የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ይሖዋ የቃል ኪዳን አምላክ ነው
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 1
    • ይሖዋ የቃል ኪዳን አምላክ ነው

      “ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል።” —ኤርምያስ 31:​31

      1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 ምሽት ላይ ያቋቋመው በዓል ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሞቱ ጋር አያይዞ የጠቀሰው ስለ የትኛው ቃል ኪዳን ነው?

      ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 ምሽት ላይ ከ12 ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የማለፍን በዓል አክብሯል። ኢየሱስ ይህ ከእነርሱ ጋር በማዕድ የሚቀመጥበት የመጨረሻ አጋጣሚ እንደሆነና ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጠላቶቹ እጅ እንደሚገደል ስለተገነዘበ ይህን ወቅት ለቅርብ ደቀ መዛሙርቱ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ለማስረዳት ተጠቅሞበታል።​—⁠ዮሐንስ 13:​1–17:26

      2 ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን ካስወጣ በኋላ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ያከብሩት ዘንድ የታዘዙትን ብቸኛ ሃይማኖታዊ በዓል ማለትም የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያቋቋመው በዚህ ጊዜ ነበር። በጽሑፍ የሰፈረው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና:- እንካችሁ፣ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” (ማቴዎስ 26:​26-28) የኢየሱስ ተከታዮች የእርሱን ሞት ቀለል ባለና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሊያስቡት ይገባ ነበር። ኢየሱስ ከሞቱ ጋር በማያያዝ ስለ አንድ ቃል ኪዳን ተናግሯል። በሉቃስ ዘገባ ውስጥ “አዲስ ኪዳን” ተብሎ ተጠርቷል።​—⁠ሉቃስ 22:​20

      3. አዲሱን ቃል ኪዳን በሚመለከት ምን ጥያቄዎች ተነስተዋል?

      3 ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ምንድን ነው? አዲስ ቃል ኪዳን ነው ከተባለ አሮጌ ቃል ኪዳን ነበር ማለት ነው? ከዚህ ጋር የሚዛመዱ ሌሎች ቃል ኪዳኖችስ አሉ? ኢየሱስ የቃል ኪዳን ደሙ “ለኃጢአት ይቅርታ” የሚፈስ መሆኑን ስለተናገረ እነዚህ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። እንዲህ ያለውን ይቅርታ ማግኘት ለሁላችን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።​—⁠ሮሜ 3:​23

      ከአብርሃም ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን

      4. ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ለመረዳት የሚያስችለን ጥንት የተነገረ የትኛው ተስፋ ነው?

      4 ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ለመረዳት ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ካከናወነበት ጊዜ 2,000 ዓመታት ገደማ ወደኋላ ተመልሰን አብራም (በኋላ አብርሃም ተብሏል) እና የአብራም ሚስት ሦራን (በኋላ ሣራ ተብላለች) ጨምሮ ታራንና ቤተሰቡ ከበለጸገችው የከለዳውያን ዑር ከተማ ወጥተው በሰሜን ሜሶጶጣሚያ ወደምትገኘው ወደ ካራን ስላቀኑበት ጊዜ መዳሰስ ያስፈልገናል። ታራ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ከዚያም የ75 ዓመቱ አብርሃም የአምላክን ትእዛዝ በመቀበል በድንኳን ውስጥ የዘላኖች ዓይነት ኑሮ ለመኖር የኤፍራጥስን ወንዝ አቋርጦ በደቡብ ምዕራብ በኩል ወደ ከነዓን ምድር ተጓዘ። (ዘፍጥረት 11:​31–12:​1, 4, 5፤ ሥራ 7:​2-5) ይህ የሆነው 1943 ከዘአበ ነበር። አብርሃም ገና በካራን ሳለ ይሖዋ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።” አብርሃም ወደ ከነዓን ከገባ በኋላም ይሖዋ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” ሲል ጨምሮ ነግሮታል።​—⁠ዘፍጥረት 12:​2, 3, 7

      5. ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ከየትኛው ታሪካዊ ትንቢት ጋር የሚዛመድ ነው?

      5 ለአብርሃም የተገባለት ቃል ይሖዋ ከሰጣቸው ሌሎች ተስፋዎች ጋር የሚዛመድ ነበር። በእርግጥም ይህ የተስፋ ቃል አብርሃምን የትንቢቶች ሁሉ መጀመሪያ ከሆነው ትንቢት ጋር የሚያዛምደው ስለነበር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት አድርጎታል። አዳምና ሔዋን በኤደን የአትክልት ሥፍራ ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ይሖዋ በሁለቱም ላይ ብያኔውን ያሳለፈ ሲሆን ሔዋንን ያሳሳታትን ሰይጣንን በዚያው ጊዜ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” ሲል ተናግሮታል። (ዘፍጥረት 3:​15) ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን የሰይጣንን ሥራ የሚያፈርሰው ዘር በዚህ የእምነት አባት የዘር መስመር እንደሚመጣ የሚጠቁም ነበር።

      6. (ሀ) ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው በማን በኩል ነው? (ለ) የአብርሃም ቃል ኪዳን ምንድን ነው?

      6 ይሖዋ የሰጠው የተስፋ ቃል ከዘር ጋር ተዛምዶ ያለው ስለነበር አብርሃም ይህን ዘር ለማስገኘት እንዲችል ልጅ ሊኖረው ያስፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ እርሱና ሣራ ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር፤ ልጅም አልነበራቸውም። ሆኖም የኋላ ኋላ ይሖዋ የመራቢያ ኃይላቸው በተዓምራዊ ሁኔታ እንዲታደስና ሣራ ለአብርሃም፣ ይስሐቅ የሚባል ወንድ ልጅ እንድትወልድለት በማድረግ ስለባረካቸው አንድ ዘር እንደሚመጣ የገባው የተስፋ ቃል ሕያው እንዲሆን አድርጓል። (ዘፍጥረት 17:​15-17፤ 21:​1-7) በጣም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ይሆን እንደሆነ እስከመጠየቅ ድረስ የአብርሃምን እምነት ከፈተነው በኋላ ይሖዋ ከብዙ ዓመታት በፊት የገባውን ቃል እንደሚከተለው በማለት በድጋሚ አረጋገጠለት:- “በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችህን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ [“ራሳቸውን ይባርካሉ፣” NW]፣ ቃሌን ሰምተሃልና።” (ዘፍጥረት 22:​15-18) ይህ ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ተስፋ አብዛኛውን ጊዜ የአብርሃም ቃል ኪዳን በመባል የሚጠራ ሲሆን የኋለኛው አዲስ ቃል ኪዳን ከዚህ ጋር በቅርብ የሚዛመድ ይሆናል።

