-
ወሳኝ የሆነው ቀን ሲጀምርእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 105
ወሳኝ የሆነው ቀን ሲጀምር
ኢየሱስ ሰኞ ምሽት ኢየሩሳሌምን ከለቀቀ በኋላ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ ዐቀበት ወደምትገኘው ወደ ቢታንያ ተመለሰ። በኢየሩሳሌም ካከናወነው የመጨረሻ አገልግሎት ሁለቱ ቀኖች ተገባደዋል። ኢየሱስ አሁንም ሌሊቱን ያሳለፈው በወዳጁ በአልዓዛር ቤት እንደሆነ አያጠራጥርም። ዓርብ ዕለት ከኢያሪኮ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በቢታንያ ሲያድር ይህ አራተኛ ጊዜው ነው።
አሁን ኒሳን 11 ማክሰኞ ጠዋት ማለዳ ላይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንደገና መጓዝ ጀመሩ። ይህ ቀን በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ ወሳኝ ነገሮች የተከናወኑበትና እስካሁን ካሳለፋቸው ጊዜያት ሁሉ በበለጠ በሥራ የተጠመደበት ዕለት ነበር። ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ለመጨረሻ ጊዜ የሄደበት ዕለት ነበር። ፍርድ ፊት ቀርቦ ከመገደሉ በፊት የመጨረሻውን ሕዝባዊ አገልግሎት ያከናወነውም በዚህ ቀን ነው።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ። ከቢታንያ ተነሥተው እየተጓዙ ሳለ መንገድ ላይ ጴጥሮስ በፊተኛው ቀን ጠዋት ኢየሱስ የረገማትን ዛፍ ተመለከተ። “መምህር ሆይ፣ እነሆ፣ የረገምሃት በለስ ደርቃለች” አለው።
ኢየሱስ ዛፏን ያደረቃት ለምን ነበር? ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ምክንያቱን ገልጿል:- “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፣ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ [ቆመውበት የነበረውን የደብረ ዘይት ተራራ] እንኳ:- ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”
ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ በማድረግ በአምላክ ማመን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሠርቶ ማሳያ አቀረበላቸው። “የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል” ሲል ገለጸ። በተለይ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሚያጋጥሟቸው አስፈሪ ፈተናዎች አንጻር ሲታይ ይህ ሊማሩት የሚገባ እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነበር! ሆኖም የበለስ ዛፏ መድረቅ ከእምነት ጋር የሚያያዝበት ሌላም ሁኔታ ነበር።
የእስራኤል ሕዝብ ልክ እንደ በለስ ዛፏ አታላይ የሆነ መልክ ነበረው። ምንም እንኳ ሕዝቡ ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን የተዛመደ ቢሆንና ከውጪ ሲታይ የአምላክን ሥርዓት የሚጠብቅ ቢመስልም መልካም ፍሬ የሌለው እምነተ ቢስ ሕዝብ መሆኑን አሳይቷል። ሕዝቡ እምነት የጎደለው በመሆኑ የራሱን የአምላክን ልጅ አልቀበልም በማለት ላይ ነበር! ስለዚህ ኢየሱስ ፍሬያማ ያልሆነችውን የበለስ ዛፍ እንድትደርቅ በማድረግ ይህ ፍሬ አልባና እምነተ ቢስ የሆነ ሕዝብ በመጨረሻ ምን እንደሚደርስበት ግልጽ በሆነ መንገድ አስረድቷል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ እንደ ልማዳቸውም ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱና ኢየሱስ በዚያ ማስተማር ጀመረ። የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” በማለት ተፈታታኝ ጥያቄ አቀረቡለት። ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ኢየሱስ ከዚህ ቀን በፊት በነበረው ዕለት በገንዘብ ለዋጮቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ በአእምሯቸው ይዘው እንደሆነ አያጠራጥርም።
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?”
ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ምን ብለው እንደሚመልሱ እርስ በርሳቸው መመካከር ጀመሩ። “ከሰማይ ብንል:- እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፣ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ።
መሪዎቹ ምን ብለው እንደሚመልሱ ግራ ገባቸው። ስለዚህ “አናውቅም” ብለው ለኢየሱስ መለሱለት።
ኢየሱስም መልሶ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ማቴዎስ 21:19-27፤ ማርቆስ 11:19-33፤ ሉቃስ 20:1-8
▪ ማክሰኞ ዕለት የዋለውን ኒሳን 11 ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?
▪ ኢየሱስ የበለስ ዛፏን በማድረቅ ምን ትምህርቶች ሰጥቷል?
▪ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች ያከናወነው በምን ሥልጣን እንደሆነ ጥያቄ ላቀረቡለት ሰዎች መልስ የሰጠው እንዴት ነው?
-
-
በወይን አትክልት ምሳሌዎች ተጋለጡእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 106
በወይን አትክልት ምሳሌዎች ተጋለጡ
ኢየሱስ ያለው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ነው። የፈጸማቸውን ነገሮች ያከናወነው በማን ሥልጣን እንደሆነ የጠየቁትን የሃይማኖት መሪዎች ግራ ያጋባቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። ግራ በተጋቡበት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ኢየሱስ “ምን ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም አንድ ምሳሌ በመጠቀም ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ አመለከታቸው።
“አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤” በማለት ኢየሱስ ታሪኩን መናገር ጀመረ። “ወደ አንደኛው ቀርቦ:- ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ:- አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ:- እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?” በማለት ኢየሱስ ጠየቃቸው።
ተቃዋሚዎቹ “ፊተኛው” ብለው መለሱለት።
ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።” ቀራጮቹና ጋለሞቶቹ በመጀመሪያ አምላክን ለማገልገል ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ያህል ነበር። በኋላ ግን እንደ መጀመሪያው ልጅ ተጸጸቱና አገለገሉት። በሌላ በኩል ግን የሃይማኖት መሪዎቹ እንደ ሁለተኛው ልጅ አምላክን እናገለግላለን ብለው ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “[አጥማቂው] ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፣ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።”
ኢየሱስ በመቀጠል የእነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጉድለት አምላክን አለማገልገላቸው ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። መጥፎዎችና ክፉዎችም ነበሩ። “የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ” ሲል ኢየሱስ ተናገረ፤ “ቅጥርም ቀጠረለት፣ መጥመቂያም ማሰለት፣ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፣ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፣ እንዲሁም አደረጉባቸው።”
“ባሮቹ” “ባለቤት” የሆነው ይሖዋ አምላክ ‘በወይን አትክልቱ ቦታ’ ወደሚሠሩት “ገበሬዎች” የላካቸው ነቢያት ናቸው። እነዚህ ገበሬዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ “የወይን አትክልት” እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው የእስራኤል ሕዝብ ዋና ወኪሎች ናቸው።
“ገበሬዎቹ” “ባሮቹን” ስላሠቃዩአቸውና ስለገደሏቸው ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “በኋላ ግን:- [የወይን አትክልቱ ባለቤት] ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው:- ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።”
አሁን ኢየሱስ “የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?” ሲል የሃይማኖት መሪዎቹን ጠየቃቸው።
የሃይማኖት መሪዎቹ እንዲህ ብለው መለሱ:- “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፣ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል።”
የሃይማኖት መሪዎቹ የይሖዋ “የወይን አትክልት” በሆነው በእስራኤል ብሔር ላይ ከሚሠሩት እስራኤላውያን “ገበሬዎች” መካከል የሚገኙ በመሆኑ ሳያውቁት በዚህ መንገድ በራሳቸው ላይ ፍርድ በይነዋል። ይሖዋ ከእነዚህ ገበሬዎች ይጠብቀው የነበረው ፍሬ እውነተኛ መሲሕ በሆነው ልጁ ማመንን ነበር። እንዲህ ዓይነት ፍሬ ባለማፍራታቸው ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው:- “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፣ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ [በመዝሙር 118:22, 23 ላይ] አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።”
በዚህ ጊዜ ጻፎቹና የካህናት አለቆቹ ኢየሱስ ስለ እነርሱ እየተናገረ እንዳለ ተገነዘቡና ሕጋዊ ‘ወራሽ’ የሆነውን ኢየሱስን ሊገድሉት ፈለጉ። ስለዚህ በብሔር ደረጃ በአምላክ መንግሥት ገዥዎች የመሆን መብታቸው ይወሰድባቸዋል። በምትኩ ተስማሚ የሆኑ ፍሬዎችን የሚያፈሩ ‘የወይን አትክልት ገበሬዎችን’ ያቀፈ አዲስ ብሔር ይፈጠራል።
ሕዝቡ ኢየሱስን ነቢይ አድርገው ይመለከቱት ነበር፤ ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎቹ ሕዝቡን ስለፈሩ በዚህ ጊዜ ኢየሱስን ለመግደል አልሞከሩም። ማቴዎስ 21:28-46፤ ማርቆስ 12:1-12፤ ሉቃስ 20:9-19፤ ኢሳይያስ 5:1-7
▪ ኢየሱስ በተናገረው የመጀመሪያ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ልጆች እነማንን ያመለክታሉ?
