-
በአትክልቱ ሥፍራ ያሳለፈው ሥቃይእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 117
በአትክልቱ ሥፍራ ያሳለፈው ሥቃይ
ኢየሱስ ጸሎቱን ሲጨርስ እሱና 11 የታመኑ ሐዋርያቱ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘመሩ። ከዚያም ደርብ ላይ ከሚገኘው ክፍል ወጥተው በቀዝቃዛው የሌሊት ጨለማ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው እንደገና ወደ ቢታንያ አቀኑ። ሆኖም በመካከሉ መንገድ ላይ እጅግ ተወዳጅ ወደሆነው ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ጎራ አሉ። ይህ የአትክልት ሥፍራ የሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አለዚያም በዚያው አካባቢ ነው። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ወደዚህ ሥፍራ እየመጣ በወይራ ዛፎቹ መካከል ከእነርሱ ጋር ይወያይ ነበር።
ከሐዋርያቱ መካከል ስምንቱን ለብቻቸው ተዋቸውና “ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ” አላቸው። እነዚህን ሐዋርያት የተዋቸው በአትክልት ሥፍራው መግቢያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ሌሎቹን ሦስቱን ሐዋርያት ማለትም ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አትክልት ሥፍራው ውስጥ ገባ። ኢየሱስ እጅግ አዘነ፤ መንፈሱም በጣም ተረበሸ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤” አላቸው። “በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ [“ነቅታችሁ ጠብቁ፣” NW]።”
ኢየሱስ ጥቂት ወደ ፊት እልፍ ብሎ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፋና እንዲህ ሲል አጥብቆ መጸለይ ጀመረ:- “አባቴ፣ ቢቻልስ፣ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን።” ምን ማለቱ ነበር? ‘እስከ ሞት ድረስ እጅግ ያዘነው’ ለምንድን ነው? ለመሞትና ቤዛውን ለማቅረብ ከወሰደው ውሳኔ እያፈገፈገ ነበርን?
በፍጹም! ኢየሱስ ከሞት ለመትረፍ እንዲችል መማጸኑ አልነበረም። አንድ ጊዜ ጴጥሮስ አቅርቦለት የነበረውን መሥዋዕታዊውን ሞት የማስቀረቱን ሐሳብ እንኳ ጭራሽ ወደ አእምሮው ሊያመጣው አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ በጭንቀት እየተሠቃየ ያለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተናቀ ወንጀለኛ እንደሆነ ተቆጥሮ የሚሞትበት መንገድ በአባቱ ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ በጣም ስላሳሰበው ነው። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አምላክን የሰደበ ከሁሉም የከፋ መጥፎ ሰው እንደሆነ ተቆጥሮ በእንጨት ላይ እንደሚሰቀል ተገንዝቧል! መንፈሱን በጣም የረበሸው ነገር ይህ ነው።
ኢየሱስ ረዘም ላለ ጊዜ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ሲመለስ ሦስቱ ሐዋርያት ተኝተው አገኛቸው። ጴጥሮስን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ [“ነቅታችሁ በመጠበቅ ያለ ማቋረጥ ጸልዩ፣” NW]” አለው። ይሁን እንጂ ያደረባቸውን ጭንቀትና የሌሊቱን ሰዓት መግፋት ግምት ውስጥ በማስገባት “መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” አለ።
ከዚያም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ እልፍ ብሎ ሄደና ‘ጽዋውን’ ማለትም ይሖዋ የመደበለትን ዕጣ ወይም ለእሱ ያለውን ፈቃድ እንዲያስቀርለት ለመነው። ሲመለስ አሁንም ሦስቱ ሐዋርያት ወደ ፈተና እንዳይገቡ መጸለይ ሲገባቸው ተኝተው አገኛቸው። ኢየሱስ ሲያናግራቸው ምን እንደሚመልሱለት ግራ ገባቸው።
በመጨረሻ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ የድንጋይ ውርወራ ያህል ራቀና ተንበርክኮ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” በማለት ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸለየ። ኢየሱስ እጅግ ከባድ የሆነ ጭንቀት እንዲሰማው ያደረገው እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ የሚሞት መሆኑ በአባቱ ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ ነው። አምላክን የተሳደበና ያቃለለ ነው ተብሎ መወንጀል በጣም ከባድ ነው!
