የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አምላክ ስለ አንተ ያስባል?
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

      አምላክ ከቁም ነገር ይቆጥርሃል?

      “እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል።”a​—እስራኤላዊው ዳዊት፣ 11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.

      አንዲት ጠብታ ውኃ ከባልዲ ውስጥ ስትወርድ

      ብሔራት በሙሉ “ከአንድ የውሃ ጠብታ ያነሱ ናቸው።”—ኢሳይያስ 40:15

      ዳዊት፣ አምላክ ስለ እሱ እንዲያስብ መጠበቁ ምክንያታዊ ነበር? አምላክ ለአንተስ ያስብልሃል? ብዙዎች፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እነሱን ከቁም ነገር እንደሚቆጥራቸው ለማመን ይቸገራሉ። ለምን?

      አንዱ ምክንያት አምላክ ከሰዎች እጅግ በጣም ከፍ ያለ በመሆኑ ነው። አምላክ ከሰው ልጆች በጣም የላቀ በመሆኑ ብሔራት በሙሉ ከእሱ አንጻር ሲታዩ “ከአንድ የውሃ ጠብታ ያነሱ ናቸው፤ . . . ምንም ክብደት እንደሌላቸው እንደ ትቢያ የቀለሉ ናቸው።” (ኢሳይያስ 40:15 የ1980 ትርጉም) በዘመናችን ያለ በአምላክ የማያምን አንድ ጸሐፊ “ለአንተም ሆነ ለምታደርገው ነገር ሁልጊዜ ትኩረት የሚሰጥ መለኮታዊ አካል አለ ብሎ ማመን ከሁሉ የከፋ እብሪት ነው” እስከ ማለት ደርሷል።

      በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በሚያደርጓቸው ነገሮች የተነሳ የአምላክን ትኩረት ለማግኘት እንደማይበቁ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጂም የሚባል በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ሰላም እንዲኖረኝና ራሴን መግዛት እንድችል አዘውትሬ ብጸልይም ይዋል ይደር እንጂ የግልፍተኝነት ባሕርዬ ያገረሽብኛል። በመጨረሻም በጣም መጥፎ ሰው ስለሆንኩ አምላክ ሊረዳኝ አልቻለም ብዬ ደመደምኩ።”

      አምላክ ለሰው ልጆች ትኩረት መስጠት እስከማይችል ድረስ ከእኛ በጣም የራቀ ነው? ፍጹም ስላልሆኑት ፍጥረታቱ ምን ይሰማዋል? አምላክ ራሱ፣ ካልነገረን በስተቀር ማንኛውም የሰው ልጅ ስለ አምላክ ሆኖ መናገርም ሆነ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አይችልም። ይሁን እንጂ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለሰው ልጆች የሰጠው መልእክት ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ እሱ ከሰዎች የራቀና ለግለሰቦች ትኩረት የማይሰጥ አምላክ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” በማለት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) በቀጣዮቹ አራት ርዕሶች ላይ አምላክ ለግለሰቦች እንደሚያስብ የሚያሳዩ ሐሳቦችን እንመረምራለን፤ እንዲሁም እንደ አንተው ላሉ ሰዎች እንዲህ ያለውን አሳቢነት እንዴት እንዳሳየ እንመለከታለን።

      a መዝሙር 40:17

  • አምላክ ይመለከትሃል
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

      አምላክ ይመለከትሃል

      “[አምላክ] ዐይኖቹ የሰውን አካሄድ ይመለከታሉ፤ ርምጃውንም ሁሉ ይከታተላሉ።”—ኢዮብ 34:21

      አንድ አባት ከትንሽ ልጁ ጋር ሲጫወት

      አንድ ልጅ ዕድሜው ትንሽ በሆነ መጠን የወላጁ እንክብካቤ ይበልጥ ያስፈልገዋል

      አንዳንዶች የሚጠራጠሩበት ምክንያት፦ በቅርብ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት እኛ ያለንበት ጋላክሲ ብቻ ቢያንስ 100 ቢሊዮን ፕላኔቶች ይኖሩት ይሆናል። ጽንፈ ዓለም እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ አንጻር ብዙ ሰዎች ‘ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ በአንዲት ትንሽ ፕላኔት ላይ የምንኖር ከቁጥር የማንገባ ሰዎች የምናደርገውን ነገር የሚያይበት ምን ምክንያት ይኖራል?’ ብለው ይጠይቃሉ።