▪ በሁለተኛው ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ‘ባለቤቱ፣’ ‘የወይኑ አትክልት፣’ “ገበሬዎቹ፣” “ባሮቹ” እና “ወራሹ” እነማንን ያመለክታሉ?
▪ ‘የወይኑ አትክልት ገበሬዎች’ ምን ይሆናሉ? እነርሱን የሚተኳቸውስ እነማን ናቸው?
-
-
የሠርጉ ድግስ ምሳሌእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 107
የሠርጉ ድግስ ምሳሌ
ኢየሱስ ሁለት ምሳሌዎች በመናገር ጻፎቹንና የካህናት አለቆቹን ስላጋለጣቸው ሊገድሉት ፈለጉ። ሆኖም ኢየሱስ በዚህ ብቻ አላበቃም። አሁንም እንዲህ በማለት ሌላ ምሳሌ ነገራቸው:-
“መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም።”
ሠርጉን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ የደገሰው ንጉሥ ይሖዋ አምላክ ነው። መቶ አርባ አራት ሺዎቹን ቅቡዓን ተከታዮች ያቀፈችው ሙሽራ በመጨረሻ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ትጣመራለች። የንጉሡ ተገዥዎች በ1513 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ወደ ሕጉ ቃል ኪዳን በመግባት “የካህናት መንግሥት” የመሆን አጋጣሚ የተቀበሉት የእስራኤል ሕዝብ ናቸው። ስለዚህ በዚያ ወቅት ወደ ሠርጉ ድግስ እንዲመጡ በመጀመሪያ የተጋበዙት እነርሱ ነበሩ።
ይሁን እንጂ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ (የንጉሡ ባሮች) የመንግሥቱን ስብከት ሥራቸውን እስከ ጀመሩበት እስከ 29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የመከር ወራት ድረስ ኑ የሚለው ጥሪ ለተጋበዙት ሰዎች አልቀረበም ነበር። ሆኖም ከ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር አንስቶ እስከ 33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ድረስ በባሮቹ አማካኝነት ይህ ጥሪ የቀረበላቸው ሥጋዊ እስራኤላውያን ለመምጣት ፈቃደኞች አልሆኑም። ስለዚህ አምላክ ለተጋባዡ ሕዝብ ሌላ አጋጣሚ ሰጠ፤ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:-
“ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ:- የታደሙትን:- እነሆ፣ ድግሴን አዘጋጀሁ፣ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፣ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ።” ይህ ለተጋበዙት ሰዎች የቀረበው ሁለተኛውና የመጨረሻው ጥሪ የጀመረው በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ በፈሰሰበት ጊዜ ነበር። ይህ ጥሪ እስከ 36 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ድረስ ቀጥሏል።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ እስራኤላውያን አሁንም ይህን ጥሪ ንቀዋል። “እነርሱ ግን ቸል ብለው” አለ ኢየሱስ፤ “አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም።” ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ንጉሡም ተቈጣ፣ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።” ይህ ኢየሩሳሌም በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሮማውያን በወደመችበትና እነዚያ ነፍሰ ገዳዮች በተገደሉበት ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ኢየሱስ በዚህ መካከል የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “በዚያን ጊዜ [ንጉሡ] ባሮቹን:- ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፣ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ።” ባሮቹ የታዘዙትን አደረጉ፤ “የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት።”
ከተጋባዦቹ ከተማ ውጪ ካሉ መንገዶች እንግዶችን የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው በ36 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ነው። ወደ ሠርጉ ከተሰበሰቡት ያልተገረዙ አሕዛብ መካከል የመጀመሪያዎቹ የሮማ ሠራዊት አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ናቸው። መጀመሪያ የቀረበላቸውን ጥሪ አልቀበልም ያሉትን ሰዎች የሚተኩትን እነዚህን አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች የመሰብሰቡ ሥራ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ ቀጥሏል።
ሠርጉ የተደገሰበት ቤት የሞላው በ20ኛው መቶ ዘመን ነው። ኢየሱስ ከዚያ በኋላ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየና:- ወዳጄ ሆይ፣ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው፤ እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን:- እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ።”
የሠርግ ልብስ ያልለበሰው ሰው የሕዝበ ክርስትናን አስመሳይ ክርስቲያኖች ይወክላል። አምላክ እነዚህን ሰዎች የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ትክክለኛ መለያ እንዳላቸው አድርጎ በመቁጠር እውቅና አልሰጣቸውም። አምላክ የመንግሥቱ ወራሾች አድርጎ በቅዱስ መንፈሱ አልቀባቸውም። ስለዚህ ጥፋት ወደሚያገኛቸው ወደ ጨለማው ተጥለዋል።
ኢየሱስ “የተጠሩ [“የተጋበዙ፣” NW] ብዙዎች፣ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና” በማለት ምሳሌውን ደመደመ። አዎን፣ የክርስቶስ ሙሽራ አባላት እንዲሆኑ ከእስራኤል ሕዝብ የተጋበዙ ሰዎች ብዙ ነበሩ፤ የተመረጡት ሥጋዊ እስራኤላውያን ግን ጥቂቶች ናቸው። ሰማያዊ ሽልማት ከሚያገኙት 144,000 እንግዶች መካከል አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ማቴዎስ 22:1-14፤ ዘጸአት 19:1-6፤ ራእይ 14:1-3
▪ ወደ ሠርጉ ድግስ በመጀመሪያ የተጋበዙት እነማን ነበሩ? ግብዣው የቀረበላቸውስ መቼ ነበር?