ሆኖም ኢየሱስ በመቀጠል “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” ሲል ጸለየ። ኢየሱስ በታዛዥነት የራሱን ፍላጎት ለአባቱ ፈቃድ አስገዝቷል። በዚህ ጊዜ አንድ መልአክ ከሰማይ ታየና በሚያበረታቱ ቃላት አጠነከረው። መልአኩ ኢየሱስ በአባቱ ፊት ያለውን ሞገስ ሳይነግረው አይቀርም።
ሆኖም በኢየሱስ ጫንቃ ላይ እጅግ ታላቅ የሆነ ኃላፊነት ወድቋል! የእሱም ሆነ የመላው የሰው ዘር የዘላለም ሕይወት በእሱ ላይ የተመካ ነው። ይህ ነው የማይባል የስሜት ውጥረት ይዞታል። ስለዚህ ኢየሱስ ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲየሽን “ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የማያጋጥም ቢሆንም እንኳ . . . ከፍተኛ የስሜት ውጥረት በሚኖርበት ጊዜ ደም የተቀላቀለበት ላብ ሊወጣ ይችላል” ሲል ገልጿል።
ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ሐዋርያቱ ሲመለስ እንደገና ተኝተው አገኛቸው። የተሰማቸው ጥልቅ ሐዘን በጣም አድክሟቸው ነበር። “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን?” ሲል በመደነቅ ጠየቃቸው። “እነሆ፣ ሰዓቱ ደርሶአል፤ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”— የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ የአስቆሮቱ ይሁዳ ችቦ፣ ፋኖስና መሣሪያዎች ከያዙ ብዙ ሕዝብ ጋር ሆኖ መጣ። ማቴዎስ 26:30, 36-47፤ 16:21-23፤ ማርቆስ 14:26, 32-43፤ ሉቃስ 22:39-47፤ ዮሐንስ 18:1-3፤ ዕብራውያን 5:7
▪ ደርብ ላይ ከሚገኘው ክፍል ከወጡ በኋላ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ወዴት ወሰዳቸው? እዚያስ ምን አደረገ?
▪ ኢየሱስ እየጸለየ ሳለ ሐዋርያቱ ምን እያደረጉ ነበር?
▪ ኢየሱስ በጭንቀት ሲሠቃይ የነበረው ለምንድን ነው? ለአምላክ ያቀረበው ልመናስ ምንድን ነው?
▪ የኢየሱስ ላብ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆኖ መውረዱ ምን ያመለክታል?
-
-
በይሁዳ ጠቋሚነት መያዝእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 118
በይሁዳ ጠቋሚነት መያዝ
ይሁዳ ወታደሮችን፣ የካህናት አለቆችን፣ ፈሪሳውያንንና ሌሎች ሰዎችን ያቀፈ ትልቅ ጭፍራ አስከትሎ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ሲመጣ እኩለ ሌሊት አልፎ ነበር። ካህናቱ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጣቸው ለይሁዳ 30 ብር ለመስጠት ተስማምተዋል።
ቀደም ሲል ይሁዳ ከማለፍ በዓሉ እራት ላይ ተነሥቶ ሲወጣ በቀጥታ ወደ ካህናት አለቆቹ እንደሄደ ግልጽ ነው። እነርሱም ወዲያውኑ የራሳቸውን መኮንኖችና አንድ የወታደሮች ቡድን ሰበሰቡ። ይሁዳ መጀመሪያ የወሰዳቸው ኢየሱስና ሐዋርያቱ የማለፍ በዓልን ወዳከበሩበት ቤት ሳይሆን አይቀርም። ከዚያ እንደሄዱ ሲገነዘቡ መሣሪያ የታጠቁትና ፋኖስና ችቦ የያዙት ጭፍሮች ይሁዳን ተከትለው ከኢየሩሳሌም ወጡና የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገሩ።
ይሁዳ ጭፍሮቹን እየመራ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወሰዳቸው፤ ኢየሱስን የት እንደሚያገኘው እርግጠኛ ነበር። ባለፈው ሳምንት ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወደ ቢታንያና ወደ ኢየሩሳሌም ሲመላለሱ ብዙውን ጊዜ አረፍ ብለው ለመወያየት ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ጎራ ይሉ ነበር። አሁን ግን ኢየሱስ ያለው በወይራ ዛፎች ሥር ጨለማ ውስጥ ሊሆን ስለሚችል ወታደሮቹ እንዴት ሊለዩት ይችላሉ? ከዚህ በፊት ጭራሽ አይተውት ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ ይሁዳ “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
ይሁዳ ጭፍሮቹን እየመራ ወደ አትክልት ሥፍራው ገባና ኢየሱስን ከሐዋርያቱ ጋር ሲመለከተው በቀጥታ ወደ እሱ ሄደ። “መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳም አደረገው።