      የአምላክ ቃል ምን ያስተምራል? አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ከሰጠንም በኋላ ስለ እኛ ማሰቡን አልተወም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋa “እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—መዝሙር 32:8

      በ20ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረችን አጋር የምትባል አንዲት ግብፃዊት ሴት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አጋር ለአሠሪዋ ለሦራ አክብሮት ባለማሳየቷ ሦራ አዋረደቻት፤ በመሆኑም አጋር ወደ ምድረ በዳ ኮበለለች። ታዲያ አጋር ስህተት በመሥራቷ አምላክ ለእሷ ትኩረት መስጠቱን አቆመ? መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን . . . በምድረ በዳ አገኛት” በማለት ይነግረናል። መልአኩም አጋርን “እግዚአብሔር ችግርሽን ተመልክቶአል” በማለት አጽናናት። ከዚያም አጋር ይሖዋን “አንተ የምታይ አምላክ ነህ” (NW) አለችው።—ዘፍጥረት 16:4-13

      “የምታይ አምላክ ነህ” የተባለለት አምላክ አንተንም ይመለከትሃል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አንዲት አፍቃሪ እናት በተለይ ትናንሽ ልጆቿን በትኩረት ትከታተላቸዋለች፤ ምክንያቱም አንድ ልጅ ዕድሜው ትንሽ በሆነ መጠን የወላጁ እንክብካቤ ይበልጥ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይ እኛም ከቁጥር የማንገባና በቀላሉ የምንጎዳ በመሆናችን አምላክ ይበልጥ በዓይኖቹ ይከታተለናል። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።”—ኢሳይያስ 57:15

      ይሁን እንጂ ‘አምላክ እኔን የሚመለከተኝ እንዴት ነው? የሚመዝነኝ ከላይ በሚያየው ነገር ነው? ወይስ ከዚያ ባለፈ ውስጤን በመመልከት ማንነቴን ይረዳልኛል?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል።

      a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

  • አምላክ ስሜትህን ይረዳልሃል
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

      አምላክ ስሜትህን ይረዳልሃል

      “[“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ።”—መዝሙር 139:1

      ዲ ኤን ኤ እና ሽል

      “ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ።”—መዝሙር 139:16

      አንዳንዶች የሚጠራጠሩበት ምክንያት፦ ብዙዎች አምላክ የሰው ልጆችን የሚያየው እንደ ኃጢአተኞች ማለትም እንደረከሱና የእሱን ትኩረት ለማግኘት እንደማይበቁ አድርጎ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በመንፈስ ጭንቀት ትሠቃይ የነበረችው ኬንድራ የአምላክን መሥፈርቶች ፍጹም በሆነ ሁኔታ ማሟላት ስላልቻለች በጥፋተኝነት ስሜት ተውጣ ነበር። በዚህም የተነሳ “መጸለይ አቁሜ ነበር” ብላለች።

      የአምላክ ቃል ምን ያስተምራል? ይሖዋ ትኩረት የሚያደርገው በውስጣዊ ማንነትህ ላይ እንጂ ፍጹም ባለመሆንህ ላይ አይደለም። “እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከዚህም በላይ እኛን የሚይዘን “እንደ ኃጢአታችን” አይደለም፤ ንስሐ ስንገባም በምሕረት ይቅር ይለናል።—መዝሙር 103:10, 14

      ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች በመጀመሪያው ላይ የተጠቀሰውን የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንውሰድ። ዳዊት ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ . . . ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ። . . . እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ።” (መዝሙር 139:16, 23) አዎን፣ ዳዊት ከባድ ኃጢአት የሠራበት ጊዜ ቢኖርም ከተጸጸተ ይሖዋ የልቡን ሁኔታ መመልከት እንደሚችል እርግጠኛ ነበር።