      7. የአብርሃም ዘር በቁጥር እየጨመረ መሄድ የጀመረው እንዴት ነው? በግብጽ ነዋሪዎች ለመሆን ያበቋቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

      7 ከጊዜ በኋላ ይስሐቅ ሁለት መንትያ ወንዶች ልጆች ማለትም ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ። ይሖዋ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ቅድመ አያት እንዲሆን የመረጠው ያዕቆብን ነበር። (ዘፍጥረት 28:​10-15፤ ሮሜ 9:​10-13) ያዕቆብ 12 ልጆች ነበሩት። ከዚህ በኋላ የአብርሃም ዘር በቁጥር እያደገ እንደሚሄድ ግልጽ ነበር። የያዕቆብ ልጆች ለአካለ መጠን ደርሰው በነበረበትና ብዙዎቹም የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው መኖር በጀመሩበት ጊዜ በረሃብ ምክንያት ሁሉም ወደ ግብጽ ለመሰደድ ተገደዱ። በዚያም የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በመለኮታዊ ድጋፍ መንገዱን አመቻችቶ ነበር። (ዘፍጥረት 45:​5-13፤ 46:​26, 27) ከጥቂት ዓመታት በኋላ በከነዓን የነበረው ረሃብ አቆመ። ይሁን እንጂ የያዕቆብ ቤተሰብ መጀመሪያ በእንግድነት ከዚያም በባርነት ግብጽ ውስጥ ቆየ። ሙሴ የያዕቆብን ዝርያዎች ከግብጽ እየመራ ነፃ ያወጣቸው በ1513 ከዘአበ ማለትም አብርሃም የኤፍራጥስን ወንዝ ከተሻገረ ከ430 ዓመታት በኋላ ነበር። (ዘጸአት 1:​8-14፤ 12:​40, 41፤ ገላትያ 3:​16, 17) ከዚህ በኋላ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።​—⁠ዘጸአት 2:​24፤ 6:​2-5

      ‘አሮጌው ቃል ኪዳን’

      8. ይሖዋ በሲና ከያዕቆብ ዝርያዎች ጋር የተጋባው ቃል ምንድን ነው? ይህስ ከአብርሃም ቃል ኪዳን ጋር ምን ዝምድና አለው?

      8 ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ ሲገቡ አንድ ትልቅ ቤተሰብ የነበሩ ቢሆንም ልጆቻቸው ግብጽን ለቅቀው ሲወጡ ግን ብዙ ሕዝብ ያቀፉ ነገዶች ሆነው ነበር። (ዘጸአት 1:​5-7፤ 12:​37, 38) ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ከነዓን ከማስገባቱ በፊት በአረቢያ ምድር ወደሚገኘው የኮሬብ (ወይም ሲና) ተራራ ግርጌ በደቡብ በኩል መራቸው። በዚያም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ይህ ቃል ኪዳን ‘ከአዲሱ ቃል ኪዳን’ አንጻር “ብሉይ [አሮጌ] ኪዳን” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ቆሮንቶስ 3:​14) ይሖዋ በአሮጌው ቃል ኪዳን አማካኝነት ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን የመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።

      9. (ሀ) ይሖዋ በአብርሃም ቃል ኪዳን አማካኝነት እንደሚያከናውናቸው ቃል የገባቸው አራት ተስፋዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ይሖዋ ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ምን ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ከፍቷል? ይህ የሚሆነውስ ምን ቅድመ ሁኔታ ከተሟላ ነው?

      9 ይሖዋ የዚህን ቃል ኪዳን ስምምነት ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።” (ዘጸአት 19:​5, 6) ይሖዋ የአብርሃም ዘር (1) ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን፣ (2) በጠላቶቹ ላይ ድል እንደሚቀዳጅ፣ (3) የከነዓንን ምድር እንደሚወርስ እንዲሁም (4) አሕዛብ የሚባረኩበት መስመር እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር። አሁን ደግሞ እስራኤላውያን ትእዛዛቱን የሚጠብቁ ከሆነ የእርሱ ልዩ ሕዝብ ማለትም “የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ” ሆነው እነርሱ ራሳቸው እነዚህን በረከቶች እንደሚወርሱ ገለጸላቸው። እስራኤላውያን በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ለመግባት ተስማምተው ነበርን? እንደ አንድ ሰው ሆነው “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መልሰዋል።​—⁠ዘጸአት 19:​8

      10. ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር መልክ ያደራጃቸው እንዴት ነው? ምን እንዲያደርጉስ ይጠብቅባቸው ነበር?

      10 ከዚህ በኋላ ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር ደረጃ አደራጃቸው። አምልኮአቸውንም ሆነ ማኅበራዊ ኑሯቸውን የሚመሩበት ሕግ ሰጣቸው። በተጨማሪም የመገናኛ ድንኳንና (በኋላም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ) በውስጡ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የክህነት አገልግሎት አዘጋጀላቸው። ቃል ኪዳኑን መጠበቅ ማለት የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ በተለይም ደግሞ እርሱን ብቻ ማምለክ ማለት ነበር። ለእነዚያ ሕጎች አስኳል የሆነውና ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል መጀመሪያ የተጠቀሰው ሕግ የሚከተለው ነበር:- “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁንልህ።”​—⁠ዘጸአት 20:​2, 3

      በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት የሚገኙ በረከቶች

      11, 12. በአሮጌው ቃል ኪዳን ውስጥ የተሰጡት ተስፋዎች ለእስራኤላውያን የተፈጸሙላቸው በምን መንገዶች ነው?