ኢየሱስ “ወዳጄ ሆይ፣ ለምን ነገር መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ከዚያም የራሱን ጥያቄ ራሱ በመመለስ “ይሁዳ ሆይ፣ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ሆኖም ይሁዳ ተልዕኮውን ፈጽሞ ነበር! ኢየሱስ የችቦዎቹና የፋኖሶቹ መብራት ወዳለበት ቦታ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
“የናዝሬቱን ኢየሱስን” ሲሉ መለሱለት።
ኢየሱስ በሁሉም ፊት በድፍረት ቆሞ “እኔ ነኝ” አላቸው። ሰዎቹ በድፍረቱ ተደንቀውና ምን ሊያደርግ እንደሆነ ስላላወቁ ፈርተው ወደ ኋላ አፈገፈጉና ወደቁ።
ኢየሱስ “እኔ ነኝ አልኋችሁ” በማለት በተረጋጋ መንፈስ መናገሩን ቀጠለ። “እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ። ከጥቂት ጊዜ በፊት ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ እያሉ ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱን እንደጠበቃቸውና “ከጥፋት ልጅ በቀር” ከእነርሱ አንድም የጠፋ እንደሌለ ለአባቱ በጸሎት ገልጾለት ነበር። ስለዚህ ቃሉ መፈጸም ይችል ዘንድ ተከታዮቹ መሄድ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቀረበ።
ወታደሮቹ ድንጋጤያቸው ለቀቅ ሲያደርጋቸው ተነሱና ኢየሱስን ማሰር ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ ምን ሊፈጸም እንደሆነ ገባቸው። “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸውን?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ መልስ ከመስጠቱ በፊት ጴጥሮስ ሐዋርያቱ ይዘዋቸው ከነበሩት ሁለት ሰይፎች መካከል አንደኛውን መዘዘና የሊቀ ካህናቱ ባሪያ የሆነውን ማልኮስን መታው። ጴጥሮስ የሰነዘረው ሰይፍ የባሪያውን ጭንቅላት ሳተና የቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።
ኢየሱስ ጣልቃ ገባና “ይህንስ ፍቀዱ” አለ። የማልኮስን ጆሮ ዳሰሰና ቁስሉን ፈወሰው። ከዚያም ጴጥሮስን እንደሚከተለው ብሎ በማዘዝ አንድ ትልቅ ትምህርት ሰጠ:- “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?”
ኢየሱስ “እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” ሲል በመግለጽ ለመያዝ ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል። አክሎም “አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን?” ሲል ተናገረ። አምላክ ለእርሱ ካለው ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ ነበር!
ከዚያም ኢየሱስ ጭፍሮቹን አነጋገራቸው። “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። “በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው።”
በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ፣ የወታደሮቹ አዛዥና የአይሁድ መኮንኖች ኢየሱስን ያዙና አሰሩት። ሐዋርያቱ ይህን ሲመለከቱ ኢየሱስን ጥለው ሸሹ። ሆኖም አንድ ወጣት፣ ምናልባትም ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም፣ በጭፍሮቹ መካከል ቀረ። ቀደም ሲል ኢየሱስ የማለፍ በዓሉን ባከበረበት ቤት ውስጥ የነበረ ይመስላል። ከዚያም ጭፍሮቹን ተከትሎ መጥቶ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አሁን ማንነቱን ሲያውቁ ሊይዙት ሞከሩ። ሆኖም ወጣቱ እንዲሁ አጣፍቶት የነበረውን በፍታ ጥሎ ሸሸ። ማቴዎስ 26:47-56፤ ማርቆስ 14:43-52፤ ሉቃስ 22:47-53፤ ዮሐንስ 17:12፤ 18:3-12
▪ ይሁዳ ኢየሱስን በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ እንደሚያገኘው እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው?