      ይሖዋ ከማንም ሰው በላይ ጠንቅቆ ያውቅሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” ይላል። (1 ሳሙኤል 16:7) አምላክ በዘር የወረስከው ነገር፣ አስተዳደግህ፣ አካባቢህና የራስህ ባሕርይ አንድ ላይ ተዳምረው አንተነትህን እንዴት እንደቀረጹት ያውቃል። ስህተት ብትሠራም እንኳ ምን ዓይነት ሰው ለመሆን ጥረት እያደረግህ እንዳለህ ይመለከታል፤ እንዲሁም ጥረትህን ከፍ አድርጎ ያየዋል።

      ይሁንና አምላክ ስለ አንተ እውነተኛ ማንነት ያለውን ጥልቅ እውቀት አንተን ለማጽናናት የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

  • አምላክ ሊያጽናናህ ይችላል
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

      አምላክ ሊያጽናናህ ይችላል

      “ሐዘንተኞችን የሚያጽናናው አምላክ . . . እንድንጽናና አደረገን።”—2 ቆሮንቶስ 7:6

      A young woman reading her Bible

      ‘የአምላክ ልጅ ወድዶኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል።’—ገላትያ 2:20

      አንዳንዶች የሚጠራጠሩበት ምክንያት፦ አንዳንድ ሰዎች መጽናኛ ማግኘት በጣም በሚያስፈልጋቸው ጊዜም እንኳ አምላክ ጣልቃ ገብቶ ችግሮቻቸውን እንዲቋቋሙ እንዲረዳቸው መጠየቅ ራስ ወዳድነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ራኬል የምትባል አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “በዓለም ላይ ያለውን ሕዝብ ብዛት እንዲሁም የሚደርሱባቸውን ከባድ ችግሮች ስመለከት እኔን የሚያሳስቡኝ ችግሮች ከቁም ነገር የማይገቡ እንደሆኑ ስለሚሰማኝ የአምላክን እርዳታ ከመለመን ወደኋላ እላለሁ።”

      የአምላክ ቃል ምን ያስተምራል? አምላክ፣ የሰው ልጆችን ለመርዳትና ለማጽናናት አስደናቂ የሆነ እርምጃ ወስዷል። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለው ሰው ሁሉ ኃጢአትን ወርሷል፤ በመሆኑም የአምላክን መሥፈርቶች መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ማሟላት አንችልም። ይሁን እንጂ አምላክ “[ስለወደደን] ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮልናል። (1 ዮሐንስ 4:10) አምላክ በኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ፣ ንጹሕ ሕሊናና ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖረን አስችሎናል።a ይሁን እንጂ ይህ መሥዋዕት አምላክ በጥቅሉ ለመላው የሰው ዘር እንደሚያስብ የሚያሳይ ብቻ ነው? ወይስ ለአንተም በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ ያሳያል?

      ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ ባቀረበው መሥዋዕት ልቡ በጥልቅ ስለተነካ “የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 2:20) በእርግጥ ኢየሱስ የሞተው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ነበር። ሆኖም ጳውሎስ የኢየሱስን መሥዋዕት፣ አምላክ ለእሱ በግሉ የሰጠው ስጦታ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል።

      የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አምላክ ለአንተም በግልህ የሰጠህ ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ አንተ ለአምላክ ምን ያህል ውድ እንደሆንክ ያረጋግጣል። ስጦታው “ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ” ሊሰጥህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ “በመልካም ሥራና ቃል ሁሉ [ያጸናሃል]።”—2 ተሰሎንቄ 2:16, 17