      11 በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠባቸው ነገሮች ለእስራኤላውያን ተፈጽመውላቸዋልን? እስራኤል “የተቀደሰ ሕዝብ” ሆኗልን? እስራኤላውያን የአዳም ልጆች እንደመሆናቸው መጠን ኃጢአተኞች ነበሩ። (ሮሜ 5:​12) ሆኖም በሕጉ ሥር ኃጢአታቸውን ለመሸፈን መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር። በዓመታዊው የስርየት ቀን የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች በሚመለከት ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተሰሪያ ይሆንላችኋልና . . . በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።” (ዘሌዋውያን 16:​30) በመሆኑም እስራኤላውያን የታመኑ ሆነው ሲገኙ ለይሖዋ አገልግሎት የጸዱ ቅዱስ ሕዝብ ይሆኑ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ንጽሕናቸው የተመካው ሕጉን በመታዘዛቸውና መሥዋዕቶችን ማቅረባቸውን በመቀጠላቸው ላይ ነበር።

      12 የእስራኤል ብሔር “የካህናት መንግሥት” ሆኖ ነበርን? ገና ከጅምሩ አንስቶ ይሖዋ ሰማያዊ ንጉሡ የሆነለት መንግሥት ነበር። (ኢሳይያስ 33:​22) ከዚህም በተጨማሪ የሕጉ ቃል ኪዳን ሰብዓዊ ነገሥታት መግዛት የሚችሉበትንም ዝግጅት ያቀፈ ነበር፤ በመሆኑም ከጊዜ በኋላ መቀመጫቸውን ኢየሩሳሌም ያደረጉ ነገሥታት ይሖዋን በመወከል አስተዳድረዋል። (ዘዳግም 17:​14-18) ይሁን እንጂ የእስራኤል ብሔር የካህናት መንግሥት ነበርን? በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት የሚቀርብበት የክህነት ሥርዓት ነበር። የመገናኛው ድንኳን (በኋላም ቤተ መቅደሱ) ለእስራኤላውያኑም ሆነ እስራኤላዊ ላልሆኑት ሰዎች የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። እንዲሁም ብሔሩ ለሰው ዘር የተገለጠው እውነት የሚተላለፍበት ብቸኛ መስመር ነበር። (2 ዜና መዋዕል 6:​32, 33፤ ሮሜ 3:​1, 2) ሌዋውያን ካህናቱ ብቻ ሳይሆኑ የታመኑት እስራኤላውያን በሙሉ የይሖዋ ‘ምሥክሮች’ ነበሩ። የእስራኤል ብሔር ‘ምስጋናውን እንዲነግር’ የተቋቋመ የይሖዋ “ባሪያ” ነበር። (ኢሳይያስ 43:​10, 21) አንዳንድ ትሑት መጻተኞች ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል ያደረገውን የኃይል መግለጫ በማስተዋል ወደ ንጹሕ አምልኮው ተስበዋል። ወደ ይሁዲነት ተለውጠዋል። (ኢያሱ 2:​9-13) ይሁን እንጂ ቅቡዓን ካህናት ሆነው ያገለግሉ የነበሩት የአንድ ነገድ አባላት ብቻ ነበሩ።

      በእስራኤላውያን መካከል የነበሩ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች

      13, 14. (ሀ) ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች የሕጉ ቃል ኪዳን ተካፋዮች አልነበሩም ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች ከሕጉ ቃል ኪዳን በታች የነበሩት እንዴት ነው?

      13 ወደ ይሁዲነት የተለወጡት እነዚህ ሰዎች ምን ቦታ ነበራቸው? ይሖዋ ቃል ኪዳኑን ያደረገው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ብቻ ነበር፤ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” በቦታው የተገኘ ቢሆንም የቃል ኪዳኑ ተካፋይ ተደርጎ አልተጠቀሰም። (ዘጸአት 12:​38፤ 19:​3, 7, 8) የእስራኤል በኩሮች የቤዛነት ዋጋ ሲሰላ የእነርሱ በኩሮች አልተቆጠሩም። (ዘኁልቁ 3:​44-51) ከአሥርተ ዓመታት በኋላም የከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን ነገዶች ሲከፋፈል እስራኤላዊ ላልሆኑት አማኞች የተሰጠ ርስት አልነበረም። (ዘፍጥረት 12:​7፤ ኢያሱ 13:​1-14) ለምን? ምክንያቱም የሕጉ ቃል ኪዳን የተደረገው ወደ ይሁዲነት ከተለወጡት ሰዎች ጋር አልነበረም። ይሁን እንጂ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ወንዶች ሕጉን በመታዘዝ ይገረዙ ነበር። የሕጉን መመሪያዎች ይታዘዙና ከዝግጅቶቹ ይጠቀሙ ነበር። ወደ ይሁዲነት የተለወጡትም ሆኑ እስራኤላውያኑ ከሕጉ ቃል ኪዳን በታች ነበሩ።​—⁠ዘጸአት 12:​48, 49፤ ዘኁልቁ 15:​14-16፤ ሮሜ 3:​19

      14 ለምሳሌ ያህል ወደ ይሁዲነት የተለወጠ አንድ ሰው ድንገት ሰው ቢገድል እንደ ሌላው እስራኤላዊ ሁሉ እርሱም ወደ አንደኛው የመማጸኛ ከተማ መሸሽ ይችል ነበር። (ዘኁልቁ 35:​15, 22-25፤ ኢያሱ 20:​9) በስርየት ቀን “ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ” አንድ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች የጉባኤው አባል እንደመሆናቸው መጠን በሥርዓቱ ይካፈሉና የመሥዋዕቱም ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:​7-10, 15, 17, 29፤ ዘዳግም 23:​7, 8) ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች በሕጉ ሥር ከእስራኤላውያን ጋር በቅርብ የተሳሰሩ በመሆናቸው በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት እስራኤላውያን በመጀመሪያው ‘የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ’ በተከፈተላቸው ጊዜ ወደ ይሁዲነት የተለወጡትም ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ መሠረት ‘ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረው የአንጾኪያው ኒቆላዎስ’ ክርስቲያን ከመሆኑም ሌላ የኢየሩሳሌምን ጉባኤ ጉዳይ እንዲከታተሉ ከተሾሙት ‘በመልካም የተመሠከረላቸው ሰባት ወንዶች መካከል’ ሊሆን ችሏል።​—⁠ማቴዎስ 16:​19፤ ሥራ 2:​5-10፤ 6:​3-6፤ 8:​26-39

      ይሖዋ የአብርሃምን ዘር ባረከ

      15, 16. ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

      15 ይሖዋ የእምነት አባት ለሆነው ለአብርሃም በገባው ቃል መሠረት በሕጉ ሥር በብሔር መልክ የተደራጁትን የአብርሃም ዝርያዎች ባርኳቸዋል። በ1473 ከዘአበ በሙሴ እግር በተተካው በኢያሱ መሪነት እስራኤላውያኑ ወደ ከነዓን ምድር ገብተዋል። ከዚያ በኋላ የተከናወነው ምድሪቱን በየነገዱ የመከፋፈሉ ሥራ ይሖዋ ምድሪቱን ለአብርሃም ዘር እንደሚሰጥ የገባውን ቃል ያስፈጸመ ነበር። የእስራኤል ብሔር የታመነ ሆኖ ሲገኝ ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ ድል እንደሚቀዳጁ የገባላቸውን ቃል ይጠብቅ ነበር። ይህ በተለይ በንጉሥ ዳዊት የግዛት ዘመን በተግባር ታይቷል። በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ዘመን ደግሞ የአብርሃም ቃል ኪዳን ሦስተኛ ዘርፍ ፍጻሜውን አግኝቷል። “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሏቸው ነበር።”​—⁠1 ነገሥት 4:​20