▪ ለተጋበዙት ሰዎች ኑ የሚለው ጥሪ በመጀመሪያ የቀረበው መቼ ነበር? ጥሪውን እንዲያደርሱ የተላኩት ባሮችስ እነማን ናቸው?
▪ ሁለተኛው ጥሪ የተሰማው መቼ ነው? ከዚያ በኋላ የተጋበዙትስ እነማን ናቸው?
▪ የሠርግ ልብስ ባልለበሰው ሰው የተመሰሉት እነማን ናቸው?
▪ የተጠሩት ብዙዎችና የተመረጡት ጥቂቶች እነማን ናቸው?
-
-
ኢየሱስን ማጥመድ ሳይችሉ ቀሩእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 108
ኢየሱስን ማጥመድ ሳይችሉ ቀሩ
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ስላስተማረና ከጥቂት ጊዜ በፊት ሦስት ምሳሌዎች በመናገር የሃይማኖታዊ ጠላቶቹን ክፋት ስላጋለጠ ፈሪሳውያን ተናደዱና እርሱን ለመያዝ የሚያስችላቸውን ነገር እንዲናገር በማድረግ ሊያጠምዱት ተማከሩ። አንድ ተንኮል ሸረቡና እሱን ለማጥመድ እንዲሞክሩ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ የፖለቲካ ቡድን ተከታዮች ጋር ላኳቸው።
የተላኩት ሰዎች እንዲህ አሉት:- “መምህር ሆይ! አንተ እውነተኛ መሆንህንና የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት የምታስተምር መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራት የምታደርገው ነገር የለም፤ ምክንያቱም አንተ ለሰው አታደላም። በል እስቲ ንገረን ምን ይመስልሃል? ለቄሳር ግብር መክፈል ተገቢ ነውን ወይስ ተገቢ አይደለም?”— የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ በሽንገላቸው አልተታለለም። ‘የለም፣ ይህን ግብር መክፈል ተገቢ ወይም ትክክል አይደለም’ ብሎ ቢመልስ በሮም መንግሥት ላይ ዓመፅ አነሳስተሃል ተብሎ እንደሚወነጀል ያውቃል። ‘ተገቢ ነው፣ ይህን ግብር መክፈል አለባችሁ’ ብሎ ቢመልስ ደግሞ በሮም ቀንበር ሥር መውደቃቸውን ያልወደዱት አይሁዶች ሊጠሉት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ “እናንተ ግብዞች፣ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ብር አሳዩኝ” ብሎ መለሰላቸው።
አንድ ሳንቲም አምጥተው ሲያሳዩት “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” ብሎ ጠየቃቸው።
“የቄሣር” ብለው መለሱለት።
“እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” አላቸው። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የሰጠውን ጥበብ የተሞላበት መልስ ሲሰሙ ተደነቁ። ከዚያም ትተውት ሄዱ።
ትንሣኤ የለም ብለው የሚያምኑት ሰዱቃውያን፣ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ሊያስወነጅለው የሚችል ነገር ሊያገኙበት እንዳልቻሉ ሲመለከቱ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና እንዲህ ሲሉ ጠየቁት:- “መምህር ሆይ፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ። ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፣ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፣ እስከ ሰባተኛው ድረስ። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች። ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?”
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፣ አይጋቡምም። ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር:- እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።”
አሁንም ሕዝቡ በኢየሱስ መልስ በጣም ተደነቁ። እንዲያውም ከጻፎቹ አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ፣ መልካም ተናገርህ” ለማለት ተገደዋል።
ፈሪሳውያን ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ተመለከቱና አንድ ግንባር ፈጥረው ወደ እሱ መጡ። ኢየሱስን እንደገና ለመፈተን ከመካከላቸው አንዱ ጸሐፊ “መምህር ሆይ፣ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ብሎ ጠየቀው።
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ:- እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፣ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” እንዲያውም ኢየሱስ “የሙሴ ሕግና የነቢያት ትምህርት ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዞች ላይ ነው” ሲል አክሎ ተናግሯል።— የ1980 ትርጉም
ጸሐፊው እንዲህ በማለት በነገሩ መስማማቱን ገለጸ:- “መልካም ነው፣ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፣ ባልንጀራህንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው።”
ኢየሱስ ጸሐፊው አስተዋይነት የተንጸባረቀበት መልስ እንደሰጠ በመረዳት “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው።
ኢየሱስ አሁን ለሦስት ቀናት ማለት እሁድ፣ ሰኞና ማክሰኞ በቤተ መቅደሱ ሲያስተምር ቆይቷል። ሕዝቡ በትምህርቱ የተደሰቱ ቢሆንም የሃይማኖት መሪዎቹ ግን ሊገድሉት ፈልገዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ያደረጓቸው ሙከራዎች ከሽፈዋል። ማቴዎስ 22:15-40፤ ማርቆስ 12:13-34፤ ሉቃስ 20:20-40
▪ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማጥመድ ምን ተንኮል ሸርበው ነበር? አዎ ወይም አይደለም የሚል ቀጥተኛ መልስ ቢሰጥ ኖሮስ ምን ውጤት ያስከትል ነበር?
▪ ኢየሱስ ሰዱቃውያን እሱን ለማጥመድ ያደረጉትን ጥረት ያጨናገፈው እንዴት ነው?
▪ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለመፈተን ምን ተጨማሪ ሙከራ አድርገዋል? ውጤቱስ ምን ነበር?
▪ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ባከናወነው የመጨረሻ አገልግሎት ወቅት በቤተ መቅደሱ ያስተማረው ለስንት ቀናት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?
-
-
ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን አወገዘእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 109
ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን አወገዘ
ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹን አፋቸውን ስላስያዛቸው ሌላ ነገር ለመጠየቅ ፈሩ። ስለዚህ ራሱ ቅድሚያውን ወስዶ በማነጋገር ድንቁርናቸውን አጋለጠባቸው። “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው። “የማንስ ልጅ ነው?”
ፈሪሳውያን “የዳዊት” ብለው መለሱለት።
ኢየሱስ ምንም እንኳ ዳዊት የክርስቶስ ወይም የመሲሑ ሥጋዊ ቅድመ አያት መሆኑን ባይክድም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “እንኪያስ ዳዊት:- ጌታ ጌታዬን:- ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ [በመዝሙር 110 ላይ] ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፣ እንዴት ልጁ ይሆናል?”
