-
ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 1መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሰኔ 15
-
-
ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 1
“ስምህ ይቀደስ።”—ማቴ. 6:9
1. በማቴዎስ 6:9-13 ላይ የሚገኘውን ጸሎት በአገልግሎታችን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
ብዙ ሰዎች የጌታን ጸሎት በቃላቸው መድገም ይችላሉ። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር እንደሆነና በምድር ላይ አስደናቂ የሆኑ ለውጦችን እንደሚያመጣ ለሰዎች ለማስረዳት ብዙውን ጊዜ ይህን ጸሎት እንጠቅሳለን። አሊያም ደግሞ አምላክ የግል ስም እንዳለውና ይህ ስም መቀደስ ወይም ‘ብሩክ መሆን’ እንዳለበት ለማጉላት በጸሎቱ ላይ ያለውን የመጀመሪያ ልመና አውጥተን እናሳያቸው ይሆናል።—ማቴ. 6:9 የግርጌ ማስታወሻ
2. ኢየሱስ የጸሎት ናሙናውን ያስተማረን በጸለይን ቁጥር ቃል በቃል እንድንደግመው አስቦ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?
2 ኢየሱስ ይህን ጸሎት ያስተማረን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በርካታ ሰዎች እንደሚያደርጉት በጸለይን ቁጥር ቃል በቃል እንድንደግመው አስቦ ነው? በፍጹም። ኢየሱስ ይህን ናሙና ከማስተማሩ በፊት “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 6:7) ከጊዜ በኋላም ይህን ጸሎት በድጋሚ ሲያስተምር ለየት ያለ አገላለጽ ተጠቅሟል። (ሉቃስ 11:1-4) ኢየሱስ፣ ስለ የትኞቹ ነገሮች መለመን እንዳለብንና በጸሎታችን ላይ ቅድሚያ መስጠት የሚገባን ለምን ነገሮች እንደሆነ አስገንዝቦናል። ይህ ጸሎት፣ የጸሎት ናሙና ተብሎ የሚጠራውም ለዚህ ነው።
3. የጸሎት ናሙናውን ስንመረምር በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል እንችላለን?
3 በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን የጸሎት ናሙና አንድ በአንድ እንመረምራለን። ይህን ስናደርግ ‘ይህ ናሙና፣ የጸሎቴን ይዘት ለማሻሻል የሚረዳኝ እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከዚህ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖርኩ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ”
4. “አባታችን ሆይ” የሚለው አገላለጽ ምን ያስታውሰናል? ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ይሖዋን “አባት” ብለው መጥራት የሚችሉት ከምን አንጻር ነው?
4 በጸሎት ናሙናው ላይ “አባቴ ሆይ” ሳይሆን “አባታችን ሆይ” መባሉ እርስ በርስ ከልብ በሚዋደድ “የወንድማማች ማኅበር” ውስጥ እንደታቀፍን ያስታውሰናል። (1 ጴጥ. 2:17) ይህ እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸውና ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋን “አባት” ብለው የመጥራት ልዩ የሆነ መብት አላቸው። (ሮም 8:15-17) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ይሖዋን “አባት” ብለው መጥራት ይችላሉ። ይሖዋ ሕይወት ሰጪያቸው ከመሆኑም ሌላ ለሁሉም እውነተኛ አምላኪዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በፍቅር ተነሳስቶ ያቀርብላቸዋል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ፍጽምና ደረጃ ላይ ከደረሱና በመጨረሻው ፈተና ታማኝ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ “የአምላክ ልጆች” ተብለው ይጠራሉ።—ሮም 8:21፤ ራእይ 20:7, 8
5, 6. ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጡ የሚችሉት ግሩም ስጦታ ምንድን ነው? እያንዳንዱ ልጅ ይህን ስጦታ እንዴት ሊይዘው ይገባል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
5 ወላጆች ልጆቻቸውን መጸለይ ሲያስተምሯቸውና ይሖዋን እንደ አፍቃሪ ሰማያዊ አባታቸው አድርገው እንዲመለከቱት ሲረዷቸው ትልቅ ስጦታ እየሰጧቸው ነው። በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሴቶች ልጆቻችን ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ፣ ቤት እስካለሁ ድረስ ሁልጊዜ ማታ ማታ አብሬያቸው እጸልይ ነበር። ልጆቻችን፣ ምሽት ላይ በምናደርገው ጸሎት ላይ ምን እጠቅስ እንደነበር በትክክል እንደማያስታውሱ ብዙ ጊዜ ይነግሩኛል። ይሁንና በጸሎቱ ወቅት የነበረውን መንፈስ፣ ከአባታችን ከይሖዋ ጋር በጸሎት መነጋገር ቅዱስ ነገር መሆኑን ይገነዘቡ እንደነበር እንዲሁም የሚያድርባቸውን የመረጋጋትና የደኅንነት ስሜት ያስታውሳሉ። ልጆቻችን መጸለይ የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ፣ ለይሖዋ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ሲገልጹ ለመስማት ስል ጮክ ብለው እንዲጸልዩ አበረታታቸው ነበር። ይህም በልባቸው ውስጥ ያለው ነገር በተወሰነ መጠን ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶልኛል። ከዚያም ጸሎታቸው ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያስችሉ ከጸሎት ናሙናው ላይ የተወሰዱ አስፈላጊ ነጥቦችን እንዲያካትቱ በደግነት እረዳቸዋለሁ።”