▪ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ያለውን አሳቢነት የገለጸው እንዴት ነው?
▪ ጴጥሮስ ኢየሱስን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል ምን እርምጃ ወሰደ? ሆኖም ኢየሱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጴጥሮስን ምን አለው?
▪ ኢየሱስ፣ አምላክ ለእርሱ ካለው ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ ያሳየው እንዴት ነው?
▪ ሐዋርያቱ ኢየሱስን ጥለው በሸሹ ጊዜ እዚያው ቀርቶ የነበረው ማን ነው? ምንስ ደረሰበት?
-
-
ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 119
ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ
ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ተራ ወንጀለኛ ታስሮ ከፍተኛ ተሰሚነት ወዳለውና ቀደም ሲል ሊቀ ካህናት ወደነበረው ወደ ሐና ተወሰደ። ኢየሱስ በ12 ዓመቱ በቤተ መቅደሱ የነበሩትን የአይሁድ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች በጣም አስደንቋቸው በነበረ ጊዜ ሐና ሊቀ ካህናት ነበር። ከዚያ በኋላ በርከት ያሉ የሐና ልጆች ሊቀ ካህናት ሆነው አገልግለዋል፤ አሁን ደግሞ ይህን ቦታ የያዘው የሐና አማች የሆነው ቀያፋ ነው።
ኢየሱስ መጀመሪያ ወደ ሐና ቤት የተወሰደው ይህ የካህናት አለቃ በአይሁድ ሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ለረጅም ጊዜ በነበረው ከፍ ያለ ቦታ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሐናን ለማነጋገር ወደ እሱ ቤት ጎራ ማለታቸው ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሳንሄድሪንን ማለትም 71 አባላት ያሉትን የአይሁድ ከፍተኛ ሸንጎና የሐሰት ምሥክሮችን ለመሰብሰብ ጊዜ እንዲያገኝ ረድቶታል።
የካህናት አለቃ የሆነው ሐና አሁን ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፣ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለ ምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፣ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ።”
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አጠገብ ቆመው ከነበሩት መኮንኖች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ በጥፊ መታው።
ኢየሱስም “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ስለ ምን ትመታኛለህ?” ሲል መለሰለት። ይህን የሐሳብ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ሐና ኢየሱስን እንደታሠረ ወደ ቀያፋ ላከው።
በዚህ ወቅት የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች እንዲሁም ጻፎቹ ሁሉ፣ ማለትም ጠቅላላው የሳንሄድሪን አባላት መሰብሰብ ጀምረዋል። እየተሰበሰቡ ያሉት በቀያፋ ቤት እንደሆነ ግልጽ ነው። በማለፍ በዓል ሌሊት እንዲህ ዓይነት ችሎት ማካሄድ የአይሁድን ሕግ በቀጥታ የሚጻረር ነው። ሆኖም ይህ የሃይማኖት መሪዎቹ የክፋት ዓላማቸውን ከማከናወን አላገዳቸውም።
ከሳምንታት በፊት ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት ጊዜ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ኢየሱስ መገደል እንዳለበት ተስማምተው ወስነዋል። ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ረቡዕ ዕለት የሃይማኖት ባለ ሥልጣኖቹ ኢየሱስን በተንኮል ዘዴ ይዘው ለመግደል ተማክረው ነበር። እስቲ አስበው፣ ገና ችሎት ፊት ሳይቀርብ ተፈርዶበት ነበር!