ፈሪሳውያን የክርስቶስን ወይም የተቀባውን እውነተኛ ማንነት ስለማያውቁ ዝም አሉ። ፈሪሳውያን መሲሑ የዳዊት ሰብዓዊ ዝርያ እንደሆነ ብቻ አድርገው ያምኑ የነበረ ይመስላል፤ ሆኖም መሲሑ የዳዊት ዝርያ ብቻ ሳይሆን በሰማይ ይኖር የነበረና የዳዊት የበላይ ወይም ጌታ ነው።
አሁን ኢየሱስ ወደ ሕዝቡና ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞረና ከጻፎችና ከፈሪሳውያን እንዲጠበቁ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። ‘በሙሴ ወንበር ተቀምጠው’ የአምላክ ሕግ የሚያስተምሩ በመሆናቸው ኢየሱስ “ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም” በማለት አጥብቆ መከራቸው። ሆኖም “እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” ሲል አክሎ ተናግሯል።
ግብዞች ናቸው። ኢየሱስ ከተወሰኑ ወራት በፊት በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋብዞ በነበረበት ጊዜ የተናገረውን አባባል በመጠቀም አወገዛቸው። “ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ” ሲል ተናገረ። በተጨማሪም የሚከተሉትን ምሳሌዎች አቀረበ:-
“አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ።” እነዚህ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ አነስተኛ የሆኑ በግንባር ላይ ወይም በክንድ ላይ የሚታሠሩ ክታቦች የሕጉን አራት ክፍሎች ይኸውም ዘጸአት 13:1-10, ዘጸአት 13:11-16ን፣ ዘዳግም 6:4-9ንና ዘዳግም 11:13-21ን የያዙ ናቸው። ሆኖም ፈሪሳውያን ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው እንዲባሉ የእነዚህን ክታቦች መጠን አሳድገው ነበር።
ኢየሱስ በመቀጠል “የልብሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ” ሲል ተናገረ። (የ1980 ትርጉም) እስራኤላውያን በልብሶቻቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያበጁ በዘኍልቁ 15:38-40 ላይ ታዘው ነበር። ፈሪሳውያን ግን ዘርፋቸውን ሌላ ማንኛውም ሰው ከሚያደርገው የበለጠ ያስረዝሙ ነበር። ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት ለታይታ ነበር! ኢየሱስ ‘የከበሬታ ስፍራ እንደሚወዱ’ ተናገረ።
የሚያሳዝነው፣ የእሱም ደቀ መዛሙርት ልክ እንደዚሁ የላቀ ቦታ የማግኘት ፍላጎት ተጠናውቷቸው ነበር። ስለዚህ የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “እናንተ ግን:- መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና:- ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።” ደቀ መዛሙርቱ አንደኛ የመሆንን ፍላጎት ማስወገድ ነበረባቸው! ኢየሱስ ‘ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሁን’ ሲል አጥብቆ መከራቸው።
ኢየሱስ በመቀጠል ፈሪሳውያንንና ጻፎችን በተደጋጋሚ ግብዞች እያለ በመጥራት በእነርሱ ላይ የሚደርሱ ተከታታይ ወዮታዎችን ተናግሯል። “መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት” እንደሚዘጉ ተናገረ። በተጨማሪም ‘በጸሎት ርዝመት እያመካኙ የመበለቶችን ቤት ይበዘብዛሉ።’
ኢየሱስ “እናንተ . . . ዕውሮች መሪዎች፣ ወዮላችሁ” ሲል ተናገረ። በገዛ ፈቃዳቸው በሚያወጧቸው ደንቦች ላይ እንደተንጸባረቀው መንፈሣዊ ነገሮችን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ በመሆኑ ኢየሱስ አውግዟቸዋል። ለምሳሌ ያህል ‘ማንም በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ይሉ ነበር። የአምልኮ ቦታው ከነበረው መንፈሳዊ ዋጋ ይበልጥ የቤተ መቅደሱን ወርቅ ከፍ አድርገው በመመልከታቸው በመንፈስ ዕውሮች መሆናቸውን አሳይተዋል።
ከዚያም ኢየሱስ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ፈሪሳውያን ከትናንሽ ተክሎች አሥራት ማውጣትን ወይም አንድ አሥረኛውን መክፈልን ከፍ አድርገው እየተመለከቱ ‘በሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ነገሮች ማለትም ፍርድን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን’ ግን በመተዋቸው አውግዟቸዋል።
ኢየሱስ ፈሪሳውያንን “ዕውሮች መሪዎች፣ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ” ብሏቸዋል። ከሚጠጡት ወይን ውስጥ ትንኝ ያወጡ የነበረው በራሪ ነፍስ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታቸው ርኩስ ስለነበረ ነው። ሆኖም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የበለጠ ክብደት የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ችላ ማለታቸው በሃይማኖታቸው እንደ ርኩስ የሚታየውን ግመልን ከመዋጥ ጋር የሚመሳሰል ነው። ማቴዎስ 22:41 እስከ 23:24፤ ማርቆስ 12:35-40፤ ሉቃስ 20:41-47፤ ዘሌዋውያን 11:4, 21-24
▪ ፈሪሳውያን ዳዊት በመዝሙር 110 ላይ ስለተናገረው ነገር ኢየሱስ በጠየቃቸው ጊዜ ዝም ያሉት ለምንድን ነው?
▪ ፈሪሳውያን ክታቦቻቸውን ያሰፉትና የልብሶቻቸውን ዘርፎች ያስረዘሙት ለምንድን ነው?
▪ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጠ?
▪ ፈሪሳውያን በገዛ ፈቃዳቸው ምን ደንቦችን አውጥተዋል? ኢየሱስ ይበልጥ ክብደት የሚሰጣቸውን ነገሮች በመተዋቸው ያወገዛቸውስ እንዴት ነው?
-
-
በቤተ መቅደሱ ያከናወነው አገልግሎት ተፈጸመእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 110
በቤተ መቅደሱ ያከናወነው አገልግሎት ተፈጸመ
ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ በቤተ መቅደሱ የተገኘው በዚህ ዕለት ነው። እንዲያውም በምድር ላይ ያከናወነውን ሕዝባዊ አገልግሎት እያጠናቀቀ ነው፤ ከዚህ በኋላ የቀሩ ነገሮች ቢኖሩ ከሦስት ቀናት በኋላ ፍርድ ፊት ቀርቦ ሲገደል የሚፈጸሙት ሁኔታዎች ናቸው። አሁን ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ማውገዙን ቀጠለ።
እንደገና ሦስት ጊዜ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ . . . ወዮላችሁ” ሲል ተናገረ። በመጀመሪያ ወዮላችሁ ያላቸው “በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ” ያጠሩ ስለነበረ ነው። ስለዚህ “ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ” በማለት አጥብቆ መከራቸው።
ከዚህ በመቀጠል ጻፎችና ፈሪሳውያን በውስጥ ያለውን የተበላሸና የበሰበሰ ነገር ከውጪ በሚታይ የሃይማኖተኛነት ሽፋን ለመደበቅ በመሞከራቸው ወዮላችሁ ሲል አስጠነቀቃቸው። “በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን” ትመስላላችሁ አላቸው።
በመጨረሻም፣ ምጽዋታቸው የሰዎችን ትኩረት እንዲስብ ለማድረግ ሲሉ ለነቢያት መቃብሮች መሥራታቸውና መቃብሮቹን ማስጌጣቸው ግብዝነታቸውን የሚያንጸባርቅ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደገለጸው እነርሱ “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ናቸው። በእርግጥም ግብዝነታቸውን ለማጋለጥ የደፈረ ማንኛውም ሰው ሕይወቱ አደጋ ላይ ይወድቃል!