6 የዚህ ወንድም ሴቶች ልጆች ግሩም መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸው የሚያስገርም አይደለም። በአሁኑ ወቅት አስደሳች ትዳር ያላቸው ሲሆን ከባሎቻቸው ጋር ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመሳተፍ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ነው። ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሊሰጧቸው ከሚችሉት ስጦታ ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር የቀረበና የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት ነው። እርግጥ ነው፣ ይህን ውድ ዝምድና ጠብቆ ማቆየት የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ነው። ይህ ደግሞ የአምላክን ስም መውደድን ማለትም ለስሙ ጥልቅ አክብሮት ማዳበርን ይጨምራል።—መዝ. 5:11, 12፤ 91:14
“ስምህ ይቀደስ”
7. የአምላክ ሕዝቦች ምን መብት አለን? ይህስ ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል?
7 የአምላክን የግል ስም ከማወቅም አልፈን “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” በመሆን በስሙ መጠራታችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው። (ሥራ 15:14፤ ኢሳ. 43:10) በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን “ስምህ ይቀደስ” ብለን እንለምነዋለን። እንዲህ ያለ ልመና ማቅረብህ፣ ቅዱስ የሆነውን የይሖዋን ስም የሚያስነቅፍ ነገር ላለመናገር ወይም ላለማድረግ እንዲረዳህ እሱን ለመጠየቅ ሊያነሳሳህ ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ ያላደረጉ ክርስቲያኖች መሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእናንተ ምክንያት የአምላክ ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” በማለት ጽፎላቸዋል።—ሮም 2:21-24
8, 9. የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ማድረጋቸው የሚያሳስባቸውን ክርስቲያኖች ይሖዋ እንዴት እንደሚባርክ የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።
8 የአምላክ ስም እንዲቀደስ ማድረግ እንፈልጋለን። በኖርዌይ የምትኖር አንዲት እህት ባሏ ሲሞት ከሁለት ዓመት ልጇ ጋር ብቻዋን ቀረች። “በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከባድ ወቅት ነበር” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ስሜታዊ ሆኜ ሚዛኔን እንዳልስት ይሖዋ ጥንካሬ እንዲሰጠኝ በየዕለቱ እንዲያውም በየሰዓቱ እጸልይ ነበር፤ ይህንንም የማደርገው ጥበብ የጎደለው ውሳኔ በመወሰኔ ወይም ታማኝነቴን በማጉደሌ ሰይጣን ይሖዋን የሚነቅፍበት ነገር እንዳያገኝ ስል ነው። የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ልጄም አባቱን በገነት እንዲያገኝ እመኛለሁ።”—ምሳሌ 27:11
9 ይሖዋ እንዲህ ላሉ ከራስ ወዳድነት ነፃ ለሆኑ ጸሎቶች ምላሽ ይሰጣል? በሚገባ። ይህች እህት አሳቢ ከሆኑ የእምነት ባልንጀሮቿ ጋር አዘውትራ ጊዜ በማሳለፏ ድጋፍ ማግኘት ችላለች። ከአምስት ዓመት በኋላ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አገባች። አሁን ልጇ 20 ዓመቱ ሲሆን የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ነው። “ባለቤቴ ልጄን ሳሳድግ ስላገዘኝ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች።
10. የአምላክ ስም ሙሉ በሙሉ እንዲቀደስ ምን ያስፈልጋል?
10 የአምላክ ስም ሙሉ በሙሉ እንዲቀደስና ከደረሰበት ነቀፋ ሁሉ ነፃ እንዲሆን ምን ያስፈልጋል? ይሖዋ የእሱን ሉዓላዊነት ሆን ብለው የሚቃወሙትን ሁሉ ማጥፋት ያስፈልገዋል። (ሕዝቅኤል 38:22, 23ን አንብብ።) ከዚያም የሰው ዘር ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ይደርሳል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ የይሖዋን ስም የሚያስቀድሱበትን ጊዜ ለማየት ምንኛ እንጓጓለን! በመጨረሻም አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል።—1 ቆሮ. 15:28
“መንግሥትህ ይምጣ”
11, 12. በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ማስተዋል አገኙ?
