-
አምላክን እንደምትቀርበው ይሰማሃል?መጠበቂያ ግንብ—2014 | ታኅሣሥ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ
አምላክን እንደምትቀርበው ይሰማሃል?
“ከአምላክ ጋር መቀራረብ የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርብህ ያደርጋል። አምላክ ምንጊዜም አንተን የሚጠቅም ነገር እንደሚያደርግ ይሰማሃል።”—ክሪስቶፈር፣ በጋና የሚኖር ወጣት
“በምታዝንበት ጊዜ አምላክ ይመለከትሃል፤ ከዚያም ከምታስበው የበለጠ ፍቅርና ትኩረት ይሰጥሃል።”—የ13 ዓመቷ ሐና፣ አላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“የአምላክ የቅርብ ወዳጅ እንደሆንክ ማወቅ እጅግ በጣም ልዩና ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል!”—ጂና፣ በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ጃማይካዊት ሴት
እንዲህ የሚሰማቸው ክሪስቶፈር፣ ሐናና ጂና ብቻ አይደሉም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ እንደሚመለከታቸው እርግጠኞች ናቸው። አንተስ? ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳለህ ይሰማሃል? ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ ትፈልጋለህ? ምናልባትም እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘በእርግጥ አንድ ተራ ሰው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ይችላል? ከሆነ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?’
ወደ አምላክ መቅረብ ይቻላል
መጽሐፍ ቅዱስ፣ እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት እንደሚችል ይናገራል። አምላክ ዕብራዊ የእምነት አባት የነበረውን አብርሃምን “ወዳጄ” በማለት እንደጠራው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 41:8) እንዲሁም በያዕቆብ 4:8 ላይ የሚገኘውን “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚለውን አስደሳች ግብዣ ልብ በል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ወደ አምላክ መቅረብ ማለትም ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል። ይሁን እንጂ አምላክ አይታይም፤ ታዲያ ወደ እሱ ‘መቅረብ’ እና ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ ሰዎች ወዳጅነት የሚመሠርቱት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በአብዛኛው መጀመሪያ ላይ ሁለቱም ሰዎች ስማቸውን ይተዋወቃሉ። አዘውትረው የሚነጋገሩ እንዲሁም ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አንዳቸው ለሌላው የሚያካፍሉ ከሆነ ጓደኝነታቸው ይጠናከራል። አንዳቸው ለሌላው ጥሩ ነገር ሲያደርጉ ደግሞ ወዳጅነታቸው እየጠበቀ ይሄዳል። ከአምላክ ጋር ዝምድና የምንመሠርተውም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
-
-
የአምላክን ስም ታውቀዋለህ? በስሙስ ትጠቀማለህ?መጠበቂያ ግንብ—2014 | ታኅሣሥ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ
የአምላክን ስም ታውቀዋለህ? በስሙስ ትጠቀማለህ?
ስሙን የማታውቀው የቅርብ ጓደኛ ሊኖርህ ይችላል? ሊኖርህ እንደማይችል የታወቀ ነው። ኢሪና የምትባል በቡልጋሪያ የምትኖር አንዲት ሴት እንዳለችው “የአምላክን ስም ሳታውቅ ወደ እሱ መቅረብ አትችልም።” ደስ የሚለው ነገር ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው አምላክ ወደ እሱ እንድትቀርብ ይፈልጋል። በመሆኑም አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” በማለት ራሱን አስተዋውቆሃል።—ኢሳይያስ 42:8 NW
አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” በማለት ራሱን አስተዋውቆሃል።—ኢሳይያስ 42:8 NW
ይሖዋ የሚለውን ስም ማወቅህና በስሙ መጠቀምህ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የአምላክ ስም የሚጻፍባቸው ቴትራግራማተን ተብለው የሚጠሩት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ ላይ 7,000 ጊዜ ገደማ ይገኛሉ። የዚህን ስም ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ሌላ ስም የለም። ይህ በእርግጥም ይሖዋ ስሙን እንድናውቅና እንድንጠቀምበት እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው።a
ብዙውን ጊዜ ሁለት ሰዎች ጓደኝነት የሚጀምሩት ስም በመተዋወቅ ነው። አንተስ የአምላክን ስም ታውቀዋለህ?