ኢየሱስ በመቀጠል እጅግ ኃይለኛ ቃላት በመጠቀም አወገዛቸው። “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣” አላቸው፤ “ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” ገሃነም የኢየሩሳሌም ቆሻሻ የሚጣልበት ሸለቆ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያን መጥፎ ጎዳና በመከተላቸው ዘላለማዊ ጥፋት እንደሚደርስባቸው መናገሩ ነበር።
ኢየሱስ ወኪሎቹ አድርጎ ስለሚልካቸው ሰዎች ሲናገር እንዲህ አለ:- “ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፣ ከእነርሱም በምኲራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ [በሁለተኛ ዜና ላይ ዮዳሄ ተብሏል] ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።”
የእስራኤል መሪዎች ዘካርያስ ስለነቀፋቸው “ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት።” ሆኖም ኢየሱስ በተነበየው መሠረት እስራኤል በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ የእጅዋን ማግኘቷ የማይቀር ነበር። ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ኢየሩሳሌም በሮማ ሠራዊት ስትጠፋና ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ አይሁዶች ሲገደሉ ቅጣታቸውን ተቀብለዋል።
ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ሲያስበው በጣም አዘነ። አሁንም በድጋሚ እንዲህ አለ:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ . . . ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።”
ከዚያም ኢየሱስ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም” ሲል አክሎ ተናገረ። ይህ የሚሆነው ክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥቱን በመውረስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ነው፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች በእምነት ዓይን ያዩታል።
አሁን ኢየሱስ በመቅደሱ ውስጥ ያሉትን የገንዘብ መዋጮ የሚደረግባቸው ዕቃዎችና ዕቃዎቹ ውስጥ ገንዘብ የሚከቱትን ሰዎች ማየት ወደሚችልበት ቦታ ሄደ። ሀብታሞቹ ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር። ሆኖም አንዲት ድሀ መበለት መጣችና ምንም ያህል ዋጋ የሌላቸው ሁለት ሳንቲሞች ከተተች።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠራና “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች” አላቸው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብለው ሳያስቡ አልቀረም። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፣ ይህች ግን ከጒድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ቤተ መቅደሱን ለመጨረሻ ጊዜ ለቆ ሄደ።
ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በቤተ መቅደሱ ስፋትና ውበት በመደነቅ “መምህር ሆይ፣ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ” አለው። በእርግጥም ድንጋዮቹ ርዝመታቸው ከ11 ሜትር በላይ እንደሆነ፣ ወርዳቸው ከ5 ሜትር እንደሚበልጥና ከፍታቸው ከ3 ሜትር በላይ እንደሆነ ይነገራል!
ኢየሱስ ‘እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያላችሁን?’ ሲል መለሰላቸው። “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም።”
ኢየሱስና ሐዋርያቱ ይህን ከተነጋገሩ በኋላ የቄድሮንን ሸለቆ አቋርጠው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። እዚያ ላይ ሆነው በጣም የሚያምረውን ቤተ መቅደስ ቁልቁል መመልከት ይችላሉ። ማቴዎስ 23:25 እስከ 24:3፤ ማርቆስ 12:41 እስከ 13:3፤ ሉቃስ 21:1-6፤ 2 ዜና መዋዕል 24:20-22
▪ ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደሱ በሄደበት ወቅት ምን አከናውኗል?
▪ የጻፎቹና የፈሪሳውያኑ ግብዝነት በግልጽ የታየው እንዴት ነው?
▪ የ“ገሃነም ፍርድ” ማለት ምን ማለት ነው?
▪ ኢየሱስ መበለቷ ከሀብታሞቹ የበለጠ መዋጮ እንዳደረገች የተናገረው ለምንድን ነው?
-
-
የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክትእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 111
የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት
አሁን ጊዜው ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ነው። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን ቁልቁል እየተመለከተ ሳለ ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ብቻቸውን ሆነው ወደ እርሱ መጡ። ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ በዚህ ሥፍራ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም በማለት ተንብዮ ስለነበረ የቤተ መቅደሱ ሁኔታ አሳስቧቸዋል።
ሆኖም ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ሌላም ጉዳይ በአእምሯቸው ይዘው የነበረ ይመስላል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ‘የሰው ልጅ ስለሚገለጥበት’ ወቅት ማለትም ስለ ‘መገኘቱ’ ተናግሮ ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ‘ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ነግሯቸው ነበር። ስለዚህ ሐዋርያቱ ከፍተኛ የሆነ የማወቅ ጉጉት አድሮባቸዋል።
“ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? [ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የሚጠፉበት ማለት ነው] የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ብለው ጠየቁት። (NW) ጥያቄያቸው ሦስት ክፍል ያለው ነው ማለት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ቤተ መቅደሷ ፍጻሜ፣ ከዚያም ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን ስለመገኘቱና በመጨረሻ ደግሞ ስለ ጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ማወቅ ፈልገዋል።
ኢየሱስ ረጅም በሆነው መልሱ ለሦስቱም የጥያቄው ክፍሎች ምላሽ ሰጥቷል። የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት የሚያበቃበትን ጊዜ የሚጠቁም ምልክት ሰጥቷል፤ ሆኖም ሌላ ተጨማሪ ምልክትም ሰጥቷል። ወደፊት የሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበትና ጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት የሚያከትምበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት ላይ የሚኖሩ መሆናቸውን እንዲያውቁ የሚያስችል ምልክት ሰጥቷል።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሐዋርያቱ የኢየሱስን ትንቢት ፍጻሜ ተመልክተዋል። አዎን፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገራቸው ነገሮች በእነርሱ ዘመን መፈጸም ጀምረዋል። በመሆኑም ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሕይወት የነበሩ ክርስቲያኖች የአይሁድ ሥርዓት ከቤተ መቅደሱ ጋር ሲጠፋ ዱብ ዕዳ አልሆነባቸውም።
ይሁን እንጂ ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ የተገኘው በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር አይደለም። ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን የተገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። ይህ የሆነው ግን መቼ ነው? የኢየሱስን ትንቢት መመርመራችን ለዚህ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል።
ኢየሱስ ‘ጦርነትና የጦርነት ወሬ’ እንደሚኖር ተንብዮአል። “ሕዝብ በሕዝብ ላይ” እንደሚነሣና የምግብ እጥረት፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ቸነፈር እንደሚኖር ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱ ጥላቻ ይደርስባቸዋል፤ እንዲሁም ይገደላሉ። የሐሰት ነቢያት ተነስተው ብዙዎችን ያስታሉ። ዓመፅ ይጨምራል፤ የብዙ ሰዎች ፍቅርም ይቀዘቅዛል። በዚሁ ጊዜ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ምሥክር እንዲሆን ለሁሉም ብሔራት ይሰበካል።