11 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ሐዋርያቱ “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ፣ የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀመርበትን ወቅት የሚያውቁበት ጊዜ እንዳልደረሰ የሚያሳይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ሊያከናውኑት በሚገባው አስፈላጊ ሥራ ይኸውም በስብከቱ ተልእኮ ላይ እንዲያተኩሩ ነገራቸው። (የሐዋርያት ሥራ 1:6-8ን አንብብ።) ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንዲጠባበቁ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። በመሆኑም ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች ይህ መንግሥት እንዲመጣ ሲጸልዩ ኖረዋል።
12 ኢየሱስ የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት ከሰማይ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ሲደርስ፣ ይሖዋ ነገሮች የሚከናወኑበትን ጊዜ እንዲያውቁ ሕዝቡን ረድቷቸዋል። በ1876 ቻርልስ ቴዝ ራስል የጻፈው አንድ ርዕስ ባይብል ኤግዛሚነር በተባለ መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር። “የአሕዛብ ዘመናት የሚያበቁት መቼ ነው?” የሚል ጭብጥ ያለው ይህ ርዕስ 1914 ልዩ ዓመት መሆኑን ጠቁሞ ነበር። በዳንኤል ትንቢት ላይ የተገለጹት “ሰባት ዘመናት” ኢየሱስ ከጠቀሳቸው “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በዚህ ርዕስ ላይ ተብራርቷል።a—ዳን. 4:16፤ ሉቃስ 21:24
13. በ1914 ምን ተከናወነ? ከዚያ ወዲህ በዓለም ላይ የተፈጸሙ ሁኔታዎችስ ምን ያረጋግጣሉ?
13 በ1914 በአውሮፓ በሚገኙ አገራት መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ ጦርነቱም በመስፋፋቱ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በ1918 ጦርነቱ ሲያበቃ ከባድ የምግብ እጥረት ተከሰተ፤ ቀጥሎም በጦርነቱ ከሞቱት የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች የጨረሰ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ተነሳ። በመሆኑም ኢየሱስ የምድር አዲሱ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን እንደሚጠቁም የሚያሳየው “ምልክት” መፈጸም ጀመረ። (ማቴ. 24:3-8፤ ሉቃስ 21:10, 11) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አክሊል የተሰጠው’ በ1914 መሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አለ። “እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።” (ራእይ 6:2) ኢየሱስ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ጦርነት በማወጅ ሰማይን ያጸዳ ሲሆን እነሱንም ወደ ምድር አካባቢ ወረወራቸው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጆች፣ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ እውነተኝነት እየተመለከቱ ነው።—ራእይ 12:7-12
14. (ሀ) አሁንም ቢሆን የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ምን የማድረግ መብት ተሰጥቶናል?
14 በራእይ 12:7-12 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ የአምላክ መንግሥት የተወለደበትና በሰው ልጆች ላይ አሁንም ድረስ ሥቃይ እያስከተሉ ያሉት ክንውኖች የጀመሩበት ወቅት ተመሳሳይ ጊዜ ላይ የዋለው ለምን እንደሆነ ያብራራል። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ፣ መግዛት የጀመረው በጠላቶቹ መካከል ነው። ኢየሱስ ድሉን እስኪያጠናቅቅና በምድር ላይ ያለውን ክፋት ጨርሶ እስኪያስወግድ ድረስ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያችንን እንቀጥላለን። እስከዚያው ግን አስገራሚ የሆነው ‘የምልክቱ’ ገጽታ ፍጻሜውን እንዲያገኝ የበኩላችንን በማድረግ ከጸሎታችን ጋር በሚስማማ መንገድ ልንኖር ይገባል። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴ. 24:14
“ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም”
15, 16. የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከምናቀርበው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
15 ከዛሬ 6,000 ዓመታት ገደማ በፊት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተፈጽሞ ነበር። ይሖዋ፣ ለሰዎች ሁሉን ነገር ካመቻቸላቸው በኋላ ሁኔታውን ተመልክቶ “እጅግ መልካም ነበር” ያለው ለዚህ ነው። (ዘፍ. 1:31) ይሁንና ሰይጣን ዓመፀ፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአምላክን ፈቃድ በምድር ላይ ያደረጉት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ነው። በዛሬው ጊዜ ግን ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከመጸለይ አልፈው ከዚህ ጸሎት ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት እያደረጉ ነው፤ በእርግጥም በዚህ ዘመን በመኖራችን ታድለናል። እነዚህ ሰዎች በአኗኗራቸው እንዲሁም ደቀ መዛሙርት በማፍራቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ከጸሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚኖሩ ያሳያሉ።