      ሆኖም ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ ወደ 2,000 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ አምላክ በዛሬው ጊዜ ወደ አንተ መቅረብ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

      a ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።

  • አምላክ ወደ አንተ መቅረብ ይፈልጋል
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

      አምላክ ወደ አንተ መቅረብ ይፈልጋል

      “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።”—ዮሐንስ 6:44

      አንዳንዶች የሚጠራጠሩበት ምክንያት፦ በአምላክ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ወደ እሱ መቅረብ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ክሪስቲና የምትባል በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን የምትሄድ አንዲት አየርላንዳዊት እንዲህ ብላለች፦ “አምላክን የምመለከተው ሁሉንም ነገር እንደፈጠረ አካል አድርጌ ነው። ይሁን እንጂ ስለ እሱ የማውቀው ነገር አልነበረም። አንድም ቀን ወደ እሱ እንደቀረብኩ ተሰምቶኝ አያውቅም።”

      የአምላክ ቃል ምን ያስተምራል? ግራ ገብቶን በምንባዝንበት ጊዜ ይሖዋ እኛን ለመርዳት ጥረት ማድረጉን አይተውም። ኢየሱስ አምላክ ለእኛ ያለውን አሳቢነት በሚከተለው ምሳሌ ገልጾታል፦ “አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነሱ አንዷ ብትጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ አይሄድም?” ትምህርቱ ምንድን ነው? “በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱም እንዲጠፋ አይፈልግም።”—ማቴዎስ 18:12-14

      ‘እነዚህ ታናናሾቹ’ የተባሉት በሙሉ ለአምላክ እጅግ ውድ ናቸው። ታዲያ አምላክ “የጠፋችውን ለመፈለግ” የሚሄደው እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ያለው ጥቅስ እንደሚገልጸው ይሖዋ ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባል።

      በዛሬው ጊዜ ስለ አምላክ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ሰዎች ቤት እየሄዱም ሆነ በአደባባይ የሚሰብኩት እነማን ናቸው?

      አምላክ ቅን የሆኑ ሰዎችን ወደ ራሱ ለመሳብ ቀዳሚ ሆኖ እርምጃ የወሰደው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አምላክ፣ ፊልጶስ የተባለውን ክርስቲያን ወደ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ልኮት ነበር፤ ፊልጶስ የባለሥልጣኑ ሠረገላ ላይ ሮጦ ከደረሰ በኋላ ባለሥልጣኑ ሲያነበው ስለነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ትርጉም አወያየው። (የሐዋርያት ሥራ 8:26-39) ከጊዜ በኋላም አምላክ፣ እየጸለየና እሱን ለማምለክ ጥረት እያደረገ ወደነበረ ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሮማዊ መኮንን ቤት እንዲሄድ ሐዋርያው ጴጥሮስን አዝዞታል። (የሐዋርያት ሥራ 10:1-48) በተጨማሪም አምላክ ሐዋርያው ጳውሎስንና ጓደኞቹን ከፊልጵስዩስ ከተማ ውጭ ወደሚገኝ አንድ ወንዝ እንዲሄዱ መርቷቸዋል። እዚያም ሊዲያ የምትባል “አምላክን የምታመልክ” ሴት ያገኙ ሲሆን “ይሖዋም ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል እንድትሰማ ልቧን በደንብ ከፈተላት።”—የሐዋርያት ሥራ 16:9-15

      ከላይ ከተጠቀሱት ታሪኮች ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ እሱን ሲፈልጉ የነበሩት ሰዎች እሱን የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጓል። በዛሬው ጊዜስ ስለ አምላክ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ሰዎች ቤት እየሄዱም ሆነ በአደባባይ የሚሰብኩት እነማን ናቸው? ብዙዎች “የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው” ብለው መልስ ይሰጣሉ። አንተም ‘አምላክ ወደ እኔ ለመቅረብ እነዚህን ሰዎች እየተጠቀመባቸው ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። አምላክ አንተን ወደ ራሱ ለመሳብ ለሚያደርገው ጥረት ቀና ምላሽ ለመስጠት እንዲረዳህ በጸሎት እንድትጠይቀው እንመክርሃለን።a

      a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት www.pr2711.com/am በተባለው ድረ ገጻችን ላይ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተሰኘውን ቪዲዮ ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