      16 ይሁንና አሕዛብ የአብርሃም ዘር በሆነው በእስራኤል ብሔር አማካኝነት ራሳቸውን የሚባርኩት እንዴት ነው? ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የእስራኤል ብሔር በሌሎች አሕዛብ መካከል ይሖዋን የሚወክል የእርሱ ልዩ ሕዝብ ነበር። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ “እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 32:​43) ብዙ መጻተኞች ለዚህ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” እስራኤላውያንን ተከትለው ከግብጽ ከመውጣታቸውም ሌላ ይሖዋ በምድረ በዳ ኃይሉን ሲያሳይ የዓይን ምሥክር ነበሩ፤ እንዲሁም ሙሴ ያቀረበውን ደስ ይበላችሁ የሚለውን ጥሪ ሰምተዋል። (ዘጸአት 12:​37, 38) ከጊዜ በኋላ ሞዓባዊቷ ሩት እስራኤላዊውን ቦዔዝን አግብታ የመሲሑ ቅድመ አያት ለመሆን ችላለች። (ሩት 4:​13-22) በትውልድ አይሁዳዊ የሆኑ ብዙዎች የታመኑ ሳይሆኑ በቀሩበት ጊዜ ቄናዊው ኢዮናዳብና ልጆቹ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ከትክክለኛው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ተጣብቀው የሚመላለሱ ሰዎች መሆናቸውን አሳይተዋል። (2 ነገሥት 10:​15-17፤ ኤርምያስ 35:​1-19፤ 38:​7-13) በፋርስ ግዛት ሥር የነበሩ ብዙ መጻተኞች ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሲሆን ከእስራኤል ጋር ወግነው ጠላቶቻቸውን ተዋግተውላቸዋል።​—⁠አስቴር 8:​17 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

      አዲስ ቃል ኪዳን አስፈለገ

      17. (ሀ) ይሖዋ የእስራኤልን ሰሜናዊና ደቡባዊ መንግሥታት የተዋቸው ለምንድን ነው? (ለ) አይሁዳውያን ጨርሶ እንዲተዉ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?

      17 ይህም ሆኖ አምላክ የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም የአምላክ ልዩ ብሔር የታመነ ሆኖ መገኘት ያስፈልገው ነበር። ሆኖም የታመነ ሆኖ አልተገኘም። እርግጥ ነው ድንቅ እምነት ያሳዩ እስራኤላውያን ነበሩ። (ዕብራውያን 11:​32–12:1) ይሁን እንጂ ብሔሩ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወደ አረማዊ አማልክት ፊቱን ያዞረባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። (ኤርምያስ 34:​8-16፤ 44:​15-18) ግለሰቦች ሕጉን አላግባብ ተጠቅመውበታል አለዚያም ቸል ብለውታል። (ነህምያ 5:​1-5፤ ኢሳይያስ 59:​2-8፤ ሚልክያስ 1:​12-14) ከሰሎሞን ሞት በኋላ እስራኤል በሰሜኑና በደቡቡ መንግሥት ለሁለት ተከፈለች። የሰሜኑ መንግሥት ጨርሶ ዓመፀኛ በሆነ ጊዜ ይሖዋ “አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ” ሲል ተናግሯል። (ሆሴዕ 4:​6) የደቡቡም መንግሥት ቃል ኪዳኑን ሳያከብር በመቅረቱ ከባድ ቅጣት ደርሶበታል። (ኤርምያስ 5:​29-31) አይሁዳውያን ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመቀበል አሻፈረኝ ባሉ ጊዜ እርሱም እንዲሁ ትቷቸዋል። (ሥራ 3:​13-15፤ ሮሜ 9:​31–10:4) በመጨረሻ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አዲስ ዝግጅት አደረገ።​—⁠ሮሜ 3:​20

      18, 19. ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ሲል ምን አዲስ ዝግጅት አድርጓል?

      18 ይህ አዲስ ዝግጅት አዲሱ ቃል ኪዳን ነው። ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ስለዚህ ቃል ኪዳን ትንቢት መናገሩ ነበር:- “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ . . . ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።”​—⁠ኤርምያስ 31:​31-33

      19 ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 ቀን የጠቀሰው አዲስ ቃል ኪዳን ይህ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህ ተስፋ የተሰጠበት ቃል ኪዳን በኢየሱስ መካከለኛነት በደቀ መዛሙርቱና በይሖዋ መካከል የሚደረግ መሆኑን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 11:​25፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​5፤ ዕብራውያን 12:​24) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንደምናየው በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን አማካኝነት ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ይበልጥ ክብራማ የሆነና ዘላቂ ፍጻሜውን ያገኛል።

  • በአዲሱ ቃል ኪዳን በኩል የሚገኙ የላቁ በረከቶች
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 1
    • በአዲሱ ቃል ኪዳን በኩል የሚገኙ የላቁ በረከቶች

      ‘ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን መካከለኛ ሆኗል።’​ —⁠ዕብራውያን 8:​6

      1. በኤደን ተስፋ የተሰጠበት ‘የሴቲቱ ዘር’ ማን ሆኖ ተገኘ? ‘ሰኮናው የተቀጠቀጠውስ’ እንዴት ነው?

      አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ይሖዋ፣ ሔዋንን ባሳሳታት በሰይጣን ላይ እንዲህ በማለት ብያኔውን አሳልፏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:​15) ኢየሱስ በ29 እዘአ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ በኤደን ቃል የተገባለት ዘር በመጨረሻ ተገለጠ። በ33 እዘአ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ይህ ጥንታዊ ትንቢት በከፊል ፍጻሜውን አገኘ። ሰይጣን የዘሩን ‘ሰኮና ቀጠቀጠ።’

      2. ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው የእርሱ ሞት የሰውን ዘር የሚጠቅመው እንዴት ነው?