ወላጆች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከሚቀርበው ልመና ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ልጆቻችሁን እየረዳችኋቸው ነው? (አንቀጽ 16ን ተመልከት)
16 ለምሳሌ ያህል፣ በ1948 የተጠመቁና በአፍሪካ ያገለግሉ የነበሩ አንዲት ሚስዮናዊት እንዲህ ብለዋል፦ “የጸሎት ናሙናው ክፍል ከሆነው ከዚህ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ፣ በግ መሰል ሰዎች ሁሉ ጊዜው ከማለቁ በፊት እንዲገኙና ይሖዋን ለማወቅ የሚያስችላቸው እርዳታ እንዲደረግላቸው ብዙ ጊዜ እጸልያለሁ። በተጨማሪም ለአንድ ሰው ከመመሥከሬ በፊት የግለሰቡን ልብ መንካት እንድችል ጥበብ እንዲሰጠኝ ይሖዋን እጠይቀዋለሁ። የተገኙትን በግ መሰል ሰዎች በተመለከተ ደግሞ ይሖዋ እነሱን ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት እንዲባርከው እጸልያለሁ።” እኚህ የ80 ዓመት አረጋዊት በአገልግሎት ስኬታማ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም፤ ከሌሎች ጋር አብረው በመሥራት ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር እንዲሆኑ ረድተዋል። አንተም የዕድሜ መግፋት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ተቋቁመው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን መሥዋዕት ያደረጉ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ክርስቲያኖችን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም።—ፊልጵስዩስ 2:17ን አንብብ።
17. ይሖዋ፣ ፈቃዱ በምድር እንዲፈጸም ለምናቀርበው ጸሎት ምላሽ ለመስጠት ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር ምን ይሰማሃል?
17 የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ከምድር እስኪወገዱ ድረስ፣ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም መጸለያችንን እንቀጥላለን። ከዚያም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ይበልጥ በተሟላ መንገድ ሲፈጸም እንመለከታለን። ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ [ድምፄን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” ብሏል፤ እነዚህ ሰዎች ከመቃብር “ይወጣሉ።” (ዮሐ. 5:28, 29) በሕይወት ኖረን፣ በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎች መቀበል መቻል እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! አምላክ “እንባን ሁሉ [ከዓይናችን] ያብሳል።” (ራእይ 21:4) ከሞት የሚነሱት አብዛኞቹ ሰዎች “ዓመፀኞች” ይኸውም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ እውነቱን የማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ግለሰቦች ናቸው። ከሞት ለተነሱ ሰዎች ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ በማስተማር “የዘላለም ሕይወት” ለማግኘት እንዲበቁ መርዳት ትልቅ መብት ነው።—ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 17:3
18. የሰው ልጅ ከምንም በላይ የሚያስፈልጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
18 በአጽናፈ ዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ስም በመቀደሱ ላይ የተመካ ነው። በመሆኑም በጸሎት ናሙናው ላይ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ልመናዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ሲያገኙ የሰው ልጆች ከምንም በላይ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይሟላሉ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ለማግኘት የምንፈልጋቸው ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች አሉ፤ እነዚህም ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ በጠቀሳቸው አራት ልመናዎች ላይ ተገልጸዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ እነዚህ ልመናዎች እንመረምራለን።
a ይህ ትንቢት በ1914 የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ሲወለድ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 215-218 ተመልከት።
-
-
ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 2መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሰኔ 15
-
-
ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 2
“አባታችሁ . . . ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።”—ማቴ. 6:8
1-3. አንዲት እህት፣ ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያውቅ እርግጠኛ የሆነችው ለምንድን ነው?