አሁን በኢየሱስ ላይ የወንጀል ክስ ማቅረብ እንዲቻል የሐሰት ምሥክርነት የሚሰጡ ሰዎች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ እርስ በርሱ የሚስማማ ምሥክርነት የሚሰጡ ሰዎች ሊገኙ አልቻሉም። በመጨረሻ ሁለት ሰዎች ቀረቡና “እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው” ብለው ተናገሩ።
“አንዳች አትመልስምን?” ሲል ቀያፋ ጠየቀው። “እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድን ነው?” ኢየሱስ ግን ዝም አለ። በዚህ የሐሰት ክስ እንኳ ምስክሮቹ የሚናገሩት ነገር እርስ በርሱ ሊጣጣም አለመቻሉ የሳንሄድሪንን ሸንጎ የሚያዋርድ ነበር። ስለዚህ ሊቀ ካህናቱ ሌላ ዘዴ ተጠቀመ።
ቀያፋ አይሁዶች የአምላክ ልጅ ነኝ ብሎ የሚናገር ማንኛውም ሰው ምን ያህል እንደሚያስቆጣቸው ያውቅ ነበር። ቀደም ሲል በሁለት የተለያዩ ጊዜያት አይሁዶች ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነኝ ብሎ እንደተናገረ አድርገው በተሳሳተ መንገድ በመረዳት አምላክን ስለተሳደበ ሞት ይገባዋል ብለው ወዲያውኑ ደምድመው ነበር። አሁን ቀያፋ የተንኮል ዘዴ በመጠቀም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” ሲል ጠየቀው።
አይሁዶች ምንም ይምሰላቸው ምን ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው። ዝም ካለ ደግሞ ክርስቶስ መሆኑን እንደካደ ተደርጎ ሊተረጎምበት ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ በድፍረት “እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” ሲል መለሰ።
በዚህ ጊዜ ቀያፋ ተውኔት እንደሚያሳይ ሰው ልብሱን ቀደደና “ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፣ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ።
የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት “ሞት ይገባዋል” አሉ። ከዚያም ያሾፉበትና ያንቋሽሹት ጀመር። በጥፊ መቱት፤ ምራቃቸውንም ተፉበት። ሌሎቹ ደግሞ ፊቱን በሙሉ ሸፍነው በቡጢ እየመቱ “ክርስቶስ ሆይ፣ . . . የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። ይህ ሰብዓዊነት የጎደለው ሕገ ወጥ ድርጊት የተፈጸመው ሌሊት በተካሄደው ችሎት ላይ ነው። ማቴዎስ 26:57-68፤ 26:3, 4፤ ማርቆስ 14:53-65፤ ሉቃስ 22:54, 63-65፤ ዮሐንስ 18:13-24፤ 11:45-53፤ 10:31-39፤ 5:16-18
▪ ኢየሱስ መጀመሪያ የተወሰደው ወዴት ነው? እዚያስ ምን ደረሰበት?
▪ ኢየሱስ ቀጥሎ የተወሰደው ወዴት ነው? ወደዚያ የተወሰደውስ ለምን ነበር?
▪ ቀያፋ የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስ ሞት ይገባዋል ብሎ እንዲበይን ማድረግ የቻለው እንዴት ነው?
▪ በችሎቱ ወቅት የተፈጸመው ሰብዓዊነት የጎደለው ሕገ ወጥ ድርጊት ምንድን ነው?
-
-
በሊቀ ካህናቱ ግቢ የተፈጸመ ክህደትእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 120
በሊቀ ካህናቱ ግቢ የተፈጸመ ክህደት
ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስን በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ጥለውት ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ከሸሹ በኋላ ሽሽታቸውን አቆሙ። ምናልባትም ኢየሱስን ወደ ሐና ቤት እየወሰዱት ሳለ ሳይደርሱበት አይቀሩም። ሐና ኢየሱስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሲልከው ጴጥሮስና ዮሐንስ በቅርብ ርቀት ተከተሉት። በአንድ በኩል ለራሳቸው ሕይወት በመፍራት በሌላ በኩል ደግሞ ጌታቸው ስለሚደርስበት ነገር በመጨነቅ ልባቸው ለሁለት የተከፈለ ይመስላል።
ወደ ሰፊው የቀያፋ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ ዮሐንስ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ወደ ግቢው መግባት ቻለ። ጴጥሮስ ግን ውጪ በሩ ላይ ቆመ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ዮሐንስ ተመልሶ በር ጠባቂ የነበረችውን አገልጋይ አነጋገራትና ጴጥሮስም እንዲገባ ተፈቀደለት።