ይሁንና አንዳንዶች፣ አምላክ ቅዱስና ሁሉን ቻይ ስለሆነ የእሱን ስም መጥራታችን ክብሩን ዝቅ እንደሚያደርግበት ይሰማቸዋል። እርግጥ ነው፣ የቅርብ ጓደኛህን ስም አላግባብ እንደማታነሳ ሁሉ የአምላክንም ስም ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥራት አይኖርብህም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እሱን የሚወዱ ሰዎች ስሙን እንዲያከብሩና እንዲያሳውቁለት ይፈልጋል። (መዝሙር 69:30, 31፤ 96:2, 8) ኢየሱስ፣ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን ማስተማሩን አስታውስ። እኛም የአምላክን ስም ለሌሎች የምናሳውቅ ከሆነ ስሙ እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እንዲህ ማድረጋችን ከእሱ ጋር ይበልጥ ያቀራርበናል።—ማቴዎስ 6:9
አምላክ “ስሙን ለሚያከብሩ” ሰዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሚልክያስ 3:16) እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን በተመለከተ ይሖዋ እንዲህ የሚል ቃል ገብቷል፦ “ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ።” (መዝሙር 91:14, 15) ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ከፈለግን ስሙን ማወቃችንና በስሙ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ ነው።
a የአምላክ ስም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን እየተባለ በሚጠራው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፤ የሚያሳዝነው ግን ይህ ስም ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል። ተርጓሚዎቹ የአምላክን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ መጠሪያዎች ተክተውታል። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 195-197 ተመልከት።
-
-
ከአምላክ ጋር ትነጋገራለህ?መጠበቂያ ግንብ—2014 | ታኅሣሥ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ
ከአምላክ ጋር ትነጋገራለህ?
የቅርብ ጓደኛሞች በአካል ተገናኝተው፣ በስልክ፣ በኢ-ሜይል፣ በቪዲዮም ይሁን በደብዳቤ አማካኝነት አዘውትረው ለመነጋገር ጥረት ያደርጋሉ። ወደ አምላክ ለመቅረብም ከእሱ ጋር አዘውትረን መነጋገር ያስፈልገናል። ይሁንና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ሐሳባችንን ለይሖዋ መንገር የምንችለው በጸሎት አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ አምላክን የምናነጋግረው እኩያችንን በምናነጋግርበት መንገድ አይደለም። በምንጸልይበት ጊዜ እያናገርን ያለነው የአጽናፈ ዓለም ልዑል የሆነውን ፈጣሪ እንደሆነ መገንዘብ አለብን። ይህም ጸሎታችንን ጥልቅ አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንድናቀርብ ሊያነሳሳን ይገባል። አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ አንዳንድ መሥፈርቶችም አሉ። ከእነዚህ መሥፈርቶች መካከል ሦስቱን እንመልከት።
አንደኛ፣ ጸሎት መቅረብ ያለበት ለይሖዋ ብቻ ነው፤ ለኢየሱስ፣ ቅዱሳን ተብለው ለሚጠሩ አካላት ወይም ለምስሎች ጸሎት ማቅረብ የለብንም። (ዘፀአት 20:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 4:6) ሁለተኛ፣ ጸሎታችን መቅረብ ያለበት የአምላክ ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ኢየሱስ ራሱ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ገልጿል። (ዮሐንስ 14:6) ሦስተኛ፣ ጸሎታችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” የሚል ሐሳብ ይዟል።a—1 ዮሐንስ 5:14
የሚቀራረቡ ጓደኛሞች በተቻለ መጠን አዘውትረው እርስ በርስ ይነጋገራሉ
እርግጥ ነው፣ ሁልጊዜ ሐሳቡን የሚገልጸው አንደኛው ወገን ብቻ ከሆነ ወዳጅነቱ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ጓደኛሞች እርስ በርስ መነጋገር እንዳለባቸው ሁሉ እኛም አምላክ እንዲያነጋግረን መፍቀድና እሱ ሲናገር ማዳመጥ ይኖርብናል። አምላክ ለእኛ የሚናገረው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?
በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አምላክ ለእኛ “የሚናገረው” በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ከቅርብ ጓደኛህ የተላከ አንድ ደብዳቤ ደረሰህ እንበል። ደብዳቤውን ካነበብክ በኋላ “ጓደኛዬ እኮ እንዲህ አለኝ!” ብለህ በደስታ ለሌሎች ትናገር ይሆናል። ሆኖም ጓደኛህ የነገረህ በአፉ ሳይሆን በጽሑፍ ነው። በተመሳሳይም አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ይሖዋ እንዲያናግርህ እየፈቀድክለት ነው ማለት ነው። በመሆኑም በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ጂና “አምላክ ወዳጁ አድርጎ እንዲመለከተኝ ከፈለግሁ ለእኛ የላከልንን ‘ደብዳቤ’ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብላለች። አክላም “መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ ወደ አምላክ ይበልጥ እንድቀርብ አድርጎኛል” በማለት ተናግራለች። ታዲያ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ ይሖዋ እንዲያናግርህ ትፈቅድለታለህ? እንዲህ ማድረግህ የአምላክ ወዳጅ እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደርጋል።
a በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት።
-
-
አምላክ የሚጠይቅህን ነገር ታደርጋለህ?መጠበቂያ ግንብ—2014 | ታኅሣሥ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ
አምላክ የሚጠይቅህን ነገር ታደርጋለህ?
“የፈለግከውን ጠይቀኝ፤ ምንም ቢሆን አደርግልሃለሁ።” ጨርሶ ለማታውቀው ወይም ከሰላምታ ያለፈ ትውውቅ ለሌለህ ሰው እንዲህ ብለህ እንደማትናገር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በጣም ለምትወደው ጓደኛህ እንዲህ ብለህ መናገር ላይከብድህ ይችላል። የሚቀራረቡ ጓደኛሞች አንዳቸው ሌላኛው የጠየቃቸውን ነገር ለመፈጸም ፈቃደኞች ናቸው።
ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያስደስታቸውን ነገር ዘወትር እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና የነበረው ንጉሥ ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም” ብሏል። (መዝሙር 40:5) ከዚህም በላይ ይሖዋ እሱን ለማያውቁትም ጭምር ‘የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባቸውን በደስታ በመሙላት’ የሚያስደስታቸውን ነገር ያደርጋል።—የሐዋርያት ሥራ 14:17
የምንወዳቸውና የምናከብራቸው ሰዎች የሚፈልጓቸውን ነገሮች ማድረግ ያስደስተናል
ይሖዋ ሌሎችን የሚያስደስት ነገር ለማድረግ ይፈልጋል፤ በመሆኑም የእሱ ወዳጆች መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ‘ልቡን ደስ የሚያሰኙ’ ነገሮችን እንዲያደርጉ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። (ምሳሌ 27:11) ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ ምክንያቱም አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታል” በማለት መልስ ይሰጣል። (ዕብራውያን 13:16) ታዲያ ይሖዋን ለማስደሰት መልካም ማድረግና ያለንን ነገር ለሌሎች ማካፈል ብቻውን በቂ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 11:6) አብርሃም “የይሖዋ ወዳጅ” ተብሎ የተጠራው ‘በይሖዋ ካመነ’ በኋላ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል። (ያዕቆብ 2:23) ኢየሱስ ክርስቶስም የአምላክን በረከት እንድናገኝ ከተፈለገ ‘በአምላክ እንደምናምን በተግባር ማሳየት’ አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 14:1) ታዲያ አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ከሚመለከታቸው ሰዎች የሚፈልገውን ዓይነት እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ማጥናት ይኖርብሃል። እንዲህ ስታደርግ ስለ አምላክ ፈቃድ “ትክክለኛ እውቀት” ይኖርሃል፤ ይህም ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድታውቅ ያስችልሃል። ስለ ይሖዋ ያለህ ትክክለኛ እውቀት ሲጨምርና ጽድቅ ስለሆኑት መሥፈርቶቹ ያወቅኸውን ነገር ተግባራዊ ስታደርግ በእሱ ላይ ያለህ እምነት እየጠነከረ ይሄዳል፤ እሱም ይበልጥ ወደ አንተ ይቀርባል።—ቆላስይስ 1:9, 10