ላና ጀርመን ውስጥ በ2012 አንድ ቀን ያጋጠማትን ነገር መቼም ቢሆን አትረሳውም። ሁለት ነገሮችን ለይታ በመጥቀስ ያቀረበችው ጸሎት ምላሽ እንዳገኘ ተሰምቷታል። የመጀመሪያውን ጸሎት ያቀረበችው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ለመሄድ በባቡር ባደረገችው ረጅም ጉዞ ላይ ነው። ምሥክርነት መስጠት እንድትችል አጋጣሚውን እንዲከፍትላት ይሖዋን ጠየቀችው። ሁለተኛውን ጸሎት ያቀረበችው ደግሞ አውሮፕላን ማረፊያው ደርሳ በረራው በአንድ ቀን እንደተራዘመ ስታውቅ ነው። ላና ከነበራት የአውሮፓ ገንዘብ የቀራት በጣም ትንሽ ሲሆን የምታርፍበት ቦታም አልነበራትም፤ በመሆኑም ይህን አስመልክታ ጸለየች።
2 ላና ሁለተኛውን ጸሎቷን ልክ እንደጨረሰች አንድ ሰው “ታዲያስ ላና፣ እዚህ ምን ትሠሪያለሽ?” አላት። ይህን ያላት አብሯት የተማረ አንድ ወጣት ነው። ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሄድ በመሆኑ እናቱና አያቱ ሊሸኙት አብረውት መጥተዋል። የወጣቱ እናት ኤልኬ፣ ላና ያጋጠማትን ሁኔታ ስታውቅ እነሱ ቤት እንድታርፍ በደግነት ጋበዘቻት። ኤልኬና እናቷ ላናን ጥሩ አድርገው ያስተናገዷት ሲሆን ስለ እምነቷና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ በመሆን ስለምታከናውነው ሥራ ብዙ ጥያቄዎች አቀረቡላት።
3 በሚቀጥለው ቀን ላና ጥሩ ቁርስ ከበላች በኋላ ኤልኬና እናቷ ላነሷቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ሰጠቻቸው፤ ከዚያም ያስተናገዷትን እነዚህን ሰዎች ተከታትሎ የሚረዳቸው ሰው ለማመቻቸት ስትል አድራሻቸውን ወሰደች። ላና በሰላም ወደ ቤቷ ተመልሳ በአቅኚነት ማገልገሏን መቀጠል ችላለች። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ ነገሮችን እንዳሳካላት ይሰማታል።—መዝ. 65:2
4. ስለ የትኞቹ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንመረምራለን?
4 ድንገተኛ ችግር ሲያጋጥመን ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ አይከብደን ይሆናል፤ ይሖዋም ቢሆን ታማኞቹ የሚያቀርቡትን እንዲህ ያለውን ልመና መስማት ያስደስተዋል። (መዝ. 34:15፤ ምሳሌ 15:8) ይሁንና በጸሎት ናሙናው ላይ የምናሰላስል ከሆነ አንዳንድ ጊዜ በጸሎታችን የማንጠቅሳቸው ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ እናስተውል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በጸሎት ናሙናው ላይ በሚገኙት የመጨረሻዎቹ ሦስት ልመናዎች ላይ መንፈሳዊ ፍላጎታችን የተገለጸው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በሌላ በኩል ደግሞ ከዕለት ምግባችን ጋር ከተያያዘው ከአራተኛው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን?—ማቴዎስ 6:11-13ን አንብብ።
“የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን”
5, 6. በቂ ቁሳዊ ነገር ቢኖረንም እንኳ ይሖዋ የዕለት ምግባችንን እንዲሰጠን መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ይህን ልመና ስናቀርብ የዕለት “ምግቤን” ብቻ ሳይሆን የዕለት “ምግባችንን” ማለት እንዳለብን ልብ በል። በአፍሪካ የሚያገለግል ቪክቶር የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ የምንበላውን ምግብ ከየት እንደምናገኝ ወይም የቤት ኪራይ ማን እንደሚከፍልልን መጨነቅ ስለማያስፈልገን ይሖዋን ብዙ ጊዜ ከልቤ አመሰግነዋለሁ። ወንድሞቻችን የሚያስፈልገንን ነገር በየዕለቱ በደግነት ይሰጡናል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛን የሚንከባከቡን ወንድሞች የሚያጋጥሟቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች መቋቋም እንዲችሉ ይሖዋ እንዲረዳቸው እጸልያለሁ።”
6 እኛም ለብዙ ቀን የሚሆን ምግብ ይኖረን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ድሃ የሆኑ ወይም አደጋ በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ማሰብ አለብን። ስለ እነሱ ከመጸለይም አልፈን ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ ያለንን ነገር እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ማካፈል እንችላለን። በተጨማሪም ለዓለም አቀፉ ሥራ የምናደርገው መዋጮ እንደማይባክን እርግጠኛ በመሆን አዘውትረን የገንዘብ መዋጮ የማድረግ አጋጣሚ አለን።—1 ዮሐ. 3:17
7. ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ” የሚለውን ምክር ለማብራራት ምን ምሳሌ ተጠቀመ?