ምንም እንኳ የኢየሱስ ትንቢት ኢየሩሳሌም በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከመጥፋቷ በፊት በተወሰነ ደረጃ የተፈጸመ ቢሆንም ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው ኢየሱስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበትና በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ላይ ነው። ከ1914 ወዲህ የተከናወኑትን የዓለም ሁኔታዎች በሚገባ ስንመረምር ኢየሱስ የተናገረው ታላቅ ትንቢት ከዚያ ዓመት አንስቶ ዋነኛ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ እንዳለ እንረዳለን።
ኢየሱስ የሰጠው ሌላው የምልክቱ ክፍል ‘የጥፋት ርኩሰት’ መታየት ነው። በ66 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የሮም ‘ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ’ የቤተ መቅደሱን ግንብ በሰረሰረበት ጊዜ ይህ ርኩሰት ታይቶ ነበር። ‘ርኩሰቱ’ መቆም በማይገባው ሥፍራ ቆሞ ነበር።
በምልክቱ ዋነኛ ፍጻሜ ርኩሰቱ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና በእሱ እግር የተተካው የተባበሩት መንግሥታት ነው። ሕዝበ ክርስትና ለዓለም ሰላም ተብሎ የተቋቋመውን ይህን ድርጅት የአምላክ መንግሥት ምትክ አድርጋ ትመለከተዋለች። እንዴት ያለ ርኩሰት ነው! ስለዚህ ከጊዜ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት አባል የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች በሕዝበ ክርስትና (በታላቂቱ ኢየሩሳሌም) ላይ ተነስተው ድምጥማጧን ያጠፏታል።
በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።” በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደተገደሉበት የሚነገርለት ታላቅ መከራ ነው። የዚህኛው የኢየሱስ ትንቢት ክፍል ዋነኛ ፍጻሜ ከዚህ እጅግ የከፋ ይሆናል።
በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ተማምኖ መኖር
ኒሳን 11 ማክሰኞ ዕለት እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን የሚገኝበትን ጊዜና የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜን የሚጠቁመውን ምልክት በተመለከተ ከሐዋርያቱ ጋር የሚያደርገውን ውይይት ቀጠለ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችን እንዳይከተሉ አስጠነቀቃቸው። ‘ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ለማሳት’ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናገረ። ሆኖም እነዚህ የተመረጡ ሰዎች ልክ ከርቀት እንደሚመለከቱት ንስሮች እውነተኛው መንፈሳዊ ምግብ ወደሚገኝበት ማለትም በማይታይ ሁኔታ በሥልጣኑ ላይ ወደተገኘው ወደ እውነተኛው ክርስቶስ ይሰበሰባሉ። ተታልለው ወደ አንድ ሐሰተኛ ክርስቶስ አይሰበሰቡም።
ሐሰተኛ ክርስቶሶች በሚታይ ሁኔታ ብቅ ከማለት በቀር ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የለም። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ በሥልጣኑ የሚገኘው በማይታይ ሁኔታ ነው። ኢየሱስ ታላቁ መከራ ከፈነዳ በኋላ “ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም” ሲል ገልጿል። አዎን፣ ይህ ወቅት በሰው ዘር ሕይወት ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የጨለማ ዘመን ይሆናል። ፀሐይ በቀን እንደጨለመችና ጨረቃ ደግሞ በሌሊት ብርሃንዋን እንደማትሰጥ ያህል ይሆናል።
ኢየሱስ በመቀጠል “የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ” ሲል ተናገረ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ግዑዙ ሰማይ አስፈሪ መልክ እንደሚኖረው አመልክቷል። ፍርሃቱና ዓመፁ ቀደም ባለው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ካጋጠሙት ነገሮች ሁሉ የከፋ ይሆናል።
በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም ይህ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የጨለማ ዘመን ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ።”
ሆኖም “የሰው ልጅ” ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት ‘በኃይል ሲመጣ’ ዋይ ዋይ የሚሉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። “የተመረጡት” ማለትም ከክርስቶስ ጋር የሰማያዊ መንግሥት ተካፋዮች የሚሆኑት 144,000ዎችም ሆኑ ቀደም ሲል ኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ብሎ የጠራቸው ተባባሪዎቻቸው አያለቅሱም። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ የጨለማ ዘመን ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ [“ደኅንነታችሁ፣” የ1980 ትርጉም] ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” በማለት ለሰጠው ማበረታቻ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።
ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ ፍጻሜው ምን ያህል እንደቀረበ መረዳት እንዲችሉ የሚከተለውን ምሳሌ ሰጠ:- “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”
በዚህ መንገድ ደቀ መዛሙርቱ የምልክቱ የተለያዩ ገጽታዎች በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ሲመለከቱ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቅረቡንና የአምላክ መንግሥት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ መገንዘብ አለባቸው። ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮች በሚከናወኑባቸው የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩትን ደቀ መዛሙርት ሲመክር እንዲህ አለ:-
“ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።”
ልባሞቹና ሰነፎቹ ቆነጃጅት
ኢየሱስ ሐዋርያቱ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚጠቁም ምልክት እንዲሰጣቸው ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ሦስት ምሳሌዎችን በመጠቀም የምልክቱን ተጨማሪ ገጽታዎች ተናገረ።
ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች የእያንዳንዱን ምሳሌ ፍጻሜ ይመለከታሉ። የመጀመሪያውን ምሳሌ በሚከተሉት ቃላት ገለጸ:- “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቈነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።”
ኢየሱስ ‘መንግሥተ ሰማያት አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች’ ሲል ሰማያዊውን መንግሥት ከሚወርሱት ሰዎች መካከል ግማሾቹ ሰነፎች ግማሾቹ ደግሞ ልባሞች ናቸው ማለቱ አይደለም! ከዚህ ይልቅ ከመንግሥተ ሰማያት ጋር በተያያዘ ይህን የመሰለ ሁኔታ አለ ብሎ ለመጥቀስ ወይም ደግሞ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች አሉ ብሎ ለመግለጽ ፈልጎ ነው።
አሥሩ ቆነጃጅት መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ አጋጣሚ ያላቸውን ወይም ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን የሚሉ ክርስቲያኖችን በሙሉ ያመለክታሉ። የክርስቲያን ጉባኤ ከሞት ተነሥቶ ክብር ለተቀዳጀው ሙሽራ ለኢየሱስ ክርስቶስ የታጨችው በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ነው። ሆኖም ጋብቻው ወደፊት ተለይቶ ባልተጠቀሰ ጊዜ ላይ በሰማይ ይከናወናል።
በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው አሥሩ ቆነጃጅት የወጡት ሙሽራውን ለመቀበልና በሠርጉ አጀብ ውስጥ ለመቀላቀል ነው። ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደተዘጋጀላት ቤት ሲያመጣት አጀቡን በመብራታቸው በማድመቅ ለእሱ ያላቸውን አክብሮት ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።”