ብርድ ስለነበረ የቤቱ አገልጋዮችና የሊቀ ካህናቱ መኮንኖች የከሰል እሳት አንድደዋል። ጴጥሮስ እሳት እየሞቀ የኢየሱስን ጉዳይ እየተመለከተ ያለውን ችሎት ውጤት ለመጠባበቅ ከእነርሱ ጋር ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስን ያስገባችው በር ጠባቂ በእሳቱ ብርሃን በደንብ ተመለከተችው። “አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።
ጴጥሮስ ማንነቱ በመታወቁ ደንግጦ ኢየሱስን ጭራሽ እንደማያውቀው በመናገር በሁሉም ፊት ካደ። “የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም” አለ።
ከዚያም ጴጥሮስ ወደ በሩ ሄደ። እዚያም ሌላ ሴት አየችውና ቆመው ለነበሩት ሰዎች “ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ በመማል አሁንም ካደ።
ጴጥሮስ በተቻለ መጠን ራሱን ለመደበቅ በመሞከር እዚያው ግቢው ውስጥ ቆየ። በዚህ ወቅት ሊነጋጋ አካባቢ ዶሮ ሲጮኽ ጴጥሮስ ሳይደነግጥ አልቀረም። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢየሱስን ጉዳይ የሚያየው ችሎት እየተካሄደ ነበር፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ችሎቱ እየተካሄደ የነበረው በግቢው ውስጥ ከፍ ብሎ በሚገኘው ቤት ውስጥ ባለ አንድ ክፍል ነው። ጴጥሮስና ሌሎች ከታች ሆነው ሲጠብቁ ምሥክርነት ለመስጠት ይገቡና ይወጡ የነበሩትን የተለያዩ ሰዎች ያዩ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።
ሰዎች የጴጥሮስን ማንነት ለይተው ከኢየሱስ ጋር እንደነበረ ለመጨረሻ ጊዜ ከተናገሩ አንድ ሰዓት ገደማ አልፏል። አሁን በአካባቢው ቆመው ከነበሩት መካከል በርከት ያሉ ሰዎች ወደ እሱ መጥተው “አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ” አሉት። ከሰዎቹ አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው የማልኮስ ዘመድ ነበር። “በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበርሁምን?” አለው።
ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም” በማለት አስረግጦ ተናገረ። እንዲያውም እየማለና እየተገዘተ ሁሉም እንደተሳሳቱ ሊያሳምናቸው ሞከረ። የተናገርኩት እውነት ካልሆነ መጥፎ ነገር ይድረስብኝ ማለቱ ነበር።
ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ እንደካደ ዶሮ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ዞር ብሎ አየው። ይህ ሲሆን ኢየሱስ በግቢው ውስጥ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው ሰገነት ወጥቶ የነበረ ይመስላል። ወዲያውኑ ጴጥሮስ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ እያሉ ኢየሱስ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስ በፈጸመው ከባድ ኃጢአት ቅስሙ ተሰብሮ ወደ ውጪ ወጣና ምርር ብሎ አለቀሰ።
ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ጴጥሮስ ስለ መንፈሳዊ ጥንካሬው በጣም እርግጠኛ አልነበረምን? እንዴት ጌታውን በተከታታይ ሦስት ጊዜ ሊክደው ቻለ? ሁኔታዎቹ ጴጥሮስ ፈጽሞ ያልጠበቃቸው እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። እውነት ተዛብቶ ነበር፤ ኢየሱስ መጥፎ ወንጀለኛ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቦ ነበር። ትክክል የሆነው ነገር ስህተት እንደሆነ ንጹሕ የሆነው ሰው ደግሞ ወንጀለኛ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቦ ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስ ሁኔታው በፈጠረበት ጭንቀት ሳቢያ ሚዛኑን ሳተ። ለታማኝነት የነበረው ትክክለኛ አመለካከት ድንገት ተናጋ፤ በሰው ፍርሃት ተሽመድምዶ ለከፍተኛ ጸጸት ተዳረገ። ይህ ፈጽሞ አይድረስብን! ማቴዎስ 26:57, 58, 69-75፤ ማርቆስ 14:30, 53, 54, 66-72፤ ሉቃስ 22:54-62፤ ዮሐንስ 18:15-18, 25-27
▪ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ እንዲገቡ ሊፈቀድላቸው የቻለው እንዴት ነው?
▪ ጴጥሮስና ዮሐንስ በግቢው ውስጥ ሳሉ በቤቱ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነበር?
▪ ዶሮ የጮኸው ስንት ጊዜ ነው? ጴጥሮስ ክርስቶስን አላውቀውም ብሎ የካደውስ ስንት ጊዜ ነው?
▪ ጴጥሮስ መማሉና መገዘቱ ምን ትርጉም አለው?
▪ ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ እንዲክድ ያደረገው ምንድን ነው?
-