የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በእርግጥ ሰይጣን አለ?
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ኅዳር 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በእርግጥ ሰይጣን አለ?

      በእርግጥ ሰይጣን አለ?

      የወደቀውን መልአክ ሰይጣንን የሚያሳይ ሐውልት

      ሰይጣን ክፉና የወደቀ መልአክ መሆኑን የሚያሳይ በማድሪድ፣ ስፔን የሚገኝ ሐውልት

      የወደቀውን መልአክ ሰይጣንን የሚያሳይ ሐውልት

      ሰይጣን ክፉና የወደቀ መልአክ መሆኑን የሚያሳይ በማድሪድ፣ ስፔን የሚገኝ ሐውልት

      “በልጅነቴ እናቴ አልታዘዝ ስላት ‘ዲያብሎስ መጥቶ ይወስድሃል!’ ብላ ታስፈራራኝ ነበር። እኔም ‘ይምጣ! ማን ይፈራዋል?’ እላት ነበር። በአምላክ መኖር ባምንም ዲያብሎስ አለ ብዬ አላምንም ነበር።”—ሮሄሊዮ፣ ኤል ሳልቫዶር

      አንተስ በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ሐሳቦች መካከል ትክክል እንደሆነ የሚሰማህ የቱ ነው?

      • ሰይጣን በእውን ያለ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የክፋት ባሕርይ ነው።

      • ሰይጣን አለ፤ ይሁንና በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም።

      • ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳድር ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ነው።

      እነዚህ አመለካከቶች እያንዳንዳቸው በጣም ብዙ ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አሏቸው። ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ ያለህ አመለካከት የትኛውስ ቢሆን ለውጥ ያመጣል? አዎ፣ ለምሳሌ ሰይጣን የሚባል አካል ከሌለ እሱ እንዳለ የሚያምኑ ሰዎች ተታልለዋል ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን ቢኖርም በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ከሌለው ብዙ ሰዎች ከእሱ የሚጠነቀቁት አልፎ ተርፎም እሱን የሚፈሩት በከንቱ ነው ማለት ነው። ይሁን እንጂ ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልል መሠሪ ፍጡር ከሆነ አብዛኞቹ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ አደገኛ ነው።

      እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመርምር፦ ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው? ወይስ መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጡር? ሰይጣን መንፈሳዊ አካል ከሆነ ደግሞ ጉዳት ሊያደርስብህ ይችላል? ከሆነ ራስህን ከእሱ መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

  • ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ኅዳር 1
    • ሰይጣን ከሰማይ ሆኖ መከራ የደረሰበትን ኢዮብን ሲመለከት
      ሰይጣን ከሰማይ ሆኖ መከራ የደረሰበትን ኢዮብን ሲመለከት

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በእርግጥ ሰይጣን አለ?

      ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው?

      በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው ብሎ መደምደም ቀላል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል? ደግሞስ ሰይጣን ከኢየሱስ ክርስቶስና ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽ የለ? ሰይጣን እንዲህ ያደረገባቸውን ሁለት አጋጣሚዎች እንመልከት።

      ሰይጣን ከኢየሱስ ጋር ተነጋግሯል

      ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ዲያብሎስ ሦስት የተለያዩ ማባበያዎችን በማቅረብ ኢየሱስን ሊፈትነው ሞክሮ ነበር። በመጀመሪያ ሰይጣን፣ ኢየሱስ ረሃቡን ለማስታገሥ ሲል በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ አምላክ የሰጠውን ኃይል እንዲጠቀምበት ለመገፋፋት ጥረት አደረገ። ከዚያም ኢየሱስ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲል ሕይወቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር እንዲፈጽም ለማደፋፈር ሞከረ። በመጨረሻም ሰይጣን፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ ወድቆ ቢሰግድለት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው ነገረው። ኢየሱስ በሦስቱም ማባበያዎች አልተሸነፈም፤ ከዚህ ይልቅ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ምላሽ ሰጠ።—ማቴዎስ 4:1-11፤ ሉቃስ 4:1-13

