18 በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ዳንኤል ስለዚህ ዘር ተጨማሪ ትንቢት ተናግሯል። የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ የሚታይበት ጊዜ እንደሚመጣ ከገለጸ በኋላ “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩም ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው” ብሏል። (ዳንኤል 7:13, 14) በመሆኑም ይህ መጪው ዘር ሰማያዊ መንግሥት የሚወርስ ከመሆኑም ሌላ ንጉሣዊ ሥልጣኑ መላዋን ምድር የሚጠቀልል ይሆናል።
እንቆቅልሹ ተፈታ
19. መልአኩ እንደገለጸው ማርያም በዘሩ አመጣጥ ረገድ የምትጫወተው ሚና ምን ነበር?
19 የሴቲቱ ዘር ማንነት ከብዙ ጊዜ በኋላ በዘመናችን አቆጣጠር መባቻ ላይ ተገለጠ። በ2 ከዘአበ አንድ መልአክ ከዳዊት ዘር ለሆነች ማርያም ለምትባል አንዲት አይሁዳዊት ወጣት ተገለጠላት። መልአኩ አንድ ልዩ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ከገለጸላት በኋላ እንዲህ አለ:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:32, 33) በመሆኑም ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው “ዘር” በመጨረሻ ተገለጠ።
20. የተስፋው ዘር ማን ነው? በእስራኤልስ ምን መልእክት ሰብኳል?
20 በ29 እዘአ (ይህን ዘመን በሚመለከት ዳንኤል ከረጅም ዘመን በፊት ተናግሮ ነበር) ኢየሱስ ተጠመቀ። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደበት፤ አምላክም ልጁ መሆኑን አሳወቀ። (ዳንኤል 9:24-27፤ ማቴዎስ 3:16, 17) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” እያለ ለአይሁዳውያን ሲያውጅ ቆይቷል። (ማቴዎስ 4:17) በዚህ ወቅት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ትንቢቶችን በማስፈጸሙ የተስፋው ዘር እርሱ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አልነበረም።
21. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የዘሩን ማንነት በሚመለከት ምን ነገር ተረድተው ነበር?
21 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ነገር በሚገባ ተረድተው ነበር። ጳውሎስ በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር:- ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን:- ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ።” (ገላትያ 3:16) ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረለት “የሰላም አለቃ” ኢየሱስ ነው። በመጨረሻ በመንግሥቱ ሲመጣ በዓለም ዙሪያ ጽድቅና ፍትሕ ይሰፍናል።
ታዲያ ሴቲቱ ማን ነች?
22. በኤደን በተነገረው የይሖዋ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰችው ሴት ማን ነች?
22 ዘሩ ኢየሱስ ከሆነ ታዲያ በኤደን የተጠቀሰችው ሴት ማን ነች? ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው ኃይል መንፈሳዊ ፍጥረት ስለነበር ሴቲቱም ሰብዓዊ ፍጥረት ሳትሆን መንፈሳዊ መሆኗ ሊያስገርመን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት” ባለ ጊዜ ስለ አንዲት ሰማያዊት ‘ሴት’ እየተናገረ ነበር። (ገላትያ 4:26) “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ለብዙ ሺህ ዓመታት እንደኖረች ከሌሎች ጥቅሶች መረዳት እንችላለን። ይህች ሴት መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችው የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ስትሆን ኢየሱስ ‘የሴቲቱ ዘር’ በመሆን ተልእኮውን ለመፈጸም የመጣው ከዚያው ነው። ‘በቀደመው እባብ’ እና በእርሷ መካከል ያለው ጠላትነት ለብዙ ሺህ ዓመታት ሊዘልቅ የሚችለው መንፈሳዊ “ሴት” ከሆነች ብቻ ነው።—ራእይ 12:9፤ ኢሳይያስ 54:1, 13፤ 62:2-6
23. ይሖዋ በኤደን የተናገረው ትንቢት ትርጉም ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ መሄዱ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?
23 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ጥንታዊ ትንቢት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት ግልጽ እየሆነ እንደመጣ በአጭሩ የተመለከትነው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ስምምነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ትንቢቱን መረዳት የቻልነው በ20ኛው፣ በ11ኛው፣ በ8ኛው እንዲሁም በ6ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተከናወኑትንና የተነገሩትን ነገሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ከተደረጉትና ከተነገሩት ነገሮች ጋር በማጣመር መሆኑ በእርግጥም አስገራሚ ያደርገዋል። ይህ እንዲሁ ባጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ይህን እንዲሆን ያቀነባበረው ወገን መኖር አለበት።—ኢሳይያስ 46:9, 10
ለእኛ የሚኖረው ትርጉም
24. የዘሩ ማንነት መገለጥ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
24 ይህ ሁሉ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ‘የሴቲቱ ዋነኛ ዘር’ ኢየሱስ ነው። በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ጥንታዊ ትንቢት ተረከዙ በእባቡ ‘እንደሚቀጠቀጥ’ አስቀድሞ ገልጾ ነበር። ይህም ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በሞተ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። ተረከዙ ላይ መቀጥቀጡ ዘላቂ ጉዳት የሚያመጣ ነገር አልነበረም። በመሆኑም ኢየሱስ ትንሣኤ ሲያገኝ እባቡ ያገኘው ይመስል የነበረው ድል ወደ ሽንፈት ተለወጠ። (በምዕራፍ 6 ላይ እንዳየነው የኢየሱስን ትንሣኤ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃዎች አሉ።) የኢየሱስ መሞት ቅን ልብ ያላቸው የሰው ልጆች መዳን እንዲያገኙ የሚያስችል መሠረት በመጣሉ አምላክ ለአብርሃም ቃል እንደገባለት ዘሩ በረከት ሆኗል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰማያዊ መንግሥት ይዞ ምድራዊ ግዛቱን በሙሉ እንደሚቆጣጠር የሚናገሩት ትንቢቶችስ?