      2 የደረሰበት ጉዳት ከባድ ስቃይ የሚያስከትል ቢሆንም ዘላቂ አለመሆኑ ደስ ይላል። ኢየሱስ የማይጠፋ መንፈሳዊ አካል በመልበስ ከሞት ተነሥቶ ወደ ሰማያዊ አባቱ በመሄድ “ለብዙዎች ቤዛ” እንዲሆን የፈሰሰውን የደሙን ዋጋ አቅርቧል። በዚህ መንገድ ራሱ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት በትክክል ተፈጽመዋል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው . . . የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ማቴዎስ 20:​28፤ ዮሐንስ 3:​14-16፤ ዕብራውያን 9:​12-14) አዲሱ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

      አዲሱ ቃል ኪዳን

      3. አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን የጀመረው መቼ ነው?

      3 ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የፈሰሰው ደሙ ‘የአዲስ ኪዳን ደም’ እንደሆነ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 26:​28፤ ሉቃስ 22:​20) ወደ ሰማይ ካረገ ከአሥር ቀናት በኋላ 120 ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ሰገነት ላይ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን እንደጀመረ የሚያሳይ ነበር። (ሥራ 1:​15፤ 2:​1-4) እነዚህ 120 ደቀ መዛሙርት ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን መግባታቸው “ፊተኛው” ማለትም የሕጉ ቃል መሻሩን ያመለክታል።​—⁠ዕብራውያን 8:​13

      4. አሮጌው ቃል ኪዳን ጉድለት ነበረበት ማለት ነውን? አብራራ።

      4 አሮጌው ቃል ኪዳን ጉድለት ነበረበት ማለት ነውን? በፍጹም። እርግጥ ነው፣ ይህ ቃል ኪዳን በሌላ ስለተተካ ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክ ልዩ ሕዝቦች የመሆናቸው ጉዳይ አክትሞለታል። (ማቴዎስ 23:​28) ይሁን እንጂ ይህ የሆነው እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸውና የይሖዋን ቅቡዕ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ነው። (ዘጸአት 19:​5፤ ሥራ 2:​22, 23) ነገር ግን ሕጉ ከመተካቱ በፊት ብዙ ነገሮችን አከናውኗል። ለብዙ መቶ ዘመናት ወደ አምላክ ለመቅረብና ከሐሰት ሃይማኖት ጥበቃ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ሆኖ አገልግሏል። የአዲሱን ቃል ኪዳን ገጽታዎች ከወዲሁ ያመላከተ ከመሆኑም ሌላ በተደጋጋሚ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረብን የሚጠይቅ መሆኑ የሰው ልጅ የግድ ከኃጢአትና ከሞት የሚቤዠው እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ነበር። በእርግጥም ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚት ነበር።’ (ገላትያ 3:​19, 24፤ ሮሜ 3:​20፤ 4:​15፤ 5:​12፤ ዕብራውያን 10:​1, 2) ይሁን እንጂ ለአብርሃም ቃል የተገባለት በረከት ሙሉ በሙሉ እውን የሚሆነው በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው።

      አሕዛብ በአብርሃም ዘር በኩል ተባርከዋል

      5, 6. በአብርሃም ቃል ኪዳን ዋነኛው መንፈሳዊ ፍጻሜ መሠረት የአብርሃም ዘር ማን ነው? በእርሱ አማካኝነትስ በረከት ለማግኘት የመጀመሪያ የሆነው ብሔር የትኛው ነው?

      5 ይሖዋ ለአብርሃም “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ [“ራሳቸውን ይባርካሉ፣” NW]” ሲል ቃል ገብቶለታል። (ዘፍጥረት 22:​18) በአሮጌው ቃል ኪዳን ሥር ገር ልብ የነበራቸው ብዙ መጻተኞች በብሔር ደረጃ የአብርሃም ዘር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር በነበራቸው ቅርርብ ተባርከዋል። ይሁን እንጂ በተስፋው ዋነኛ መንፈሳዊ ፍጻሜ መሠረት የአብርሃም ዘር አንድ ፍጹም ሰው ነው። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ይህን ጉዳይ ገልጾታል:- “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር:- ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን:- ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ።”​—⁠ገላትያ 3:​16

      6 አዎን፣ ኢየሱስ የአብርሃም ዘር ነው። በእርሱ አማካኝነትም አሕዛብ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ሊያገኙት ከሚችሉት እጅግ የላቀ በረከት ያገኛሉ። ይህን በረከት ለማግኘት የመጀመሪያ አጋጣሚ የተከፈተለት የእስራኤል ብሔር እንደነበረ ግልጽ ነው። በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ አንድ ላይ ለተሰባሰቡ አይሁዳውያን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እናንተ የነቢያት ወራሾች ናችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችን ጋር የገባው ቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር ልጁን የላከው በመጀመሪያ ለእናንተ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው እያንዳንዳችሁን ከክፉ መንገዳችሁ በመመለስ እንዲባርካችሁ ነው።”​—⁠ሥራ 3:​25, 26 የ1980 ትርጉም

      7. የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት የተባረኩት አሕዛብ የትኞቹ ናቸው?

      7 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በረከቱ ለሳምራውያን ቀጥሎም ለአሕዛብ ተዘረጋ። (ሥራ 8:​14-17፤ 10:​34-48) ከ50 እስከ 52 እዘአ ገደማ ባለው ጊዜ መሐል ጳውሎስ በትንሿ እስያ ለነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ:- በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።” (ገላትያ 3:​8, 9፤ ዘፍጥረት 12:​3) በገላትያ የነበሩት ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ‘ከአሕዛብ ወገን’ ቢሆኑም በእምነታቸው ምክንያት በክርስቶስ አማካኝነት ተባርከዋል። በምን መንገድ?

      8. በጳውሎስ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች በአብርሃም ዘር አማካኝነት መባረክ ምን ነገር የሚያስገኝ ነበር? የዚህ በረከት ተቋዳሽ የሚሆኑት ጠቅላላ ቁጥርስ ስንት ነው?