      ታዲያ ኢየሱስ የተነጋገረው ከማን ጋር ነበር? በውስጡ ካለ የክፋት ባሕርይ ጋር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አስመልክቶ “እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ነው፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት የለበትም” ይላል። (ዕብራውያን 4:15) በተጨማሪም “እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም፤ ከአንደበቱም የማታለያ ቃል አልወጣም” በማለት ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 2:22) ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ እስከ መጨረሻው ፍጹም ሆኖ ቀጥሏል። በውስጡ ምንም ዓይነት የክፋት ባሕርይ እንዲኖር አልፈቀደም። ኢየሱስ የተነጋገረው በእውን ካለ አንድ አካል ጋር እንጂ በራሱ ውስጥ ከሚገኝ የክፋት ባሕርይ ጋር እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

      ሰይጣን ኢየሱስን እንዳነጋገረው የሚገልጸው ይህ ዘገባ ሰይጣን በእውን ያለ አካል መሆኑን የሚያሳይ ሌላም ማስረጃ ይዟል።

      • ዲያብሎስ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ቢያመልከው የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንደሚሰጠው ለኢየሱስ ቃል እንደገባለት አስታውስ። (ማቴዎስ 4:8, 9) ሰይጣን በእውን ያለ አካል ባይሆን ኖሮ ያቀረበው ግብዣ ምንም ትርጉም አይኖረውም ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሰይጣን እንዲህ ያለ ታላቅ ሥልጣን ያለው መሆኑን አላስተባበለም።

      • ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ ለቀረቡለት ማባበያዎች እንዳልተሸነፈ ሲያይ “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ።” (ሉቃስ 4:13) ታዲያ ይህ የሚያሳየው ሰይጣን የክፋት ባሕርይ መሆኑን ነው? ወይስ ተስፋ ቆርጦ የማይተው ክፉ ባለጋራ መሆኑን?

      • ዘገባው “መላእክትም [ኢየሱስን] መጥተው ያገለግሉት ጀመር” እንደሚል ልብ በል። (ማቴዎስ 4:11) ኢየሱስን እንዲያበረታቱትና እንዲረዱት የተላኩት እነዚህ መላእክት መንፈሳዊ አካል ያላቸው ፍጥረታት ናቸው? እንደሆኑ ግልጽ ነው። ታዲያ ሰይጣንስ መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጡር አይደለም የምንልበት ምን ምክንያት ይኖራል?

      ሰይጣን ከአምላክ ጋር ተነጋግሯል

      ፈሪሃ አምላክ ስለነበረው ስለ ኢዮብ ታሪክ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ሰይጣን ከአምላክ ጋር እንደተነጋገረ የሚገልጽ ሐሳብ እናገኛለን። ይህ ታሪክ ዲያብሎስና አምላክ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተነጋገሩ ይገልጻል። በሁለቱም አጋጣሚዎች አምላክ፣ ንጹሕ አቋሙን የማያጎድፍ ሰው እንደሆነ በመግለጽ ኢዮብን አመስግኖታል። ሰይጣን ግን ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለራሱ ጥቅም ሲል እንደሆነ ተናግሯል፤ በተዘዋዋሪ ሰይጣን፣ ኢዮብ ታማኝ የሆነው አምላክ በጥቅም ስለደለለው እንደሆነ መናገሩ ነው። ዲያብሎስ ይህን ሲል ‘ከአምላክ ይበልጥ ኢዮብን የማውቀው እኔ ነኝ’ ማለቱ ነበር። ይሖዋ፣ ሰይጣን የኢዮብን ንብረት፣ ልጆችና ሌላው ቀርቶ ጤንነቱንም ጭምር እንዲነጥቅ ፈቀደ።a ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ስለ ኢዮብ የተናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ ሰይጣን ደግሞ ሐሰተኛ መሆኑ በግልጽ ታየ። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ባለማጉደፉ አምላክ ባርኮታል።—ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7

      በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ይሖዋ እየተነጋገረ የነበረው በውስጡ ካለ የክፋት ባሕርይ ጋር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው” ይላል። (2 ሳሙኤል 22:31) በተጨማሪም የአምላክ ቃል “ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” ይላል። (ራእይ 4:8) ቅዱስ ማለት ንጹሕ ወይም ከኃጢአት የራቀ ማለት ነው። ይሖዋ ፍጹምና እንከን የለሽ ነው። ምንም ዓይነት የክፋት ባሕርይ ሊኖረው አይችልም።