25, 26. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ‘በሴቲቱ ዘርና’ በእባቡ መካከል ያለው ጠላትነት ምን ነገሮችን ይጨምራል?
25 በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ ተገልጾ በምናገኘው ግልጽ ትንቢታዊ መግለጫ ውስጥ የዚህ መንግሥት አጀማመር አንድ ወንድ ልጅ በሰማይ ከመወለዱ ጋር ተመሳስሏል። የተስፋው ዘር “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም ያለው ሚካኤል የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቶት በዚህ መንግሥት ውስጥ ሥልጣኑን ይረከባል። ‘የቀደመውን እባብ’ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሰማይ በመጣል ማንም የይሖዋን ሉዓላዊነት ሊገዳደር እንደማይችል ያሳያል። እንዲህ እናነባለን:- “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ።”—ራእይ 12:7-9
26 ይህም በሰማይ እፎይታ እንዲሰፍን ሲያደርግ በምድር ላይ ወዮታን አስከትሏል። “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ” የሚል የድል ድምፅ ተሰምቷል። ከዚህም በመቀጠል እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን:- “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”—ራእይ 12:10, 12
27. ሰይጣን ከሰማይ እንደሚጣል የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው? እንዴት እናውቃለን?
27 ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ እንደሆነ መናገር እንችላለንን? በምዕራፍ 10 ውስጥ እንደተወያየነው ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ጠጋ ብለው ‘የመገኘቱና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱ’ ምን እንደሚሆን ሲጠይቁ ይህንኑ ጥያቄ ማንሳታቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:3 NW) ቀደም ሲል እንዳየነው ኢየሱስ በ1914 የሰማያዊ መንግሥቱን ሥልጣን እንደጨበጠ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። በእርግጥም ከዚያ ጊዜ አንስቶ ‘በምድር ላይ ወዮታ’ ሆኗል!
28, 29. ገና ወደፊት በምድር ላይ የሚካሄዱት ታላላቅ ለውጦች ምንድን ናቸው? በቅርቡ እንደሚከናወኑስ እንዴት እናውቃለን?
28 ይሁን እንጂ አንድ ነገር አስተውል:- ከሰማይ የተሰማው ታላቅ ድምፅ ሰይጣን “ጥቂት ጊዜ” ብቻ እንደቀረው አስታውቋል። በመሆኑም በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው የመጀመሪያ ትንቢት ወደማይቀረው ታላቅ መደምደሚያው እየገሰገሰ ነው። እባቡና የእርሱ ዘር እንዲሁም ሴቲቱና የእርሷ ዘር እነማን መሆናቸው ታውቋል። ዘሩ ‘ተረከዙ ተቀጥቅጦ’ ነበር፤ ይሁን እንጂ ድኗል። በቅርቡ ደግሞ አሁን በመግዛት ላይ ባለው ንጉሥ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰይጣን (ከነዘሩ) ይቀጠቀጣል።
29 ይህም በምድርም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል። ሰይጣንና የእርሱ ዘር ለመሆን የመረጡ ሁሉ ይጠፋሉ። መዝሙራዊው አስቀድሞ እንደተናገረው “ገና ጥቂት ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።” (መዝሙር 37:10) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ለውጥ ይሆናል! ከዚህ በኋላ መዝሙራዊው የተናገራቸው ተጨማሪ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:- “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
30. ከእውነታው የራቁት መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በመንፈስ አነሳሽነት ነው በሚለው ሐሳብና በአምላክ መኖር ላይ እንኳ ሳይቀር የጥርጣሬ ደመና እንዲያጠላ የሚያደርጉት ሰዎች ራሳቸው ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
30 ‘የሰላሙ ገዥ’ በመጨረሻ በዚህ ሁኔታ ለሰው ልጅ ሰላም ያጎናጽፈዋል። በኢሳይያስ 9:6, 7 ላይ እንዳየነው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ነው። በዚህ የጥርጣሬ መንፈስ በተጠናወተው ዓለም ብዙዎች እንዲህ ያለውን ተስፋ ከእውነታው የራቀ ሆኖ ይታያቸዋል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የሚያቀርበው ምን ሌላ አማራጭ አለ? ምንም አማራጭ የለም! በአንጻሩ ግን ይህ ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የሚናገረው ሁሉ መሬት ጠብ የማይል የአምላክ ቃል ነው። በእርግጥም ከእውነታው የራቁት ይህን የሚጠራጠሩት ሰዎች ናቸው። (ኢሳይያስ 55:8, 11) መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ አማካኝነት ላስጻፈውና ከሁሉ በላይ ለሆነው አካል ለአምላክ ጀርባቸውን ሰጥተዋል።
[በገጽ 151 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ችግር ላይ ለወደቀው የሰው ልጅ ተስፋ ሰጥቶታል
[በገጽ 154 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተስፋው ዘር የሚመጣው በአብርሃም ዝርያዎች በኩል መሆኑን በ20ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ ለአብርሃም ነግሮታል
[በገጽ 155 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሥ ዳዊት ዘሩ በእርሱ የንግሥና መስመር በኩል እንደሚመጣ በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተነግሮታል
[በገጽ 156 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢሳይያስ ዘሩ የሚያስገኛቸውን በረከቶች ገልጿል
[በገጽ 157 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘሩ በሰማያዊ መንግሥት እንደሚገዛ ዳንኤል በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አስታውቋል
[በገጽ 159 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርያም የአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ መባቻ ሲቃረብ ዘሩ እርሷ የምትወልደው ኢየሱስ የሚባለው ወንድ ልጅ እንደሚሆን አውቃ ነበር
-