7 ኢየሱስ ስለ ዕለት ምግባችን ሲጠቅስ በየቀኑ ስለሚያስፈልገን ነገር መናገሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። አምላክ፣ አበቦችን እንደሚያለብስ ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? ስለዚህ . . . ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ።” ከዚያም “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ” የሚለውን ጠቃሚ ምክር በድጋሚ በመናገር ሐሳቡን ደመደመ። (ማቴ. 6:30-34) ይህም ለቁሳዊ ነገሮች ፍቅር ከማዳበር ይልቅ መሠረታዊ ስለሆኑት በየዕለቱ የሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ ማሰብ እንዳለብን ያሳያል። ከእነዚህ ፍላጎቶች መካከል ተስማሚ መኖሪያ፣ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር የሚያስችለን ሥራ እንዲሁም የጤና ችግሮችን ለመወጣት የሚረዳን ጥበብ ይገኙበታል። ይሁንና የምንጸልየው ከአካላዊ ፍላጎታችን ጋር ስለተያያዙት ስለ እነዚህ ነገሮች ብቻ ከሆነ ይህ ሚዛናዊ እንዳልሆንን የሚጠቁም ነው። ምክንያቱም ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ መንፈሳዊ ፍላጎት አለን።
8. ኢየሱስ የዕለት ምግብን መጥቀሱ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው ስለ የትኛው ፍላጎታችን እንድናስታውስ ሊያደርገን ይገባል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
8 ኢየሱስ የዕለት ምግባችንን መጥቀሱ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያስፈልገንም ሊያስታውሰን ይገባል። ጌታችን “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴ. 4:4) እንግዲያው ይሖዋ በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል ምንጊዜም ልንጸልይ ይገባል።
“በደላችንን ይቅር በለን”
9. ኃጢአታችን እንደ “ዕዳ” ሊቆጠር የሚችለው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ የተጠቀመበት “በደላችን” ወይም “ኃጢአታችን” የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ዕዳችን” ማለት ነው፤ ኢየሱስ “ዕዳ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ማቴ. 6:12 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሉቃስ 11:4) ከ60 ዓመት በፊት በዚህ መጽሔት ላይ የሚከተለው ግሩም ማብራሪያ ወጥቶ ነበር፦ “የአምላክን ሕግ ስንተላለፍ የምንፈጽመው ኃጢአት የእሱ ባለዕዳዎች ያደርገናል። . . . አምላክ ለሠራነው ኃጢአት ሕይወታችንን ሊያስከፍለን ይችላል። . . . ሰላሙን ሊወስድብን በሌላ አባባል ከእኛ ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ሊያቋርጥ ይችላል። . . . ታዛዥ በመሆን የምንከፍለው የፍቅር ዕዳ አለብን፤ ኃጢአት በፈጸምን ቁጥር ደግሞ ለእሱ ያለብንን የፍቅር ዕዳ ሳንከፍል እንቀራለን፤ ምክንያቱም ኃጢአት መፈጸማችን ለአምላክ ያለን ፍቅር መቀነሱን ያሳያል።”—1 ዮሐ. 5:3
10. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር የሚለን ምንን መሠረት አድርጎ ነው? ይህን በተመለከተስ ምን ሊሰማን ይገባል?
10 በየዕለቱ ይቅርታ የሚያስፈልገን መሆኑ፣ አምላክ ኃጢአታችንን መሰረዝ የሚችልበት ብቸኛ ሕጋዊ መሠረት ይኸውም የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። ይህ ቤዛ የተከፈለው ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ቢሆንም ዛሬ እንደተቀበልነው ስጦታ በአድናቆት ልንመለከተው ይገባል። ለሕይወታችን የተከፈለው “የቤዛ ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ” ፍጹም ያልሆነ ማንኛውም ሰው ቤዛውን ለመክፈል ምንም ማድረግ አይችልም። (መዝሙር 49:7-9ን እና 1 ጴጥሮስ 1:18, 19ን አንብብ።) በእርግጥም ለዚህ ታላቅ ስጦታ ይሖዋን ሁልጊዜ ልናመሰግነው ይገባል። በተጨማሪም በጸሎቱ ላይ “በደሌን” ሳይሆን “በደላችንን” መባሉ የእምነት ቤተሰባችን አባላት በሙሉ ምሕረት የተንጸባረቀበት ይህ ዝግጅት እንደሚያስፈልጋቸው እንድናስታውስ ያደርገናል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ስለ ራሳችን መንፈሳዊ ደህንነት ብቻ ሳይሆን እንደበደሉን የሚሰማንን ሰዎች ጨምሮ ስለ ሌሎች መንፈሳዊ ፍላጎትም እንድናስብ ይፈልጋል። በእርግጥ ብዙውን ጊዜ የሚደርሱብን በደሎች ቀላል ናቸው፤ ሆኖም ወንድሞቻችንን ይቅር ስንላቸው፣ ከልብ እንደምንወዳቸውና መሐሪው አምላክ ይቅር እንዳለን ሁሉ እኛም እነሱን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆንን እናሳያለን።—ቆላ. 3:13
አምላክ ይቅር እንዲልህ ከፈለግህ ሌሎችን ይቅር በል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)