      ሰይጣን ከአምላክ ጋር መነጋገሩ በኢዮብ ላይ ያስከተለው ውጤት አለ

      ያም ሆኖ አንዳንዶች፣ ኢዮብም እንኳ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው መሆኑን ይጠራጠራሉ፤ በመሆኑም አምላክና ሰይጣን እንደተነጋገሩ የሚገልጸው በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዘገባ ምሳሌያዊ ትርጉም የያዘ ሐሳብ ነው በማለት ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ ነው? ኢዮብ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው እንደሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በ⁠ያዕቆብ 5:7-11 ላይ ክርስቲያኖች መከራ ሲደርስባቸው እንዲጸኑ ለማበረታታትና ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ጽናት ለሚያሳዩ ሰዎች ወሮታ እንደሚከፍል ለማሳሰብ ኢዮብ እንደ ምሳሌ ተጠቅሷል። ኢዮብ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ካልሆነና በሰይጣን የተሰነዘረበት ጥቃትም የፈጠራ ታሪክ ብቻ ከሆነ እሱ እንደ ምሳሌ ተደርጎ መጠቀሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ከዚህም በላይ በ⁠ሕዝቅኤል 14:14, 20 ላይ ሦስቱ ጻድቃን ሰዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል አንዱ ኢዮብ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ኖኅና ዳንኤል ናቸው። እንደ ኖኅና እንደ ዳንኤል ሁሉ ኢዮብም በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ታላቅ የእምነት ሰው ነበር። ኢዮብ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ከሆነ ደግሞ በእሱ ላይ ጥቃት የሰነዘረበትና ስደት ያደረሰበትም በእውን ያለ አካል ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም?

      መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጡር አድርጎ እንደሚገልጸው ከዚህ መረዳት ይቻላል። ይሁንና ‘ሰይጣን በዚህ ዘመናዊ ዓለምም ጭምር በእኔና በቤተሰቤ ላይ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ወደ አእምሮህ ይመጣ ይሆናል።

      ሰይጣን በዚህ ዘመን ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል?

      የምትኖርበት ከተማ በድንገት በወንጀለኞች ተጥለቀለቀ እንበል። በዚህ የተነሳ የምትኖርበት አካባቢ ለደኅንነትህ አስጊ እንደሚሆን እንዲሁም የነዋሪዎቹ ሥነ ምግባር እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ግልጽ ነው። እስቲ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ ሌላ ሁኔታ እንመልከት፦ ሰይጣንና አጋንንቱ ማለትም እንደ እሱ በአምላክ ላይ ያመፁ መንፈሳዊ አካላት በድንገት በምድር አካባቢ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ተደረገ። ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? በአካባቢህም ሆነ በዓለም ዙሪያ በዜና ማሰራጫዎች ስለሚተላለፉት ነገሮች እስቲ ለማሰብ ሞክር።

      • በዓለም ዙሪያ ብዙ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በጭካኔ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እንደሆነ ልብ አላልክም?

      • ብዙ ወላጆች ጉዳዩ ቢያሳስባቸውም በመዝናኛው ዓለም መናፍስታዊ ነገሮች የሚታዩባቸው መዝናኛዎች እየበዙ እንደመጡ አላስተዋልክም?

      • ምድርን ከጥፋት ለመታደግ ብዙ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በምድራችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ እንደሆነ ልብ አላልክም?

      • መላውን የሰው ዘር ወደ ጥፋት እየገፋ ያለ አንድ ኃይል እንዳለ ተሰምቶህ አያውቅም?

      መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ችግሮች መንስኤው ማን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተወረወረ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ። . . . ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” (ራእይ 12:9, 12) ብዙ ሰዎች ማስረጃውን ከመረመሩ በኋላ፣ ሰይጣን በዓለም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ አደገኛ መንፈሳዊ አካል ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

      ከሰይጣን ጥቃት ጥበቃ ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያሳስብህ ይሆናል። ይህ ጉዳይ ቢያሳስብህ አያስገርምም። ቀጣዩ ርዕስ በዚህ ረገድ ምን ማድረግ እንደምትችል ይጠቁምሃል።

      a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

  • ሰይጣንን ልንፈራው ይገባል?
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ኅዳር 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በእርግጥ ሰይጣን አለ?