-
-
ከዚህ የሚበልጥ አስደሳች ሕይወት የለምመጠበቂያ ግንብ—2014 | ታኅሣሥ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ
ከዚህ የሚበልጥ አስደሳች ሕይወት የለም
ወደ አምላክ ለመቅረብ ምን ማድረግ ትችላለህ? ልታደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችን ከዚህ በፊት ባሉት ርዕሶች ላይ ተመልክተናል፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦
ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ማወቅና በዚህ ስም መጠቀም
በመጸለይና መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ከአምላክ ጋር አዘውትረህ መነጋገር
ምንጊዜም ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ማድረግ
የአምላክን ስም በመጠቀም፣ ወደ እሱ በመጸለይ፣ ቃሉን በማጥናትና እሱን የሚያስደስተውን ነገር በማድረግ ወደ አምላክ ቅረብ
የአምላክን ስም በመጠቀም፣ ወደ እሱ በመጸለይ፣ ቃሉን በማጥናትና እሱን የሚያስደስተውን ነገር በማድረግ ወደ አምላክ ቅረብ
ከእነዚህ መሥፈርቶች አንጻር ራስህን ስትመለከተው ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስፈልገውን ነገር እያደረግህ እንደሆነ ይሰማሃል? ማሻሻል እንዳለብህ የሚሰማህ ነገር አለ? ይህን ማድረግ ጥረት እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው፤ ይሁን እንጂ የሚያስገኘውን ውጤት ተመልከት።
በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ጄኒፈር እንዲህ ብላለች፦ “ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ምንም ዓይነት ጥረት ቢደረግ አያስቆጭም። ይህ ዝምድና ብዙ በረከቶችን ያስገኛል፤ ይኸውም በአምላክ ይበልጥ እንድትተማመኑና ስለ ማንነቱ የበለጠ እንድታውቁ ያስችላችኋል፤ ከሁሉ በላይ ግን ለአምላክ ያላችሁ ፍቅር ያድጋል። ከዚህ የሚበልጥ አስደሳች ሕይወት የለም!”
የአምላክ ወዳጅ መሆን የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ያለክፍያ መማር የምትችልበትን ዝግጅት ሊያደርጉልህ ይችላሉ። በተጨማሪም በአካባቢህ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚካሄደው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን፤ በስብሰባው ላይ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከፍ አድርገው ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር መቀራረብ የምትችልበት አጋጣሚ ታገኛለህ።a እንዲህ ካደረግህ አንተም “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት የተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ይኖርሃል።—መዝሙር 73:28
a የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስተምሩህ ወይም በአቅራቢያህ የመሰብሰቢያ አዳራሻቸው የት እንደሚገኝ ማወቅ ከፈለግህ ይህን መጽሔት ያመጣልህን የይሖዋ ምሥክር አነጋግር፤ አሊያም www.pr2711.com/am የተሰኘውን ድረ ገጻችንን ተመልከት፤ በድረ ገጹ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን ከእኛ ጋር ለመገናኘት የሚለውን ተመልከት።
-