11. የይቅር ባይነት መንፈስ ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 የሚያሳዝነው ነገር፣ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ላይ ቂም እንይዝ ይሆናል። (ዘሌ. 19:18) ስለ ጉዳዩ ለሌሎች የምናወራ ከሆነ አንዳንዶች ከእኛ ጋር እንዲወግኑና በጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር እናደርጋለን። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲቀጥል የምንፈቅድ ከሆነ ደግሞ ለአምላክ ምሕረትና ለቤዛው አድናቆት እንደጎደለን እናሳያለን። የይቅር ባይነት መንፈስ የማናሳይ ከሆነ አባታችን በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት እኛን ይቅር ማለቱን ይተዋል። (ማቴ. 18:35) ኢየሱስ የጸሎት ናሙናውን ካስተማረ በኋላ ወዲያውኑ ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:14, 15ን አንብብ።) በመጨረሻም አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን፣ በኃጢአት ጎዳና ላለመመላለስ ጥረት ማድረግ አለብን። ከኃጢአት ለመራቅ ያለን ፍላጎት ደግሞ የሚቀጥለውን ልመና ለማቅረብ ያነሳሳናል።—1 ዮሐ. 3:4, 6
“ወደ ፈተና አታግባን”
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ምን አጋጠመው? (ለ) በፈተና ብንወድቅ ጥፋቱ የራሳችን መሆኑን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? (ሐ) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆኑ ምን አረጋግጧል?
12 ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ያጋጠመውን ነገር መመልከታችን “ወደ ፈተና አታግባን” ብለን መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። የአምላክ መንፈስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ መራው። ለምን? ጥቅሱ “ዲያብሎስ ይፈትነው ዘንድ” ይላል። (ማቴ. 4:1፤ 6:13) ይህ ሊያስገርመን ይገባል? አምላክ፣ ልጁን ወደ ምድር የላከበትን ዋነኛ ምክንያት ካወቅን ይህ አያስገርመንም። ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው አዳምና ሔዋን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ሲያምፁ ለተነሳው ጥያቄ እልባት ለመስጠት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች አስነስቷል፦ አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ጉድለት ነበረው? ፍጹም የሆነ ሰው፣ “ክፉው” ተጽዕኖ ቢያሳድርበትም እንኳ የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፍ ይችል ነበር? ደግሞስ ሰይጣን እንዳለው የሰው ዘር ከአምላክ አገዛዝ ውጭ የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላል? (ዘፍ. 3:4, 5) እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ጊዜ ያስፈልጋል፤ ሆኖም ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘታቸው የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ አምላክ ሉዓላዊነቱን ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት ማየት እንዲችሉ ያደርጋል።
13 ይሖዋ ቅዱስ ነው፤ በመሆኑም ማንንም ክፉ እንዲያደርግ አይፈትንም። ከዚህ ይልቅ “ፈታኙ” ዲያብሎስ ነው። (ማቴ. 4:3) ዲያብሎስ ወደ ፈተና የሚመሩ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል። ሆኖም እያንዳንዱ ግለሰብ ፈተና ውስጥ መግባት አለመግባቱ በራሱ ላይ የተመካ ነው። (ያዕቆብ 1:13-15ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ሰይጣን ያቀረበለትን እያንዳንዱን ፈተና ከአምላክ ቃል ውስጥ ተስማሚ ጥቅስ በመጥቀስ ወዲያውኑ ተቃውሟል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የአምላክን ሉዓላዊነት ደግፏል። ሰይጣን ግን ተስፋ አልቆረጠም። “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ” ጠበቀ። (ሉቃስ 4:13) ኢየሱስም ቢሆን ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ሰይጣን ባደረገበት ተጽዕኖ አልተሸነፈም። ክርስቶስ፣ የይሖዋ ሉዓላዊነት በጽድቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያረጋገጠ ከመሆኑም ሌላ አንድ ፍጹም ሰው ከምንም በላይ ከባድ የሆነ ፈተና ቢያጋጥመውም እንኳ ታማኝ መሆን እንደሚችል አሳይቷል። ያም ቢሆን ሰይጣን አንተን ጨምሮ የኢየሱስን ተከታዮች ለማጥመድ ጥረት ያደርጋል።
14. ወደ ፈተና እንዳንገባ ምን ማድረግ አለብን?