      ሰይጣንን ልንፈራው ይገባል?

      አንድ ባልና ሚስት ንጹሕ አየር ለማግኘት በጭስ ከታፈነው ቤታቸው ሮጠው ወደ ውጪ ሲወጡ

      እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ ሁሉ ሰይጣንም በዓይን የማይታይና አደገኛ ነው

      አንድ ባልና ሚስት ንጹሕ አየር ለማግኘት በጭስ ከታፈነው ቤታቸው ሮጠው ወደ ውጪ ሲወጡ

      እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ ሁሉ ሰይጣንም በዓይን የማይታይና አደገኛ ነው

      መኖር አለመኖሩን ማወቅ አዳጋች ነው። ቀለምም ሆነ ሽታ የለውም፤ በመሆኑም ብዙ ሰዎች ሳያውቁት ሰለባው ይሆናሉ። በመላው ዓለም በመመረዝ ምክንያት ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ምናልባትም ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ሞት ተጠያቂ ነው፤ ይህ አደገኛ ነገር ካርቦን ሞኖክሳይድ የተባለው ጋዝ ነው። ይሁን እንጂ መሸበር አይኖርብህም። ይህ ጋዝ መኖር አለመኖሩን ማወቅና ራስህን መጠበቅ የምትችልባቸው መንገዶች አሉ። ብዙ ሰዎች ይህ ጋዝ መኖሩን የሚጠቁም መቆጣጠሪያ ያስገጥማሉ፤ ከዚያም መቆጣጠሪያው የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሲያሰማ እርምጃ ይወስዳሉ።

      እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ ሁሉ ሰይጣንም በዓይን ስለማይታይ ተጽዕኖ እያደረገብን መሆን አለመሆኑን ማወቅ አዳጋች ሊሆንብን ይችላል፤ በመሆኑም ሰይጣን እጅግ አደገኛ ጠላት ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ሊረዳን ይችላል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አምላክ የሰጠህን ነገሮች የምትጠቀምባቸው ከሆነ ሰይጣንን የምትፈራበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

      የመምረጥ ነፃነት። ያዕቆብ 4:7 “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” በማለት ይነግረናል። ሰይጣን ከፍተኛ ኃይል ቢኖረውም እንኳ አንተ ማድረግ የማትፈልጋቸውን ነገሮች እንድታደርግ ሊያስገድድህ አይችልም። ምክንያቱም የመምረጥ ነፃነት አለህ። 1 ጴጥሮስ 5:9 “በእምነት ጸንታችሁ በመቆም [ዲያብሎስን] ተቃወሙት” ይላል። ኢየሱስ ሰይጣን ላቀረበለት ሦስት ማባበያዎች የማያወላውል መልስ እንደሰጠ አስታውስ፤ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ትቶት ሄደ። (ማቴዎስ 4:11) አንተም ከፈለግክ ሰይጣን የሚያመጣቸውን ፈተናዎች መቋቋም ትችላለህ።

      ከአምላክ ጋር መወዳጀት። ያዕቆብ 4:8 ‘ወደ አምላክ እንድንቀርብ’ ያበረታታናል። ይሖዋ የእሱ የቅርብ ወዳጅ እንድትሆን ጋብዞሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ከአምላክ ጋር ወዳጅ ለመሆን በመጀመሪያ ስለ እሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር አለብህ። (ዮሐንስ 17:3) ስለ ይሖዋ የምትማረው ነገር እሱን እንድትወደው ያደርግሃል፤ እሱን መውደድህ ደግሞ ፈቃዱን እንድታደርግ ያነሳሳሃል። (1 ዮሐንስ 5:3) በሰማይ ወዳለው አባትህ ይበልጥ እየቀረብክ ስትሄድ እሱስ ምን ያደርጋል? ያዕቆብ ‘እሱም ወደ አንተ ይቀርባል’ ብሏል።