      8 ጳውሎስ ትውልዳቸው ምንም ይሁን ምን በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጠቅላላ ሲናገር “የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” ብሏል። (ገላትያ 3:​29) ለእነዚያ የገላትያ ሰዎች በአብርሃም ዘር በኩል የሚገኘው በረከት የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮችና ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች በመሆን ከኢየሱስ ጋር የአብርሃም ዘር ክፍል የመሆንን መብት የሚያስገኝላቸው ነበር። የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ምን ያህል የሕዝብ ብዛት እንደነበረው አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር “እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ” እንደነበሩ ብቻ ነው። (1 ነገሥት 4:​20) ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ መንፈሳዊ ዘር የሚሆኑት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ግን ስንት እንደሆነ እናውቃለን፤ 144,000 ነው። (ራእይ 7:​4፤ 14:​1) እነዚህ 144,000 ሰዎች ከሰው ዘር ‘ነገድ፣ ቋንቋ፣ ወገን፣ ሕዝብ ሁሉ’ የተውጣጡ ሲሆኑ እነርሱም በተራቸው ከአብርሃም ቃል ኪዳን የሚገኙትን በረከቶች ለሌሎች በማዳረሱ ሥራ ይካፈላሉ።​—⁠ራእይ 5:​9

      ፍጻሜውን ያገኘ አንድ ትንቢት

      9. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች የይሖዋ ሕግ በውስጣቸው ተጽፏል ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

      9 ኤርምያስ ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ።” (ኤርምያስ 31:​33) ይሖዋን በፍቅር ተገፋፍቶ ማገልገል በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች ባሕርይ ነው። (ዮሐንስ 13:​35፤ ዕብራውያን 1:​9) የይሖዋ ሕግ የተጻፈው በልባቸው ውስጥ ሲሆን ፈቃዱን ለማድረግ ልባዊ ምኞት አላቸው። በጥንቷ እስራኤል ውስጥም የይሖዋን ሕግ በጣም የሚወዱ አንዳንድ የታመኑ ግለሰቦች እንደነበሩ አይካድም። (መዝሙር 119:​97) ነገር ግን ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አልነበራቸውም። ሆኖም የብሔሩ ክፍል ሆነው ቀጥለዋል። በአዲሱ ቃል ኪዳን ግን የአምላክ ሕግ በልቡ ካልተጻፈለት በቀር ማንም ቢሆን በቃል ኪዳኑ ሥር ሊቆይ አይችልም።

      10, 11. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ሰዎች ይሖዋ ‘አምላካቸው የሚሆነው’ በምን መንገድ ነው? ሁሉም የሚያውቁትስ እንዴት ነው?

      10 ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ስለሚኖሩት ሰዎች ጨምሮ ሲናገር “እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” ብሏል። (ኤርምያስ 31:​33) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ብዙዎች የአሕዛብን አማልክት እያመለኩ እስራኤላውያን ሆነው ይቀጥሉ ነበር። ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን መሠረት ሥጋዊ እስራኤላውያንን ለመተካት አንድ መንፈሳዊ ብሔር ማለትም ‘የአምላክን እስራኤል’ አዘጋጅቷል። (ገላትያ 6:​16፤ ማቴዎስ 21:​43፤ ሮሜ 9:​6-8) ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ይሖዋን ብቻ ማምለኩን ካቆመ የዚህ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ክፍል ሆኖ ሊቀጥል አይችልም።

      11 በተጨማሪም ይሖዋ “ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ያውቁኛል” ብሏል። (ኤርምያስ 31:​34) በእስራኤል ውስጥ የነበሩ ብዙዎች “እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም” ብለው ችላ ያሉት ያክል ነበር። (ሶፎንያስ 1:​12) ይሖዋን ችላ የሚል ወይም ደግሞ ንጹሕ አምልኮውን የሚበርዝ ማንኛውም ሰው የአምላክ እስራኤል ክፍል ሆኖ አይቀጥልም። (ማቴዎስ 6:​24፤ ቆላስይስ 3:​5) መንፈሳዊ እስራኤላውያን “አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ” ናቸው። (ዳንኤል 11:​32) ‘ብቻውን እውነተኛ ስለሆነው አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት’ በማግኘታቸው ይደሰታሉ። (ዮሐንስ 17:​3) ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ ስለ ‘አምላክ የተረከው’ ኢየሱስ ስለሆነ ስለ እርሱ ማወቅ ስለ አምላክ ያላቸው እውቀት እንዲያድግ ይረዳቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 1:​18፤ 14:​9-11

      12, 13. (ሀ) ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉትን ሰዎች ኃጢአት ይቅር የሚለው ምንን መሠረት በማድረግ ነው? (ለ) የኃጢአት ይቅርታን በተመለከተ አዲሱ ቃል ኪዳን ከአሮጌው ቃል ኪዳን የሚበልጠው በምን መንገድ ነው?

      12 በመጨረሻም ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።” (ኤርምያስ 31:​34) የሙሴ ሕግ በመቶ የሚቆጠሩ በጽሑፍ የሰፈሩ መመሪያዎችን የያዘ ሲሆን እስራኤላውያን እነዚህን መመሪያዎች እንዲታዘዙ ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 28:​1, 2, 15) ሕጉን የሚተላለፉ ሁሉ ኃጢአታቸውን ለመሸፈን መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። (ዘሌዋውያን 4:​1-7፤ 16:​1-31) ብዙ አይሁዳውያን በሕጉ መሠረት በገዛ ሥራቸው ሊጸድቁ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር። ይሁንና ክርስቲያኖች በራሳቸው ሥራ ፈጽሞ ጻድቅ ሆነው ሊቆጠሩ እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። (ሮሜ 5:​12) በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ማግኘት የሚቻለው በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አቋም ስጦታ ማለትም ይገባናል የማንለው የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ነው። (ሮሜ 3:​20, 23, 24) ይህም ቢሆን ይሖዋ አገልጋዮቹ ታዛዥ እንዲሆኑ ይፈልግባቸዋል። ጳውሎስ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች “በክርስቶስ ሕግ በታች” እንዳሉ ተናግሯል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​21

      13 ለክርስቲያኖችም ቢሆን የኃጢአት መሥዋዕት ይቀርባል፤ ይሁን እንጂ ይህ መሥዋዕት በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ይቀርቡ ከነበሩት መሥዋዕቶች እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ያሉት] ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ።” (ዕብራውያን 10:​11, 12) በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ክርስቲያኖች በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው ይሖዋ እንደ ጻድቅ ማለትም ኃጢአት እንደሌለባቸው አድርጎ በመቁጠር መንፈሳዊ ልጆቹ ሆነው ለመቀባት የሚያስችል አቋም እንዳላቸው አድርጎ ይቀበላቸዋል። (ሮሜ 5:​1፤ 8:​33, 34፤ ዕብራውያን 10:​14-18) በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ኃጢአት ሲፈጽሙ የይሖዋን ይቅርታ መጠየቅ ይችላሉ፤ ይሖዋም በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት መሠረት በማድረግ ይቅር ይላቸዋል። (1 ዮሐንስ 2:​1, 2) ይሁን እንጂ ሆነ ብለው የኃጢአትን ጎዳና ለመከተል ቢመርጡ የጽድቅ አቋማቸውንና የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች የመሆን መብታቸውን ያጣሉ።​—⁠ዕብራውያን 2:​2, 3፤ 6:​4-8፤ 10:​26-31

      አሮጌውና አዲሱ ቃል ኪዳን

      14. የሕጉ ቃል ኪዳን ምን ዓይነት ግርዘት እንዲከናወን ይጠይቅ ነበር? አዲሱ ቃል ኪዳንስ?