14 ከአምላክ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ መልስ ስላላገኘ ፈታኙ በዚህ ዓለም ተጠቅሞ እንዲፈትነን ይሖዋ ፈቅዶለታል። ወደ ፈተና የሚያስገባን አምላክ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ በእኛ የሚተማመን ከመሆኑም ሌላ ሊረዳን ይፈልጋል። ይሁንና ይሖዋ የመምረጥ ነፃነታችንን ሊጋፋ ስለማይፈልግ ወደ ፈተና እንዳንገባ አይከለክለንም። እኛ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይኸውም በመንፈሳዊ ንቁ መሆንና በጸሎት መጽናት አለብን። ታዲያ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው?
መንፈሳዊነታችሁንና ለአገልግሎቱ ያላችሁን ቅንዓት ጠብቃችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 15ን ተመልከት)
15, 16. (ሀ) ልንቋቋማቸው የሚገቡ አንዳንድ ፈተናዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) አንድ ሰው በፈተና ቢወድቅ ተጠያቂው ማን ነው?
15 ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ያለውን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጥንካሬ እንድናገኝና ፈተናን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። በተጨማሪም አምላክ ልንርቃቸው ስለሚገቡ ሁኔታዎች በቃሉና በጉባኤው አማካኝነት አስቀድሞ ያስጠነቅቀናል፤ ከማስጠንቀቂያዎቹ መካከል እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ማጥፋትን አስመልክቶ የሚሰጠን ምክር ይገኝበታል። ኢስፔንና ያኒ የሚኖሩት በአውሮፓ በሚገኝ አንድ የበለጸገ አገር ነው። እነዚህ ባልና ሚስት በአገራቸው ውስጥ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለብዙ ዓመታት በዘወትር አቅኚነት አገልግለዋል። የመጀመሪያ ልጃቸው ሲወለድ አቅኚነትን ለማቆም ተገደዱ፤ አሁን ሁለተኛ ልጅ ወልደዋል። ኢስፔን እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል እናደርገው እንደነበረው አሁን በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ አንችልም፤ በመሆኑም ፈተና ውስጥ እንዳንወድቅ አዘውትረን ወደ ይሖዋ እንጸልያለን። መንፈሳዊነታችንንና ለአገልግሎቱ ያለንን ቅንዓት ጠብቀን ለመኖር እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቀዋለን።”
16 በዘመናችን የተስፋፋው ሌላው ፈተና ደግሞ ፖርኖግራፊ ማየት ነው። እንዲህ ባለው ፈተና ከወደቅን በሰይጣን ልናሳብብ አንችልም። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም የማንፈልገውን ነገር እንድናደርግ ሊያስገድዱን አይችሉም። አንዳንዶች፣ መጥፎ በሆኑ ነገሮች ላይ በማሰላሰላቸው በዚህ ፈተና ወድቀዋል። ሆኖም በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እንዳደረጉት እኛም ይህን ፈተና መቋቋም እንችላለን።—1 ቆሮ. 10:12, 13
“ከክፉው አድነን”
17. (ሀ) ከክፉው እንዲያድነን ከምናቀርበው ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በቅርቡ ምን እፎይታ እናገኛለን?
17 “ከክፉው አድነን” ከሚለው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ከፈለግን፣ የሰይጣን ‘ዓለም ክፍል ላለመሆን’ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ እንዲሁም የሰይጣንን ‘ዓለምም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች መውደድ’ የለብንም። (ዮሐ. 15:19፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ይህን ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ትግል ይጠይቃል። ይሖዋ፣ ሰይጣንንም ሆነ የእሱን ክፉ ዓለም በማጥፋት ለዚህ ልመና ምላሽ ሲሰጠን እንዴት ያለ እፎይታ እናገኛለን! ይሁንና ሰይጣን ከሰማይ ሲወረወር፣ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ እንደነበር ማስታወስ አለብን። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን እንድናጎድፍ ለማድረግ የተቻለውን ያህል ይፍጨረጨራል። እንግዲያው ይሖዋ ከእሱ እንዲያድነን ሁልጊዜ መጸለይ ይኖርብናል።—ራእይ 12:12, 17
18. የሰይጣን ዓለም ሲጠፋ ለመትረፍ ምን ማድረጋችንን መቀጠል አለብን?
18 እንዲህ ባለው አስደሳች ጊዜ መኖር ትፈልጋለህ? እንግዲያው የአምላክ መንግሥት፣ የእሱን ስም እንዲያስቀድስና ፈቃዱን በምድር ላይ እንዲፈጽም መጸለይህን ቀጥል። መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎትህን እንዲያሟላልህ ይሖዋን ጠይቀው። አዎን፣ ከጸሎት ናሙናው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
-