      አንድ ሰው መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና፣ ከዚያ ወደ አምላክ ሲጸልይ፣ በመጨረሻም መናፍስታዊ ነገሮችን ሲያቃጥል

      ይሖዋ ከሰይጣን ጥቃት ጥበቃ የምታገኝባቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶችን አድርጎልሃል

      አንድ ሰው መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና፣ ከዚያ ወደ አምላክ ሲጸልይ፣ በመጨረሻም መናፍስታዊ ነገሮችን ሲያቃጥል

      ይሖዋ ከሰይጣን ጥቃት ጥበቃ የምታገኝባቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶችን አድርጎልሃል

      ጥበቃ እንደምናገኝ የተሰጠን ተስፋ። ምሳሌ 18:10 “[የይሖዋ] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” ይላል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ሲባል የአምላክ ስም ምትሃታዊ ኃይል አለው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ስም በጥልቅ የሚያከብሩ ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ይህን ስም በመጥራት ጥበቃ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው።

      በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ምሳሌዎች። ሥራ 19:19 በኤፌሶን የነበሩ ሰዎች ወደ ክርስትና ሲለወጡ ስላደረጉት አስገራሚ ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሁሉ ሰው ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ ሃምሳ ሺህ የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት።”a እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ዋጋቸው ምንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ አቃጥለዋል። እነሱ ከተዉት ምሳሌ በጣም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ይህ ዓለም በአስማትና በመናፍስታዊ ድርጊት ተሞልቷል። ምንም ጉዳት የሌላቸው የሚመስሉ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ግንኙነት ያላቸው ዕቃዎችና ልማዶች እንኳ ለአጋንንት ጥቃት ሊያጋልጡ ይችላሉ። በመሆኑም ምንም ዓይነት መሥዋዕት ቢያስከፍልህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማስወገድህ አስፈላጊ ነው።—ዘዳግም 18:10-12

      በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሮሄሊዮ 50 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ሰይጣን መኖሩን አያምንም ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አመለካከቱ ተቀየረ። ለምን? ሮሄሊዮ እንዲህ ብሏል፦ “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት እውቀት ዲያብሎስ መኖሩን አሳመነኝ። አሁንም ቢሆን በእሱ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳልወድቅ እየጠበቀኝ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን ማወቄ ነው።”

      “ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት እውቀት ዲያብሎስ መኖሩን አሳመነኝ። አሁንም ቢሆን በእሱ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳልወድቅ እየጠበቀኝ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን ማወቄ ነው”

      ሰይጣን የማይኖርበትን ጊዜ ለማየት ትጓጓለህ? ይህ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ብዙዎችን የሚያሳስተው ዲያብሎስ “ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ” የሚወረወርበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። (ራእይ 20:10) እርግጥ ነው፣ እሳትና ድኝ ቃል በቃል አንድን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር ሊጎዱ አይችሉም። በመሆኑም የእሳቱ ሐይቅ ዘላለማዊ ጥፋትን የሚያመለክት መሆን አለበት። አዎን፣ ሰይጣን ለዘላለም ይጠፋል። ያ ጊዜ ለአምላክ ወዳጆች በጣም የሚያስደስት ወቅት ይሆናል!

      እስከዚያው ድረስ ግን ስለ ይሖዋና ስለ ባሕርያቱ የቻልከውን ያህል መማርህን ቀጥል።b “ሰይጣን የለም!” ማለት በሚቻልበት ጊዜ በሕይወት መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ።

      a እዚህ ላይ የተጠቀሰው የብር ሳንቲም የሮማውያን ዲናር ከሆነ ይህ ገንዘብ ከ50,000 ሠራተኞች የቀን ደመወዝ ጋር የሚተካከል ነው፤ ይህ ደግሞ በጣም ብዙ ገንዘብ ነው!

      b ስለ ሰይጣን እንዲሁም አምላክ መናፍስታዊ ድርጊትን በተመለከተ ስላለው አመለካከት ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት። ይህን መጽሐፍ ለማግኘት አንድ የይሖዋ ምሥክር ጠይቅ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