      14 በአሮጌው ቃል ኪዳን ሥር የነበሩት ወንዶች በሕጉ ሥር መሆናቸውን ለማሳየት ይገረዙ ነበር። (ዘሌዋውያን 12:​2, 3፤ ገላትያ 5:​3) የክርስቲያን ጉባኤ ሥራውን ከጀመረ በኋላም አንዳንዶች አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ሊገረዙ ይገባቸዋል የሚል አቋም ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩት ሽማግሌዎች በአምላክ ቃልና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ይህ ነገር አስፈላጊ እንዳልሆነ ተገነዘቡ። (ሥራ 15:​1, 5, 28, 29) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፣ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፣ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም።” (ሮሜ 2:​28, 29) በሥጋ አይሁዳዊ ለሆኑት እንኳ ሳይቀር በሥጋ የሚደረግ መገረዝ ከዚያ በኋላ በይሖዋ ፊት ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ጠቀሜታ አልነበረውም። በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር የነበሩት ሰዎች የሚያስፈልጋቸው የልብ መገረዝ እንጂ የሥጋ መገረዝ አልነበረም። ይሖዋን የሚያሳዝን ወይም በፊቱ ንጹሕ ያልሆነው አስተሳሰባቸው፣ ምኞታቸውና ዝንባሌያቸው ሁሉ ሊወገድ ይገባው ነበር።a ዛሬ መንፈስ ቅዱስ በዚህ መንገድ የሰዎችን አስተሳሰብ የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ብዙ ሕያው ምሥክሮች አሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9-11፤ ገላትያ 5:​22-24፤ ኤፌሶን 4:​22-24

      15. ንጉሣዊ አገዛዝን በተመለከተ ሥጋዊ እስራኤልንና የአምላክ እስራኤልን ማነጻጸር የሚቻለው እንዴት ነው?

      15 በሕጉ ቃል ኪዳን ዝግጅት ውስጥ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ይሖዋ ሲሆን ከጊዜ በኋላም በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ሰብዓዊ ነገሥታት ሥልጣኑን በውክልና በመስጠት አስተዳድሯል። (ኢሳይያስ 33:​22) ይሖዋ የአምላክ እስራኤል ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤላውያንም ንጉሥ ነው፤ ከ33 እዘአ አንስቶ ደግሞ ‘በሰማይና በምድር ሁሉ ሥልጣንን ባገኘው’ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እየገዛ ነው። (ማቴዎስ 28:​18፤ ኤፌሶን 1:​19-23፤ ቆላስይስ 1:​13, 14) ዛሬ የአምላክ እስራኤል ኢየሱስ በ1914 የተቋቋመው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነ ይቀበላሉ። ኢየሱስ እንደ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ካሉትና ከሌሎቹም የጥንቷ እስራኤል የታመኑ ነገሥታት እጅግ የላቀ ንጉሥ ነው።​—⁠ዕብራውያን 1:​8, 9፤ ራእይ 11:​15

      16. የአምላክ እስራኤል ክህነት ምን ዓይነት ነው?

      16 የእስራኤል ብሔር መንግሥት ከመሆኑም በተጨማሪ ቅቡዕ ካህናት ነበሩት። በ33 እዘአ የአምላክ እስራኤል የሥጋዊ እስራኤላውያንን ብሔር በመተካት የይሖዋ ‘ባሪያ’ እንዲሁም የእርሱ ‘ምሥክር’ ሆኗል። (ኢሳይያስ 43:​10) ከዚያ በኋላ ይሖዋ እስራኤልን በሚመለከት የተናገራቸው በኢሳይያስ 43:​21 እና በዘጸአት 19:​5, 6 ላይ የሚገኙት ቃላት ለአምላክ መንፈሳዊ እስራኤል አገልግለዋል። አዲሱ የአምላክ መንፈሳዊ ብሔር ‘የይሖዋን በጎነት የመናገር’ ኃላፊነት የተጣለበት “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ሆኗል። (1 ጴጥሮስ 2:​9) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በአምላክ እስራኤል ውስጥ የታቀፉት ሁሉ አንድ የካህናት ቡድን ይሆናሉ። (ገላትያ 3:​28, 29) በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ የአብርሃም ዘር እንደመሆናቸው መጠን “እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላሉ። (ዘዳግም 32:​43) ከመንፈሳዊ እስራኤል መካከል በምድር ላይ የቀሩት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነዋል። (ማቴዎስ 24:​45-47) ለአምላክ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ የሚቻለው ከእነርሱ ጋር በመተባበር ብቻ ነው።

      የአምላክ መንግሥት​—⁠የመጨረሻ ፍጻሜው

      17. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉ ሰዎች ይወለዳሉ ሲባል ምን ማለት ነው?

      17 ከዘአበ ከ1513 በኋላ የተወለዱት እስራኤላውያን የሕጉ ቃል ኪዳን ክፍል የሆኑት በውልደት ነበር። ይሖዋ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን የሚያስገባቸውም ሰዎች ቢሆኑ እንዲሁ መወለድ አለባቸው፤ ይሁን እንጂ የእነርሱ መንፈሳዊ ውልደት ነው። ኢየሱስ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ለፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ እንዲህ ሲል ነግሮታል:- “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።” (ዮሐንስ 3:​3) ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች መካከል ይህን አዲስ ውልደት ለማግኘት የመጀመሪያ የሆኑት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ተሰብስበው የነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ናቸው። በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር እንደ ጻድቅ በመቆጠር የንጉሣዊ ርስታቸው “መያዣ” የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለዋል። (ኤፌሶን 1:​14) የአምላክ ልጆች ለመሆን ‘ከመንፈስ ተወልደዋል፤’ ይህም የኢየሱስ ወንድሞች በመሆን ከክርስቶስ ጋር ‘አብረው የመውረስ’ መብት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። (ዮሐንስ 3:​6፤ ሮሜ 8:​16, 17) ‘ዳግም መወለዳቸው’ ድንቅ የሆኑ ተስፋዎችን እንዲያገኙ በር ከፍቶላቸዋል።

      18. በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ላሉት ሰዎች ዳግም መወለድ የትኞቹን ድንቅ ተስፋዎች እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል?