ሙሽራው ረዘም ላለ ጊዜ መዘግየቱ ክርስቶስ ንጉሣዊ ገዥ ሆኖ በሥልጣኑ ላይ የሚገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደነበረ ያመለክታል። ከረጅም ጊዜ በኋላ በ1914 በዙፋኑ ላይ ተቀምጧል። ከዚህ በፊት በነበረው ረጅም ሌሊት ቆነጃጅቱ በሙሉ ተኝተው ነበር። ሆኖም በዚህ አልተነቀፉም። ሰነፎቹ ቆነጃጅት የተነቀፉት በዕቃቸው ውስጥ ዘይት ባለመያዛቸው ነው። ኢየሱስ ቆነጃጅቱ ሙሽራው ከመምጣቱ በፊት እንዴት እንደነቁ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኩል ሌሊትም ሲሆን:- እነሆ ሙሽራው ይመጣል፣ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቈነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን:- መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው:- ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።”
ዘይቱ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ብርሃን አብሪዎች ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ነገር ያመለክታል። ይህም ክርስቲያኖች ዘወትር አጥብቀው የሚይዙት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃልና ይህን ቃል ማስተዋል እንዲችሉ የሚረዳቸው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈሳዊው ዘይት ልባሞቹ ቆነጃጅት ወደ ሠርጉ ድግስ በሚደረገው ጉዞ መብራታቸውን አብርተው ሙሽራውን እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል። ሰነፎቹ ቆነጃጅት ግን በውስጣቸው ማለትም በዕቃቸው ውስጥ አስፈላጊው መንፈሳዊ ዘይት የላቸውም። ስለዚህ ኢየሱስ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገለጸ:-
“[ሰነፎቹ ቆነጃጅት ዘይት] ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፣ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፣ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና:- ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ:- እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም አለ።”
ክርስቶስ ወደ ሰማያዊ መንግሥቱ በመጣ ጊዜ የልባሞቹ ቆነጃጅት ክፍል የሆኑት እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተመልሶ ለመጣው ሙሽራ ክብር በዚህ በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን የማብራት ልዩ መብታቸውን ለመጠቀም ንቁዎች ሆነዋል። በሰነፎቹ ቆነጃጅት የተመሰሉት ግን ይህን ክብራማ አቀባበል ለማድረግ ዝግጁዎች አልነበሩም። ስለዚህ ጊዜው ሲደርስ ክርስቶስ ወደ ሰማያዊው ሠርግ የሚያስገባውን በር አይከፍትላቸውም። ከሌሎች ዓመፅ አድራጊዎች ጋር እንዲጠፉ ውጪ በዓለም የሌሊት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይተዋቸዋል። ኢየሱስ “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ሲል ደመደመ።
የመክሊቱ ምሳሌ
ኢየሱስ ከሦስቱ ተከታታይ ምሳሌዎች ውስጥ ሁለተኛውን ምሳሌ በመናገር ከሐዋርያቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እያደረገ ያለውን ውይይት ቀጠለ። ከጥቂት ቀናት በፊት በኢያሪኮ እያለ መንግሥቱ የሚመጣው ገና ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ለማመልከት የምናኑን ምሳሌ ተናግሮ ነበር። አሁን የተናገረው ምሳሌ በርከት ያሉ ተመሳሳይ የሆኑ ገጽታዎች ቢኖሩትም ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚገኝበት ጊዜ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች የሚገልጽ ነው። ምሳሌው ደቀ መዛሙርቱ በምድር ላይ ሳሉ “ንብረቱን” ለማሳደግ መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው።
ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምሳሌውን መናገር ጀመረ:- “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ [“ንብረቱን፣” የ1980 ትርጉም] እንደ ሰጣቸው [ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘው ሁኔታም] እንዲሁ ይሆናልና።” ወደ ሌላ አገር ማለትም ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት ለባሮቹ ማለትም ሰማያዊውን መንግሥት የመውረስ አጋጣሚ ላላቸው ደቀ መዛሙርቱ ንብረቱን የሰጠው ሰው ኢየሱስ ነው። ይህ ንብረት ቁሳዊ ነገር ሳይሆን ኢየሱስ ያዘጋጀውን ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት የሚያስችል የለማ እርሻ ያመለክታል።
ኢየሱስ ንብረቱን ለባሪያዎቹ በአደራ የሰጠው ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? የመንግሥቱን መልእክት እስከ ምድር ዳርቻዎች በመስበክ በለማው እርሻ ላይ መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ መመሪያ በመስጠት ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፣ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር . . . ሄደ።”
በዚህ መንገድ ስምንቱ መክሊት ማለትም የክርስቶስ ንብረት እንደ ባሪያዎቹ ችሎታ ወይም መንፈሳዊ አቅም ተከፋፈለ። ባሪያዎቹ የደቀ መዛሙርት ቡድኖችን ያመለክታሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምስት መክሊት የተቀበለው ቡድን ሐዋርያትን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ኢየሱስ በመቀጠል አምስትና ሁለት መክሊት የተቀበሉት ባሪያዎች ሁለቱም በመንግሥቱ የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራቸው መክሊቶቹን እጥፍ አደረጓቸው። አንድ መክሊት የተቀበለው ባሪያ ግን መክሊቱን መሬት ውስጥ ደበቀው።
ኢየሱስ በመቀጠል “ከብዙ ጊዜ በኋላ የነዚያ አገልጋዮች ጌታ መጣና ከአገልጋዮቹ ጋር መተሳሰብ ጀመረ” ሲል ተናገረ። (የ1980 ትርጉም) ክርስቶስ ከባሪያዎቹ ጋር ለመተሳሰብ ተመልሶ የመጣው ከ1,900 ዓመታት በኋላ በ20ኛው መቶ ዘመን ላይ በመሆኑ በእርግጥም የተመለሰው “ከብዙ ጊዜ በኋላ” ነው። ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:-
“አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ:- ጌታ ሆይ፣ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ፣ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም:- መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።” በተመሳሳይም ሁለት መክሊት የተቀበለው ባሪያ መክሊቱን እጥፍ አድርጎ በማትረፉ ተመሳሳይ የሆነ ምስጋናና ወሮታ አገኘ።
ይሁን እንጂ እነዚህ ታማኝ ባሪያዎች ወደ ጌታቸው ደስታ የሚገቡት እንዴት ነው? የጌታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ ወደ ሌላ አገር ማለትም አባቱ ወደሚገኝበት ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ መንግሥቱን በባለቤትነት መረከቡ ነው። በዘመናችን ያሉት ታማኝ ባሪያዎች እምነት ተጥሎባቸው ተጨማሪ የመንግሥቱን ኃላፊነቶች በመቀበላቸው ታላቅ ደስታ አግኝተዋል፤ ምድራዊ ሕይወታቸውን ሲጨርሱም ከሞት ተነሥተው ሰማያዊውን መንግሥት በመውረስ የመጨረሻውን ደስታ ያገኛሉ። ይሁን እንጂ ሦስተኛው ባሪያስ?
ይህ ባሪያ “ጌታ ሆይ፣ . . . ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ” ሲል ተቃውሞውን ገለጸ። “ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፣ መክሊትህ አለህ።” ባሪያው በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ በለማው እርሻ ላይ ለመሥራት ሆን ብሎ አሻፈረኝ ብሏል። ስለዚህ ጌታው “ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ” አለው፤ ከዚያም የሚከተለውን ፍርድ በየነበት:- “መክሊቱን ውሰዱበት . . . የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” የዚህ ክፉ ባሪያ ክፍል አባላት ወደ ውጭ ስለተጣሉ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ደስታ የላቸውም።
ይህ የክርስቶስ ተከታዮች ነን ለሚሉ ሁሉ ከበድ ያለ ትምህርት ያስተላልፋል። የእሱን ምስጋናና ወሮታ እንዲያገኙና ውጭ ወዳለው ጨለማ ተወርውረው ለአንዴና ለመጨረሻ እንዳይጠፉ ከፈለጉ በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ በመካፈል የሰማያዊ ጌታቸው ንብረት እንዲጨምር መሥራት አለባቸው። በዚህ ረገድ ትጉህ ነህን?
ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚመጣበት ጊዜ
ኢየሱስ አሁንም ያለው ከሐዋርያቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው። ስለ መገኘቱና ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት እንዲሰጣቸው ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ በመስጠት አሁን ከሦስቱ ተከታታይ ምሳሌዎች የመጨረሻውን ተናገረ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምሳሌውን መናገር ጀመረ:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል።”
ኢየሱስ የሚመጣው የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በጣም በሚቃረብበት ጊዜ ላይ ነው። የሚመጣው ግን ለምን ዓላማ ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።”
ኢየሱስ ሞገሱን ወዳገኙበት ጎን የተለዩት ሰዎች ስለሚያጋጥማቸው ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል:- እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” በዚህ ምሳሌ ላይ የተገለጹት በጎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ አይገዙም፤ ከዚህ ይልቅ የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዥዎች በመሆን መንግሥቱን ይወርሳሉ። ‘ዓለም የተፈጠረው’ አዳምና ሔዋን አምላክ የሰውን ዘር ለመቤዠት ባዘጋጀው ዝግጅት መጠቀም የሚችሉ ልጆችን መውለድ በጀመሩበት ጊዜ ነው።
ይሁን እንጂ በጎቹ የንጉሡን ሞገስ ወዳገኙበት ወደ ቀኝ ጎኑ የተለዩት ለምንድን ነው? ንጉሡ “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣” ሲል ተናገረ፤ “ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።”
በጎቹ ያሉት ምድር ላይ ስለሆነ እነዚህን መልካም ነገሮች ለሰማያዊ ንጉሣቸው ሊያደርጉ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ፈለጉ። “ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ?” ሲሉ ጠየቁት፤ “ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?”
ንጉሡም “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” ሲል መለሰላቸው። የክርስቶስ ወንድሞች የተባሉት ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙ በዚህ ምድር ላይ ያሉ የ144,000 ቀሪዎች ናቸው። ኢየሱስ ለእነርሱ ጥሩ ነገር ማድረግ ለእሱ ጥሩ ነገር እንደማድረግ የሚቆጠር መሆኑን ተናግሯል።
ከዚህ በመቀጠል ንጉሡ ፍየሎቹን እንዲህ አላቸው:- “እናንተ ርጉማን፣ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፣ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና።”
ይሁን እንጂ ፍየሎቹ እንዲህ ሲሉ አቤቱታቸውን አቀረቡ:- “ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም?” በጎቹ ጥሩ ፍርድ እንዲፈረድላቸውና ፍየሎቹ ደግሞ መጥፎ ፍርድ እንዲፈረድባቸው ያደረገው ነገር አንድ ነው። ኢየሱስ “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ [ወንድሞቼ] ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” በማለት መልሱን ሰጥቷል።
ስለዚህ ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት በታላቁ መከራ ከመጥፋቱ በፊት ያለው ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ የሚገኝበት ጊዜ የፍርድ ወቅትንም የሚጨምር ይሆናል። ፍየሎቹ “ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን [በጎቹ] ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” ማቴዎስ 24:2 እስከ 25:46፤ 13:40, 49፤ ማርቆስ 13:3-37፤ ሉቃስ 21:7-36፤ 19:43, 44፤ 17:20-30፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 14:1-3
▪ ሐዋርያቱ ጥያቄ እንዲያነሱ የገፋፋቸው ምን ነበር? ሆኖም ምን ሌላ ተጨማሪ ነገር በአእምሯቸው ሳይዙ አይቀርም?
▪ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የተፈጸመው የትኛው የኢየሱስ ትንቢት ክፍል ነው? በዚያ ጊዜ ያልተፈጸመውስ ነገር የትኛው ነው?
▪ የኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነበር? ሆኖም ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?
▪ ርኩሰቱ በመጀመሪያውና በመጨረሻው ፍጻሜ ላይ የሚያመለክተው ማንን ነው?
▪ ታላቁ መከራ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ የመጨረሻ ፍጻሜውን ያላገኘው ለምንድን ነው?
▪ የክርስቶስን መገኘት የሚያመለክቱት የትኞቹ የዓለም ሁኔታዎች ናቸው?
▪ ‘የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ የሚሉት’ መቼ ነው? ሆኖም በዚያን ጊዜ የክርስቶስ ተከታዮች ምን ያደርጋሉ?
▪ ኢየሱስ የወደፊቶቹ ደቀ መዛሙርቱ መጨረሻው ሲቀርብ ማስተዋል እንዲችሉ ለመርዳት ምን ምሳሌ ሰጠ?
▪ ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጥቷል?
▪ በአሥሩ ቆነጃጅት የተመሰሉት እነማን ናቸው?
▪ የክርስቲያን ጉባኤ ለሙሽራው የታጨችው መቼ ነው? ሆኖም ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደ ሠርጉ ድግስ ለመውሰድ የመጣው መቼ ነው?
▪ ዘይቱ ምን ያመለክታል? ልባሞቹ ቆነጃጅት ዘይቱን መያዛቸው ምን ለማድረግ ያስችላቸዋል?
▪ የሠርጉ ድግስ የሚካሄደው የት ነው?
▪ ሰነፎቹ ቆነጃጅት ምን ታላቅ ሽልማት አጥተዋል? የመጨረሻ ዕጣቸውስ ምንድን ነው?
▪ የመክሊቱ ምሳሌ ምን ትምህርት ያስተላልፋል?
▪ ባሪያዎቹ እነማን ናቸው? በአደራ የተሰጣቸው ንብረትስ ምንድን ነው?
▪ ጌታው ሒሳቡን ለመተሳሰብ የመጣው መቼ ነው? ያገኘውስ ነገር ምን ነበር?
▪ ታማኞቹ ባሪያዎች የገቡት ወደ የትኛው ደስታ ነው? ክፉ የሆነው ሦስተኛው ባሪያስ ምን ደረሰበት?
▪ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት ዘመን ምን የፍርድ ሥራ ያከናውናል?
▪ በጎቹ መንግሥቱን የሚወርሱት በምን መንገድ ነው?
▪ ‘ዓለም የተፈጠረው’ መቼ ነው?
▪ ሰዎች በጎች ወይም ፍየሎች ተብለው የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ነው?
-
-
ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 112
ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበ
ኒሳን 11 ማክሰኞ እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለሐዋርያቱ ሲሰጥ የነበረውን ትምህርት ጨረሰ። እንዴት ያለ ሥራ የበዛበትና አድካሚ ዕለት ነበር! አሁን፣ ምናልባትም በቢታንያ ለማደር ወደዚያ እየተመለሱ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ [“የማለፍ በዓል፣” NW] እንዲሆን ታውቃላችሁ፣ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።
-