      18 ኢየሱስ ለአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖ ባገለገለበት ጊዜ እንዲህ በማለት ከተከታዮቹ ጋር ተጨማሪ ቃል ኪዳን ገብቷል:- “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።” (ሉቃስ 22:​29 NW) ይህ የመንግሥት ቃል ኪዳን በዳንኤል 7:​13, 14, 22, 27 ላይ የተገለጸው አስገራሚ ራእይ ፍጻሜውን እንዲያገኝ መንገድ የሚጠርግ ነው። ዳንኤል “የሰው ልጅ የሚመስል” ‘በዘመናት በሸመገለው’ በይሖዋ አምላክ ፊት ቀርቦ ንጉሣዊ ሥልጣን ሲቀበል ተመልክቷል። ከዚያም ዳንኤል ‘የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ሲወርሱ’ አይቷል። “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው በ1914 ሰማያዊ መንግሥቱን ከይሖዋ አምላክ የተቀበለው ኢየሱስ ነው። “ቅዱሳኑ” ከእርሱ ጋር በዚያች መንግሥት የሚካፈሉት በመንፈስ የተቀቡት ደቀ መዛሙርቱ ናቸው። (1 ተሰሎንቄ 2:​12) እንዴት?

      19, 20. (ሀ) ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ሰዎች ምን የመጨረሻና ክብራማ ፍጻሜ ይኖረዋል? (ለ) ልንመረምረው የሚገባን ተጨማሪ ጥያቄ የትኛው ነው?

      19 እነዚህ ቅቡዓን ከሞት ከተነሡ በኋላ እንደ ኢየሱስ የማይጠፋ መንፈሳዊ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት በመሆን ከእርሱ ጋር ሰማያዊ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:​50-53፤ ራእይ 20:​4, 6) እንዴት ያለ ክብራማ ተስፋ ነው! በከነዓን ምድር ብቻ ሳይሆን በመላዋ ‘ምድር ላይ ይነግሣሉ።’ (ራእይ 5:​10) ‘የጠላቶቻቸውን ደጅ ይወርሱ’ ይሆን? (ዘፍጥረት 22:​17) አዎን፣ የጠላትነት ዝንባሌ ያላትን የሃይማኖታዊቷን ጋለሞታ የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት በዓይናቸው ሲመለከቱና እነዚህ ትንሣኤ ያገኙት ቅቡዓን ‘አሕዛብን በብረት በትር’ በመግዛቱና የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጡ ሥራ ከኢየሱስ ጋር ሲካፈሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የጠላቶቻቸውን ደጅ ይወርሳሉ። በዚህ መንገድ በዘፍጥረት 3:​15 ላይ የተገለጸው ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን እንዲያገኘ በማድረግ ተካፋይ ይሆናሉ።​—⁠ራእይ 2:​26, 27፤ 17:​14፤ 18:​20, 21፤ ሮሜ 16:​20

      20 አሁንም ቢሆን የአብርሃም ቃል ኪዳንና አዲሱ ቃል ኪዳን የሚያቅፉት እነዚህን 144,000 የታመኑ ነፍሶች ብቻ ነውን? የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን። የለም፣ በሚቀጥለው ርዕስ እንደምንመለከተው በቀጥታ በእነዚህ ቃል ኪዳኖች ውስጥ ያልታቀፉ ሌሎችም ይባረካሉ።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግን እና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (በእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 470 ተመልከት።

      ታስታውሳለህን?

      ◻ አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን የጀመረው መቼ ነው?

      ◻ አሮጌው ቃል ኪዳን ምን ነገር አከናውኗል?

      ◻ ዋነኛው የአብርሃም ዘር ማን ነው? በዚህ ዘር አማካኝነት አሕዛብ የተባረኩበት ቅደም ተከተልስ ምን ይመስላል?

      ◻ የአብርሃም ቃል ኪዳንና አዲሱ ቃል ኪዳን በ144,000ዎቹ ላይ የሚኖራቸው የመጨረሻ ፍጻሜ ምንድን ነው?

      [በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      የኃጢአት ይቅርታ በአሮጌው ቃል ኪዳን ውስጥ ከታቀፉት ሰዎች ይልቅ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ሰዎች የበለጠ ጥልቅ ትርጉም አለው

  • ሌሎች በጎችና አዲሱ ቃል ኪዳን
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 1
    • ሌሎች በጎችና አዲሱ ቃል ኪዳን

      “መጻተኞች፣ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፣ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ።”​ —⁠ኢሳይያስ 56:​6, 7

      1. (ሀ) በዮሐንስ ራእይ መሠረት የይሖዋን የጥፋት ፍርድ የሚያስፈጽሙት ነፋሳት ተይዘው እያለ ምን ነገር ተከናውኗል? (ለ) ዮሐንስ የተመለከተው የትኛውን አስገራሚ የሆነ ብዙ ሕዝብ ነው?

      ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ አራተኛ ራእይ ውስጥ ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት በሙሉ ታትመው እስኪያበቁ ድረስ የይሖዋን ፍርድ የሚያስፈጽሙት አውዳሚ ነፋሳት እንደተያዙ ተመልክቷል። ዋነኛው የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት የሚባረኩት የመጀመሪያዎቹ ወገኖች እነዚህ ናቸው። (ገላትያ 6:​16፤ ዘፍጥረት 22:​18፤ ራእይ 7:​1-4) በዚሁ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ የሚከተለውን ሁኔታ ተመልክቷል:- “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ . . . በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” (ራእይ 7:​9, 10) እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ማዳን የበጉ ነው’ ማለታቸው እነርሱም ጭምር በአብርሃም ዘር አማካኝነት እንደሚባረኩ ያሳያል።

      2. እጅግ ብዙ ሰዎች ብቅ ያሉት መቼ ነው? እንዴትስ ታወቁ?

      2 እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን መሆናቸው የታወቀው በ1935 ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከአምስት ሚልዮን በላይ ሆኗል። ታላቁን መከራ በሕይወት እንዲያልፉ ምልክት የተደረገላቸው በመሆናቸው ኢየሱስ “በጎችን” “ከፍየሎች” በሚለይበት ጊዜ ለዘላለም

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